Friday, 22 January 2016

በዓለም ምድረ ከብድ ቆይታዬ(4) *** “Wealth Democracy” Vs “Schedule Democracy”


እድሜ ጠገብዋ ቤጂንግ በየ5 አመቱ በጉባኤ የሚመረጠውና 205 የቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ ማእከላዊ ኮሚቴ ማዘዣው ነች፡፡ በነገራችን ላይ ከቋሚ ማእከላዊ ኮሚቴዎች በተጨማሪ 172 የማእከላዊ ኮሚቴ ተለዋጭ አባላት አሉት፡፡ የፓርቲው ከፍተኛ ስልጣን 2300 አባላት ያሉት የፓርቲው ጉባኤ ነው፡፡የፓርቲው አራቱ ዲፓርትመንቶች ማዘዣ ጣቢያቸው ቤይጂንግ ነው፡፡ የድርጅት ጉዳይ ዲፓርትመንት፣ የህዝብ አደረጃጀት ጉዳይ ዲፓርትመንት፣ የፓርቲዎች የጋራ ግንኝነት ዲፓርትመንት/ በነገራችን ላይ በቻይና ስምንት ኮሚኒስት ያልሆኑ ፓርቲዎች አሉ/፣ አለምአቀፍ ግንኝነት ዲፓርትመንት መገኛቸው ቤይጂንግ ነው፡፡ ለ3 ሚሊዮን ሰባት መቶ ሺህ የፓርቲው መዋቅርና 87 ሚሊዮን አባላት ተልእኮ የሚተላለፍላቸው ከቤጂንግ ነው፡፡ በነገራችን ላይ የቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ በርካታ አባላት ካላቸው የአለማችን ፓርቲዎች ሁለተኛ ነው፡፡ የህንዱ ባህርታያ ጃናታ ፓርቲ /Bharatiya Janata Party/ የተመዘገቡ 100 ሚሊዮን አባላት አሉት፡፡

Thursday, 21 January 2016

በዓለም ምድረ ከብድ ቆይታዬ(3) *** ካዳፍኔ ያመለጠው የምደረ ከብድ ኮሚኒስት ፓርቲ ‹‹Bombard the Headquarter››

የትልቅና የታላቋ አገር ቻይና ዋና የፖለቲካ ማእከል ቤይጂንግ የመንግስት ብቻም ሳትሆን የኮሚኒስት ፓርቲው ማእከላዊ ኮሚቴ ምክር ቤት ፅ/ቤት መገኛም ነች፡፡
ኮሚኒስት ፓርቲ ቻይና የተወለደው በ1921 እ.ኤ.አ ነበር፡፡ ቻይና ለሶስት አስርት አመታት በርስበርስ ጦርነትና ራሷን ከጃፓን ወራሪ ሃይል ጋር ጦርነት ላይ ያሳለፈች ሃገር ናት፡፡ ኮሚኒስት ፓርቲው በ1949 የኮሚታንት መንግስትን ከቻይና ዋና ክፍል አስወግዶ መንግስትነት ተቆጣጠረ፡፡ ህዝባዊት ሪፓብሊክ ቻይና መሰረተ፡፡ አብዮቱን በመምራትና ሪፓብሊክ ቻይና በመመስረት ማኦ ትልቅ ድርሻ ነበረው፡፡ ነገር ግን በህዝባዊት ቻይና ሪፐብሊክ ምስረታ ማኦ ፤ ‹‹ቻይና ደካማ ኢንዳስትሪ ነው ያላት፡፡ ገንዘብዋ ትርጉም የለውም፡፡ በከተሞች ስራጥነት ተንሰራፍቷል፣በገጠር የሰብል እጥረት ገጥሟል፡፡ በአንፃሩ የቻይና ህዝብ በአመት በ14 ሚሊዮን እየጨመረ ነው፡፡›› በማለት ያደረገው ታሪካዊ ንግግር ሃገሪቷ በምን ያህል ቀውስ ውስጥ እንደነበረች ያሳያል፡፡ ቻይናውያን ማኦ በሚያቀነቅነው ‹‹አዲስ ዴሞክራሲ›› ፅንሰ ሐሳብ ከሩሲያ የተለየ የሶሻሊዝም ኮሚኒዝም አተያይ እንዳላቸው አስቀመጡ፡፡ አንዳንዶቹ ማኦይዝም ይሉታል፡፡ ይህንን ተከትሎ በ1950 የግብርና ሪፎርም ህግ ይፋ ተደረገ፡፡ በ1956 ደግሞ የግብርና ስርአቱ ወደ ወል እርሻ እንዲሆን ተደረገ፡፡ ይህንን ተከትሎም በሚሊዮን የፓርቲው አባላት የሪፎርም መፅሐፍ ይዘው፣ የሚያደሉት የግብርና እንስሳት፣ማሽነሪዎች አስከትለው ገጠር ገቡ፡፡ አርሶ አደሩም መሬት እንዲያግኝ ተደረገ፡፡ በ1953 የግል ኢንዳስትሪና ቢዝነስ በሙሉ በማገር ሶሻሊስት ኢኮኖሚ እንደሚገነባ ይፋ ሆነ፡፡በተመሳሳይ አመትም የጋብቻ ህግ ወጣ፡፡ በእነዚህ ስር ነቀል እርምጃዎች በእርግጥም በመጀመሪያ አመታት በኢኮኖሚው እምርታ የሚመስል እድገት ተመዘገበ፡፡ በ1952 የቻይና ኢኮኖሚ በ1936 ከነበረው በእጥፍ አደገ፡፡ የኢኮኖሚ ግሽበቱ ተገታ፡፡ የአርሶአደሮችና ላባደሮች ጤና እና ኑሮ መሻሻል አሳየ፡፡ ነገር ግን የለውጥ ብርሃኑ የአደጋ ደመና አንዣበበት፡፡ በ1958 ማኦ ‹‹ታላቅ እመርታ ወደፊት›› የሚል ፖሊሲ ይዞ መጣ፡፡ ይህ ከተማውም ገጠሩም፣ ኢንዳስትሪውም ግብርናውም ያተራመሰ ‹‹በሁለት ጉልበታቸን እንራመድ›› በሚል መፈክር የተቀነቀነው የማኦ የስህተት መንገድ ግን መስፈንጠር ቀርቶ መዳኽ የጀመረው የቻይና ኢኮኖሚን እንደ ሙቀጫ እንዲንከባለል አደረገው፡፡ ‹‹እመርታው›› ትልቅ ርሃብን አመጣ፡፡ ከ1958 እስከ 1961 በተከታተለው ታላቁ ረሃብም ከ20 ሚሊዮን በላይ ቻይናውያን እንደቅጠል ረገፉ፡፡ የህዝባዊት ሪፓብሊክ ቻይና የመጀመሪያ ጠቅላይ ሚኒስተር የነበረው ዝሁዋ ኢናሊያ/Zhou Enlai/ የአስቸኳይ አደጋ ፕሮግራም እንዲቀረፅና እንዲተገበር ማኦን ቢጠይቅም ተሰሚት አላገኘም፡፡

Tuesday, 19 January 2016

በዓለም ምድረ ከብድ ቆይታዬ(2) Think Chinese Speak English!

ምን ይሁን ምን ግን ቻይናውያን ምድረከብድ መሆናቸው አይቀሬ ሆኗል፡፡ የአለም እምብርት፡፡ የአያቶታቸውና ቅድመ አያቶቻቸውን ምኞትና እምነት የልጅ ልጆቻቸው እውን ለማድረግ ተነስተዋል፡፡ በዘመናዊና ማተሪያላዊ ሁኔታ፡፡ ቻይና ዛሬ ሶሻሊስትም ተባለች ሶሽዮ-ካፒታሊስት በዘመናዊ ርእዮተአለማዊ ፍልስፍናዋ ኮንፊሺዮስና ማኦ ትልቅ ቦታ እንዳለቻው ያስተውላሉ፡፡ ማኦ በየህንፃቸው፣ በየአደባበዩ፣ በታሪካዊ ቦታዎች በስእልና በስነቅርፅ ያገኙታል፡፡ 70 በመቶ ጠቅሞን 30 በመቶ ጎዳን የሚሉት ማኦ ለቻይናውያን ያጎናፀፈው የማንነት ኩራት ይበልጥባቸዋል፡፡ በማኦ የተሳሳተ የባህላዊ አብዮት ኢኮኖሚ ፍልስፍና ወደ ፊት እንስፈነጠራለን ሲሉ ቁልቁል የተወረወሩበት ስህተትን አያመነዥኩም፡፡ ያን መንገድ እንዳይደገም ግን ለትውልድ ጠንቅቀው ያስተምሩተል፡፡ ኮንፊሺዮስ ደግሞ በእያንዳንዱ ቻይናዊ ልብና የእለተ እለት እንቅስቃሴ አለ፡፡ የግብረ ገብነት ምንጭ የሚቀዳው ከምድራዊ ‹‹አምላካቸው›› ኮንፊሽዮስ ነው፡፡ ሶሻሊዝም + ማኦይዝም + ኮንፊሺዮሲዝም = ቻይናይዝም፤የህብረተሰባዊ ኢኮኖሚ መንገድ፡፡

በዓለም ምድረ ከብድ ቆይታዬ(1)


በኢትዮጵያ ምድረ ከብድ የሚባል ቦታ እንዳለ አውቃለሁኝ፡፡ ይህንን ስም የሰጡ ሰዎች የአለም እምብርት እዚህ ነው ብለው ያምኑ ነበርም አሉ፡፡ እናም ምድረከብድ ወይም የአለም ሆድ/እምብርት/ አሉት፡፡ እንዲህ ያለው ግንዛቤና አጠራር በሌሎች የአለም ሃገራትም ይኖራል ብዬ እገምታለሁኝ፡፡ ምክንያቱም ከዘመናት በፊት ሰዎች መንደራቸው፣ ሃገራቸውም አለማቸውም በቅርብ ርቀት የሚያውቃትና የሚያይዋት ጎጣቸው ብቻ ነበረች፡፡ ምስጋና ለስልጣኔ እንደዛሬው ከኢትዮጵያ ተነስቶ አሜሪካን ወይም ቻይናን ለመድረስ የአንድ ፀሃይ ጉዞ ብቻ በቂ ሆኖ አለም አንድ መንደር ሳትሆን ማለት ነው፡፡