Wednesday, 4 May 2016

መሰረታዊው የዲሞክራሲ ጥያቄ…part 1



የዴሞክራሲ ጥያቄ በርካታ መሠረታዊ የዜጎችና የህዝብን መብት የማክበርን ጉዳይ የሚያጠቃልል ነው፡፡ ዜጎች በተናጠልም ሆነ በቡድን ሊጎናፀፏቸው የሚገባ መብቶችን ያለገደብ የማክበር ጉዳይ ነው፡፡ ከግል መብት አኳያ በነፃነት የማሰብ፣ በነፃነት የመኖር፣ በህይወትም ሆነ በአካል ላይ ከሚደርሱ ሰው ሠራሽ ጉዳቶች የመጠበቅ፣ በአገር ውስጥም ሆነ ከአገር ውጭ በነፃነት የመንቀሳቀስ፣ ፍላጎትን በተቃውሞም ሆነ በድጋፍ መልክ በዴሞክራሲያዊ መንገድ የመግለፅ፣ የመደራጀት፣ በመምረጥም ሆነ የመመረጥ መብት በመጠቀም ለፖለቲካ ስልጣን የመወዳደርና ያሻህን የፖለቲካ ኃይል የመደገፍ እንዲሁም ሥራ የማቆም ወዘተ…. መብቶችን ሁሉ ያጠቃልላል፡፡ እነዚህ መብቶች ከሰብዓዊ መብቶች ጋር በጥብቅ የተቆራኙና የማይሰጡም የማይከለከሉም መብቶች ናቸው፡፡ ዜጎች ሰብዓዊ ፍጡራን በመሆናቸው ብቻ እውቅና ሊሰጣቸውና ሊከበሩ የሚገባቸው መብቶች ናቸው፡፡
ከዚህ አኳያ ሲታይ ቀደምት የአገራችን ስርዓቶች እነዚህን መሰረታዊ የዜግነት መብቶች ከልክለው አገራችንን የሁሉም ህዝቦችና የዜጎች እስር ቤት አድርገዋት እንደቆዩ ለመገንዘብ ይቻላል፡፡ በዚያው ልክ ደግሞ ዜጎች ለእነዚህ ክቡር መብቶች የሚያበቃ ህጋዊ ዋስትና ተነፍገው መብቶቻቸውን በአመፅና በትግል ለማስከበር ሲገደዱ ቆይተዋል፡፡ በመሆኑም የግለሰብ ዴሞክራሲያዊ መብቶችን ባለማክበር ላይ የተመሠረቱት ሥርዓቶች እዚያው በዚያው አገራዊ ሰላማችንን ያናጉ፣ የዜጎችን ተሳትፎና ንቁ አስተዋፅዖ በመገደብ ዕድገታችንን የገቱና በአገራችን ላይ የህልውና ፈተናን እስከመደቀን የደረሱ ነበሩ፡፡ በመሆኑም በአገራችን ዴሞክራሲን የማስፈን ጉዳይ ከዜጎች መብት በመነሳት ጭምር ሲታይ የህልውና ጥያቄን የመመለስ ጉዳይ ነበር፡፡
በአገራችን የዴሞክራሲ ጥያቄን ከቡድን መብቶች በመነሳት መመለስም ወሳኙ የህልውናችን ፈተና ሆኖ የቆየ ነበር፡፡ የቡድን መብቶች በመባል የሚታወቁት የብሄሮች፣ የሃይማኖቶች፣ የሴቶች፣ የሠራተኞች፣ የህፃናትና የአካል ጉዳተኞችን ወዘተ ... የሚመለከቱ መብቶች ናቸው። እነዚህ የመብት ጉዳዮች ዜጎች ሰፋ ባለ ደረጃ ከሚቀራረቡዋቸው መሰሎቻቸው ጋር በመሆን የሚያነሱዋቸው የቡድን ጥያቄዎች ናቸው፡፡ ሁሉም የቡድን ጥያቄዎች በትክክል እውቅና ተሰጥቶዋቸው ዴሞክራሲያዊ ምላሽ ማግኘት ያለባቸው መሆኑ እንደተጠበቀ በአገራችን ከባድ ግጭትና ደም መፋሰስ በመቀስቀስ አገራዊ አንድነታችንን ለከፋ አደጋ እስከማጋለጥ የመድረስ ተጨባጭ ክብደት የነበራቸው የብሄርና የሃይማኖት እኩልነትን ከማስከበር አኳያ የተቀሰቀሱ ዴሞክራሲያዊ ጥያቄዎች ነበሩ፡፡
ቀደምት መንግስታት ለእነዚህ የቡድን ጥያቄዎች ዴሞክራሲያዊና ፍትህዊ እውቅና መስጠት ተስኖዋቸው፣ ከዚህም አልፈው የብሄርና የሃይማኖት ብዝሃነትን በኃይልና ጭፍጨፋ ለመገደብና ለማጥፋት በመንቀሳቀሳቸው የብሄርና የሃይማኖት ጥያቄዎች በሰፊው ከመቀስቀስ አልፈው አንዳንዴ በተሳሳተ አቅጣጫ እስከመገለፅ የደረሱበት ወቅት ነበር። የብሄርን ጥያቄ ከትምክህት አስተሳሰብ በመነሳት የመድፈቅም ሆነ ይህን በመፃረር የተቀሰቀሰው የጠባብነት አማራጭ እርስ በርስ እየተመጋገቡ አገሪቱን ወደ ጥፋት አስጠግተዋት ነበር፡፡ በደርግ ሥርዓት የመጨረሻ ዓመታት ላይ በአገራችን እስከ 17 የታጠቁ ድርጅቶች ሲንቀሳቀሱ የነበሩ መሆኑና ከእነዚህም መካከል የሚበዙት የመገንጠል አማራጭን የሚያቀነቅኑ የነበሩ መሆናቸው የብሄር እኩልነትን ያለማክበር አቅጣጫ ምን ያህል አፍራሽና አገሪቱን ለጥፋት የዳረገ እንደነበር የሚያመላክት ነው፡፡
በሃይማኖት ብዝሃነት ረገድ የተፈፀመውም ስህተት ተመሳሳይ ዋጋ ያስከፈለና በአገሪቱ ላይ የህልውና አደጋ እስከ መቀስቀስ የደረሰ ነበር። አገራችን የብዙ ሃይማኖቶች አገር ሆና እያለ እነዚህን በእኩልነትናበዴሞክራሲያዊ መንገድ ለመያዝ ባለመቻሉ ምክንያት በአንድ በኩል የሃይማኖት የበላይነት በሌላ በኩል ደግሞ ሃይማኖት ሽፋን ያደረገ አክራሪነት እንዲንሰራፋ ምክንያት እስከመሆን ደርሷል፡፡ ከዚህ አኳያ ሲታይ የቡድን መብቶችን ሁሉ በተለይ ደግሞ የብሄርና የሃይማኖት እኩልነት ጥያቄዎችን በዴሞክራሲያዊ መንገድ የማስተናገድ ወይም ያለማስተናገድ ችሎታ የአገራችንን ሰላምና መረጋጋት እንዲሁም በመፈቃቀድ ላይ የተመሠረተ ህዝባዊ አንድነት የሚወስን ጉዳይ ነበር፡፡ የደርግ ሥርዓት ከመውደቁ በፊትና በኋላ ባሉት ወቅቶች በአገራችን የዴሞክራሲ ጥያቄ በዜጎች መብትም ሆነ በቡድን መብቶች መልክ የተቀሰቀሱ ፍትሃዊ ጥያቄዎችን የማስተናገድና ይህን በማድረግ ደግሞ አገራችንን በአዲስ ዴሞክራሲያዊ መሠረት ላይ አዋቅሮ የማስቀጠል እጅግ ወሳኝ የአገራዊ ህልውና ጥያቄ ሊሆን የቻለውም በዚህ ምክንያት ነው፡፡
ድርጅታችን ኢህአዴግ ከደርግ ውድቀት በፊት ጀምሮ የዴሞክራሲ ጥያቄ በአገራችን መሠረታዊ የህልውና ጥያቄ መሆኑን በመገንዘብ ለዚህ የዜጎችና የህዝቦች ጥያቄ የተሟላና መሰረታዊ ምላሽ መስጠት እንደሚያስፈልግ በአፅንዖት የተገነዘበ ነበር፡፡ ከዚህም አልፎ ከደርግ ውድቀት በኋላ የሚመሠረተው አዲስ ሥርዓት ከምንም ነገር በፊትና በላይ የዜጎችና የህዝብን ዴሞክራሲያዊ መብቶች በማስከበር መጀመር እንዳለበት የጠራ አቋም ወስዷል፡፡ ይህን መሠረት በማድረግ መጀመሪያ በሽግግሩ ወቅት ቻርተር መሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ መብቶች እንዲከበሩ ከፍተኛ ትግል አካሂዷል፡፡ በመቀጠል ደግሞ በአገራችን የህጎች ሁሉ የበላይ የሆነው ህገ መንግስት ሁሉንም ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች የግልና የቡድን መብቶችን በማይነጣጥልና ይልቁንም በተሟላ ውህደት የሚያስከብር ሆኖ እንዲቀረፅ ያላሰለሰ ትግል አካሂዷል፡፡ ዛሬ አገራችን የምትመራበት ዴሞክራሲያዊ ህገ መንግስት ይህን ምሉዕነት ያለው ይዘትና መልክ ተላብሶ እንዲወጣ በተካሄደው ትግል ድርጅታችን የበኩሉን ቁልፍ ሚና ተጫውቷል፡፡ ህገ መንግስቱን አሳታፊ በሆነ መንገድ ከማዘጋጀት ጀምሮ እስከ 16 ሚሊዮን የሚደርሱ ዜጎች ተከራክረውበት በወኪሎቻቸው አማካይነት እንዲያፀድቁት የተደረገውም በዚሁ መንገድ ነው፡፡
በአገራችን ለዴሞክራሲያዊ ለውጥ የተካሄደው ትግል በዚህ አኳኋን የተጀመረ ከመሆኑም በላይ ተጨባጭ ግንባታውም ይህንኑ ህገ መንግስታዊ አቅጣጫ ተከትሎ በመፈፀም ላይ የሚገኝ ነው፡፡ ህገ መንግስታችን በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ቻርተር ላይ የሰፈሩ መብቶችን በሙሉ የሚያስከብር ነው፡፡ ከዚህም አልፎ በሌሎች አገሮች በብዛት ባልተለመደ አኳኋን ለብዝሃነትን እውቅና በመስጠትና በማክበር ላይ በተመሰረቱ ዴሞክራሲያዊ መርሆች የተዋቀረ እንደመሆኑ መጠን ትግበራውም እነዚህን መብቶች መሠረት ያደረገ ነው፡፡ በዚህ መሰረት ህገ መንግስታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓታችን በእኛ ተጨባጭ ሁኔታ ልዩ ተፈላጊነትና ጠቀሜታ ያላቸውን ሁለት መብቶች በጉልህ አኳኋን ምላሽ እንዲያገኙ አድርጓል፡፡ እነዚህም በአንድ በኩል የብሄሮች የእኩልነት መብቶችን በማክበርና በሌላ በኩል ደግሞ በሰፊው የህዝብ ቀጥተኛ ተሳትፎ ላይ የተመሰረተ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ የሚያረጋግጥ ከመሆኑ ጋር የተያያዙ ናቸው፡፡ ከዚህ በመነሳት ሲታይ በድርጅታችን መሪነት የተጀመረው የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ሂደት ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ያገኙ የዴሞክራሲ መርሆዎችን ከእኛ ተጨባጭ ሁኔታ ጋር በማጣጣምና በማዳበር ተግባራዊ የተደረገበት ሂደት እንደሆነ በማያሻማ አኳኋን ሊቀመጥ ይገባዋል፡፡ የእኛ ዴሞክራሲ ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ያገኙ መርሆዎችን በራሳችን ተጨባጭ ሁኔታ ሊታከሉ ወይም ሊጎሉ ከሚገባቸው የዴሞክራሲ መብቶች ጋር በማዋሃድ የበለፀገ አገር በቀል ዴሞክራሲ ነው፡፡ በዚህ ባህሪው በሌሎች ግፊት የተጫነብንና ሌሎችን ለማስደሰት ሲባል ለይስሙላ ያልተኮረጀ ዴሞክራሲ ነው፡፡ ይልቁንም ከህዝባችን የዘመናት ጥያቄና ተጋድሎ የመነጨ በእርግጥም ለአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ተስማሚነት ያለው ዴሞክራሲ ነው፡፡ ይህን መሰረት በማድረግ አገራዊ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ሂደታችን የዴሞክራሲ ጀማሪዎች ከሆኑት አገሮች ጋር ያለውን ተመሳሳይነትና ልዩነት በጥቂቱዘርዘር አድርገን በመመልከት ለማነፃፀር ስንሞክር የእኛ ዴሞክራሲ አገር በቀል ብቻ ሳይሆን በታሪካዊ አነሳስና አጀማመሩ የራሱ ለየት ያሉና የዳበሩ ባህሪያቶች እንዳሉት እንገነዘባለን፡፡
3. ህዝባዊ ትግላችን ለዴሞክራሲያዊ ለውጥ ቅድሚያ
በመስጠት የጀመረ ነው፣
እንደሚታወቀው አገራችን ለዘመናት በጨቋኝ አስተዳደሮች ስትመራ ከቆየች በኋላ የህዝቡ ዴሞክራሲያዊ ጥያቄዎች ከምንም ነገር በላይ ጎልተው ምላሽ የሚሹ ጉዳዮች እስከመሆን ደርሰው ነበር፡፡ የግልና የቡድን መብቶች ጥሰት ሥር የሰደደ ብቻ ሣይሆን ከፍተኛ ደረጃ ላይ በመድረሱ የመብት ጥያቄዎቹ መሠረታዊ ምላሽ ካላገኙ በስተቀር የማያላውሱ መሆን ጀምረው ነበር፡፡ የዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች፣ የብሄሮች፣ የሃይማኖቶችና የፆታ እኩልነት ጥያቄዎች መሠረታዊ ምላሽ የሚጠይቁ የህልውና ፈተናዎች መሆን ጀመሩ፡፡ በዴሞክራሲያዊ መብት እጦት ምክንያት የህዝቡ ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ሊቃለሉ የማይችሉበት ሁኔታ ተፈጠረ፡፡ መንግስታቱ በተለይ ደግሞ የደርግ አገዛዝ ይከተሉት የነበረው የተበላሸ የኢኮኖሚ ፖሊሲና በዚህ ምክንያት የተፈጠረው ድህነት ዴሞክራሲን በማስፈን ካልሆነ በስተቀር በሌላ መንገድ ሊስተካከል የማይቻልበት ሁኔታ ተፈጠረ፡፡ በዚህም ምክንያት ድርጅታችን የደርግን ሥርዓት በህዝባዊ የትጥቅ ትግል ገርስሶ ወደ ዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ በተሸጋገረበት ወቅት በእርግጥም በአገራችን የዴሞክራሲ ጥያቄን በትክክል የመመለስና ያለመመለስ ጉዳይ የህልውና ፈተና የሆነበት ደረጃ ላይ ተደርሶ ነበር፡፡
ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ መነሻ መሰረታችን ይህ መሠረታዊ እውነታ የነበረ የመሆኑን ያህል የአገራችን ዴሞክራሲ እንደ ምዕራቡ ዴሞክራሲ በጠባቡ ተከፍቶ ቀስ በቀስ እየሰፋ እንዲሄድ ለማድረግ የሚያስችል ዕድል የሚሰጥም አልነበረም፡፡ በአንድ በኩል የዘመናት የዴሞክራሲ ጥማት የነበረው ህዝባችን መብቱን ያለገደብ ለማስከበር የሚሻ ስለነበር ዴሞክራሲያችንን በጠባቡ ከፍቶ በሂደት የማስፋት አማራጭን ለመቀበል የሚችልበት ሁኔታ አልነበረም፡፡ የአገራችን ህዝቦች ከአውሮፓ አቻዎቻቸው ዘግይተው ለዴሞክራሲ የበቁ ቢሆንም በእኛ ተጨባጭ ሁኔታ ከጅምሩ ሰፊ ዴሞክራሲ እንዲያጣጥሙ የሚያስችል ከአውሮፓውያን መሰሎቻቸው የተሻለ የኃይል ሚዛን ብልጫ ነበራቸው፡፡ የደርግን አገዛዝ ለማስወገድ በብሄርና የሃይማኖት እንዲሁም በልዩ ልዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ዴሞክራሲያዊ ጥያቄዎች ዙሪያ የተቀሰቀሰው ትግል ህዝቡ በታዛቢነት ዳር ሆኖ የሚመለከተው ሳይሆን በተደራጀ አኳኋን በንቃትና በሰፊው የሚሳተፍበት ነበር፡፡ ይህም የአገራችን ዴሞክራሲ በጠባቡ ሣይሆን ወለል ብሎ በተከፈተ ሰፊ በር እንዲጀምር ያስቻለው ወሳኝ ምክንያት ነበር። በሌላ በኩል ደግሞ ህዝባዊ ትግሉን የሚመራው ድርጅታችን በአስተሳሰብ ደረጃ ለህዝቡ ያልተገደበ የዴሞክራሲ መብትን የማጎናፀፍ ዓላማ አንግቦ የሚታገል ድርጅት በመሆኑ ዴሞክራሲያችን በተመጠነ በር እንዲያልፍ ሣይሆን ወለል ብሎ በተከፈተ ሰፊ በር የሚተላለፍ ዴሞክራሲ እንዲሆን ብቃት ያለው የአመራር ሚና መጫወቱ ገና ከማለዳው የኃይል ሚዛኑ ለሰፊ ዴሞክራሲ የተመቸ እንዲሆን አድርጎታል፡፡
በአገራችን የዴሞክራሲ መብቶችን ታሪካዊ አነሳስ በተመለከተ ይህን ያህል ካልን በቂ ቢሆንም በህገ-መንግስታችን ዋስትና የተሰጣቸውን የዴሞክራሲ መብቶች መነሻ በማድረግ ንፅፅር ብንሰራም ተመሳሳይ ድምዳሜ ላይ መድረስ እንደምንችል ይታመናል፡፡ ህገ-መንግስታችን የዜጎችን መብቶች በተመለከተ በተባበሩት መንግስታት ቻርተር ላይ የተቀመጡ መሠረታዊና ዝርዝር መብቶችን ተቀብሎ ህጋዊ ጥበቃ አድርጎላቸዋል፡፡ በመሆኑም በዚህ ረገድ አገራችን በየትኛውም ቀደምት የዴሞክራሲ አገር ከተደረገው አዝጋሚና የተበጣጠሰ የመብት ዕውቅና ሂደት በተለየ ሁኔታ የዜጎችን መብቶች አክብራለች፡፡ ለምሳሌ የመምረጥ መመረጥ መብት በሌሎች አገሮች በተሸራረፈ አኳኋን እውቅና የተሰጠውናበአዝጋሚ ሂደት ተግባር ላይ የዋለ መብት የነበረ ሲሆን፣ በእኛ አገር ደግሞ ከመጀመሪያው አንስቶ በተሟላና ባልተበጣጠሰ አኳኋን የተከበረና በተግባር ላይ የዋለ መብት ሆኖ ይገኛል፡፡ በዚህ ባህሪው ዴሞክራሲያችን የዜጎችን መብት አንዴ ከንብረት ባለቤትነት ይዞታ ጋር፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ ከዘርና ፆታ ልዩነት ጋር አያይዞ ሲያጠብ ከነበረው የምዕራቡ ዴሞክራሲ በእርግጥም የላቀ ሆኖ የጀመረ ዴሞክራሲ ነው፡፡
ለቡድን መብቶች በተለይ ደግሞ ለብሄር ብሄረሰቦች መብቶች የሰጠው ትኩረትና መፍትሄም በመሠረቱ ብዙዎች ከሩቅ የሚሸሹዋቸውን የዴሞክራሲ አማራጮች በድፍረትና በሙሉ ህዝባዊ መንፈስ በመቀበል የጀመረ እንደሆነ የሚያሳይ ነው፡፡ የብሄር ብሄረሰቦችን የራስ ዕድል በራስ የመወሰን መብት ነፃ መንግስት እስከ መመስረት በሚደርስ አቅጣጫ ዕውቅና የሰጠ ዴሞክራሲ በማንኛውም መስፈርት ቢለካ የቡድን መብቶችን በመገደብ ቅኝት ከተገነቡ ዴሞክራሲዎች የማይተናነስ ይልቁንም የተሻለ እንደሆነ ለመገንዘብ አያዳግትም፡፡
እነዚህ ሁለት ተመጋጋቢና ጠንካራ አቅሞች የአገራችን ዴሞክራሲ ከምዕራቡ ዴሞክራሲ ዘግይቶ የጀመረ ቢሆንም ገና ከጥዋቱ የብዙሃኑን መብት ያስከበረና በሰፊው የተለቀቀ ዴሞክራሲ እንዲሆን አድርገውታል። ከዚህም በመነሳት የእኛ ዴሞክራሲ በይዘቱም ሆነ በባህሪው የተሻለ ዴሞክራሲ ነው እንላለን፡፡ እንደገናም በየአምስት ዓመቱ እየመጡ የዴሞክራሲ ኦዲተሮች ለመሆን የሚቃጣቸው አንዳንድ ምዕራባውያን ተቋማትና ግለሰቦች የራሳቸውን አዝጋሚ የዴሞክራሲ ጉዞ የማናውቅ ይመስል ስለእኛ ዴሞክራሲ በተናገሩ ቁጥር ደረጃውን ዝቅ አድርገነዋል ቢሉን ሆድ ሲያውቅ ዶሮ ማታ እንላለን፡፡ ስለዴሞክራሲ ሐዋርያ ሆነው የሚሰብኩና የእኛ ዴሞክራሲ በሁሉም መስፈርቶች ያነሰ እንደሆነ ለማረጋገጥ ለሚሹም ሆነ ለሚሞክሩ ሁሉ ከዚህ መሠረታዊ ግንዛቤ በመነሳት በሙሉ መተማመን መልስ መስጠት እንችላለን፡፡ ይገባናልም፡፡ አምስተኛውን አገራዊና ክልላዊ ምርጫ ለማካሄድ በተዘጋጅንበት በዚህ መድረክ ስለአገራችን ዴሞክራሲ ስናስብ በዚህ እውነታ ላይ ልንመሰረት ይገባናል፡፡ ስለ ዴሞክራሲያችን ታሪካዊ አነሳስ ይህን ያህል ካልን በምርጫ ዴሞክራሲያችን ዙሪያ ደግሞ የተወሰነ ምልከታ በማድረግ ቀጣዩ ምርጫ በእርግጥም የህዝብ አመኔታ ያተረፈ፣ ህጋዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ለማድረግ ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገባ ጉዳዮችን ወደ መዳሰስ እንሸጋገራለን፡፡

 Took from  Addis RAEY 2007

No comments:

Post a Comment