የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ የስልጣን ዘመናቸው መገባዳዱን ተከትሎ ታይምስ ለተባለ ታዋቂ መጽሔት አንድ አነጋጋሪ
ቃለ ምልልስ ሰጥተው ነበር፡፡ በቃለ ምልልሳቸው ጎልቶ የወጣው አንድ አነጋጋሪ ነጥብ በስልጣን ዘመናቸው የሰሯቸው ስህተቶችን ዘርዝረው
ማስቀመጣቸው ነው፡፡ በተለይ መንግስታቸው ሊቢያን በተመለከተ የተከተከሉትን ፖሊሲ መተቸታቸው ብዙ ነጥቦችን እንድንፈትሽ የሚገፋፋ
ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡ ባራክ ኦባማ እንዳሉት "Probably failing to plan for
the day after what I think was the right thing to do in intervening in
Libya," የሚል ሀሳብ ሰጥተው ነበር፡፡ በሊቢያ ጉዳይ ጣልቃ የገባው
መንግስታቸው ከመሃመድ ጋዳፊ መወገድ በኋላ ስለምትመጣው ሀገር ቆም ብሎ አለማሰቡ ስህተት እንደነበር በገሃድ መስክረዋል፡፡
ቁምነገሩ ያለው እዚህ ላይ ነው፡፡ የእሳቸው ንግግር ምን አዲስ ነገር ይዞ መጣ ብለን እናነሳ ይሆናል፡፡ አሜሪካ
በየትኛውም ሀገር የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ገብታ ማን በስልጣን መቆየት እንዳለበት፣ ማን መወገድ እንዳለበት፣ አንዱ ከስልጣን ተወግዶ
ቀጣይ ማን እንደሚሆን የመወሰን ስልጣን አላት እንደማለት ነው፡፡ በርግጥ ይህ እውነት አዲስ እውነት አይደለም፡፡ በሊቢያ ጉዳይ
አሜሪካና ምዕራባዊያን መንግስታት ጣልቃ ገብተው እንደነበር ለመረዳት ጊዜው አልፏል፡፡
እ.አ.አ በ2010-2011 በወቅቱ የነበሩት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሂላሪ ክሊንተን በዚህ ረገድ ሚናቸው የጎላ ነበር፡፡
‹‹የአረቦች ፀደይ›› በመባል የሚታወቀው የአረብ ሀገራት ህዝባዊ መነቃቃት ከወደ ቱኒዚያ መንፈስ ሲጀምር ሊቢያ በአንፃራዊ መረጋጋት
ውስጥ ነበረች፡፡ እንዲያውም መሓመድ ጋዳፊ በህዝባዊ ንቅናቄው መጀመሪያ ከስልጣን ለተወገዱት የቱኒዚያ መሪ ቤን አሊ በላኩላቸው
የወዳጅነት መልዕክት ‹‹አንተ እኮ ሀገርህን እንደኔ ብትመራት ኖሮ እንዲህ አትሆንም ነበር፣ ድጋፌ አይለይህም›› ብለዋቸው ነበር፡፡
ቆይቶ ግን የተጀመረው ንቅናቄ ወደ ሰሜናዊ የሊቢያ ክፍል ዘልቆ ገባ፡፡ መሐመድ ጋዳፊ ሊቢያ በከፋ አምባገነናዊ ስርዓት ውስጥ የአንድ
ጎልማሳ ሰው ዕድሜን ያህል የመሩ ሰው ናቸው፡፡ በእሳቸው የስልጣን ዘመን ሊቢያዊያን የዴሞክራሲ ሽታ ርቋቸው ስለነበር የህዝቡ የለውጥ
ፍላጎት አይቀሬ ነበር፡፡ ለ42 ዓመታት አምባገነናዊ ስርዓት ያሰፈኑት ጋዳፊ ወንበራቸው መነቃነቁን የተረዱት ምዕራባዊያን መንግስታት
በዚህች አጋጣሚ የተነቃነቀውን ወንበር የበለጠ ገፍትሮ ለመጣል በማሰብ ጣልቃ ገቡ፡፡ የተለያዩ ሀገራትን ቅንጅት ፈጥረናል ብለው
በዋናነት ግን ትልልቆቹ ምዕራባዊያን ሀገራት የአየር ድብደባ ጭምር አደረጉ፡፡ በሀገር ውስጥ ጋዳፊን ለመጣል መሳሪያ ታጥቀው ከተፋለሙት
አማፂያን በላይ በምዕራባዊያን የአየር ጥቃት ብዙ ንፁሃን ህይወታቸውን አጡ፡፡ ጋዳፊም ከተደበቁበት ቱቦ ወጥተው ተገደሉ፡፡
ከዚያ ወዲህ ሊቢያ በሁለት መንግስታት ተከፈለች፡፡ በትሪፖሊ ያለው መንግስትና ቶብሩክ ከተማ ያለው መንግስት ተብለው
ሁለት የተለያዩ አስተዳደሮች ‹‹እኔ ነኝ ህጋዊ መንግስት››
ብለው ሀገሪቱን ሰላምና መረጋጋት አሳጧት፡፡ ከዚያም አልፎ ቁጥራቸው እስከ 1700 የሚደርሱ ታጣቂ ቡድኖች ተፈጠሩ፡፡ እነዚህም
ባህሪያቸው በአራት ክፍሎች የሚገለፅ ነው፡፡ አንደኛ እስላማዊ ቡድን እንዲፈጠር የሚፈልጉ ታጣቂ ቡድኖች አሉ፡፡ እነዚህ ከለየላቸው
ኣሸባሪ ቡድኖች ጋር ግንኙነት ፈጥረው የሚንቀሳቀሱ ናቸው፡፡ ሁለተኛው እስላማዊ ህገ መንግስት ያለው ነገር ግን ጽንፈኛ ያልሆነ
መንግስት እንዲመሰረት የሚፈልጉ አሉ፡፡ ሶስተኛው ምንም ዓይነት ሃይማኖታዊ ገጽታ የሌለውና ሴኩላር መንግስት እንዲመሰረት የሚፈልጉ
አሉ፡፡ አራተኛው ደግሞ በውል የሚታወቅ አጀንዳ የሌላቸው ነገር ግን በየአከባቢው ያለውን ነዳጅ ተቆጣጥረው የተወሰነች አከባቢ ብቻ
ማስተዳደር የሚፈልጉ የጎበዝ አለቆች አሉ፡፡ ሀገሪቱ እንዲህ ተበታትና መቅረቷ ለፅንፈኛ ቡድኖች ማበብ እድል በመስጠቱ በርካታ ሽብርተኛ
ቡድኖች እንዲፈጠሩ አድርጓል፡፡ ከዚህ ውስጥ ዋነኛውና ተጠቃሹ የዓለም ትልቁ አደገኛ አሸባሪ ቡድን (Islamic State) በሊቢያ
ውስጥ የራሱ ቅርንጫፍ ከፍቶ እንዲንቀሳቀስ አድርጎታል፡፡ ይህ ቡድን በሰሜን አፍሪካም ሆነ በአውሮፓ ውስጥ ላሉ ሀገራት ከፍተኛ
ስጋት የፈጠረ ቡድን ሆኗል፡፡ ሌላው ቢቀር 28 ኢትዮጵያዊያንና ኤርትራዊያንን በሚዴትራኒያን ባህር ወስዶ በግፍ መግደሉ የቅርብ
ጊዜ ትውስታችን ነው፡፡
ከጋዳፊ መወገድ በኋላ ሊቢያዊያን ጥያቄያቸው ዴሞክራሲ ይምጣልን የሚል መሆኑ ቀርቷል፡፡ አሁን ዋናው ጥያቄ እንደ
ሀገር የመኖርና ያለመኖር ሆኗል፡፡ አንድ ሊቢያዊ በሌላ ሀገር ሄዶ ራሱን ሲያስተዋውቅ ‹‹ሀገር አለኝ›› ብሎ በድፍረት የሚናገርበት
የዜግነት ፀጋ አጥቷል፡፡ ቢያንስ ሀገሩ ማዕከላዊ መንግስት እንደሌላት ሲያስብ የበታችነት ስሜት እንደሚሰማው ግልጽ ነው፡፡ የአሁኑን
የባራክ ኦባማ ‹‹ስህተት ሰርተን ነበር!›› የሚል ንግግር ስናስብ
ይህንን ሁሉ እውነታ እንድናነሳ ያስገድደናል፡፡
ከዓመታት ዝምታ በኋላ የመጣው የዚህ ዓይነቱ ‹‹ስህተት
ሰርተናል›› ድምዳሜ ምንጩ የምዕራባዊያን መንግስታት የተሳሳተ ፖሊሲ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ባራክ ኦባማ ወደ ስልጣን ከመምጣታቸው
በፊት በነበረው የምርጫ ቅስቀሳ ወቅት ለድል ያበቃቸው አንዱ ነጥብ የጆርጅ ቡሽን የተሳሳተ የውጪ ግንኙነት ፖሊሲ ‹‹አስተካክላለሁ!!›› ማለታቸው እንደነበር ይታወሳል፡፡ በዚህ ረገድ
አንዳንድ ‹‹ስኬቶቻቸውን›› መጥቀስ ይቻል ይሆናል፡፡ ነገር ግን አሜሪካና ምዕራባዊያን መንግስታት በአረቡ ዓለም ከተፈጠረው አለመረጋጋት
በኋላ እየከፈሉት ያለው ዋጋ ፖሊሲያቸውን እንዲፈትሹ የሚያደርግ ስለመሆኑ ደፍሮ መናገር ይቻላል፡፡
የአንድ ሀገር መንግስት ፖሊሲ መመንጨት ያለበት ከህዝቡ ፍላጎት ነው፡፡ አዛዡም መሆን ያለበት የሀገሩ ህዝብ ነው፡፡
አምባገነን መንግስታት በዋናነት ሊዳኙ የሚገባቸው በህዝባቸው ትግልና ከትግሉ በሚመነጭ አጋርነት መሆን አለበት፡፡ ዛሬ በሊቢያ ጉዳይ
እንዲህ ዓይነት አቋም ላይ የደረሱት ባራክ ኦባማ በብዙ ሀገራትም ሀገሪቱ የተከተለችው ፖሊሲ ውድቀትን መመስከር አለባቸው፡፡ የዛሬይቱ
ዓለም ከቁጥጥርና ‹‹የዓለም ፖሊስነት›› ፍልስፍና ወጥታ የትብብርና አጋርነት (cooperation and partnership) ዓለም
ልትቀየር ይገባል፡፡ ምዕራባዊያን መንግስታት ለራሳቸው የሚበጃቸው አሻንጉሊት መንግስት በየሀገሩ ለማስቀመጥ ሲሉ በሚከፍቱት ዘመቻ
ደካማ መንግስታት እዚህም እዚያም የሚፈጠሩበት ሁኔታ መቀየር እስካልተቻለ ድረስ ዓለማችን ከተስፋፊነትና አዲስ መልክ ይዞ ከመጣው
የኒዮ ሊብራሊዝም ችግር የምትወጣበት ሁኔታ ሊፈጠር አይችልም፡፡
የምዕራባዊያን መንግስታት በነዳጅ ላይ ተኮፍሰው ህዝባቸውን ሲበዘብዙ የኖሩትን የአረብ ሀገራት መንግስታት ሲጠብቁና
ሲንከባከቡ፣ ገንዘባቸውን በባንኮቹ ሲያከማቹ፣ በመሳሪያ ሀይል ሲደግፉ ቆይቶ የአረብ ሀገራት ዜጎች አምባገነን ሀይሎችን ለማውገዝ
ወደ አደባባይ ሲወጡ ‹‹እኛ ከህዝቡ ጎን አለን›› ማለት ጀመሩ፡፡
ታላቁ መሪያችን መለስ ዜናዊ የአረቦች ፀደይ የተሰኘው ህዝባዊ መነቃቃት ከመጀመሩ አስቀድመው በ2000 ዓ.ም በታተመው
አዲስ ራዕይ መጽሔት ላይ እንዳስቀመጡት የምዕራቡ ዓለም መንግስታት የአረብ ሀገራትን ወደ ራሳቸው መንገድ በመውሰድ የሃይል ሚዛናቸውን
ለማስጠበቅ የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም፣ ቆመንለታል የሚሉት ሰብዓዊ መብትና ዴሞክራሲ በወረቀት ላይ አስቀርተው ያቀዱትን ለመፈፀም
ወደኋላ እንደማይሉ አንስተው ነበር፡፡ ለአብነት አቅርበውት የነበረው የኢራቅ ጉዳይ ብንመለከት ዛሬ ኢራቅ ከነበረችበት አንፃራዊ
መረጋጋት ወጥታ የሽብርተኛ ቡድኖች ማዕከል ወደ መሆን የደረሰችው በምዕራባዊያን የተሳሳተ ፖሊሲ መሆኑ ሀቅ ነው፡፡ ከቀዝቃዛው የዓለም
ጦርነት ማብቃት በኋላ ዓለም አንድ አለቃ ብቻ ይዛ ቆይታለች፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ዓለማችን ከአንድ ዋልታ (Uni Polar) ወደ ብዙ ዋልታዎች (Multi Polar) እየተቀየረች
በመሆኑ የበላይነትን አስጠብቆ ለማቆየት በሚደረግ ሩጫ ውስጥ የዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ተረግጠው ተላላኪ መንግስታትን
በየአቅጣጫው የመፍጠር ሩጫውን ዓላማችንን ብዙ ዋጋ እያስከፈላት መጥቷል፡፡
ከዚህ ዓለማዊ ሁኔታ ውስጥ የምንወስዳቸው ቁምነገሮች አሉ፡፡ ቀዳሚው ጉዳይ የሀገራት ፖሊሲ መመንጨት ያለበት ከራሱ
ብሔራዊ ጥቅም መሆን የሚገባው መሆኑ ነው፡፡ ለዚህም በጽናት የሚቆም ህዝባዊና ዴሞክራሲያዊ መንግስት መኖሩ ወሳኝ እንደሆነ ያሳያል፡፡
ታላቁ መሪ መለስ ዜናዊ ‹‹የኛ መንግስት ቁጭ በል ሲሉት የሚቀመጥ፣ ተነስ ሲሉት የሚነሳ አይደለም፡፡›› ያሉትን እውነታ ደጋግመን
ስናስብ ቱኒዚያ፣ ሊቢያ፣ ሶሪያ፣ የመን፣ ኢራቅ፣ ዩክሬን ከዓይነ ህሊናችን ሊጠፉ አይችሉም፡፡