Saturday, 1 July 2017

በከተማችን አማካይ የቀን ገቢ ግብር ትመና በ1996 ዓ.ም እንዲሁም በ2003 ዓ.ም ተሰርቷል፡፡ የግብር ትመናው ለዚህ ተብሎ በወጣው አዋጅ የተደገፈ ቢሆንም የአሰራር መመሪያ አልነበረውም፡፡ አሁን ላይ አዋጁ በአዲስ አዋጅ ከመተካቱ በተጨማሪ መመሪያ ቁጥር 123/2009 ተግባር ላይ ውሏል”” ከስድስት አመታት በኋላም አማካይ የቀን ገቢ ግብር ትመና ተከናውኗል፡፡ አጠቃላይ የአሰራር ሂደቶችንና የተካተቱ አዳዲስ መረጃዎችን በሚመለከት ከአዲስ አበባ ከፍተኛ ግብር ከፋዮች ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ስራ አስኪያጅ ከአቶ አትክልት ገ/እግዚአብሄር ጋር ከህዳሴ ጋዜጣ ያደረጉትን ቃለ ምልልስ እንደሚከተለው አቅርበናል፡፡




ህዳሴ፡- የቀን ገቢ ግብር ትመና ስራ በምን መልኩ ሲከናወን ቆየ?

አቶ አትክልት፡- አጠቃላይ ሂደቱ ከዝግጅት ምዕራፍ ጀምሮ ሰናየው ሊያሰራ የሚችል የማስፈፀሚያ ዕቅድ ታቅዷል፡፡ ከሚመለከታቸው ባለ ድርሻ አካላት ጋር ውይይት ተደርጎበትም መተማመን ተፈጥሮበታል፡፡ በአሰራር መደገፍ ያለበትንም መመሪያ ቁጥር 123/2009 ተዘጋጅቷል”” ሌሎችም መረጃ ለመሰብሰብ የሚጠቅሙ ከቅፅ 001 እስከ ቅፅ 013 ያሉት የቀን ገቢ ትመና መረጃ መሰብሰቢያዎች ተዘጋጅተዋል፡፡ ሌላው አማካይ የቀን ገቢ ግምት የሚገምቱ አካላት ከየት ከየት ሴክተር መሆን አለባቸው የሚለውም በመመሪያው ጭምር ተመልሷል፡፡ አማካይ የቀን ገቢ መረጃ ሰብሳቢ ቡድን አራት አራት ሰው ሆኖ ተዋቅሯል፡፡ አማካይ የቀን ገቢ ግምት ምን ማለት ነው? በምን መልኩ መከናወን አለበት፣ አመላካቾቹ ምንድን ናቸው? በሚሉት እና በመሳሰሉት ለባለሙያዎቹ ዝርዝር ስልጠና ተሰጥቷል፡፡

ከዚህ ቡድን በተጨማሪ የኢንስፔክሽን ቡድንም ተቋቁሞ በሁሉም ወረዳዎች ስልጠና እንዲያገኝ ተደርጓል፡፡ የመረጃ አጣሪ ቡድንም አለ፡፡ ከዚህ ስልጠና በመቀጠልም ግብር ከፋዩንና የከተማችንን ነዋሪዎች እስከ ቀጠና ድረስ በየአደረጃጀቱ እንዲወያዩ ተደርጓል፡፡

በአጠቃላይ የዝግጅት ምዕራፉን በዝርዝር ገምግመናል፡፡ የተሳካ እንደነበርም አይተናል፡፡ ከዛም ከሚያዚያ 17 ጀምረን ወደ ትግበራ ምዕራፍ ገብተናል፡፡ አማካይ የቀን ገቢ ግምት በ1996 ዓ.ም ከተሰራ በኋላ በ2003 ዓ.ም ነው የተሰራው፡፡ በየሶስት አመቱ መሰራት ነበረበት”” ነገር ግን ባለፉት ስድስት ዓመታት አልሰራንም ነበር፡፡ ይህንን ታሳቢ በማድረግ አስፈላጊነቱን በማስፈፀሚያ እቅዳችን ጠቅሰናል፡፡ አንደኛው በየሶስት አመቱ መደረግ ነበረበት፤ በተለያዩ ምክንያቶች ስድስት ዓመት ቆይቷል፡፡ ሁለተኛው በአማካይ የቀን ገቢ ግምት ካለ ንግድ ፈቃድ የሚነግዱ በርካታ ነጋዴዎችን ወደ ስርዓቱ ለማስገባት፣ ሶሰተኛው ደግሞ የንግድ ፈቃድ ኑሯቸው ከዘርፋቸው ውጪ የሚነግዱም ስላሉ ከትርፉ እዳጌው ላይም መክፈል ከሚገባቸው አንፃር ልዩነት ስለ ሚኖር ይህንን ለማስተካከል ወደተግባር ተገብቷል፡፡

ሌላው ደግሞ የፌዴራል የገቢ ግብር አዋጅም ማሻሻያ ተደርጎበታል፡፡ ቀድሞ የነበረው የገቢ ግብር አዋጅ በአዋጅ ተሽሮ አዲስ አዋጅ ወጥቷል”” ይህ አዋጅ የደረጃ ለውጥ አድርጓል፡፡ ቀድሞ የነበረው አዋጅ እስከ 100 ሺህ ብር ዓመታዊ ሽያጭ ያለው ደረጃ ሐ ግብር ከፋይ ብሎ ነበር የሚያስቀምጠው፡፡ አሁን ግን እስከ 500 ሺህ ብር ተብሎ ተሻሽሏል፡፡ የበፊቱ አዋጅ የደረጃ ለ ግብር ከፋይ ከ100 ሺህ ብር በላይ ከ500 ሺህ ብር በታች ነበር፡፡ አሁን ግን ከ500 ሺህ ብር በላይ እስከ አንድ ሚሊዮን ብር ሆኗል፡፡ ደረጃ ሀ ከ500 ሺህ ብር በላይ ነበር በአዲሱ አዋጅ ከ1 ሚሊዮን ብር በላይ ሆኗል፡፡ ስለዚህ ይህንን ታሳቢ ያደረገ የደረጃ ምደባ መደረግ የግድ ብሏል፡፡ ይህ የደረጃ ምደባም በ2003 ዓ.ም በነበረው መረጃ ሳይሆን አሁን በተጨባጭ ባለው መረጃ መሰረት ነው፡፡ ምክንያቱም ቢዝነስ በባህሪ ያድጋል ባለበት ይቆማል ወይም ደግሞ ወደ ኋላ ሊመለስ ስለሚችል እንደ አዲስ ታይቷል፡፡

ሌላው ደግሞ የገንዘብ የመግዛት አቅም ነው፡፡ በ2003 ዓ.ም የነበረው የገንዘብ የመግዛት አቅም አሁን ካለው የተለየ በመሆኑ እንደ አዲስ ስራው ተከናውናል፡፡ ለደረጃ ሐ የተሰበሰበውን መረጃ ወዲያውኑ እንጠቀምበታለን”” ምክንያቱም የቁርጥ ግብር ከፋዮች ናቸው፡፡ የሂሳብ መዝገብ የማቅረብ ግዴታ በህጉም አልተቀመጠም፡፡ አይገደዱም፡፡ የደረጃ ሀ እና የደረጃ ለ ግብር ከፋዮች ግን የሂሳብ መዝገብ የማቅረብ ግዴታ አለባቸው፡፡ ስለዚህ አማካይ የቀን ገቢ ግምት መረጃው ለደረጃ ሀ ና ለ የሂሳብ መዝገብ መረጃ ካላቀረቡ በዚሁ መረጃ የግብር አወሳሰን ስርዓቱ ይከናወናል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ ያቀረቡት የሂሳብ መዝገብ በባለስልጣኑ በህገ አግባብ ተቀባይነት ከአጣ እና አማካይ የቀን ገቢ ግብር ትመና መረጃ መጠቀም አስፈላጊ ነው ብሎ ተቋሙ ካመነ ይጠቀምበታለ፡፡ ሂደቱ ከዝግጅት ምዕራፍ ጀምሮ ትግበራ ምዕራፍን በዚህ መልኩ ማየት ይቻላል፡፡

ህዳሴ፡- አማካይ የቀን ገቢ ትመናው በየሶስት ዓመቱ መሆን ሲገባው የተራዘመበት ምክንያት ምንድን ነው?
አቶ አትክልት፡- የቀን ገቢ ግብር ትመናው በየሶስት ዓመቱ መሰራት ሲገባው ለ6 ዓመት የተራዘመው የከተማ አስተዳደሩ እና የተለያዩ ኮሚቴዎች በጋራ ተቀናጅተው የሚሰሩት ስራ በመሆኑ የተመቻቸ ጊዜ ስለሚያስፈልግ ነው፡፡ ሌላው ምክንያት ደግሞ አዲሱ የፌዴራል የገቢ ግብር አዋጅም ይጠበቅ ነበር፡፡ እንደሚወጣ ይታወቅ ስለነበረ ማለት ነው፡፡

ህዳሴ፡- እስከ አሁን ሲደረግ ከነበረው የቀን ገቢ ትመና የዘንድሮው በምን መልኩ ይለያል?

አቶ አትክልት፡- ከእስካሁኑ የቀን ገቢ ግብር ግምቶች ለየት የሚያደርገው ከአሰራር አንፃር ስንመለከት እራሱን የቻለ ሊመራ የሚችል መመሪያ አልነበረም፡፡ በ1996 ዓ.ም እና ለ2003 ዓ.ም ባደረግነው፡፡ አሁን ግን ራሱን የቻለ ይህን ሊመራ የሚችል መመሪያ ወጥቶለት ነው የተሰራው፡፡ መመሪያ ቁጥር 123/2009 ዝርዝር ነገሮችን ይዟል”” ሌላው ለየት የሚያደርገው ዘንድሮ የሰጠነው ስልጠና ዘርዘር ያለ ነው”” ሰፋ ያለ ጊዜም የተሰጠው ነው የባለሙያዎች ስልጠና ከኤንስፔክሽን ጋር ተያይዞ ባለፉት ጊዜያት በዚህ ደረጃ አልነበረም፡፡ አሁን ግን እንደየ ወረዳው ተጨባጭ ሁኔታ ስፋትና ጥብበት የኢንስፔክሽን ኮሚቴዎች ተቋቁመው ይህንን ስራ የመደገፍ የመከታተል ሰራ ሲሰሩ ነበር፡፡ ሌላው ደግሞ ከከተማ እስከ ወረዳ የተጠናከረ ቅንጅት ነበር፡፡ አስተዳደሩም እራሱ ገብቶበት በተለየ መልኩ ሲደግፍና ሲከታተል ነበር፡፡ በእነዚህ እና በመሳሰሉት ከባለፈው ለየት ይላል ብሎ መውሰድ ይቻላል፡፡

ህዳሴ፡- በከተማችን ምን ያህል ግብር ከፋይ ነጋዴ ይገኛል? ከፍተኛ፣ መካከለኛና ዝቅተኛ ብለው ቢገልፁልን?
አቶ አትክልት፡- በከተማችን ወደ 331 ሺህ ግብር ከፋዮች አሉ”” ከእነዚህ ውስጥ ግምት የማይገመትላቸ በመረጃ የሚስተናገዱ አሉ፡፡ አማካይ የቀን ገቢ ግምት መወሰድ አለበት ብለን የተንቀሳቀስንባቸው እስከ 200 ሺህ ይደርሳሉ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ 68 በመቶው የደረጃ ሐ ግብር ከፋዮች ናቸው፡፡ 21 በመቶው ደግሞ ደረጃ ሀ ሲሆን ሌላው 11 በመቶ የሚሆነው የደረጃ ለ ግብር ከፋይ ነው፡፡ የእስካሁኑ መረጃ የሚያሳየው፡፡ የአሁኑ ግን ገና እየተሰራ ነው፤ ወደፊት እንገልፃለን፡፡

ህዳሴ፡- የቀን ገቢ ግምት የማይሰራላቸው የትኞቹ ዘርፎች ናቸው?

አቶ አትክልት፡- የማይገመትላቸው ግብር ከፋዮች በግልፅ በስልጠና ማንዋላችን ላይም ተቀምጠዋል፡፡ ለምሳሌ መረጃ የሚገኝባቸው አስመጭና ላኪ ከሆኑ አንገምትም፡፡ ምክንያቱም ሲያስመጣና ሲልክ መረጃ እናገኛለን”” ስራ ተቋራጮ ውል አላቸው፣ የኮንስትራክሽን መሳሪያ ኪራይ፣ መኪና ማከራየት፣ አማካሪነት፣ አስጎብኝና የጉዞ ወኪል፣ የውጪ አገር ስራና አሰሪ አገናኞች፣ ትራንስፖርትም የቁርጥ ግብር ከፋይ ነው፡፡ ይህን ያህል መጫን የሚችል መኪና ይህን ያህል ይከፍላል ተብሎ ተለይቷል”” ወፍጮ ቤቶችም ይህን ያህል ቋት ያለው ይህን ያህል ይከፍላል ተብሎ ተቀምጧል፡፡ በመሆኑም አማካይ የቀን ገቢ ግብር ትመና መረጃ መሰብሰብ የሚያስፈልገው ከነዚህ መሰል ዘርፎች ውጪ ለተመሰማሩ ነጋዴዎች ነው፡፡

ህዳሴ፡- በግብር ትመና ስራው ያጋጠሙ ችግሮችስ ምን ምን ናቸው? እንዴትስ ተፈቱ?

አቶ አትክልት፡- በአማካይ የቀን ገቢ ግምት መረጃ አሰባሰብ ያጋጠሙ ችግሮች በራሳችን ላይ በነበሩ ክፍተቶች አንደኛው በቀን በአንድ ቡድን ከ20 እስከ 25 ለሚሆኑት ነጋዴዎች አማካኝ የቀን ገቢ ግምት እንሰራለን ብለን ነበር ነገር ግን ከ7 እስከ 10 ነው አፈፃፀማችን”” በአንድ ወር ውስጥ እናጠናቅቃለን ባልነው መሰረት ለመጓዝ አዳጋች ነበር፡፡ ሁለተኛው ችግር በአማካይ የቀን ገቢ ግምት ሰብሳቢው ቡድን የሚሞሉ ቅፆችን በአግባቡ ያለመሙላት ችግር ይታይ ነበር፡፡ ወደ መረጃ ቋትም በየእለቱ እንዲገባ መመሪያው ያዝዝ ነበር፡፡ ማንጠባጠቦች ነበሩ፡፡ የኢንስፔክሽን ቡድኑ የድጋፍና ክትትል አግባብም በጠንካራ ዲሲፕሊን እንዲመራ ካስቀመጥነው አንፃር የተወሰነ ክፍተት ታይቷል፡፡ ገምግመን የማስተካከያ እርምጃ ወስደናል፡፡ ሌላኛው በግብር ከፋዩ ህብረተሰብ ያጋጠመን ችግር ነው”” ለሽያጭ የተዘጋጁ እቃዎችን መሰወር፣ ሱቆችን ማሳነስ፣ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ትክክለኛ መረጃ እንዳያገኝ የተለያዩ እንቅፋቶችን መፍጠር፣ ህፃናትን ማስቀመጥ፣ ቋንቋውን የማይናገሩ ልጆችን ማስቀመጥ፣ ሱቅ ዘግቶ መጥፋት የመሳሰሉት ተስተውለዋል፡፡

የግብር ከፋዮች አደረጃጀቶችም ስለነበሩ ከነሱ ጋር በመነጋገር ችግሩ ትርጉም ባለው መልኩ እንዲፈታ አድርገናል፡፡ የተወሰኑ ግለሰቦች ግን ተደጋጋሚ ስላስቸገሩ አማካኝ የቀን ገቢ መረጃውን ቀደም ብለንም አይተን ስለነበር በዚያ መሰረት ሰርተናል፡፡ ግብር ከፋዩ ቅሬታ ካለበት በህግና ስርዓቱ መሰረት አቅርበው የማታይ ይሆናል፡፡ አማካይ የቀን ገቢ ግብር መረጃ መሰብሰብ የጀመርነው ሚያዚያ 17 ነው፡፡ ነገር ግን ቡድኖቹ ቀደም ብለው የሚገምቱት ብሎክ ተሰጥቷቸው የአካል ምልከታ ለሁለት ቀን ያህል ስለ አደረጉ ቢዝነሳቸው ምን ይመስላል የሚለውን ቀድመው መረጃ ወስደዋል፡፡ ይህንን መረጃ መሰረት አድርገው ሰርተውታል፡፡
ህዳሴ፡- ግብር በሚተምኑ ባለሙያዎች በኩል የነበረው የኪራይ ሰብሳቢነት አስተሳሰብና ተግባርስ እንዴት ይገለፃል?
አቶ አትክልት፡- እንደዚህ አይነት ችግሮች አጋጥመዋል፤ በተወሰነ መልኩም ቢሆን፡፡ ‘እኔ ነኝ የምገምተው እንደዚህ አዋጡልን’ የሚሉና መሰል ችግሮች ነበሩ፡፡ ግብር ከፋዮች ወዲያውኑ ለባለ ስልጣን መስሪያ ቤቱ ጥቆማ አድርሰዋል፡፡ ችግር እንዳለባቸው የተጠቆሙትን ከቡድኑ እንዲወጡ የማድረግ ስራ ወዲያውኑ ሰርተናል፡፡ ከዚያም በተቋሙ አሰራ ርመሰረት እንዲጠየቁ እየተደረገ ነው፡፡ መረጃው እየተጣራ ማለት ነው”” መመሪያውም በዚህ አግባብ ስላስቀመጠ፡፡

ህዳሴ፡- የኪራይ ሰብሳቢነት አስተሳሰብና ተግባርን ለመከላከል ተቋሙ ምን አይነት አሰራር ዘርግቶ ተንቀሳቅሷል?

አቶ አትክልት፡- አሰራሩ በመመሪያ ቁጥር 123/2009 በግልፅ ተቀምጧል፡፡ ፀብ፣ ዝምድና ካለ ወዲያውኑ አሳውቆ ከኮሚቴው አባልነት የመውጣትና በሌላ አካል እንዲገመት የመጠየቅ መብት ለፈፃሚውም ለግብር ከፋዩም ተመላክቷል፡፡ ግብር ከፋዩም እከሌ ከኔ ጋር ዝምድና አለው ወይም ፀብ አለው ስለዚህ መገመት አይችልም የማለት መብት አለው፡፡
ከዚህ አሰራር ከተላለፈ ደግሞ የሰራተኛ አስተዳደር ህግ አለ፡፡ በዚያ አግባብ የሚጠየቅበት ግልፅ አሰራር ተዘርግቶ ወይይት ተደርጎበት
እናአምኖበት ነው የገባው፡፡ በተግባር ደግሞ ቅድመ እንዳልኩት ኪራይ ለመሰብሰብ ጥረት ያደረጉ አካላት ነበሩ፡፡ ከቡድኑ የማውጣትና በህግ አግባብ ተጠያቂ የማድረግ ስራ እየተከናወነ ነው፡፡ ስለዚህ ለኪራይ ሰብሳቢነት አስተሳሰብና ተግባር ተገቢው እርምጃ ቀደም ብሎ በአሰራር መመሪያው ተገልጿል፡፡ ቅፆችን ግልፅ የማድረግ ስራም ጭምር ተሰርቷል፡፡ ቅፅ 001 የሚባለውን ወዲያውኑ ለግብር ከፋዩ እንዲሰጠው ተደርጓል፡፡

ህዳሴ፡- የቀን ገቢ ግብር ትመናው በተያዘለት የጊዜ ገደብ ተጠናቅቋል ማለት ይቻላል?

አቶ አትክልት፡- ሚያዚያ 17 ነው ስራው የተጀመረው፡፡ በ30 ቀን ውስጥ የመጨረስ እቅድ ነበርን፡፡ ማስተካከያ ስንሰራ የተወሰነ ቀን አቋርጠናል፡፡ በ30 ቀናችን አጠናቅቀናል፡፡ በእቅዳችን መሰረት በተያዘለት የጊዜ ገደብ አጠናቅቀናል፡፡
ህዳሴ፡- የቀን ገቢ ትመናውን ህጋዊና ፍትሀዊ ነው ማለት የሚያስችሉ አሰራሮችን በጥብቅ የመከተሉ ጉዳይ እንዴት ተከናወነ?
አቶ አትክልት፡- የቀን ገቢ ግምት ይህን ያህል ያገኛል ብለን በማየት ብቻ ሳይሆን በተለያዩ አመላካቾች በመታገዝ ነው የሚሰራው፡፡ ለምሳሌ ፀጉር ቤት ስንት ወንበር አለው የሚለው ለገቢው አመላካች ነው፡፡ ሌሎች የጥፍር ቀለምና መሰል ቁሳቁሶችን ጎን ለጎን የሚሸጥ ከሆነም ሌላው አመላካች ነው፡፡ ግምት ስለሆነ በተወሰነ መልኩ ችግር አይኖርም ብሎ መውሰድ ባይቻልም እንዳይጎሉ ግን በጥንቃቄ ተንቀሳቅሰናል፡፡ የግል ማስታወሻ በማየት፣ የሽያጭ መመዝገቢያ መሳሪያ በማየት፣ የአካባቢውን ገበያ (መጀመሪያ መንገድ፣ ሁለተኛ መንገድ፣ መጋቢ መንገድ፣ ሶስተኛ መንገድ) በተመሳሳይ አመላካቾች ናቸው፡፡ በመሆኑም በተቻለ መጠን ፍትሃዊ እንዲሆን ተንቀሳቅሰናል፡፡

ህዳሴ፡- አጎራባች ቀጠናዎች በተቀናጀ መልኩ ትመናውን እንዲያስኬዱ ማድረጉስ ምን ይመስላል?
አቶ አትክልት፡- በመመሪያችንም በግልፅ ተቀምጧል፡፡ በተለይ አዋሳኞች አሉ ክፍለ ከተማ ከክፍለ ከተማ ወረዳ ከወረዳ አንዱ መንገድ ከአንዱ መንገድ የሚዋሰኑ አሉ፡፡ ይሄ ጉራማይሌ እንዳይሆን ኮሚቴዎቹ እየተነጋገሩ በጋራ እንዲሰሩ ነው የተደረገው፡፡ ለምሳሌ ቦሌንና የካን የሚሰሩ በአዋሳኝ ቦታዎች ላይ ኮሚቴዎቹ ተናብበው እንዲሰሩ ተደርጓል”” ሌላው ከከተማ እስከ ወረዳ በየጊዜው መረጃው እየተገመገመ በቅንጅት ነው የተሰራው፡፡

ህዳሴ፡- ከዚህ በኋላ የተቋሙ የቀጣይ አቅጣጫ ምንድን ነው?

አቶ አትክልት፡- አማካኝ የቀን ገቢ ግምቱ ለግብር ከፋዩ በደብዳቤ እንዲደርሰው ይደረጋል፡፡ ቅሬታም ካለ ቅሬታውን ያቀርባል፡፡ ይህንን የሚቀበል በየወረዳው የቅሬታ ሰሚ ኮሚቴ ተደራጅቷል፡፡ በየክፍለ ከተማውም በተመሳሳይ ተዋቅሯል፡፡
ከዚህ በኋላ ወደ ግብር እና ታክስ ወደ መክፈል ይገባል፡፡ ከሀምሌ አንድ ጀምሮ እስከ ጥቅምት 30 የግብርና የታክስ መክፈያ ወቅት ነው፡፡ ከሀምሌ 1 እስከ 30 ደረጃ ሐ ግብርና ታክስ ይከፍላል፡፡ ደረጃ ለ ከሀምሌ 1 እስከ ጳጉሜ መጨረሻ ገብርና ታክሰ ይከፍላል፡፡ ደረጃ ሀ ደግሞ ከሀምሌ 1 እስከ ጥቅምት 30 ግብር እና ታክሱን ይከፍላል፡፡

ህዳሴ፡- በመጨረሻም ለግብር ከፋዩ ህብረተሰብ የሚያስተላልፉት መልዕክት ካለ?

አቶ አትክልት፡- አማካኝ የቀን ገቢ ግብር ግምት መረጃ ሲሰበሰብ በርካታ ግብር ከፋዮቻችን ስራው የተቃና እንዲሆን ከኮሚቴውና ከባለስልጣኑ ጎን ሆነው ላበረከቱት አስተዋጽኦ ምስጋና እናቀርባለን፡፡ መረጃ በመሰወር እና ስራው እንዲደናቀፍ ሲንቀሳቀሱ የነበሩት ደግሞ ግብርን የመክፈልን ሀገራዊ ዓላማ ተረድተው ግዴታቸውን ወደፊትም በአግባቡ እንዲወጡ መልዕክት አስተላልፋለሁ፡፡ ግብር ከፋዮቻችን በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ ግብርና ታክሳቸውን እንዲከፍሉ ጥሪዬን አስተላልፋለሁ፡፡

ህዳሴ፡- ስለነበረን ቆይታ እናመሰግናለን፡፡
አቶ አትክልት፡- እኔም አመሰግናለሁ፡፡

Tuesday, 27 June 2017

የኦሮሚያ ክልል በአዲስ አበባ ከተማ ላይ ያለውን ህገ-መንግሥታዊ ልዩ ጥቅም አስመልክቶ የቀረበ መግለጫ

 

የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ሰፊ ውይይት ካካሄዱበት በኋላ በተወካዮቻቸው አማካይነት ያፀደቁት ህገ-መንግሥት የሁሉንም ሕዝቦች መብቶችና ጥቅምች የሚያስጠብቅ ነው፡፡

ህገ-መንግሥቱም የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የቃል-ኪዳን ሰነድ ሲሆን ዓላማውም በሕዝቦች መፈቃቀድና ፍላጎት እንዲሁም ዴሞክራሲያዊ አንድነት ለማጎልበት እንዲቻል በጋራ ያፈሯቸው እሴቶችና ሃብቶች እንዲሁም ትስስሮች እንዳሏቸው በማመን- በታሪካቸው ሂደት ውስጥ ያጎለበቷቸውን የጋራ ጉዳዮች ይበልጥ ለማበልፀግና የተዛቡ ግንኙነቶችንም በማረም አንድ ጠንካራ የጋራ ኢኮኖሚያዊ ማህበረሰብ እና የጋራ ፖለቲካዊ ማህበረሰብ ለመገንባትና ለማጠናከር የታለመ ነው፡፡