Saturday, 22 August 2015

ህዝባዊ ሃላፊነታችን ለላቀ እድገትና ትራንስፎርሜሽን!!!ድልና ድምቀት ለ11ኛዉ ድርጅታዊ ጉባያችን!!!ብአዴን

ብአዴን እና የአማራ ክልል

የብሄረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ /ብአዴን/ 11ኛ ድርጅታዊ ጉባኤ በድርብ ድርብርብ ድሎች ላይ ሆኖ የሚካሄድ ጉባኤ ነው፡፡ በብዙ መለኪያዎች የድል ጉባኤ ነው፡፡ ህዝባዊ ሃላፊነቱን ለላቀ እድገትና ትራንስፎርሜሽን ለማዋል በቁርጠኝነት እየተጋ ያለው ብአዴን በ35ኛ አመት የምስረታ በአሉ የሚያካሂደው 11ኛ ድርጅታዊ ጉባኤ በእርግጥም ልዩ ትርጉም የሚሰጠው ነው፡፡ ብአዴን ከምስረታው እለት አንስቶ በህዝባዊ ወገንተኝነትና በአላማ ፅናት መንፈስ በድል አድራጊነት የዘለቀ አኩሪ ታሪክ ያለው ድርጅት ነው፡፡
ብአዴን በ9ኛውና 10ኛው ድርጅታዊ ጉባኤዎቹ የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድን መሰረት ያደረጉ የድርጅትና የመንግስት ስራዎች የሚመራበት አቅጣጫዎች አስቀምጦ ነበር፡፡ በወቅቱ  የድርጅቱ የአቅም ግንባታ ስራ በተለይም የድርጅት አመራሩ ፖለቲካዊና ርእዮተአለማዊ ብቃት ልዩ ትኩረት እንዲሰጠው ነበር ጉባኤው ውሳኔውን አስተላልፎ የነበረ፡፡ በተግባርም አባሉን ጨምሮ በሁሉም የአመራር እርከን የሚገኘው ሃይል በስልጠና የአስተሳሰብ አንድነት ተመጣጣኝነት እንዲኖረው ሰፊ ስራ ተሰርቷል፡፡ በድርጅቱ የሚካሄዱ ኮንፈረንሶች ሳይቆራረጡ ለማካሄድ ከተደረገው ጥረት በላይ ድርጅቱ የተሻለ አቅም የሚፈጥሩ የንድፈ ሃሳብ ትንታኔዎች በማዘጋጀት ለብሄራዊ ድርጅቱ/በተወሰነም ለግንባር አባላት/ በማድረስ የፋናወጊ ሚና ነበረው፡፡

የገጠርና ግብርና ልማት

 በክልሉ በእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዘመኑ የግብርና ዘርፍ  በ8 በመቶ ለማሳደግ ታቅዶ የነበረ ሲሆን ሙሉ በሙሉ የታቀደው ግብ መድረስ ባይቻልም የተመዘገበው የ7 ነጥብ 2 በመቶ እድገት በምንም መለኪያ ትልቅ የሚባል ነው፡፡ ለምሳሌ የሰብል ምርት የተመለከትን እንደሆነ ወደ 87 ነጥብ 6 ሚሊዮን ኩንታል ከፍ ማለቱን እናያለን፡፡ ከክልሉ አጠቃላይ ምርት ውስጥ ግብርና የ55 ነጥብ 9 በመቶ በመያዝ የክልሉ እድገት ምንጭ መሆኑን አረጋግጧል፡፡ ክልሉ በምግብ ራሱን ከመቻሉ በላይ ከድህነት ወለል በታች የሚኖረው ህዝብ ከነበረበት 30 ነጥብ 5 በመቶ ወደ 22 በመቶ ዝቅ ማድረግ ተችሏል ተብሎ ይገመታል፡፡ አርሶ አደሩ ምርትና ምርታማነቱን በማሳደግ ከሚደረጉ ዘርፈ ብዙ ጥረቶች መካከል አርሶ አደሩ በይዞታው ላይ ተማምኖ ዘላቂ ልማት ማምጣት እንዲችል ሙሉ በሙሉ ሊባል በሚቻል ደረጃ የይዞታ ማረጋገጫ ደብተር እንዲያገኝ ተደርጓል፡፡
የገጠርና የግብርና ልማትና እድገቱ ዘላቂነት የሚኖረው ተፈጥሮን በመጠበቅና የተጎዳውም እንዲያንሰራራ መሆኑ በ10ኛ ጉባኤ ግልፅ አቅጣጫ ያስቀመጠው ጉባኤ በ11ኛው ጉባኤ በስኬት ከሚገመግማቸው ተግባራት አንዱ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ምክንያቱም ከ5 አመት በፊት 7 ነጥብ 9 በመቶ ገደማ የነበረው የክልሉ የደን ሽፋን በዘንድሮ አመት 15 በመቶ መድረስ እንደ ቻለ መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡ ይህ ደግሞ በገጠር ጠንካራ የተፈጥሮ ሃብት ሰራዊት መገንባት በመቻሉና የአርሶ አደሩ ጥረት ውጤት ነው ማለት ይቻላል፡፡

የከተማ ልማት

የድርጅቱ ነባር አመራሮች እንደሚገልፁት ድርጅቱ ቆቡን ፈቶ የሚሰፋ ስራ ፈት ድርጅት አይደለም፡፡ የተለያዩ የትምክህትና የጥገኛ ሃይሎች በተደራጀና ባልተደራጀ መልኩ በክልሉ በድርጅቱ እየተገነባ ያለውን ዴሞክራሲያዊ ብሄርተኝነት ግንባታና አስተሳሰብ ለመሸርሸር እንዲሁም በክልሉ የህዝቡን ሁለንተናዊ ኑሮ እየለወጡ ያሉ እድገቶችን ለማጠልሸት ቢፍጨረጨሩም የድርጅቱ አመራርና አባላት ግን ‹‹ እኛ ስራ ላይ ነን›› በማለት ጥርሳቸውን ነክሰው በስራ ላይ ተጠምደዋል፡፡
በክልሉ ከእድገታቸው የገዘፈ ስም የነበራቸው በእድገት ግን የቀጨጩ ከተሞች ከፍተኛ የኢኮኖሚ መነቃቃት ይታይባቸዋል፡፡ የክልሉ ርእሰ ከተማ የሆነችው ባህርዳርን ጨምሮ በርካታ ከተሞች ከስያሜ ባለፈ የእውነተኛ ከተማነት ገፅታ ተላብሰዋል፡፡
በሃገራዊ የከተማ ልማት ስትራቴጂ መሰረት የጥቃቅንና አነስተኛ ልማት የከተማ ልማት እምብርት ነው፡፡ ክልሉም ይህንን አቅጣጫ በመያዝ ስራውን ለማሳካት ያስችላል ያለውን ‹‹የቴክንክና ሙያ ኢንተርፕራይዞች ልማት ቢሮ›› በማደራጀት በሰራው ስራ በአጠቃላይ 202 ሺህ 274 ኢንተርፕራይዞች የተመሰረቱ ሲሆን በዚሁም በድምሩ ለ2 ሚሊዮን 161 ሺህ 825 ዜጎች የስራ እድል ተፈጥሯል፡፡ በክልሉም 4214 ያህል ሼዶች ተገንብተው ስራ ላይ ውለዋል፡፡ የክልል የካፒታል እቃዎች ና ፋይናንስ አቅራቢ ድርጅትም እንዲቋቋም ተደርጓል፡፡
በክልሉ የፀና ንግድ ፍቃድ ያላቸው 314 ሺህ 331 ዜጎች ነግደው የሚያተርፉበት እድል ተመቻችቶላቸው እነሱም ከግል ገቢያቸው ባሻገር በክልሉ ልማት እቅድ መሳካት ትልቅ ሚና እያበረከቱ ይገኛሉ፡፡
በአበባና በሰሊጥ የተሰማሩ ኢንቨስተሮችን ጨምሮ በ10 ቢሊዮኖች የሚገመት የኢንቨስትመንት አቅም በክልሉ ተፈጥሯል”” በማኑፋክቸሪንግም ቢሆን በክልሉ 373 አምራቾች ወደ ምርት ተሸጋግሯል፡፡ እንደ ኮምቦልቻ ያሉት የክልሉ ከተሞች ደግሞ ዋናው የሀገሪቱ የኢንዱስትሪ ፓርክ እንዲሆኑ ተለይተዋል፡፡ ሆኖም በክልሉ ካለው እምቅ ሃብት አንፃር የማኑፋክቸሪንግ ንኡስ ዘርፍ ድርሻ መድረስ የነበረበት ደረጃ ደርሷል የሚባል አይደለም፡፡ በባለሃብቱ ዘንድ ወደ አገልግሎት ዘርፉ የማዘንበል ሁኔታዎች እንዳሉ የኢንቨስትመንት መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ስለሆነም በቀጣዩ የእድገትና ትራንስፎርሜሽን በዚህ ረገድ ያለውን ውስንነት በማስወገድ በክልሉ የኢኮኖሚ መዋቅር ሽግግር እንዲሳለጥ የሚያስችል አቅጣጫ ከጉባኤው ይጠበቃል፡፡

መሠረተ ልማት

ዞንን ከዞን፣ ወረዳን ከወረዳ፣ ቀበሌን ከቀበሌ ማዕከል ጋር የሚያገናኙ  መንገዶችና ድልድዮችን በመገንባት እንዲሁም ነባር የገጠር መንገዶችን በመጠገን ያልተቋረጠ አገልግሎት መስጠት እንዲቻል ማድረግ በሚሉ የጉባኤው አቅጣጫ መሰረት ከ9ኛ ድርጅታዊ ጉባኤ ወዲህ በሁለት አመት ውስጥ 11 ሺህ ኪሎሜትር መንገድ ተገንብቷል፡፡ በእቅድ ዘመኑ 1274 የቀበሌ ማዕከላት ከዋና መንገድ የተገናኙ ሲሆኑ ቀደም ባሉ አመታት ከዋና መንገድ የተገናኙ 725 ቀበሌዎችን ጨምሮ በድምሩ 1999 ቀበሌዎች ከዋና መንገድ ጋር ተገናኝተዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ የክልሉ የውሃ ሽፋን በአማካይ 89 ነጥብ 5 በመቶ የደረሰ ሲሆን በድምር 1177 ቀበሌዎች ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡ ይህም ሆኖ የኤሌክትሪክ ሽፋኑ እና የሽቦ አልባ ስልኮች ስርጭት በቀጣይ ከፍተኛ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው ጉዳይ መሆኑንና ጉባኤውም በዚህ ዙሪያ ትኩረት ሰጥቶ ይወያይበታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ማህበራዊ ልማት

በክልሉ በትምህርት ዘርፍ የምእተ አመቱ ግብ ለማሳካትና ፍትሃዊነትን ለማረጋገጥ ስኬታማ ስራዎች ተከናውነዋል፡፡ በእቅድ ዘመኑ በተለይም የቅድመ መደበኛ ትምህርት ተደራሽነትና ተሳትፎ በ2002 ከነበረበት እጅግ ዝቅተኛ የሚባለው የ2 ነጥብ1 በመቶ ወደ 51 ነጥበ 6 በመቶ መድረሱ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ሽፋን ንጥር ተሳትፎ 92 በመቶ፣ የ2ኛ ደረጃ ደግሞ 36 በመቶ የደረሰ ሲሆን  ማንበብና መፃፍ የማይችሉ ጎልማሶች በክልሉ 60 ነጥብ 8  በመቶ የነበረ ሲሆን በተሰራው ስኬታማ ስራ 27 በመቶ የሚሆኑ የጎልማሳ ትምህርት መርሃ ግብር ተምረው ያጠናቀቁ ሲሆን 45 በመቶ ደግሞ ትምህርታቸውን እየተከታተሉ ይገኛሉ፡፡
ከትምህርት መሠረተ ግንባታ አንፃር 261 ሁለተኛ ደረጃ ተምህርት ቤቶች  እንዲገነቡ ተደርጓል፡፡ የአንደኛ ደረጃ የተማሪ መጠነ ማቋረጥ ወደ 1 ነጥብ 57 በመቶ ዝቅ እንዲል ተደርጓል፡፡ በአንደኛ ደረጃው የወንድና ሴት ተማሪ ተሳትፎ ተመጣጣኝ ደረጃ የደረሰ ሲሆን በሁለተኛ ደረጃ የሴት ቁጥር ብልጫ እንዳለው መረጃው ያሳያል፡፡
መከላከልን ማዕከል ባደረግው የጤና ፖሊሲ መሰረት የጤና ኤክስተንሽን ፕሮግራም በሁሉም የገጠርና ከተማ ቀበሌዎች ተግባራዊ ሆኗል፡፡ በመሆኑም በክልሉ 89 በመቶ አባወራ/ እማወራ/ በጤና አክስቴንሽን ፓኬጅ ስልጠና ተሰጥቷቸዋል፡፡
በ2002 ከ100 ሺህ እናቶች 676 ይሞትበት የነበረው እውነታ በመቀየር ዛሬ ወደ 420 ዝቅ ብሏል”” የህፃናት ሞትም በሁለት ሶስተኛ መቀነስ ተችሏል፡፡ በክልሉ በርካታ ወረዳዎችና በሺህ የሚቆጠሩ ቀበሌዎች ለአስከፊ የወባ ወረርሽኝ በሽታ ተጋላጭና በሽታው በክልሉ አንደኛ ገዳይ እንደነበረ ይታወቃል”” ነገርግን በዚህ ዙሪያ በተሰራው ስኬታማ ስራ ችግሩ ሙሉ በሙሉ ባይወገድም  ከፍተኛ የጤና ችግር ወደ ማይሆንበት ደረጃ ደርሷል፡፡ ከመከላከል በተጓዳኝ የጤና አገልግሎት ተደራሽነት ማስፋትም ትኩረት የተሰጠው ነበር፡፡ በመሆኑም በክልሉ 820 የጤና ጣቢያዎች ተገንብተው አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ፡፡ የሆስፒታሎች ቁጥርም በእቅድ ዘመኑ ከነበረበት 16 ተቋማት  በመገንባት ያሉትን ጨምሮ ወደ 74 ማድረስ ተችሏል፡፡


No comments:

Post a Comment