Friday, 24 June 2016

ትርምስ የኤርትራ መንግስት እስትንፋስ



 . ነጋሽ


 

የኤርትራ መንግስት ሰሞኑን በኢትዮጵያ ላይ ትንኮሳ መፈፀሙን ተከትሎ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ጠንከር ያለ እርምጃ ወስዷል። የተወሰደውን እርምጃ አስመልክቶ በኢፌድሪ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች /ቤት በሰጠው መግለጫ እርምጃው በኤርትራ ለተፈፀመው ትንኮሳ የተሰጠ አፀፋ መሆኑን አስታውቋል። የጽህፈት ቤቱ ሃላፊ ሚኒስትር ጌታቸው ረዳ በጉዳዩ ላይ በሰጡት ማብራሪያ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በኤርትራ ጦር ላይ በወሰደው አፀፋዊ እርምጃ የደረሰው ኪሳራ ሻዕቢያ ለሚፈፅማቸው ጥፋቶች ሁሉ ቆም ብሎ እንዲያስብበት የሚያደርግ ነው ብለዋል። በዚህ አጸፋዊ እርምጃም የተፈለገው ውጤት ተገኝቷል ያሉት ሚኒስትሩ እርምጃው የኤርትራ መንግስት የሚያደርጋቸውን ትንኮሳዎች ሊያስቆም ይችላል የሚል እምነት እንዳላቸው ብቻ ሳይሆን የኤርትራ መንግስት ከዚህ በኋላ የሚያደርገውን ትንኮሳ ከቀጠለ፣ መንግስት የሚወስደውን ተመጣጣኝ እርምጃ እንደሚቀጥልም ገልጸዋል።

Wednesday, 22 June 2016

ሰበብ የማያልቅበት የጥቃቅንና አነስተኛ ዘርፍ የሼዶችና ህንፃዎች አስተዳደር!



  መነሻችንን ጦር ሀይሎች አድርገን ወደ ወይ ሰፈር አመራን፡ የኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ ስድስት መገኛ ነው፡፡ በወረዳው አንድ ዘመናዊ ህንፃ ይታያል፡፡ ይህ ባለ አራት ፎቅ ህንፃ ባለፉት አምስት አመታት ይህ ነው የሚባል አገልግሎት መስጠት ያልቻለ እንደቆመ የቀረ ሆኗል፡፡ መብራትና ውሃ ተሟልቶለታል፡፡ ከዋናው አስፖልት መንገድም በቅርብ ርቀት ላይም ይገኛል፡፡ ከአካባቢው ከየትኛውም አቅጣጫ ጎልቶ የሚታይ መስህብ ያለው ዘመናዊ ህንፃ ነው፡፡ የዜጎችን የስራ አጥነት ችግር ከመቅረፍ አልፎ የኢንዱስትሪ እርሾ ማብላያ፤ ለጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት ደግሞ ምርት ማሳያና መሸጫ በመሆን ሊያጋጥማቸው የሚችለውን የገበያ ችግር ለመቅረፍ ታስቦ የተገነባ ህንፃ ነው፡፡
ከዚህ ቀደም የክፍለ ከተማው ጥቃቅንና አነስተኛ ቢሮ ህንፃውን ከስደት ተመላሽ ለሆኑ ዜጎች በአገራቸው ሰርተው እንዲለወጡ ቢያስተላልፍም፤ ቦታ ወስደው ያልጀመሩ፤ ንግድ ፍቃድ አውጥተው በዛው የውሃ ሽታ ሆነው በቀሩ ኢንተርፕራይዞች ምክንያት ተገቢውን አገልግሎት እየሰጠ እንዳልነበረ ማንሳታችን ይታወሳል፡፡
እርግጥ ዛሬ አንፃራዊነት ሊባል በሚችል መልኩ መሻሻል ይታይበታል፡፡ 137 ኢንተርፕራይዞች መስሪያ መሸጫ ሼዱን ተረክበው ስራ ጀምረዋል፡፡ ዙሪያውን ከቦት የነበረው አጥርም ለእይታ ማራኪ ሆኗል፡፡ ይህ ለውጥ የመጣው በርካታ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ በማዘጋጀትና በተደጋጋሚ ማስታወቂያ ስራ ያልጀመሩትን በመመሪያው መሰረት ውላቸው እንዲቋረጥ በማድረግ ነው የምትለው የወረዳው የማዕከላት አቅርቦትና አስተዳደር ባለሙያ ሀና ጫላ ናት፡፡
ህንፃው በአጠቃላይ ለ300 ኢንተርፕራይዞች መሸጫና ማሳያ እንዲሆን ነው የተገነባው፡፡ ዛሬም ለ163 ኢንተርፕራይዞች የሚሆን ክፍት ቦታ አለው፡፡ ይህ የሆነው ለምንድነው? በወረዳውስ የሚደረጅ ስራ አጥ ወጣት የለም ወይ? ስንል ለአቶ ሳሙኤል አበበ የወረዳው ጥቃቅንና አነስተኛ ጽ/ቤት ሃላፊ ጥያቄ አዘል አስተያየት ሰነዘርን፡፡ በህንፃው ቦታ የወሰዱ ኢንተርፕራይዞችን ሙሉ በሙሉ ስራ ለማስጀመር አንቀሳቃሾቹ ላይ የሚታዩ የአመለካከት ችግሮችን ቀርፎ ወደ ስራ መግባት ላይ የሚታይ ውስንነቶች እንዳሉም በመግለፅ፡፡ ይህም ቦታው ለገበያ አይመችም፤ ሞቅ ደመቅ አላለም የሚል ተደጋጋሚ ምላሽ ከኢንተርፕራይዞቹ እንደሚሰጣቸው ነው የገለፁት፡፡ ሀላፊው ችግሩን ለመቅረፍና ስራ እንዲጀምሩ ህንፃውን የማስተዋወቅ፣ ቅጥር ግቢውን ለገበያ ምቹ የማድረግ ስራ ቢሰራም አሁንም ይህ ነው የሚባል ተነሳሽነት ባለመኖሩ የሚፈለገው ውጤት ሊመዘገብ አልቻለም ይላሉ፡፡ ሆኖም ጽ/ቤቱ ከክፍለ ከተማው ጋር በመሆን ለአመታት በተዘጉና በማስታወቂያ ሊመጡ ያልቻሉ ኢንተርፕራይዞች ላይ እርምጃ መውሰድ መጀመሩን ነው የተናገሩት፡፡ በዚህም በህንፃው ላይ ቦታ ከወሰዱ ኢንተርፕራይዞች ውስጥ 36 ያህሉን ለሌላ ስራ ፈላጊ በማስተላለፍ በቅርቡ ስራ እንዲጀምሩ መደረጉን ተናግረዋል፡፡
በቅርቡ ህንፃው ላይ ስራ ከጀመሩ ከስደት ተመላሾች መካከል አንዷ ቤተልሄም መኮንን ናት፡፡ ለ6 አመታት ከቆየችበት የስደት ኑሮ ባዶ እጇን ነው ወደ ሃገሯ የተመለሰችው፡፡ በሀገሬ ሰርቼ መለወጥ እንደምችል ከጥቃቅንና አነስተኛ ያገኘሁት ስልጠና አስተምሮኛል የምትለው ወጣቷ በወተትና የወተት ተዋፅኦ ዘርፍ ስራ ለመጀመር ደፋ ቀና እያለች ነው ያገኘኋት፡፡
ሌሎች ኢንተርፕራይዞች እስከዛሬ ሙሉ በሙሉ ስራ ያልጀመሩት ለምንድነው የሚል ጥያቄ አነሳሁላት፡፡ ዋናው ምክንያት የአመለካከት ችግር ነው ትላለች፡፡ ወረዳው ወይም ክፍለ ከተማው ስራ ያልጀመሩ ኢንተርፕራይዞች ላይ በተደጋጋሚ ጊዜ ማስታወቂያ ከማውጣት የዘለለ እርምጃ ቢወስድ እንዲህ አይሆንም ነበር ባይ ናት፡፡
በህንፃው 3ኛ ፎቅ ላይ የልብስ ሰፊት ስራውን የጀመረው አብዱልሀዲድ ኑር ሁሴን የቤተልሄምን ሀሳብ ያጠናክራል፡፡ ህንፃው ምንም የገበያ ችግር የለበትም የሚለው ወጣቱ ዋናው ችግር ሲለምድ እንመጣለን እያሉ፤ ቦታ ወስደው የቀሩ አካላት በቦታቸው ካለመገኘት የመነጨ ነው ይላል፡፡
የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ልማት ዘርፍ ከ1996 ዓ.ም ጀምሮ ድህነትንና ስራ አጥነትን ትርጉም ባለው መልኩ ታሪክ ለማድረግና ወደ ኢንዱስትሪያላይዜሽን ለሚደረገው ኢኮኖሚያዊ ሽግግር ፅኑ መሰረት የሚጥል መሆኑ ታምኖበት በመንግስት በኩል ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶት ርብርብ ቢደረግም እንደ ወረዳ 6ቱ ሁሉ የተወሰኑ ማሳያዎችና ማምረቻዎች የሚጠበቅባቸውን ያህል አገልግሎት እየሰጡ አይደሉም፡፡ ከአመታት በፊት ተገንብተው፤ መሰረተ ልማት ተሟልቶላቸው በጣት የሚቆጠሩ ኢንተርፕራይዞችን ብቻ ታቅፈው የተቀመጡ ህንፃዎች ብዙ ናቸው፡፡
የዛኑ ያህልም የነበረባቸውን ችግር ቀርፈው የተሻለ ውጤት ማስመዝገብና ተስፋ ሰጪ ውጤት ማምጣት የቻሉ በርካቶች ናቸው፡፡ ለዚህ አንዱ ማሳያ የሚሆነው በተለምዶ ቤቴል ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ወረዳ 7 ቤተል ሆስፒታል ጎን የሚገኘው ባላ 4 ፎቅ ማሳያ ህንፃ ነው፡፡ ወደ ህንፃው ስናመራ ምሳ ሰአት ገደማ ነበር፡፡ ተደራጅተው ምግብ የሚሸጡ አንቀሳቃሾች ለአፋታም ቢሆን ቆመው አይታዩም”” ደንበኞቻቸውን ያስተናግዳሉ፤ በችርቻሮ ንግድ፣ በደረቅ ምግብና ባልትና በአትክልት ፍራፍሬ ንግድ የተሰማሩትም እንዲሁ፡፡ ከወራት በፊት ከነበረው ዝምታ እየተላቀቁ ይመስላል፡፡ የህንፃው አንደኛና ሁለተኛ ፎቅ ቦታዎች የተሻለ እንቅስቃሴ ይታይባቸው ጀምሯል፡፡ ሙቀትና እንቅስቃሴው ግን የህንፃው ደረጃ እየጨመረ በሄደ ቁጥር ይቀንሳል”” እዚህም ወደ ስራ ያልጋቡ ክፍሎች አይተናል”” ከዚህ ቀደም የመብራትና የውሃ ችግር የነበረበት ህንፃ ዛሬ ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ የመሰረተ ልማት ችግሮቹ ተቀርፈውለታል፡፡ ሆኖም ዛሬም ለሁለት አመት ያህል የተዘጉ ግማሽ ኪሎ በሶ፤ በርሬ አስቀምጠው የውሃ ሽታ የሆኑ ኢንተርፕራይዞችን በዚህም ህንፃ ላይ መመልከት ቀላል ነው፡፡
አለምነሽ ወንድሙ በዚህ ህንፃ በጥቃቅን ተደራጅታ ቦታ ያገኘችው ከ2 አመት በፊት ነው”” አሁን ላይ ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ስራዋን በተሳካ መንገድ ጀምራለች፡፡ እንደሌሎቹ ሁሉ አለምነሽም ትልቁ ችግር የኢንተርፕራይዞቹ ነው ባይ ናት፡፡ የግለሰብ ቤት ተከራይተው ቢያዩት ኖሮ እንደወርቅ ይንከባከቡት ነበር ትላለች፡፡
“ከዚህ ቀደም ስራ ጀምረው አሁን የቀሩት አንቀሳቃሾች የውጭ ሀገር ምርት የመሸጥ ዝንባሌ ነው የነበራቸውም” ትላለች፡፡ በርግጥ መጀመሪያ ሙሉ በሙሉ የተሟላ መረጃ ሳይዙ ወደስራ እንደገቡም አልሸሸገችም፡፡ ህንፃው የተገነባው የጥቃቅንና አነስተኛ አንቀሳቃሾችን ምርት ለመሸጥ ነበር የምትለው አለምነሽ ህንፃው ከተገነባበት አላማ ጋር ለሚፃረር ተግባር መዋል የለበትም፤ በሀገር ውስጥ የጥቃቅንና አነስተኛ ምርት እንዲተካ ሲነገራቸውም አያዋጣንም ብለው መቅረታቸውን ትናገራለች፡፡ ህንፃው ወደ ውስጥ የገባ ቢሆንም በባዛሮች ላይ የመሳተፍ እድል ስላለን የገበያ ችግራችንን እንቀርፋለን በባዛር ያገኘናቸው ገዢዎች እዚህ ድረስ መምጣት ጀምረዋል በማለት ተጨማሪ ሀሳብ ሰጥታናለች፡፡
የወረዳው የማዕከላት አቅርቦት ባለሙያ የሆኑት አቶ ዓለሙ ነብዬ በበኩላቸው “ህንፃው ባለአራት ፎቅ መሆኑ ችግር ሆኖብናል፤ ወደ ላይ ወጥተን መስራት አንችልም፡፡ ገበያ አናገኝም” የሚል ተደጋጋሚ ቅሬታ በኢንተርፕራይዞቹ እንደሚነሳ ነው የገለፁት፡፡ በዚህም ለ198 ኢንተርፕራይዞች ታስቦ የተሰራው ህንፃ ላይ 62 ኢንተርፕራይዞች ብቻ እየሰሩበት ይገኛሉ፡፡ ችግሩን ይዘን አንቀጥልም የሚሉት ሃላፊው ከአመት በላይ ስራ ያልጀመሩ ኢንተርፕራይዞችን ውል በመሰረዝ በቅርቡ ተደራጅተው ስልጠና እየወሰዱ ላሉ የቴክኒክና ዩኒቨርስቲ ተመራቂዎች ለማስተላለፍ በዝግጅት ላይ መሆናቸውን ገልፀውልናል፡፡
በቀጣይም ስራ ከጀመሩ ኢንተርፕራይዞች ጋር በመሆንና ኮሚቴ በማዋቀር የህንፃውን የገበያ እንቅስቃሴ የበለጠ ውጤታማ ለማድረግ ከወረዳው ጽ/ቤት ጋር የሚሰራ ኮሚቴ በማዋቀር የተሻለ ስራ ለመስራት በሂደት ላይ መሆናቸውን ነግረውናል፡፡
ቀጣዩ ጉዞአችንን ያደረግነው በዛው በኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ 12 ነው፡፡ 18 ማዞሪያ አካባቢ የሚገኘው ይህ ባለ 4 ፎቅ ማሳያና መሸጫ ላይ ከዚህ ቀደም የነበሩ ችግሮች በምን መልኩ ተፈቱ የሚለውን መመልከት ቀጥለናል፡፡ በዚህ ህንፃ ከዚህ ቀደም የነበረው አይነት ድባብ አይታይም፡፡ በአንፃሩም ቢሆን የተሻለ ቁጥር ያላቸው በምግብ፣ በባልትና፣ በህትመት፣ በቆዳና የቆዳ ውጤቶች፣ በእንጨት ስራ ውጤቶች የተሰማሩ አንቀሳቃሾች ይታያሉ፡፡ ሌላ ለገበያ ምቹ የሆነ ተጨማሪ በርም ተሰርቶለታል”” ከዚህ ቀደም የነበረውም የውሃና የመብራት ችግር ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ተቀርፏል፡፡ ነገር ግን እንደሌሎቹ ማሳያና መሸጫ ህንፃዎች ሁሉ በዚህም ህንፃ ከ3ኛ ፎቅ በኋላ ተደራጅቶ ስራ የጀመረ ኢንተርፕራይዝ አንቀሳቃሾች ማየት ዘበት ነው”” የንግድ ፍቃዱን ያንጠለጠለ የተወሰኑ ምርቶችን የደረደረ ብቻ ነው የሚመለከቱት፡፡
በቅርቡ ስራ ከጀመሩ አንቀሳቃሾች መካከል አንዱ አለሙ ታደሰ ነው፡፡ በኤሌክትሮኒክስ ሙያ ዘርፍ በዊንጌት ስልጠና ተሰጥቶት ነው ወደዚህ ህንፃ የመጣው፡፡ “ከዚህ በፊት የነበረብን የመብራትና የውሃ ችግር ተቀርፏል” የሚለው ወጣቱ እንደ ችግር የሚያነሳው ወረዳውንም ሆነ ክፍለ ከተማውን ቦታ የወሰዱ ኢንተርፕራይዞችን ስራ አስጀምሩልን ብለን በተደጋጋሚ ብንጠይቅም አጥጋቢ ምላሽ አላገኘንም ይላል፡፡ በዚህም ምክንያት ከ3ኛ ፎቅ በኋላ ባዶውን ሊቀር ችሏል ነው ያለው፡፡ በስራ እንቅስቃሴያቸውም ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደሩን ነው በምሬት የተናገረው፡፡
በወረዳ 12 የአንድ ማዕከል የኢንተርፕራይዞች ልማት ዋና ተወካይ የሆኑት አቶ ገላና ቶላ ቦታ ከወሰዱ 41 ኢንተርፕራይዞች መካከል ስራ የጀመሩት ከ20 በታች ናቸው ይላሉ፡፡ የመብራትና የውሃ ችግሩን ከክፍለ ከተማው ጋር ብንቀርፍም እስከ አሁን ሙሉ በሙሉ ስራ መጀመር አልቻሉም ነው ያሉት፡፡ በቀጣይም ውል ተዋውለው ስራ ያልጀመሩ ኢንተርፕራይዞችን ፍቃድ ለመሰረዝ የመጨረሻ ማስታወቂያ አውጥተናል ነው ያሉት፡፡
የኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ የጥቃቅንና አነሰተኛ ኢንተርፕራይዞች ልማት ዋና የስራ ሂደት አስተባባሪ የሆኑት አቶ አሸናፊ ከበደ በበኩላቸው ችግሩን የመለየት ስራ ሰርተናል ጥናትም አካሄደናል ይላሉ፡፡ በጥናትም የህንፃዎቹ ለገበያ ያለመመቸት ችግርንም ለይተናል ነው ያሉት፡፡ ለዚህም ከ4ኛ ፎቅ ጀምሮ ያሉትን ወደታች የማሸጋሸግ ስራ ሰርተናል ነው ያሉት፡፡ ከ1ኛ ፎቅ ጀምሮ ያሉትንም ማምረቻ ለማድረግ መታሰቡን ነው የገለፁት ለዚህም የከተማውን የጥቃቅንና አነስተኛ ቢሮ ጠይቀን ምላሽ እየጠበቅን ነው ብለዋል፡፡ በወረዳ ስድስት ብቻ ለሁለት አመታት ስራ ባልጀመሩ 36 ኢንተርፕራይዞች ላይ ውል አቋርጠናል ያሉት አቶ አሸናፊ ብዙ ስራ አጥ ያለበት ክፍለ ከተማ ስላለን ለሌላ እናስተላልፋለን ነው ያሉት፡፡ ለዚህም በቅርቡ ከዩኒቨርስቲና ቴክኒክና ሙያ የተመረቁ 457 ሰልጣኞችን በጄነራል ዊንጌት ማሰልጠን ጀምረዋል፡፡ ስልጠናቸውን ከጨረሱ በኋላም እንዲገቡ ይደረጋል፡፡
በርግጥ ከዚህ ቀደም በተለያዩ የጋዜጣችን እትሞች ላይ ስናነሳቸው ከነበሩ ችግሮች በአንፃራዊነት መላቀቅ የቻሉ እና ከዚህ ቀደም የውሻ ማደሪያ ሆኑ ሼዶችን፤ ከተዘጉ አመታት ያስቆጠሩ ህንፃዎችን ወደታለመላቸው አላማ ያስገቡ ክፍለ ከተማች አሉ”” ለአብነት በጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 8 ፌስታሎጂ ቅጥር ግቢ ውስጥ ያሉ ሼዶችና ከመለስ ፓርክ ፊት ለፊት የሚገኘው የአዲሱ ገበያ የደረቅ ምግብ ማቀነባበሪያን ማንሳት ይቻላል፡፡ 6 ባለ ጂ 4 ህንፃዎችን የያዙ 6 ህንፃዎች የሚገኙበት የፌስታሎጂ ቅጥር ግቢ ተዘግተው የነበሩ ህንፃዎች ዛሬ ነገን የተሻለ ለማድረግ የሚጥሩ ባለራዕይ አንቀሳቃሾች ደፋ ቀና እያሉበት ነው፡፡ እንደ ክፍለ ከተማው የማዕከላት አስተደደር ኬዝ ቲም አስተባባሪ አቶ ታከለ አላኔ ገለፃ ክፍለ ከተማው ችግሮችን ለመቅረፍ በክፍለ ከተማው ካሉ 10 ወረዳዎች ከሚገኙ ስራ አጦች ጋር ውይይት አድርጓል፡፡ ባለፉት 9 ወራት ጊዜ ውስጥም ለ240 ኢንተርፕራይዞች ቦታ ለመስጠት አቅደው ለ260 ኢንተርፕራይዞች ቦታ ሰጥተዋል፡፡ 19 ማህበራት ከአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ መጥተው በልብስ በቆዳ በሹራብ ስራ ጀምረዋል፡፡
የጉለሌ በጎ ጅምር በዚህ ብቻ አያበቃም በአንድ ወቅት የእህል ማስጫ፣ የእንስሳት መዋያና መፀዳጃ፣ ሆኖ የነበረውን የቀለበት መንገድ የደረቅ

ምግብ ማቀነባበሪ ህንፃ ገፅታ ሙሉ በሙሉ ቀይሯል፡፡ የራሱ ጥበቃ ተቀጥሮለታል፡፡ ከ10ሩም ወረዳዎች ለተደራጁ ለ180 አንቀሳቃሾች ሚያዚያ 11/2008 ዓ.ም በእጣ ሸንሽኖ አስተላልፏል፡፡ የውሃና የመብራት አቅርቦቱንም አሟልቷል፡፡ የመስመር ዝርጋታውና የመብራት ቆጣሪ በማስገባት ስራው ተጠናቋል፡፡
የጉለሌ ጥቃቅንና አነስተኛ ልማት ጽ/ቤት በአጠቃላይ የተሻለ የስኬት ምዕራፍ ላይ ቢገኝም አሁንም ቀሪ ስራዎች አሉት፡፡ በየህንፃዎቹ ላይ ያሉ ክፍት ቦታዎች አፋጣኝ እልባት ያሻቸዋል፡፡ የህንፃዎቹ ደህንነትና አያያዝም ቢሆን እንዲሁ በቀላሉ መታለፍ የለበትም፡፡ በአንዳንድ ኢንተርፕራይዞች ላይ የሚታየውን ህንፃውን የሌላ አካል አድርጎ የማየት ዝንባሌ የሚቀይር የአመለካከት ግንባታ መስራት ይገባል፡፡ ይሁን እንጂ ተመሳሳይ ግብአትና አንድ አይነት አሰራር ተዘርግቶ እያለ በቁርጠኛ አመራር ክፍተት በኮልፌ ቀራኒዮ በርካታ ሼዶች ላይ የሚታይ ችግር ይስተዋላል፡፡ ጉለሌዎች ግን በርቱ የሚያሰኝ ደረጃ ላይ ይገኛሉ፡፡
ባለፉት አስር አመታት በመዲናችን አዲስ አበባ ከ27 ሺህ የሚበልጡ ኢንተርፕራይዞች በአምስት እድገት ተኮር ዘርፎች (በማኑፋክቸሪግ፣ በኮንስትራክሽን፣ በአገልግሎት በንግድና በከተማ ግብርና) ተደራጅተው በመስራት ላይ ናቸው፡፡ የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ልማት ቢሮና በስሩ ያሉ መዋቅሮች ለኢንተርፕራይዞች ስልጠና በመስጠት የብድር አገልግሎት በማመቻቸት የመስሪያ ቦታ በአነስተኛ ኪራይ በማስተላለፍና የገበያ ትስስር በመፍጠር ድጋፍና ክትትል በማድረጋቸው ብዙዎቹ አንቀሳቃሾች ሀብት አፍርተዋል፡፡ በየአመቱ 4 ቢሊዮን ብር ያህል የገበያ ትስስር ይፈጠርላቸዋል፡፡ በዘርፍ ልማትም አበረታች ውጤት ተመዝግቧል፡፡ በአንዳንድ ወረዳዎችና ክፍለ ከተሞች ላይ የሚታዩ ክፍተቶችን ሳይታረሙ ይህን ያህል ውጤት ማስመዝገብ መቻሉ ይበል የሚያሰኝ ነው፡፡ ክፍተቶቹ ቢታረሙ ምን ያህል የበለጠ ውጤት ማስመዝገብ ይቻል እንደነበረ ያሳዩና ቁጭት ውስጥ የከተቱን ናቸው፡፡
በሼዶች ማምረቻና መሸጫ ህንፃዎች ላይ ያለውን የውጤታማነት ችግር በተደጋጋሚ ፅፈናል፡፡ ክፍተቶች አሳይተናል፡፡ መፍትሄዎች ጠቁመናል፡፡ ዛሬም በየወረዳውና ክፍለ ከተማ አመራር የሚሰጠው ምክንያት የእናቴ መቀነት አደናቀፈኝ ነው፡፡ ሼዶቹና ህንፃዎቹ ወደ ስራ አለመግባታቸው በየግምገማው ምክንያት ሆኖ ሲቀርብ የነበረው የውሃና የመብራት ችግር ሲፈታ አሁንም ምክንያት መደርደር ቀጥሏል፡፡ አሁን ደግሞ ሄዶ ሄዶ “አንቀሳቃሾች ፍላጎት ስለሌላቸው” የሚል የአመራርነት ሚናን የዘነጋ አስገራሚ አስተያየት እየተሰጠ ነው፡፡
አንቀሳቃሾች ወደ ስራ እንዲገቡ በአግባቡ የመለየት፣ አስተሳሰብ የመቀየር ጉዳይ የአመራር ሚና መሆኑን የዘነጋ አመራር ብቻ ነው ይህንን ሰበብ ማቅረብ ያለበት፡፡ በነገራችን ላይ ሼዶችንና ህንፃዎች አለአግባብ አሳልፈው የሰጡ አመራሮችና ፈፃሚዎች እስከ ማሰናበት የሚደርስ እርምጃ ሲወስድ እናያለን፡፡ የተገነቡ ሼዶችን ህንፃዎች ማለቂያ በሌለው ሰበብ ለአመታት ጥቅም ላይ እንዳይውሉ እያደረገ ባለው አመራር ተመሳሳይ እርምጃ ግን ሲወስድ አይስተዋልም፡፡ ኪራይ ሰብሳቢነት ብር መስረቅ ብቻ አይደለም፡፡ የመንግስት ንብረትን ለማይገባው አካል አላግባብ አሳልፎ መስጠት ብቻም አይደለም፡፡ መንግስት ከዚህም ከዚያም ብሎ ባሰባሰበው ሃብት የተገነቡ ተቋማትን ለአመታት ተዘግተው እንዲቀመጡ በዚህም የከተማው የልማት አቅም እንዲመክን የሚያደርገው አካል የትኛውም ዓይነት ኪራይ ሰብሳቢነት ከሚፈፅም የተለየ ስላልሆነ ጠንካራ እርምጃ ሊወሰድበት ይገባል፡፡ ይህ መልእክታችን ለማንም አይደለም ለከተማው ድርጅትና አስተዳደር የበላይ አመራር ነው፡፡