ለፍትህና እኩልነት የተከፈለ ዋጋ
የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች በወቅቱ
በነበሩት ዴሞክራሲያዊ ድርጅቶች ህወሓትና
ኢህዴን/ብአዴን ኋላም ኦህዴድ ውስጥ በመታቀፍ
ወጣቱ ሲያነሳቸው ከነበሩት ጥያቄዎች የህዝባዊ
መንግስት ምስረታ፣ የእኩል ተጠቃሚነት፣ የብሄርና
የኃይማኖት እኩልነት፣ የፍትህና ዴሞክራሲ
ጥያቄዎችን ለመመለስ በኢህአዴግ ጥላ ስር
ሆነው በፅናት የትጥቅ ትግል አካሂደዋል። በርካታ
መስዋዕትነትም ከፍለዋል።
ብረት አንስተው በትጥቅ ትግሉ ፍልሚያ የተሳተፉ
ታጋዮች ብቻም ሳይሆኑ ንፁሃን የአገራችን
ጭቁን ህዝቦች በደርግ የጦር አውሮፕላኖች
ዘግናኝ በሆነ መልኩ በጋራ የተፈጁባቸው እንደ
ሀውዜን፣ መርሳና በለሳ ያሉ መንደሮች ለፍትህ፣
ለዴሞክራሲና ለብሄር እኩልነት መረጋገጥ ሲባል
የተከፈሉ መራር መስዋዕትነቶችን አጉልተው
አሳይተዋል። በደርግ የአፈና መዋቅር ከመማረክ
ራስን ማጥፋትን የመረጡ ወጣት ታጋዮች በደርጎች
እጅ ወድቀው እንኳ ከቆሙለት ዓላማ ፍንክች
እንዳላሉ አረጋግጠዋል። እንደ ህወሓት ጓዶች
አሞራው (ወልደገሪማ)፣ ቐሺ ገብሩ (ሙሉ
ገብረእግዚያብሄር) እንዲሁም እንደ ኢህዴን/
ብአዴን ጓድ ዘለቀ ደምሴ ያሉ በደርግ የግፍ በትር
የተገደሉ ታጋይ የኢትዮጵያ ወጣቶች የኢህአዴግ
የዓላማ ፅናትና ለህዝቦች ጥቅም ሲባል የተከፈለ
መስዋዕትነት የሁልጊዜም ማነፃፀሪያዎች ናቸው።
ደርግ ሲያደርሰው ከነበረው ጭፍጨፋ ባሻገር
የአገሪቱን ኢኮኖሚ በማዳከም ህዝቡን ለከፋ
ድህነት ዳርጓል።