Monday, 11 January 2016

በግድባችን ያልታዩ እጆች የሉም! አሉላ ወርቁ



ህዳር 16 ረፋድ ላይ ነበር የአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ወደ ዝግጅት ክፍላችን የላከው የሚዲያ ሽፋን ደብዳቤ በእጄ የገባውና መመደቤን ያወኩት፡፡ አላማውም ወደ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ መሆኑ ደግሞ አስፈነደቀኝ፡፡ በደብዳቤው እንዲህ የሚል ጎልቶ ይነበባል፡፡ “2ኛው ዙር የኪነ ጥበብ ለህዳሴ ጉዞ” እነሆ በእለቱ የመሄድ አጋጣሚውን ማግኘቴ አስደስቶኝ ከቢሮ የሚያስፈልጉኝን ግብአቶች በመያዝ ወደ ቤት አቅንቼ ለጉዞዬ ስሰናዳ በእለቱ ይተላለፍ የነበረ የምሽት ዜና ትኩረቴን ሳበው፡፡
ዜናው የሻሸመኔ ከተማ ነዋሪ ወ/ሮ አሰለፈች ፀጋዬ የ33 ሺህ ብር ቦንድ መግዛታቸውን ያትት ነበር፡፡ ወይዘሮዋ የግድቡ ስራ ከጀመረ ከ2003 ጀምሮ በ1 ሺህ ብር ቦንድ ግዥ የጀመሩት ድጋፍ ዛሬ ላይ በችርቻሮ ንግድ ተሰማርተው በሚያገኙት ገቢ የ33 ሺህ ብር ቦንድ ለመግዛት መብቃታቸውን ለኢብኮ ጋዜጠኛ ያስረዳሉ፡፡
“አባይ ተገድቦ ሲያልቅ ሰው ሁሉ ይጠግባል፣ ሁሉም መብራት ያገኛል ብዬ አስባለሁ” ሲሉም ተስፋቸውን ተናገሩ፡፡ እኔም የእኚህ ሴት ወ/ሮ ጥንካሬ እጅግ እያስገረመኝ የጉዞዬን ዝግጅት አጠናቅቄ ወደ መኝታዬ አመራሁ፡፡
በማግስቱ ቀጠሮአችን ሀገር ፍቅር ትያትር ግቢ መሆኑ አስቀድሞ ተነግሮናልና ወደ ስፍራው ለማቅናት በማለዳ ከእንቅልፌ ነቃሁ፡፡ የአዲስ አበባ ሰማይ ጨለማ ተገፎላት ወጋገኑ ለሰው ልጆች እንቅስቃሴ ምቹ ሆኖ ነበር፡፡ ከመኖርያ ቤቴ በጥቂት ርቀት ያገኘኋት ሚኒባስ ላይ በመሳፈር መዳረሻዬን ሀገር ፍቅር አደረኩ፡፡ በደረስኩበት ወቅት ሰባት ረጃጅም ደረጃ አንድ የሆኑ አውቶቢሶች ቆመው ተመለከትኩ፡፡ ተጓዦችም የተመደቡበትን መኪና ፈልገው አነስተኛ የጉዞ ሻንጣቸውን ይጭናሉ፤ አስተባባሪዎችም ከቲያትር ቤቱ ትይዩ ቆመው ተጓዦችን ያስተባብራሉ፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥ አብዛኞቹ ተጓዦች በሚዲያና በተለያዩ አጋጣሚዎች የማውቃቸው የኪነ ጥበብ ሙያተኞች ነበሩ፡፡ አዎ የጉዞ አላማ 2ኛ ዙር ኪነ ጥበብ ለህዳሴ በመሆኑ መብዛታቸው አይገርምም ነበር፡፡
የአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ይህንን ጉዞ ለ2ኛ ጊዜ ሲያደርግ በስሩ ከሚተዳደሩ አራቱ ቲያትር ቤቶች ማለትም ሀገር ፍቅር፣ ራስ ቲያትር፣ ህፃናትና ወጣቶች እና ከአዲስ አበባ ቲያትርና ባህል ማዕከል የተውጣጡ ተጓዦች በሰአቱ ተገኝተዋል”” ለጉዞው የተጋበዙ የሚዲያ ባለሙያዎች አነስተኛ መኪና ወደ ቆመበት እንድንሄድ መመሪያ ተሰጥቶን ገባን፡፡
ሁሉም ተጓዥ አለመቅረቱ ተረጋግጦ የ850 ኪሎ ሜትር መንገድ አንድ ተብሎ ተጀመረ”” መዲናችንን ገና በጠዋት ጀርባችንን ሰጥተን ስንወጣ የማለዳዋ ጀንበር ብቅ ማለቷ ነበር”” በመኪናችን ጥቂት ዜና አዳምጠን እንዳበቃን ጨዋታ ተጀመረ”” ስለስራ ቁም ነገር አውርተን፣ አርቲስቱን፣ ባለሀብቱን፣ ባለስልጣኑን፣ አትሌቱን፣ ጋዜጠኛውን ብቻ ሁሉንም በሌሉበት ቢሆንም አቋርጠን ከምናልፋቸው ከተሞች ጋር ስራዎቻቸውን እያስተሳሰርን አምቦ ከተማ ስንደርስ ለቁርስ አረፍን፡፡
ባለኝ መረጃ መሠረት አምቦ እንኳን ሰው እንሰሳም ግራውን ይዞ እንደሚጓዝ ሰምቻለሁ፡፡ ሆኖም ዛሬ ላይ ጥብቅ ህግ መሆኑ ቀርቶ ጥቂቶች ህጉን ሲጥሱት ተመልክቻለሁ፡፡ ሆኖም በእርግጠኝነት ግን ከከተማችን የተሻለ መሆኑን መናገር ይቻላል፡፡ ለመግባባት የማንቸገር ጋዜጠኞች ልክ እንደአብሮ አደግ ሆነን ቁርስ በልተን ወደ መኪናችን ተመለስን፡፡ ጭውውታችንንም በሙዚቃ አጅበን መንገዳችንን ቀጠልን፡፡
አምቦን ወደ ኋላ ትተን ቀጣይ መዳረሻችን ነቀምት ስንደርስ የምሳ ሰአት አልፎ የፀሐይ ሙቀት በረድ ብሎ ነበር፡፡ አስቀድመን የማደሪያ ስፍራችንን በማመቻቸት ምግብ በልተን የከተማዋን ገፅታ ለመቃኘት መዘዋወር ጀመርን፡፡ ከአንድ አመት ከስድስት ወር በፊት እንዳየሁት ለረዥም አመታት ከማገልገሉ የተነሳ የከተማው ዋና መንገድ ለመኪና እንቅስቃሴ አስቸጋሪ ነበር”” አሁን ላይ ግን ያንን የሚቀይርና ደረጃውን የጠበቀ የከተማ አስፓልት ለመገንባት የግንባታ መሳሪያዎችና ግብአት በመንገዱ ላይ አስተዋልኩ፡፡ ከተማዋ አረንጓዴ ተክል የሚበዛት ሲሆን በየስፍራው አዳዲስ ግንባታዎችን ለተመለከተ ነቀምት በፈጣን እድገት ላይ መሆኗን ለመመስከር አይቸገርም፡፡
ማምሻውን የነቀምትን ውበት ተዘዋውሮ ለተመለከታት ሌላ አስደናቂ ነገር ይሆንበታል፡፡ መዝናኛ ቤቶቿ ምግብና መጠጥ አዘጋጅተው እንግዶቻቸውን በአክብሮት ተቀብለው ያስተናግዳሉ”” እኛም ከጥቂት ተጓዦች ጋር በተዘዋወርኩበት ውስን ሰአት የከተማዋን ህዝብ እንግዳ አክባሪነት እና ጥሩ መስተንግዶ ተቋዳሽ መሆን ችያለሁ፡፡ ምሽቱ መግፋቱን ተከትሎ ለበነጋታው ጉዞ ሁላችንም መልካም ምኞታችንን ተለዋውጠን ወደ ማረፊያችን አቀናን፡፡
በማግስቱ የአሶሳን ጉዞ ለመጀመር ስንነሳ ሌሊቱን የጀመረው ዝናብ እያካፋ ነበር፡፡ በዚህም ደግሞ የነቀምት ልምላሜ ሚስጥር ተፈጥሮ ያደላት ገፀ - በረከት መሆኑን ማወቅ ይቻላል”” አስገራሚው ነገር በመጀመሪያ ጉዞዬም ነቀምት ተመሣሣይ የአየር ንብረት ክስተት መፋጠሩ እንድደመም አድርጎኛል፡፡ ሁሉም ተጓዥ ወደየመኪናው ገብቶ ተከታትለን መጓዝ ጀመርን በመንገዳችን በአካባቢው ያስተዋለውን ልምላሜ እያደነቅን የሁለተኛ ቀን ጉዞአችንን ተያያዝነው፡፡
ረፋዱ ላይ ከአባይ ገባር ወንዞች ትልቁን ድርሻ የሚይዘው ዴዴሳ ወንዝ ስንደርስ ሁሉም ከየመኪናው ለሽንት ወርዶ በአካባቢው ፎቶ የመነሳት ስነ ስርአት ካደረገ በኋላ መንገዱን ቀጠለ፡፡ በተለመደው ጨዋታ ታጅበን እኩለ ቀን ላይ ነጆ ከተማ የምሳ ፕሮግራማችንን አደረግን፡፡
የተፈቀደልን አጭር ሰአት ነበርና በቀትሩ የፀሐይ ሙቀት ታጅበን የአሶሳን መንገድ ቀጠልን”” በጉዞው የገበሬው ማሳ በቢጫ ቀለም ደምቆ ይታይ ነበር፡፡ ብዙዎቻችን አደይ አበባ መሆኑን እያሰብን ከመሀከላችን የኑግ ሰብል መሆኑን በተናገረ ቅጽበት መሣሣታችን ገባን፡፡
ከ661 ኪሎ ሜትር ጉዞ በኋላ የአሶሳን ጫፍ ረገጥን፡፡ በከተማው ግራ እና ቀኝ የቆመው ረዣዥም የሰንበሌጥ ሳር አቀባበል ያደረገልን ይመስል አጅቦን መግቢያው ላይ ለፍተሻ ቆምን፡፡ ለአሶሳ ከተማ መዳረሻ ልዩ ሞገስ የሰጠውን የተንጣለለ አየር ማረፊያ አይተን ሳናበቃ የከተማው እብርት ራሣችንን አገኘነው፡፡
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ርዕሰ ከተማ የሆነችው አሶሳ ወከባ የማይታይባት የተረጋጋች ከተማ ናት፡፡ በማግስቱ አሶሳን በጠዋት ለቀን መንገዳችንን ወደ ታላቁ የህዳሴ ግድብ አደረግን፡፡ ከአሶሳ ተነስተን ልክ 150 ኪሎ ሜትር መንገድ እንዳጠናቀቅን ወደ ቀኝ የሚታጠፍ መገንጠያ ትተን ፊት ለፊት በሚወስደው መንገድ 21 ኪሎ ሜትር ያህል ኢትዮ - ሱዳን ድንበር ራሣችንን አገኘነው የጋዜጠኞች ቡድን፡፡ ከድንበር ጠባቂው በተሰጠን ማስተካከያ ወደ ኋላ ተመላልሰን አስቸጋሪውን የኮረኮንች መንገድ ወደ ግድቡ ተያያዝነው፡፡
ከግድቡ በሰባት ኪሎ ሜትር ርቀት ፍተሻ አድርገን የኢትዮጵያውያን አንድነት መገለጫ ታላቁ የህዳሴ ግድብ ስንደርስ ቀድሞን የደረሱት የጉብኝቱ የመጀመሪያ የአቀባበል ስነ ስርአት ተደርጎላቸው በግድቡ ቀኝ ክንፍ ገለፃ እየተደረገላቸው ደረስን፡፡ ከመቅጽበት ካሜራና መቅረጽ ድምፃችንን ወደ ኢንጂነር ስመኘው በቀለ ደገን፡፡ እሳቸው የእኛን መድረስ ተከትሎ ፒካፕ መኪና ላይ ከኋላ ወጥተው ገለፃቸውን ቀጠሉ፡፡
በስፍራው ለተገኙት መሬት በምንላት ፕላኔታችን ላይ ትልቁ ህዝቦች በጋራ ሆነው እየገነቡት ያለው ብቸኛ ፕሮጀክት መሆኑን ኢንጂነር ስመኘው ተናግረው፤ ብዙ ነገሮችን የቀየረ ፕሮጀክት በመሆኑ ሁሌም ልናስበው ይገባልም ሲሉም ለጐብኝው አሳሰቡ፡፡ ለግድቡ 18 ሚሊዮን ኪዩቢክ አፈርና ድንጋይ እስከአሁን ተቆፍሮ ተነስቷል፡፡ ግድቡ ሲጠናቀቅ ለሱዳን 30 በመቶ፣ ለግብጽ 20 በመቶ ወንዙን ተከትሎ ይደርስባቸው የነበረ የጎርፍ የደለል ጉዳት ይቀንስላቸዋል፡፡ ይህ ታዲያ ኢትዮጵያ ለተያያዘችው የጋራ ተጠቃሚነት ለሌሎች የአህጉራችን ሀገሮችም ምሣሌ ለመሆን በቅቷል፡፡
ግድቡ ለኢትዮጵያ ከሚሰጠው ጥቅም ባለተናነሰ ለታችኛው የተፋሰስ ሀገሮች ጥቅም መስጠት ያስችላል፡፡ የውሃው ፋሰት አሁን ካለው በምንም የማይቀንስ መሆኑንም የተፋሰሱ ሀገራት ማመናቸው በአህጉሪቱ ፖለቲካ የፈጠረውን ተጽእኖ መገመት ይቻላል፡፡ በአሁኑ ሰአት አንድ ሺህ 78 ሜትር እርዝመት ያለው ግድባችን ከፍታው 80 ሜትር ደርሷል፡፡ አጠቃላይ አፈፃፀሙ ደግሞ 50 በመቶ መድረስ ችሏል፡፡ በግድቡ ግራና ቀኝ ተዘዋውረን ከጐበኘን በኋላ ለ350 ጎብኚዎች የተዘጋጀውን የምሳ ፕሮግራም በተንጣለለው አዳራሽ ተገኝተን ተጋበዝን፡፡
የምሳ ፕሮግራም እንደተጠናቀቀ 60 ያህል የኪነ - ጥበብ አባላትና ጋዜጠኞች እንዲሁም የዝግጅቱ አስተባባሪዎች በግድቡ ስፍራ ቀርተን ሌላው ጉዞውን ወደ አሶሳ አቀና፡፡ ከ38 ድግሪ ሴሊሼስ ሙቀት ጋር ራሣችንን ለማላመድ ጥረት በማድረግ በተመደበልን ማረፊያ እረፍት እያደረግን ስለምሽቱ ፕሮግራም ምን ሊሆን እንደሚችል ሀሳብ መለዋወጥ ተያያዝን፡፡
ከዚህ ጉዞ በፊት በመጀመሪያው ዙር “ጥበብ ለህዳሴ” ጉዞ በዝናብ ምክንያት ፕሮግራሙን ማካሄድ አልተቻለም ነበር፡፡ በዚህኛው ዙር ለተወሰኑ ደቂቃዎች ከመብራት መቋረጥ በስተቀር በጉባ ተራሮች መካከል በደማቅ ጨረቃ ታጅበን አባይን “በቃህ” ካሉት ውድ ልጆቻችን ጋር ጥሩ ጊዜ ለማሳለፍ ታድለናል፡፡ የቀኑን ፈረቃ ሲያቀላጥፍ የዋሉ የግድቡ ሰራተኞች ከመድረኩ ፊት ተሰየሙ፡፡ ኢንጂነር ስመኘው እና በፕሮጀክቱ የሚሳተፉ የውጭ ሀገር ዜጎችም በተዘጋጀላቸው ስፍራ ተገኝተዋል፡፡ ዝግጅቱ በይፋ መጀመሩ ከመድረክ ተበሰረ፡፡
በሀገር ፍቅር ቲያትር ቤት ስራ አስኪያጅ ካሣዬ ገበየሁ መድረክ አስተዋዋቂነት የደመቀው ዝግጅት የባህላዊ ባንድ ሙዚቃን አስከተለ፡፡ አስቀድሞ የኦሮምኛ ሙዚቃ ተጫዎች ሀይሉ ዴሲሳ ወደ መድረክ መጣ
“Itoopiyaan yoo tokkoo tatee …
Beleef deega bate …”
ትርጉሙ ኢትዮጵያ አንድ ከሆነች ከችግር እና ከረሀብ መውጣት ትችላለች ማለት ነው፡፡ እውነትም ሀይሉ በዛ ሙቀት የሰውነቱን ክብደት ተቋቁሞ የሀገራችንን አንድነት ሲያዜም ከችግርና ረሀብ ለመውጣታችን ቀና ደፋ የሚሉ ወንድምና እህቶቻችን በ”እያሴ”
ስልት መድረኩን ተቆጣጠሩት፡ ቀጠለና አርቲስት ሀብተሚካኤል ደምሴ መድረኩን ተቆጣጠረ፡፡
“ተመለሽ አንችዬ ተመለሽ” ሲያዜም በዛ ምሽት ጨረቃ አባይን በቃህ ተመለስ ብለው የታጠቁ ታታሪ ሰራተኞች በእስክስታውም ወገባቸውን አውረገረጉት፡፡
ሀብተሚካኤል ዜማ ውሰጥ “አውላላው ሜዳ ላይ ፍሪዳ ተጥሎ እምቢ አለ ቢላዋ ልብ አልቆርጥም ብሎ” የሚል ግጥም አለ፡፡ ታዲያ እኛ በጉባ ተራሮች ሁሌ ፍሪዳና ፌሽታ በሌለበት ወገባቸውን ሸብ አድርገው የተነሱ ወገኖች ለዘመናት ሲፈስ የኖረውን አባይን ተመለስ ብለውታል፡፡ ቀጠለ ግጥሙ አውላላው ሜዳ ላይ አንጓላኝ አንጓላኝ … እዚያ ሜዳ በሌለበት በተራራ አጀብ ሀሩር በረሃ አንጓላኝ ሣይሆን እልህና ቁጭት የመወጣት ጥማት አለብኝ ብለው ግድቡንም አጋምሰውታል፡፡
አሁን እኔ ብሞት ምኔ ይቀበራል … ሲል ሀብቴ
“አባይን ገድበን ደማቅ ስም ጽፈናል” ታታሪዎቹ ከስር ያጅቡት ነበር፡፡ በመከላከያ እንጂነሪንግ መካኒካል ባለሙያ የሆነውን ወጣት ተገኘው ትዛዙን ከዝግጅቱ በመነጠል የተሰማውን እንዲነግረኝ ጋበዝኩት፤ በበረሃው የሁለት አመት ቆይታ አድርጓል፡፡ በሙያው ግድቡ እስኪጠናቀቅ ሞራል ሰንቋል በስራው ፅናት ማንገቡን በመናገር፡፡ በኪነ ጥበቡ ምሽት መደሰቱን እና ዘና ማለቱን ሌላኛው በሹፍርና ሙያ የሚሰራው ወጣት ዳኛቸው ሞላ ነው፤ የመጀመሪያው ዙር በዝናብ ምክንያት የተቋረጠው ዝግጅት በእለቱ ተሣክቶ ፈታ ማለቱን አውስቷል፡፡ “በየ 6 ወር የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች እኛን ለማዝናናት ቃል መግባታቸው ደስ ብሎኛል” ብሎ ወደ ጓደኞቹ ለጨዋታ ተቀላቀለ፡፡
በዚህ መልኩ ሌሊቱን ያጋመሰው ደማቅ ዝግጅት በማብቅያው ከመድረክ ወርዶ አጠር ያለ ቆይታ ከጋዜጠኞች ጋር ያደረገው አስተባባሪው ካሣዬ ገበያው ዝግጅቱ በስድስት ወር አንዴ እያቀረበ ሰራተኛውን ለማዝናናት መታቀዱን ነገረን፡፡ “እናንተ ናችሁ” የተሰኘ ሙዚቃ ግጥምና ዜማ ባለቤት የሆነው ካሣዬ ጥበብ በሀገራችን ህዳሴ የበኩሏን ያበረከተችበት አጋጣሚ መሆኑን ጠቅሶ በህዳሴ ጉዞውም ጥበብ የመድረክ ገበታውን ማበርከት እንደምትቀጥል እና በተግባሩም ግንባር ቀደም ተሰላፊ እንደሚሆን አውስቶን ወደ መድረኩ ተመለሰ፡፡
በእለቱም መርሀ ግብር “እናንተ ናችሁ” የተሰኘ ሙዚቃ ምርቃት ተደረገና በኢንጂነር ስመኘው በቀለ በኩል ለግድባችን እንደተርብ ለሚረባረቡ ታታሪ ሰራተኞች ተበረከተ፡፡ የጥበብ ባለሙያዎች እና ሰራተኞችም በጋራ አዜሙት፡፡
እናንተናችሁ … እናንተናችሁ …
ደከመን ሰለችን አንድምቀን ሳትሉ
ውጤታችሁ ታየ ሄያው ሆነ ቃሉ
የቁርጥ ቀን ልጆች የልማት አለኝታ
የሀገርም ኩራት … የትውልድ መከታ
የኢትዮጵያ ተስፋ … ታላቅ ባለውለታ
ታሪክ አይረሳችሁ ለጥቂት ላንዳፍታ
አዎ! የግድባችን ህያውነት በዚህ መልኩ በጥበብ አንደበት ተገልጿል፡፡ ለስኬቱ እውን መሆን ደግሞ ካለን ያበረከትነው እኛው ውድ የኢትዮጵያ ልጆች ነን፡፡ ዝግጅቱን በስኬት ያከናወነው ልዑክ አዳሩን በጉባ አድርጎ ህዳር 21 ማለዳ ጉዞውን ከግድቡ ምስራቅ አቅጣጫ አድርጎ ረፋዱ ላይ አሶሳ ከተማ ደረሰ፡፡ ከቤንሻንጉል ርዕሰ ከተማ ጥቂት ቆይታ በኋላ ያለፍንባቸውን ከተሞች ወደ ኋላ ትተን ከትውስታችን ጋር ወደ መነሻ መዲናችን አደረግን፡፡ የአዲስ አበባ ባልህና ቱሪዝም ቢሮ እያደረገ ያለውን አስተዋጽኦም አደነቅን፡፡

No comments:

Post a Comment