Thursday, 7 April 2016

በሲቪል ሰርቪሱ የውስጥ መልካም አስተዳደር እመርታ ማረጋገጥ የከተማችንን የመንግስት ሠራተኞች እንደ ውስጥ ደንበኞች ቆጥሮ በየተቋሙ በማሳተፍ ፈጣን አገልግሎት መሰጠት ይኖርበታል




ከተማችን አዲስ አበባ መልካም አስተዳደርን የማረጋገጥ ትልቅ ተልእኮ ከተሰጣቸው አካላት መካከል ዋነኛው ተቋም የሲቪል ሰርቪስ ተቋማትና በሲቪል ሰርቪስ ተቋማት ውስጥ የሚገኘው በቁጥር 80 ሺህ የሚሆነው ሰራተኛ ነው፡፡ ይህ የሲቪል ሰርቪስ ሃይል በከተማችን እስከአሁን በመጡ የህዝብ የልማትና የተጠቃሚነት እቅዶች መሳካት ላይ ትልቅ ድርሻ ተጫውቷል እየተጫወተም ይገኛል፡፡ ይህ ሃይል በዴሞክራሲያዊ ልማታዊ ሲቪል ሰርቪስ መስመር በመቅረፅ የህዝብ አገልጋይነት አስተሳሰብ እንዲላበስ የማድረግ ጉዳይ ቁልፍ የአመራር ጉዳይ በመሆኑ ሰፋፊ የአቅም ግንባታ ስራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ፡፡ በከተማው እያደገ እና እየሰፋ ከመጣው ልማትና የህዝብ ጥያቄ አንፃር ከሲቪል ሰርቪስ ሃይላችን የሚጠበቀው የአገልግሎት ቅልጥፍናና ጥራት በዛው ልክ ሰፊና ውስብስብ እየሆነ መሄዱ አይቀርም፡፡ እስከአሁን ያለው ተጨባጭ ተሞክሯችንም የሚያረጋግጥልን ይህንን እውነታ ነው፡፡ አስተዳደሩም የሲቪል ሰርቪስ ሃይላችን የትራንስፎርሜሽን እቅዶቻችንና በአጠቃላይ የህዳሴ ጉዟችን ማሳካት የሚችል የሲቪል ሰርቪስ ተቋማት፣ የሰው ሃይልና ስምሪት ለመፍጠር የተለያዩ ስራዎች እየሰራ መጥቷል”” የሲቪል ሰርቪስ ሃይላችን ለህዝብ የሚሰጠው አገልግሎት እርካታ እንዲያረጋግጥ ከሆነ የመጀመሪያውና መሰረታዊ ጉዳይ በተቋሙ ያለው ሰራተኛ በተቋሙ ባለው መስተጋብርና ምህዳር እርካታ የሚሰማው መሆን አለበት፡፡ በሰራተኛውና በተቋሙ አመራር መካከል ያለው ግንኝነት ቅርብና ዴሞክራሲያዊ መሆን ይኖርበታል፡፡
በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች አንድ ሊገነዘቡት የሚገባ ጉዳይ ‹‹በከተማችን በተለያዩ ተቋማት ተቀጥረው የሚሰሩ ሠራተኞች የውስጥ ደንበኞቻችን ናቸው፡፡›› የሚል ፅኑ እምነትና አስተሳሰብ ሊኖራቸው ይገባል፡፡ ነገር ግን በየተቋሙ ያሉ ኃላፊዎች ሠራተኞቻቸውን የማብቃትና እንደ ደንበኛ አይቶ ማስተናገድ በከተማችን ግንዛቤው ገና አላደገም”” የየተቋሙ ሠራተኞች በየመስሪያ ቤቱ ላሉ ተልዕኮዎችና ለሚሰሩት ተግባራት ወሳኞች መሆናቸው መዘንጋት የለበትም፡፡ እንዲህ አይነት አስተሳሰብን ቁሳዊ በሆነ መልኩ ማረጋገጥ አይቻልም፡፡ ወሳኝ ስራው ጠንካራ የውስጥ የህዝብ ግንኝነት ስራ ነው፡፡ የአስተሳብ ግንባታ ነው፡፡
የአስተሳሰብ ግንባታ ደግሞ የሚፈጠረው ሰፊ የአሳታፊነት ምህዳር በማመቻቸት ነው፡፡ በከተማችን በሚገኙ መስሪያ ቤቶች ከላይ እስከ ታች ያሉትን ሠራተኞች በአግባቡ ሳናሳትፍና ሳናሳምን ተቋማቱ የተሟላ ህልውና ሊኖራቸውና ተልእኮአቸውን በአግባቡ መወጣት ይችላሉ ብሎ በልበ ሙሉነት መናገርም አያስደፍርም፡፡ ተቋማቱ እንደ መስሪያ ቤት ውጤታማና ለህዝቡ የተሟላ አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ ከተፈለገ በቅድሚያ የውስጥ ሠራተኞች በአግባቡ ስራቸውን ሲወጡ ወይም አገልግሎት ሲሰጡ ብቻ ነው፡፡
ስለሆነም አንድ መስሪያ ቤት ብቁ ነው ስንል በተቋሙ የሚሰሩ ሠራተኞች ብቁ አገልግሎት የመስጠት ችሎታ ሲኖራቸው ብቻ ነው፡፡ የመስሪያ ቤቶቹ ስኬትም ሆነ ውድቀት ምንጩ የውስጥ ሠራተኞቻቸው ካላቸው የጠራ አመለካከት መያዝ ወይም አለመያዝ ጋር በቀጥታ የተቆራኘ እንደሚሆን መገመት አያዳግድትም፡፡ የጠራ አመለካከት የያዙ ሰራተኞች ተልእኮአቸውን ጠንቅቀው ይገነዘባሉ፡፡ በተነሳሽነትም ይሰራሉ፡፡ በተነሳሽነት የሚሰሩ ሠራተኞች ደግሞ ውጤት ያስመዘግባሉ፡፡
በተቃራኒው በተነሳሽነትና በኃላፊነት መንፈስ በማይሰራበት መስሪያ ቤት ውድቀት ይታያል፡፡ በከተማው በየጊዜው የሚካሄዱ የተቋማት ምዘናና ግምገማዎች ይህንን ያረጋግጣሉ፡፡ እስከአሁን የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያመላክቱት ለተቋማት የአገልግሎት አሰጣጥ መሻሻል ልዩነት በተቋማቱ ከሚከፈለው ደሞወዝ ጋር ቀጥተኛ ትስስር የሌለው መሆኑን ያስረዳሉ፡፡ ስለሆነም የውስጥ ሠራተኞች ህዝብን የሚያረካ አገልግሎት የሚሰጡት የተሻለ ደሞወዝ ስለሚከፈላቸው ወይም ተቀጣሪ በመሆናቸው ሳይሆን በተሟላ እምነት እንዲሰሩ የሚያስችል ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር ለአንድ መስሪያ ቤት ውጤታማነት ወሳኝ ድርሻ አለው፡፡ ከዚህ አንፃር የውስጥ ሠራተኞች በየተቋሙ ቁልፍ የጀርባ አጥንት ሰዎች ናቸው፡፡
በመሆኑም የውስጥ ደንበኞች (ሠራተኞች) ከውጭ ደንበኞች ባልተናነሰ እንክብካቤ ሊደረግላቸው ይገባል፡፡ የሚያነሷቸው የመልካም አስተደደር ጥያቄዎች ሊፈቱላቸው ይገባል፡፡ የማይፈታ ጥያቄ ከሆነም ምክኒያቱ በግልፅ ቀርቦ መግባባት ሊደረስበትና የጋራ አረዳድ ሊያዝበት ይገባል፡፡ በተሰጣቸው የስራ ድርሻ ብቻ ሳይታጠሩ በአጠቃላይ የተቀመጡ ስራዎች ላይ አስተያየት እንዲሰጡና ሃሳብ እንዲያመነጩ ሊበረታቱ ይገባል፡፡ መደመጥ አለባቸው፣ መከበርም አለባቸው፡፡ ሲደመጡ ደግሞ ሁሉም ሰራተኛ በማንኛው መልኩ በእኩል መታየት አለበት፡፡
ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው እያንዳንዱ ሰራተኛ በመስሪያ ቤቱ በሁሉም ጉዳዮች መሳተፍ አለበት፡፡ የተቋሙን ተልእኮና ራእይ በትክክል እንዲገነዘብ መደረግ ይኖርበታል፡፡ ከእቅድ ዝግጅት እስከ ማጠቃለያ ምዕራፍ ያሉ የህዳሴ አመራር ዑደቶች ላይ በቂና እውነተኛ ተሳትፎ ማደረግ አለበት፡፡ በተቋሙ በየደረጃው ያሉ አመራሮች የሰራተኞቻቸውን መደበኛ የግንኝነት ጊዜ በመመደብ ማወያየትና ማዳመጥ አለባቸው፡፡ በአጠቃላይ ሰራተኛው በተቋሙ በዕድገት፣ በስልጠና በውሳኔ አሰጣጥ፣ በትምህርትና በአያያዝ በእኩልነት መሳተፍ ይኖርባታል፡፡
ይህንን ጉዳይ ከምንገኝበት የመድረኩ ጥያቄና ከልማታዊ ዴሞክራሲያዊ መንግስት ባህሪ አንፃር መመልከት ይገባናል፡፡ የውስጥ ሠራተኞች በመንግስት ተቀጥረው ደሞዝ እየተከፈላቸው መሆኑ እውነት ነው፡፡ እነዚህ ሰራተኞች እንደ አምባገነን መንግስታት ‹‹የመንግስት ሰራተኞች›› አይደሉም፡፡ የህዝብ አገልጋዮች ናቸው፡፡ በሚከፈላቸው ልክ ህዝቡን የማገልገል ኃላፊነት አለባቸው፡፡ ነገር ግን ደሞዝ የሚከፈላቸው በመሆኑ ብቻ በተቀጣሪ አስተሳሰብ ስርአቱ የሚጠይቀውንና ደንበኛውን የሚያረካ ውጤት ያመጣሉ ማለት ግን የተሳሳተ አመለካከት ነው፡፡ ሰራተኛው የምንገኝበትን ሀገራዊ መድረክ በሚገባ እንዲያውቀው ጠንካራ የህዝብ ግንኙነት ስራ መሰራት አለበት፡፡ እንዲህ አይነት የተቋሙን የሰው ሃይል ወደ አንድ ተራማጅ አስተሳሰብ ለማድረስ ደግሞ ስራው መመራትም መሰራትም ያለበት በተቋሙ ዋና የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ ነው፡፡ የተቋሙ ዋና የህዝብ ግንኙነት ደግሞ የተቋሙ የበላይ ሃላፊ ነው”” ይህ የተቋሙ ዋና የህዝብ ግንኝነት ሃላፊ ወይም አመራር የውስጥ ደንበኞች እርካታ መረጋገጫ እቅድ ማቀድ እቅዱን በጊዜ መሸንሸን፣ እድገቱና ጉድለቱን ለመለካትም በየጊዜው ማወያየት፣ ግንባታ ማካሄድና መገምገም ይኖርበታል፡፡ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት በመስሪያ ቤቱ ያልተመቸው ሠራተኛ ለውጭ ደንበኞች ተገቢ አገልግሎት ሊሰጥ አይችልም፡፡
ለዚህ ተጨባጭ ማሳያ የሚሆነው በቢሮው አስተዳደር አያያዝ ያልተደሰተ የውስጥ ሠራተኛ ቅሬታውን የሚወጣው በመስሪያ ቤቱ ኃላፊዎች ሳይሆን ወደ መስሪያ ቤቱ በሚመጡት ደንበኞች ላይ ነው”” እርግጥ ነው በደንበኞቹ ላይ በደል የሚፈፅምና የሚያመናጭቅ ሰራተኛ ሁሉ በተቋሙ ማግኘት ያለበትን ተገቢ ጥቅም ባለማግኘቱ ብቻ አይደለም”” ሌሎች የኪራይ ሰብሳቢነትና የቅንነት ችግሮችም ፍትሃዊና ተገቢ አገልግሎት እንዳይሰጥ ያደርጉታል፡፡ ዞሮ ዞሮ በየመስሪያ ቤቱ በሥራው ያልተደሰተና ያልተገባ ጥቅም የሚጠይቅ ሠራተኛ ፋይል ይደብቃል፡፡ ደንበኛን ደጋግሞ ያመላልሳል፡፡ ያንገላታል፡፡
የዚህ ፅሁፍ ዋና ትኩረት የውስጥ አያያዝን የሚመለከትና ይህ ጉድለት በተቋሙ ተልእኮ ላይ የሚያሳድረውን አሉታዊ ጫና ማሳየት በመሆኑ ሌሎች ሰራተኛውን ቀልጣፋና ፍትሃዊ አገልግሎት እንዳይሰጥ የሚገፋፉ ጉዳዮችን ለጊዜው እንለፋቸው፡፡
በፅሁፉ መነሻ ለማየት እንደተሞከረው የውስጥ መልካም አስተደደር ሲጠፋ ሰራተኛው ደንበኛውን በማበሳጨት ንዴቱን መወጣጫ ያደርገዋል”” በመስሪያ ቤቱ ባልደረቦችና የመስሪያቤቱ ኃላፊዎች ላይ በረባ ባልረባም እንዲያማርር ያደርገዋል፡፡ ውስጣዊ የመሥራት ፍላጎቱ ይዳከማል፡፡ ውስጣዊ ፍላጎት የሌለው ሠራተኛ ሥራውን መጥላት ይጀምራል፡፡ ደንበኞችን በአብዛኛው የሚያጉላሉ ሠራተኞች የውስጥ እርካታ የሌላቸው ሠራተኞች ናቸው ቢባል ከሃቅ የራቀ አይደለም፡፡
እንደዚህ አይነት ሠራተኞች ፍቃድ መጠይቅ ያበዛሉ፤ ለውጭ ደንበኞች ብቻ ሳሆን ለውስጥ ደንበኞች /ባልደረቦቻቸውም/ የሚመቹ አይሆኑም፡፡ የመስሪያ ቤቱን ንብረት በጥንቃቄ መጠቀምና መያዝ ላይ ደንታ የሌላቸው ይሆናሉ፡፡ በመስሪያ ቤቱ ውጤት ቢያመጣም ባይመጣም ደንታ የላቸውም፡፡ አላአግባቡ ጥቅም ፈላጊና ተነሳሽነት የሌላቸው ሠራተኞች ይሆናሉ፡፡ እንዲህ አይነት ሰራተኞች በቀላሉ አኩራፊ፣ ነጭናጫና የሥራ ዝግጁነትም የሌላቸው ናቸው፡፡ ደንበኛን የሚያከብር ስነ ምግባርም ሊኖራቸው አይችልም፡፡ በዚህ መሐል የሚጎዳው መስሪያ ቤቱና የውጭ ደንበኛው ነው፡፡
በአጠቃላይ በተቋሙ የዴሞክራሲያዊ ግንኙነት መሳሳትና መዳከም በገነገነበት ተቋም ውስጥ የውስጥ ሠራተኛ ጉልበቱንና እውቀቱን አሟጦ ይጠቀማል ማለት አስቸጋሪ ነው፡፡ ስለሆነም እውቀቱን አሟጦ እንዲጠቀምና ለደንበኛው በአግባቡ ለማገልገል መደመጥና ቀጣይ የአቅም ግንባታ ማካሄድ ወሳኝነት አለው፡፡ በአግባቡ የተያዘ ሠራተኛ አመለካከቱ ጤናማ ሊሆን እንደሚችል መገመት ይቻላል፡፡
በአጠቃላይ የብዙ ስኬታማ መስሪያ ቤቶች የስኬታማነታቸው ሚስጥር የሆነው አመራሩና የውስጥ ሠራተኞቹ እጅና ጓንት ሆነው ለመስራታቸው ነው፡፡ የየተቋሙ ኃላፊዎች ሠራተኞቹ እጅና ጓንት ሆነው በመስራቤታቸው ስኬት በጋራ በማሰብና መንቀሳቀስ በመቻላቸው ነው”” አመራሩና ሠራተኛው ተናበው ሲሰሩ የተቀላጠፈ አገልግሎት ይሰጣሉ”” ስኬት ማምጣትም ይቻላል፡፡ የውጭ ደንበኛንም በአግባቡ የመያዝና የማስተናገድ ፍላጎት የሚመነጨው የውስጥ ደንበኛው (ሠራተኛው) የተሟላ ግንባታና እንክብካቤ ሲደረግለት ብቻ ነው፡፡
በእርግጥ እንክብካቤ ሲባል የማይገባውን ጥያቄ ሲጠይቅ አመለካከቱን ማረም የለብንም ማለት አይደለም፡፡ ነገር ግን ሠራተኛው የሚያነሳቸውን ጥያቄዎች በአግባቡ በማዳመጥ ምላሽ ማግኘት ይኖርበታል፡፡ ስለሆነም በአመራሩና በሠራተኛው የጋራ ፍላጎት እምነት እየተፈጠረ ከሄደ ደንበኛን በአግባቡ ማገልገልና መያዝ ይጀመራል ማለት ነው፡፡ የአገልግሎት አሰጣጡም ቀልጣፍ ይሆናል፡፡ የየተቋሙ ኃላፊም ሆነ ሠራተኛው ደንበኞቻቸውን በአክብሮትና በቅንነት ማገልገል ይጀምራሉ፡፡ ይህ ሲሆን በየተቋማቱ የመልካም ስም (Good will) ይጨምራል፡፡
በአጠቃላይ የውስጥ ሠራተኞችን መንከባከብና ማነቃቃት የውጭ ደንበኛን ለማርካትና አገልግሎትን ለማሻሻል መሠረታዊ ለውጥ ማምጣት ይኖርብናል፡፡ ስለሆነም በከተማችን የሚገኙ የመንግስት ተቋማት ለህዝቡ ቀልጣፋና ፍትሃዊ አገልግሎት በመስጠት በመልካም አስተደደር የሚያታየውን ጥልቀት ያለው ችግር ከመሰረቱ መፍታትና ከችግሩ መሻገር የሚችሉት በመጀመሪያ የውስጥ ደንበኛው /ሰራተኛው/ የሚያነሳቸውን የውስጥ መልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ሲፈታ መሆኑን ተገንዝበው በመልካም አስተዳደር ዙሪያ ሁሉን አቀፍ እመርታ የመምጣት ጉዳይ ከቤታቸው መጀመር አለባቸው፡፡

1 comment: