በተለይም ከ2000 ዓ.ም ጀምሮ በርካታ አፍራሽ ግብረ ሀይሎችን በማቋቋም ህገ ወጥነትን የመከላከል ስራ በስፋት ሲሳራ
ቢቆይም የተለያዩ ወቅቶችን በመጠበቅ በተለይም በምርጫ ወቅት፣ ቅዳሜና እሁድ፣ የበአላት ቀናት፣ሌሊትን በተለይም ጨረቃ በማትኖርበት
ጨለማን ተገን በማድረግ፣የክፍለከተማና የወረዳ አመራራችን በግምገማና በውይይት ላይ በሚሆንበት ጊዜ ወራሪዎች አካባቢውን በህገ ወጥ
የቤት ግንባታ የሚያጥለቀልቁበት በእነሱ ልምድ ‹‹ ምቹ ወቅት›› የሚሉት ነው፡፡
በዚህ አመትም ሰፊ የሆነ አዳዲስ የአመራር መተካካት ስራ በወረዳዎች በመሰራቱና ግማሽ ያህሉ አመራር አዲስ በመሆኑ የተፈጠረውን
ክፍተት በመጠቀም በክፍለ ከተማው ህገ ወጥ የመሬት ወረራው በስፋት መካሄዱን ዋና ስራአስፈፃሚው ያስረዳሉ፡፡
ከዚህ በተጨማሪም በአንዳንድ የሀገራችን አከባቢዎች የፀጥታ ችግሮች ሲከሰቱ አመራሩ በፀጥታ ስራዎች ትኩረት በሚያደርግበት
ጊዜ ህገ ወጥ የመሬት ወረራው የመስፋፋት እድል አግኝቷል፡፡ ቀውሶችን የሚቀጠሉ የሚመስለውና የህገ የበላይነትን ወደ ጎን የሚተው
ግለሰብ ሀገር ሲወረር አብረህ ውረር በሚል ኋላቀር አመለካከትና በደላላ እየተገፋፋ የህገ ወጥ ድርጊቱ ተሳታፊ የሆነበት አጋጣሚ
መሰረታዊ የአመለካከት ለውጥ የሚጠይቅ ነው፡፡
የወረዳው ስራ አስፈፃሚዋም በወረገኑ ያለው የህገ ወጥ ቤት ግንባታም ቀን ቀን ሳይሆን ጨለማን ተገን በማድረግ እንደሚከናወን
ያስረዳሉ”” እንደህም ይላሉ፤ ‹‹ለቤቱ ግድግዳ የሚሆን ጭቃ ሳይቀር ሌላ ቦታ
በማስቦካትና በመኪና በማጓጓዝ በአንድ ሌሊት ሰርተው ቀለም በመቀባት አሮጌ እያስመሰሉ ህገ ወጥ ድርጊቱን እያሰፋፉ›› እንደመጡ
ህገወጦች የሚጠቀሙበት ተጨማሪ ስልት ያስረዳሉ፡፡
ስለዚህ የተጠቀሱትን ወቅቶችና ኹነቶች ህገወጥ የመሬት ወረራ ለመፈፀም ምቹ ጊዜ በማለት ኪራይ ሰብሳቢው ለይቶ እየሰራበት
ከሆነ በተጠቀሱ ወቅቶች የመንግስት መዋቅሩ በቂ የሆነ ክትትልና የሰው ሃይል ምደባ ማድረግ ይኖርበታል፡፡
የደላሎችና የሌሎች አካላት ሚና
በወረገኑ ህገ ወጥነትን የሚያበረታቱና መሬት በመውረር ቤቶች እንዲገነቡ የሚያደርጉ በርካታ የንግድ ማዕከላትም በወረዳው
ነበሩ፡፡ ከዚህ ከወረገኑ ተሞክሮ ሌላው አከባቢም ትምህርት መውሰድ ያለበት አንድ ተግባር ነበረ፡፡ በወረዳው ባለተለመደ ሁኔታ
25 የሚደርሱ የአጣና መሸጫዎች ተከፍተዋል፡፡ በተደረገው ግምገምማና ጥናት እነዚሀ አጠና ቤቶች ለህገወጥ ግንባታ ዋና ግብአት አቅራቢ
ሆኖው ተገኝተዋል፡፡ እናም ዛሬ እነዚህ ቤቶች ሙሉ በሙሉ እንዲፀዱ ተደርጓል፡፡ እናም የወረዳ መዋቅሩ በአንድ ወቅት ያልተለመዱ
የንግድ እንቅስቃሴዎችና ሌሎች እንቅስቃሴዎች ሲመለከት ለምን ብሎ መጠየቅና መፈተሽ ይኖርበታል”” በወረዳችን የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ጨምሯል ብሎ በአዎንታዊ ገፅታው ብቻ መታየት የለበትም፡፡
ከወረገኑ ሌላ ትምህርት የሚወሰደው ይኸው ነው፡፡
በአካባቢ የንግድ ፈቃድ ሳይኖራቸው ከፍተኛ የሆነ የንግድ እንቅስቃሴ ሲያካሂዱ የነበሩ ሌሎች የንግድ መደብሮች ላይም
እርምጃ ተወስዷል፡፡ አሁን ላይ 78 የሚሆኑ አርሶ አደሮች መሬት መሸጣቸውን በተደረገው ጥናት 32 የሚደርሱ ደላሎችና አሻሻጮችም
መለየታቸውና ለህግ ለማቅረብና የእርምት እርምጃ ለመውሰድ ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑ ከክፍለከተማውና ከወረዳው ሃላፊዎች መረጃው
አግኝተናል፡፡
መንግስት የአርሶ አደሩን የተለያዩ ችግሮች ለመፍታት ጥረት እያደረገ ባለበት፣ ለልማት ሲነሳም ለራሱና ለልጆቹ መሬት
/ቤት የሚቀልስበት/ እና ለራሱም ቋሚ ገቢ የሚያገኝበት ፓኬጅ ተቀርፆ ለመተግበር አስተዳደሩ ወስኗል፡፡ በዚህ ወቅት ለሌላ ሶስተኛ
ወገን በህገወጥ መሸጥና ህገ ወጥ ግንባታ በቦታው ላይ እንዲሰራ መፍቀዱ የህገመንግስት ጥሰት ከመሆኑ በተጨማሪ የአርሶ አደሩ ዘላቂ
ጥቅምም የሚያስቀር ስለሆነ አስተዳደሩ በዝምታ የሚያልፈው ጉዳይ እንዳልሆነ አቶ ታምራት ይናገራሉ፡፡
ህገ ወጥ ግንባታን ማፍረስ የመጀመሪያ እርምጃ መሆን የለበትም!!
ህገ ወጥ ግንባታን ማፍረስ የመጀመሪያ ምርጫ አይደለም፡፡ መጀመሪያ እንዳይሰራ መከላከል ይገባል፡፡
በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ የመንግስትም ሆነ የህዝብ ሀብት ይባክናል፡፡ ኪራይ ሰብሳቢውና በስሌት በወረራው የሚሰማራ ሃይል እንዳለ
ሆኖ በጥረቱና በላቡ ለፍቶ ደክሞ ያፈራውን ሀብት በዚህ ህገ ወጥ ድርጊት ላይ የሚያውል ህዝብም አለ”” ይህ መጠሊያ ለማግኘት በሚል ተግበሩ ህገወጥ በመሆኑ ድርድር ሊደረግበትባይገባም/ ያለችውን
ጥሪት እዛ መሬት ያፈሰሰ ወገን ተጎጂ መሆኑ አይቀርም፡፡ እንዲህ እንዲሆን የመንግስት ፍላጎት አይደለም፡፡ የዚህ ወገን ሃብት በሌላ
ህጋዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ያለው ተግባር ቢውል ከግለሰባዊም አልፎ ሀገራዊ ፋይዳም ነበረው፡፡ ከዚህም ሌላ ህገወጥ ፈረሳ ወጪ አለው፡፡
መንግስት ለልማት የያዘውን በጀት ለአፍራሽ የሰው ሀይልና ለማሽነሪ ለማዋል ይገደዳል፡፡ በልማት መዋል የነበረበት የሰው ጉልበት
ለማፍረስ ይፈሳል፡፡ አመራሩ ሌሎች የህዝብ ጉዳዮችን መስራት ሲገባ ለቀናት በዚህ ይጠመዳል፡፡ ይህ ቀድሞ የመከላከል ስራ ሳይሰራ
በመቅረቱ በህዝብም በመንግስትም በድምር በሃገር ሃብት የሚደርስ ኪሳራ ነው፡፡ ወረራ ከተፈፀመ ጉዳዩ መቀልበስ ስላለበት የመጨረሻ
የሆነውን የማፍረስ እርምጃ መውሰዱ ግን ትክክልና ተገቢ ነው፡፡
እናም ክፍለ ከተማው በቅድሚያ ከ2003 ዓ.ም ጀምሮ በአየር ካርታ የማይታዩትን በሙሉ ከግንቦት
10/2008 ጀምሮ ማፍረስ ጀምሯል”” በዚህም የህዝብና የመንግስት ሀብት የሆነውን በርካታ መሬት እያስመለሰ
ነው፡፡ ገና ለመኖሪያነት ያልተጠቀሙባቸውን ተዘግተው የሚገኙትንና አንዳንዶቹም ቆርቆሮ ያልተመታላቸውን 940 የሚደርሱ ቤቶችን በማፍረስ
ነው ስራው የተጀመረው፡፡ እርምጃው አንዱን ከአንዱ ስለማይለይ “ህብረተሰቡ እርምጃው በዚህ ደረጃ ከሆነ እኛ ችግር የለብንም” በሚል
አብዛኛው ህብረተሰብ ቀድሞ እራሱ በማፍረስ እንደተባበረም አቶ ታምራት አስርድተዋል፡፡
ወረዳው ካልተቀናጀ እንቅስቃሴ ወደ ተቀናጀ ተግባር ገብቷል
የወረዳ 12 አስተዳደርም ችግሩን ለመቀልበስ ሌት ተቀን ቢሰራም ከርቀትና በተለያዩ ምክንያትቶች
ሙሉ በሙሉ ህገ ወጥነትን ሊከላከል ባለመቻሉ ከክፍለ ከተማው በጋራ በመሆን መፍትሄ አስቀምጠው ተንቀሳቅሰዋል፡፡ በአሁኑ ሰአት ህገ
ወጥ ግንባታን ለማፍረስ ከመጀመራቸውም በፊት ከክፍለ ከተማው አመራር ጋር በመሆን ህገ ወጡን በምን አይነት መንገድ መለየት እንደሚቻል
በጋራ ሆኖ በመምከር ወደ ተግባር ገብተዋል፡፡ በዚህም ወረዳ 12ን ብቻ የሚመለከት በእቅድ የተመራ ልዩ የጋራ ግብረ ሀይል በማቋቋም
በእቅዱ መሰረት ህገ ወጥ ግንባታን ከማፍረስ በፊት የማስቆም ስራውን በማስቀደም መሬት በህገ ወጦች እንዳይሸነሸን ማድረጉን ዋና
ስራአስፈፃሚዋ ያብራራሉ፡፡
ከክፍለ ከተማው 14ቱ ወረዳዎች የተወጣጡ የደንብ ማስከበር አባላትና ሰባት የወረዳው አመራሮች
በቋሚነት ተመድበው በመስራት አዳዲስ ግንባታዎችን በማስቆም ለቀጣይ እርምጃ ለመውሰድ የሚያስችል ጥናት አድርገዋል፡፡ በጥናታቸውም
የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ ህገ ወጡንና ህጋዊውን የመለየት ስራ በመስራት ወደ ተግባር መግባታቸውን ነው ዋና ስራ አስፈፃሚዋ
ያረጋገጡልን፡፡
በቀጣይም ህገ ወጥ ተግባራት ከማስቆምና ከመከላከል ባለፈ ወረዳ አስተዳደሩ ከህብረተሰቡ ጋር
በየ 15 ቀኑ በመወያየት የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራ በመስራት ህገ ወጥነቱን አምኖ በራሱ ለማፍረስም መግባባት ላይ ደርሷል፡፡ በዚህም
ህገ ወጥነትን ለመከላከል ለሚደረገው እንቅስቃሴ ህብረተሰቡን በማሳተፍና ከጎናቸው እንዲቆም በማድረጋቸው ከግማሽ በላይ በህገ ወጥ
መንገድ የተገነቡ ቤቶችን ራሱ ህብረተሰቡ ያፈረሰበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡
በህገ ወጥ መንገድ የተሰሩ ቤቶችም በ2006 እና 2007 በተጠና ጥናት ምን ያህል ቤት እንዳለና
ማን እንደሚኖረበት እንዲሁም ሰው የማይኖርባቸው ባዶ ቦታዎችና ታጥረው የታያዙ ቦታዎችን የመለየት ስራ ተሰርቷል፡፡ በተጨማሪም ቤቶቹን
ብቻ ሳይሆን ቤቶቹን በህገ ወጥ መንገድ የገነቡ ግለሰቦችንም አጠቃላይ ሁኔታና ከየት እንደመጡና የኑሮ ደረጃቸውን የሚያሳይ ዝርዝር
ጥናት ተካሂዷል፡፡ በዚህም በተያዘው አመትና አምና የተሰሩ 2 ሺህ 890 ቤቶችንና 1600 ህገ ወጥ ይዞታዎች የተለዩ ሲሆን
940 ሰው አልባ ባዶ ቤቶችንና ታጥረው የተያዙና 1600 ቦታዎችን ቀድመው እንዲፈርሱ አቅጣጫ በማስቀመጥ ተግባራዊ አድርገዋል፡፡
“ህገ ወጥ ግንባታንና ወረራን እርምጃ መውሰድ ብቻ ሳይሆን በዘላቂነት የተወረረውን መሬት
ድጋሚ እንዳይወረር ወደ መሬት ባንክ እያስገባን ለመሄድ እቅድ አውጥተን እየተንቀሳቀስን ነው” ይላሉ ወ/ሮ ልክነሽ ተገኔ፡፡
ድርጅት በግንባር ቀደምትነት በህገ መንግስት የተቀመጡ ውሳኔዎችን በመጠበቅና በማክበር ድርብ
ሃላፊነቱን እየተወጣ ይገኛል ያሉት የቦሌ ክፍለ ከተማ ድርጅት ጽ/ቤት ሀላፊ አቶ ወርቁ ተሾመ ሲሆኑ በዚህ ረገድ ህገ መንግስቱ
መሬትን የህዝብና የመንግስት መሆኑን በግልፅ መደንገጉን እና በተቃራኒው ይህንን መተላለፍ ህጋዊ እርምጃ የሚያስወስድ እንደሆነ መቀመጡን
ገልፀዋል፡፡ አቶ ወርቁ በክፍለ ከተማው በተለይም በወረዳ 12 ወረገኑ አካባቢ ህገ ወጥ ግንባታን የማፍረሱን ሂደት አስመልክተው
ክስተቱን ሲያብራሩ ውስን የሆነውን መሬት ለግል ጥቅማቸው ለማዋል ግለሰቦቹ እያደረጉት ያለው መፍጨርጨር ህገ መንግስቱንም ሆነ የሊዝ
አዋጁን ካለመቀበል የመነጨ በመሆኑ የህግ የበላይነትን ለማስከበር ሲባል ልማታዊ መንግስት እና የሚመራው ድርጅት በህገ ወጦች ላይ
አስፈላጊውን እርምጃ እየወሰደ ይገኛል፡፡
ህገ ወጥነት ለጥቂቶች እንጂ ለአብዛኛው ህብረተሰብ የማይጠቅም መሆኑን የገለፁት አቶ ወርቁ
መንግስትን የቤቶች ግንባታን እንዲያፋጥንና ሌላ አማራጮችን እንዲያይ መግፋት ሲገባ በህገ ወጥነት መሬትን መውረር ትክክል አይደለም
ብለዋል፡፡
መሬትን በህገ ወጥ መንገድ ለሚያሸጡ ደላሎች ምቹ ሁኔታን ሲፈጥር ቆይቷል ይላሉ የአመራር
በየጊዜው መቀያየርም ለጉዳዩ ክፍተት የፈጠረ መሆኑን የገለፁት አቶ ወርቁ የአመራር ሰጭነት ጉዳይም ሌላው ችግር እንደነበር ያስረዳሉ፡፡
በተለይም በተለያዩ ጊዜያት ተመድበው የነበሩ የወረዳው አመራሮች ቁርጠኛ ውሳኔ በመስጠትና ራሳቸውንም ከተግባሩ የፀዱ በመሆን ረገድ
ክፍተቶች እንደነበሩባቸው ያሰምሩበታል፡፡
የህግ መላላት ሳይሆን ከህገ አስከባሪው ጋር በድብብቆሽ ተሰውረው የገነቡ አለፍ ሲልም ከህግ አስከባሪው ጋር ያልተገባ
ጥቅም ለማግኘት የተሄደበትን ርቀት ቁልጭ ባለ መልኩ ከህብረተሰቡ ጋር ውይይት ተደርጓል፡፡ በዚህም የመሬትና የሊዝ አዋጁን በመተላለፍ
ለስርአቱ ተገዢ ባልሆኑት ላይ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን ይገልፃሉ፡፡
ወደ እርምጃ በተገባበት በአሁኑ ወቅት መጀመሪያ ሰው አልባ የሆኑትን ቤቶች ለይቶ የማፍረስ እርምጃ ከተወሰደ በኋላ የክፍለ
ከተማው እና የወረዳው የመሬት አስተዳደር ባለሙያዎች በተገኙበት የግለሰቦቹ ሰነዶች እና የአስተዳደሩ ማስረጃ እየተመሳከረ ነው ውሳኔ
የሚሰጠው ሆኖም አንዳንድ ሀይሎች ውይይት እንዳልተደረገ እና ልክ ከፍተኛ የሰው ህይወት እንደጠፋ አድርገው ለማቅረብ ሞክረዋል፡፡
ነገር ግን መረጃቸው ፈፅሞ ከእውነት የራቀ መሆኑና በአሁኑ ሰአት ያለምንም ግርግር ህገ ወጥ ፈረሳው እየተከናወነ ይገኛል፡፡
ከላይ ህገ ወጥ ግንባታ የሚስፋፉባቸውን እና በስፋት የተሰማሩ ግለሰቦችንም ጭምር የጠቀሱትን የድርጅት ሀላፊ ሀሳብ በመጋራት
ረገድ የወረዳው የመዋቅር አባላት ያለ ልዩነት ይስማሙባቸዋል፡፡ የወጣት ሊግ አባል የሆነው ወጣት መስፍን አስራት በተለይም መንግስት
መሬት የዜጎች የጋራ ሀብት መሆኑን ባስቀመጠበት አግባብ እንዲከበር የፀና አመለካከት አለው፡፡ የጋራ በሆነው የመሬት ሀብትም ጥቂቶች
ብቻ ፍትሃዊ ባልሆነ አግባብ መጠቀም የለባቸውም ባይ ነው፡፡ በመሆኑም ከተግባሩ በመራቅና በማውገዝ ተግባር ተሰማርቷል፡፡
ሌላኛዋ የሴት ሊግ አባል ወ/ሮ ወሰኔ ድንበሩ ተግባሩ ለህገ መንግስት ያለመታዘዝና በአቋራጭ መሬት ለመያዝ የሚደረግ
ህገ ወጥ ተግባር መሆኑን ይናገራሉ፡፡ የዜጎችን እኩል ተጠቃሚነት የሚፃረር ኢፍትሃዊ በመሆኑ እንደ አንድ ዜጋም በአባልነታቸውም
ይታገሉታል፡፡ የመንግስት ውሳኔ ትክክለኛ ወቅቱን የጠበቀ ነው ይላሉ፡፡ ምክንያቱም እርምጃው ባይወሰድ ሊባባስና ህገ ወጦችም ሊበረታቱ
ይችላሉና እርምጃው በሚያስተምር በማያዳግም መልኩ መሆኑ መንግስትንም ድርጅትንም ያስመሰገነ በመሆኑ የሁሉም ድጋፍ እንደማይለይና
ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ያስረዳሉ፡፡
ዜጎችን እኩል ተጠቃሚ የሚያደርግ ፍትሃዊ አማራጭ
በከተማችን የመኖሪያ ቤት ችግር በስፋት መኖሩ አያጠያይቅም፡፡ ነገር ግን ድርጅታችንና መንግስታችን አቅም በፈቀደና የተለጠጠ
በሚባል ልክ የቤት ልማት ፕሮግራም እያካሄደ ነው፡፡ በተነፃፃሪ የተሻለ ገቢ ላላቸው የ40 በ60፣ ለመካከለኛና ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው
የህብረተሰብ ክፍሎች ደግሞ የ20 በ80 እና የ10 በ90 የቤት አማራጮችን በመንግስት ድጎማ እያቀረበ ነው፡፡ በመሆኑም ሁሉም የከተማው
ነዋሪ ጊዜውን ጠብቆ እየቆጠበ ተጠቃሚ እየሆነ ይገኛል፡፡ የተሻለ አቅም ያለውም በሪልስቴቶችና በግሉም ህጉን ተከትሎ ቤት የሚሰራበት
አግባብ ተቀምጧል፡፡ ሆኖም በእላፊ ጥቅም ፍለጋ አማራጭ ሊሆን የማይችል አማራጭ የሚከተሉ ግለሰቦች ከህገ ወጥ ድርጊታቸው እንዲቆጠቡና
ለብዙሀኑ ተጠቃሚነት ሲባል ሁሉም ሀይ ሊላቸው ይገባል፡፡
ነዋሪዎችስ ምን ይላሉ?
ገብረ እግዚያብሄር ወልደ ስላሴ ይባላሉ፡፡ የቦሌ ወረዳ 9 የነዋሪዎች ፎረም አደረጃጀት አባል ናቸው፡፡ እንደ እርሳቸው
አገላለፅ መሬት ውስን ሀብት እንደመሆኑ መጠን በአሁኑ ሰዓት መንግስት ከዘራፊዎች ለመመለስ የሚያደርገው ጥረት ትክክለኛ በመሆኑ
ሁሉም ዜጋ የመንግስትን አቅጣጫ ተከትሎ ህገ ወጥነትን ሊከላከል ይገባል ይላሉ፡፡
አብዛኛው የመሬት ወረራ የሚያካሂደው አካል መሬትን በመሸጥ ትርፍ ማገላበጥ እንጂ የሚኖሩበት ውስን ናቸው የሚሉት አቶ
ገብረእግዚያብሄር ይሄም እላፊ ተጠቃሚነት ፍለጋ እንጂ ከኑሮ ደረጃ ጋር መያያዝ እንደሌለበት ይስማላሉ፡፡ “ህዝቡ በህገ ወጥ መንገድ
መሬት የወረሩ አካላት አፋጣኝ እርምጃ ሲወሰድባቸው አያይም” በማለትም ይወቅሳሉ፡፡ አክለውም ግለሰቦች በህገ ወጥ መንገድ መሬት
በመያዝ በከፍተኛ ዋጋ እየቸበቸቡ ኪራይ በመሰብሰብ ኪሳቸውን ሲያደልቡ ሁሌም ይቆጫቸው ነበር ለወደፊትም “ህግን አክብረው በተቀመጠው
ህብረተሰብ ዘንድም የመገፋፋት ስሜት እንዳይፈጠር መንግስትና ህዝቡ ተቀራርበው መስራት ይገባቸዋል” ብለዋል፡፡
በተለይ በከተማችን ህገ ወጥነትን ነዋሪዎች አምርረው እንደሚቃወሙት ያምናሉ፡፡ ሆኖም በመንግስት አካላትም ጭምር የተሰገሰጉ
ሙሰኞች በመኖራቸው ጩ¡ታቸው በአግባቡ እየተደመጠ እንዳልሆነ ያምናሉ፡፡ ደንብ አስከባሪዎች
ይህንን ህገ ወጥ ድርጊት የመከላከልና የመቆጣጠር ሀላፊነት እንዳለባቸው እየታወቀ አንዳንድ ሃላፊነት የጎደላቸው ደንብ አስከባሪዎች
ነዋሪዎች የሚሰጧቸውን ጥቆማ ይዘው አስፈላጊውን እርምጃ መውሰድ ሲችሉ “እከሌ ጠቁሞኝ መጣሁ” በማለት በነዋሪዎች ዘንድ የተፈጠረውን
የመተጋገል ግለት ውሀ እየቸለሱበት እንደሚገኙም ጠቁመዋል፡፡
በተመሳሳይ በክፍለከተማው ወረዳ ዘጠኝ የሚካሄደው ህገ ወጥ የመሬት ወረራም ከነዋሪዎች የተደበቀ አይደለም ይላሉ፡፡ በወረዳው
ብቻ ሳይሆን በሁሉም አካባቢዎች መሬት ከመልካም አስተዳደር ችግርና ከኪራይ ሰብሳቢነት ጋር እየተያያዘ የሚነሳው፤ እናም ሁሉም ሊታገለውና
የህግ የበላይነት ሊከበር እንደሚገባ ይናገራሉ፡፡
በተለይም በየቀጠናው የሚገኙ የድርጅትና የመንግስት መዋቅር አባላትና አመራሮች ህብረተሰቡን በማስተባበር ግንባር ቀደም
ሚናቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል፡፡
በወረዳ 12 ወረገኑ ቀጠና ላይ መንግስት እያከናወነው ያለው ህገ ወጥነትን የማፅዳት ተግባር ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ቁርጠኛ
መሆኑን ያመላክታል ያሉት ደግሞ የወረዳ 11 ነዋሪው አቶ ሲሳይ ተክሉ ናቸው”” በወረዳቸው
ነዋሪውና አመራሩ በህገ ወጥ የመሬት ወረራ ላይ ድርድር የለውም ይላሉ፡፡
ነዋሪው ከወረዳው አልፎ በክፍለ ከተማው አንዳንድ ወረዳዎችና በሌሎችም ክፍለ ከተሞች የሚደረገውን አሳሳቢ የመሬት ወረራ
በእጅጉ እንደሚያወግዙት ይገልፃሉ፡፡ ዜጎች በጥረታቸው ያካበቱት ሀብት ህገ ወጥ ግንባታ ላይ እንዲውል የሚያማልሉና ለኪሳራ የሚዳርጉ
ደላሎችና አመራሮች በህግ እንዲጠየቁም ይጠይቃሉ፡፡ በኪራይ ሰብሳቢነትና በህገ ወጥ ግንባታ ላይ የሚሳተፍ አባልም ተገምግሞ ከአባልነት
እስከማሰናበት ድረስ አባላት በመሰረታዊ ድርጅትም ሆነ በህዋስ የሚያደርጉትን ትግልም አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡
በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የመልካም አስተዳደር ጉዳዮች አስተባባሪ አቶ አባተ ስጦታው በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር
2ኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ ህገ ወጥ የመሬት ወረራንና ግንባታን አስመልክተው አስተያየታቸውን ሰጥተው ነበር፡፡ ተግባሩንም አስቀድሞ
መከላከል ያልተቻለው በወረዳ ካለው መዋቅራችን ችግር የሚመነጭ ነው ያሉ ሲሆን ይህ ጉዳይ የደንብ ማስከበር ጽ/ቤትንም በቀጥታ እንደሚመለከት
ነው የተናገሩት”” ለእያንዳንዱ መሬት ፖሊስ መመደብ አንችልም ያሉት አቶ አባተ ይህንን
ህገ ወጥ የመሬት ወረራና ተግባር ለመከላከል የእያንዳንዱ ህብረተሰብ ሃላፊነት ነው ብለዋል፡፡ አብዛኛው የከተማችን ነዋሪ ያለበትን
የቤት ችግር ለመቅረፍ ከመንግስት ጋር በጥምረት እየሰራ ነው ሲሉም ተደምጠዋል”” በዚህ
ህገ ወጥ ተግባር ላይ በተጨባጭ እየተሰማሩ ያሉት ጥቂቶች ናቸው፡፡ ከቦሌ በተጨማሪ በንፋስ ስልክ ወረዳ 1 ያለውም ሁኔታ ተመሳሳይ
ዝንባሌ እንዳለው ምክትል ከንተባው ይናገራሉ፡፡
አሰራሩ “ታጥቦ ጭቃ” እንዳይሆን ትኩረት ይሻል
ክፍለ ከተማው ወደ ህትመት እስከገባንበት ጊዜ ድረስ ከ4 ሺህ 238 በላይ ቤቶችንና ከ1 ሺህ 673 በላይ ታጥረው የተያዙ
ቦታዎችን የማፅዳት ስራ አከናውኗል፡፡ በቀጣይም የህግ የበላይነትን የማስጠበቅ ተግባሩን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቋል፡፡
ነገር ግን በህገ ወጥ የመሬት ወረራ ላይ ሁለት ሶስት ጊዜ ካልፈረሰ አይፀድቅም በሚል የተሳሳተ አመለካከት በተደጋጋሚ
የመስራትና መንግስትን የመፈታተን ሁኔታዎች የተለመደ ስለሆነ ልዩ ትኩረት መስጠት ያስፈልጋል፡፡ ለዚህም የቁጥጥር አቅምን በተሻለ
ደረጃ ለማጠናከርና ህገ ወጥነትን ለመከላከል በወረዳ 12 በአምስቱም ቀጠናዎች የደንብ ማስከበር ቢሮዎች ይቋቋማሉ፡፡ በቀጣይ ግን
ማፍረስ ብቻ የመጨረሻ እርምጃ አለመሆኑንና ድርጊቱን የሚፈፅም አካል በህግ ተጠያቂ የሚደረግበት አሰራር ስላለ ሁሉም ከድርጊቱ ሊርቅ
ይገባል፡፡