Friday, 21 August 2015

አመራር አቅማችንን በቀጣይ በማጠናከር የከተማችንን ህዳሴ እናረጋግጥ! ይስሐቅ ግርማይ

አመራር አቅማችንን በቀጣይ በማጠናከር የከተማችንን ህዳሴ እናረጋግጥ!
በከተማችን ስር ሰደው የቆዩትን ድህነትና ኋላ ቀርነት በማስወገድ ልማትና መልካም አስተዳደርን ለማስፈን ርብርብ በመደረግ ላይ ይገኛል፡፡
ይህንኑ ተጨባጭ ለውጥ ለማምጣት የአገራችን ይሁን የከተማችንን መሠረታዊ የህዝብ ጥያቄዎችን የሚመልሱ መስመሮችን፣ ስትራቴጂያዊ እቅዶችና ፖሊሲዎችን በማዘጋጀት በእንቅስቃሴ ላይ ነን”” ምልዓተ ህዝቡን በማንቀሣቀስም በለውጥ ሂደት ላይ እንገኛለን፡፡
ከተማችንን ጨምሮ በሀገር አቀፍ በ5 አመቱ የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዘመን በኢኮኖሚና ማህበራዊ ልማት፣ በዴሞክራሲ ስርአት ግንባታና በመልካም አስተዳደር የተመዘገቡ ስኬቶች ከዚህ በፊት በተለያዩ ሰነዶች የቀረቡና የተወያየንባቸው በመሆኑ እዚህ ላይ መድገም አስፈላጊ አይደለም፡፡
 ነገር ግን አንድ መያዝ ያለበት ሀቅ በሁሉም ዘርፍ ያስመዘገብናቸው ድሎች የህዝቡ ተጠቃሚት ብቻ ሣይሆን የህዝብ ተሳታፊነት የተረጋገጠባቸው እንዲሆኑ ሰፊ የአደረጃጀትና አሰራር ዘርግተን ያከናወናቸው ነበሩ፡፡ ይህም ሆኖ ምንም እንኳን የተደራጀ የህዝብ አቅም አሟጠን ተጠቅመናል ለማለት ባንችልም የከተማችን ነዋሪዎች ከእቅድ ዝግጅት ጀምረው በሶስት ምዕራፎች ሚናቸው እያደገ እንደመጣ ግልፅ ነው፡፡
የህዝቡን እንቅስቃሴ የሚመራውና የሚያጠናክረው ደግሞ መሪ ድርጅት ነው፡፡ ይህ ሲባል ድርጅቱ የህዝቡን እንቅስቃሴ እየመራና በህዝቡ እንቅስቃሴ ውስጥ ድርጅታዊ ብቃቱንና ጥንካሬውን እያጎለበተ የሚሄድበትን የተሳሰረ ሁኔታ መፍጠር ወሣኝ የአመራር ተግባር ነው፡፡
በከተማችን ድርጅታችን ኢህአዴግ በህዝቡ ውስጥ ፖለቲካዊና ድርጅታዊ ስራዎችን እያከናወነ በየጊዜው ከህዝቡ እንቅስቃሴ ግንባር ቀደሞችን በመመልመል የድርጅቱን አቅም ለማስፋት ጥረት እየተደረገ ይገኛል፡፡ የአባላችንን ግንባታም በተመሣሣይ ሰፊ ጥረት በማድረግ የውስጥ ድርጅት ፖለቲካዊ አቅሙን ለማሣደግ ሰፊ ጥረት ተደርጓል፡፡
ነገር ግን ይህንን ያህል ጥረት ተደርጎም አሁንም ቀላል የማይባል የማስፈፀም አቅም ችግር ይታያል፡፡ በከተማችን በህዝቡም ይሁን በአባሉ ዘንድ ያለው ዝንባሌ ኢህአዴግ የፖሊሲና ስትራቴጂ ችግር ሣይሆን የማስፈፀም አቅም ችግር አለበት የሚል ትችት ያቀርባል፡፡
ስለሆነም በአሁኑ ጊዜ እየተካሄደ ያለው ግምገማ እነዚህን ችግሮች ግምት ውስጥ በማስገባት የጠራ አመለካከት በመያዝ መሠረታዊ የአቅም፣ የስነ - ምግባርና የዝግጁነት ችግር ያለባቸውን አመራሮች የሚያጠራ መሆን ይኖርበታል፡፡
በከተማችን በአጠቃላይ ከ3 ሺህ 400 በላይ አመራር ያለ ሲሆን በእጅጉ ቁጥሩ እየጨመረ ያለውን አባላል በብቃት የሚመራና አቅሙ እያደገ የሚሄድ አመራር መፍጠር ወሣኝ ጉዳይ ይሆናል፡፡
የአመራር አቅማችንን የማሣደግ ጉዳይ በስልጠና ብቻ የሚከናወን ተግባር አይደለም፡፡ በማያቋርጥ የዕለት ተዕለት ተግባር ውጤታማ ስራዎችን ማከናወን ወሣኝ ነው፡፡ በተለይም በየደረጃው ካለው አመራር ለህዝብ ቅርብ ሆኖ ወሣኝ ሚና የሚጫወተው የወረዳ አመራራችን ሲሆን የውስጥ ፖለቲካዊ ትግል በማካሄድ መልሶ ማደራጀት ላይ ልዩ ትኩረት ሊደረግ ይገባል፡፡ በእርግጥ አመራርን የማጠናከር ጉዳይ በአንድ ወቅት ተሰርቶ የማይጠናቀቅ ቢሆንም ከቀጣይ ሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅዳችን አንፃር ሲታይ አሁን መጀመሩ ትክክለኛና ተገቢ መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል፡፡
የወረዳ አመራራችን ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ሲሆን ከቁጥሩ መስፋት ባሻገር አብዛኛው አመራር በድርጅት አባልነት ቆይታው አዲስ ነው፡፡ ስለሆነም የአመራር ተሞክሮና ልምድ የሚያንሰው መሆኑ የሚያከራክር ጉዳይ አይሆንም፡፡ ከዚህ አንፃር የአመራሩ አቅም በቀጣይ በተለያዩ ስልጠናዎችና በተግባር መገንባት ትኩረት ተሰጥቶት የሚፈፀም መሆን ይኖርበታል፡፡
ስለአመራር መጠናከር ሲታሰብ ሌላው ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው ጉዳይ በየደረጃው ያለው አመራራችን የዴሞክራሲና የልማታዊ እሴቶችን መላበሱን በየጊዜው ክትትል ማድረግ ይገባል፡፡ የአመራራችን አቅም እንዲጠናከር ብቻ ሣይሆን አስተማማኝ የህዳሴ አመራር ሆኖ እንዲቀጥል ዴሞክራሲና ልማታዊ አስተሳሰብና ተግባርን የዕለት ተዕለት መመሪያዎቹ አድርጎ መንቀሣቀስ ሲቻል ብቻ ነው፡፡ ተልዕኮ ሲፈፅምም በማናቸውም መስክ ሁሉ የዴሞክራሲና ልማታዊነት ባህሪ ይዞ ሲመራ ብቻ ነው፡፡
የዴሞክራሲ እሴቶች የሚባሉት በዋነኛነት የህግ የበላይነትን ማረጋገጥ፣ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን ጥቅሞች የማስቀደም ሲሆን አመራሩ በዚህ ዙሪያ ግንባር ቀደምና አርአያ ሆኖ ራሱም ከተለያዩ የስነ ምግባር ችግሮች ፀድቶ መንቀሣቀስ ይጠበቅበታል፡፡
የልማታዊነት እሴት ሲባል ደግሞ ህዝቡ በልማቱ ተጠቃሚ እንዲሆን፣ በዚህ ሂደት እያንዳንዱ አመራር ህዝቡ ተጠቃሚ የሚሆንበትን ሁኔታ ለመፍጠር መንቀሣቀስና ጥረት ማድረግ አለበት፡፡ የራስን ጥቅም ከህዝብ ጥቅም አለማስቀደም ወዘተ የሚሉትን መሠረታዊ ባህሪያት መላበስን ከአንድ አመራር የሚጠበቅ ተግባር ይሆናል፡፡ ነገር ግን አመራራችን ከላይ ከተገለፁት ችግሮች የፀዳ አይደለም፡፡
ስለሆነም የዴሞክራሲና ልማታዊነት እሴትን የተላበሰ አመራር የመገንባት ጉዳይ በየደረጃው ያለው አመራር ከኪራይ ሰብሣቢነት አመለካከትና ተግባር የሚፀዳበትን ሁኔታ ተግባራዊ በማድረግ ሁሌም በኪራይ ሠብሣቢነት ላይ የሚደረገውን ትግል ትኩረት ልናደርግበት ይገባል፡፡
ጠንካራ አመራር የሚባለው ስራዎችን በዘፈቀደ ሣይሆን በታቀደው መንገድ የሚፈፅም መሆን አለበት፡፡ በአንድ ወቅት እንዲከናወኑ የሚፈለጉ በርካታ ተግባራት ይኖራሉ፤ ሁሉንም ተግባራት ግን በአንድ ጊዜና በተመሣሣይ ትኩረት መፈፀም አይቻልም፡፡ ስለሆነም አመራር ተግባራቱን እንደየ አንገብጋቢነታቸውና በሚኖራቸው ሚዛን ደረጃ በደረጃ በመመደብ ቁልፍ ተግባሩን ለይቶ የሚረባረብ መሆን ይኖርበታል፡፡
አመራሩ በማናቸውም ስራ ግንባር ቀደም መሆን የሚገባው ሲሆን ከሁሉም በላይ ደግሞ የራሱን ብቻ ተግባራት ጠቅልሎ በመያዝ ተልዕኮውን ሊያሣካ አይችልም”” የአመራር ብቃት አንዱና ወሣኙ ጉዳይ ሰርቶ የሚያሰራ መሆን ሲችል ነው”” ስለሆነም አመራሮች የሚመለከታቸው አካላት ወይም ሦስቱ የልማት ኃይሎችን በማብቃት ማንቀሣቀስ ይጠበቅበታል፡፡
ጠንካራ አመራር የሚባለው በድርጅትም ሆነ በመንግስት በተቀመጠው የክትትልና ድጋፍ ስርአት በአግባቡ መንቀሣቀስ የሚችል ነው፡፡ ይህ ሲባል ያልተጋነነ ሪፖርት የሚያቀርብ የበታች አካላትን ስራ በቅርብ የሚከታተልና ተገቢ ድጋፍ የሚሰጥ፣ ነገሮች ከመበላሸታቸው በፊት አስቀድሞ ዝንባሌዎችን እየተከታተለ አፋጣኝ መፍትሔ የሚሰጥ ሲሆን ነው፡፡
በየደረጃው ያለው የአመራር ጥንካሬ የሚለካው ከሁሉም በላይ ባስመዘገበው ውጤት ነው፡፡ ከስራ ውጤት ውጭ የሚኖር ማናቸውም አይነት ሚዛን ተጨባጭነት የሌለው ለተለያዩ አዝማሚያዎች የተጋለጠ መሆኑ የማይቀር ሀቅ ነው፡፡
ስለሆነም በአሁኑ ጊዜ በየደረጃው የሚካሄደው የአመራር ግምገማ ስራዎቹ በዝርዝር እየተቆጠሩ፤ የእያንዳንዱ ተግባር አፈፃፀም በዝርዝር እየተገመገመና በስነ - ምግባር የተመሰገኑና ችግር ያለባቸው የሚለዩበትን ስርአት ተግባራዊ በማድረግ እንደአካልም ሆነ እንደ ግለሰብ በውጤቱ የሚታወቅበት ሁኔታ መፈጠር ይኖርበታል፡፡
በኮሚቴ ስም በጅምላ ጠንካራ ወይም ደካማ እየተባለ የሚታለፍበት፣ የጎላ ስነ ምግባር የሌለበትና በኪራይ ሰብሣቢነት ተግባር የገባ በድምፅ ብልጫ እየተባለ ጥገኝነት የሚጠናከርበት ሣይሆን እያንዳንዱን ግለሰብ በአብዮታዊ ስነ ምግባሩና በስራ ውጤቱ በመመዘን ውሣኔ የሚሰጥበትን አሰራር በማዳበር የከተማችንን የለውጥ ህዳሴ አመራር ማጠናከር ወሣኝ ተግባር ይሆናል፡፡


No comments:

Post a Comment