ከህዳሴ ጋዜጣ ክፍል ጋር ያደረጉት
ቆይታ
የህዝብን ጥያቄ አድምጦ ተገቢውን ምላሽ
መስጠት ለአንድ ሀገር መንግስትና ለሚመራው ድርጅት ወሣኝ ስራ ነው፡፡ የህዝብ ውግንና ያለው ድርጅታችን ኢህአዴግ ደግሞ ሉአላዊ
የስልጣን ባለቤት የሆነውን ህዝብ በሚገባ ማገልገል መለያ ባህሪው ነው፡፡
ይህም በየደረጃው በሚገኝ የአመራር አካላት
እየተተገበረ ይገኛል፡፡ እኛም የየካ ከፍለ ከተማ አስተዳደር በተለይም ከምርጫ 2007 በኋላ የህዝቡን ችግር ለመፍታት ምን ቅድመ
ዝግጅት እያደረገ እንዳለ ከክፍለ ከተማው ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ይክፈለው ወ/መስቀል ጋር ያደረግነውን ቆይታ ይዘን ቀርበናል፡፡
ህዳሴ፡-
የክፍለ ከተማችሁ ህዝብ በምርጫ ወቅት ያነሣቸው ጥያቄዎች ይዘት ምን ይመስላል?
አቶ ይክፈለው
ወ/መስቀል፡- በከተማችን ማስፋፊያ ከሆኑ ክፍለ ከተሞች ክፍለ ከተማችን አንዱ እንደመሆኑ ከዚህ ጋር ተያይዞ የመልካም አስተዳደርና
የልማት ጥያቄዎች ተነስተዋል”” የመፀዳጃ እና የማብሰያ ቤት፣ የቤት
እድሣት፣ የፍሣሽ፣ የጐርፍ እና ሌሎችም ጥያቄዎቹ በቀጠናና መንደር ከህብረተሰቡ ጋር ባደረግነው ውይይት ተነስተዋል፡፡ ህዝቡ ያነሳቸውን
ከ1 ሺህ 230 በላይ ችግሮችን በመሰብሰብ ተጠምረው 80 በመቶ የሚሆኑትን በምርጫው ወቅት ለመፍታት ተችሏል፡፡ የቀሩትን ደግሞ ለመፍታት አቅደን እየተንቀሣቀስን ነው፡፡
ህዳሴ፡-
እነዚህን ችግሮች እስከአሁን መፍታት ያልተቻለበት ምክንያት ምንድን ነው ይላሉ?
አቶ ይክፈለው
ወ/መስቀል፡- ችግሮችን ሳንፈታቸው የቆየንባቸው ምክንያቶች በዋናነት በሁለት ተከፍለው የሚታዩ ናቸው፡፡ አንደኛ በልማት እንቅስቃሴና
በለውጥ ላይ ስለምንገኝ ይሄ በራሱ በህብረተሰቡ ላይ የሚፈጥረው ፍላጐት አለ”” ከህብረተሰቡ መስፋፋትና
እድገት ጋር የሚያያዝ ማለት ነው፡፡ ሁለተኛ የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ እስከ 1988 ዓ.ም ድረስ ያለውን ከዚህ በፊት መንግስት መመሪያ
አውጥቶ እኛም 11 ሺህ ካርታዎችን ሰጥተናል፡፡ ከ1988 – 1997 ያሉት መመሪያ እየተዘጋጀላቸው ስለነበር በህገ ወጥ የተያዙም
ስለነበሩ ፖለቲካዊ ውሣኔ ተወስኖ መመሪያ ወጥቶ ስራ እስኪጀመር ድረስ የይዞታ ማረጋገጫ አላገኙም ነበር፡፡
በመሆኑም
ግንባታ ፈቃድ ማግኘት አልቻሉም፣ መፀዳጃ ቤትና ማብሰያ ቤት ለመገንባት ይቸገሩ ነበር፡፡ ሆኖም ካርታ መስጠት በመጀመራችን የመልካም
አስተዳደር ችግሮችን በመፍታት ላይ እንገኛለን፡፡
በሌላ በኩል
የአመራራችን የመፈፀም አቅም ውስንነትና የአመለካከት ችግርም እንደነበረ ገምግመን መፈፀም እየቻልን ያለመፈፀም ችግር መደገም የሌለበት
መሆኑን መተማመን ችለናል””
በተጨማሪም
በክፍለ ከተማው አቅም የማይፈቱትንም ለይተናል፡፡ በተለይም ከጐርፍ ጋር በተያያዘ የቀበና ወንዝ ከፍተኛ ወጭ የሚጠይቅ በመሆኑ ከከተማው
አስተዳዳር ጋር በመቀናጀት ችግሩን እያቃለልን እንገኛለን፡፡ በተመሣሣይ ወንድይራድ ትምህርት ቤት አካባቢ የሚሰራው መንገድ በመዘግየቱ
ጐርፍ በነዋሪዎች ላይ ችግር እየፈጠረ በመሆኑ ለከተማ አቅርበን መፍትሔውን እየተጠባበቅን ነው፡፡
ከህገ ወጥ
ግንባታ ጋር በተያያዘም አመራሩ ከደንብ ማስከበር ጋር በመሆን ለመከላከል ቢንቀሣቀስም ሙሉ በሙሉ ስላልቆመ ነዋሪው የመገንባት አመራሩ
ደግሞ የማፍረስ ሁኔታ ይታያል፡፡ ከኪራይ ሰብሣቢነት ጋርም የተያያዙ የህገ ወጥነት ችግሮች አሉ፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ግን ከጊዜ
ወደ ጊዜ እየተቆጣጠርነው እንገኛለን፡፡
ህዳሴ፡-
አሁን ችግሮችን /ጥያቄዎችን ለመመለስ ምን ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ ነው?
አቶ ይክፈለው
ወ/መስቀል፡- ከምርጫ በኋላም በፊት በጀመርንበት ሂደት ስራውን ማስቀጠል አለብን በማለት የቀጣይ እቅድ አዘጋጅተናል”” በተለይም
ወጣቶች በምርጫ ወቅት ያነሷቸውን ጥያቄዎች መሠረት አድርገን ከዚህ በፊት የመኪና እጥበት፣ የመኪና ጥበቃና ፓርኪንግ በመመሪያ ተከልክሎ
የነበረ ቢሆንም የከተማ አስተዳደሩ በመልካም አስተዳደር በማየት ችግሮችን እንድንፈታ በሰጠን አቅጣጫ መሠረት ጥያቄያቸውን እየመለስን
እንገኛለን፡፡
በክረምት
በጐ ፈቃድ አገልግሎት ከ100 ሺህ በላይ ወጣቶችን ለማሣተፍ አቅደን ተወያይተናል”” በዚህ አመት 25 ሺህ 870 የስራ እድል ለመፍጠር አቅደን እስከ አሁን ከ27
ሺህ በላይ ለሚሆኑት የስራ እድል ፈጥረናል”” ነገር ግን ወጣቱ ካነሣው ጥያቄ አንፃር በቂ ስላይደለ በሚቀጥለው አመትም ከዚህ የሰፋ
የስራ እድል መፍጠር አለብን ብለን ዝግጅት እያደረግን ነው”” ለዚህም
እንዲረዳ በቅርቡ ያስመረቅናቸውን የማምረቻና ማሣያ ህንፃዎች ለተጠቃሚዎች አስተላልፈናል፡፡
ከመንግስትና
ከድርጅታችን ጋር ተቀራርበው እየሰሩ ቢገኙም ሴቶች ከዚህም የበለጠ ተጠቃሚ የሚሆኑበትን እየለየን እንገኛለን፡፡ ማንኛውም ነዋሪ
ካርታ የለህም ተብሎ ማድቤት እንዳይቸገር እንዲሁም ካርታ የለህም ተብሎ ያለመፀዳጃ ቤት እንዳይኖር ለማድረግ እየሰራን ነው፡፡
ህዳሴ፡-
በምርጫ ወቅት በርካታ የህዝቡ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች እንደተፈቱ ይታወሣል? ይህንን ከፍተኛ የማስፈፀም አቅም ግለቱን
ጠብቆ እንዲሄድ ማድረግ አይቻልም ወይ?
አቶ ይክፈለው
ወ/መስቀል፡- በሚገባ ይቻላል”” ዋናው የልማት ሀይል ህዝቡ ነው””
አመራሩ የማስተባበር ሚና የሚወጣ ካልሆነ በስተቀር በእውቀቱ በጉልበቱ በገንዘቡ ታምር መስራት የሚችለው ህዝቡ ነው፡፡
በምርጫው ያረጋገጥነውም ይህንኑ ነው፡፡ የተለየ በጀት አልፈቀድንም የተለየ መመሪያ አላዘጋጀንም ነገር ግን ከህዝቡ ጋር ተቀራርበን
ጥያቄው ምን እንደሆነ አዳምጠን መልሰን ህብረተሰቡን አሣትፈን መስራት በመቻላችን ነው በርካታ ችግሮችን መፍታት የቻልነው፡፡ አሁንም
አጠናክረን መቀጠል አለብን በሚል እንደክፍለ ከተማ መግባባት ላይ ደርሰናል፡፡
ህዝቡን
በማሣተፋችን በክፍለ ከተማችን ከ33 በላይ ደረጃውን የጠበቀ የፖሊስ ማዕከል በህብረተሰቡ ተሣትፎ ብቻ ተገንብቷል፡፡ አሁንም ከ20
በላይ የፖሊስ ማዕከሎች በመገንባት ላይ ናቸው፡፡ ለህብረተሰቡ የአንድ ማዕከል አገልግሎት እንዲያገኝ መንግስት ከ240 ሚሊዮን ብር
በላይ በማውጣት ያሰራው የአስተዳደር ህንፃና ሌሎች ከ21 በላይ የመንግስት ፕሮጀክቶችና በርካታ የህብረተሰብ የልማት ስራዎች በቅርቡ
መመረቃቸውም የሚታወስ ነው፡፡
በከተማ
አስተዳደሩም ከ8 በላይ መንገዶች በክፍለ ከተማችን በመገንባት ላይ ናቸው፡፡ የፈረንሣይ አካባቢ ነዋሪ የረጅም ጊዜ የመንገድ ጥያቄ
የመለሰውን የፈረንሣይ መንገድ መጥቀስ ይቻላል፡፡
በኮተቤ
አካባቢ የሚገኙ ወረዳዎች አካባቢያቸውን ኮብል ስቶን አንጥፈው ወደ ትምህርት ቤትና መሰል ተቋማት ገብተዋል፡፡ ይህ የሚያሣየን የህዝቡ
የማልማት አቅምና ፍላጐት አሁንም ከፍተኛ መሆኑን ነው፡፡ ስለዚህም ይህን የልማት ግለት ለማስቀጠል በህዝቡ ዘንድ ምቹ ሁኔታ ያለ
በመሆኑ ግለቱን ጠብቆ መቀጠል ይቻላል፡፡
ህዳሴ፡-
ቀጣይ በሚሰሩ ስራዎች ላይ የህዝቡ ሚና ምን መሆን አለበት ይላሉ?
አቶ ይክፈለው
ወ/መስቀል፡- ህዝቡ ከእድገት ጋር ተያይዞ የሚመጡ ችግሮችን ለመፍታት ከአመራሩ ጋር መተባበር፣ ተሣታፊነቱን እያዳበረ መሄድና በሌላ
በኩል በአመራራችን የሚታዩ የአመለካከትና የስነ ምግባር ችግሮችን እየታገለ ተጠያቂነትን ለመፍጠር የምናደርገውን እንቅስቃሴ እያገዘ
መሄድ ከቻለ ሚናውን መወጣት ይችላል፡፡ እንደከዚህ በፊቱ አክራሪነትንና ኪራይ ሰብሣቢነትን ከአስተዳደሩ ጐን እየታገለ የልማት ተሣትፎውን
አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል፡፡
ህዳሴ፡-
በአምስተኛው አገር አቀፍ ምርጫ ህዝቡ ድምፁን ለኢህአዴግ መስጠቱ የሚፈጥረውን ድርብ ኃላፊነት እንዴት ይገልፁታል?
አቶ ይክፈለው
ወ/መስቀል፡- ህዝቡ ትልቅ አደራ ነው ያሸከመን፡፡ ትልቅ ኃላፊነት ነው የጣለብን”” ለአመራሩ እንቅልፍ የሚነሣ ነው፡፡ እስካሁን
ከሰራነው እጥፍ መስራት እንደሚጠበቅብን ያሣያል”” በየጊዜው የህብረተሰቡ ፍላጐት እያደገ ነው የሚመጣው፡፡
ባለፉት
አመታት ጥሩ ሰርታችኋል”” ነገር ግን የሚቀራችሁ አለ ብሎ ነግሮናል”” ይህም ቢሆን ከናንተ በላይ አማራጭ የለምና አጠናክራችሁ
ልትመሩን ይገባል ብሎ በሁሉም አካባቢ ይሁንታውን ስለሰጠን ተመርጠናል”” በመሆኑም በምርጫው የተረከብነው ኃላፊነትና አደራ ከባድ
ነው፡፡
ህዳሴ፡-
በመጨረሻም ለክፍለ ከተማው ህዝብና በየደረጃው ለሚገኘው አመራር የሚያስተላልፉት መልዕክት ካለ?
አቶ ይክፈለው
ወ/መስቀል፡- በመጀመሪያ ህዝባችን ጉድለታችንን እንደጉድለት ዘርዝሮ በመንገር ይህንንም እንዲሞላው ለድርጅታችን ይሁንታውን ስለሰጠን
ከልብ ማመስገን እፈልጋለሁ”” በቀጣይም 2008 እና በሁለተኛው እድገትና ትራንስፎርሜሽን ከእቅድ ጀምሮ እስከ ተግባር ግምገማ አብሮን
እየተሣተፈ በውጤታማነት ለነዋሪዎቿ የተመቸችና ጽዱ ክፍለ ከተማ እንድትሆን ከጎናችን እንዲቆም ለህዝቡ መልዕክት ማስተላለፍ እፈልጋለሁ፡፡
ለአመራሩና
ለፈፃሚው ደግሞ ህዝቡ የጣለብንን አደራ በትክክለኛ ትርጉም ተገንዝቦ ከዚህ በፊት የነበሩ ጉድለቶች እንዳይደገሙ ተገቢውን ጥንቃቄ
በማድረግ የህዝቡን ጥያቄ ለመመለስ የድርጅቱን አላማና የሀገሪቱን ህዳሴ ለማረጋገጥ የበኩሉን አስተዋጽኦ መወጣትና መስዋዕትነቱን
አጠናክሮ መቀጠል አለበት የሚል መልዕክት ለማስተላለፍ ነው የምፈልገው፡፡
ህዳሴ፡-
አመሠግናለሁ፡፡
አቶ ይክፈለው
ወ/መስቀል፡- እኔም አመሠግናለሁ፡፡
No comments:
Post a Comment