አዲሱ ኢትዮጵያዊነትና አሮጌው ኢትዮጵያዊነት የሚሉት ጽንሰ ሀሳቦች የሚለዩበት መሰረታዊ ነጥብ የሚመነጨው ኢትዮጵያዊ ማንነትን ከምንተረጉምበት መሰረታዊ ትርጓሜ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነትና የኢትዮጵያ አንድነት የቆሙበት መሰረታዊ መነሻ ኢትዮጵያዊነት በራሱ የቆመበት መሰረት የሚያርፈው ምን ላይ ነው ከሚለው ጥያቄ ይመነጫል፡፡ ከዚህ ውጪ ኢትዮጵያዊትንም ሆነ የኢትየጵያ አንድነትን ለመተርጎም የሚደረገው ጥረት ትክክለኛ ስዕልን ካለማስጨበጡም በላይ ባረጀ አስተሳሰብ ውስጥ መዋጥን ሊያስከትል ይችላል፡፡ የኢትዮጵያ ህዝቦች ለዘመናት በጋራ ኖረው፣ሀብት አፍርተው፣ ክፉና ደጉና አይተው ዘመናትን አስቆጥረዋል፡፡ በግዛት አንድነት ስም የቆመው የገዢ መደቡ የኢትዮጵያ አንድነት ፍላጎትና በህዝቡ ውስጥ ያለው ተጨባጭ ፍላጎት ለየቅል ሆነው ኖረዋል፡፡ ተፈቃቅደንና ተቻችለን አንድ የጋራ ቤት እንገንባ የሚለው የህዝብ ፍላጎት ወደ ጎን ተትቶ ኢትዮጵያ ማለት በአንድ ቀለም ልትቃኝ ይገባል በሚሉት የገዢ መደቡ ሀይሎች ለዘመናት ስንታመስ ኖረናል፡፡
ኢትዮጵያዊነት በፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ሊመጣ የማይችል ጉዳይ መሆኑንና ጉዳዩን የምንመለከትበትን አተያይ ማስተካከል ይገባናል በሚል መለስ ዜናዊ ይህንን ሁኔታ በሚከተለው መልኩ ይገልጹታል፡፡
‹‹ከሁሉ በፊት ሊታወቅ የሚገባው ነገር ቢኖር አንድ ህዝብ ኢትዮጵያዊ ነኝ ብሎ የሚያምነው ኢትዮጵያዊነቱ ስለተነገረው ይህንን በማስመልከት ሰፊ ፕሮፖጋንዳ ስለተነዛለት እንዳልሆነ
ነው፡፡ ኢትዮጵያዊ ነኝ ብሎ ሊያምንና ሊኮራ የሚያስችለው መብትና ጥቅሞች ካገኘ ብቻ ነው፣ ነጋሪ ሳያስፈልገው ኢትዮጵያዊነት የሚሰማው፡፡ በዜግነት፣ በኢትዮጵያዊነት ጥያቄ
ነጋሪና ተናጋሪ ሊኖር አይችልም፡፡›› ይላሉ፡፡አብዮታዊ ዴሞክራሲ በኤርትራና አንድነት ጥያቄ ላይ ገጽ 80 በኢትዮጵያ የሽግግር መንግስት ውስጥ ኢትዮጵያዊነትን በአዲስ ቅኝት መቃኘትን እንደ አጀንዳ ይዘው የቀረቡት መሪ መለስ ዜናዊ ናቸው፡፡ በየመድረኩ በጽንሰ ሀሳቡ ዙርያ ግልጽነት ለመፍጠር ጥረዋል፡፡ ደርግ የህዝቦች እኩልነት ለማረጋገጥ ብረት ያነገቡ
ህወሓትና ሌሎች አብዮታዊ ዴሞክራት ድርጅቶችን ገንጣይ አስገንጣይ ብሎ ይፈርጅ ስለነበር በተፈጠረው ጥርጣሬ ምክንያት ወዴት ልናመራ እንችላለን የሚለው ጥያቄ ጎልቶ የወጣ ነበር፡፡
በትጥቅ ትግሉ አሸናፊ ሆኖ የሚኒልክን ቤተ መንግስት የተረከበው አዲሱ መንግስት በተለይም ኤርትራን በተመለከተ ያራምደው የነበረው አቋም በመሃል ሀገር ባለው ህዝብ ዘንድ የደርግ ቅስቀሳ
ከፈጠረው ውዥንብር አኳያ ጥርጣሬን የፈጠረበት አጋጣሚ ታይቷል፡፡ በዚህም ምክንያት አዲሶቹ መሪዎች የኢትዮጵያን አንድነት በዘላቂነት የማስጠበቅ ሚና ሊኖራቸው አይችልም፣ ስለዚህ
እንደ ዩጎዝላቪያ እኛም የመነጣጠል እጣ ይገጥመናል የሚል ስጋትም አሳድሮ ነበር፡፡
አዲሱ ሀገራዊ መድረክ ኢትዮጵያዊያንን በአንድነት ማኖር የማይችል ነው ከሚለው ቅስቀሳ ባሻገር በወቅቱ የነበሩ የፖለቲካ ሀይሎች አዲሱን መንግስት የመነጣጠል ፖለቲካን እያረመደ ነው የሚል ስሞታ በተደጋጋሚ ያቀርቡ ነበር፡፡ በወቅቱ በተፈቀደው የነፃ ፕሬስ በመጠቀምም አዲሱ መንግስት የጎሳና የመነጣጠል ፖለቲካ በሀገራችን ለማስፈን እየጣረ መሆኑን በመግለጽ ለዚህም ህዝቡ
ትግል እንዲያደርግ እንደ መቀስቀሻ ተጠቅመውበታል፡፡ በአቶ መለስ ዜናዊ አመራር በተዘጋጀው ጽሁፍ ላይ እንደቀረበው የአዲሱ መድረክ ባህሪና ዋና ግብ የጎሳና የመነጣጠል ፖለቲካ ነውየሚሉ ወገኖች አቋም ስህተት እንደሆነ በማስመር ይህንኑ በሚከተለው መልክ ለማስቀመጥ ተችሏል፡፡
‹‹….. ባለንበት መድረክ ያለው ዋነኛ ፖለቲካ የጎሳና የመነጣጠል ፖለቲካ አይደለም፡፡ ህዝቦች ማንነታቸው ተጠብቆ፣ መብታቸውም ተከብሮላቸው የሚመሰርቱት የአዲስ ህዝባዊ
አንድነት ፖለቲካ ነው፡፡ ይህ የህዝባዊ አንድነት ፖለቲካ ከሁሉ በፊት ህዝቦች በየእለቱ ከሚኖሩት ህይወት በእኩልነት ላይ ለተመሰረተ አንድነት ምቹ ሁኔታ እንደተፈጠረ በተግባር በማሳየትና ከዚህ ጋርም ተያይዞም ያለፈው አንድነት የነበሩትን ጉድለቶች በግልጽ በማስቀመጥ፣ በመገንባት ላይ ያለው አንድነት ካለፈው በዓይነቱ የተለየ መሆኑን በማስገንዘብ፣ ህዝቦች በፍላጎታቸው አንድ ሲሆኑ ጥቅሞቻቸው ከማንኛውም ሌላ መንገድ በበለጠ እንደሚጠበቅላቸው በማስተማር እንደዚሁም
ከግዛት አንድነትም ሆነ ከመነጣጠል አመለካከት የሚነሳ ፕሮፖጋንዳን በሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ መንገድ በመመከት የሚካሄድ ፖለቲካ ነው፡፡››
አብዮታዊ ዴሞክራሲ በኤርትራና በአንድነት ጥያቄ ላይ ገጽ 36 የመድረኩ አጀንዳ ከላይ በቀረበው አቋም ግልጽ የተደረገ ቢሆንም ጥያቄዎች መነሳታቸውና የጥርጣሬ መንፈስን በህዝብ ውስጥ
የሚረጭበት ሁኔታ መፈጠሩ አልቀረም፡፡ በተለይ ብሔርና ብሔራዊ ማንነት አይነኬ አጀንዳ ሆኖ በመቆየቱ፣ በተዛባ ታሪካዊ ግንኙነታችን ዛሬን ለመቃኘት የሚሞክር ሀይል በመኖሩ፣ በርካታ
የታጠቁ ድርጅቶች የተጨቆነው ብሔራችንን ነፃ እናወጣለን የሚል አቋም ከመያዝ አልፈው በተዛባ የትግል ስልት የሚንቀሳቀሱትም ቁጥራቸው ቀላል ባለመሆኑ የጎሳ ፖለቲካ ሰፍኗል ለሚለው ክርክር
ማሳመኛ ተደርጎ ይቀርቡም ነበር፡፡
የሽግግር መንግስቱ ማዕበል የታለፈው ሀገር በማረጋጋት፣ ህገ መንግስት በማርቀቅና ከዚህ ቀደም ታስረው የነበሩ እጆችን በማፍታታት ወደ ምርትና ምርታማነት እንዲገቡ በማድረግ ነው፡፡ ከዚህ በኋላ የመጣው ጊዜ በአዲሱ ህገ መንግስት መሰረት የተፈጠረ አዳዲስ አስተዳደራዊ ክልሎች ቋንቋ፣ ባህልና ብሔራዊ ማንነትን መነሻ አድርገው መቋቋማቸው ነው፡፡ በየብሔረሰቡ ህዝቡ ፡፡ንቋው
ሲዳኝ፣ የትምህርት ቋንቋ አድርጎ ሲጠቀም፣ ባህላዊ ማንነቱን ያለገደብ ማንፀባረቅ ሲጀምር በህዝቦች እኩልነት ላይ የተመሰረተ ኢትዮጵያዊ አንድነት ይገነባል፡፡ ትልቁ ቁምነገር የሚያርፈው
ህዝቦች በቋንቋቸው መማራቸው፣ የዳኝነት ስርዓቱ በቋንቋቸው መሆኑ፣ ባህላቸው፣ ሃይማኖታዊ እኩልነታቸው መከበሩ ብቻ አይደለም፡፡
አዲሱ ኢትዮጵያዊነት በየብሔርና ብሔረሰቡ የተፈጠረው ይህንኑ ዓይነት ሁኔታ ወደመነጣጠልና መገነጣጠል ከማምጣት ይልቅ የሀገራዊ ጥንካሬ ምንጭ እየሆነ በመምጣቱ ነው፡፡ ኢትዮጵያ አንድ ቀለም ሳትሆን በህብረ ቀለማት ያሸበረቀች ሀገር መሆኗ እየጎላ መጣ፡፡ አንድ ቋንቋ ስንናገር የኢትዮጵያ አንድነት የሚረጋገጥ የሚመስላቸው የግዛት አንድነት ተከራካሪዎች አዲሱ ሀገራዊ ሁኔታ
ይበልጥ እያሳመናቸው መምጣት ጀመረ፡፡ አዲሱ ኢትዮጵያዊነት ካስገኛቸው ድሎች መካከል አንዱ የአንድነት መሰረቱ እያንዳንዱን ብሔር፣ ብሔረሰብና ህዝብ መብትና የእኩልነት መብቱን አምኖ
በመቀበል ኢትዮጵያዊነትን የኩራቱና የውበቱ ምንጭ አድርጎ እንዲቀበል በሚያደርግ አግባብ መቃኘቱ ነው፡፡
አሁን እየተገነባች ባለችው አዲሷ ኢትዮጵያ ወደኋላ ሊመለስ የሚችል ሁኔታ ሊፈጠር አይችልም፡፡ በርካታ ተጨባጭ ሁኔታዎች ተቀይረዋል፡፡ አስተሳሰቦች ካገኘነው ሀገራዊ ሰላምና አንድነት አኳያ
መቃኘት ጀምረዋል፡፡ በትርጓሜ ደረጃም ህዝቡ ውስጥ የኢትዮጵያን አንድነት መሰረቶች በውል የመገንዘብ ሁኔታው እየጨመረ መጥቷል፡፡
No comments:
Post a Comment