Tuesday, 19 July 2016

ታዳጊ ዴሞክራሲያችን የሚጐለብተው መቻቻልን በሚቀበል ህብረተሰብ ነው ክፍል 2 (በሓጎስ ገ/ክርስቶስ )

. ዴሞክራሲያዊ የአስተሳሰብ ትግል በማጎልበት ጠባብነትና ትምክህተኝነትን እንመክት

ታዳጊ ዴሞክራሲያችን የሚጐለብተው መቻቻልን በሚቀበል ህብረተሰብ ነው

በመጀመርያ ክፍል ፅሑፌ ጠባብነትና ትምክህተኝነትን የምንዋጋው በዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብ መሆኑ፣ የዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብ እሴት ከሆኑት መካከል ደግሞ አንዱ ምክንያታውነትን የመቀበል፣ በህግጋተ ምክንያታውነት መመራት እንደሆነ ለመግለፅ ተመኩራል፡፡ በፅሑፉ ዙርያ የተሰጡ አስተያየቶች ገምቢ ሐሳብን በገንቢነቱ፣ አፍራሽ ሐሳብ ደግሞ በአፍራሽነቱ ለመረዳት፣ ከገንቢ አስተያየቶችን ሁሌም እንደማደረገው ትምህርት ለመውሰድ ችያለሁኝ፡፡
የሐሳብ ነፃነት ለዜጐች የተሠጠ መብት መሆኑን በመረዳት፣ ሐሳብ የመግለፅ መብትም እንደገበያ የሚመስል፣ በገበያ የሚጠቅምህንና የሚያስፈልግን በገበያ ህግጋተ የመግዛት፣ የማያስፈልግህንና የማይጠቅምህን ደግሞ በገበያ ህግጋት እንደመተው አድርጌ ለማዛመድ ጥረት በማድረጌ በዚህ አጋጣሚ የሽንፈትና የፀረ-ዴሞክራሲ ምልክቶችና የአሮጌ አስተሳሰብ አራማጅ የሆኑትን አስተያየቶችን አይቼ አላየኋቸውም፣ ሰምቼም አልሰማኋቸውም፡፡ ከተሳዳቢዎች ጋር መሳደብ ማርን በኮሶ እንደመብላት ተደርጐ የሚወሰድና ከአንድ በ21ኛው ክፍለ ዘመን የተፈጠረ የህዳሴው ትውልድን የማይጠበቅ በመሆኑ በግሌ አያሳክከኝም፡፡ ስድብ የዴሞክራሲ የመጨረሻ የዘቀጠ አተላ በመሆኑንም ዛሬም ነገም አተላ የመጨለጥ ባህሪ አይኖርብኝም፡፡ እናም የክፍል ሁለት ዋናው ጭብጥ ከመግባቴ በፊት የ21ኛው ክፍለ ዘመን ትውልድ ነኝ የሚል ሰው ሐሳብን በሐሳብ የመመጐት ባህል ማዳበር ይኖርበታል በሚል ጥቆማየን አቀርባለሁ፡፡
ዴሞክራሲ ስር ሊሰድ የሚችለውንና ተኮትክቶ ሊያድግ የሚችለው በምክንያታዊነት ከሚያምን ህብረተሰብ ባሻገር መቻቻልን ቅቡል ያደረገ ህብረተሰብ ጭምር ሲፈጠር እንደሆነ እሙን ነው፡፡ መቻቻልና የመቻቻል እሴቶችን መተግበር በማይቻልበት ሁኔታ አስተማማኝ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ማስፈን አይቻልም፡፡ መቻቻል በሌለበት ዴሞክራሲ ያድጋል ብሎ ማሰብ ውሃን በድንጋይ እንደማፍሰስ ነው፡፡ መቻቻል ባልተፈጠረበት ሁኔታ ዴሞክራሲ በአስተማማኝ ደረጃ ይገነባል ብሎ ማሰብ በምድረባ ስንዴ እንደማብቀል ነው፡፡ እንደኛ በመሰሉ በዕድገት ላይ የሚገኙ ሃገራትና በርካታ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ባለበት ሁኔታ ደግሞ የመቻቻል ትርጉም የላቀ ነው፡፡ የተለያየ ሃይማኖትና እምነት ተከታይ የሆነ ህዝብ ባለበት ሃገር የሃይማኖት ነፃነትን፣ የሃይማኖት እኩልነትን እንዲሁም የመንግስትና ሃይማኖት መለያየትን መቀበል መሰረታዊ ነው፡፡ የብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች እናት በሆነች ሃገር በተለያዩ ብሄር በሄረሰቦችና ህዝቦች የሚነገሩ ቋንቋዎች ማክበርና ማስከበር መሠረታዊ ነው፡፡ የብሄር ብሄረሰብና ህዝቦች ባህል፣ እሴቶችን እንዲሁም ማንነትን ቅቡል አድርጐ ተቻችሎ የመኖር ጉዳይ ለሃገራችን ህልውና መሰረታዊ ነው፡፡
የመቻቻል ጉዳይ የባህል፣ የሃይማኖት፣ የቋንቋ፣ የትውፊት ልዩነትን የመቀበል መሆኑን፣ መቻቻል ሲባል የሐሰብ ልዩነትን በዴሞክራሲያዊ መንገድ የማስተናገድ፣ የሐሳብ ክርክርን በሰለጠነ መንገድ የማስተናገድ ጉዳይ ነው፡፡ መቻቻል ሲባል ምንም ዓይነት የሐሳብ ትግል የሌለበት ማለት ሳይሆን በተለያዩ ግለ-ሰዎችም፣ ድርጅቶችም የሚነሱ ሐሳቦችን ለማዳመጥ ዝግጁ የመሆን፣ እኔ ከያዝኩት ውጪ በሚል ፈሊጥ በስነ-ልቦናና በተግባር ለመቀበል ዝግጁና ፍቃደኛ አለመሆን ደግሞ ለፀረ-መቻቻልን መቆምን ማለት ነው፡፡ እኔ ያልኩትን ሁሌም ትክክለኛ ነው፤ በእኔ ከሚራመደውን አቋም በተለየ መንገድ የማራመድ ጉዳይ በእኔ መቃብር ነው የሚል ፈሊጥ የዴሞክራሲያዊ እሴት የሆነውን መቻቻል ከመግደል ውጪ የሚፈይደው ነገር የለውም፡፡ ሊኖርውም አይችልም፡፡
ሲጠቃለል ዴሞክራሲያዊና ገምቢ መቻቻል በውስጠ ድርጅት፣ መቻቻል በስራ ቦታ፣ መቻቻል በምንኖርበት አከባቢ፣ መቻቻል በምንማርበት ትምህርት ቤት ከዴሞክራሲ አንፃር ፋይዳው የጐላ ነው፡፡ መቻቻል በህዝብ ታሪክ ዙርያ ትልቅ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ነው፡፡ ከዚህ አኳያ አንድን ብሄር በኢትዮጵያ የተለየ ታሪክ ሰሪ፣ የኢትዮጵያ አንድነት ጠበቃ፣ የስልጣኔ ባለቤት፣ ሌላኛው ደግሞ ለኢትዮጵያ ፀረ-አንድነት የቆመ፣ ታሪክ የሌለው ወይም ከሌሎች ኢትዮጵያውያን በተለየ መንገድ ተጠርጣሪ አድርጎ የማየት አዝማምያ በህዝቦች ታሪክ ላይ ያለው የተዛባ የታሪክ አለመቻቻል ተደርጐ የሚወሰድ ነው፡፡ መቻቻል የሐሳብ ልዩነትን መቀበልና ማክበር ነው፡፡ መቻቻል የባህል ልዩነትን መቀበልና ማክበር ነው፡፡ መቻቻል የብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦችን ቋንቋ፣ ባህል፣ ሃይማኖት፣ እሴቶች፣ ታሪክ፣ ልዩነትን መቀበልና ማክበር ነው፡፡
በአንፃሩ በቀደምት ስርዓቶች ተመኩሮ ሃገራችን ለብተና ዳርጓት የነበረውን የአንድ ባንዴራ፣ አንድ ሃይማኖትና አንድ ቋንቋ የጥቂት ትምክህተኞች ቀረርቶና የመቻቻልን እሴት የሚያጠፋ ነው፡፡ ባለፉት ሁለት 10 ዓመታት እየተገነባ ያለውን የዴሞክራሲያዊ ብሄርተኝነትን አስተሳሰብ ቅቡል አድርጐ አለመውሰድ፣ የብሄር ብሄረሰቦችንና ህዝቦችን ባህል፣ ቋንቋ፣ ትውፊቶች ለመጨፍለቅ (Assimilate) ለማድረግ የሚደረግ በመሆኑ ፀረ-መቻቻልና በባህሪው ፀረ-ዴሞክራሲ ነው፡፡ የህገ-መንግስቱ ትርፋት፣ የሰላማችን ምንጭ የሆነውን የዴሞክራሲያዊ ብሄርተኝነት አስተሳሰብን የሚቀበል ሃይል በፀረ-ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብና ብብዕር ቢጤ ለማሸማቀቅና ለማጥቃት መሞከርም ከጠባብና የትምክህት ሃይሎች የሚጠበቅ ቢሆንም ፀረ-የሐሳብ መቻቻልና ፀረ-ዴሞክራሲያዊ ነው፡፡በድምሩ ጠባብነት ብሎ መቻቻል አይታሰብም፣ ጠባብነት ጅብ ለጅቡ እንኳን የሃገሬ ጅብ ይብላኝ የሚል፣ በጅቦች መካከል የጐጡን ጅብ የሚመርጥ እስከሆነ ድረስ በሰኒ አስተሳሰቡ ተወስኖ የሚኖር እና በሰኒ ውስጥ የሚዋኝ እንጂ መቻቻልን የሚጠብቅ እንዲሁም የመቻቻልን እሴት የሚቀበል አይደለም፡፡
በተመሳሳይ ትምክህት ብሎ ስለ መቻቻል ማሰብ በምንም ተአምር አይታሰብም፡፡ የዴሞክራሲያዊ ብሄርተኝነትን አስተሳሰብ ፈፅሞ ለመቀበል ባልተቻለበት፣ የማንኛውም ብሄር በሄረሰብና ህዝቦች የቋንቋ፣ የባህልና የትውፊት ልዩነት መቀበል “አንድነት ወይም ሞት” በሚል ፈሊጥ የትምክህት ሊቀ-ሊቃውትነት ለመሆን ሽርጉድ በሚባልበት፣ ኢትዮጵያ ሁሉም ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ተቻችለው ሊኖሩባት የምትገባ የብዙሃነት ሃገር ናት በሚባልበት “ጃ” በሚዘመርበት ሁኔታ መቻቻል አይታሰብም፡፡ “ጃ” ና “ጥቁር ሰው” ብሎ መቻቻል የለም፡፡ “ጃና ጥቁር ሰው” ብሎ አንድ ላይ ጨፍልቆ መግዛት (Assimilation policy) ነው ያለው፡፡ በ “ጃ”ም “ጥቁር ሰውም” ውስጥ አሁን ያለውን የዴሞክራሲያዊ እሴት ተደርጐ የሚወሰደውን መቻቻል ብሎ አይታሰብም ፡፡ በመሆኑም ጠባብነትና ትምክህተኝነት አመለካከት ነው፡፡ የተዛባ አመለካከት ደግሞ የሚስተካከለው በመጥረብያ ሳይሆን በዴሞክራሲያዊ የሐሰብ ትግል ነው፡፡ መጥረብያ በመጠቀም የጠባብነትና ትምክህት አመለካከት ችግር እንቅረፍ ብንል በንድፈ ሃሳብም በተግባርም አይቻልም፡፡ ከዴሞክራያዊ ባህርያችን አንፃርም ፈፅሞ ተቀባይነት የለውም፡፡
በተመሳሳይ ጠባብነትና ትምክህት እንደ ፀረ-ኩፍኝ በሽታ በክትባት የምንከላከላቸው አይደሉም፡፡ ዋናው የመከላከያ መድሃኒቱ ዴሞክራሲያዊ የአስተሳሰብ ትግል መሆኑን፣ መልሶ መላልሶ ማስተማር መሆኑን፣ የመቻቻል እሴትን ሊቀበል የሚችል ህ/ሰብ የመፍጠር ጉዳይ መሆኑን፣ ይህ ለማድረግም የስነ-ዜጋና ስነ-ምግባር ትምህርት ወሳኝ መሆኑን፣ ዴሞክራሲያዊ የሆነ ሚድያም ከዚሁ አንፃር የላቀ ሚና ያለው መሆኑን መረዳት ተገቢ ነው፡፡
ጠባብነትና ትምክህት አመለካከት ነው፣ ጠባብነትና ትምክህት ተከትሎ የሚወረወረው ድንጋይ ይሁን ጥይት አመለካከቱ የወለደው ነው፡፡ ድርጊቱ ፍፁም ፀረ-ዴሞክራሲ ነው፡፡ መድሃኒቱም የዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብ ትግል ነው፡፡ የተሻለ መድሃኒቱም የዴሞክራሲያችን እሴት የሆነውን መቻቻል ማጐልበት ነው፡፡ በእኛ ተጨባጭ ሁኔታ መቻቻል ማለት የዴሞክራሲያዊ ብሄርተኝነት አስተሳሰብ እንዲጐለብት መጣርና መረባረብ ማለት ነው፡፡ ይህ የሚገኘውም በእልህ ሳይሆን የዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብ ስበእናና ትጥቅ በመያዝ ነው፡፡ የዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብ እሴት የሆነውን መቻቻልን በማጠናከር ነው፡፡
ክፍል 3 ይቀጥላል