መሐል 6 ኪሎ ላይ ተገኝተናል፡፡ ነጩ የስድስት ኪሎ ሰማእታት መታሰቢያ ሓወልት ቆሞ የታሪክ ትውስታችን ይቀሰቅሳል”” ሐወልቱ ነጭ ቀለም እንዲሆን የተደረገው
የተፈፀመው ግፍ በነጮች እንደተፈፀመ ለማመላከት ይሆን? የዛሬ 78 ዓመት በወርሀ የካቲት በኢጣሊያ ፋሽስት ግራዝያኒ ትእዛዝ ለሶስት
ተከታታይ ቀን በተካሄደው ግፍ ነበር ከ30 ሺህ በላይ የከተማዋ ነዋሪዎች የተጨፈጨፉት፡፡ ለመታሰቢያነቱም ሐወልቱ ቆሟል፡፡
እኛም የግጥምጥሞሽ ነገር ሆነና በየካቲት ወር ወደ አከባቢው አቀናን፡፡ ከሐወልቱ ፊት ለፊት በሚገኝ አንድ
ተቋም ጉዳይ አለን”” ያ ተቋም እነዛ በኢጣሊያ ፋሽስት አገዛዝ በተጨፈጨፉ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች መታሰቢያ እንዲሆን የተሰየመ ነው፡፡
የካቲት 12 ሆስፒታል!
ቅጥር ግቢው መግቢያ በር ላይ ተገኝተናል፡፡ ፈራ ተባ እያልን ወደ ፀጥታ ሃላፊው ተጠጋን፡፡ በሌሎች ተቋማት
ከዚህ በፊት የነበረውን አይነት‹‹የህሙማን መጠየቂያ ሰአት ገና ነው!! አሁን መግባት አይቻልም›› የሚል ቀጭን ትዕዛዝ አዘል ምላሽ
ይጠብቀን ይሆን እያልን ነበር የተጠጋነው፡፡ ሆኖም ከግምታችን በተቃራኒ የጥበቃ ባለሙያው በምጥን ፈገግታ አጅቦ ወደ ውስጥ እንድንዘልቅ
ፈቀደልን፡፡ ቅጥር ግቢው ፈጣን እንቅስቃሴ ይታይበታል፡፡ የህክምና ባለሙያው፣ ታማሚው፣ አስታማሚው፣ እጩ የህክምና ተማሪዎች ከወዲያ
ወዲህ ከላይ ወደታች ይርመሰመሳሉ፡፡ ለአይን ማራኪ እና ፅዱ የሆነውን የሆስፒታሉን መንገድ ይዤ መዳረሻዬን ወደ አዲሱ ዘመናዊ ህንፃ
7ኛ ፎቅ አደረግኩ፡፡ ከ7ኛ ፎቅ ቁልቁል ወደታች ስመለከት ከዚህ ቀደም የማውቀው የካቲት 12 ሆስፒታል ስለመሆኑ ጥርጣሬ እስኪያድርብኝ
ድረስ በአድናቆት ተዋጥኩኝ”” ፅዱ ሰርገኞችን ለማስተናገድ የተዘጋጀ ለፎቶ የሚመረጥ ውብ የመናፈሻ ስፍራ መስሏል፡፡ ፋውንቴኑ፣ በመልክ በመልክ
የተተከሉት ውብና ማራኪ አበቦች፣ በአጠቃላይ በተጠና መልኩ ተተክለው የሚታዩት በርካታ አይነት ተክሎች ልብን ያሸፍታሉ፡፡ ለአይን
ይማርካሉ፣ ከፍትፍቱ ፊቱ እንዲሉ የመንፈስ ህክምናው በየካቲት ሆስፒታል ከፅዱ ቅጥር ግቢው ይጀምራል፡፡
አቶ አስራኤል አታሮ የየካቲት 12 ሆስፒታል አስተዳደርና ልማት ፕሬዝዳንት ናቸው፡፡ ሆስፒታሉ 19 አይነት
የተለያዩ የህክምና ግልጋሎት እንደሚሰጥ ይገልፃሉ፡፡ ሰፊ የህክምና አገልግሎት እንዲሰጥ የሚጠበቅበት ተቋም ቢሆንም ከዚህ ቀደም
ሰፊ የአገልግሎት አሰጣጥ ችግርና ቅሬታ ይነሳበት እንደነበር ይገልጻሉ፡፡ በተለይም ከድንገተኛ ህክምና አገልግሎት አሰጣጥ፤ የተመላላሽ
ህክምናና ከካርድ ክፍል አገልግሎት አሰጣጥ ጋር የተያያዙ ቅሬታዎች ይነሱበት ነበር ይላሉ፡፡ በቂ የሰው ሀይል አለመሟላት ጠንካራ
አደረጃጀት አለመኖር፣ ችግሮቹ ስር እንዲሰዱና የመልካም አስተዳደር ቅሬታ ምንጭም እስከመሆን መድረሳቸውን ይናገራሉ፡፡
ታዲያ የዛሬ መልካም እንቅስቃሴው ከየት መጣ ስንል ጠየቅን”” ችግሮቹን ለመቅረፍም በቅድሚያ የተቋሙን
የሰው ሀይል ማሳደግ ላይ ሰፊ ርብርብ እንደተደረገና 632 ብቻ የነበረውን የሰው ሀይል በእጥፍ በማሳደግ ከ1 ሺህ 200 በላይ
በማድረስ በሰው ሀይሉ ላይ ለነበረው ክፍተት ቅድሚያ በመስጠት አፋጣኝ ምላሽ እንዲያገኝ መደረጉን ያወሳሉ፡፡
በመቀጠልም በተቋሙ 8 የለውጥ ቡድንና 115 የ1 ለ5 አደረጃጀቶችን በተጠናከረ መልኩ እንዲዋቀር መደረጉ ሌላው
መፍትሄ አምጪ እርምጃ ነበር ይላሉ፡፡ በዚህም በየስራ ክፍሉ የሚነሱ ቅሬታዎችና አቤቱታዎችን በፕሮሰስ ካውንስል መድረኮች ላይ በማንሳትና
መፍትሄ በማበጀት ችግሮችን ከመሰረታቸው ለመቅረፍ እንዳስቻላቸው ይናገራሉ፡፡ በዚህም በተቋሙ አገልግሎት ፈልገው የሚመጡ ህሙማንና
ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች የእርካታ መጠን መሻሻል እንዳሳየ ይናገራሉ፡፡ይህንንም ከጤና ቢሮና ከከተማው አስተዳደር ጋር በመሆን
በተደረገ ጥናት በዘንድሮው አመት የእርካታ መጠኑ ከ85 በመቶ በላይ እንደደረሰ ተናግረዋል፡፡ ለተገኘው መሻሻልም የለውጥ ቡድኖች
ትግል ቁልፍ ስፍራ እንደሚይዝ ነው የተናገሩት፡፡
‹‹በደፈናው አደረጃጀት ስለተፈጠረ ብቻ
ችግር አይፈታም›› የሚሉት ፕሬዝዳንቱ ይልቁኑ ያልተፈቱ ችግሮችን በጊዜ ቅደም ተከተል በማስቀመጥ እስከ መጨረሻው ትግል እንዲካሄድበት
መደረጉን ያብራራሉ፡፡ እርምጃውንም ከካርድ ክፍል ጀምሮ በማቀጣጠልና መዋቅራዊ ለውጥ በመፍጠር ካርዴ ጠፋ፤ አለአግባብ ተንገላታሁ፣
ተበደልኩ የሚሉ የተገልጋይ ቅሬታዎችን በፍጥነት መቅረፍ መቻሉን ይናገራሉ፡፡ በተጨማሪም ህክምና ፈልገው የመጡ ህሙማን ወዴት መሄድ
እንዳለባቸው ጭምር ከካርድ ክፍሉ የእለት ተረኞች በቂ መረጃ የሚያገኙበት አዲስ አገልግሎት አሰጣጥ መዘርጋቱን ነው የገለፁት፡፡
ሌላው ከተመላላሽ ህክምና ጋር በተያያዘ
ይነሳ የነበረውን ቅሬታና መንገላታት በየደረጃው ካሉ የህክምና ባለሙያዎች ጋር በመነጋገር መፍታታቸውን ይገልፃሉ፡፡ እኛም በሆስፒታሉ
ፕሬዝንዳንት ተጀመሩ፤ ስራላይ ዋሉ የተባሉትን እውነታዎች መሬት ላይ መኖራቸውን ለማረጋገጥ ወደ ተለያዩ ክፍሎች ተዘዋውረን ቅኝት
አደረግን፡፡
የሺሀረግ ጎላ በካርድ ክፍሉ ለረጅም አመታት
ሰርታለች፡፡ ከዚህ በፊት በነበረው አሰራር ሁሉም አይነት ህክምናዎች አንድ ላይ ይስተናገዱ ስለነበረ ከፈጣን አገልግሎት አለመኖር
ጋር ተያይዞ የህክምና ፈላጊው እሮሮ ከፍተኛ ነበረ ትላለች፡፡ አሁን ላይ የ1ለ5 ውይይቶች ተጠናክረው ወደ ተግባር መግባታቸው ለነበሩ
ችግሮች መፍትሄ መስጠት እንዳስቻላቸው ትገልፃለች፡፡ በተጨማሪም የድጋፍ ሰጪ ሰራተኞች ቁጥር መበራከቱ፣ የፕሮሰስ ካውንስል ላይ
በነፃነት የሚደረጉ ውይይቶች እልባት አምጪ መሆናቸው በካርድ ክፍል ላይ ይነሱ የነበሩ ቅሬታና አቤቱታዎች እንዲወገዱ እንዳስቻለ
ነግራናለች፡፡
ለወሊድ ክትትል ከልደታ ክፍለ ከተማ ሪፈር
ይዛው እንደመጡ የነገሩን ወ/ሮ አልማዝም የካርድ ክፍሉን አገልግሎት አሰጣጥ መሻሻሉን ይመሰክራሉ፡፡ ከዚህ ቀደም የነበረው የካቲት
ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ አገልግሎት አሰጣጡ መሻሻሉን እንደታዘቡም ነግረውናል፡፡ ቀጣይ የእርግዝና ክትትላቸውንም እዚሁ ለመከታተል
ለመውለድ ማቀዳቸውን ነው የነገሩን፡፡
የየስራ ክፍሎቹ ተናቦ መስራት የነበረውን
እንግልት እና አላስፈላጊ ምልልስ አስቀርቷል፡፡ ይህ ተጠናክሮ በሌሎችም ተቋማት ሊቀጥል ይገባል ሲሉ ነው ነፍሰ ጡሯ ተጨማሪ ሀሳባቸው
ያጋሩን፡፡
የሆስፒታሉ አገልግሎት አሰጣጥ፣ የባለሙያዎቹ
ክትትልና ድጋፍ መደነቅን እንደፈጠረባቸው የሚገልፁት ደግሞ አቶ ለገሠ ደምሴ ናቸው፡፡ ለአንገት በላይ ህክምና ተኝተው ህክምናቸውን
በመከታተል ላይ መሆናቸውን ነግረውናል፡፡ እስከ አሁን በነበራቸው ቆይታም ብዙ መልካም ጎኖችን እንደታዘቡ ነው የተናገሩት፡፡ አጎታቸውን
እያስታመሙ ያገኘናቸው ወ/ሮ አስናቀች ወዳጆም የአቶ ለገሠን ሀሳብና አስተያየት ያጠናክራሉ፡፡ ‹‹ይህ ለውጥ የአጭር ጊዜ ብቻ መሆን
የለበትም ወደፊትም ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል፡፡›› ነው ያሉን፡፡
አሁን ላይ ያለው ቅሬታና አቤቱታ ምን
ላይ ደርሷል? ተቋሙስ እንዴት ነው ቅሬታና አቤቱታን በየጊዜው የሚመለከተው? ስንል ቀጣይ ቅኝት ያደረግነው ወደ ተቋሙ የደንበኞች
ቅሬታ ሰሚ ክፍል ነበር፡፡ የክፍሉ አስተባባሪ ሃላፊ አቶ አብርሃም ድርባ ከዚህ ቀደም ከተለያዩ ባለጉዳዮች በየእለቱ በርካታ ቅሬታዎች
ይመጡ እንደነበር፤በተለይም በካርድ፣ በላቦራቶሪና በመድሃኒት ክፍል እንዲሁም በድንገተኛ ክፍል ላይ የነበረው ቅሬታ መጠኑ ሰፊ እንደነበር
ያወሳሉ፡፡ በስራ ክፍሎቹ ላይ ይነሱ የነበሩ ተደጋጋሚ ቅሬታዎች አሁን ላይ ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ መፊታታቸውን ተናግረዋል፡፡
የካርድ ክፍሉ በተለየ አሰራር እንዲዋቀር
መደረጉ የሚጠፋ ካርድ እንዳይኖር፣ ካርድ ወደሌላ ክፍል የሚወስደውም ሆነ የሚቀበለው አካል በፊርማው የተቀበለውን ካርድ ብዛትና
አይነት እንዲያረጋገጥ በማድረግና በየጊዜው ከባለጉዳዩ የሚሰጡ አስተያየቶችን በመሰብሰብ ቅሬታ ለተነሳባት ጉዳይ አፋጣኝ እልባት
እንዲያገኝ ለማስቻል በተሰራው ስራ ለውጥ መገኘቱን ይገልፃሉ፡፡
በሆስፒታሉ የፕላስቲክና የአጥንት ህክምና
ዋርድ ሃላፊና ፕሮፌሽናል ነርስ የሆኑት አቶ ሠለሞን አሰፋ በበኩላቸው የቅሬታና አቤቱታ ሰሚ ኮሚቴዎች መዋቀራቸውና ባለጉዳዩን የሚያጋጥሙ
ችግሮች ያለምንም ውጣ ውረድ በኮሚቴው አፋጣኝ እልባት እንዲያገኙ እየተደረገበት ያለው አሰራር በተቋሙ የሚያጋጥሙ ችግሮች ስር ሳይሰዱ
በቀላሉ እንዲፈቱ አስችሏል ይላሉ፡፡
በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ብቻ የሚስተዋለውን
ችግር ሳይሆን የተቋሙን የግዥ ስርአት ህጋዊ መልክ በማስያዝ እንዲሁም በድንገተኛ ህክምና ላይ የነበረውን የአገልግሎት አሰጣጥ ውስንነት
በማስቀረት አሁን ላይ ያለ ገደብ ለድንገተኛ ህክምና የመጣውን ህክምና ፈላጊ ማስተናገድ መጀመሩን ይናገራል፡፡
ዛሬ የካቲት በጨቅላ ህፃናትና እናቶች
ህክምና እንዲሁም የፕላስቲክ ሰርጀሪን ጨምሮ ከፍተኛ የእሳት አደጋ ተጎጂ የሆኑ ህሙማንን ለረጅም ጊዜ አስተኝቶ በማከምና ድነው
ማህበረሰቡን እንዲቀላቀሉ በማድረግ ረገድ እያደረገ ያለው ሰብአዊ ተግባር አንቱታን እያጎናፀፈው ይገኛል በማለት ተጨማሪ አስተያየታቸው
ሰጥተዋል፡፡
ወቅታዊ መረጃዎች እንደሚያመላክቱትና እኛም
በአይናችን እንደተመለከትነው በከተማ ውስጥ ያሉ የሪፈራል ሆስፒታሎችን ጨምሮ የካቲት 12 ድንገተኛ ህክምናን በማስተናገድ ግምባር
ቀደም ሚናውን በመወጣት ላይ ይገኛል፡፡
በ2007 ዓ.ም የአዲስ አበባ ጤና ጥበቃ
ቢሮ በሰራው የደንበኞች እርካታ ምዘናም በተቋሙ አገልግሎት አሰጣጥ የደንበኞች እርካታ ከ85 በመቶ በላይ መድረሱን ነው በጥናቱ
ያረጋገጠው፡፡ ይህ ማለት ግን የመጨረሻው የአገልግሎት አሰጣጥና ደረጃ ላይ ደርሷል ማለት አይደለም፡፡ አሁንም ተቋሙ የጀመረውን
መልካም ጅማሮ አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል፡፡ ህዝብ ደረጃ ሲሰጥ፤ ህዝብ ሲመሰክር ለበለጠ ውጤት እንዲተጋ ተጨማሪ የሞራል ስንቅ ይሆናልና
የካቲቶች በርቱ መልዕክታችን ነው፡፡
በማያባራ ለውጥ ላይ ያለ ተቋም
ቀጣዩ ጉዞአችንን ያደረግነው ወደ ጃንሜዳ
ጤና ጣቢያ ነው፡፡ ሀገራችን ከሁለት አስርት አመታት በፊት የ153 ጤና ጣቢያዎችና ከ70 የማይበልጡ ሆስፒታሎች ብቻ ነበሩዋት፡፡
ዛሬ ላይ ግን 3 ሺህ 500 ጤና ጣቢያዎች፣ 16 ሺህ 250 ጤና ኬላዎችና 350 ሆስፒታሎች ተገንብተው አገልግሎት በመስጠት ላይ
ይገኛሉ”” ከ39 ሺህ በላይ የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎችም
ለጤና ፖሊሲያችን ስኬትና ተግባራዊነት ጉልህ ሚና በመጫወት ላይ ይገኛሉ፡፡ ከእነዚህ ጤና ጣቢያዎች አንዱ የጃን ሜዳው ጤና ጣቢያ
ነው፡፡ ብዙዎች በማያቋርጥ ለውጥ ላይ ያለ ተቋም በማለት ያሞካሹታል፡፡
ጤና ጣቢያው በአራዳ ክፍለ ከተማ በሰሜን
ወረዳ 10 እንዲሁም በደቡብ ወረዳ 7 በምዕራብ ደግሞ ወረዳ 9 ያዋስኑታል”” ለ28 ሺህ 922 የወረዳው ነዋሪዎች ዘርፈ
ብዙ አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡ በ5000 ካሬ ቦታ ላይ የተገነባ ባለአራት ፎቅ ህንፃ ነው፡፡ የህክምና ጤና ማጎልበትና
በሽታ መከላከልን ጨምሮ በአራት የስራ ሂደቶች በመመራት የተደራጀና የተጠናከረ አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡ ከቅድመ ወሊድ
እስከ ድህረ ወሊድ አገልግሎት፣ የሳንባ ነቀርሳ ህክምና፤ የኤች.አይ.ቪ ክትትል እንዲሁም የህፃናት ህክምና ግልጋሎት ይሰጣል፡፡
መንግስት የህብረተሰቡን የጤና ፍላጎት
ተደራሽ ባደረገ መልኩ በከተማችን ሰፊ ስራዎችን በማከናወን ውጤታማ ስራ እየሰራ መሆኑን ማሳያ ሊሆን የሚችል ተቋም ነው፡፡ በከፍተኛ
ወጪ የተገነባው ይህ ጤና ጣቢያ አገልግሎት መስጠት ከጀመረ 3 አመታትን አስቆጥሯል”” በክፍለ ከተማው ካሉ ግዙፍ ሆስፒታሎች
በተጨማሪ ከተገነቡ 8 ዘመናዊ የጤና ጣቢያዎች መካከል አንዱ ነው፡፡
ለአይን የሚማርክ ሰፊና ፅዳቱ የተጠበቀ
ቅጥር ግቢን በውስጡ ይዟል፡፡ በ128 ሰራተኞች የተዋቀረው ጤና ተቋሙ 54 የጤና ባለሙያና የድጋፍ ሰጪ ሰራተኞች አሉት፡፡ ከዚህ
ቀደም ከአገልግሎት ተደራሽነት ጋር በተያያዘ ቅሬታ ይነሳበት እንደነበር አቶ ጋሻው አያሌው የጃን ሜዳ ጤና ጣቢያ ሜዲካል ዳይሬክተር
ይናገራሉ፡፡ በካርድና በድንገተኛ ክፍል ላይም የነበረው የአገልግሎት ተደራሽነት ቅሬታ የነበረበትና የደንበኞችን ፍላጎት መሰረት
ያላደረገ ነበር ይላሉ”” ይህም ለከፍተኛ የአገልግሎት አሰጣጥ ችግር ዳርጓቸው እንደነበረ ነው የገለፁት፡፡
በመሆኑም የዚህ ችግር ዋና መፍትሄ የጤና ሰራዊት በተቋሙ መገንባት መሆኑ መግባባት ተያዘበት፡፡ 8 ሞዴል የ1
ለ5 አደረጃጀቶችን ያቀፈ 20 የ1 ለ5፣ 1 የሴቶች ፎረም እና 4 ሞዴል የሆኑ የለውጥቡድን አደረጃጀቶችን አዋቅሮ አፋጣኝ ምላሽ
መስጠት ጊዜ ሊሰጠው የማይገባ ተግባር መሆኑን በማመን ወደ ስራ ገቡ፡፡ የለውጥ ቡድኖችም መልሰው ተደራጁ፡፡ በለውጥ ቡድን አደረጃጀቶቹ
በመታገዝም ችግሮችን በፕሮሰስ ካውንስል ከማኔጅመንቱና ከሰራተኛው ጋር በመፍታት ከዚህ ቀደም ለነበሩ ችግሮች ምላሽ መስጠት ቻሉ፡፡
ቀደም ሲል የነበረውን የአደረጃጀትና የተደራሽነት ችግር ለመቅረፍም የአንድ መስኮት አገልግሎት አሰጣጥን እውን ማድረግ ቻሉ፡፡ ከካርድ
ክፍል ጀምሮም የአለም የጤና ድርጅት መስፈርትን ተግባራዊ በማድረገ የደንበኞች መጉላላትን፣ መመላለስን በማስቀረት አሰራሩን በሙሉ
ወደ ቴክኖሎጂ በማሸጋገር ተስፋ ሰጪውን ጅማሮ ይበልጥ በተሻለ አደረጃጀት አፋጠኑት፡፡ በመቀጠልም ምቹ ያልነበረውን የድንገተኛ ክፍልም
ለደንበኞች አመቺ ወደ ሆነው ወደ በር አካባቢ በማምጣት ለድንገተኛ ታካሚው ምቹ ሁኔታን ፈጠሩለት፡፡
የለውጥ ሂደቱን በዚህ ያላበቃው ተቋሙ የላብራቶሪ አደረጃጀቱንም ችግር በመቅረፍ በጊዜ በጥራት በመስራት ደረጃውን
የጠበቀ የላብራቶሪ አገልግሎት በመስጠት ላይ ነው፡፡ ይህም የላብራቶሪ አገልግሎቱን ለተገልጋዩና ለባለሙያው ምቹ እንዲሆን ከማድረግ
ይጀምራል”” በዋናነትም ለላብራቶሪ ስራ የሚያስፈልጉ
ግብአቶችን በመጠንም በአይነትም በማሟላት አንድ አለ፡፡ ይህም ያለምንም መቆራረጥ የተሟላ ዘመናዊ የላብራቶሪ አገልግሎት እንዲሰጥ
አስችሎታል”” በቅርቡም በላብራቶሪ አገልግሎት ከአዲስ
ከተማው ጤና ጣቢያ ቀጥሎ በከተማችን ሁለተኛው ባለ 5 ኮኮብ ደረጃ ላይ የደረሰ ተቋም ሊያደረገው የሚያስችለውን ራዕይ የሰነቀ ቀልጣፋ
የላብራቶሪ አገልግሎት በመስጠት ላይ ነው፡፡
በዚህ ብቻ ያልቆመው ጤና ጣቢያው የለውጥ ማዕበሉንም ፋርማሲ ክፍል ድረስ አደረሰው፡፡ ያጋጥመው የነበረውን
የመድሃኒት አቅርቦት ችግር ከመድሃኒት አቅርቦትና አስተዳደር ኤጀንሲ ጋር በጥምረት በመቅረፍ የ24 ሰዓት የተሟላ የመድሃኒት ሽያጭ
አገልግሎት በመስጠት ላይ ነው፡፡ በዚህም የደንበኞች እርካታ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መጥቷል፡፡ ከአቅም በላይ በሆነ የአቅርቦት
ችግር ካልሆነ በቀር ደንበኞች መጥተው የማያገኙት የመድሃኒት አይነት እንደሌለ ፋርማሲስት ትዕግስት የሻኖ ትናገራለች፡፡ ይህም የህሙማንን
ውጣ ውረድ በእጅጉ ማስቀረቱን ነው የገለፀችው፡፡
ጤና ጣቢያው ለሰራተኞች ምቹ የስራ አካባቢንም ፈጥሯል፡፡ የራሱ ዘመናዊ የጤና ነክ ሳይንስና ምርምርን ያካተቱ
መፅሃፍትን የያዘ ዘመናዊ ቤተመፅሃፍት አለው፡፡ ከሁሉም በላይ በጥቂት የግልና የመንግስት ጤና ተቋማት የሚገኘውን የዶፕላር ማሽን
አስገብቷል”” ማሽኑ አንድ እናት ከመውለዷ በፊት ፅንሱ
ያለበትን አጠቃላይ የጤንነት ሁኔታ፣ የልብ ትርታ ጤናማነት ለመከታተል የሚረዳ ማሽን ነው፡፡ በተጨማሪም ፅንሱ ከመወለዱ በፊት ሊያጋጥሙ
የሚችሉትን የጤና ስጋቶች አስቀድሞ ለመከላከል የሚረዳ ነው፡፡
ለእናቶች የወሊድ ክትትል የሚሆንም በሚገባ የተደራጀ ከብክለት ነፃ የሆነ የእናቶች ወሊድ መቆጣጠሪያ ክፍል
አለው፡፡ በተቋሙ ለወለዱ እናቶች የጤና ጣቢያው ማህበረሰብ የሚያደርገው ቤተሰባዊ እንክብካቤም ለየት ያደርገዋል፡፡ እናቶች ከመውለጃ
ጊዜያቸው መቃረቢያ ጀምሮ ወልደው ወደቤታቸው እስኪመረሱ ድረስ አስፈላጊውን ግብአት በማሟላት ቡና፣ ሻይ በማፍላት በቤታቸው ያሉ
ያህል ስሜት እንዲፈጠርባቸው ያደርጋል፡፡
ተቋሙ በሚሰጠው አገልግሎት የህብረተሰቡ እርካታ ከጊዜ ወደ ጊዜ ጨምሯል፡፡ ከአጎራባች ክፍለ ከተሞች ጭምር
መጥተው የሚታከሙ ህሙማን ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እንዲጨምር እንዳደረገው የምትገልፀው አፀደ ብርሃኔ ናት፡፡ ከየካ ክፍለ ከተማ ነው
ለወሊድ ክትትል የመጣሁት የምትለው አፀደ ከካርድ ክፍል ጀምሮ ያለው ፈጣን አገልግሎት አሰጣጥና እንክብካቤ በራሱ የመንፈስ እርካታ
ነው ትላለች፡፡ ተቋሙም የደንበኞችን እርካታ በተመለከተ መመሪያው በሚያዘው መሰረት በ6 ወር ብቻ የነበረውን የደንበኞች እርካታ
ልኬት በየ 3 ወር ጊዜ ውስጥ በመለካት ላይ ይገኛል፡፡ በዚህም በአሁኑ ሰአት የደንበኞች እርካታ 93 በመቶ ያህል መድረሱን ነው
የጤና ጣቢያው ሜዲካል ዳይሬክተር የገለፁልን፡፡
እኛም እዛው ተገኝተን የታዘብነው ይህንን
ሀቅ ነው፡፡ የጤና ጣቢያው ውስጣዊ አደረጃጀት ልዩ ነው፡፡ የአመራሩና የፈፃሚው መልካም ግንኙነትም ይበል የሚያሰኝ ነው፡፡ በማያባራ
የለውጥ ሂደት ውስጥ ያለው ጃንሜዳ በቅርቡ የባለ 3 ፎቅ የፋርማሲ አገልግሎት ብቻ የሚሰጥ ህንፃ ከክፍለ ከተማው ጤና ጽ/ቤት እና
ከከተማው ጤና ቢሮ ጋር በመሆን ለመገንባት ቅድመ ሁኔታዎችን አጠናቋል፡፡ ግንባታውም በመጪዎቹ አምስት ወራት ጊዜ ውስጥ እንደሚጠናቀቅ
ነው ዳይሬክተሩ የገለፁት፡፡ ጃን ሜዳዎች ተቋማዊ የአሰራር ለውጦችን በመጠቀም ወደ ሞዴል ተቋምነት ደረጃ ደርሰዋል፡፡ ይህ ውጤት
የሁሉም የተቋሙ ማህበረሰብ ልፋት ነው፡፡ ጃን ሜዳዎችን በርቱ ማለት እንወዳለን፡፡ ወገንን ከማገለግል በላይ የሚያስደስት ምንም
የለም ብለናል፡፡ አሁንም ያሉ መልካም ተሞክሮዎችን በማስፋት ወደፊትም ተጠናክሮ ከዚህ የበለጠ መጓዝ ይገባል፡፡ ደግሞም ይቻላል”” የዛሬ ድልና ስኬት ነገን እንዳያዘናጋችሁ
አደራ እንላለን፡፡
የኮልፌው አምባሳደር
የጉዞአችን መጨረሻ ወደሆነው ኮልፌ ጤና
ጣቢያ አቅንተናል”” በክፍለ ከተማው ከሚገኙ 11 ጤና ጣቢያዎች መካከል አንዱ የሆነው የኮልፌ ጤና ጣቢያ በክፍለ ከተማው ወረዳ
10 አጠና ተራ አካባቢ ይገኛል፡፡ አዋሳኝ የኦሮሚያ ዞንን አዋሳኝ ክፍለ ከተሞችና አጠቃላይ የአካባቢው ነዋሪዎችን ጨምሮ ከ61
ሺህ በላይ ለሆኑ ነዋሪዎች አገልግሎት በመስጠት ላይ ነው፡፡ እዚህም የጤና ሰራዊቱ ዋና የአገልግሎቱ አንቀሳቃሽ ሞተር ነው፡፡ ሰራዊቱ
በ29 የ1 ለ5፤ በ2 የለውጥ ቡድን አደረጃጀትና በአንድ የፕሮሰስ ካውንስል ስራውን በየጊዜው ይመራል ይገመግማል፡፡ ጤና ጣቢያው
ለችግሮች አፋጣኝ እልባትና መፍትሄ በማበጀት መልካም ስምን ገንብቷል፡፡ ሰኞ፣ ሐሙስ እና አርብ የአደረጃጀቶቹ የግንኙነት፣ የስራ
አፈፃፀም ግምገማ የሚካሄድባቸውና የቀጣይ ስራ እቅድ የሚተለምባቸው ጊዜያት ናቸው ያሉን ሲስተር ጥላዬ ዘዋለ በጤና ጣቢያው የበሽታ
መከላከል የስራ ሂደት መሪ ናቸው”” በአደረጃጀቶቹ የግንኙነት ወቅት ያጋጠሙ ችግሮች መፍትሄ ያገኛሉ፡፡ የተሻለ አፈፃፀም ላስመዘገቡ ፈፃሚዎችና
የጤና ጣቢያው ማህበረሰብ አባላት እውቅና ይሰጣል፡፡ በዚህም ጥሩ የስራ ተነሳሽነትና የስራ አካባቢ መፈጠሩን ይናገራሉ፡፡
ጤና ጣቢያው በቀዶ ህክምና መዋለድ፣ በማህፀን
ጫፍ ካንሰር ምርመራ እና በ8 ተመላላሽ የህክምና አገልግሎት መስጫዎች ልዩ፤ ቀልጣፋ አገልግሎት በመስጠት ላይ ነው፡፡ በተጨማሪም
በጤና ማጎልበትና በሽታ መከላከል ዋና የስራ ሂደት ውስጥ ከቤተሰብ ምጣኔ ጀምሮ እስከ ፀረ ኤች.አይ.ቪ /ኤድስ/ ህክምናና የምክር
አገልግሎት ድረስ ላሉ 14 አይነት የህክምና አይነቶች አገልግሎት ይሰጣል፡፡
ከዚህ ቀደም ጤና ጣቢያው ለጳውሎስ አጠቃላይ
እስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ሪፈር ይፅፍባቸው የነበሩ የቀዶ ጥገናና በምጥ መርፌ የማዋለድ አገልግሎት በራሱ መስጠት በመቻሉ የእናቶችን
ውጣ ውረድ ቀንሷል፡፡ ይህ ተግባሩም በመዲናው ውስጥ ካሉ የመንግስት ጤና ጣቢያዎች መካከል ተመራጭ እንዳደረገው የማዋለጃ ኬዝ ቲም
ሃላፊው ወጣት ዳዊት ንቁ ይገልፃል፡፡ በወር እስከ 240 የሚደርሱ እናቶችም ይህንን አገልግሎት በማግኘት ላይ መሆናቸው ከተቋሙ
ያኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡ ወ/ሮ ቤተልሄም አክሊሉ እና ወ/ሮ ከድጃ ብርሃኑ የጤና ጣቢያው መልካም አገልግሎት ምስክሮች ናቸው፡፡
በእለቱ በጤና ጣቢያው ያገኘናቸው ሁለቱ እንስቶች ለስነተዋልዶ ጤና ክትትልና ስለ ጤናማ አመጋገብ ትምህርት ለመውሰድ መምጣታቸውን
ነግረውናል፡፡ ከዚህ ቀደምም በዚሁ ጤና ተቋም ወልደው ስመዋል”” ዛሬም ጤናን በተመለከተ ከተቋሙ ጋር ያላቸው ቁርኝት ይበልጥኑ ተጠናክሯል፡፡ ስለ ስነተዋልዶና ጤናማ አመጋገብ
ያላቸው እውቀትም መጨመሩን ይገልፃሉ፡፡
ብልህ ወንድም በአስተምህሮው ይሳተፋል፡፡
ወጣት ጌታቸው እንዳለን ያገኘነው በጤና ጣቢያው ባለቤቱን ለህክምና ይዞ መጥቶ ነው፡፡ ከወረዳ 13 ዊንጌት አካባቢ፡፡ የተቋሙን
አገልግሎት አሰጣጥ ይበል የሚያሰኝ ነው ሲል ያሞካሻል፡፡ ከተጠቃሚው ቁጥር ጋር ተያይዞ ያለውን መጨናነቅ ግን የሚመለከተው አካል
ቢያስብበት መልካም ነው ሲል ተጨማሪ ሀሳቡን ሰጥቷል፡፡
ቀጣዩ ጉዛችንን ወደ ጤና ጣቢያው መለስተኛ
ቀዶ ጥገና፣ የግርዛት አገልግሎት ወደሚሰጥበት ክፍል አድርገናል፡፡ በክፍሉ ትርፉ ጣቶችን የማስወገድ፣ በሰውነት ላይ የሚበቅሉ በአድ
ነገሮችን በመለስተኛ ቀዶ ጥገና ከሰውነት ማውጣት፤ እባጮችን በዘመናዊ ህክምና የማስወገድ አገልግሎት እንደሚሰጡ ነው የጤና ባለሙያው
አቶ ዳዊት ላቀው የገለፁት፡፡ የጤና ጣቢያው ደንበኞች በግል ሆስፒታሎች በከፍተኛ ዋጋ የሚያገኛቸውን ግልጋሎቶች እዚህ እስከ
90 ብር ብቻ በመክፈል ያገኛሉ ይላሉ፡፡
የጤና ጣቢያው መልካም ተሞክሮ በዚህ ብቻ
አያበቃም፡፡ ጤና ጣቢያው በከተማችን የመድሃኒት ዝውውርን ኦዲት ትግበራ ከ3 አመታት በፊት ተግባራዊ በማድረጉም ለሌሎች በአርአያነት
እንዲነሳ እንዳደረገው የፋርማሲ ክፍል ሃላፊው አቶ ሙሉጌታ ተሾመ ይገልፃል፡፡ ይህም እያንዳንዱ መድሃኒት ለተገልጋዩ እንዴት እንደደረሰ
ከማሳየቱ በላይ የአንድ የመስኮት አገልግሎትን ዘመናዊ በማድረግ ህሙማን ስለሚጠቀሙት መድሃኒት ጠቀሜታና ተያያዥ የጎንዮሽ ጉዳት
በቂ መረጃ እንዲኖራቸው በማሳወቅ ረገድ ብዙ ርቀት በመጓዝ ላይ ነው፡፡ በቆይታችን እንደታዘብነው የኮልፌ ጤና ጣቢያ አመራሮችና
ፈፃሚዎች እያደረጉት ያለው ዘርፈ ብዙ የለውጥ ትግበራ የተሻለ ገፅታን መገንባት አስችሏቸዋል፡፡ በርቱ ጠንካራ ጎናችሁ እስከመጨረሻው
ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል እንላለን፡፡
እኛም ከብዙ በጥቂቱ በየተቋማቱ ዞረን የቃኘነውን መልካም ተሞክሮ ለእናንተ ለአንባቢያን አቀረብን፡፡ ተቋማቱን
በርቱ እያልን ሌሎች በአገልግሎት አሰጣጥና መልካም አስተዳደር ወደኋላ የቀሩ ተቋማት ቢሮዎችና ሴክተር መስሪያ ቤቶች የእነዚህን
ግምባር ቀደም የጤና ተቋማት ልምድና ተሞክሮን ቢቀስሙ ጠቀሜታው የጎላ ነው ብዙ ታተርፋላችሁ እንላለን፡፡ ጤና ይስጥልን፡፡