Tuesday, 5 May 2015

ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር የሞት ቀጠና ጉዞ፤ የተስፈኞች መቅሰፍት (ህዳሴ ጋዜጣ)


 
መግቢያ

ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር የዓለማችን ቀዳሚ አስከፊ ወንጀል ተብሎ የሚፈረጅ ሆኗል፡፡ በዓለም ኢትዮጵያን ጨምሮ 127 ሃገራት ለከፍተኛ ድንበር ተሻጋሪ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ተጋላጭ መሆናቸውን ነው መረጃዎች የሚጠቁሙት”” በተለይ ምስራቅ እስያ፣ አውሮፓ፣ አሜሪካ፣ መካከለኛው ምስራቅ፣ ማዕከላዊ እስያና አፍሪካ ግንባር ቀደም ተጠቃሾች ናቸው፡፡ ይህ ከ32 ቢሊዮን ዶላር በላይ የሚንቀሳቀስበት ህገወጥ የሰዎች ዝውውር /ድንበር ማቋረጥ/ ለጥቂቶች ሲሳይ ለብዙዎች መቅዘፍት ሆኗል፡፡ ከጦር መሳሪያ ንግድ በመቀጠል ሁለተኛ ደረጃ ይዞ የነበረውን የዕፅ ዝውውር ንግድን በመብለጥ ከፍተኛ የወንጀል ሃብት ማግኛ የሆነው  ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር በተደራጁ ወንበዴዎች የሚፈጸም ወንጀል ነው፡፡ ኢትዮጵያውያንም የዚህ ከሃገርውስጥ ጀምሮ እስከ አለምአቀፍ ትስስር ያለው የዚሁ ወንጀል ሰለባ በመሆን ዜገቿ ለማቴሪያላዊ፣ አካላዊና ስነልቦናዊ ጉዳት ከመዳረግ አልፈው የበረሃ አውሬና የባህር ዓሳ ነባሪ ሲሳይ እየሆኑ ነው፡፡ ወደ ደቡብ አፍሪካ ከሚደረገው ህገወጥ ዝውውር በስተቀር በሁሉም አቅጣጫ ውቅያኖስና ባህር ተሻጋሪ በመሆናቸው በቅጡ እንኳን ስለመሞታቸው ያልተነገረላቸው ዜጎች ቁጥር የት የለሌ ነው፡፡ ህገወጥ ሰዎች አዘዋዋሪዎችና ሌሎች ወንጀለኞች ደግሞ እንደ ሊቢያ ያሉትን ማእከላዊ መንግስት ቀውስ የገባባቸው ሃገሮችን እንደ ምቹ ሁኔታ ይጠቀማሉ፡፡ 

* የሰዎች ዝውውር አለም አቀፋዊ ገጽታ
   የሰዎች ከቦታ ቦታ መዘዋወር የሰው ልጅ መብት ሲሆን ይህ ዝውውር በሁለት መልክ ይፈጸማል፡፡ አንደኛው ሕጋዊ ስርአትን የተከተለ ሲሆን ሌላኛው ህገ-ወጥ በሆነ መንገድ የሚፈጸም ነው፡፡ አለም አቀፍ ህግና ስርአት እስከተከበረ ድረስ የሰዎች ከአንድ አገር ወደ ሌላ አገር መዘዋወር ተፈላጊና ተቀባይነት ያለው ጉዳይ ነው፡፡ በሃገራችንም የሰዎች ከቦታ ቦታ በነፃ መንቀሳቀስ ህገመንግስታዊ ዋስትና ካገኘ ሁለት አስርት ዓመታት ተቆጥሮዋል፡፡
 አሁን ባለንበት ግሎባላይዜሽን ዘመን ለልማትና ብልጽግና አገሮች አለም አቀፋዊ የስራ አገልግሎት ትብብር (International Labour Service Cooperation) ማድረግ እንደሚገባቸው በሁሉም ዘንድ የሚታመንና ተግባራዊም እየተደረገ ያለ እንቅስቃሴ ነው፡፡ይህ አለም አቀፋዊ ትብብርም በሁለት መልክ የሚታይ ነው፡፡አንደኛው የሠው ሀይል ወደ አገሮች መላክን (Labour Exporting) ሲያመላክት ሁለተኛው የሠው ሀይልን ወደ አገር ውስጥ ማስገባትን (Labour Importing) የሚያመላክት ነው፡፡ ሁለቱም የየራሳቸው ፋይዳ አላቸው፡፡
   የሠው ሀይል ወደ ውጭ አገር መላክ የውጭ ምንዛሬ ወደ አገር በማስገባት ረገድ ፣ የስራ  አጥ ችግር ከመፍታት አኳያ፣ የላቀ ቴክኖሎጂና የስራ አመራር እውቀትና ክህሎት ለማሸጋገር እና የአገር ውስጥ ምርት ወደ ውጭ ለመላክ መልካም አጋጣሚ ከመፍጠርና ከማስፋት አኳያ ጠቃሚ ነው፡፡ እንደዚሁም የሠው ሀይል ወደ አገር ውስጥ ማስገባት የሚከሰተውን የሰራተኛ ሀይል ዕጥረት ከመሙላት አንፃር፣ በአገር ውስጥ የሚያጋጥሙትን የቴክኒክ ችግር ከመፍታት እና የምርት ወጪን በመቀነስ በገበያ ተወዳዳሪነትን የሚያጠናክር ይሆናል፡፡ በሌላ በኩል በአለም ኢኮኖሚ ውስጥ ሳይንስና ቴክኖሎጂን በአለም ዙሪያ በማስተላለፍ ፣የየአገሮችን ምርት በማስተዋወቅ ከማስረጽና አለም አቀፍ ንግድን ከማስፋፋት አኳያ ከፍተኛ ጥቅም አለው፡፡
  ከሰዎች ህጋዊ ዝውውር ጋር ተያይዞ ከላይ የተጠቀሰው ልማታዊ አስተዋጽኦ ቢኖረውም በድርጅታችንም የሚደገፍ ቢሆንም በአንፃሩ ህጋዊ ባልሆነ መንገድ /በህገወጥ/ የሚደረግ የሰዎች ዝውውር ሰውን ለተለያዩ ወንጀሎች ይዳርጋል”” በዚህ ህገወጥ ሰለባ የሚሆኑ ሰዎች እስከ ሞት የሚያደርስ አደጋ ያጋጥማቸዋል፡፡ በሃገር መልካም ገፅታም የራሱን አሉታዊ ጥላ ያጠላል፡፡

* የህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ምንነትና ገፅታ
ህገወጥ የሰዎች ዝውውር ሲባል ድንበር ተሻጋሪና በአንዲት ሀገር ውስጥ የሚደረግ ጭምር ነው፡፡ በህገ-ወጥ መንገድ ድንበር ማቋረጥ/Human Smuggling/  ሲባል ሰዎች በህገ-ወጥ መንገድ ማለትም ምንም ዓይነት የዜግነት መብት ወይም ህጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ ሳይኖራቸው የተቀባዩን ሃገር ይሁንታ ሳያገኙ ወይም ወደ ተቀባዩ ሃገር ለመግባት መሟላት ያለባቸውን ቅድመ ሁኔታዎችን ሳያሟሉ ቀጥተኛም ሆነ ቀጥተኛ ባልሆነ መንገድ ወይም ገንዘብና ሌሎች ጥቅሞችን በመፈለግ የአንድን አገር ድንበር ያለፈቃድ በድብቅ አቋርጦ መግባት ማለት ነው፡፡
   ሰዎችን በህገ-ወጥ መንገድ የማዘዋወር አይነተኛ አላማ አንድን ግለሰብ ለብዝበዛ መዳረግ ሲሆን፣ የሰዎች ድንበር ተሸጋሪነት ዋና አላማ ሰዎችን ዜግነት ወደሌላቸው ወይም ህጋዊ ነዋሪ ወደ አልሆኑበት አገር በህገ-ወጥ መንገድ ማስገባት ነው፡፡ ነገር ግን ሁለቱም ድርጊቶች ለጥቅም ሲባል በሰው ልጆች ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች ናቸው፡፡
ህገወጥ ድንበር ማቋረጥ በባህሪው መደበኛ ያልሆነ ፍልሰት/Irregular Migration/ በመሆኑ ይህ ዓይነቱ ፍልሰት ከላኪ፣ ከተቀባይ እና ከመሸጋገሪያ ትራንዚት አገሮች አካሔድ ቁጥጥር ውጭ የሚደረግ የሰዎች እንቅስቃሴ ነው፡፡ ይህ በመሆኑም ተጓዦቹ ከማንኛውም አደጋ ከለላ ውጪ ናቸው፡፡
ጉዞዎቹ እንደየ አካባቢው እና ሁኔታዎች አመችነት ከመደበኛ ትራንስፖርት አገልግልሎት ጀምሮ፣ በሌሊት፣ በበረሃ ሃሩር፣ በባሕር እና በውቅያኖስ ማጓጓዝን፣ ኬላዎችን እና የቁጥጥር ቦታዎችን ተሰውሮ ማለፍን ያካትታል፡፡ እነዚህ ሁሉ ግን በሞት ቀጠና ላይ የሚደረጉ የሞት ጉዞ ናቸው፡፡ ሁሉም አስቸጋሪ ፈተናዎችንና አደጋዎች የመሸከም ግዴታ በስደተኛው እንጂ በአዘዋዋሪዎቹ የሚወድቅ ሃላፊነት አይደለም፡፡
በእነዚህ ተጓዦች የሚደርሰው የብዝበዛው አይነትም እጅግ ዘግናኝ ነው፡፡ ከነዚህ መካከል ወሲባዊ ጥቃት፣ የዝሙት አዳሪነት ስምሪት፣ የጉልበት ሥራ፣ ባርነት፣ ባርነት መሰል ተግባር፣ የግዴታ አገልጋይነት እና የሰውነት አካል ክፍልን ማውጣትና መሸጥን ያጠቃልላል”” እነዚህ ወንጀሎች በሰሃራ በረሃ በየቀኑና በየደቂቃ የሚፈፀሙ ናቸው፡፡ 

* ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር በኢትዮጵያ
 ያለው ገጽታ
   ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ዓለም አቀፋዊ ችግር እንደመሆኑ መጠን ኢትዮጵያ በችግሩ ውስጥ ከሚገኙ ሀገራት ተርታ ትገኛለች”” በተለያዩ ጊዜ የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት በኢትዮጵያ ውስጥ በስፋት ሕፃናት፣ ሴቶችና ወጣቶች ለችግሩ ሰለባ ሆኖዋል እየሆኑም ነው፡፡ ኢትዮጵያ አብዛኛውን ጊዜ በዚህ ችግር ውስጥ እንደመነሻ ሀገር የምትታወቅ ሲሆን አልፎ አልፎም ከሌሎች የአፍሪካ ሃገራት ለሚነሱ ሰለባዎች እንደመተላለፊያ መስመርም ሆና ታገለግላለች፡፡

* የሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ዋና
  ተዋናዩች
የሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ዋና ተዋናዩች ሕገ ወጥ ደላላዎች ናቸው፡፡  በሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ውስጥ ግለሰቦችን ከመመልመል አንስቶ ማጓጓዝን እና በመጨረሻም በብዝበዛም ላይ ቀጥተኛም ይሁን ቀጥተኛ ባልሆነ መንገድ የሚሣተፉና በምልመላ ወቅት የግለሰቦችን ልብ የሀሰት ተስፋና መደለያ በመስጠት የሚያነሳሱ በጉዞ ወቅትም ግለሰቦች በሕገ ወጥ መንገድ የሚጓጓዙበትን መንገድ የማመቻቸትና የማስተላለፍ ሥራ በመሥራት በመጨረሻ ለብዝበዛ ወደ ተፈለገው ቦታ ያደርሣሉ፡፡ ሕገ ወጥ ደላላ የምንላቸው በአራት የሚከፈሉ ሲሆኑ እነሱም የአካባቢ ደላላ፣ አገናኝ ደላላ፣ ተረካቢ ደላላና መንገድ መሪ ደላላ የምንላቸው የተሳሰረ ኔትወርክ ያላቸው ናቸው፡፡

የሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር መነሻ ገፊ ምክንያቶች

ሀ) የአመለካከት ችግር
 በሀገራችን ነባራዊ ሁኔታ ለሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር መባባስ ዋነኛው ችግር የአስተሳሰብ ድህነት ነው፡፡ በሀገራችን ያለውን መልካም አጋጣሚ ከማየት ይልቅ በሆነ አጋጣሚ ከአመታት በፊት ሔደው የተሳከላቸውን ሰዎች ብቻ እንደሞዴል በማየት ሁኔታው በተገላበጠበት ዘመን ሰው ራሱን ለስደት እየዳረገና ለከፋ አደጋ እየተጋለጠ ይገኛል፡፡
የችግሩ ዋነኛ ምንጭም በአካባቢ ያለን መልካም አጋጠሚ ሳያስተውሉ በስደት ያልፍልኛል በማላውቀው ሀገር የተሻለ ነገር ይገጥመኛል ብሎ መመኘት ነው፡፡ ይህ ምኞት ሁለት አደጋ ያስከትላል የመጀመሪያው ያለንን ሀብት እንዳናይ በሀገራችን ሰርተን መለወጥ የምንችልበትን አማራጭ እንዳናማትር አይናችንን ይጋርደናል፡፡ የራሱንና የቤተሰቡን በሃገር ውስጥ ሰርቶና ለፍቶ የቋጠረውን ሃብት ጠራርጎ በመውሰድ በማባከን ወይም የብድር ቀንበር ውስጥ በማስገባት ቤተሰቡን ጭምር ለከፋ የድህነት አደጋ ያጋልጣል፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ጉም አስጨብጦ ህይወትን ለአደጋ ይዳርጋል፡፡ በቅርቡ ያጋጠመው የሊቢያው ዘግናኝ መርዶ የዚህ በቂ ማሳያ ነው፡፡

ለ) ድህነት /የገቢ ማነስ/ እና ስራ አጥነት
ለሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር እንድ መነሻ ምክንያት ከሚጠቀሱት ውስጥ ድህነት/ የገቢ ማነስና ስራ አጥነት ነው የሚል የቆየ መግባባት አለ፡፡ በድህነት ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች ደላሎች በሚሰጡት የሀሰት ተስፋና መደለያ የመሣሳት እድላቸው የሰፋ በመሆኑ ሕገ ወጥ አዘዋዋሪዎች በድህነት ውስጥ የሚኖሩ ሰዎችን ዓላማ አድርገው ይንቀሣቀሣሉ፡፡
 ነገርግን በተለይም ድንበርን በማቋረጥ የሚደረገው ህገወጥ የሰዎች ዝውውር በ10ሺዎች ከዚህም አልፎ እስከ መቶ ሺህ ብር ገንዘብ ለደላሎች የሚከፈልበት መሆኑን ሲታይ/እንግዲህ ተጓዡ ለስንቅና ሌሎች ጉዳዮች የሚያወጣውን ሳይጨምር/ ድሃ ተብለው ሊፈረጁ ይችላሉ ወይ የሚለው ጥያቄ በስፋት እንዲደመጥ አድርጎታል፡፡
አንዳንድ ጊዜም በአገር ውስጥ የተመቻቸ ኑሮ ያላቸውም ቢሆኑም ለዚህ ህገወጥ ድርጊት ሲዳረጉ እና ሰለባ ሲሆኑ ይታያል”” ያም ሆኖ ሃገራችን ድህነትን ለማስወገድ ከፍተኛ ርብርብ እያደረገች ባለችበት ሁኔታ አሁንም ስራአጥነትና ድህነት በመኖሩ ምክንያት የተሻለ  ስራ ፍለጋ በሚል ዜጎች ውጭን እንዲያስቡና ለህገወጥ ድርጊት ተጠቂ እየሆኑ ያሉበት ጉዳይ በመሆኑ ትኩረት ሊሰጥበት የሚገባ ነው፡፡

ሐ) የቤተሰብ እና የጓደኛ ግፊት
አንዳንድ የሕብረተሰብ ክፍሎች በአካባቢያቸው ነዋሪ የነበሩ ዜጐችን ውጭ ሀገር ወጥተው ሰርተው በመመለስ የራሳቸውንና የቤተሰባቸውን ኑሮ ሲያሻሽሉ በመመልከትና ለቤተሰባቸው በሚልኩት የውጭ ምንዛሬ በመማረክ ለሰለባው/ተጎጂው ቅርብ የሆነ የቤተሰብ አባል እና ጓደኛ ሰለባው/ተጎጂው ወደ ውጭ ሀገር ሄዶ እንዲሠራ ጫና በመፍጠር ዜጐችን በሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር መረብ ውስጥ እንደሚከትዋቸውም ጥናቶች ያመላክታሉ፡፡

መ) ሕገ ወጥ ደላሎች የሚሰጡት ሀሰተኛ 
    መረጃና ተስፋ
ሕገ ወጥ ደላሎች በዚህ ድርጊት ውስጥ የሚያገኙት ጥቅም እጅግ በጣም የተጋነነ ከመሆኑ የተነሣ ሰለባዎችን ለመመልመልና ልባቸውን ለማንሣት ከፍተኛ የሆኑ ስልቶችን በመጠቀም ዜጐችን የሀስት ተስፋና መደለያ በመስጠት ዜጐች ወደ ውጭ ሀገር ቢሄዱ ለራሣቸውና ለቤተሰባቸው የሚተርፍ ሀብት ማፍራት እንደሚችሉ፣ የተሻለ ሥራ እና የኑሮ ሁኔታ እንደተመቻቸላቸው ቃል በመግባት የሚጠቀሙበት ሀሰተኛ መረጃና ተስፋ ለሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር የራሱን ድርሻ ይዞ ይገኛል፡፡

ረ) የተሻለ ሕይወት ፍለጋ
ዜጐች አሁን ያሉበትን የኑሮ ሁኔታ ወደ ሌላ ሀገር ቢሄዱ ሊስተካከልና የተሻለ ሊሆን እንደሚችል በማሰብበ በሃገራቸው መካከለኛ ገቢ የሚያገኙ ቢሆኑም የተሻለ የሥራ እንቅስቃሴ እና የኢኮኖሚ አቅም ወዳለበት ሀገር በመጓዝ ከትሩፋቱ ለመቋደስ በማለም በሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ውስጥ ይወድቃሉ፡፡

* ችግሩን ለመግታት የተወሰዱ ወቅታዊ
  እርምጃዎች
 በሀገራችን የሚገኙ ዜጎች ለህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ሰለባ በመሆን በሚፈልጉበት ቦታ ለመድረስ በሚንቀሳቀሱባቸው ቦታዎች ሆነ በተለያዩ ችግሮች ውጣ ውረድ ውስጥ አልፈው በህገ-ወጥ መንገድ ተጉዘው ተስፋ ወደ አደረጉበት አገር ከደረሱ በኃላ  የሚደርስበቸው ስቃይና እንግልት በየጊዘው እየጨመረ በመምጣቱና አሰቃቂ ግፍና በደልን ለመግታት በሀገር ደረጃ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ  የሚመራ አገር አቀፍ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር አስወጋጅ ብሔራዊ ምክር ቤት ተቋቁሟል፡፡ በመላው ሃገሪቱም በተዋረድ ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ተከላካይ ምክር ቤት ተቀቁሟል፡፡ በዚህም ህበረተሰቡ በጉዳዩ ላይ በቂ ግንዛቤ እንዲያገኝ በሃገር ደረጃ ሰፋፊ መድረኮች ተፈጥረው እንዲወያይበትና የመፍትሄው አካል እንዲሆን በየክልሉ ሰፊ  ስራ ሲሰራ ቆይቷል፡፡
 በተደራጀው ግብረ ሀይልም በሀገራቸውም ሆነ ወደ ውጭ ሀገር በህጋዊ ተንቀሳቅሰው መስራት ለሚፈልጉ ዜጎች በመንግስት ቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች በማስገባት በተለያዩ የስራ መስኮች የአጭር ጊዜ ስልጠና መስጠት፣ ከሥልጠና በኋላ በሠለጠኑበት ሙያ በሀገር ውስጥ በመደራጀት ወደ ሥራ መሰማራት የሚፈልጉ ዜጎችን ከስራ ጋር ማስተሳሰር፣ የመስሪያና የመሸጫ ቦታ አቅርቦት ለሚፈልጉ ዜጎች ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመቀናጀት አገልግሎቱን እንዲያገኙ ማድረግ፣ ለስልጠናና መሰል ስራዎች ድጋፍ የሚውል ሐብት ማስገኛ ፕሮጀክቶችን ማዘጋጀትና ሀብት ማፈላለግ ሲሆን በዚህ ረገድ በአዲስ አበባ የተለያዩ ተግባራት ተከናውነዋል፡፡ ለምሳሌ ከአረብ አገር ተመላሾችን በጊዜያዊነት በመንከባከብ እንዲረጋጉ ከማድረግም አልፎ  ለ2 ሺህ 797 ከስደት ተመላሾች የስነ ልቦ፣ የአመለካከትና የክህሎት ስልጠና እንዲያገኙና ወደተለያዩ የስራ መስኮች እንዲሰማሩ ተደርጓል፡፡
ከዚህ ጎን ለጎን በዚህ ትውልድን ለአደጋ በሚዳርግ ተግባር የተሰማሩ ደላሎች ላይ የህግ ማስከበር ስራዎችም ተወስደዋል፡፡ የሚያከናውናቸው ዋና ዋና ተግባራት፡-
የህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር መነሻ፣ መተላለፊያና መዳረሻ ቦታዎችን መለየት ችግራቸውን መሰረት አድርጎ በተመረጡ እና ቁልፍ በሆኑ ቦታዎች የቁጥጥር ስራ ተከናውኗል፡፡ በሀገሪቱ የሚገኙ የውጭ ሀገር የግል ሥራና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች ላይ ክትትልና ቁጥጥር ማድረግ ተጠያቂ እንዲሆኑ ህግን መሰረት አድርጎ ነው እንዲንቀሳቀሱ የማድረግ ስራዎችም ተሰርተዋል፡፡ የህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ተጎጂዎችን የሚመለምሉና የሚያዘዋውሩ ደላላዎችን፣ ተባባሪና ቤት አከራዮችንና አጓጓዦችን መረጃ ማሰባሰብና በመለየት በህግ ተጠያቂ የሚሆኑበትን አሰራር የመፍጠር እርምጃዎችም ሲወሰዱ ቆይቷል፡፡

* ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን
  በመከላከል ረገድ የመዋቅራችን ሚና
የህገ-ወጥ የሰዎች  ዝውውር ችግር  በዋናነት ከአስተሳሰብ የሚመነጭ ችግር በመሆኑ በአገር ሰርቶ መኖር ብሎም መክበር እንደሚቻል ያለማወቅ ወይም ለማወቅ ያለመፈለግ ትልቁን ድርሻ ይወስዳል፡፡ በመሆኑም በህገ-ወጥ መንገድ ወደ ተለያዩ ሀገራት የሚሄዱና የተለያዩ ችግሮች የሚያጋጥማቸው ሴቶችና ወጣቶች ስራ የሌላቸው ብቻ ሳይሆኑ ለህገወጥ ስደት ገፊ ምክንያቶች በሚል ንኡስ ርዕስ እንደጠቃቀስነው ሰዎች ለስደት የሚሄዱት በተለያየ ምክንያት መሆኑን መገንዘብ ይገባል፡፡
ስደትን አማራጭ ያደረጉ ሰዎች ሁሉም ቤሳቤስቲ የሌላቸው ናቸው የሚለው ድምዳሜ የተሳሰተ መሆኑ በዘርፉ የተደረጉ ጥናቶች ያረጋግጣሉ፡፡ በተለያየ የትምህርት ደረጃዎች ተምረው፣ በተለያዩ የመንግስት ስራ ተቀጣሪ የሆኑና ወደ ቢዝነስ ለማሰማራት የሚያስችል የራሳቸውና የቤተሰብ መነሻ ካፒታል ያለቸው ጭምር ሳይቀሩ ተሳታፊ የሆኑበት መሆኑም መዘንጋት የለበትም፡፡
ምንም ይሁን ምን ግን ህገወጥ የሰዎች ዝውውር በማይጨበጡ ህልሞች የተሞላ ሲሆን ህብረተሰቡ እጅግ የሚዘገንን ታሪኮችን ተሸክመው በዕድል ወደ ተነሱበት ሃገር ደርሰው የተሳካላቸውን ብቻ ሳይሆን በአንድ ቀን እስከ 800 ሰዎችም በአንድ ጃልባ ውቅያኖስ ገብተው የሚቀሩበት የመቅዘፍት መንገድ መሆኑን እያጋጠሙ ያሉ እውነታዎችን በማብራራት የድርጅቱ አባላት ትውልድን ልንታደግ ይገባል፡፡  አባላት ህብረተሰቡን በሃገር ዉስጥ ሰርቶ መለወጥ እንደሚቻል በቂ ግንዛቤና ቁርጠኝነት በመያዝ በተለይም ወጣቶችና ሴቶች በደላሎች ሰበካ እንዳይታለሉ ትክክለኛና ወቅታዊ መረጃ ለህብረተሰቡ በመስጠት የራሳቸውን አስተዋጽኦ ማበርከት የሚገባቸው መሆኑን አውቀው መንቀሳቀስና ተግባራዊ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡