
በኢትዮጵያ ምድረ ከብድ የሚባል ቦታ እንዳለ አውቃለሁኝ፡፡ ይህንን ስም የሰጡ ሰዎች የአለም እምብርት እዚህ ነው ብለው ያምኑ ነበርም አሉ፡፡ እናም ምድረከብድ ወይም የአለም ሆድ/እምብርት/ አሉት፡፡ እንዲህ ያለው ግንዛቤና አጠራር በሌሎች የአለም ሃገራትም ይኖራል ብዬ እገምታለሁኝ፡፡ ምክንያቱም ከዘመናት በፊት ሰዎች መንደራቸው፣ ሃገራቸውም አለማቸውም በቅርብ ርቀት የሚያውቃትና የሚያይዋት ጎጣቸው ብቻ ነበረች፡፡ ምስጋና ለስልጣኔ እንደዛሬው ከኢትዮጵያ ተነስቶ አሜሪካን ወይም ቻይናን ለመድረስ የአንድ ፀሃይ ጉዞ ብቻ በቂ ሆኖ አለም አንድ መንደር ሳትሆን ማለት ነው፡፡
ከአዲስ አበባ በአውቶቡስ ደሴ ወይም ጅማ ለመድረስ የሚፈጅብዎት ጊዜ መሆኑ ነው፡፡ ኢጣሊያዊ ነጋዴ ማርኮፖሎ ግን የዛሬ 700 አመት ገደማ ከጣሊያን ወደ ቻይና ከዛም ተነስቶ ኢትዮጵያ ለመድረስ ረጂም አመታት እንደ ፈጀበት ይነገራል፡፡ ዛሬ ግን እንግዲህ አለም እንዲህ ቅርብ ሆናለች፡፡ ከአመታት የእግርና ጀልባ ጉዞ በመርከብ ወደ ወራት ሲያጥር አጀብ እንዳልተባል ዛሬ በአውሮፕላን ወደ ቀናት ሳይሆን ወደ ሰአታት ቀርባለች፡፡ በዛው ልክ የሃገራት ለሃገራት ተፅእኖ ለመደጋጋፍም ለመገፋፋትም ለመመጋገብም ለመዋዋጥም ቅርብ ሆኗል፡፡አጃኢብ!
ህዝቦች የአለም እምብርት ሃገራችን ናት ብለው የሚያምኑበት እሳቤ በጂኦግራፊ መገኛ ልኬት ሳይሆን በኢኮኖሚ፣ ቴክኖሎጂና ፋይናንስ ተፅእኖአቸው አለምን ወደ እነሱ መሳብ በቻሉበት ልክ ሆኗል፡፡ እናም የሰው ልጅ ዘመናዊ ስልጣኔ ስንመለከት ብዙ ሃገሮች የአለም ምድረ ከብድ ሆኖው ነግሰዋል፡፡ ባይነግሱም እንደየአቅማቸው አበርክተዋል፡፡ የነገሱትም ቢሆን በጊዜ ዑደት ንግስናቸው አስረክበው ምድረ ከብድ መሆናቸው አብቅቶ ምድረ እግር ሲሆኑ አይተናል፡፡ ከጥንታውያውያን ሱመሪያን/Sumerian/ እስከ የትናንቱ ሶቭዮታውያን ያለውን ታሪካችን ማየት ይቻላል፡፡ አለም ስንቱን ሃያል አንግሳና ሸኝታ እዚህ ደርሳለች፡፡ መቀበልም መሸችም የለመደች ናትና እሷ እንደሆነ ዛሬም ለመቀበልም ለመሸችም ዝግጁናት፡፡
እኛም እንደ ህዝብና እንደሃገር በዚህ ረጂም የሰውልጅ መውደቅና መነሳት የበዛበት ታሪክ በመቀበልና በማቀበል የራሳችን ድርሻ ነበረን፡፡ አሸራም አለን፡፡ የአክሱም፣ የሮሃ ላሊበላ፣ የፋሲለደስ፣ የሐረር ጀጎል፣ የጢአ፣ወዘተ …የጤፍ፣ የገብስ፣ የቡና … ወዘተ፣ የድንቅነሽ/ሉሲ/፣ የሰላም. . .የዶጎሊ ፣የአድዋ ወዘተ . . .፡፡
በዘመናችን በተለይም የቀዝቃዛ ጦርነት ሲያበቃ አለም ከሁለት አለቆች ወደ አንድ አማራጭ አልባ ጌታ ተጠቃለለች፡፡ ሊበራሊዝም ነገሰ፡፡ ኮሚኒዝም ተቀለበሰ፡፡ የሊበራሊዝም ርዕዮተ አለም አሸነፊነትም እዚያው በዚያው የምዕራቡ አለም አሸናፊነት ብቻ ሳይሆን የመሪዋ የአሜሪካ ብቸኛ ልዕለኋያልነት ያረጋገጠ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ የአሜሪካ ንግስና በወታደራዊና ቴክኖሎጂ ጡንቻ እንጂ በተሻለ አስተሳሰብ አይደለም የሚሉ ቢኖሩም ምን ይሁን ምን ብቸኛ የአለም እምብርት ሆና ለሶስት አስርት አመታት ነግሳለች፡፡
ጃፓናዊ ዝርያ ያለው አሜሪካዊ ፍራንሲስ ፉኩያሃማ እንዳለው ግን ሊበራሊዝም የሰው ልጅ የታሪክ መዳረሻ /መጨረሻ/ ብሎ ነገር የለም፡፡ አሜሪካም የመጨረሻ ኤምፓየር ሆና ነግሳ እስከወዲያኛ አትዘልቅም፡፡ መቀበልና መሸኘት የለመደችው አለም ከወዲሁ ተኪ ሃይል ማፈላለግ የጀመረች ትመስላለች፡፡
ፉኩያሃማ እንዳተነበየው አሜሪካም የመጨረሻ ኢምፓየር ሊበራሊዝምም የአለም መጨረሻ የሰውልጅ ታሪክ መዳረሻ አልሆነም፡፡ የሰው ልጅ ታሪክ የመጨረሻ መዳረሻ እንደሌለው ለመመስከር ብዙ አመታት መጠበቅ አላስፈለገም፡፡ ሌሎች አማራጮች ብቅ ብቅ ብለዋል፡፡ ይህ አዲስ አማራጭ በአንድ መሪ የተጠቃለለ ባይሆንም ቻይና የዚህ አዲስ አማራጭ እምብርት መሆኗ ግን አይካድም፡፡
የቻይና እምብርትነት ከሌሎች የሚለይበት የራሱ ባህሪም አለው፡፡ ቻይናውያን የኔ መንገድ ያልተከተለ እሱ እርኩስ ነው የሚል አስተሳሰብ በመያዝ የመጠርነፍ ፖለቲክስ የማይከተሉ መሆናቸው ነው፡፡ እኔም እንደቤቴ አንተም እንደቤትህ የሚል የፀና አቋም ያራምዳሉ፡፡ ይህንን የቻይናውያን የዲፕሎማሲና ግንኝነት መንገድና አካሄድ ጅብ እስኪደላው እንደሚባል ጠንካራ አለም አቀፍ መሰረትና ተፅእኖ እስኪያገኙ የሚከተሉት እንጂ መንገሳቸው ሲያውቁ እንደ አሜሪካውያን በኔ መንገድ ተጓዝ ማለታቸው አይቀርም የሚሉ አሉ፡፡ ይህ ግምት ነው፡፡ የትናት ‹‹ነገስታት›› ባህሪ በማጣቀስ የሚሰጥ ብይን፡፡
ቻይናውያን በአንድ ነገር እርግጠኛ ሆኗል፡፡ ከጥቂት አስርት አመታት በኋላ የአለም ኢኮኖሚ መሪነታቸው ይረከባሉ፡፡ ዛሬ በብዙ ነገሮች ጥሩ ሁለተኛ መሆናቸው አረጋግጠዋል፡፡ ፈተናቸውም አብጠርጥረው ያውቃሉ፡፡ የሃብት ዴሞክራሲ/ Wealth Democracy/ ማረጋገጥ ቁልፍ ትኩረት አድርገዋል በ13ኛው ‹‹ኢንዳስትሪ መር ትራንስፎርመሽን›› ጉዟቸው፡፡ 100 ሚሊዮን ወንደሞቹ እና እህቶቹ በድህናት ላይ ያሉት ቻይናዊ አይተኛም የሚል እንደ መሪ ቃል የሚደጋግሙት ቃል ነው፡፡ ዛሬ እንዲህ በእድገታቸው አለም የሚደመምባቸው ቻይናውያን የዛሬ አርባ አመት 30 ሚሊዮን ዜገቻቸው በርሃብ ምክንያት ያጡ፣ ጠፍር በልተው ያን ዘመን የተሻገሩ፣ በቻይና ከጠረጵዛ በስተቀር አራት እግር ያለው የማይበላ የለም ተብሎ የተተረተባቸው ናቸው፡፡
የገንዘብ፣ የሀብትና የጊዜ ቁጠባ ለቻይና ከምናቸው በላይ ነው፡፡ የቻይና ሀገራዊ የቁጠባ መጠን ጂዲፒ 53 በመቶ ሲሆን የአሜሪካ ከ10 በመቶ አይበልጥም፡፡ ይህ የሚላችሁ በኤሽያ ንግድና ፋይናንስ ስፔሻላይዝ ያደረገው ዋይነ ኤም ሞሪሶን /Wayne M. Morrison/ ነው፤ ለአሜሪካ ኮንግሮስ በ2013 ባቀረበው ጥናት፡፡ እኛም ከቻይናውያን እንማር ነበር ያለው፡፡
ከአመታት በፊት በፈፀሙት ስህተት ከልብ የተቆጩ የሚመስሉ ቻይናውያን አከባቢን መንከባከብ ስነምህዳርን መጠበቅና ከጥፋት መታደግንም ትኩረታችን ማድረግ አለንብን ብለው ተነስተዋል፡፡ በጣም እንደረፈደባቸው ግልፅ ነው፡፡ ግን ደግሞ አልመሸባቸውም፡፡ የባለአራት ተሽከርካሪ፣ የባለሁለት እግር ሞተር አልባ ፣ የእግረኛ መንገድ በሚል በሶስት በተከፈሉ የቤጂንግ፣ የናታል፣ የሻሃንጋሃይ ከተሞች ስፋት እና ፅዳት ብቻ ሳይሆን ለአረንጓዴ አደባባዮችና መንገድ አካፋዮች የሰጡት ትኩረት እውነት ይች ሃገር በአየር ብክለት የምትወቀሰው ቻይናና ናትን እንዲሉ ያደርጎቷል፡፡ በቻይና መንገድ ብቻውን፣ ህንፃ ብቻውን አያገኝቱም፡፡ በቻይና ህንፃ ማለት በዛፎችና በሳር ያጌጠና የተከበበ ውህድ ነው፡፡ መንገድም እንዲሁ፡፡. . . ዛሬ የሚታየው፡፡ የተከተሉት አካባቢን የሚቃረን የልማት መንገድ ግን ዋጋ እያስከፈላቸው ነው፡፡ እናም ከቻይና ከስኬቷ ብቻ ሳይሆነ ከስህተቷም መማር ይገባናል፡፡
No comments:
Post a Comment