ከተወሰኑ አመታት በኋላ ኢንዱስትሪ መር የኢኮኖሚ ስርአት እንደምንከተል እሙን ነው፡፡ ኢንዱስትሪያዊነት
የአንድ ሀገር ህዝብ ሁሉን አቀፍ የህይወት ለውጥ ነው፡፡ በመሆኑም በየጊዜው እየተሻሻለ የሚመጣ ማህበረሰባዊ እድገት እንጂ በአዋጅ
የሚነገር ስርአት አይደለም፡፡ ሁሉንም ነገር በእቅድ ስለምንፈፅም ኢንዱስትሪው የመሪነቱን ቦታ ሙሉ በሙሉ የሚረከብበት ጊዜ በስትራቴጂዎቻችን
መመላከቱ ይታወቃል፡፡
ኢንዱስትሪው መሪ የመሆኑ ሂደት ከነጉድለቱም ቢሆን መንግስት በያዘው አቅጣጫ መሰረት እየሄደ
ይገኛል፡፡ በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ በጨርቃ ጨርቅ፣ ብረታ ብረት፣ እንጨት ስራ ወዘተ ጅምር ለውጦች እየተመዘገቡ ነው፡፡ በገጠርና
በከተማ በፍጥነት እያደገ የሚገኘው የመንገድ አውታር፣ የአገልግሎት ዘርፍ ግስጋሴ፣ መዲናችን ጨምሮ ሌሎች ትናንሽ ከተሞችንም ፈጣን
እድገት እንዲያስመዘግቡና በምርቶቻቸው ላይ እሴት ጨምሮ ወደመላክ የተሸጋገሩ ኢንዱስትሪያሊስቶች ብቅ ብቅ ብለዋል፡፡
በከተሞች በርካታ ዜጎችን የሀብት ባለቤት እያደረገ የሚገኘው ጥቃቅንና አነስተኛ ልማት ኢንተርፕራይዝ
ደግሞ የኢንዱስትሪ ሽግግሩን እያፋጠነው ይገኛል፡፡ ከምንም ተነስተው ራሳቸውን ጠቅመው ለሌሎችም የስራ እድል እየፈጠሩ የሚገኙና
በህዳሴያችንም በየጊዜው ከአንባቢዎቻችን ያስተዋወቅናቸው በርካታ አንቀሳቃሾች ለዚህ ማሳያ ናቸው፡፡ በተስፋ መቁረጥ ስሜት ገና ከጅምሩ
የሚበተኑ አንዳንድ አንቀሳቃሾች ዛሬም ባይጠፋም ዘርፍ ግን በርካታ ሴቶችና ወጣቶች ወደ ሀብት ማማ የሚወጡበት መንገድ መሆኑን ቀጥሏል፡፡
እኛም በአንድ አመት ውስጥ ስኬታማ ስራዎችን በማከናወን በዘርፉ ውጤታማ የሆኑ እንስቶችን የስራ እንቅስቃሴ ቃኝተን ለሌላው ተሞክሯቸውን
እንዲያካፍሉ በዚህ መልኩ ይዘንላችሁ ቀርበናል፡፡
እንስቶቹ የስራ ቦታቸውና መኖሪያቸው በጉለሌ ክፍለ ከተማ በተለምዶ ሽሮ ሜዳ አካባቢ ነው፡፡
በ2007 ዓ.ም በጥቃቅንና አነስተኛ ከመደራጀታቸው በፊት ተባራሪ ስራ የሚሰሩና ከፊሎቹም ያለምንም ስራ የቆዩ ናቸው፡፡ እርስ በእርሳቸው
ይተዋወቁ ስለነበር ቋሚ ሀብት ለማፍራት በጋራ ለመስራት ወሰኑ፡፡ ለዚህም በጥቃቅንና አነስተኛ መደራጀትን ቀዳሚ ምርጫቸው በማድረግ
ዘርፉን ሀ ብለው ተቀላቀሉ፡፡
በ2007 ዓ.ም ሲደራጁም ስምንት እንስቶችና ሁለት ወንዶች በመሆን “ሸዋዬ አልማዝና ጓደኞቻቸው ብረታ ብረት የህብረት
ሽርክና ማህበር” በሚል በጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ አንድ ጥቃቅንና አነስተኛ ጽ/ቤት ስር ተደራጁ፡፡ የስራ ተነሳሽነትና ዝግጁነት
እንጂ እውቀቱ ስላልነበራቸው ሽሮ ሜዳ ቴክኒክና ሙያ ከንድፈ ሀሳብ እስከ ተግባር ስልጠና እንዲያገኙ በማድረጉ አቅም ፈጠረላቸው”” ከመንግስት ባገኙት 42 ሺህ ብር የገንዘብ ብድር ለስራቸው የሚያስፈልጋቸውን
ቁሳቁሶች ማሟላትም ቻሉ፡፡ በብረታ ብረት ስራ የተደራጁት እንስቶች የድምፅ ብክለት እንዳይኖር ታስቦ ይመስላል ከመኖሪያ ሰፈር ወጣ
ያለና ለስራ ምቹ የሆነ ሼድ ለማግኘትም ጊዜ እንዳልፈጀባቸውም የማህበሩ ሰብሳቢ ወይዘሮ ሸዋዬ በርሽ አጫውተውናል፡፡
በተደረገላቸው የቴክኖሎጂ ድጋፍም ተደራራቢ የብረት አልጋዎችን፣ የተለያዩ በሮችንና መስኮቶችን፣ የሽንኩርት መፍጫ ማሽን፣
የኤሌክትሪክ ምድጃዎችን፣ ምጣድና የፍራፍሬ መጭመቂያ ማሽኖችን እንደሚያመርቱና በከተማችን በስፋት ያልተለመደውን የተለያዩ ማሽኖችን
ሞተር ጥገናም በጥራት እየሰሩ እንደሚገኙም በማምረቻ ቦታቸው ላይ ተገኝተን አረጋግጠናል፡፡
የብረታ ብረት ስራን ከአባታቸው እንደወረሱት የሚናገሩት ወይዘሮ ሸዋዬ በተለይም የተለያዩ ማሽኖች ሞተር ሲቃጠሉና ሲበላሹ
በአዲስ መልኩ የመስራቱን ሙያ ተቀብሮ እንዳይቀር በመንግስት የተፈጠረላቸውን ምቹ ሁኔታ ተጠቅመው እንዲሰሩ በማድረጉ አመስግነው
አይጠግቡም፡፡ በልምድና በስልጠና ያዳበሩትን ሙያ ለስራ ባልደረቦቻቸው በማካፈል ተባብረው በመስራት ድህነትን ድል እየነሱ ይገኛሉ፡፡
ከመደራጀታቸው በፊት ቋሚ ስራ እንዳልነበራቸው የሚናገሩት እንስቷ አሁን ላይ ማህበራቸው የተበደረውን ብድር መልሰው ተጨማሪ 80
ሺህ ብር ብድር ማግኘታቸውንና ስራቸውም በተጠቃሚው ዘንድ “በጥቃቅንና አነስተኛ እንደዚህ አይነት እቃ ይመረታል ወይ?” እያስባለ
እንደሚገኝና የዘርፍን ስኬታማነት እያስመሰከረ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡
ህብረተሰቡ በሺዎች ብር አፍስሶ የገዛው ማሽን ሞተር ሲበላሽበት አዲስ ከመግዛት አስጠግኖ እንዲጠቀምበት ማድረጋቸው እንደሚያስደስታቸው
የገለፁት እንስቷ ከጥገና በኋላ የሁለት አመት ዋስትና እንደሚሰጡም ነግረውናል፡፡ በዚህም ደንበኞቻቸውን ይበልጥ ተጠቃሚ ማድረግ
ችለዋል፡፡
ሌላዋ የማህበሩ አባል ወይዘሮ ገነት ጌታቸውም ከመደራጀታቸው በፊት ስራ አልነበራቸው፡፡ አሁን ላይ ግን ከተለያዩ ስልጠናዎችና
ከጓደኞቻቸው በመማር “የተዋጣልኝ ባለሙያ ሆኛለሁ” ይላሉ፡፡ ስራ የሌላቸውና አንዳንዶቹም በሚሰሩት ልክ ተጠቃሚ የማይሆኑ ሴቶች
በየአካባቢው መኖራቸውን የጠቆሙት ወይዘሮዋ ሁሉም ተባብሮ ዘለቄታዊ ተጠቃሚነታቸው እንዲረጋገጥ ሀላፊነቱን ሊወጣ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
በባዛርና ኢግዚቢሽን አውደርዕዮች በመሳተፍ ምርቶታቸውን ለተጠቃሚው እያስተዋወቁ የሚገኙት እንስቶቹ እንደነሱ ተደራጅተው
አልጋዎችንና ሌሎች የእንጨት ስራዎችን ለሚያመርቱ አንቀሳቃሾች የአልጋ ርብራብ በማቅረብ ተሳስረው እንደሚሰሩ ማረጋገጥ ችለናል፡፡
ሌላኛዋ እንስት ወይዘሮ አልማዝ ሙሉጌታ ይባላሉ፡፡ በተመሳሳይ ከመደራጀታቸው በፊት የቤት እመቤትና “ስራ አጥ” እንደነበሩ
ይናገራሉ፡፡ አሁን ላይ ግን እኛም እንዳየናቸው ለወሬም ጊዜ የላቸውም፡፡ ሙሉ ሀሳባቸውንና ትኩረታቸውን በስራቸው ላይ አድርገው
የተለያዩ የብረታ ብረት ምርቶችን በደስታ ሲሰሩ ታዝበናል፡፡ አሁን ላይ የስራ ባለቤት በመሆናቸው ኑሯቸውን በተሻለ ሁኔታ እየመሩ
እንደሚገኙ ይናገራሉ፡፡
የህብረት ሽርክና ማህበሩ ከአባላቱም ባለፈ ለሁለት ሴቶችና ለአንድ ወንድ የስራ እድል ፈጥሯል፡፡ አጠቃላይ ካፒታሉንም
በተደራጁ በአንድ አመት ውስጥ 150 ሺህ ብር አድርሷል፡፡ በዚህም ለሌሎች ዜጎችም የስራ እድል መፍጠር ችሏል፡፡
ወጣት ተመስገን በየነ በማህበሩ ተቀጥሮ መስራት ከጀመረ ስምንት ወር ሆኖታል፡፡ በተመሳሳይ ሙያ ሌላ ቦታ ሲሰራ እንደነበረ
ይናገራል፡፡ በክፍያ ደረጃ ያን ያህል ልዩነት ባይኖረውም “የሚያጠግብ እንጀራ ከምጣዱ ያስታውቃል” ነውና የእንስቶቹ የስራ ጥራትና
የወደፊት አላማ እርሱንም ማርኮት አብሮ እንደሚለወጥ በመተማመን ስራውን በአግባቡ እየሰራ ይገኛል፡፡
በቅርቡም ይህንን ስኬታማነታቸውን ያረጋገጠው ሽሮ ሜዳ ቴክኒክና ሙያ ተቋም ከሚያደርግላቸው የስልጠና ድጋፍ በተጨማሪ
የቴክኖሎጂ ሽግግርም አድርጎላቸዋል፡፡ ተቋሙ ባሉት አሰልጣኞችና ሰልጣኞች የተሰሩ የተለያዩ ችግር ፈቺ የፈጠራስራዎችን ወደ አንቀሳቃሾች
በማሸጋገር እንደነ ሸዋዬና ጓደኞቻቸው የህብረት ሽርክና ማህበር አባላት አይነቶችን ተጠቃሚ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ በቅርቡም ለማህበሩ
አባላት የሊስትሮ ባለሙያውንና ጫማውን የሚያስቦርሸውን አካል ምቾት የሚጠብቅና ለከተማው ውበትም የተሻለ ገፅታ የሚፈጥር የሊስትሮ
ተንቀሳቃሽ ቤት ሞዴል ሰርቶ እንዳሸጋገረላቸው ወይዘሮ ሸዋዬ ነግረውናል፡፡ በቅርቡም ምርቱን በማምረት ለገበያ እንደሚያቀርቡት ያስረዳሉ፡፡
በመንግስት በኩል ከማደራጀት፣ የመስሪያ ቦታና ብድር እንዲሁም ከገበያ ትስስር ባለፈ ቴክኖሎጂ ስለተሸጋገረላቸው ተደስተዋል፡፡
ከጠበቁት በላይ ድጋፍ እየተደረገላቸው እንደሚገኝ የሚናገሩት እንስቶቹ የገበያ ትስስሩ ግን ተጠናክሮ እንዲቀጥልላቸው ጠይቀዋል፡፡
በተለይም በክፍለ ከተማው በእንጨት ውጤቶች፣ በብሎኬትና በሌሎችም ዘርፎች ተደራጅተው ከሚሰሩ አንቀሳቃሾች ጋር የእርስ በእርስ ትውውቅና
ትስስር እንዲፈጥሩ ድጋፍ ቢደረግላቸው የገበያ እጥረቱ እንዳይፈጠር እንደሚያስችል አመላክተዋል፡፡
እኛም የጉለሌ ክፍለ ከተማ ጥቃቅንና አነስተኛ ጽ/ቤት የኢንተርፕራይዞች ልማት ዋና የስራ ሂደት መሪ ከአቶ አብዮት ታደሰ
ጋር ባደረግነው ቆይታ በክፍለ ከተማው 2 ሺህ 476 ኢንተርፕራይዞችና 13 ሺህ 133 አንቀሳቃሾች ይገኛሉ፡፡ ከዚህም ውስጥ 4
ሺህ 450 ሴት አንቀሳቃሾች እንደሚገኙ ገልፀው ከወረዳ እስከ ፌዴራል በሚፈጠሩ ባዛርና ኤግዚቢሽኖች ኢንተርፕራይዞች በስፋት እንዲሳተፉና
ምርቶቻቸውን ከማስተዋወቁ ባለፈ እርስ በእርሳቸው በመተዋወቅ በዘላቂነት አብረው የሚሰሩበት መንገድ መኖሩንና በቀጣይም ተጠናክሮ
እንደሚቀጥል ነግረውናል፡፡
እንስቶቹ በቀጣይ ስራቸውን በኢንዱስትሪ ደረጃ የማሳደግ ህልም አላቸው፡፡ በርካታ ሴቶችን የስራ እድል ተጠቃሚ የማድረገ
ውጥንም ይዘዋል፡፡ ለዚህ ስኬታቸውም የህብረተሰቡና የሚመለከተው ባለድርሻ አካል ድጋፍም እንደማይለያቸው እንተማመናለን፡፡