ከፍያለው እውነቱ

የዛሬ አርባ አመት በደደቢት በረሃ የተጀመረው ትግል የአስርት ሺዎችን ህይወትንና የአካል መሰዋትነት ተከፍሎበታል። ይሁንና ያ ትግል ውጤታማ ሆኖ በአገራችን በህዝቦች መፈቃቀድ ላይ መሰረት ያደረገ ጠንካራ ዴሞክራሲያዊ መንግስት መገንባት በመቻሉ ዘላቂነት ያለው ሰላም በአገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን በአካባቢው ጭምር ማስፈን ተችሏል። ለዛሬው ሰላም መስፈን መሰረት የሆኑት እነዚያ ቁርጠኛ የህዝብ ልጆች ለዛሬው ሰላምና ልማት መሰረት ሆነዋል። የዛሬው የድህነት ትግል እንደትላንቱ የህይወትና የአካል መሰዋዓትነትን አይጠይቅም። ይህን ያስባለኝ ለነጻነት ትግል ህይወትንና አካልን ገብረናል። አሁን ላይ የብሄሮች እኩልነት፣ የተናፈቀው የዴሞክራሲ ስርዓትን መገንባት ተችሏል። ነጻነት ለማግኘት እንደተከፈለው የ17 ዓመታት መራራ ትግል የድህነት ትግል የህይወት መሰዋትነትም ሆነ የአካል መጉደልን አይጠይቅም። አሁን ያለው የተደላደለ የድህነት የትግል መንገድ መራብ መጠማትን፣ ተራራ መውጣትና ቁልቁለት መውረድን፣ ስቃይና መከራን የሚጠይቅ አይደለም። የህዝብ ልጆች የተነሱለትን የሰላም፣ የእኩልነትና የእድገት ዓላማ ከዳር ለማድረስ ዛሬ ላይ የሚጠበቅብን በተሰማራንበት መስክ ሁሉ ድህነትን በጽናት መዋጋት ብቻ ነው። ዛሬ በአገራችን ድህነትን ለመታገል የሚያስችል ምቹ ሁኔታ አለ።