በአዲሱ አረጋ ቂጤሳ (ሚኒስትር ዲኤታ)
ከበራሪ አዕዋፋት እንደ ንስር ፈጣን የመብረር ችሎታና ጥሩ የእይታ ብቃት ያለዉ የለም፡፡ ንስር ከሌሎች አዕዋፋት ረጅም ዕድሜም እንደሚኖር ይታወቃል፡፡ ቢያንስ እስከ ሰባ አመታት በህይወት መቆየት ይችላል፡፡ ይህን ሁሉ ዘመን በህይወት ሲኖር ግን ነገሮች አልጋ በአልጋ ሆነዉለት አይደለም፡፡ በህይወት ዘመኑ እጅግ የሚያሳምም የመታደስ ዉሳኔ ለመወሰን፣ የወሰነዉን ዉሳኔ ደግሞ በጥብቅ ንስራዊ ዲሲፕሊን ለመፈጸም ይገደዳል፡፡ ይህን ዉሳኔ ወስኖ ህመሙን ችሎ ካልፈጸመው ያለዉ አማራጭ መሞት ብቻ ይሆናል፡፡
ንስር እድሜዉ አርባ አመት ሲሞላዉ አካሉ ያረጃል፡፡ ሹል፣ ረዣዥም እና ጠንካራ ጥፍሮቹ ይዶለዱሙና ይደክማሉ፡፡ ለንስሩ የዕለት ምግቡን መንጭቀዉ ማንሳት ያቅታቸዋል፡፡ ንስሩ የሚታወቅበት ያ የሾለ ምንቃሩ ወይም አፉ ከዕድሜ ብዛት ወደ ደጋንነት ይቀየራል፡፡ ክንፎቹም ይዝላሉ፡፡ ላባዎቹ ይነትቡና ያ በበረራ ፍጥነቱ ይታወቅ የነበረዉ ፍጡር እንደዶሮ ጫጩት መብረር ያቅተዋል፡፡