“ማንን ይዞ ጉዞ” እንዲሉ የከተማችንም ሆነ የሀገራችን ልማትና ሰላም ያለ ወጣቶች የነቃ ተሳትፎ
ይረጋገጣል ብሎ ማሰብ ዘበት ነው፡፡ ይሄ ደግሞ ወጣቶች ካላቸው እምቅ አቅም ጋር የተያያዘ ብቻ ሳይሆን ከተማችንም ይሁን ሀገራችን
እንደ አብዛኛው ታዳጊ ሀገራት የወጣቶች ሀገር በመሆናቸው ነው፡፡ ይህ ፀጋ ነው፡፡ ይህ ፀጋ ግን በሀገር ግንባታ ሃላፊነቱን በብቃት
የሚወጣው በትምህርት ሲገነባ፣ ጤናው ሲጠበቅ፣ በስነ ምግባር ሲታነፅና ተጠቃሚነቱም የሀገሪቱ ኢኮኖሚ በሚፈቅደው አቅም እያደገ ከመጣ
ብቻ ነው፡፡ ወጣቱን አግላይ የሆኑ አስተሳሰቦችና ሀገራዊ ፖሊሲዎች በአሳታፊ አስተሳሰቦችና ፖሊሲዎች ሲተኩ ብቻ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ
የህግ ማዕቀፎች ወሳኝ ድርሻ አላቸው፡፡ በሀገራችን ወጣቶች እንደማንኛውም የህብረተሰብ ክፍል መብቶቻቸው ህገ መንግስታዊ ዋስትና
አግኝተዋል፡፡ ወጣቶችን በተለየ ሁኔታ የሚያስተናግዱ ፖሊሲዎችና ፓኬጆችም ተቀርፀዋል፡፡
Friday, 8 April 2016
Thursday, 7 April 2016
ፌደራሊዝም ወዴት እየወሰደን ነው?(በመቃብሽ ርግበይ)
የፅሁፉ ሰበብ
ከጥቂት ወራት በኋላ አምባገነኑ የደርግ ስርአት የተገረሰሰበትን 25ኛ አመት የግንቦት 20 በዓል እናከብራለን፡፡
ኢህአዴግ እንደ ድርጅት መንግስትም እንደመንግስት እስከአሁን በዓሉን እንዴት ለማክበር ማሰባቸውን ባላውቅም ዝምታው ግን አልገባኝምም
አልጣመኝምም፡፡ 25ኛ አመት ነው፡፡ ሩብ ክፍለ ዘመን፡፡ የብር ኢዮቤልዩ፡፡ በዜጎች ደም የተመሰረተች የአንዲት ዴሞክራሲያዊት ሃገር
በዓል ቀርቶ ግለ ሰቦችም ልደታቸውን በተለየ ፕሮግራም ያከብሩታል”” ምክንያቱም 25 አመት ማለት የሰው ልጅ የአፍለኛ እድሜውን አጠናቆ ራሱን ወደ በርካታ ሃላፊነቶች የሚያዘጋጅበት
ነው፡፡ ወደ ላቀ የህይወት ምእራፍ የሚንደረደርበት ነው፡፡
ለአንድ ድርጅት፣ ለአንድ መንግስት፣ ለአንድ ሃገር ሲሆን ደግሞ ከዚህ የላቀ ትርጉም አለው”” እናም 25ኛ የግንቦት በአል ሲከበር ኢትዮጵያ
በአዲስ አስተሳሰብ የተጓዘችባቸው አመታት ስኬትና ጉድለቶችን መገምገም፣ ከግምገማ በመነሳትም ለወርቅ ኢዮቤልዩ ለሚደረገው ጉዞ አቅጣጫዎች
የሚቀየሱበት ይሆናል ብዬ አስባለሁኝ፡፡ ይህ የሃሳብ ብልጫ ሰበብ ሆነብኝና ብእሬን አነሳሁ፡፡ ሃሳብ ለመጫር ያህል ማለት የምችለውን
እንሆ አልኩ፡፡
መነሻችን ምን ነበር?
መንደርደሪያችን በግርድፉ የ1960ዎቹ ትውልድ የሚባለው ነው፡፡ ያ ትውልድ፣ትውልድን ያናወጠ ትውልድ ነው ይሉታል፡፡
ተራሮችን ያንቀጠቀጠ ብለው የሰየሙትም አሉ፡፡ የሚባለውን ልድገመውና አብዮት የመደቦች መሸጋሸግና መገለባበጥ ነው የሚለው የወቅቱ
ፖለቲካ ሃይሎችና ሰዎች የወል እምነትም፣ ፍልስፍናም፣ ርዕዮትም ነበር፡፡ ሃገሪቷም በሚሳይል ፍጥነት ከስዩመ እግዚአብሄር ወደ ስዩመ
ማርክስሌኒንዝም ተስፈነጠረች፡፡
በምድረ ኢትዮጵያ የሶስቱ ስላሴዎች ልዕልና በሶስቱ ኮሚኒስቶች /ማርክስ ኤንግሊስ እና ሌኒን/ የተነጠቀች ትመስላለች፡፡
ሁሉም ሶሻሊስት ነኝ አለ፡፡ ማለትና መሆን ግን ለየቅል ነበር፡፡ አለም አቀፋዊነትን /ኢንተርናሲዮናል/ መመሪያችን ያለው ሃይል
ሁላ ገና ከመንደሩ ሳይወጣ በኢትዮጵያ ትርጓሜና ግብ ላይ ተለያይቶ ተቧቀሰ፡፡ አድዮስ አለምአቀፋዊነት!
በተምታታ እሳቤና ተግባር የኢትዮጵያ አብዮት እጅግ ቅራኔዎች የተካረሩበት ሆኖ ተመርቷል፣ ተራምዷል፣ ተተራምሷል፣
አብዮቱ ልጆቹን በልቷል፡፡ መጨረሻም የፖለቲካ ትግል የመጨረሻ ጫፍ በሆነው አፈሙዝ ትግል ተጠናቋል፡፡ ተጠናቋል ማለትም የሚቻል
ቢሆንም ቅሪላዎች ግን አልተንጠፈጠፉም፡፡ አሉ፡፡
በዚህ ምንም አይነት ለመቻቻል እድል የማይሰጥ ምህረት የለሽ የአብዮት ሂደት (እንደሚባለውም) ላይመለሱ የተደመሰሱ
ሃይሎች የነበሩትን ያህል ነገርግን ህመም የበዛበት በርካታ የቀጠሉ መቆሳሰሎችና ጠባሳዎች ትቶም አልፏል፡፡ ቀጥሏልም፡፡
እርግጥ ነው በተለይ ከገዥመደቦች ተቋማዊ ስርአት አንፃር በኢትዮጵያ ሽግሽጉ ሙሉ በሙሉ ተጠናቅቋል ሊባል ይቻላል፡፡
በ1967 ወታደራዊ ጊዚያዊ መንግስት የመንግስት ስልጣኑ በመቆጣጠሩ አብዮቱ ሽንፈት የተበየነበት አብዮት ገፅታ ቢይዝም እስከወዲያኛው
አልከሸፈም፡፡
በሌላ ገፅታው በወቅቱ ከነበረው እሳቤ አንፃር ከተመለከትነው አሮጌ ስርአትን በመደምሰስ አዲስ ስርአትን ይገነባል
በሚለው መፈክር በአሮጌው ስርአት መቃብር የላባደራዊ/ወዛደራዊ/ አምባገነንነት የተረጋጋጠበት ስርአት የመተካት እቅድ ግን በትልቁ
የአለም ፖለቲካ ለውጥ ምክንያት ከሽፏል፡፡ በዚህ የሚቆጩ ያሉትን ያህል እንኳንም የአለም ሁኔታ ተለወጠ እንኳንም አልሆነ የሚሉም
አሉ፡፡
ኢህአዴግን ጨምሮ ሁሉም በወቅቱ መመሪያችን
ማርክሲዝም ሌኒኒዝም ነው ይሉ የነበሩ ድርጅቶች ከስም በስተቀር የሶቭዮት መር የምስራቁ ዓለም ተወዳዳሪነት መፈረካከስን ተከትሎ
በሀገር ውስጥም ርእዮተአለማዊ ሽግሽግ አድርገዋል፡፡
ያደረጉት ሽግሽግ ስትራቴጂካዊ ነው ታክቲካዊም
ነው ብሎ መደምደም አይቻልም፡፡ ለጊዜው የሰው ሆዱ የወፍ ወንዱ አይታወቅም ብለን ከማለፍ በቀር መልስ መስጠት የሚቻል አይደለም፡፡
በውዴታ ብቻ ሳይሆን በግዴታም አዲሱን የአለም የፖለቲካ ሽግሽግ የተቀበሉ መኖራቸው ግን አንድ ሁለት የለውም፡፡
ከዚሁ የኢትዮጵያ አብዮትን የአለምአቀፍ
አብዮት አካል ለማደረግ ከነበረው የተለያዩ ሃይሎች መወጣጠር ባሻገር ግን በየትኛውም የትግል አግባብና ርእዮተአለማዊ አስተሳሰብም
ቢሆን መልስ ማግኘት የነበረባቸው ሃገራዊ ቁልፍና በርካታ አበይት አጀንዳዎች ነበሩ፡፡ በመሆኑም መታወቅ ያለበት እነዚህ ከርእዮተአለም
በላይ የሆኑ ሀገር በቀል አጀንዳዎች ናቸው አብዮቱን ያቀጣጠሉት እንጂ አብዮት የፈጠራቸው አይደሉም፡፡
የኢትዮጵያ አብዮት ቁልፍ አጀንዳዎች የእኩል
ተጠቃሚትና ተሳታፊነት ጥያቄዎች ሲሆኑ በመደባዊ ጭቆናና በብሄራዊ ጭቆና መልክ የሚገለፁ ነበሩ፡፡ እነዚህን ቁልፍ የህዝቦች የዘመናት
ጥያቄዎች ለመመለስ በግድ ደም ካልፈሰሰ ስርየት የለም እንደሚባለው ደም አፍሳሽ በሆነ ትግል መመለስ የነበረባቸው ባይሆኑም የሆነው
ግን ይኸው ነው”” በኢትዮጵያ ሁኔታ እነዚህን ቁልፍ ጥያቄዎች ለመመለስ ደም አፍሳሽ የሆነ የፖለቲካ ትግል ማካሄድ ግድ ያለበት
ሁኔታ የተፈጠረው ‹‹በመሬት አንድነት›› እና ‹‹በህዝቦች አንድነት›› አስተሳሰብ አራማጆች መካከል የማይታረቅ ቅራኔ ውስጥ በመግባታቸው
ነው፡፡
ሁለቱም ሃይሎች አንዱ ሌላውን ከመደምሰስ
ውጪ የያዘው አቋም ማሳካት የማይቻል ሆኖ ቅራኔው በትጥቅ ትግል ብቻ መፈታት የሚችልበት ብቸኛ እድል በመያዙም የባላባታዊ ስርአት
የሆነው የአፄዎች ስርአትን ለማስወገድ ከተከፈለው መስዋእት በላይ ያስከፈለ ትግል ማካሄድን ጠየቀ፡፡ በአብዮቱ ዘመን ትልቅ ሚና
የነበራቸው ሃይሎች በስማቸው አልያም በፕሮግራማቸው ‹‹አብዮት›› ወይም ‹‹ሶሻሊዝም›› የሚል ቃል ተቀጽላ የሚጠቀሙ አልያም የአብዮት
መገለጫ ተደርጎ የሚወሰደው የላባደር/ ወዛደር ስም ስለሚጠሩ የየራሳቸው ተከታይ ማፍራት ችለዋል”” በዚህ ሂደት በአብዮቱ አፍላ ወቅት ወታደራዊ
ደርግ የመንግስት ወንበር በመያዙ፣ ኢህአፓ ራሱን የተማሪና የወጣቱ ወካይ ሆኖ በመምጣቱ ሁለቱም የያዙት ተከታይ ከየትኛውም ቡድንም
ሆነ ድርጅት እጅግ የላቀ ነበር፡፡
ሁለቱንም ቡድኖች የሚመራው አመራር በመሰረቱ
የመሬት አንድነት አድናቂና የፍፁማዊ አንድነት አምላኪ በመሆኑ በዚህ ዙሪያ ተቃርኖ ባይኖረውም፤በኢትዮጵያ አብዮት ቁልፍ ጥያቄዎች
የነበራቸው የአተያይ ልዩነት ያንያህል የሰፋ ባልሆነበት ሁኔታ ተሸናናፊነታቸው ከተሞችን በደም ባጥለቀለቀ ትግል እንዲደመደም ሆኗል፡፡
በዚህ ወቅት ድንኳን ሰባሪው መኢሶን በመሃል በመግባት የነበረው የአጫዋችነት ሚና በፍፁም መዘንጋት የሌለበት ሆኖ እናገኘዋለን፡፡
ከላይ ለመጠቆም እንደተሞከረው የኢትዮጵያ
ህዝቦች ቁልፍ ጥያቄ የብሄር ብሄረሰቦች እኩልነት ጥያቄ ሲሆን በሀገሪቱ የነበረው የመደቦች ተቃርኖው አንድና ዋነኛ መልክም ብሄራዊ
ጭቆና ሆኖ እያለ የአብዮቱን የትግል መድረክ የተቆጣጠሩት በአንዳንዶቹ አገላለፅ ‹‹የታላቋ ኢትዮጵያ›› ተከታዮች ‹‹የፍፁማዊ አንድነት››
አምላኪዎች በመሆናቸው በብሄር ዘውግ የተደራጁ ድርጅቶች በጥቅል ‹‹ፀረ አንድነት›› የሚል ቅጥያ ተለጥፎላቸዋል፡፡
ስልጣኑን በተቆጠረው ወታደራዊ ቡድንም
ሆነ ባልተቆጣጠረው ተስፈኛው ሃይል እኩል የተገፉ ነበሩ፡፡ እነዚህ ገፍያን ቡድኖች በሶስቱም ሃይሎች የሚሳደዱ ነበሩ፡፡ በተሸነፈው
ነባር ስርአት አስመላሽ/ ኢዲዩና መሰሎቹ/፣ አዲስ ገዢ መደብ ሆኖ በአፈሙዝ ቤተመንግስቱን በተቆጣጠረው ደርግ እንዲሁም ስልጣኑ
የሚገባኝ ለኔ ነው በሚለው ኢህአፓ በሶስት አቅጣጫ የሚመቱ ቡድኖች ሆኑ፡፡
የማታማታ ግን ገፊዎች እየተፈረካከሱ ግፍዓኑ
እየተጠናከሩ መጥተው የብሄር ጥያቄ የማይሸራረፍ የህዝቦች ጥያቄ ነው ብለው በተነሱ ሃይሎች አሸናፊነት የአብዮቱ የመጀመሪያ ምዕራፍ
የሆነው የትጥቅ ትግል ከተደመደመ አንድ አራተኛ ምዕተ አመት አስቆጥሯል፡፡
የማይሸራረፍ የመሬት አንድነት ጥያቄ ወይስ
የማይሸራረፍ የህዝቦች መብት ጥያቄ መመለስ የሚችል አንድነት የሚለው አተካራ ግን ዛሬም ቢሆን ሞቶ የተቀበረ አጀንዳ አልሆነም፡፡
ዛሬም ‹‹የፍፁማዊ አንድነት ተከታዮች ዘመን›› ተመልሶ ይመጣል የሚለው ሃይል የተስፈኝነት ትግሉ አላቋረጠም፡፡ በሌላው ፅንፍ
‹‹የፍፁማዊ ነፃነት›› አቀንቃኝም ጥያቄውን አላነሳም፡፡ የፌደራል ስርአቱ በሌላ ብልሃት የመጣ የአቢሲያኒስት ተንኮል ነው የሚለውም
አልጠፋም፡፡ ‹‹የህዝቦች አንድነት›› ተከታይ አስተሳሰብ ወካይ ሃይል ደግሞ መንግስታዊ ስልጣን ይዞ የሩብ ምዕተአመት እድሜ አስቆጥሯል፡፡
በዚህ በኩል ያለው ተቋማዊ አቅምን ወደ
ጎን ትተን የአስተሳሰብ አቅም ሚዛን መገምገም ይገባል”” የህዝቦች አንድነት አስተሳሰብ ፍፁማዊ ልዕልና አረጋግጧል ወይ፤ ይህንን አስተሳሰብ ፍፁማዊ ልዕልና እንዲያረጋገጥ
ሩብ ክፍለዘመን በቂ ነው አይደለም፣ መልሱ አሉታዊ ቢሆንም አዎንታዊ ብቁና ሳይንሳዊ ምላሽ እንዲያገኝ ማድረጊያ ጊዜው አሁን ነው፡፡
በመሆኑም ከዚህ አንፃር የብሄር ተኮር ፌደራላዊ ስርአት ግንባታ ተስፋ፣ ስጋትና እውነታን የግምገማውና ምዘናው ማጠንጠኛ ማድረግ
ይገባል ብዬ አምናለሁኝ፡፡
ፌደራሊዝም ወዴት እየወሰደን ነው?
ኢትዮጵያ የብዝሃነት አገር ነች፡፡ በውስጧ
ራሳቸውን ያለምንም መምታታት ማንነታቸውን የሚገልፁ ብሄርና ብሄረሰቦች አሏት፡፡ ይህ ብዝሃነት በፍፁም በማንም ሊካድ የማይችል ቢሆንም
አሰያየሙ ላይ ግን ልዩነቶች አሉ፡፡ ብሄር፣ ዘር፣ ነገድ፣ ጎሳ የመሳሰሉ ስያሜዎች ስራ ላይ ይገኛሉ፡፡ ከእነዚህ አሰያየም በስተጀርባ
ደግሞ አመለካከት አለ፡፡ ይህ ምልከታ በራሱ ኢትዮጵያ እንዴት መዋቀር አለባት ለሚለው ትርክትም የተለያየ አማራጭ እንዲቀርብ ያደርጋል፡፡
ኢትዮጵያ የረጂም ክፍለዘመን ህልውና ያላት
ሃገር ናት የሚል የታሪክ ትርክት የምንቀበል ከሆነ ከዚሁ መሳ ለመሳ ትልቁን ድርሻ የሚወስደው አወቃቀሯ የተማከለ አስተዳደር ሳይሆን
ያልተማከለ አስተዳደር /ፌደራላዊ ይዘት ያለው/ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በተማከለ አስተዳደር እሳቤ የተዳደረችው በንጉስ ቴድሮስ /በተግባር
ባይሳካለትም/፣ ንጉስ ሚኒሊክ፣ ንጉስ ሃይለሰላሴና የደርግ መንግስት ዘመን ብቻ ነው””
ይህ ደግሞ መሃል ላይ የተሰነቀረ ከመቼውም
ዘመን ጎላ ብሎ ከታየው የንጉስ ዮሃንስ ፌደራላዊ አወቃቀር /de facto federal system/ ሁለት አስርት አመታት በስተቀር
ለአንድ ክፍለ ዘመን ተኩል የታየ ስርአተ መንግስት ነው ይላሉ ዶክተር አሰፋ ፍስሃ፡፡
በየዘመኑ የትግራይ፣ የበጌምድር፣ የጎጃም፣
የወሎ፣ የሀውሳ፣ የሸዋ ባላባቶች የአከባቢያቸው ገዥዎች እንደነበሩ የታወቀ ነው፡፡ በተመሳሳይ እንዲህ ያለ የላላ አንድነት በደቡብንና
ደቡብ ምዕራብ አከባቢም የነበረ ነው፡፡ የግቤ አምስት ነገስታት ተብለው የሚተወቁት ሊሙ ኢናሪያ፣ ጎማ፣ ጉማ፣ ጌራ እና ጅማ ተብለው
የሚታወቁትም ሙሉ በሙሉ የተለያዩ ባይባሉም ትስስራቸው ግን ፌደራላዊ መልክ ነበረው፡፡
የእነዚህ ነፃ አስተዳደር ያበቃው ሚኒሊክ
ሰኔ 14/ 1890 በእምባቦ ጦርነት የጎጃሙን ንጉስ ተክለሃይማኖትን ካሸነፉ በኋላ ነበር፡፡ በእርግጥ የግቤ ሞናርኪ ብቻ ሳይሆን
የወለጋና ኢሉባቦር ነፃ መንግስታትም ጭምር ነው ህልውናቸው ያከተመው”” የኦሞ ስልጣኔ የሆኑ እና በ14ኛና በ15ኛ ክ/ዘመን ጀምሮ የራሳቸው ህልውና እንደነበራቸው የሚገልፁ የከፋ፣
የወላይታ /ንጉሰ ጦና/፣ ሲዳማ፣ ከምባታ እና የም /ጃንጃሮ/ ነፃ ግዛቶች መኖራቸውንም መርሳት አይገባም፡፡ ነባሩ የእስልምና ሱልጣኔት
ታሪክ ያለው የምስራቁ ክፍል የአፋር፣ የሶማሊያና የሀረሪ
ኤምሬቶች ነፃ ግዛቶችም፡፡ የሀውሳ ሱልጣኔት
ስርወ መንግስት ማእከል የሆነው የአፋር ነፃ ግዛት ያከተመው በ1930 እኤ አ ሃይለስላሴ ሙሉ በሙሉ ስልጣኑን እንደተቆጣጠሩ ነበር፡፡
በተለይም ከ8ኛው ክ/ዘመን ጀምሮ የእስላም መንግስት ማእከል ብቻ ሳይሆን የምስራቅ ኢትዮጵያ የፖለቲካና ባህል ማእከል ሆና እስከ
ዘመናችን የዘለቀችውን ሀረር የመሰለ ለረጂም ክፍለ ዘመናት የቀጠለ ከተማ መንግስት /City state/ በደጋማው ኢትዮጵያም ማግኘት
አይቻልም፡፡
በዚህ ረገድ ሀረር ወደር የላትም፡፡በድምር
የታሪክና የፖለቲካ ሳይንስና ማህበራዊ ሳይንስ ተመራማሪዎች እንደሚያስረግጡት እነዛ አካባቢያዊ ግዛቶች ከማእከላዊ መንግስት ጋር
የነበራቸው ግንኙነት ሙሉ በሙሉ የተበጠሰ ነው ባይባልም ከማእከላዊ መንግስት ጋር የነበራቸው ትስስር ቀጥታዊ ያልሆነ በዋነኝነት
ግብርን በመክፈል ነበር፡፡ ዶክተር ፍስሃም በመፅሀፋቸው እንዲህ ይሉናል፤
‹‹In short, the majority
of the Kingdoms of the South, South West and Eastern sides existed as
autonomous units only indirectly associated with the center usually marked by
the payment of tributes.”
ከውጫዊ ገፅታ አንፃር ኢትዮጵያ ከሞላ
ጎደል አሁን ያለችበት ቅርፅ የያዘችው በአፄ ሚኒሊክ ዘመን ነበር፡፡ ስርአተ መንግስቷም ለአንድ ክፍለ ዘመን ተኩል አሃዳዊ ሆኖ
ቆይቷል፡፡ ከደርግ መደምሰስ ማግስት ግን ኢትዮጵያን በአንድ አሃዳዊ ስርአት ማስቀጠል እንደማይቻል ግልፅ ነበር፡፡ በፌደራላዊ ስርአት
መተዳደር ነበረባት፡፡ ይህ አንዳንድ ወገኖች እንደሚሉት የፖለቲካ ሃይሎች ጠባብ ፍላጎት የፈጠረው አይደለም”” የፌደራላዊ ስርአተ መንግስት አወቃቀር
የኢትዮጵያ ህዝብ ነባራዊና ህሊናዊ ዝግጅት ያልፈጠረው አድርጎ መመልከት የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረ ሰቦች ለዘመናት /በሰላ መልኩ ደግሞ
ለ17 አመታት/ ያካሄዱትን ትግልና መስዋእትነት ላይ የሚፈፀም ክህደት ነው፡፡
ከመንግስት ቅርፅ አንፃር በአለማችን ከሁለት
ደርዘን የማያንሱ በፌደራል ስርአት የሚተዳደሩ ሃገራት የአለም ህዝብን 40 በመቶ የሚይዙ መሆናቸውን ስንመለከት የፌደራል አወቃቀር
በአመዛኙ የትላልቅ ሃገሮች አደረጃጀት መሆኑን ልብ እንላለን፡፡ በእርግጥ በቆዳ ስፋታቸው ጠበብ ያሉ ሃገራትም የፌደራሊዝም አደረጃጀትን
ይሆነኝ ብለው የተቀበሉ አሉ፡፡
ምክንያቱም ይህንን እንዲሆን የሚገፉ ሌሎች
ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ታሪካዊና ባህላዊ የየሃገራቱ ተጨባጭ እውነታዎችም ስላሉ”” ስለሆነም በየትኛው መመዘኛም ቢሆን ኢትዮጵያ
የፌደራል ስርአተ መንግስትን መምረጧ ቅቡል ያደርገዋል፡፡ ሩዋል ብሊንደንባቸር እና ሮናልድ ዋትስ የተባሉ ፀሃፍት ፌደራሊዝምን ተመራጭ
የሚያደርገው መሰረታዊ ምክንያት ለሰላምና መቻቻል በእጅጉ ተመራጭ መሆኑ በሚከተለው መልኩ ይነግሩናል፡፡
‹In the contemporary
world, federalism as a political idea has become increasingly important as a
way of peacefully reconciling unity and diversity within a political system.›
እርግጥ ነው እንዲህ ያለ አስተሳሰብ ዘግይቶ
የመጣ እንጂ ያኔ ኢትዮeያ ወደ ፌደራላዊ ካምፕ በተቀላቀለችበት ወቅት አልነበረም፡፡ ይልቁንስ በወቅቱ የዩጎዝላቪያ ፌደሬሽን መፈረካከስ
በፌደራሊዝም ላይ መጥፎ ጥላው በጣለበት አለማዊ ሁኔታ ነበር ፌደራላዊት ኢትዮጵያ የተጠነሰሰችው፡፡ አሁን አሁን ግን የፖለቲካ መሪዎች፣
ልሂቃን እና ጋዜጠኞች ፌደራሊዝም ጤናማ፣ ዋስትና ያለውና አዎንታዊ ፖለቲካዊ ተቋም መሆኑን እየተናገሩለት ይገኛሉ፡፡ ይሉናል ከላይ
የተጠቀስናቸው ሁለቱ ምሁራን ‹‹Federalism in a Changing World›› በሚለው ስራቸው፡፡
የሆነው ሆኖ በኢትዮጵያ በፌደራላዊ አወቃቀሩ
መሰረት የውስጥ አደረጃጀቷን ማስተካከል ግድ የሚል ነበር፡፡ የፌደራሊዝም ስርአተመንግስት በአንዳንድ ሀገሮች መንግስትን የማዋቀር
አንድ መንገድ ወይም ስልት ሲሆን ብሊንደንባቸር እና ዋትስ እንዳሉት በኢትዮጵያ ግን ከዚህም በላይ የጠለቀ ትርጉም ወይም አንደምታ
አለው፡፡
እርግጥ ነው ትላልቅ ሀገሮች የፌደራሊዝምን
መንገድ የሚመርጡት በአንድ የማዕከላዊ አስተዳዳር በተዋቀረ መንግስት ማስተዳደር ከባድ ስለሚሆንባቸው ነው፡፡ በኢትዮጵያ ግን በመሰረቱ
ከዚህ መነሻ በእጅጉ የተለየ ፖለቲካዊ መነሻ ነበረው፡፡ ኢትዮጵያ በፌደራሊዝም እንድትዋቀር የተደረገችው ከፊቷ የተደቀነው በአንድነት
የመቆየትና ያለመቆየት አደጋ ስለነበረ ነው፡፡ ብቸኛው ፍቱን መድሃኒትም ያ ስለነበረ ነው፡፡ ሌላ የተሻለ አማራጭ አልነበረም፡፡
ስለሆነም የፌደራል ስርአቱ ዋና ምሰሶ
የአንድነት በልዩነት ማወቀር ነው፡፡ ይህ ግን በተለይ ‹‹በፍፁማዊ አንድነት›› አቀንቃኞች ብቻ ሳይሆን በሌሎች ዜጎችም አዲሱ አወቃቀር
ሃገሪቷን ይበታትናታል ባልካናይዜሽን በኢትዮጵያ ይታያል የሚል ጭንቀት ነበራቸው፡፡ ሟርትም ጭምር”” የፌደራሊዝም ስርአቱ ሻምፒዮን ኢህአዴግ
ግን ይልቁንስ በኢትዮጵያ ቫልካናይዜሽን የሚፈጠረው በፌደራል የማዋቀሩ ድፍረት አጥተን ካፈገፈግን ብቻ ነው የሚል እምነት ያዘ፡፡
የግንባሩ ሊቀመንበር ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ይህንን እውነት በተለያያ ሚዲያ ሲገልፁት
ተደምጧል፡፡ በአንድ ወቅት ታላቁ መሪ መለስ ዜናዊ /ጥር 2011 እ ኤ አ/ ለሮይተርስ በሰጡት ማብራሪያ የምንፈራውን ቫልካናይዜሽን
መቀልበስ የምንችለው ለብሄር ብሄረሰቦች እውቅና የሰጠ ፌደራላዊ ስርአት ስንገነባ ብቻ ነው ነበር ያሉት፡፡ እኔም በዚህ ሃሳብ መቶ
በመቶ እስማማለሁ፡፡ ለዛሬ የፅሁፌ መቋጫም ይኸው ነው፡፡በሲቪል ሰርቪሱ የውስጥ መልካም አስተዳደር እመርታ ማረጋገጥ የከተማችንን የመንግስት ሠራተኞች እንደ ውስጥ ደንበኞች ቆጥሮ በየተቋሙ በማሳተፍ ፈጣን አገልግሎት መሰጠት ይኖርበታል
በከተማችን አዲስ አበባ መልካም አስተዳደርን የማረጋገጥ ትልቅ ተልእኮ
ከተሰጣቸው አካላት መካከል ዋነኛው ተቋም የሲቪል ሰርቪስ ተቋማትና በሲቪል ሰርቪስ ተቋማት ውስጥ የሚገኘው በቁጥር 80 ሺህ የሚሆነው
ሰራተኛ ነው፡፡ ይህ የሲቪል ሰርቪስ ሃይል በከተማችን እስከአሁን በመጡ የህዝብ የልማትና የተጠቃሚነት እቅዶች መሳካት ላይ ትልቅ
ድርሻ ተጫውቷል እየተጫወተም ይገኛል፡፡ ይህ ሃይል በዴሞክራሲያዊ ልማታዊ ሲቪል ሰርቪስ መስመር በመቅረፅ የህዝብ አገልጋይነት አስተሳሰብ
እንዲላበስ የማድረግ ጉዳይ ቁልፍ የአመራር ጉዳይ በመሆኑ ሰፋፊ የአቅም ግንባታ ስራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ፡፡ በከተማው እያደገ እና
እየሰፋ ከመጣው ልማትና የህዝብ ጥያቄ አንፃር ከሲቪል ሰርቪስ ሃይላችን የሚጠበቀው የአገልግሎት ቅልጥፍናና ጥራት በዛው ልክ ሰፊና
ውስብስብ እየሆነ መሄዱ አይቀርም፡፡ እስከአሁን ያለው ተጨባጭ ተሞክሯችንም የሚያረጋግጥልን ይህንን እውነታ ነው፡፡ አስተዳደሩም
የሲቪል ሰርቪስ ሃይላችን የትራንስፎርሜሽን እቅዶቻችንና በአጠቃላይ የህዳሴ ጉዟችን ማሳካት የሚችል የሲቪል ሰርቪስ ተቋማት፣ የሰው
ሃይልና ስምሪት ለመፍጠር የተለያዩ ስራዎች እየሰራ መጥቷል”” የሲቪል
ሰርቪስ ሃይላችን ለህዝብ የሚሰጠው አገልግሎት እርካታ እንዲያረጋግጥ ከሆነ የመጀመሪያውና መሰረታዊ ጉዳይ በተቋሙ ያለው ሰራተኛ
በተቋሙ ባለው መስተጋብርና ምህዳር እርካታ የሚሰማው መሆን አለበት፡፡ በሰራተኛውና በተቋሙ አመራር መካከል ያለው ግንኝነት ቅርብና
ዴሞክራሲያዊ መሆን ይኖርበታል፡፡
በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች አንድ ሊገነዘቡት የሚገባ ጉዳይ ‹‹በከተማችን በተለያዩ ተቋማት
ተቀጥረው የሚሰሩ ሠራተኞች የውስጥ ደንበኞቻችን ናቸው፡፡›› የሚል ፅኑ እምነትና አስተሳሰብ ሊኖራቸው ይገባል፡፡ ነገር ግን በየተቋሙ
ያሉ ኃላፊዎች ሠራተኞቻቸውን የማብቃትና እንደ ደንበኛ አይቶ ማስተናገድ በከተማችን ግንዛቤው ገና አላደገም”” የየተቋሙ ሠራተኞች በየመስሪያ ቤቱ ላሉ ተልዕኮዎችና ለሚሰሩት ተግባራት ወሳኞች መሆናቸው
መዘንጋት የለበትም፡፡ እንዲህ አይነት አስተሳሰብን ቁሳዊ በሆነ መልኩ ማረጋገጥ አይቻልም፡፡ ወሳኝ ስራው ጠንካራ የውስጥ የህዝብ
ግንኝነት ስራ ነው፡፡ የአስተሳብ ግንባታ ነው፡፡
የአስተሳሰብ ግንባታ ደግሞ የሚፈጠረው ሰፊ የአሳታፊነት ምህዳር በማመቻቸት ነው፡፡ በከተማችን
በሚገኙ መስሪያ ቤቶች ከላይ እስከ ታች ያሉትን ሠራተኞች በአግባቡ ሳናሳትፍና ሳናሳምን ተቋማቱ የተሟላ ህልውና ሊኖራቸውና ተልእኮአቸውን
በአግባቡ መወጣት ይችላሉ ብሎ በልበ ሙሉነት መናገርም አያስደፍርም፡፡ ተቋማቱ እንደ መስሪያ ቤት ውጤታማና ለህዝቡ የተሟላ አገልግሎት
መስጠት እንዲችሉ ከተፈለገ በቅድሚያ የውስጥ ሠራተኞች በአግባቡ ስራቸውን ሲወጡ ወይም አገልግሎት ሲሰጡ ብቻ ነው፡፡
ስለሆነም አንድ መስሪያ ቤት ብቁ ነው ስንል በተቋሙ የሚሰሩ ሠራተኞች ብቁ አገልግሎት የመስጠት
ችሎታ ሲኖራቸው ብቻ ነው፡፡ የመስሪያ ቤቶቹ ስኬትም ሆነ ውድቀት ምንጩ የውስጥ ሠራተኞቻቸው ካላቸው የጠራ አመለካከት መያዝ ወይም
አለመያዝ ጋር በቀጥታ የተቆራኘ እንደሚሆን መገመት አያዳግድትም፡፡ የጠራ አመለካከት የያዙ ሰራተኞች ተልእኮአቸውን ጠንቅቀው ይገነዘባሉ፡፡
በተነሳሽነትም ይሰራሉ፡፡ በተነሳሽነት የሚሰሩ ሠራተኞች ደግሞ ውጤት ያስመዘግባሉ፡፡
በተቃራኒው በተነሳሽነትና በኃላፊነት መንፈስ በማይሰራበት መስሪያ ቤት ውድቀት ይታያል፡፡
በከተማው በየጊዜው የሚካሄዱ የተቋማት ምዘናና ግምገማዎች ይህንን ያረጋግጣሉ፡፡ እስከአሁን የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያመላክቱት ለተቋማት
የአገልግሎት አሰጣጥ መሻሻል ልዩነት በተቋማቱ ከሚከፈለው ደሞወዝ ጋር ቀጥተኛ ትስስር የሌለው መሆኑን ያስረዳሉ፡፡ ስለሆነም የውስጥ
ሠራተኞች ህዝብን የሚያረካ አገልግሎት የሚሰጡት የተሻለ ደሞወዝ ስለሚከፈላቸው ወይም ተቀጣሪ በመሆናቸው ሳይሆን በተሟላ እምነት
እንዲሰሩ የሚያስችል ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር ለአንድ መስሪያ ቤት ውጤታማነት ወሳኝ ድርሻ አለው፡፡ ከዚህ አንፃር የውስጥ ሠራተኞች
በየተቋሙ ቁልፍ የጀርባ አጥንት ሰዎች ናቸው፡፡
በመሆኑም የውስጥ ደንበኞች (ሠራተኞች) ከውጭ ደንበኞች ባልተናነሰ እንክብካቤ ሊደረግላቸው
ይገባል፡፡ የሚያነሷቸው የመልካም አስተደደር ጥያቄዎች ሊፈቱላቸው ይገባል፡፡ የማይፈታ ጥያቄ ከሆነም ምክኒያቱ በግልፅ ቀርቦ መግባባት
ሊደረስበትና የጋራ አረዳድ ሊያዝበት ይገባል፡፡ በተሰጣቸው የስራ ድርሻ ብቻ ሳይታጠሩ በአጠቃላይ የተቀመጡ ስራዎች ላይ አስተያየት
እንዲሰጡና ሃሳብ እንዲያመነጩ ሊበረታቱ ይገባል፡፡ መደመጥ አለባቸው፣ መከበርም አለባቸው፡፡ ሲደመጡ ደግሞ ሁሉም ሰራተኛ በማንኛው
መልኩ በእኩል መታየት አለበት፡፡
ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው እያንዳንዱ ሰራተኛ በመስሪያ ቤቱ በሁሉም ጉዳዮች መሳተፍ አለበት፡፡ የተቋሙን ተልእኮና ራእይ
በትክክል እንዲገነዘብ መደረግ ይኖርበታል፡፡ ከእቅድ ዝግጅት እስከ ማጠቃለያ ምዕራፍ ያሉ የህዳሴ አመራር ዑደቶች ላይ በቂና እውነተኛ
ተሳትፎ ማደረግ አለበት፡፡ በተቋሙ በየደረጃው ያሉ አመራሮች የሰራተኞቻቸውን መደበኛ የግንኝነት ጊዜ በመመደብ ማወያየትና ማዳመጥ
አለባቸው፡፡ በአጠቃላይ ሰራተኛው በተቋሙ በዕድገት፣ በስልጠና በውሳኔ አሰጣጥ፣ በትምህርትና በአያያዝ በእኩልነት መሳተፍ ይኖርባታል፡፡
ይህንን ጉዳይ ከምንገኝበት የመድረኩ ጥያቄና ከልማታዊ ዴሞክራሲያዊ መንግስት ባህሪ አንፃር መመልከት ይገባናል፡፡ የውስጥ
ሠራተኞች በመንግስት ተቀጥረው ደሞዝ እየተከፈላቸው መሆኑ እውነት ነው፡፡ እነዚህ ሰራተኞች እንደ አምባገነን መንግስታት ‹‹የመንግስት
ሰራተኞች›› አይደሉም፡፡ የህዝብ አገልጋዮች ናቸው፡፡ በሚከፈላቸው ልክ ህዝቡን የማገልገል ኃላፊነት አለባቸው፡፡ ነገር ግን ደሞዝ
የሚከፈላቸው በመሆኑ ብቻ በተቀጣሪ አስተሳሰብ ስርአቱ የሚጠይቀውንና ደንበኛውን የሚያረካ ውጤት ያመጣሉ ማለት ግን የተሳሳተ አመለካከት
ነው፡፡ ሰራተኛው የምንገኝበትን ሀገራዊ መድረክ በሚገባ እንዲያውቀው ጠንካራ የህዝብ ግንኙነት ስራ መሰራት አለበት፡፡ እንዲህ አይነት
የተቋሙን የሰው ሃይል ወደ አንድ ተራማጅ አስተሳሰብ ለማድረስ ደግሞ ስራው መመራትም መሰራትም ያለበት በተቋሙ ዋና የህዝብ ግንኙነት
ሃላፊ ነው፡፡ የተቋሙ ዋና የህዝብ ግንኙነት ደግሞ የተቋሙ የበላይ ሃላፊ ነው”” ይህ
የተቋሙ ዋና የህዝብ ግንኝነት ሃላፊ ወይም አመራር የውስጥ ደንበኞች እርካታ መረጋገጫ እቅድ ማቀድ እቅዱን በጊዜ መሸንሸን፣ እድገቱና
ጉድለቱን ለመለካትም በየጊዜው ማወያየት፣ ግንባታ ማካሄድና መገምገም ይኖርበታል፡፡ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት በመስሪያ ቤቱ ያልተመቸው
ሠራተኛ ለውጭ ደንበኞች ተገቢ አገልግሎት ሊሰጥ አይችልም፡፡
ለዚህ ተጨባጭ ማሳያ የሚሆነው በቢሮው አስተዳደር አያያዝ ያልተደሰተ የውስጥ ሠራተኛ ቅሬታውን የሚወጣው በመስሪያ ቤቱ
ኃላፊዎች ሳይሆን ወደ መስሪያ ቤቱ በሚመጡት ደንበኞች ላይ ነው”” እርግጥ
ነው በደንበኞቹ ላይ በደል የሚፈፅምና የሚያመናጭቅ ሰራተኛ ሁሉ በተቋሙ ማግኘት ያለበትን ተገቢ ጥቅም ባለማግኘቱ ብቻ አይደለም”” ሌሎች የኪራይ ሰብሳቢነትና የቅንነት ችግሮችም ፍትሃዊና ተገቢ አገልግሎት እንዳይሰጥ ያደርጉታል፡፡
ዞሮ ዞሮ በየመስሪያ ቤቱ በሥራው ያልተደሰተና ያልተገባ ጥቅም የሚጠይቅ ሠራተኛ ፋይል ይደብቃል፡፡ ደንበኛን ደጋግሞ ያመላልሳል፡፡
ያንገላታል፡፡
የዚህ ፅሁፍ ዋና ትኩረት የውስጥ አያያዝን የሚመለከትና ይህ ጉድለት በተቋሙ ተልእኮ ላይ የሚያሳድረውን አሉታዊ ጫና
ማሳየት በመሆኑ ሌሎች ሰራተኛውን ቀልጣፋና ፍትሃዊ አገልግሎት እንዳይሰጥ የሚገፋፉ ጉዳዮችን ለጊዜው እንለፋቸው፡፡
በፅሁፉ መነሻ ለማየት እንደተሞከረው የውስጥ መልካም አስተደደር ሲጠፋ ሰራተኛው ደንበኛውን በማበሳጨት ንዴቱን መወጣጫ
ያደርገዋል”” በመስሪያ ቤቱ ባልደረቦችና የመስሪያቤቱ ኃላፊዎች ላይ በረባ ባልረባም
እንዲያማርር ያደርገዋል፡፡ ውስጣዊ የመሥራት ፍላጎቱ ይዳከማል፡፡ ውስጣዊ ፍላጎት የሌለው ሠራተኛ ሥራውን መጥላት ይጀምራል፡፡ ደንበኞችን
በአብዛኛው የሚያጉላሉ ሠራተኞች የውስጥ እርካታ የሌላቸው ሠራተኞች ናቸው ቢባል ከሃቅ የራቀ አይደለም፡፡
እንደዚህ አይነት ሠራተኞች ፍቃድ መጠይቅ ያበዛሉ፤ ለውጭ ደንበኞች ብቻ ሳሆን ለውስጥ ደንበኞች /ባልደረቦቻቸውም/ የሚመቹ
አይሆኑም፡፡ የመስሪያ ቤቱን ንብረት በጥንቃቄ መጠቀምና መያዝ ላይ ደንታ የሌላቸው ይሆናሉ፡፡ በመስሪያ ቤቱ ውጤት ቢያመጣም ባይመጣም
ደንታ የላቸውም፡፡ አላአግባቡ ጥቅም ፈላጊና ተነሳሽነት የሌላቸው ሠራተኞች ይሆናሉ፡፡ እንዲህ አይነት ሰራተኞች በቀላሉ አኩራፊ፣
ነጭናጫና የሥራ ዝግጁነትም የሌላቸው ናቸው፡፡ ደንበኛን የሚያከብር ስነ ምግባርም ሊኖራቸው አይችልም፡፡ በዚህ መሐል የሚጎዳው መስሪያ
ቤቱና የውጭ ደንበኛው ነው፡፡
በአጠቃላይ በተቋሙ የዴሞክራሲያዊ ግንኙነት መሳሳትና መዳከም በገነገነበት ተቋም ውስጥ የውስጥ ሠራተኛ ጉልበቱንና እውቀቱን
አሟጦ ይጠቀማል ማለት አስቸጋሪ ነው፡፡ ስለሆነም እውቀቱን አሟጦ እንዲጠቀምና ለደንበኛው በአግባቡ ለማገልገል መደመጥና ቀጣይ የአቅም
ግንባታ ማካሄድ ወሳኝነት አለው፡፡ በአግባቡ የተያዘ ሠራተኛ አመለካከቱ ጤናማ ሊሆን እንደሚችል መገመት ይቻላል፡፡
በአጠቃላይ የብዙ ስኬታማ መስሪያ ቤቶች የስኬታማነታቸው ሚስጥር የሆነው አመራሩና የውስጥ ሠራተኞቹ እጅና ጓንት ሆነው
ለመስራታቸው ነው፡፡ የየተቋሙ ኃላፊዎች ሠራተኞቹ እጅና ጓንት ሆነው በመስራቤታቸው ስኬት በጋራ በማሰብና መንቀሳቀስ በመቻላቸው
ነው”” አመራሩና ሠራተኛው ተናበው ሲሰሩ የተቀላጠፈ አገልግሎት ይሰጣሉ”” ስኬት ማምጣትም ይቻላል፡፡ የውጭ ደንበኛንም በአግባቡ የመያዝና የማስተናገድ ፍላጎት የሚመነጨው
የውስጥ ደንበኛው (ሠራተኛው) የተሟላ ግንባታና እንክብካቤ ሲደረግለት ብቻ ነው፡፡
በእርግጥ እንክብካቤ ሲባል የማይገባውን ጥያቄ ሲጠይቅ አመለካከቱን ማረም የለብንም ማለት አይደለም፡፡ ነገር ግን ሠራተኛው
የሚያነሳቸውን ጥያቄዎች በአግባቡ በማዳመጥ ምላሽ ማግኘት ይኖርበታል፡፡ ስለሆነም በአመራሩና በሠራተኛው የጋራ ፍላጎት እምነት እየተፈጠረ
ከሄደ ደንበኛን በአግባቡ ማገልገልና መያዝ ይጀመራል ማለት ነው፡፡ የአገልግሎት አሰጣጡም ቀልጣፍ ይሆናል፡፡ የየተቋሙ ኃላፊም ሆነ
ሠራተኛው ደንበኞቻቸውን በአክብሮትና በቅንነት ማገልገል ይጀምራሉ፡፡ ይህ ሲሆን በየተቋማቱ የመልካም ስም (Good will) ይጨምራል፡፡
በአጠቃላይ የውስጥ ሠራተኞችን መንከባከብና ማነቃቃት የውጭ ደንበኛን ለማርካትና አገልግሎትን ለማሻሻል መሠረታዊ ለውጥ
ማምጣት ይኖርብናል፡፡ ስለሆነም በከተማችን የሚገኙ የመንግስት ተቋማት ለህዝቡ ቀልጣፋና ፍትሃዊ አገልግሎት በመስጠት በመልካም አስተደደር
የሚያታየውን ጥልቀት ያለው ችግር ከመሰረቱ መፍታትና ከችግሩ መሻገር የሚችሉት በመጀመሪያ የውስጥ ደንበኛው /ሰራተኛው/ የሚያነሳቸውን
የውስጥ መልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ሲፈታ መሆኑን ተገንዝበው በመልካም አስተዳደር ዙሪያ ሁሉን አቀፍ እመርታ የመምጣት ጉዳይ ከቤታቸው
መጀመር አለባቸው፡፡
Subscribe to:
Posts (Atom)