Friday, 21 August 2015

ድልና ድምቀት ለብሄራዊ ድርጅቶቻችንና ለኢህአዴግ ጉባኤ!!


ብሄራዊ ድርጅቶቻችንና የጋራ ግንባራችን የሆነው የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር/ኢህአዴግ/ ከነሐሴ አጋማሽ ጀምረው መደበኛ ድርጅታዊ ጉባኤያቸውን ያካሂዳሉ፡፡ የድርጅታችን ጉባኤ ከውስጠ ድርጅት ጉዳዮች ባለፈ በምርጫ ስልጣን ይዞ መንግስትን እንደሚመራ ድርጅት መጠን ትላልቅ ሃገራዊ የኢኮኖሚና ማህበራዊ ልማት፣ ፖለቲካዊና ዲፕሎማሲያዊ ጉዳዮች የሚመከሩበትና ለቀጣይ አመታት አቅጣጫዎች የሚቀመጡበት ውሳኔዎች የሚወሰኑበት በመሆኑ ትልቅ ሃገራዊ ክንውን ተደርጎ ይወሰዳል፡፡
እስከ አሁን በተደረጉት ጉባኤዎች የተወሰኑ ውሳኔዎች በኢትዮጵያ ህዳሴ ጉዞ የየራሳቸው አሻራ ያሳረፉ ታሪካዊ ክንዋኔዎች በመሆናቸውና የድርጅታችን ጉባኤዎች ለይስሙላና የግዜ ሰሌዳውን ጠብቆ መካሄድ ስላለባቸው ብቻ የሚካሄዱ ሳይሆኑ እንደድርጅትና እንደሃገር ከአንድ ምዕራፍ ወደ ሌላ ምዕራፍ ለመሸጋገር የሚያስችሉ መሆናቸው እስከአሁን ከተካሄዱት ጉባኤዎች መላው ህዝባችን የድርጅታችንና የሃገራችን ወዳጆችና ከድርጅታችን የተለየ አቋም ያላቸው ሃይሎች ጭምር የሚገነዘቡት ሐቅ ነው፡፡
ስለሆነም በነሐሴ ወር ‹‹ህዝባዊ አደራን በላቀ እድገትና ትራንስፎርሜሽን›› በሚል መሪ ቃል የሚከናወነው የኢህአዴግ ጉባኤ እንዳለፉት ጉባኤዎቻችን ሰፋፊ ሃገራዊ እቅዶችንና የሃገራችንን የልማትና የዴሞክራሲያዊ ስርአት ተጨማሪ ድልና መደላድል የሚፈጥሩ ውሳኔዎች እንደሚያስተላልፍ ይጠበቃል፡፡
 የብሄራዊ ድርጅቶቻችንም ሆኑ የኢህአዴግ ጉባኤ ባለፉት አምስት የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዓመታት የመድረኩን ተልእኮ ለመፈፀም ድርጅታዊ የአመራር አቅም በማጠናከር፣ የህዝብ ተሳትፎ ከመቼውም በተለየ በማደራጀት፣ እንዲሁም አገልግሎት የሚሰጠው ሲቪልሰርቪሱም የተልእኮውን ፖለቲካዊ አላማና ግብ ተገንዝቦ እንዲተጋ አደራጅቶ በመምራት የልማትና የመልካም አስተዳደር እንዲሁም የምርጫ ተግባራትን ለማሳካት ሰፊ ጥረት የተደረገበትና በሁሉም እቅዶች ስኬቶች በተመዘገቡበት ወቅት የሚካሄዱ በመሆናቸው የድል ጉባኤዎች ናቸው፡፡
እንደ ግንባር በሃገር ደረጃ እንዲሁም ብሄራዊ ድርጅቶቻችን በየክልሉ በእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዘመኑ የታቀዱና የተጣሉ ግቦችን ለማሳካት በተደረገው ርብርብ አብዛኛዎቹ ተግባራት በግቡና ከግቡ በሚቀራረብ ደረጃ መሳካታቸው የሁለተኛው 5 አመት የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅዶችን በተለጠጠ ግብ ለማቀድና እንደሃገርና እንደድርጅት የይቻላል በራስ መተማመናችን ከመቸውም ጊዜ በላይ በላቀ ደረጀ በሚገኝበት ወቅት ሆነን የምናካሂደው ጉባኤ ነው፡፡፡
የግቦቹ ዋና ማሳኪያ መሳሪያ የተደራጀ የድርጅት፣ የመንግስትና የህዝብ አቅም መሆኑ በተያዘው አቅጣጫ መሰረት ባለፉት ሁለት አመታት የሰራዊት ግንባታ ዋናው የአቅም ግንባታ ማእከል በማድረግ በተሰራው ስራ የሰራዊቱ ፈፃሚ አቅሞች እቅዶችን በማሳካት ረገድ የነበራቸው ብቃት እንደድርጅት መመዘን በሚቻልበት ወቅት ላይ ሆነን  የምናካሂደው ጉባኤ ነው፡፡
የዘንድሮ ጉባኤ የዛሬ አምስት አመት የመጀመሪያው አምስት አመት የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ሲታቀድ እቅዱን በማቀድና እቅዱ በድርጅቱና በህዝብ ዘንድ ጠንካራ መግባባትና መነሳሳት እንዲፈጠር ወሳኝ ድርሻ የነበረው ታላቁ መሪያችን መለስ ዜናዊ በሌለበት ነገርግን በተሰዋበት ወቅት የድርጅታችን አመራር የተፈጠረውን የአመራር ክፍተት መሙላት የሚያስችል የአመራር ስልት በመቀየስ ጠቅላላ የድርጅቱ አባላት፣ የመንግስት መዋቅሩና ህዝቡን አደራጅቶ በማነቃነቅ የመለስን ራእይ ማሳካት እንደሚቻል በተረጋገጥንበት ወቅት የሚካሄድ መሆኑም ልዩ ያደርገዋል፡፡
ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ በሰራዊት ግንባታ ከክልል ክልል፣ በገጠርና በከተማ፣ በሴክተሮችና በህዝብ አደረጃጀቶች እንዲሁም በድርጅቱ ውስጥም ሰፊ የሆነ አለመመጣጠን እንደሚታይበት ይታወቃል፡፡ ከህዝብ ተጠቃሚነት አንፃርም በአለማችን እየተገነቡ ካሉት ኢኮኖሚዎች በየትኛውም መመዘኛ ሲመዘን ፍትሃዊና የአብዛኛው ህዝብ ተጠቃሚነትና ተሳታፊነት ያረጋገጥንበት እንደነበረ የመጀመሪያው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን አፈፃፀም ያሳያል፡፡ ይህም ሆኖ በዚህ በኩል ያለው ስራ ገና ያልተጠናቀቀና ከአካባቢ አካባቢ የአፈፃፀም ልዩነቶች የሚታይበት መሆኑ አልቀረም፡፡ ስለሆነም በዚህ ዙሪያ የተገኙ ስኬቶችን በመቀመር ጉድለቶችን ማረም የሚያስችሉ አቅጣጫዎች ከጉባኤው ይጠበቃል፡፡
በተሃድሶ ወቅት የስርአታችን አደጋ ኪራይ ሰብሳቢነት መሆኑ እና ይህም ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ መሰረቶች ያሉት መሆኑ በተቀመጠው መሰረት የኪራይ ሰብሳቢነት ፖለቲካል ኢኮኖሚው በልማታዊ ዴሞከራሲያዊ ፖለቲካል ኢኮኖሚ ለመቀየር የሞት ሽረት ትግል ሲካሄድ ቆይቷል”” በአሁኑ ወቅት በሀገራችን ገጠሮች በተገነባው የልማት ሰራዊት የኪራይ ሰብሳቢ ፖለቲካል ኢኮኖሚ ሙሉ በሙሉ የተሸነፈበት ደካማ መሬት ይዞ የሚንገዳገድበት ደረጃ ላይ እንገኛለን፡፡  ይህም ሆኖ አሁንም በገጠርም ጭምር ለኪራይ ሰብሳቢነት ማዳበሪያ የሆኑ የጠባብነትና የትምክህት በሽታዎች ሙሉ በሙሉ ተመምግለው ተወግደዋል የሚባሉበት ደረጃ አልተደረሰም፡፡ ስለሆነም የብሄራዊ ድርጅቶቻችንና የኢህአዴግ ጉባኤ በገጠር ከኪራይ ሰብሳቢነት አስተሳሰብና ተግባር ያልተወገዱ ቅሪቶችን በቀጣይ አምስት አመታት ጨርሰው የሚከስሙበት አቅጣጫ ያስቀምጣል ብለን እንጠብቃለን፡፡
በከተሞቻችን አዲስ አበባን ጨምሮ የነበረው የገነገነ የኪራይ ሰብሳቢ ሃይል የተደራጀ አቅምና ስብስብ የማድረግ አቅሙ እጅግ በተዳከመ ደረጃ ላይ መድረሱ በ2007 በተካሄደው አምስተኛው ሃገራዊ ምርጫ የኪራይ ሰብሳቢ ጠበቃ የሆኑ ፅንፈኛ ፓርቲዎች የተከናነቡት ሽንፈት ማረጋገጫ ነው፡፡ ይህም ሆኖ በከተማ የተገነባው የልማት ሰራዊት በገጠር የተገነባው የልማት ሰራዊት የደረሰበት የአደረጃጀትና የአስተሳሰብ ጥራት አንፃር ሲመዘን ብዙ ጉድለቶች ያሉበት በመሆኑ የኪራይ ሰብሳቢነት ፖለቲካል ኢኮኖሚ በሚፈለገው ደረጃ የተደፈቀበት አይደለም፡፡ በመሆኑም በከተሞች በእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዘመን እንደገጠሩ ሁሉ መዋቅራዊ ለውጥ ለማምጣት መደላድል የሚፈጥሩ የኢኮኖሚ፣የማህበራዊና የዴሞክራሲ ተቋማት ግንባታ የተከናወነ ቢሆንም በዛው ልክ የአስተሳሰብ ለውጥ እንዳይመጣ በመልካም አስተደደር በተለይም በአገልግሎት አሰጣጥ ያለው ጉድለት ከፍተኛ አሉታዊ ሚና ተጫውቷል፡፡
ከገጠር በተገኘው ልምድ ካለ ጠንካራ የድርጅት፣ የመንግስትና የህዝብ የተቀናጀ የልማት ሰራዊት ኪራይ ሰብሳቢነትን መድፈቅና መልካም አስተዳደር ዘላቂነት ባለው ደረጃ ማረጋገጥ አይቻልም፡፡ ስለሆነም የድርጅታችን ጉባኤ በዚህ ረገድ ያለውን ጉድለት በጥልቀት ተወያይቶ የከተማ የልማት ሰራዊት ግንባታ፣ የመልካም አስተዳደር ጉዳይ እንዲሁም የእድገት ፀር በሆነው የኪራይሰብሳቢነት ትግል ላይ እመርታዊ ለውጥ ማምጣት የሚያስችሉ ውሳኔዎችንና አቅጣጫዎችን ያመነጫል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በአጠቃላይ ዘንድሮ የሚካሄደው የድርጅቶቻችን ጉባኤ የድል ጉባኤ ነው፡፡ በኢኮኖሚና ማህበራዊ ልማት ለተመዘገበው ሃገራዊና ክልላዊ እድገት የሚመጥን ድምፅም ህዝቡ በአምስተኛው ሃገራዊ ምርጫ ለድርጅታችን ሰጥቷል፡፡ ነገርግን ህዝቡ ከመቼውም ጊዜ በላቀ ድምፅ ኢህአዴግን መምረጡ እስከአሁን ለሰራቸው ስራዎች እውቅና ብቻ ሳይሆን እስከአሁን በሁሉም ዘርፍ ከተመዘገቡ ድሎች በላይ የላቀ ሃገራዊ እድገት እንዲመዘገብ ብቁ አመራር እንዲሰጠው የሰጠው አደራና ሸክም በመሆኑ የጉባኤው ፋይዳና በጉባኤው የሚተላለፉ ውሳኔዎች በሁሉም ዘንድ በከፍተኛ ትኩረት የሚጠበቅ አድርጎታል፡፡ ለዚህም ነው የጉባኤው መሪ ቃል ‹‹ ህዝባዊ አደራን በላቀ እድገትና ትራንስፎርሜሽን›› እንዲሆን የተመረጠው፡፡ በትክክልም ጉባኤው ህዝባዊ አደራን በላቀ እድገትና ትራንስፎርሜሽን ለመወጣት ድርጅታችን የአመራር ድርጅታዊ ጥንካሬና ዝግጁነት ያለው መሆኑን የሚያረጋግጥበት ጉባኤ ይሆናል፡፡

ድልና ድምቀት ለብሄራዊ ድርጅቶቻችንና ለኢህአዴግ ጉባኤ!!

No comments:

Post a Comment