ያለፈው ሩብ ክፍለ ዘመን የአገራችን ጉዞ በፈጣን የእድገት ባቡር
ላይ የተሳፈረበትና ከፈጣኖቹ አዳጊ ሀገራት ተርታ መሰለፍ የቻልንበት ነው፡፡ ከ1983 ዓ.ም በፊት አገራችን የነበረችበት ሁኔታ
እጅጉን የከፋና የተመሰቃቀለ፤ በርካቶችን የቀጠፉ ጦርነቶችና መተላለቆች የነበሩበት ነበር፡፡ ዛሬ ፍፁም ከዛን ወቅት በተለየ ሁኔታ
ተስፋ ሰጪና በማያባራ የለውጥ ግስጋሴ ውስጥ እንድንገኝ ያስቻለ ምቹ ሁኔታ የተፈጠረበት ወቅት ላይ እንገኛለን፡፡ ለአብነት የጤናው
ዘርፍ ልማታችንን እንኳ ብንመለከት ከ80 በመቶ በላይ ለሆኑ ወላድ እናቶች ሞት ምክንያት የሆነው የደም መፍሰስ የተራዘመ ምጥ፣
ኢንፊክሽን፣ ውርጃና ከፍተኛ ደም መፍሰስ በየአካባቢው በተገነቡ የጤና ጣቢያዎች በሚካሄድ የቅድመ ወሊድ ክትትልና ድጋፍ ሙሉ በሙሉ
በሚባል ደረጃ ሊቀረፍ ችሏል”” በአንድ ወቅት በቀላሉ የዜጎቻችንን ህይወት ሲቀጥፉ የነበሩ ደዌዎች
ዛሬ ላይ ታሪክ ሆነዋል፡፡ የጤና ጣቢያዎች ተደራሽነትን ብንመለከት እንኳ ከ1983 ዓ.ም በፊት በቁጥር 12 ብቻ የነበሩ ሲሆን
በአሁኑ ወቅት ከ86 በላይ ደርሰዋል፡፡ በከተማ ደረጃ 18 ብቻ የነበሩት የፌዴራል ሆስፒታሎች የግሎቹን ጨምሮ ከ49 በላይ ከመድረሳቸውም
በተጨማሪ በርካታ የማስፋፊያ ስራዎች ተሰርተዋል፡፡ በከተማችን በሚገኙ ነባር ሆስፒታሎች ውስጥም የባለ 5 እና 8 ወለል ዘመናዊ
ጠቅላላ ህክምና መስጠት የሚያስችል ህንፃ ተገንብቶ ለሙሉ ሰአት አገልግሎት ክፍት እንዲሆን ተደርጓል”” የግንቦት 20 25ኛ ዓመት ድልን ስናስታውስ በ17 ዓመቱ መራር ትግል ውስጥ ያለፉ ታጋዮችን
ማንሳታችን አይቀርም፡፡ ከነዛ ቆራጥ ታጋዮች መካከል ደግሞ የእንስት ታጋዮች ሚና ሁሌም በታሪክ ሲወሳ ይኖራል”” እንስት ታጋዮች ከደጀንነት እስከ ከፍተኛ የአዋጊነት ደረጃ በፈፀሙት ጀብዱ ስማቸውን በታሪክ
ማህደር ላይ ማስፈር ችለዋል”” ከነዛ ቆራጥ ታጋዮች መካከል አንዷ ሲስተር ውዴ ሽፈራው ናቸው፡፡
የኢህዴን/ብአዴን ታጋይዋ ሲሰተር ውዴ በድርጅቱ ክፍለ ጦር ህክምና ውስጥ በቀዶ ህክምና ክፍል በደጀንነት ተመድበው አገልግለዋል፡፡
በአሁኑ ሰአት ደግሞ በአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ውስጥ በለውጥ ስራዎች ክፍል ውስጥ በመስራት ላይ ይገኛሉ”” በቆይታችን በበረሃው የህክምና ክፍል ውስጥ የነበረውን አጠቃላይ የህክምና አገልግሎትና የሴት
ታጋዮች ሚና ያወጉናል”” እንዲሁም እሳቸው እየተሳተፉበት ያለውና ባለፈው ሩብ ክፍለ ዘመን
በአገራችን በጤናው ዘርፍ የተመዘገበውን እምርታ በተመለከተ አስተያየታቸውን ያጋሩናል፡፡
ሲስተር ታጋይ ውዴ ሰሜን ጎንደር ምዕራባዊ ዞን አርማጮ ነው በ1966 ዓ.ም የተወለዱት፡፡
ገና በለጋ እድሜያቸውም በ1979 ዓ.ም ወደ ኢህዴን/ብአዴን የትጥቅ ትግል ተቀላቀሉ”” ከዛም አንገረብ በሚገኘው የብአዴን ህዳር 11 አዳሪ ትምህርት ቤት ገብተው እንዲማሩ ተደረገ፡፡
በዚህ ትምህርት ቤት እነጓድ ኩማ ደመቅሳን የመሰሉ ከፍተኛ አመራሮች ያስተምሩ እንደነበረም ያስታውሳሉ፡፡
ህዳሴ፡- ወደ ትግል ሲገቡ የተመደቡበት መስክ ምን ነበር?
ሲስተር ውዴ ሽፈራው፡- ወደ ትግል ስገባ 13 ዓመቴ ነበር”” ያው ድርጅቱ አምኖብህ ባስቀመጠህ ስራ ነው የምትሰራው፡፡ እዛው የቀለም ትምህርት በተማርኩበት
የህዳር 11 ትምህርት ቤት ነው ህክምና የተማርኩት፡፡ ከነበረው የሰው ሃይል እጥረት አኳያ ከቀለም ትምህርት ጎን ለጎን የጤና ሙያ
ክህሎት ይሰጠን ነበር፡፡ እዛ ነው ህክምና የተማረኩት፡፡ ትምህርቱን ከተከታተልኩ በኋላ በመጀመሪያ ላይ ሰራዊት ህክምና ላይ ነበር
የተመደብኩት”” 80 ዓ.ም ክፍለ ጦር ህክምና ውስጥ በኦፕራሲዮን ክፍል በረዳትነት
ተመደብኩ፡፡ በተጨማሪም ከደርግ ነፃ በወጡ መሬቶች ላይ ህብረተሰቡን ዳግም በማደራጀት፣ ሙያተኛው እንዳይበተን የማድረግ እና የማበረታታት
ስራ እንሰራ ነበር፡፡
ደርግ ከወደቀ በኋላ በሰንገዴ ክፍለ ጦር የአንድ ሻለቃ ፋርማሲ ሆኜ ለ2 ዓመታት አገለገልኩ፡፡
ከዛም በ1985 ወደላብ አደር ክፍለ ጦር ተዛውሬ ደሴ ጢጣ ካምፕ በክፍለ ጦር ህክምና ሰርቻለሁኝ”” ከ1990 ጀምሮ ለ8 ዓመታት በጦር ሀይሎች በአዋላጅ ነርስነት እንዲሁም በየካቲት 12 ሆስፒታል
በክሊኒካል ነርስነት ሰርቻለሁኝ””
ህዳሴ፡- በትግሉ ወቅት የነበረውን የሴቶች ሚና ቢገልፁልኝ?
ሲስተር ውዴ፡- የሴቶች ሚና ሁለገብ ነው፡፡ በኢህዴን ጊዜ ኢትሴማ የሚባል የሴቶች ማህበር
ነበረን፡፡ በርሃም ትግል ላይ ሆነን ማርች 8 አለም አቀፍ የሴቶች ቀንን እናከብር ነበር፡፡ ከኢህዴን ማዘዠ ጣቢያ ከነበረው ከፈልፈል
ወሎ ድረስ መጥተን ነበር የምናከብረው፡፡ አንድ ጊዜ በአሉን አክብረን ስንመለስ መንገድ ላይ የጠላት ጦር ገጥሞን ከፍተኛ መስዋት
ከፍለናል፡፡
ህዳሴ፡- በትግሉ ወቅት የሴቶች ፅናት በጉልህ ይነሳል፡፡ ምክንያቱ ምንድነው?
ሲሰተር ውዴ፡- ሴቶች የተሰጣቸውን ተልዕኮ በአግባቡ ነው የሚወጡት፡፡ ወደ ትግል ከመግባትህ
በፊት በቂ መረጃ ይሰጥሀል”” ከዛም በላይ ሴቷ አትችልም የሚለውን በህብረተሰባችን ውስጥ ተንሰራፍቶ
የኖረ አስተሳሰብ የሰበረ ነው፡፡ በማህበረሰባችን የነበረው ተፅዕኖ ከባድ ነው፡፡ ሴቶች የመስራት፤ የመምራት እድል ካገኙ ሃላፊነትን
ከወንዶች እኩል መወጣት እንደሚችሉ ያሳዩበት ነው”” በጊዜው
የነበሩ ተቋማት ፆታዊ መብትን ማስከበር ላይ ክፍተት ነበረባቸው፡፡ ዛሬ ላይ የሴቶች እኩልነት ተግባራዊነት በተግባር የታየ ነው፡፡
ያኔ ሴት ልጅ ጡረታ አይከበርላትም ነበር፡፡ አሁን ግን ሴቷ ስትሞት ጡረታዋ የሚከበርበት ቤተሰቧም የማይበተንበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡
ህዳሴ፡- የሴቷ የፅናት ሚስጥር ምንድነው? ሴት ታጋዮች ከድተው አያውቁም፡፡ ይሄ እንዴት ሊሆን ቻለ?
ሲስተር ውዴ፡- ሴት ለአላማዋ ሟች ናት”” ከምንም
በላይ እምነታቸውን በፅናት ነው የሚይዙት፡፡ በጊዜው ጭቆናውም ድርብ በመሆኑ ለትግሉ ሟች ነበረች፡፡ ልጅ ሆኜ ከገባሁበት የህዳር
11 አዳሪ ትምህርት ቤት ጀምሮ እነ ታጋይ ገነትን የመሰሉ ጀግና አዋጊዎች፣ ምሽግ ሰባሪዎች የነበሩበት ነው፡፡ እኛም የእነሱን
አርአያነት ይዘን ነው በትግሉ ውስጥ ታሪክ ለመስራት የራሳችንን አሻራ ማሳረፍ የቻልነው፡፡
ህዳሴ፡- በትግሉ ወቅት ከማይዘነጉ አስደሳችና አሳዛኝ አጋጣሚዎች መካከል የሚያስታውሱት ካለ?
ሲስተር ውዴ፡- የመሀል ከተማው ነዋሪ ታጋይ ሲባል ሰው አይመስለውም ነበር፡፡ በተጨማሪ እኛ ፀረ ህዝብና የድህነት ዘበኛ
የሆነውን ስርአት ለመገርሰስ የታገልን አይመስለውም ነበር፡፡ እኛ የሁሉንም ህብረተሰብ ባህልና ወግ አክብረን ነበር ትግላችንን ስናካሂድ
የነበረው ገበሬው ቤት እንኳ ገብተን አልጋ ላይ አንቀመጥም ነውር ስለነበር፡፡ ለዚህም ነው አርሶ አደሩ ሲጠማን አጠጥቶ ሲርበን
አብልቶ ከጎናችን የነበረው፡፡ በርካታ ሴት ጀግኖች የተሰውበት ሁኔታ እጅጉን ያሳዝናል፡፡ በተለይ በ80ዎቹ መጀመሪያ ላይ ህዝብ
በተሰበሰበበት ቦታ ላይ ይደረጉ የነበሩ ጭፍጨፋዎች በናፓልም ቦንብ ጭፍጨፋ ያለቁ ንፁሀን ሰማዕታት ሁኔታ እጅጉን ያሳዝናል፡፡ ሆኖም
ዋናው አስደሳቹ ነገር ደግሞ ያ አስከፊ ሰርአት መገርሰሱ ነው፡፡
ከአንድ ቤት ሰባት ሆነን ወጥተን ሶስት ነን የቀረነው፡፡ ይሄ ያሳዝንሀል፡፡ ቢሆንም ግን ዛሬ የምታየው ለውጥ የታገሉለት
የተሰውለት አላማ ግቡን መቶ ስታይ ሀዘንህን ይበልጥ ያክምልሀል፡፡
ህዳሴ፡- የበረሃ ትግልና የህክምና ሙያ እንዴት ይገለፃል?
ሲሰተር ውዴ፡- ከባድ ነው፡፡ በርካታ ገጠመኞች ይኖሩሀል፡፡ ቁስለኞችን በቃሬዛ ተሸክመህ ሱዳን ጠረፍ ድረስ ይዘህ ትሄዳለህ፡፡
በጦርነቱ ከባድ ጉዳት የደረሰበት፣ እጁ የተቆረጠ፣ አይኑ የጠፋ ጓድ ታክማለህ፡፡ ይህ ሁኔታ ትግሉን እጅጉን ከባድና ውስብስብ ያደርግብሃል፡፡
ከሁሉ በላይ በጦርነት አውድማ ውስጥ መሀል ሆነህ የምታደርገው ህክምና መሆኑ ሌላኛው የህክምናው ስራ ከባድ ፈተና ነው፡፡ የግብአት
እጥረት አለ፡፡ በዚህም በአግባቡ ቆጥቦ መጠቀም ትለምዳለህ፡፡ እየደማ የመጣ ጓድህን ሸሚዝህን ቀደህ ደሙን ለማቆም ትሞክራለህ፡፡
የመጀመሪያ ህክምና እርዳታ ታደርጋለህ፡፡
በ1981 ዓ.ም ከፈልፈል ወደ አንገረብ 25 ቁስለኞችን ይዘን ስንሄድ የአየር ጥቃት ደረሰብን፡፡ የሎጂስቲክ ሃላፊያችንን
በመስዋትነት አጣን፡፡ በየጊዜው፣ በየወቅቱ በርካታ አሳዛኝ ሁኔታዎች ይገጥሙን ነበር፡፡ ያለብህን የመሳሪያ እጥረት አጣጥመህ ነው
የምትሰራው፡፡ ወንዝ ወርደህ አጥበህ ከአርሶ አደሩ ምጣድ ተውሰህ የህክምና መሳሪያዎችን በእሳት አክመህ ዳግም የምትጠቀምበት ሁኔታ
ነው የነበረው፡፡
ህዳሴ፡- ከታካሚዎች አንፃርስ ምን ያስታውሳሉ?
ሲስተር ውዴ፡- አንድ ታጋይ እግሩ ከተሰበረ ጥብቅ ጥበቃ ነው የሚደረግለት”” ምክንያቱም ሳያገግም ወደ ጦር ግምባር ካልሄድኩ ይላል፡፡ እግሬ ነው የተጎዳው እንጂ መዋጋት
እችላለሁ ይላል፡፡ ሀሳቡ ያለው ግምባር ላይ ነው፡፡ በዚሁ ሁሉ ሂደት ጠፍቶም የሚሄድ አለ፡፡ እራስን ለትግሉ መስዋት አድርጎ የማቅረብ
ፍላጎቱ ከፍተኛ ነበር፡፡ ብዙዎች ቦንብ እየረገጡ ለሌላው ማለፊያ መንገድ ይከፍቱ ነበር፡፡ ይህ ሁሉ መስዋዕት ተከፍሎ ነው ድል
የመጣው፡፡
ህዳሴ፡- ወደ አዲሲቷ ኢትዮeያ እንምጣና ባለፉት ዓመታት በጤናው ዘርፍ በአገራችን የተመዘገበውን
ለውጥ እንዴት ይመለከቱታል?
ሲስተር ውዴ፡- ዛሬ በከተማችን አዲስ አበባ እንኳ የአገልግሎት ሽፋናችን መቶ በመቶ ደርሷል፡፡ ባደጉ አገሮች ብቻ ይሰጡ
የነበሩ የህክምና ስራዎች እዚህ እየተተገበሩ ነው፡፡ የልብ ህክምና የኩላሊት ንቅለ ተከላና ሌሎች ውስብስብ ህክምናዎች በማስፋፊያ
ሆስፒታሎች እየተካሄዱ ነው፡፡ ተደራሽነት ላይ በርካታ ስራ ተሰርቷል፡፡ በየወረዳው በየከተማው ሆስፒታል እና ጤና ኬላ አለ፡፡ በወሳንሳ
ይሄድ የነበረው አርሶ አደር ሳይቀር በአምቡላንስ ወደ ህክምና መስጫ ተቋማት
ትግሉ ሴት የሰራችው ቤት ጅብ ሲጮህ ይፈርሳል የሚለውን የተዛባ አባባል ያስቀረ ነበር የሚሉት
ደግሞ የህወሓቷ ታጋይ ሲስተር ሙሉ ተካ ናቸው፡፡ በትግሉ ወቅት የአቃቂ ክፍለ ጦር የክፍለ ጦር ጤና ሃላፊ ነበሩ፡፡ እስከ ሻለቃ
አመራርነትም ደርሰዋል፡፡ በአሁኑ ሰአት በየካ ክፍለ ከተማ ጤና ጽ/ቤት ሃላፊ ሲሆኑ ወደ ኋላ ተጉዘው የትግሉን ጉዞና የነበረውን
ውጣ ውረድ ሲያወጉ የትናንት ያህል ትዝታውን እያቀረቡ ነው፡፡ በዓሉን በተመለከተ በእንግድነት ጋብዘናቸው የሚከተለውን አውግተውናል፡፡
ህዳሴ፡- በቅድሚያ ለግንቦት 20 25ኛ አመት የድል በአል እንኳን በሰላም አደረስዎ እያልኩ
ወደ ትግል የገቡበትን አጋጣሚ ቢያጫውቱኝ?
ሲስተር ሙሉ ተካ፡- በትግራይ ክልል በቀድሞው ህንጣሎ ወረዳ በአሁኑ ሳምረ ዓዲቀዓላ ነው
የተወለድኩት፡፡ በወቅቱ በትግራይ ሰገናት የሚባል ታዳጊዎች የሚደራጁበት ማህበር ነበረን፡፡ እዛ ተደራጅተን በ1975 ዓ.ም በ14
አመቴ ነው ወደ ትግል የገባሁት፡፡ መጀመሪያ ብርጌድ 35 ነበር የተመደብኩት፡፡ ያ ወቅት ደርግ ከመ‚ለ እየተነሳ የአየር ጥቃት በማድረግ ንፁሀንን የሚገልበት ወጣቶችን እያፈነ የሚወስድበት፤
ቤቶችን የሚያቃጥልበት ጊዜ ስለነበር በጣም ከባድ ጊዜ ነበር፡፡
ህዳሴ፡- በትግሉ ወቅት የነበረውን የሴቶች ሚና እንዴት ይመለከቱታል?
ሲስተር ሙሉ፡- ወደትግሉ እንድንገባ ካደረጉን በርካታ ዋነኛ ጉዳዮች መካከል አንዱ ፆታዊ ጭቆና ነው፡፡ የስርአቱ ተፅዕኖ አለ፤ የባህል ተፅዕኖ አለ፤ በቋንቋህ እኩል የማትዳኝበት ተፅዕኖ አለ በጣም በርካታ ጉዳዮች ናቸው የነበሩት፡፡ በትግሉ ወቅት የነበረውን የሴቶች ሚና እንዲህ ተናግሬ አልጨርሰውም፡፡ የተለያዩ ተፈጥሮአዊ ተፅዕኖዎችን ተቋቁመን ነው ትግሉን ዳር ያደረስነው፡፡ ሴቶች በትግሉ ውስጥ ከጋንታ አመራርነት እስከ ሻለቃና ጀነራል አመራርነት ደርሰናል፡፡ ሴቶች ችግርን የመሸከም፤ የአልበገርም ባይነት ስሜታቸው ከፍተኛ ነው፡፡ እስከ ደርግ ፍፃሜ ድረስ በርካታ እልህ አስጨራሽ ከባድ ውጊያዎችን አካሂደናል፤ ለተከታታይ ቀናት ሳያባሩ የተካሄዱ ጦርነቶች በርካታ ናቸው፡፡ በዚህ ሁሉ ሂደት ውስጥ የማንም ሴት ምሽግ ተሰብሮ አያውቅም፡፡ ከወንድ እኩል ጥይት ተሸክመው ተራራ እየወጡ ወንዝ እየተሻገሩ ተዋግተው ያዋጉ እንስቶች በርካታ ናቸው፡፡ የሴቶች ሚና እንዲህ በቀላሉ ተነግሮ የሚያበቃ አይደለም፡፡
ህዳሴ፡- በትግሉ ወቅት ከነበሩ አሳዛኝና አስደሳች አጋጣሚዎች ወይም ክስተቶች መካከል የሚያስታውሱትን ቢያጫውቱን?
ሲስተር ሙሉ፡- በርካታ አሳዛኝና አስደሳች ገጠመኞች ይኖሩሃል፡፡ የተደሰትኩበት ቀን 604ኛ ኮር በሽሬ ውጊያ ሲደመሰስ አጠቃላይ ትግራይ ነፃ ስትወጣ የነበረኝ ደስታ ልዩ ነበር፡፡ ሌላው በርካታ ታጋዮችን በየጦር ግምባሩ ያጣንበት በተለይም በመጨረሻዎቹ የደርግ መደምሰሻ ውጊያዎች በአዋሽ አርባ አካባቢ በተካሄዱ ጦርነቶች ላይ የተሰው ታጋዮች ይህን ሰላምና እየተመዘገበ ያለ እድገት ቢያዩት ደስ ይለኝ ነበር፡፡ ሌላው አጋዚ ክፍለ ጦር የነበረው ወንድሜ መሰዋቱን ስሰማ እጅግ ነበር ያዘንኩት፡፡ መሰዋት እንዳለ ባውቅም እስከ ትግሉ ፍፃሜ ድረስ በህይወት አለ የሚል መረጃ ነው የነበረኝ፡፡ ከዛ መሞቱን ስሰማ በጣም ነው ያዘንኩት፡፡ በመሰዋቱ አይደለም ለዚህ አላማ በርካቶች ተሰውተዋል፡፡ አስቀድሜ መሞቱን ባውቅ ብዬ እንጂ፡፡
ህዳሴ፡- ወደ ህክምና ሙያ ልመልስዎትና እስከ ሻለቃ አመራርነትና የክፍለ ጦር ጤና ሃላፊነት ደረጃ ድረስ የደረሱበትን የህክምና ህይወት ያጫውቱኝ?
ሲስተር ሙሉ፡- በትግል ወቅት ታጋይ ተወግቶ ቆስሎ ሲመጣ እየተዋጋህ ነው የምታክመው፡፡ በጦርነት ትሳተፋለህ መልሰህ ታክማለህ፡፡ ታጋዩ ሞራሉ ከፍተኛ ነው ወዲያው ታክሞ ነው ወደ ግምባር መሄድ የሚፈልገው፡፡ በትግሉ ከማዕከል እስከ ሐይል ሃኪም ድረስ አለ፡፡ እስከ ግምባር ደረጃ ከፍተኛ ኦፕራሲዮን የሚካሄድበት ነው፡፡ የሚተካ ሀይል ስለማታገኝ በፍጥነት መልሰህ አክመህ እንዲያገግም አድርገህ ወደግምባር የምትገባበት ሁኔታ ነው የነበረው፡፡
ህዳሴ፡- ከግብአት አንፃር የነበረው ሁኔታስ? ሁሉ ነገር የተሟላ ነበር?
ሲስተር ሙሉ፡- ከግብአት አንፃር ሁሉ ነገር የተሟላ አይደለም፡፡ ያው የጦርነት አውድማ ማዕከል ነው ያለነው፡፡ ድንገት ጠላት ከቦ ጥቃት ሊሰነዝርብህ ይችላል፤ የአየር ጥቃት ሊከፈትብህ ይችላል ልትከበብ ትችላለህ ሌላም ሌላም፡፡ በርካታ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ናቸው የነበሩት፡፡ ዋናው የግብአታችን ምንጭ የነበረው ግን ከራሱ ከጠላት ከምንማርከው ግብአት የሚገኝ የህክምና መሳሪያ ነው፡፡ ከዛም ገበሬው ያለውን አዋጥቶ ከሚገዛልን፤ ነጠላውን እየቀደደ ከሚሰጠን ነው፡፡ በዚህ ነው ያለህን ውስን አቅርቦት አብቃቅተህና አጣጥመህ አለፍም ሲል ዳግም መሳሪያውን እራሱ በእሳት አክመህ ነው የምትጠቀመው፡፡ ይህንን በአግባቡ እየተጠቀምን ነው እዚህ የደረስነው፡፡ ያንን መራራ ወቅት ያለፍነው፡፡
ህዳሴ፡- ከጉዳታቸው ሳያገግሙ ወደግምባር መመለስ የሚፈልጉ ታካሚዎችን እንዴት ነበር የምትከታተሉት?
ሲስተር ሙሉ፡- ወደግምባር ካልተመለስኩ እያሉ በጣም ነበር የሚያስቸግሩት፡፡ በአጭር ጊዜ ነው መመለስ የሚፈልጉት፡፡ በተለይ ሳያገግሙ በከፍተኛ እልህ እና ወኔ ነው መዋጋት የሚፈልጉት ሀሳባቸው ሁሉ ግምባር ላይ ነው፡፡ እስኪሻላቸው ድረስ በደንብ እንዲያገግሙ ትጠብቃቸዋለህ ሆኖም ጠፍቶ አምልጦህ ወደግምባር የሚሄድ ግን አለ፡፡ እረፍት የለም እየተዋጋህ እያከምክ ነው የምትሰራው፡፡
ህዳሴ፡- እንደ ጤና ባለሙያነትዎ በአገራችን ባለፉት 25 አመታት በጤናው ዘርፍ የተመዘገቡ ለውጦችን እንዴት ይመለከቷቸዋል?
ሲስተር ሙሉ፡- በጤናው ዘርፍ እንደ ሀገር ብሎም እንደ አዲስ አበባ ከፍተኛ ለውጥ ተመዝግቧል”” ከጤና ኬላ እስከ ሆስፒታል በበቂ ሁኔታ በመገንባት ላይ ነው፡፡
ያኔ በጣት የሚቆጠሩ የጤና ባለሙያዎች ዛሬ በመቶ ሺዎች ደረጃ ደርሰዋል፡፡ የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራማችን በሚገባ በመተግበሩ ተጨባጭ
ለውጥ በህብረተሰባችን ጤና ላይ ማምጣት ተችሏል፡፡ በትግልም ወቅት የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራምን በአግባቡ ነበር የምንተገብረው፡፡
ፍሳሽ ማስወገጃና ሽንት ቤት ለጤና አስፈላጊ የሆኑ ነገሮችን ነፃ ባወጣናቸው መሬቶች ላይ እየገነባን የጤና ኤክስቴንሽን ፓኬጅን
እየተገበርን ህብረተሰቡ ጤናውን እንዲጠብቅ እያስተማርን ነው የነበርነው፡፡ ዛሬም ይህን በሚገባ ተግባራዊ አድርገናል፡፡ ከሽፋን
አኳያ እንኳ ብንመለከት እኔ ባለሁበት በየካ ክፍለ ከተማ ባሉ 13 ወረዳዎች ውስጥ 15 ጤና ጣቢያዎች ተገንብተው የተሟላ አገልግሎት
በመስጠት ላይ ናቸው፡፡ ድሮ ሰፊውን ህዝብ ለበሽታ ተጋላጭ ሲያደርጉ የነበሩ እንደ የልጅነት ልምሻ (ፖሊዮ) አይነት በሽታዎች ዛሬ
የሉም፡፡ ክትባቱ በሚገባ ተደራሽ በመሆኑ በፖሊዮ አካል ጉዳተኛ የሆነ ሰው አይታይም፡፡ የእናቶችም ሞት ቀንሷል”” በወሊድ ምክንያት አንድም እናት አትሞትም
የሚለው መርህ ግቡን በመምታት ላይ ነው፡፡ ከ50 በመቶ በታች የነበረው የቅድመ ወሊድ ምርመራ መቶ በመቶ ደርሷል፡፡ ተደራሽነታችንና
በአጭር ጊዜ ያስመዘገብነው ድል ለሌሎች ሀገራትም በምሳሌነት የሚነሳ ነው፡፡ በቀጣይ ይህንን ድል በጥራቱ ላይም ለመድገም የተለመደ
ግምባር ቀደም ሚናችንን መወጣት አለብን፡፡
ህዳሴ፡- በመጨረሻ ለአዲሱ ትውልድ ግንቦት 20ን አስመልክተው የሚያስተላልፉት መልዕክት?
ሲስተር ሙሉ፡- እንኳን ለግንቦት 20 25ኛ አመት የድል በአል በሰላም አደረሰን እያልኩ
አዲሱ ትውልድ የሀገር ፍቅር ስሜት ሊኖረው ይገባል እላለሁ፡፡ ከሁሉ በላይ ስለሚያደርገው ማንኛውም ነገር ምክንያታዊ መሆን አለበት፡፡
ለዚህ ቀን እንድንበቃ የተከፈለው መስዋትነት ቀላል እንዳልሆነ ሁሉም ሊያውቀው ሊገነዘበው ከትግሉም ሂደት ሊማርበት ይገባል እላለሁ፡፡
በቀይ ሽብር የረገፉ ወጣቶች በተማሪዎች እንቅስቃሴ ወጥተው የቀሩ ተማሪዎች፤ በየበረሃው ለአላማቸው የተዋደቁ የጭቁን ህዝብ የአብራክ
ክፋዮች በርካታ ናቸው፡፡ አሁን ከወጣቱ የሚጠበቀው በተሰማራበት የሙያ መስክ ራሱንና ሀገሩን የበለጠ ለመጥቀም መስራት ነው ያለበት፡፡
በዛ ትውልድ ደምና አጥንት የተገኘውን ድልና መልካም አጋጣሚ በሌሎች ዘርፎችም በድህነትና ኋላቀርነት ላይ መድገም ያስፈልጋል፡፡
ከሁሉ በላይ ሰላም ያላትን ዋጋ መገንዘብ ይገባል፡፡ ሰላም ሲኖር ነው ሀገር የሚኖረው፡፡ ሀብት ማፍራት፣ ቤተሰብ መመስረት፣ ወጥቶ
መግባት የሚቻለው፡፡ ስለዚህ ይህ ትውልድ ያለበትን ታሪካዊ አደራ ከዳር ለማድረስ ሌት ተቀን ሊሰራ ይገባዋል ማለት እፈልጋለሁ፡፡
ህዳሴ፡- ለነበረን ቆይታ በአንባቢያን ስም ከልብ አመሰግናለሁ፡፡
ሲስተር ሙሉ፡- እኔም እንግዳችሁ ስላደረጋችሁኝ ምስጋናዬ የላቀ ነው፡፡