Tuesday, 19 January 2016

በዓለም ምድረ ከብድ ቆይታዬ(2) Think Chinese Speak English!

ምን ይሁን ምን ግን ቻይናውያን ምድረከብድ መሆናቸው አይቀሬ ሆኗል፡፡ የአለም እምብርት፡፡ የአያቶታቸውና ቅድመ አያቶቻቸውን ምኞትና እምነት የልጅ ልጆቻቸው እውን ለማድረግ ተነስተዋል፡፡ በዘመናዊና ማተሪያላዊ ሁኔታ፡፡ ቻይና ዛሬ ሶሻሊስትም ተባለች ሶሽዮ-ካፒታሊስት በዘመናዊ ርእዮተአለማዊ ፍልስፍናዋ ኮንፊሺዮስና ማኦ ትልቅ ቦታ እንዳለቻው ያስተውላሉ፡፡ ማኦ በየህንፃቸው፣ በየአደባበዩ፣ በታሪካዊ ቦታዎች በስእልና በስነቅርፅ ያገኙታል፡፡ 70 በመቶ ጠቅሞን 30 በመቶ ጎዳን የሚሉት ማኦ ለቻይናውያን ያጎናፀፈው የማንነት ኩራት ይበልጥባቸዋል፡፡ በማኦ የተሳሳተ የባህላዊ አብዮት ኢኮኖሚ ፍልስፍና ወደ ፊት እንስፈነጠራለን ሲሉ ቁልቁል የተወረወሩበት ስህተትን አያመነዥኩም፡፡ ያን መንገድ እንዳይደገም ግን ለትውልድ ጠንቅቀው ያስተምሩተል፡፡ ኮንፊሺዮስ ደግሞ በእያንዳንዱ ቻይናዊ ልብና የእለተ እለት እንቅስቃሴ አለ፡፡ የግብረ ገብነት ምንጭ የሚቀዳው ከምድራዊ ‹‹አምላካቸው›› ኮንፊሽዮስ ነው፡፡ ሶሻሊዝም + ማኦይዝም + ኮንፊሺዮሲዝም = ቻይናይዝም፤የህብረተሰባዊ ኢኮኖሚ መንገድ፡፡

በቻይና መንገዶች በየትኛው ፍጥነትም ሆነ ጥድፊያ ያለ አሽከርካሪ አርጋውያንና ህፃናትን ሳያሻግር አያልፍም፡፡ ትህትና የቻይናውያን መለያ ነው፡፡ ቻይናዊ የቱን ያህል ትምህርትም ሃብትም ቢኖሮው ቤተሰብ በህይወቱ ትልቅ ቦታ አለው፡፡ ቢያገባም ቢወልድም በውሳኔዎቹ ሁሉ ቤተሰብና ቤተዘመድ ሁሌ ቦታ አላቸው፡፡ ምክንያቱም ቻይናዊ የብቻው የሆነ የለውም፡፡ የግሉ ንብረት ቢሆንም የብቻው ግን አይደለም፡፡ የኮሚኒስት ፓርቲ ህግጋትና የኮንፊሽዝም እሴቶች ቻይናዊ ልጓም አልባ ጋላቢ እንዳይሆን የሚገሩት ልጓሞች ናቸው፡፡ ግለኝነት ለቻይናዊ አውሬነት ነው፡፡ ግለሰብ ከቤተሰብ፣ ከጎረቤት፣ ከማህበረሰብ፣ ከትምህርትቤት፣ ከመስራቤት ማተሪያሎች የተገነባ ውህድ አካል እንጂ በራሱ ብቻ የቆመ አካል አይደለምና እነዚህ ባለድርሻ አካላት ባዋጡለት ልክ በግለሰቡ ላይ ቦታ አላቸው፡፡ ከምዕራባውያን ስልጣኔ እጅግ መሰረታዊ ልዩነት ይህንን ይመስለኛል፡፡
ቻይና እውነትም የአለም ምድረከብድ መሆኗ አይቀሬ እየሆነ ነው፡፡ በራሳቸው ቋንቋ ቻይና ማለት ትርጉሙ ምድረ ከብድ/የአለም እምብርት / ማለት ነው፡፡ አያቶቻቸው የአለም ማእከል ቻይና ነው ብለው ያምኑ ነበር ፤ በጂኦግራፊ፡፡ እንዲያ ባይሆንም ቻይና በኢኮኖሚ፣ በፋይናንስ፣ በቴክኖሎጂ፣ በወታደራዊና በዲፕሎማሲና በገበያ የአለም ማእከላዊ ቦታ እየሆነች ነው፡፡ ቻይና እውነትም ቻይና እየሆነች ነው፡፡
ለጥቂት ቀናት ነጭና ጥቁር ሰው ብርቅ የሆነባት ጨፍጋጋዋ ቤጂንግና ጥድፍታሞች ነዋሪዎቿ ለመቃኘት እድል ገጥሞኝ ነበር፡፡ ወደ ወሬ ቀየርኩትና ይኸው ጀባ አልኩኝ፡፡ /ቀጥሎ ስለ ጨፍጋጋዋ ቤጂንግና ጥድፍታሞች ነዋሪዎቿ እንቃኛለን/ሽየዬ ሽየዬ ብያለሁኝ፡፡ አመሰግናለሁ መሆኑ ነው በቻይንኛ፡፡
ጨፍጋጋዋ ቤጂንግና ጥድፍታሞች ነዋሪዎቿ
***
ኮራ. . . ጀነን. . .በቻይናውያን 500 ሺህ ቃላት ባለው መዝገበ ቃላታቸው ስለመኖራቸውም አላውቅም፡፡ በተግባር ግን በ20 ሚሊዮን ቤጂንጋውያን ገፅታና እንቅስቃሴ አይመለከቱም፡፡ በጥዋት ቤይጂንግ ሲመለከቷት ድብርት ልትለቅብዎት ትችላለች፡፡ ለፀሃይ መውጫ ቅርብ ብትሆንም የፀሃይዋ ውልደት በምጥ ነው፡፡ ከጋረዳት ግእዙ ነገር ትንቅንቅ ነው፡፡ ሰማይ ጠቀስ ህንፃዎችዋ ያለከልካይ እንዳይመልከቷቸው የተጋረጠ ባላንጣ አላቸው፡፡ በአንዴ ገለል በል ብለሀው ገለል የማይል፡፡ ጭጋግ፤ ቤጂንግ ጭፍግግ አድርጓታል፡፡ ይቺ ሃገር በ2008 እኤ አ ለተካሄደው ኦሎምፒክ አየሯን ለማፅዳት ለምን 17 ቢሊዮን ዶላር እንደመደበች የገባኝ ሳንባዋን የወጠረው ካርቦን ‹‹ሳጣጥም›› ነው፡፡
በመስኮቴ ብቅ ስል ግን በጨፍጋጋው አየር የማይበገሩ ቅልጥመ አጭር ተስፈንጣሪ ጥድፍታሞች ቤጂንጋውያን ባለ ስድስት ቀለበት መንገድ ከተማቸውን በማለዳ አሳብረውና ሰነጣጥቀው መሃል ከተማ ደርሰዋል፡፡ በነገራችን ቤጂንግ ሰባት ቀለበት መንገድ ነው ያላት፡፡ እናም ነዋሪዎችዋ በመኪና፣ በአውቶቡሰ፣ በሳቦይ፣ በታክሲ ፣ በባጃጅ ፣ በሞቶር ሳይክል፣ በሳይክልና ብእግር ሲጣደፉ ያያሉ፡፡
ቤይጂንግ በአለም አራተኛ ትልቅዋ ከተማ፣ በአለም መንገደኞችን በብዛት በማስተናገድ ሁለተኛ የሆነው ኤርፖርት፣ የፖለቲካ፣የባህልና ትምህርት ማእከል፣የሀገሪቱ የመንግስት ከምፓነዎች ዋና ማእከል እጅግ አስደናቂ አውራጎደናዎች ማሳለጫ መንገድ ኤክስፕረስ ወይ እጅግ ፈጣን የከተማ ባቡር ሳብዌይ ባለቤት ቤይጂንግ 99 በመቶ ነዋሪዎቿ የሃገሬ ሰዎች ቻይናውያን ናቸው፡፡ በአራት ማዘጋጃቤቶች በአስራአራት ዞኖችና ሁለት ልዩ አስተዳደሮች ተዋቅራለች፡፡
እናም ከተማዋ ሰፊ ናት የሚለው አይገልፀውም፡፡ ጠቅላላ ስፋትዋ 16 ሺህ 807 ኪሎሜትር ወይም 6490 ካሬ ኪሎሜትር ይሆናል፡፡ ከ22 ሚሊዮን ገደማ ነዋሪ ያላት ቤይጂንግ ከዚህ ውስጥ በከተማዋ የሚኖሩ የውጪ ዜጎች/የሚበዙት ከጎረቤቶችዋ የመጡ/ ከ300 ሺህ አይበልጡም፡፡ የውጭ ሃገር ብርቅ የሆነባት ከተማ ነች፡፡ ከነዋሪዎቿ 13 ሚሊዮን በላይ ቋሚ ነዋሪዎች ሲሆኑ ቀሪዎቹ ገቢ ወጪ ናቸው፡፡ ነገር ግን ሁሉም የመንግስት እቅድ የሚታቀደው ለወጪ ገቢም ታስቦ ነው፡፡ የአውቶቡስ አቅርቦት፣የባቡር ትራንስፖርት፣ የውሃ አቅርቦት፣ የቴሌኮም መሰረተ ልማት፣የምግብ ፍጆታ፣የኤሌክትሪክ ፍጆታ ከቋሚ ነዋሪው ብቻ በማነፃፀር አይሰላም፡፡ አዲስ አበባም ስሌትዋ እንዲህ መሆን ያለበት ይመስለኛል፡፡ መታወቂያ የወሰደ ብቻን እያሰቡ የእድገት እቅድን ማስላት ለከተሞች አይሰራም፡፡ስለሆነም የውሃ፣የመብራት፣የቴሌኮም፣አቅርቦት፣የእግረኛ መንገድ ስፋትና ርዝመት፣የታክስና አውቶቡስ ቁጥር፣ የፍጆታ ዕቃዎች አቅርቦት ወዘተ . . . በቋሚ ነዋሪው አራት ሚሊዮን ብቻ መሰላት የለበትም፡፡ በዚህ በኩል ኢትዮ ቴሌኮም በአዲስ አበባ የገነባው መሰረተ ልማት ከስድስት ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ሰዎች በሚያስተናግድ መልኩ መሆኑ ፈር ቀዳጅ ሳይሆን አይቀርም፡፡
በቤጂንግ በአውቶቡስ ወይም የምድርውስጥ ባቡር ተሳፍረው ወደ አንድ አቅጣጫ ቢጓዙ ከቻይናውያን ሁለት ነገር ያስተውላሉ፡፡ ወይ በሞባይላቸው እየነካኩ መረጃ ይጠጣሉ፣ አልያም እንቅልፋቸው ይለጥጣሉ፡፡ በወሬ የተጠመዱ ብዙም አይመለከቱም፡፡ በቤጂንግ ከተማ በየቀኑ 6 ሚሊዮን መኪኖች ይርመሰመሳሉ፡፡ ሰዎቹ 6 ቀለበት መንገድ አልበቃ ብሏቸው 7ኛ እየገነቡ ነው፡፡ ቤጂንግ ከ14 ሺ ኪሎሜትር የሚገመት መንገድ ብትገነባም ዛሬም በአለም ከፍተኛ የትራፊክ መጨናነቅ ከሚታይባቸው ከተሞች በቀዳሚነት የምትጠቀስ ከመሆን አላዳናትም፡፡ እናም ከዚህ ጭንቀት ለመገላገል ሁለት ነገር እያበራታተች ነው፡፡ ህዝቡ የህዝብ ትራንስፖርት እንዲጠቀም እና የኤሌክትሪክ መኪኖች እንዲጠቀም፡፡
ከ360 ቻይናውያን ቢሊዮኖሮች ቤጂንግ ላይ የሚገኙት 45 ብቻ ናቸው፡፡ ቢሆንም በቤጂንግ ዛሬ ዛሬ ኑሮ እየተወደደ ነው አሉኝ፡፡ በተለይ የቤት ጉዳይ ወጣቱ ትዳር እንዳይቀልስ እየተፈታተነው ነው ያለችን ራሷ ስታር ብላ የምትጠራ አስጎብኜ ናት፡፡ ለውጭ ሰው ስማቸው ስለሚያስቸግር ብዙ ወጣት ቻይናውያን አቻ አውሮፓዊ ስም በተደራቢነት እንዳላቸው ተገንዘቤ አለሁኝ፡፡ አፍቅሮተ ምእራብ ውልብ እያላበቸው ይሆን ብዬ አሰብኩኝ፡፡ ነገር ግን በአንድ ግድግዳ እንዲህ የሚል ፅሁፍ አነበኩኝ Think Chinese Speak English፡፡ ይቺ መፈክር እኛ ብንዋሳትስ ይከፋል?

No comments:

Post a Comment