ደኢህዴንና የብሄር ብሄረሰቦች መኖሪያዋ ደቡብ ኢትዮጵያ
ከተመሰረተ 23 አመቱ የሆነው ደኢህዴን እስከአሁን 8 ድርጅታዊ ጉባኤዎችን አከናውኗል፡፡ አሁንም 9ኛ ድርጅታዊ ጉባኤውን ለማከናወን በዝግጅት ላይ ይገኛል፡፡ ስለሆነም ጉባኤው ለቀጣይ ለውጥና እድገት ወሳኝ የሆኑ የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግር ጉዳዮች አተኩሮ እንዲሰራ በሚያስችሉ ወሳኝ የሆኑ መነሻ ሁኔታዎች ባሉበት ሁኔታ የሚካሄድ ነው፡፡ በተለይም በ7ኛ ድርጅታዊ ጉባኤ ‹‹የዕድገትና ትራንሰፎርሜሽን እቅዱን በማሳካት የኢትዮጵያ ህዳሴ ከማይቀለበሰበት ደረጃ እናደርሳለን›› በሚል መሪ ቃል የተካሄደ እንደነበር ይታወሳል፡፡ በእቅዱም በሁሉም መስኮች ተደማሪ ሳይሆን አሸጋጋሪ ውጤት የሚያመጡ ግቦች በተለጠጠ ሁኔታ በማቀድ ነበር ወደ ተግባር የተገባው”” በዚሁ መሰረትም ባለፉት አመታት የክልሉ ኢኮኖሚ በአማካይ በ10 ነጥብ 4 በመቶ አድጓል፡፡
ስለሆነም የክልሉ የምርት መጠን 62 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ደረጃ የደረሰ ሲሆን 49 በመቶ ድርሻ የነበረው ግብርና አሁንም በኢኮኖሚ እድገቱ የአንበሳ ድርሻ እንዳለው እንገነዘባለን፡፡ በድምርም ኢኮኖሚው ባሳየው እድገት የነፍስ ወከፍ ገቢ 700 ዶላር ይደርሳል ተበሎ ይጠበቃል፡፡
ፈጣን ልማቱ መዋቅራዊ ሽግግርን ከመፍጠር ውስንነት ያለው ቢሆንም እድገቱ የመነጨው አብዛኛው የክልሉ ህዝብ ከተሰማራበት ግብርና ዘርፍ መሆኑን ስንመለከት የእድገቱን ፍትሃዊነትን ያመላክተናል”” በ1997 በክልሉ የድህነት መጠን 39 በመቶ ገደማ የነበረ ሲሆን በ2007 ወደ 22 በመቶ ማሽቆልቆሉ መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡ በተለይም ግብርና የራሱን እድገት እያፋጠነ የሌሎች የኢኮኖሚ ዘርፎች እድገት እንዲያፋጥን የተሰጠውን ተልእኮ በብቃት ተወጥቷል ማለት ይቻላል ይላል ለአባላት ኮንፈረንስ የተዘጋጀ ሰነድ፡፡ የግብርና አማካይ አመታዊ እድገት 8 ነጥብ 7 በመቶ መመዝገቡ የምግብ ሰብሎች ከነበረበት 23 ሚሊዮን ኩንታል ወደ 34 ሚሊዮን የእንሰትና ስራስር ሰብሎች ከ35 ሚሊዮን አመታዊ ምርት ወደ 74 ሚሊዮን ኩንታል ማድረስ መቻሉ የጥረቱን ዋጋ ያሳያል፡፡
የከተማ ልማት
የከተማ ልማት ዋናው ማእከሉ ኢንዱስትሪ የኢንዳስትሪ ቁልፍ ሞተር ደግሞ ጥቃቅንና አነስተኛ በማድረግ በከተሞች የሚታየውን የስራአጥ ቁጥር በመቀነስ በዛው መጠን ድህነትን ለማዳከም ትኩረት ተሰጥቶት ሲሰራ ቆይቷል፡፡ ስለሆነም ባለፉት ሁለት አመታት ብቻ ለ818 ሽህ 262 የስራ እድል በመፍጠር በ5 አመቱ የእድገትና ትራንስፎርመሽን ከተያዘው እቅድ በላይ ማሳካት ተችሏል፡፡ ይህም ሆኖ በተለይ ለቋሚ የስራ እድል በቀጣይ ትኩረት የሚሻ ሆኖ ይታያል፡፡ በተለይም ደግሞ ለኢኮኖሚ ትራንስፎርሜሽን መነሻ የሚሆነው የመካከለኛና ከፍተኛ ኢንዱስትሪ ከማልማት አንፃር ያለው ጉድለት የጉባኤው የውይይት ትኩረት ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
መሰረተ ልማት
መንገድ አንድ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚ ማህበረሰብ ለመገንባት ወሳኝ ሚና የሚጫወት መሠረተ ልማት መሆኑ ይታወቃል፡፡ ባለፉ ስርዓቶች ሰፊ የብሄ ብሄረሰቦች ስብጥር የሚታይበት ክልሉ በአጠቃላይ ልማት እንዲሁም በመሰረተ ልማት የተዘነጋና እርስ በራሱ የቅርብ ሩቅ ሆኖ መቆየቱም ይታወቃል፡፡
በደኢህዴን መሪነት የክልሉ አስተዳደርና የፌደራል መንግስት ይህንን የቆየ መጥፎ ገፅታ ለመቀየር ትኩረት ሰጥተው እየሰሩ ይገኛል፡፡ በዚህም መሰረት በክልሉና በፌደራልመንግስት በተከናወነ ስራ 9488 ኪሎ ሜትር አስፋልትና ጠጠር መንገዶች ተገንብቷል”” ከዚህም በተጨማሪ 716 ቀበሌዎችን ከወረዳዎችና ዋና መንገድ ማስተሳሰር ያስቻለ የ2840 ኪሎሜትር መንገድም ተገንብቷል፡፡ ከዚህም ሌላ በክልሉ የንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ለማሻሻል 6364 ተቋማት በመገንባት በጠቅላላ በገጠርና በከተማ 6 ሚሊዮን 557 ሺህ 798 ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል፡፡ በዚህም የክልሉ የንፁህ መጠጥ ውሃ ሽፋን 61 በመቶ መድረሱ መረጃዎች ያሳያሉ”” ይህ መረጃ እስከ 2006 የነበረው ብቻ መሆኑ አንባቢው ከግንዛቤ ሊወስድ ይገባል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የቴሌኮሙኒኬሽን አገልግሎት በተለይም የሞባይል ተጠቃሚ 5 ነጥብ 6 ሚሊዮን ደርሷል፡፡
በድርጅቱ መሰረታዊ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት መስመር እምነት መሰረት በእያንዳንዱ ልማት ፍትሃዊ ስርጭቱን መርህ የተከተለ መሆኑን መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡ ለምሳሌ ባለፉት አመታት የገጠር ቴሌኮም ፕሮግራም በመዘርጋት 3871 ቀበሌዎች የሽቦ አልባ ስልክ ተጠቃሚ ተደርጓል፡፡ ይህ የቴሌኮም ፕሮግራም ለአርሶ አደሩና አርብቶ አደሩ ከሚሰጠው ማህበራዊ አገልግሎት ባለፈ ትልቅ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳም አለው፡፡ ይህም ሆኖ እስከአሁን በመሰረተ ልማት የተሰሩ ስራዎች የክልሉ ህዝብ ለዘመናት የነበረበትን የኢኮኖሚና ማህበራዊ መገለልና ጉዳትን የሰበረ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ ድርጅቱና የክልሉ መንግስት ከዚህ በላይ ስራ በቀጣይ እንደሚጠብቃቸው ሳይታለም የተፈታ ነው”” ጉባኤውም በዚህ ዙሪያ ተጨማሪ አቅጣጫዎች ያስተላልፋል ብለን እንጠብቃለን፡፡
ማጠቃለያ
ድርጅታችን ኢህአዴግ ሰኬታማ ድርጅት መሆኑ ብዙዎች የሚመሰክሩት እውነታ ነው፡፡ የድርጅታችን ስኬት በዋነኝነት የሚለካው ድርጅቱ በነደፋቸው እቅዶች በህዝብና በሃገር በመጡት ጥቅምና ፋይዳ ነው፡፡ ከፍ ብለን በወፍ በረር በቃኘነው የክልሎች የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት ስኬቶች ከተከናወኑ ዘርፈ ብዙ ስራዎች እጅግ ጥቂቱን መሆኑ መታወቅ ይኖርበታል፡፡
በተከታታይ የተመዘገበው ባለሁለት አሃዝ እድገት፣ እንዲሁም ሃገሪቱ በአለም ፈጣን ኢኮኖሚ እያስመዘገቡ ከሚገኙ 10 ሃገሮች አንዷ ሆና ከ10 ዓመታት በላይ መቀጠልዋ፣ እጅግ አለመረጋጋት በሚታይበት የአፍሪካ ቀንድ የሰላም ደሴት የመሆኗ ሚስጢር ፣ በአህጉሪቱ ብቻ ሳይሆን በአለም አቀፍ የተጐናፀፈችው ከበሬታና ተአማኒነት ከድርጅታችን ህዝባዊ መተክሎችና ፕሮግራሞች የመነጩ ናቸው፡፡
ድርጅታችን እስከአሁን ባስመዘገበው ስኬት ደግሞ የሃገራችን ህዝቦች በ5ኛው ሃገራዊ ምርጫ ከመቼውም ጊዜ የላቀ ድምፃቸውን በመስጠት ይሁንታቸውን ሰጥተውታል”” በእነዚህ ድሎች በመታጀብ የሚካሄደው የድርጅታችን ጉባኤ ለቀጣይም የህዝቡን አደራ በላቀ እድገትና ትራንስፎርሜሽን ለማሳካት ታሪካዊ ውሳኔዎች እንደሚወስን ይጠበቃል፡፡