(በውብሸት
ገ/እግዚአብሔር)
ሰሜንና ደቡብ
ኮርያ ለሶስት ዓመታት እጅግ
ጠንካራ ጦርነት አደረጉ በዚህ
አስከፊ ጦርነት ከሶስት ሚሊየን
በላይ የሰው ህይወት የጠፋ
ሲሆን ከአስር ሚሊየን በላይ
ቤተሰብ ደግሞ ላይተያይ ማዶ
ለማዶ ተለያይቷል፡፡ የዛሬዋ ደቡብ
ኮርያ ያኔ ምንም ዓይነት
መሠረተ ልማት የሌላት መንገዶችዋ
የቆሻሻ መጣያ ይመስሉ ነበር፡፡
በ1950ዎቹ ፍፁም መረጋጋት
በአገሪቷ ካለመኖሩም በላይ ያለውጭ
መንግስታት እርዳታ መኖር የማይቻልባት
አገር ሆናለች፡፡
በ1961 እ.ኤ.አ
በደቡብ ኮርያ የዜጎች የነፍስ
ወከፍ ገቢ ሰማንያ አንድ
ዶላር የነበረ ሲሆን አገሪቷና
ዜጎቿ በከፍተኛ ድህነት ውስጥ
የወደቁበት የቤተሰብ መለያየት ድህነትና
ኋላቀርነት ቋሚ መገለጫቸው ነበር፡፡
በዚህ ጊዜ የወቅቱ የአገሪቱ
ፕሬዝዳንት ፓርክ ቹንግ ሂ
የአምስት ዓመት የኢኮኖሚ ፕላን
ነደፉ፡፡ ይህ ፕላን ሁለት
ጊዜ የተካሄደ ሲሆን የመጀመሪያው
ከ1962-1966 እ.ኤ.አ
ሲሆን ሁለተኛው ከ1967-1972 ዓ.ም
የተካሄደ መርሃ ግብር ነው፡፡
በዚህ መርሃ ግብር በመጀመሪያው
አፈፃፀም 7.8% የኢኮኖሚ እድገት የተመዘገበ
ሲሆን በሁለተኛው መርሃ ግብር
አፈፃፀም 10% የኢኮኖሚ ዕድገት አስመዝግበዋል
በዚህ መርሃ ግብር በተገኘ
ውጤት የዜጎች የነፍስ ወከፍ
ገቢ 275 ዶላር ደረሰ ይሁንና
በ1960ዎቹ የአገሪቱ ኢኮኖሚ
የተመሰረተው በግብርና ላይ ብቻ
በመሆኑና በከተሞች የማምረቻ ተቋም
እና የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት
ባለመኖራቸው ኢኮኖሚው እያደገ ቢመጣም
ከተማውና ገጠሩ እኩል ባለማደጋቸው
ክፍተቱ በከተማውና በገጠር መሀል
ሰፊ በመሆኑ የተገኘው እድገት
ደቡብ ኮሪያን ወደሚፈለገው ጫፍ
ሊያደርሳት አልቻለም፡፡ ይልቁንም በአገሪቱ
ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮች በስፋት
መከሰት ጀመሩ የገጠሩ ማኀበረሰብ
ጨርቄን ማቄን ሳይል ወደከተማ
በስፋት መፍለስ ጀመረ፡፡ በ1960ዎቹ
ብቻ ከገጠር ወደከተማ ስድስት
መቶ ሺ ህዝብ ሲፈልስ
ከ1960ዎቹ መጨረሻ ደግሞ
ሁለት ሚሊየን የሚሆኑ የገጠር
ነዋሪዎች ወደ ከተማ ፈልሰዋል፡፡
ከድህነት ለመውጣት ሙከራ ያደረገችው
ደቡብ ኮሪያ ከችግሯ ልትቆራረጥ
አልቻለችም፡፡ ለአስር ዓመታት የተካሄዱት
ሁለቱን መርሃ ግብሮች የገመገሙት
ፕሬዝዳንት ፓርክ ለምን ድህነትን
ማሸነፍ አልቻልንም? ሲሉ እራሳቸውን
ጠየቁ በመጨረሻም አንድ ድምዳሜ
ላይ ደረሱ፡፡ ደቡብ ኮሪያ
ከድህነት ያልወጣችው የገጠሩና የከተማው
የኢኮኖሚ እድገት ክፍተቱ ሰፊ
በመሆኑና በእድገት መርሃ ግብሩ
የህዝቡ ተሳትፎ ያልተረጋገጠ በመሆኑ
ሲሆን በዚህም የተነሣ የገጠሩ
ህዝብ ወደከተማ በመፍለሡ በዓመት
አንድ ጊዜ ከግንቦት እስከ
ጥቅምት የሚደረገው የሩዝ እርሻ
የቆመበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ ስለሆነም
ገጠሩ ሳያድግ ደቡብ ኮሪያ
ከድህነት መውጣት አትችልም ሲሉ
ፕሬዝዳንቱ ደመደሙ፡፡ በ1970 ሚያዚያ
20 ሴማል ኢንዶንግ የሚል ፕሮጀክት
ፕሬዝዳንቱ ለአገሪቱ አስተዋወቁ ይህ
ፕሮጀክት ብቸኛ ከድህነት የመውጫ
መንገድ እንደሆነና ወደተግባርም እንዲቀየር
ያላቸውን ቁርጠኝነት አሳዩ፡፡ ሴማል
ኢንዶንግ ፕሮጀክት መንደርን መለወጥ
ላይ ያተኮረ ሲሆን ቀጥተኛ
ትርጉሙ ሴ ማለት አዲስ
ወይም ለውጥ ማለት ሲሆን
ማል የሚለው ደግሞ የአስተዳደር
የመጨረሻው አካል ማለት ነው፡፡
በእኛ አጠራር ቀበሌ ወይም
ቀጠና አሊያም ጎጥ እና
ጣቢያ እንደማለት ነው ከዚህ
ትርጉም ስንነሳ ሴማል ማለት
መንደር መለወጥ ወይም ማሳመር
ወይም አዲስ መንደር መፍጠር
ማለት ሲሆን መንደርን ፍፁም
በመቀየር የደቡብ ኮሪያን ህዳሴ
የሚያረጋግጥ አዲስ ዕቅድ ሆኖ
በስፋት የማስተዋወቅ ስራ ተሰራ፡፡
የፕሮጀክቱ ትግበራ በዋነኝነት የቤተሰብን
እና የነዋሪዎችን የአስተሳሰብ (የአመለካከት)
ለውጥ ማምጣት ላይ ያነጣጠረ
ነው፡፡ ሴማል ፕሮጀክት በከፍተኛ
ወኔና በደቡብ ኮሪያ ህዝብ
ሰፊ ተሳትፎ እንዲተገበር መላውን
ህዝብ የሚያነቃንቁ ሶስት መሪ
ቃሎች ነበሩት እነሱም፡- • ታታሪነት፡-
ታታሪነት የሚለው መሪ ቃል
መትጋትን የሚያመላክት እና ተግተው
ካልሰሩ በጥረት ካልሆነ ከድህነት
መውጣት አይቻልም የሚል መልዕክት
ያለው ነው፡ • ራስን መቻል፡-
ጠንክሮ በመስራት ከጥገኝነት ነፃ
መሆንና ራስን በመቻል ድህነትን
ማሸነፍ የሚል ሃሣብ የያዘ
ሲሆን በዚህም መንገድ የማይሄድን
ሰው ፈጣሪም አይረዳውም የሚል
መልዕክት የያዘ ነው፡፡ • መተባበር፡-
አንድ ሰው ብቻውን ለውጥ
ማምጣት አይችልም መተባበርና መደራጀት
አለበት የሚል ሲሆን በእኛ
ሀገር አባባል ድር ቢያብር
አንበሳ ያስር ዓይነት ትርጉምና
መልዕክት ያዘለ ነው፡፡ እነዚህ
ሴማል ፕሮጀክትን ለማጀብ የተሰየሙ
አንኳር መሪ ቃሎች በደቡብ
ኮሪያ ምድር በየአንዳንዱ ዜጋ
አፍ የተነገሩና የጋራ መግባባት
የተፈጠረባቸው መሪ ቃሎች ናቸው፡፡
በ1970 ፕሬዝዳንቱ እና የሀገሪቱ
ምክር ቤት አባላት የክልል
ፕሬዝዳንቶች እና የሚመለከታቸው አካላቶች
ከፍተኛ ስብሰባ አድርገው ሴማልን
በአንድ ቃል አወጁ ለተፈፃሚነቱ
ብቃት ያለው አመራር እንደሚሰጡ
ቃል ገቡ፡፡ አሁን ደቡብ
ኮሪያ ከድህነት ለመውጣት አዲስ
ንቅናቄ ጀምራለች የሴማል ንቅናቄ
በተጀመረበት ዕለት የአገሪቱ መንደሮች
ሰላሶ ሶስት ሺ ስድስት
መቶ ሆነው እንዲከለሉ ተደረገ
እያንዳንዳቸው መንደሮች ሶስት መቶ
ሰላሳ አምስት ሲሚንቶ ከመንግስት
ታደላቸው መንደሮቹ ከራሳቸው ተጨባጭ
ሁኔታ ተነስተው ወደሥራ እንዲገቡ
የተደረገ ሲሆን እያንዳንዱ መንደር
ችግሬ ነው ብሎ በለየው
ችግር ላይ ወደተግባር እንዲገባ
ተደረገ መንግስትም መንደሮቹ በለዩት
ችግር ላይ ንቅናቄ መፍጠራቸውን
ተቀብሎ አስር የሚደርሱ ትኩረት
የሚደረግባቸውን ችግሮችን ለይቶ በተጨማሪነት
ለመንደሮቹ አቀረበ እነሱም፡- • በ1970
ዛፎች ለማገዶነት በመዋላቸው በየተራራው
በስፋት ችግኝ መትከል • አስቸጋሪና
ጠባብ የነበሩትን መንገዶች ማስፋት
• ወራጅ ውሃ የሚወርድባቸውን ቦዮች
መጠገን • እርሻ በሚያርሱበተ ወቅት
የኮፖስት ማዳበሪያ ለራሳቸው ማዘጋጀት
• የውሃ ማቆሪያ ጉድጓዶችን ማዘጋጀት
እና መንከባከብ • የመንደሮችን ንፅህና
መጠበቅ • ፍሳሾችን በስርዓት ማስወገድ
• የጋራ ልብስ ማጠቢያ ገንዳዎችን
መስራት • በጊዜው ከፍተኛ ጉዳት
ያደርሱ ስለነበር አይጦችን ማደንና
ማጥፋት ሌሎችም ችግሮች ተለይተው
መንደሮቹ በራሳቸው ከለዩት ችግር
ጋር አጣምረው እንዲፈፅሙት ተደረገ
አሁን የደቡብ ኮሪያ ህዝብ
በከፍተኛ እልህና ወኔ ችግሮቹ
ላይ ተረባረበ ከገጠር እስከ
ከተማ ከፍተኛ የልማት ንቅናቄ
ተጀመረ ንቅናቄው በከፍተኛ ግለት
ይቀጥል ዘንድ ከየመንደሩ በታሪነታቸው
የተመረጡ ሞዴል አመራሮች ሴማል
ፕሮጀክት ይሳካ ዘንድ ተልኮዋቸውን
በብቃት ተወጡ፡፡ ሴማል በከፍተኛ
የህዝብ ባለቤትነት ተካሄደ፡፡ በዚህ
ወቅት ፕሬዜዳንት ፓርክ የአንደኛውን
ዓመት አፈፃፀም እንዲገመገም በማድረግ
ለሁለተኛው ዓመት ሥራ ዝግጅት
እንዲደረግ አደረጉ፡፡ በግምገማው የተሻለ
አፈፃፀም ያላቸው እና ወደ
ኋላ የቀሩ መንደሮች ጥሩ
የሠሩና ያልሠሩ በሚል ለሁለት
ተከፈሉ በሁለተኛው ዓመት ትግበራ
ሰላሳ ሶስት ሺ ስስት
መቶ ሃያ ሰባት የነበሩ
መንደሮችን ወደ አስራ ስድስት
ሺ ዝቅ እንዲሉ ተደረገ፡፡
በዚህም መንደሮች በሶስት እንዲከፈሉ
ተደረገ አከፋፈላቸውም ከፍተኛ ደረጃ
ላይ የደረሱ፣ ራሳቸውን የቻሉ
እና በጣም ራሳቸውን የቻሉ
በሚል ተከፈሉ ከዚህ በመነሳትም
ከፍተኛ ደረጃ ላይ ለደረሱ
መንደሮች አካባቢን መንከባከብ ራሳቸውን
ለቻሉት ደግሞ የገቢ ማስገኛ
ፕሮጀክት በጣም ራሳቸውን ለቻሉ
ደግሞ የማምረቻ ተቋም ፕሮጀክት
ተነደፈላቸው፡፡ በሁለተኛው ዓመት ከመጀመሪያው
ዓመት በተለየ ተጨማሪ ሲሚንቶ
እና አንድ ቶን ፌሮ
እንዲከፋፈል ተደርጓል፡፡ ውጤት እያመጣ
ያለው ይህ ንቅናቄ በአጭር
ጊዜ ስድስት ሺ መንደሮች
ራሳቸውን እንዲችሉ አደረገ ደቡብ
ኮሪያም በተቀጣጠለ የልማት ማዕበል
ተናጠች፡፡ የሩዝ ምርት ለማሳደግ
በስፋት ተሰራ ስራ አጦች
ወደስራ እንዲገቡ ተደረገ በ1974
የገጠሩ አርሶ አደር ገቢ
ከከተማው የበለጠበት ሁኔታ ተፈጠረ
እንደሚሰበሰበው የሩዝ ምርት መጠንም
የሚሠጠው ማበረታቻ ገንዘብ በመጨመሩ
መንደሮች በውድድር ለላቀ ስራ
እንዲነሳሱ አደረጋቸው ሴማል ኢንዶንግ
ፕሮጀክት ከገጠር ወደከተማ አቅጣጫ
እየተጠናከረና እየተስፋፋ በሁሉም አካባቢዎች
ተዳረሰ፡፡ በ1976 የከተማው ነዋሪ
አዲስ በተቋቋሙ ፋብሪካዎች ወደ
ሥራ ገባ በዚህ ወቅት
የገጠሩ ብቻ ሳይሆን የከተማ
ፋብሪካዎች ምርታማነት ከማደጉም በላይ
በደቡብ ኮሪያ ዜጎች የመለወጥ
የማደግ ከድህነት የመውጣት ንቃተ
ህሊና አደገ አገሪቷ አስተማማኝ
የዕድገት መንገድ ያዘች፡፡ ፍልሰቱ
አቆመ የዜጎች ገቢ ጨመረ
ሁሉም ዜጋ ዕድገቱን ለማስቀጠል
የጋራ መግባባት ላይ ደረሰ
ዳር እስከዳር በመትመም በሴማል
ፕሮጀክት ድህነትን በማሸነፍ የህዳሴያቸው
ሚስጥር አገኙ፡፡ ይህ ፈጣን
እና ውጤታማ ፕሮጀክትም የብዙዎች
መነጋገሪያ ሆነ ከዚህ በመነሳትም
በርካታ ምሁራን እና ፀሃፊዎች
ሴማል እንዴት ውጤታማ ሊሆን
ቻለ? የሚል ጥያቄ አነሱ
ለጥያቄያቸው መልስ ለማግኘትም ጥናት
ማጥናት ጀመሩ የጥናት ግኝታቸውም
የሚከተለው ሆነ፡፡ ሴማል ውጤታማ
ሊሆን የቻለው፡- • መንግስት ብቃት
ያለው አመራር መስጠቱ • በየመንዱ
የነበሩ መሪዎች ጠንካራ ተነሳሽነት
የነበራቸው መሆኑ • ህብረተሰቡ በብቃትና
በትጋት ቀጥተኛ ተሳትፎ ማድረጉ
• ሴቶች ከቤት ሥራ ወጥተው
ከሁሉም ጉዳዮች ተሳትፎ ማድረጋቸው
• መንግስት ጥሩ ለሰሩ ማበረታቻ
መስጠቱ እና ውድድር መፍጠሩ
• በመንግስት እና በህዝቡ መካከል
ጥልቅ ቁርኝት መኖሩ • በተፈጠረው
የግንዛቤ ማስጨበጥ አደናቃፊ አመለካከቶች
መሸነፋቸው ለዓብነትም ድህነት ከአምላክ
የመጣ ስለሆነ መጥፋት አይችልም
የሚል አመለካከት የነበረ ሲሆን
እንደነዚህ ዓይነት አመለካከት እንዲወገዱ
መደረጉ በአጠቃላይ ከላይ የተጠቀሱት
ዋና ዋናዎቹ የውጤታማነቱ ምክንያቶች
እንደሆኑ በጥናታቸው አረጋገጡ፡፡ ደቡብ
ኮሪያ ወደ እድገት ያመጣት
ይህ ሴማል ፕሮጀክት በሁሉም
መስክ የተሳካለት ቢሆንም በርካታ
ችግሮችም አጋጥመውታል በተለይም የፕሬዜዳንቱ
ተቋዋሚዎች ይህ ፕሮጀክት ለማደናቀፍ
ያልፈነቀሉት ድንጋይ አልነበረም ተቋዋሚዎች
ከተጠቀመበት አፍራሽ መቀስቀሻ አንዱ
እና ዋናው ይህ ነበር፡፡
ሴማል ሁለቱን ኮሪያዎች ለመለያት
የህዝቡን ትኩረት ከአንድነት ጥያቄው
ለማንሳት የተፈበረከ ነው በሚል
ራሳቸውን የአንድነት ተቆርቋሪ አድረገው
ህዝቡን በስፋት ቀሰቀሱ፡፡ ይሁንና
ዋናው ድህነት ነው ያለው
ህዝብ ጆሮ ካለመስጠቱም በላይ
ከመንግስት ጎን በመቆም ሴማልን
ወደተግባር ለመቀየር እልህ አስጨራሽ
ትግል አደረገ ዛሬ ድረስ
የደቡብ ኮሪያ ህዝቦች ሁለቱ
ኮሪያዎች ከተለያዩ በኋላ ምን
ሰራችሁ? ሲባሉ ትላንትም ዛሬም
ነገም ወደፊትም የሠራነው ሴማል
ኢንዶንግን ነው ብለው ደረታቸውን
ነፍተው ይናገራሉ፡፡ ከላይ የተጠቀሰው
እና ሌሎች ችግሮች ቢከሠቱ
መንግስት እና ህዝብ ትኩረቱን
ልማት ላይ በማድረግ ችግሮቹን
በማሸነፍ ደቡብ ኮሪያን አሁን
ለደረሰችበት የዕድገት ማማ አብቅቷታል፡፡
ደቡብ ኮሪያ ያኔ ከድህነት
የወጣችበትን ፕሮጀክት የተባበሩት መንግስታት
ስለውጤታማነቱ ዕውቅና ከመስጠቱም በላይ
አሁንም ከድህነት ያልወጡ አገሮች
ከዚህ ተሞክሮ እንዲወስዱ ሰፊ
ስራ እየሰራ ነው፡፡ በዚህ
መነሻነት በካምቦዲያ በላኦስ በሩዋንዳ
እና በኔፓል ይህ ፕሮጀክት
እንዲተገበር እያደረገ ነው በአሁን
ሰዓት በአራት የአፍሪካ ሃገራት
እና በአምስት የኢሲያ ሀገሮች
ሞዴል መንደሮች ተመርጠው ተግባራዊ
እየተደረገ ነው፡፡ በመጨረሻም በደቡብ
ኮሪያ ቆይታዬ ከሞላ ጎደል
ስለ ሴማል ኢንዶንግ ያገኘሁት
ግንዛቤ ይሄን የመሰለ ሲሆን
በቀጣይ በሌላ ፅሁፍ እስከምንገናኝ
ሰላም
No comments:
Post a Comment