ጓዲት ሮማን ገብረ ስላሴ ገና ለጋ ተማሪ እያለች በ1962ዓ.ም ነበር በሀገራችን ተንሰራፍቶ የቆየውን የፊውዳል ስርዓት ለመገርሰስ አርሶ አደሩ፣ ተማሪውና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች በሚያካሄዱት ፀረ-ፊውዳል የትግል እንቅስቃሴ ውስጥ መሳተፍ የጀመረችው፡፡ በኋላም በጦር መሳሪያ ሃይል ወደ ስልጣን የመጣው ደርግ ሰላማዊ ፖለቲካዊ ትግልን በአዋጅ በመከልከሉ የወቅቱ ብቸኛና ዘላቂ አማራጭ መፍትሄ ፋሽስታዊውን የደርግ ስርዓት በረዥም የትጥቅ ትግል ማስወገድ ስለነበር ጓዲት ሮማንም በ1968 ዓ.ም ወደ ትጥቅ ትግሉ አሃዱ ብላ ተቀላቀለች። በዚያም በቅድሚያ የሚሰጣትን ፖለቲካዊና ወታደራዊ ስልጠና በብቃት ከጨረሰች በኋላ ለተወሰነ ጊዜ ሬዲዮ ኦፕሬተርነት አገለገለች። ቀጥላም የህክምና ስልጠና ከወሰደች በኋላ ሃኪምና የፖለቲካ መምህር ሆና ሰራች። ብዙውን ጊዜ ያገለገለችው ግን የትጥቅ ትግሉ መሰረት በሆነው ህዝብን በማደራጀትና በማነሳሳት ስራ ላይ ነበር። ይህንንም ስራዋን በትግራይና ሱዳን ውስጥ በወረዳና በዞን የኃላፊነት ደረጃዎች በተለይ በሴቶች ማህበር አመራር ሆና ሰርታለች። ሽሬ ውስጥ የህዝብ አስተዳዳሪም ነበረች። ከድል በኋላም በትግራይ ሴቶች ማህበር፣ የሴቶች ጉዳይ ቢሮና የካቢኔ አባል ሆናም አገልግላለች። በተጨማሪም በተለያዩ ደረጃዎች በትግራይ ክልል ምክር ቤት አባልነት፣ በትግራይ ልማት ማህበር፣ በትግራይ ሴቶች ማህበር እና በቀይ መስቀል ቦርድ አባልነት ሰፊ አገልግሎት ሰጥታለች። በ2ዐዐ2 በተካሄደው አገራዊ ምርጫ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ሆና በመመረጥ የመንግስት ረዳት ተጠሪ ሚኒስትር ዴኤታ ሆና ከተሾመች በኋላ በሰው ሃብት ልማት ስትሰራ ቆይታለች። ከ2ዐዐ5 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ሆና ሀገሯን እያገለገለች ትገኛለች፡፡
የትግሉ መነሻና መድረሻ
እንደ ወቅቱ ወጣት ታጋዮች ሁሉ ጓዲት ሮማን ገብረስላሴም ወደ ትጥቅ ትግል ለመግባት የተነሳሳችው በሀገራችን ሰፍነው የቆዩት አፋኝ ስርዓቶች በህዝቦች ጫንቃ ላይ የጫኑትን የግፍና የጭቆና ቀንበር ለማስወገድና በምትኩ የህዝቦችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ከፍተኛ ፍላጎት ስለነበራት ነው።
በ1960ዎቹ መጀመሪያ ይካሄዱ የነበሩት ፀረ-ፊውዳል ስርዓት የትግል እንቅስቃሴዎች ስርዓቱን ለመገርሰስ የራሳቸው ሚና ቢኖራቸውም ትግሉ በተደራጀ ፖለቲካዊ ሃይል ስላልተመራ የ1966 ህዝባዊ አብዮት በወታደራዊ ቡድን ተነጠቀና ፋሽስታዊ ደርግ በትረ ስልጣኑን ጨበጠ፡፡ አምባገነኑ ደርግም በህዝቦች ሲነሱ ከነበሩት ጥያቄዎች መካከል“መሬት ላራሹ” የምትለዋን ከዴሞክራሲ በተነጠለ ጥገናዊ መልኩ ብቻ ሲመልስ፣ ህዝባዊ መንግሥት ይቋቋም፣ የብሔር ብሔረሰቦች እኩልነት ይረጋገጥ፣
ወዘተ ለሚሉት ጥያቄዎች ለመመለስ የሚችል ባህሪና አላማ አልነበረውም። እንዳውም ከ1967 ጀምሮ ሰላማዊ ፖለቲካዊ ትግል ለማካሄድ የማይቻልበት ሁኔታ ተፈጠረ። ከዚህ በኋላ ነበር ጓዲት ሮማንም ወደ ትጥቅ ትግሉ የተቀላቀለችው።
በፍፁም አስቤው አላውቅም!
“አሁን የተገኙትን ድሎች በህይወት ቆይቼ ማየት እችላለሁ ብዬ በፍፁም አስቤ አላውቅም። በወቅቱ የሁላችንም ታጋዮች አስተሳሰብ እኛ ተሰዉተን ለህዝባችን ለውጥ እናመጣለን የሚል ነው፡፡ ራዕያችንና እምነታችን በህይወት ቆይተን ለድል እንበቃለን የሚል አልነበረም። መርሃችንም ከባድ ፈተናና ችግር ሲያጋጥመን እኔ ልቅደም የሚል ነበር። ለጥሩ ነገር ሲሆን ደግሞ ቅድሚያ ለጓዶቼ ነው መርሁ። በመሆኑም ከድል በኋላ እንድትቆይ ምኞቱም ፍላጐቱም አልነበረንም፡፡ በሌላ በኩል የትጥቅ ትግሉ ከባድ ጦርነት የሚካሄድበት ብቻ አልነበረም። በእኛና በፀረ ሕዝቡ ደርግ መሃል ያለው የሰው ሃይል መጠን፣ የትጥቅ ብዛትና ዓይነት በፍጹም የማይመጣጠን ነበር፡፡ ጦርነቱ ተከታታይና ፋታ የማይሰጥ በየቀኑ የሰው ህይወት ዋጋ የሚከፈልበት ሆኖ ሳለ ታጋዮች በእምነትና በቆራጥነት የሚታገሉበት እንጂ ለመስዋዕትነት ወደ ኋላ የሚሉበት ሁኔታ አልነበረም፡፡” ትላለች ጓዲት ሮማን።
“ትግላችን ረዥምና መራራ ነው፤ ድል ማድረጋችን የማይቀር ነው”
የትግሉ ዋነኛ ዓላማ የነበረው አስከፊው የጭቆና ስርዓት ተወግዶ የህዝቦች መብት፣ እኩልነትና ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ በፅናትና ቁርጠኝነት መታገል ነው፡፡ ስለሆነም ሁኔታው የነበረው አስከፊ ጭቆና፣ግፍና ግድያ በፅናት እንድትታገል ያደርግሃል። የሰው ህይወት በየቀኑ ሲቀጠፍ፣ አካል ሲጐድል፣ ከዚያም ባለፈ ፀረ- ህዝቡ ደርግ ትግሉን በአፍላ እድሜው ከቦ ሊያጠፋው ሲሞክር በጽናት ታግሎ ለማሸነፍ ብርቱ ፅናትን ይጠይቃል
””
በአጠቃላይም በትጥቅ ትግሉ ወቅት በየጊዜው ፈታኝና እልህ አስጨራሽ ፈተናዎች አጋጥመዋል።በዚህ ፈታኝ ወቅት በታጋዩ ዘንድ የነበረው የዓላማ ጽናት እንዴት ይገለጻል? እስኪ ጓዲት ሮማን የምታስታውሳቸውን አብነቶች እንመልከት፦
በ1969 ሸራሮ አካባቢ የነበረው የህወሓት ሰራዊት በቁጥር በጣም ጥቂት ነበር። በዚህ ጊዜ ቁጥሩ ከ12 ሺህ በላይ የነበረው የኢድዩ ጦር የህወሓትን ሰራዊት ከቦ ለመደምሰስ በተንቀሳቀሰበት ወቅት በፅናት ከባድ መስዋዕትነት ተከፍሏል፡፡ በዚያ ውጊያ ከተሰዉ ታጋዮች መካከል እንደነ ሙሴ፣ ጀዓፈርና አልጋነሽ ወዘተ የከፈሉት መስዋዕትነት ለታጋዩም ለሽራሮ ሚሊሽያና ህዝብም የፅናት ተምሳሌት ሆኖ ይታወሳል። “ትግላችን ረዥምና መራራ ነው፤ ድል ማድረጋችን የማይቀር ነው” እያሉ ቁርጠኝነታቸውን አሳይተው አልፈዋል። የኢዲዩ ሰራዊት በጣም ብዙ ብቻ ሳይሆን ጨካኝም ስለነበር ከውጊያው
ሸሽቶ መሄድ ህዝቡን ለከፋ ችግር ማጋለጥ መሆኑን የተረዱት እነኝህ ቆራጥ ታጋዮች በዓላማቸው ፀንተው ላመኑበት ህዝባዊ አላማ ህይወታቸውን ገብረዋል። ይህ ዓይነቱ ጸንቶ የመታገል ተምሳሌት በመካናይዝድና በጦር ጀቶች የታገዙ የደርግ ውጊያዎችንም ጭምር ሊያሳይ ይችላል፡፡
በ1980 ዓ.ም ሓውዜን በደርግ አውሮኘላን ሲደበደብ በገበያ ላይ የነበሩ ህፃናት፣ ነፍሰ ጡሮች፣እናቶች፣ አሮጊቶች፣ ሽማግሌዎችና ወጣቶች በሙሉ በጅምላ ተጨፈጨፉ። በዚህ ጊዜ የተካሄደው የአውሮፕላን ድብደባ በአንድ ቀን እስከ 1500 ህዝብ ሲጨፈጨፍ የሰውና የእንስሳ ደም ተቀላቅሎ እንደ ጎርፍ ፈሰሰ። የሰው አካላት በአሰቃቂ ሁኔታ ተቆራርጦ በየቦታው ተበታተነ፡፡ ከጭፍጨፋው ማግስት ብሶትና ስቃይ የጠናበት ህዝብ በተለይም ወጣቱ የበለጠ በፅናት ወደ ትግሉ ጎረፈ። በህዝብ ላይ የደረሰው ግፍ ታጋዮች የጀመሩትን ትግል በፅናትና በቁጭት እንዲቀጥሉ አድርጓቸዋል። ህዝቡም የትግሉን ዓላማ
የተጋራው በመሆኑ ለደርግ ጭፍጨፋ አልተንበረከከም። ታጋዩና ህዝቡ ተዋህዶ በበለጠ ፅናትና ቁርጠኝነት ትግሉን ቀጠለ።
ሓውዜን በደርግ አውሮኘላን በተደበደበበት ወቅት ጓዲት ሮማን ሽሬ አስተዳዳሪ ከነበሩት ታጋዮች አንዷ ነበረች። ባለቤቷም በተመሳሳይ ስራ አዲግራት ነበር። አክሱምና ዓዲግራት የነበሩት ታጋዮች በሙሉ ወደ ሽሬ መጥተው ለሶስት ወራትየከተማውን ህዝብ አስተምረው ከከተሞች ለቀው ሲወጡ ነው ደርግ ከሓውዜን ጀምሮ ቀጣይነት ያለው ከፍተኛ የአየር ድብደባ፣ ያካሄደው። ከዚህም ሌላ በደርግ ባንዳዎች የተቀበሩ ፈንጂዎችም ጉዳት ያደርሱ ነበር። በዚህ ጊዜ ጓዲት ሮማን፣ ባለቤቷና ሌሎች ታጋዮች
ደርግ የሞት የሽረት ጭፍጨፋ እያካሄደ እንደሆነ በማመን ከህዝባቸው ጋር በሞት ፊት ቆመው ሞትን በዓላማ ፅናት ተጋፈጡት። በሙሉ ዝግጁነት ሁሉንም ዓይነት ዋጋ እየከፈሉ የ604 ኮርን ደመሰሱት። ከዚያ በኋላም በዘመቻ ሰላም በትግል፣ ዘመቻ ዋልልኝ፣ ዘመቻ ቴዎድሮስ፣ ዘመቻ ወጋገን፣ ዘመቻ ቢልሱማ ወልቂጡማ፣ ወዘተ በተከታታይ በፅናት ከድል ወደ ድል እየተሸጋገሩ እስከ የግንቦት 20 አይቀሬ ድል መዝለቅ ቻሉ። ሌሎች ከኢህአዴግ ታጋዮች የበለጠ ትጥቅና ሰራዊት የነበራቸው ድርጅቶች ህዝባዊ ባህርይ፣ ዓላማና ፅናት ስላልነበራቸው በየትግል ምዕራፉ እየተሸነፉ ለድል ሳይበቁ ቀሩ።
በትጥቅ ትግሉ ወቅት በተለይም በ1977 እነ ጓዲት ሮማን በርካታ ዘግናኝና አሳዛኝ ችግሮች አጋጠማቸው። “በጣም የማስታውሰውና የማይረሳኝ
ግን በ1977 ዓ.ም ያጋጠመን ድርቅና ረሃብ ነበር። በ1977 በአንድ በኩል አምባገነኑን የደርግ ስርዓት በጦር ሜዳ ስንፋለም አጋጣሚውን ተጠቅሞ
በእግረኛም በአውሮፕላንም ሲደበድበን፣ በሌላ በኩል የተፈጥሮ አደጋ ተጋርጦብን ያሳለፍነው አስከፊ የማይረሳ ጊዜ ነበር” ትላለች ጓዲት ሮማን። በዚህ ቀውጢ ጊዜ ሌላ አማራጭ በመጥፋቱ ድርጅቱ ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት የህዝቡን ህይወት ለማዳን ቀየውን እየለቀቀ ወደ ሱዳንና ሌሎች አካባቢዎች እንዲንቀሳቀስ ሲደረግ ህዝቡ ቁጥር ስፍር አልነበረውም። በጊዜው የነበረው ድርቅና ረሀብ ከማንም በላይ የሚዋደዱ ቤተሰቦችን፣
እናትና ልጅን ለያይቷል። ባል ሚስቱንና ልጆቹን ተለይቶ በየሄዱበት ሳይገናኙ ህይወታቸው አልፏል። ህፃናትና እናቶች፣ አረጋውያን በየቀኑ
ህይወታቸው ሲያልፍ ማየት ህዝባዊ ታጋዮች እጅግ ሰቆቃ ነበር። በዚህ ላይ የምድር ጦርነትና የአይሮፕላን ድብደባ ተጨምሮበት ምን ያህል ከባድ
እንደሆነ መገመት ይቻላል። ይሁን እንጂ ታጋዮች ምንም ተስፋ ሳይቆርጡ በፅናት በመታገላቸው ያ! ክፉ ቀን አልፎና ግንቦት 20/1983 የሰላም ፋና
በራ። ሰላም ተገኝቶ ለልማት ምቹ ሁኔታ ተፈጠረ። የህዝቦች መብት ተከበረ። በትክክለኛው ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ መስመራችን እየተጓዝን በመቀጠላችን አሁን ስንዴ ከመለመን እየተላቀቅን እንገኛለን። በቀጣይም ድህነትን እስከምናሸንፍ በፅናት ከታገልን መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሃገሮች ደረጃ እንደምንደርስ የሚያጠራጥር ነገር የለም።
አስቸጋሪ ነበር፤ አላስቸጋሪ አድርገነዋል”
የትጥቅ ትግሉ በተለይ ለሴቶች አስቸጋሪ አልሆነባቸውም ወይ? የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ ጓዲት ሮማን “ወቼ ጉድ! ብላ ረዘም ላለ ጊዜ
በትዝታ ወደ ኋላ ተመለሰች። መልሷ ግን እጥር ምጥን ያለ ነበር። “አስቸጋሪ ነበር፤ ግን አላስቸጋሪ አድረገነዋል” የሚል። በወቅቱ አስተሳሰብ ሴት ልጅ
መሳሪያ ታጥቃ ወደ ትግል የመግባት ጉዳይ በጣም ከባድ ነበር። በህብረተሰቡ እይታ ሴት ደካማና ፈሪ፣ ጥሩ ነገሮችን መስራት የማትችል፤ መማርና
ማስተዳደር የማትችል፣ በአጠቃላይ የሀገርና የለውጥ ጉዳይ የማይመለከታት፣ መብትም የሌላት ተደርጋ ነበር የምትታየው።
በመሰረቱ ለትግሉ መነሻ ከሆኑ የዴሞክራሲ ጥያቄዎች ውስጥ አንዱ የሴቶችን ጥያቄ የመመለስ ጉዳይ ነው። ለዚህም ተደራጅቶ መታገል ግድ
ነበር። ትግል ውስጥ ስትገባ ደግሞ ረዥም ርቀት መጓዝ፣ ውጣ ውረድ፣ ውሃ ጥም፣ ረሃብ፣ያለ ነው። ከዛም በላይ የአካል መጉደል፣ መሰዋእትነትና
ሌሎች ትግሉ የሚጠይቃቸውን ፈተናዎች ሁሉ ማለፍ ከባድ ነበር። ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ትግሉን አስቸጋሪ የሚያደርገው ከሁሉም በላይ አስተሳሰቡ
ነው። በህብረተሰቡ ውስጥ (በወንዱም በሴቷም) ሴቶች አይችሉም የሚል የተሳሰተ ከባድ አስተሳሰብ አለ። በርግጥ የትጥቅ ትግሉ ለሁሉም ከባድ
ነው። በተለይ ለሴቶች በአካላዊም ሆነ በተፈጥሮ ክስተቶች ምክንያት ሊከብድ ይችላል። ነገር ግን ማንኛውም ታጋይ ለአንድ አላማ መሳካት በፅናት
በቁርጠኝነት በመታገሉ ሁሉም እንደሚቻል በተግባር አረጋግጧል ትላለች ጓዲት ሮማን።
“እኛ ታጋይ ሴቶችም ከባዱን ነገር ችለን አስቸጋሪውን አላሰቸጋሪ አድርገን በተግባር አሳይተናል። አሁን ላይ ሆኜ ስመለከተው ይህን መሰሉን
ከባድ የፖለቲካና የትጥቅ ትግል ወጣት ሆነህ ሴትም ይሁን ወንድ አላማህን ለማሳካት ካመነክበት ምንም የሚከብድ ነገር እንደሌለ ነው የሚያሳየኝ።
በጦርነቱ ሴቶች በከፍተኛ ደረጃ አመራር እየሰጡ ድል ተጐናጽፈዋል። ነፃ በወጡ ገጠሮችና ከተሞች የሕዝብ አስተዳደር እንዲመሰረትና ዴሞክራሲያዊ
ስርዓት እንዲጠናከር መርተዋል። ተቀባይነትም አግኝተዋል። ስለሆነም በምክር ቤት ውስጥ እየተመረጡም እስከ 30 በመቶ ተሳትፈው ሕዝብን
ማስተዳደር ችለዋል። ሴቶች የህዝብ ጥያቄንና ችግርን ያዳምጣሉ፣ ፍትህም ይሰጣሉ የሚል እምነት ከህዝብ ዘንድ ማግኘት ተችሏል። ምንም ነገር
ቢከብድህ ለዓላማህ ጽኑ ከሆንክ ሁሉንም ፈተና በድል ተወጥተህ ማለፍ መቻል የሚያረካ ተግባር እንደሆነ መግለጽ እፈልጋለሁ” በማለት ሁኔታውን
ታብራራለች።
No comments:
Post a Comment