Wednesday, 8 July 2015

ተፅዕኖ ማሳደር የቻለች አገር መፍጠር የተቻለው በተዓምር ሳይሆን በስራ ነው!

ከፍያለው እውነቱ


 

የዛሬ አርባ አመት በደደቢት በረሃ የተጀመረው ትግል የአስርት ሺዎችን ህይወትንና የአካል መሰዋትነት ተከፍሎበታል። ይሁንና ያ ትግል ውጤታማ ሆኖ በአገራችን በህዝቦች መፈቃቀድ ላይ መሰረት ያደረገ ጠንካራ ዴሞክራሲያዊ መንግስት መገንባት በመቻሉ ዘላቂነት ያለው ሰላም በአገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን በአካባቢው ጭምር ማስፈን ተችሏል። ለዛሬው ሰላም መስፈን መሰረት የሆኑት እነዚያ ቁርጠኛ የህዝብ ልጆች ለዛሬው ሰላምና ልማት መሰረት ሆነዋል። የዛሬው የድህነት ትግል እንደትላንቱ የህይወትና የአካል መሰዋዓትነትን አይጠይቅም። ይህን ያስባለኝ ለነጻነት ትግል ህይወትንና አካልን ገብረናል። አሁን ላይ የብሄሮች እኩልነት፣ የተናፈቀው የዴሞክራሲ ስርዓትን መገንባት ተችሏል። ነጻነት ለማግኘት እንደተከፈለው የ17 ዓመታት መራራ ትግል የድህነት ትግል የህይወት መሰዋትነትም ሆነ የአካል መጉደልን አይጠይቅም። አሁን ያለው የተደላደለ የድህነት የትግል መንገድ መራብ መጠማትን፣ ተራራ መውጣትና ቁልቁለት መውረድን፣ ስቃይና መከራን የሚጠይቅ አይደለም። የህዝብ ልጆች የተነሱለትን የሰላም፣ የእኩልነትና የእድገት ዓላማ ከዳር ለማድረስ ዛሬ ላይ የሚጠበቅብን በተሰማራንበት መስክ ሁሉ ድህነትን በጽናት መዋጋት ብቻ ነው። ዛሬ በአገራችን ድህነትን ለመታገል የሚያስችል ምቹ ሁኔታ አለ።

የኢትዮጵያ ቀንደኛ ጠላት ድህነት እንደሆነ አበክረው ይገልፁ የነበሩት የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ክቡር አቶ መለስ ዜናዊ ህብረተሰቡ ስለልማት፣ እድገትና መለወጥ መሰረት ጥለዋል። ይህ የጠቅላይ ሚኒስትር ሁላችንም ራሳችንን እንድናይ የአገራችንን ነባራዊ ሁኔታ እንድናጤን የሚያደርግ ነው። ለድህነታችን መንስኤዎቹም ሆነ መፍትሄ አምጪዎቹ እኛው ራሳችን መሆን እንደሚገባን መገንዘብ ተገቢ ይመስለኛል። አገራችን የተከተለችው ያልተማከለ አስተዳደር የህዝቦች ዴሞክራሲያዊና ሰባዊ መብቶች ማረጋገጥ ችሏል። ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት የአገራችን ገጽታ እየተሻሻለ በመምጣቱ ኢትዮጵያ በአለም አቀፍ መድረክ የነበራት ተሰሚነት እየተሻሻለ እንደመጣ ማየት ይቻላል። አገራችን ትላንት ትታወቅበት የነበረው ድርቅ፣ ረሃብና ጦርነት ዛሬ የለም። የአገራችን ገጽታ እጅጉን ተሻሽሏል። ዛሬ ላይ አገራችን አስተማማኝ ሰላም አለ። በረሃብ የሚሞት አንድም ሰው የለም። ስራ የማማረጥ አባዜ ካልሆነ ስራ አለ። ማንም መስራት የሚችልና የሚፈልግ ዜጋ ጦሙን የማያድርባት አገር መፍጠር እየተቻለ ነው። ይህ በአትኩሮት ለተመለከተው ትልቅ ጥንካሬ ነው። በመጀመሪያው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ አገራችን ትልቅ ድል ማስመዝገብ ችላለች። ይህ ምስክርነት በሁሉም አለም አቀፍ አካላት ተቸሮታል።
የአገራችን የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ የውስጥ ግንኙነታችን ነጸብራቅ ነው። የፌዴራሊዝም ስርዓታችን ያስተማረን ትልቅ ነገር መቻቻልና መከባበርንን ነው። ኢትዮጵያ የውስጥ ችግሯን መፍታት የቻለችው ጠንካራ የፌዴራል ስርዓት መከተል በመቻሏ ነው። ኤኮኖሚክ ዲፕሎማሲን መሰረት ያደረገው የአገራችን የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ የአገሪቱን ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ከማረጋገጡም ባሻገር በቀጠናው አገሮች መካከል ምጣኔ ሀብታዊ ትስስር እንዲፈጠር በማድረጉ በአካባቢው አገሮች ዘላቄታዊ ሰላም እንዲኖር አድርጋለች።
መንግስት የሚከተለው ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ አካሄድ የአገራችንን ነባራዊ ሁኔታ ያገናዘበ በመሆኑ አለምን ያስደመመ የኤኮኖሚ እድገት እንዲሁም ጠንካራ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ሂደት ማፋጠን ተችሏል። መንግስት ከፍተኛ የኤኮኖሚ እድገት ማስመዝገብ ከቻሉ ጥቂት የምስራቁ አለም ከታይዋነና ደቡብ ኮሪያ ልምድ በመቅሰም ከአገራችን ነባራዊ ሁኔታ ጋር በመቀመር የልማታዊ ዴሞክራሲያዊ አካሄድን በመተግበር ላይ ይገኛል። ይህም ማለት ከታይዋንንና ደቡብ ኮሪያን መልካም መልካም ልምዶች በመቅሰም ከኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ጋር እንዲጣጣም በመደረጉ አገራችን ባለፉተ አስራ አንድ አመታት ባለሁለት አሃዝ እድገት ያለምንም የተፈጥሮ ሃብት ማስመዝገብ ችላለች።
ታይዋንና ኮሪያ እድገት ማስመዝገብ ከመጀመራቸው በፊት የዕድገት ደረጃቸው በአብዛኛው ከአፍሪካ ጋር የተቀራረበ ከመሆናቸውም ባሻገር እዚህ ግባ የሚባል የተፈጥሮ ሃብትያላቸው አይደሉም። ይህ ሁኔታቸው ደግሞ ለእኛ ኢትዮጵያዊያን ጥሩ ምሳሌ ሊሆኑ የሚችሉ አገሮች እንደሆኑ ማየት ይቻላል። አንዳንዶች እንደሚሉት የምዕራቡ አለም የሊበራል አስተሳሰብ በኤኮኖሚ ዕድገታቸው ጠንካራ በሆኑ የምዕራቡ አለም ጥሩ ለውጥ ማስመዝገብ ቢችልም በአፍሪካ ተጨባጭ ሁኔታ ግን ተተግብሮ ውጤት እንዳላመጣ ታይቷል። በአፍሪካ የዴሞክራሲ ስርዓቱ ጠንካራ አይደለም። በአፍሪካ መሰረተ ልማቱ እጅግ ኋላቀር ነው።
እንዲህ ባለችው ኋላ ቀር አህጉር ኤኮኖሚውን ሙሉ ለሙሉ ገበያው በውድድር ይምራው በማለት የመንግስትን የተመረጠ ጣልቃገብነት ማውገዝ የቀልድ ያህል የሚታይ ይመስለኛል። ኤኮኖሚያቸው በተፈጥሮ ሃብት በተለይ በነዳጅና ወርቅ ላይ መሰረት ካደረጉት አገራት ውጭ ይህ አስተሳሰብ ያስከተለውን ውጤት ማየቱ የሚያስቸግር አይመስለኝም።
ታይዋንና ደቡብ ኮሪያ በ30 ዓመታት ውስጥ ፈጣን እድገት በማስመዝገብ ህዝባቸውን በአጭር ጊዜ ውስጥ ከድህነት በማላቀቅ በልማት ጎዳና ማራመድ የቻሉ አገሮች ናቸው። እነዚህ አገራት በአጭር ጊዜ ውስጥ በልማት ጎዳና ሊጓዙ የቻሉት መንግስት ይከተለው በነበረው ልማታዊ አካሄድ ነው። መንግስት በተመረጡ የኤኮኖሚ መስኮች ጣልቃ በመግባት የኤኮኖሚ እድገቱ የሚፋጠንበትንና ህብረተሰቡ ተጠቃሚ የሚሆንባቸውንና ሁኔታዎች ያመቻች ነበር። ይሁንና ታይዋንም ሆነች ደቡብ ኮሪያ ይከተሉት የነበረው ልማታዊ መንግስት ይሁን እንጂ ኢ-ዴሞክራሲ አገዛዝን ይተገብሩ ነበር። እነዚህ አገራት በኤኮኖሚ ጠንካራ መሰረት እስኪኖራቸው ድረስ የመድብለ ፓርቲ ስርዓትን አልተገበሩትም።
ይሁንና የኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ከዚህ የተለየ ነው። የኢትዮጵያ መንግስት የሚከተለው ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ አካሄድን ነው። ለዚህም ዋንኛ ምክንያቱ መንግስትን የሚመራው ድርጅት ኢህአዴግ ለ17 ዓመታት የታገለለት የዴሞክራሲ ጥያቄ፣ የብሄር ብሄረሰቦች የእኩልነት ጥያቄ እጅግ አንገብጋቢ ዋንኛ የህዝብ ጥያቄዎች በመሆናቸው እነዘህን ጥያቄዎች ልደፍጥጥ ማለት የሚያስከትለውን አደጋ ስለሚረዳ ነው። ከእንግዲህ በኢትዮጵያ የብሄር ብሄረሰቦችን እኩልነት የማይቀበል አገዛዝ ተቀባይነት እንደማይኖረው በህገ-መንግስቱ ተረጋግጧል። በመሆኑም ልማትን ለማፋጠን ተብሎ ኢ-ዴሞክራሲያዊ አካሄድ በኢትዮጵያ ሊተገበር አይቻልም። ለመተግበር መሞከርም ትርፉ ጦርነትና እልቂት እንደሚሆን ካለፈው ስርዓት ጥሩ ትምህርት ተቀስሟል። በመሆኑም ከታይዋንና ከደቡብ ኮሪያ የሚበጀንን ልምድ በመቅሰም ከእኛ ነባራዊ ሁኔታ ጋር በማጣጣማችን አገራችን ባለፉት አስራ ሁለት አመታት አለምን ያስደመመ ዕድገት ማስመዝገብ ችላለች። ይህ መንግስት የሚናገረው ሳይሆን አለም የመሰከረው ሃቅ ነው።
ሌላው ታይዋንና ኮሪያ በልማት ጎዳና የተጓዙበት ወቅትን ስንመለከተው አሁን ካለው ነባራዊ ሁኔታ እጅጉን የተለየ ሆኖ እናገኘዋለን። በቅድሚያ በወቅቱ አለማችን በሁለት ጎራ ማለትም የምዕራቡ የካፒታሊስቱና የምስራቁ የሶሻሊስት ጎራ በመባል የተከፋፈለች በመሆኑ ምዕራባዊያኖች ታይዋንና ደቡብ ኮሪያ የምስራቁን ሶሻሊስት ሪዮት እንዳይቀላቀሉ ሲሉ ኢ-ዴሞክራሲያዊ አካሄዳቸውን ሲነቅፉ አይታዩም ነበር። ይልቁንም ምዕራባዊያን ለእነዚህ አገራት ከፍተኛ የኤኮኖሚ ድጋፍ ከማድረጋቸውም ባሻገር የግል ባለሃብቶቻቸው በእነዚህ አገራት ኢንሸስት እንዲያደርጉ ከፍተኛ ድጋፍ ይሰጡ ነበር።
በመሆኑም ታይዋንና ደቡብ ኮሪያ ኢዴሞክራሲያዊ አካሄድን እየተገበሩ፣ ምርጫ የተባለ ነገር ሳያካሄዱ መንግስት በገበያው እንደፈለገ ጣልቃ እየገባ እድገት ሲያስመዘግቡ ምዕራባዊያኖች አንድም ወቀሳ ሲያቀርቡ አልተደመጡም ነበር። ይሁንና የምዕራቡ ሚዲያና የሰባዊ መብት ተማጋች ነን የሚሉ እንደሂዩማን ርይትስ ዎች ያሉ ድርጅቶች በአገራችን ላይ የሌሉ ነገሮችን በመፍጠር ወይም ጥቃቅን ነገሮችን ጌጣጌጥ በመስጠትና በተለያዩ ቀለማት በመቀባባት መንግስትን በሰባዊ መብትት ጥሰት ሲከሱት ይደመጣሉ። ከዚህም ባሻገር የሊበራል አስተሳሰብ አስራጭ የሆኑት እንደአለም ባንክና የአለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም የመንግስት የልማት ተቋም የሆኑትን እንደባንክና ቴሌኮሙዩኒኬሽን ወዘተ እንዲሸጡ እንዲሁም የብዙሃን ሃብት የሆነውን መሬት እንዲሸጥ እንዲለወጥ ሲል በተደጋጋሚ በመንግስት ላይ የተለያዩ ጫናዎችን ሲፈጥሩ ነበር። ይሁንና መንግስት እነዚህን ጫናዎችን ሁሉ በመቋቋም ባለፉት አስራ ሁለት ዓመታት አገራችን አለምን ያስደመመ ፈጣንና ተከታታይነት ያለው እድገት ማስመዝገብ ከመቻሏ በተጨማሪ ዴሞክራሲያዊ መንግስት በመስረቷም ረገድ ተጨባጭ ለውጦችን ማስመዝገብ ችላለች። ከጥቂት አመታት በፊት የድርቅና ረሃብ ተምሳሌት ተደርጋ ትጠቀስ የነበረች አገር ዛሬ ላይ ባለ ብዙ ቢሊዬን ዶላር ወጪን የሚጠይቁ ትላልቅ ሜጋ ፕሮጀክቶችን ሳይቀር በራስ አቅም የመገንባት አቅም መፍጠር የቻለች በለተስፋ አገር መሆን ችላለች።
ኢትዮጵያ ዛሬ ላይ በአፍሪካ ሆነ በአለም አቀፍ መድረክ ተሰሚነቷ በማደጉ በአገሮች መካከል ግጭት ወይም ያለመግባባት ሲከሰት የኢትዮጵያ ከፍተኛ ባለስልጣናት በአደራዳሪነት ወይም ሸምጋይነት ግንባር ቀደም ተመራጭ እየሆኑ መጥተዋል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አገራችን በተባበሩት መንግስታት ያላት ተሰሚነት፣ በአፍሪካ ህብረት ያላት የመሪነት ሚና እንዲሁም በኢጋድና በሌሎች ትላልቅ መድረከኮች ያላት ቦታ ከሰማይ የወረደ መና ሳይሆን አገራችን ማስመዝገብ በቻለችው የኤኮኖሚ እድገትና በጠንካራ የዲፕሎማሲ ድል ሳቢያ መሆኑን ማመን ተገቢ ይመስለኛል።
ባለፈው የፈረንጆች አመት መገባደጃ ላይ በአሜሪካ በተካሄደውን የአፍሪካ አሜሪካ የግንኙነት መድረክ ጎን ለጎን ፕሬዚዳንት ኦባማና ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማሪያም ደሳለኝ ውይይት ባደረጉበት ወቅት ፕሬዚዳንት ኦባማ ስለአገራችን የሰጡት ምስክርነት መለብዙዎቻችን ጥሩ ትምህርት ሰጥቶናል። እጅግ የሚገርመው አንዳንድ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ፈርሳ የምትሰራዋን የአዲስ አበባ እድገት አልታይ ይላቸው ነበር። ይሁንና ስለኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት ኦባማ ይንን አይነት ምስክርነት ሲሰጡ ለብዙዎቻችን ከአይናችን ይልቅ ጆሯችንን እንድናምን አድርጎናል።
ለማንኛውም ፕሬዚዳንት ኦባማ ኢትዮጵያን በተመለከተ ከሰጡት አስተያየት አንዳንዶቹን ላንሳቸው። ፕሬዚዳንት ኦባማ እንዳሉት በአፍሪካ እየታዩ ስላሉ ለውጦች ስናወራ እንደ ኢትዮጵያ ያለ ጥሩ ምሳሌ ማግኘት አይቻልም። ኢትዮጵያ በአለማችን እጅግ ፈጣን የኤኮኖሚ እድገት ማስመዝገብ የቻለች በአጭር ጊዜ ውስጥ በርካታ ለውጦችን ማሳየት የቻለች አገር ነች። ከቅርብ ጊዜ በፊት በምግብ ሰብል ራሷን መቻል የተሳናት አገር በተከታታይ አመታት እንዲህ ያለ ፈጣን እድገት ማስመዝገብ መቿሏ ጠንካራ አመራር እንዳላት የሚያሳይ ጉዳይ ነው። በአካባቢው ካሉ አገሮች በአጠቃላይ ግብርና ምርት ከፍተኛውን ቁጥር ከመያያዟም ባሻገር በቅርቡ በግብርና ውጤቶች ኤክስፖርትም ትልቅ አቅም ልትፈጥር እንደምትችል መረዳት የሚያዳግት አይደለም። ኢትዮጵያ የአካባቢው አገሮች የሃይል ምንጭ ለመሆን እየሰራችው ያለው የታዳሽ ሃይል ግንባታም እጅግ አስገራሚ ነገር ነው ሲሉ አድናቆታቸውን ቸረዋል።
አሜሪካ ከኢትዮጵያ ጋር ጠንካራ የንግድ ሸሪኮች ነች። በቅርቡ ደግሞ አገሬ አሜሪካ በኢትዮጵያ እየተመዘገበ ካለው እድገት በተዘዋዋሪ ተጠቃሚ ሆናለች ያሉት ፕሬዚዳንት ኦባማ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአለማችን በፍጥነት እያደጉ ካሉ ጥቂት አየር መንገዶች አንዱ በመሆኑ እጅግ ዘመናዊ የሆኑ አውሮፕላኖችን እየገዛ ይገኛል። በመሆኑም ለቦይንግ ኩባንያ ተጨማሪ አውሮፕላኖችን ለኢትዮጵያ አየር መንገድ መሸጥ የሚችል ከሆነ ለአሜሪካ ዜጎች የስራ እድል ፈጠረ ማለት ነው። ለዚህ ነው አሜሪካም ከኢትዮጵያ እድገት ተጠቃሚ ሆናለች ያልኩት ሲሉ ፕሬዚዳንት ኦባማ ለጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማሪያም ደሳለኝ የገለጹት።
አሜሪካና ኢትዮጵያ ከኤኮኖሚ ትስስር ባሻገር ጠንካራ የሆነ በሰላም ማስከበርና ግጭት ማሰወገድ ዙሪያም ጠንካራ ግንኙነት እንዳላቸው ፕሬዚዳንት ኦባማ አብራርተው በአለማችን የሰላም ማስጠበቅ ዙሪያ እጅግ የተሳካለቸው አገሮች መካካል ኢትዮጵያ በቀዳሚነት የምትነሳ በዲሲፕሊን የታነጸ እጅግ በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ሳይቀር ግጭትን በማስወገድና ሰላምን በማስፈን የተሳካላቸው የሰላም አስከባሪ ሃይሎች ያሰማራች አገር ሲሉ አገራችንን አሞካሽተዋታል። ከዚህም ባሻገር ኢትዮጵያ በአለም ከፍተኛ ቁጥር ያለው የሰላም ማስከበር ሃይል ካዋጡ ጥቂት አገራት ተርታ የተሰለፈች አገር እንደሆነችም ማየት ይቻላል ሲሉ ኦባማ ተናግረዋል።
በመሆኑም ኢትዮጵያ አህጉሩን እየመራች ያለችው በኤኮኖሚ እድገት ብቻ ሳይሆን በአካባቢው በዘለቄታ ይታይ የነበረውን ግጭቶች እልባት እንዲያገኙ መፍትሄ በማፈላለግ ጭምር ያሉት ፕሬዚዳንቱ ኢትዮጵያ ለምታደርገው ለዚህ መልካም ነገር አድናቆታችንን እየቸርን እኛም ጠንካራ አጋርነታችንን መግለጽ እንፈልጋለን ብለዋል። እንዲህ ያሉ መልካም አጋጣሚዎችን ተጠቅመን ከኢትዮጵያ ጋር በግብርና በጤና በኤኮኖሚ እንዲሁም አንገብጋቢ በሆኑ የአካባቢው የጸጥታ ሁኔታ ላይ አጋርነታችንን ለማጠናከር እንፈልጋለን።
ኢትዮጵያ በፀረ ሽብር ትግሉ ጠንካራ አጋራችን ነች። በሶማሊያ ያለው የአልቃይዳ ክንፍ የሆነው ጽንፈኛ አልሸባብን በሶማሊያና በአካባቢው አገሮች እያደረሰ ያለውን ጥፋት በመተባበራችን መመከት ችለናል ።ይህን ጽንፈኛ ሃይል በመዋጋት ኢትዮጵያ እያሳየች ያለውን ጥረትና እየመጣ የለው ሰላም የሚደነቅ ነው። በዚህ ረገድ የኢትዮጵያ ጥረት የሚመሰገንና የሚበረታታ እንደሆነ መግለጽ እፈልጋለሁ። እንደ ኢትዮጵያ ካሉ የጸረ ሽብር ትግል አጋሮቻችን ጋር በመተባበር የከፈትነው ትግል ውጤታመ መሆን በመቻሉ በአጠቃላይ ሽብርተኝነትን እንዲዳከም በማደረግ ላይ ነን። በእንዲህ ያለው የአጋርነት ትግላችን ኢትዮጵያ ትልቅ ስፍራ የሚሰጣት አጋራችን ነች ሲሉ ፕሬዚዳንት ኦባማ ተናረዋለ። አገሬ የአካባቢውን ብሎም የአህጉሩን ሰላም ለማስጠበቅ ከአጋር ወገኖች ሁሉ ጋር በመተባበር እየሰራች ትገኛለች። ከሌሎች ጋር በጋራ የሰላም ማስከበሩን ስራ መስራት መቻላችን ውጤታማ መሆን ችለናል። የቀንዱን አካባቢም ሆነ የአህጉሩን ሰላም ለማስጠበቅ የምናደርገውን ጥረት አሁንም አጠናክረን የምንቀጥልበት ይሆናል። በአለም አቀፍ ደረጃም ቢሆን የሰላም ማስከበር ላይም ቢሆን የምናደርገውን ጥረት አሁንም የምንቀጥልበት ትልቅ ጉዳያችን ነው።
አዎ ፕሬዚዳንት ኦባማ መሬት ላይ ያለውን ሃቅ መስክረዋል። የኢትዮጵያ መከለከያ ሰራዊት በሚያሳየው ምስጉን ስነምግባር በተሰማራበት የሰላም ማስከበር አገራት ሁሉ አድናቆት የተቸረው ሆኗል። ሰራዊቱ የመንግስቱና የህዝቡ ነጸብራቅ ነው። ከታሪክ እንደምንረዳው ለአገሩ ህዝብ መልካም ያልሰራ መንግስት ሲወቀስ እንጂ በሌሎች በመልካም ሲነሳ አልታየም አልተሰማም።
ዛሬ ዛሬ ስለኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ለውጥ የማይዘግብ ማዲያ እና ተቋም የለም፡፡ ከእኛ ርዕዮተ ዓለም የተለየ የሚከተሉት አገራት ሳይቀር የአገራችንን እድገት እየመሰከሩ ይገኛሉ፡፡ አገራችን ስኬት በምጣኔ ሃብት ብቻ ሳይሆን በዲፕሎማሲው መስክም ውጤታማ እየሆነች መጥታለች። አገራችን እርዳታና ብድር ጠያቂ ሳትሆን ለአፍሪካ አገሮች ብቻ ሳይሆን ለኃያላን መንግስታት ሳይቀር አጋርና መፍትሄ አፈላላጊ ለመሆን በቅታለች። ይሁን ጉዳይ በሌላ ቀን እመለስበታለሁ። የዛሬ አጀንዳዬ የአገሬ የኤኮኖሚ ስኬት በመሆኑ ወደዚያው ላቅና።
ኦባማ በቅርቡ አገራችንን ለመጎብኘት የተነሱት እነዚህን እውነታዎች አረጋግጠው መሆኑን መገንዘብ የሚያዳግት አይደለም። አገራችን በትክክለኛው የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታና የኤኮኖሚ እድገት ጎዳና ላይ መሆኗን በመረዳታቸው ነው ፕሬዚዳንቱ አገራችንን ለመጎብኘት የተነሳሱት። ኦባማ አገራችንን ለመጎብኘት የተነሱት መልካም ነገሮችን ማየት በመቻላቸው ከኢትዮጵያ የሚፈልጉት ነገሮች በመኖራቸው ነው። አገራችን ዛሬ ላይ በታዳጊ አገሮች ብቻ ሳይሆን ባደጉትም አገራት ዘንድ ተፈላጊነቷ እየጨመረ መምጣቱን መረዳት የሚያዳግት አይደለም። በሁለት አስርት ዓመታት እንዲህ ያለች ተጽዕኖ ማሳደር የምትችል አገር አገር መፍጠር የተቻለው በተዓምር ሳይሆን መንግስት በየዘዘርፉ መከተል በቻለው ትክክለኛ ፖሊሲና ስትራቴጂ ነው።
አገራችን ለሁሉም ጎረቤት አገራት ዜጎች እንደሁለተኛ አገር በመቆጠር ከሰሃራ በታች ካሉ የአፍሪካ አገራት ከፍተኛ ቁጥር ያለውን ስደተኞችን ማስጠለል ብቻ ሰይሆን ለስደተኞች ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር በተባባሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ኮሚሽን ጭምር ሙገሳን ተችሯታል። በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ከሶማሊያ፣ ከደቡብ ሱዳንና ከኤርትራ የተሰደዱ ከስድስት መቶ ሺህ በላይ ለሚሆኑ ስደተኞች መጠለያ ነች።
ከሁለት አስርት ዓመታት በፊት የነበረውን የአገራችንን ሁኔታ ስናስታውስ እንኳን ለሌሎች አገሮች ዜጎች መጠለያ ልትሆን ይቅርና የራሷ ህዝቦችም በጦርነትና በረሃብ ሳቢያ የትውልድ ቀያቸውን ጥለው የሚሰደዱባት አገር ነበረች። ባለፈው የአየርላንድ ፕሬዚዳንት አገራችንን በጎበኙበት ወቅት ይህን በተመለከተ የሰጡትን ምስክርነት መመልከት ተገቢ ይመስለኛል። ኢትዮጵያ ለበርካታ የጎረቤት አገራት ስደተኞችን በማስተናገድ እያደረገች ያለችው ተግባር ሊመሰገን የሚገባው ነገር ነው ሲሉ የአገራችንን በጎ ተግባር አመስግነዋል። ስደተኞችን ማስጠለል የሚፈጥረው ማህበራዊም ሆነ ምጣኔ ሀብታዊ ጫና ከባድ ቢሆንም አገራችን አቅም በፈቀደ ሁሉ ሁኔታዎች እንዲሟሉላቸው እያደረገች ትገኛለች። ኢትዮጵያ ይህን እያደረገች ያለችው በህዝቦች መካከል ያለው መተሳሰብ የበለጠ እንዲጠናከር በማሰብ እንጂ ይህን ያህል ቁጥር ያለው ስደተኞችን ማስተናገድ የሚያመጣው ጫና ቀላል የሚባል አይደለም።
የአገራችን ምጣኔ ሀብት እድገት ሲጀምር ከጎረቤት አገራት ጋር በንግድ፣ በባህል፣ በሰላም ማስከበር፣ ወዘተ ትስስሩ እየጠነከረ መምጣት ጀምሯል። ኢትዮጵያና ከጎረቤት አገራት ጋር የጠነከረ ግንኙነት መመስረት በመቻሏ ከሁሉም አገራት ጋር በፖለቲካ፣ ምጣኔ ሀብትና ማህበራዊ ጉዳዮች ጥብቅ ቁርኝት መፍጠር ችላለች። ሁሉም የጎረቤት አገራት ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸው ግንኙነት በጋራ ተጠቃሚነት ላይ መሰረት ያደረገ ነው።
ኢትዮጵያ ከጅቡቲ፣ ከደቡብ ሱዳን፣ ከሱዳን፣ ከኬንያ እንዲሁም ከሶማሊያ ጋር አካባቢውን በምጣኔ ሀብት ሊያስተሳስሩና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን ሊያጠናክሩ የሚችሉ የተለያዩ መሰረተ ልማቶችን ማለትም የመንገድ፣ የኃይል አቅርቦት፣ የአካባቢ ሰላም፣ ንግድ ወዘተ…እንዲስፋፉ ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ ነች። እንዲሁም ኢትዮጵያ በተለያዩ የአፍሪካ አገራት በሩዋንዳ፣ ቡሩንዲ፣ ሶማሊያ፣ ላይቤሪያ፣ ሱዳን፣ ዳርፉር፣ አብዬ የሰላም ማስከበር ስራዎች ላይ ከፍተኛ ሚና ተጫውታለች። ኢትዮጵያዊያን ሰላም አስከባሪ ኃይሎችም በተሰማሩበት አገር ሁሉ በህዝብ የተወደዱና ምስጋና የተቸራቸው ናቸው።
እነዚህ ሁሉ መልካም ነገሮች የመነጩት አገራችን ከምትከተለው በህዝቦች የጋራ ጥቅም ላይ ታሳቢ ያደረገ የውጭ ፖሊሲ መሆኑን መገንዘብ የሚያዳግት አይመስለኝም። በተመሳሳይ አትዮጵያ ታላቁን የህዳሴ ግድብ መሰረት ስትጥል አገሪቱ ያለባትን ከፍተኛ የኃይይ አቅርቦት እጥረት ለመፍታት እንዲቻል እንዲሁም በተመጣጣኝ ክፍያ ለጎረቤት አገሮች ኃይል በማቅረብ ተጨማሪ የውጭ ምንዛሪ የምታገኝበትን ሁኔታ ታሳቢ በማድረግ እንጂ በሌሎች የተፋሰሱ አገራት ላይ ጫና ለመፍጠር ታስቦ አይደለም።
እነዚህ ሁሉ መልካም ነገሮች ጥንስስ የደደቢት በረሃ የተጀመረው ዛሬ 40ኛ ዓመቱን ያከበረው የወያኔ ትግል ነው። የሕወሃት ጥንስስ በትግራይ ምድር በ1967 ነፍጥ በማንሳት የትጥቅ ትግሉን ጀምሮ ከሁሉም በላይ በሕዝብ ታቅፎና በየጊዜውም አጋር ድርጅቶችን አፍርቶ ከ17 ዓመታት ቆራጥ ሕዝባዊ ተጋድሎ ጭቁኖችን ነጻ በማውጣት ችሏል።
ደርግን ለመጣል የተደረገው ትግል ረጅም ዓመታት የወሰደና እጅግ እልህ አስጨራሽ የነበረ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በሺዎች የሚቆጠሩ ታጋዮች የማይተካ ክቡር ሕይዎታቸውን ለትግሉ ስኬት ሲሉ ገብረዋል። ብዙዎችም ለአካላዊና መንሰፈሳዊ ጉዳት ተዳርገዋል።
የዛሬው ሰላም፣ እድገትና ዴሞክራሲ በእነኛ ህይወታቸውንና አካላቸውን በገበሩ የህዝብ ልጆች የመጣ መሆኑን ማሰብ ተገቢ ነው። የዛሬው ትግል የህይወትና የአካል መሰዋዓትነትን የሚጠይቅ አይደለም። ዛሬ አገራችን ከእኛ የምትፈልገው በተሰማራንበት የስራ መስክ ጠንክረን በመስራት ድህነትን መዋጋት ብቻ ነው።

No comments:

Post a Comment