Wednesday, 24 August 2016

ከቀለም አብዮት በስተጀርባ (behind the color revolution) የተደበቁ ቁማርተኞች





I. የቀለም አብዮት (color revolution) መነሻ ምክንያቶች

እንደ አውሮፓ አቆጣጠር በ1991 ዓ ም የተባበሩት የራሽያ ሶሺያሊስት ሪፓብሊክ ሀገራት ሲበታተኑ ከከረረ የአይዲዮሎጂ ልዩነት ጋር በዓለም ሁለት ኃያላን ሀገራት ተፈጠሩ። እነዚህ ኃያላን የሩሲያ የልማታዊ መንግሥት አስተሳሰብ ጎራና የአሜሪካ የገብያ አክራሪ አራማጅ ኃያላን ጎራዎች ናቸው። ሁለቱ ጎራዎች ሌሎች ሀገራትን በተጽዕኗቸው ሥር ለማስገባት የሚያደርጉት ጥረትና ድካም እንደ ተጠበቀ ሆኖ የአሜሪካና የምዕራብ አውሮፓ ኃያላን ዓለምን በሙሉ በአንድ የገብያ አክራሪነት ካምፕ ውስጥ ለማስገባት በተለያዩ ዘዴዎች አንዱን ከሌላው እያጋጩ በማተራመስ ዘዴ ሠርገው ለመግባትና የኃሳብ የበላይነታቸውን ለመጫን ብዙ ሞክረዋል፣ እስከ ዛሬም ቀጥለዋል።
በሌላ በኩል የመንግሥታዊ ካፒታሊዝም ባህሪን ይዞ የቀጠለውና በኋላም በዲንግ ምፒንግ ጠንካራ አመራር እየዳበረ የመጣው የቻይና ልዩ ፖለቲካል ኢኮኖሚ የገብያ አክራሪ አስተሳሰብን እንደ ወረደ ሳይቀበል በራሱ ተጨባጭና ነባራዊ ሁኔታ አስተካክሎ በመቀጠሉ ተአምራዊ በሆነ ፍጥነት እያንሠራራ ቀጠለ። በሩሲያም በኩል በተለይ በብላድሚር ፑቲን አመራር የራሱን ተጨባጭ አቅም መሠረት ያደረገ ልማታዊ ባህሪን አጠናክሮ በመቀጠሉ አሁንም ዓለም በአንድ የፖለቲካል ኢኮኖሚ ዋልታ ልትመራ እንደማትችል የሚያሳይ ክስተት እያቆጠቆጠ መጣ። ያልተጠበቁ እና የተለያዩ ባህርያት ያሏቸው የኢኮኖሚ ዋልታዎች የመሥፋፋት ክስተት በሌሎችም የምሥራቅ እስያ ሀገራት እያንሠራራ መምጣቱን ተከትሎ ሌሎች ሀገራት ወደእነዚህ አዳዲስ ዋልታዎች ጎራ እንዳይቀላቀሉ የቀለም አብዮት አጀንዳን መጋበዝ ጀመሩ።