በአረብ ሀገራት ኢትዮጵያውያን በብዛት ከሚኖሩባቸው ሀገራት አንዷ ሳዑዲ አረቢያ ናት።
በሀገሪቱ በየአመቱ የሚካሄዱ ሃይማኖታዊ ስነስርአቶችን ጨምሮ በልዩ ልዩ መንገዶች ወደ ሀገሪቱ የሚገቡ ዜጎች በህጋዊም ሆነ የሀገሪቱን ህግ ተላልፈው ለአመታት ሲኖሩባት የቆችው ይህቺ ሀገር፥ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በውጭ ሀገራት ዜጎች ዙሪያ ጠንካራ ህጎችን በማውጣት እርምጃ እየወሰደች የምትገኝ ሀገር ሆናለች። እንደ ሌሎች ሀገራት የውጭ ዜጎች በልዩ ልዩ የስደት ሰበቦች በሀገሪቱ ለመኖር ቢፈልጉ ይህንን የሚያስተናግድ ህግ የላትም። በአብዛኛው ከተለያዩ ሀገራት ወደ ሀገሪቱ የገቡ የውጭ ዜጎች ይኖሩባታል።
ኢኮኖሚዋ ከነዳጅ በሚገኝ ገቢ ላይ የተመሰረተው ይህች አገር የምርቱ በዓለም ገበያ ላይ ዋጋው እየወረደ መምጣት ፈተና ሆኖባታል። ይህንን ተፅእኖ ለመቋቋም የመንግስት የወጪ ቅነሳን የሚያበረታቱ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎችን አዘጋጅታ በመተግበር ላይ የምትገኝ ሲሆን፥ ስራ አጥ ለሆኑ የአገሬው ሰዎች የስራ እድልን ያመጣሉ ያለቻቸውን እርምጃዎችንም ስትወስድ ቆይታለች። ከእነዚህ እርምጃዎች መካከል በተለይም በአገልግሎት ዘርፎች ላይ የሚገኙ ስራዎች ያለ አግባብ በውጭ አገራት ዜጎች ተይዘዋልና እነዚህን የስራ እድሎች ለሳዑዲ ዜጎች ክፍት ሊደረጉ ይገባል ይላሉ ፖለቲከኞቿ። ይህ እንዲሆን ህጋዊ ሰነድ የሌላቸውን የተለያዩ አገራት ዜጎች ከግዛቷ ማስወጣትን እንደ አንድ አማራጭ በመያዝ በተለያዩ ጊዜ በዘመቻ ስታስወጣ ቆይታለች።