Thursday, 6 August 2015

አንፀባራቂ ድሎቻችን በመጠበቅ ለቀጣይ ከባድ ህዝባዊ ኃላፊነት በቁርጠኝነት እንነሳ!!

ህዳሴ ጋዜጣ

 
መጀመሪያውን ዙር የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ አጠናቀን በደማቅ አገራዊ ምርጫ ድል ታጅበን ወደ ሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ በመሸጋገር ላይ እንገኛለን”” በተግባር ላይ የዋለው የመጀመሪያው ዙር የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ በሁሉም መስኮች አንፀባራቂ ድሎች የተመዘገቡበት ሂደት የነበረ ሲሆን ወደ ፊት ሊቀረፉ የሚገባቸው ውስንነቶችም ነበሩት፡፡
በመጀመሪያ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዘመን መጨረሻ አምስተኛው ዙር አገራዊ ምርጫም ስለተካሄደ ጥንካሬዎቻችንና ድክመቶቻችን በህዝባችን እይታ ፍንትው ብለው እንዲወጡ ያደረገና መላው የከተማችን ነዋሪዎች በዴሞክራሲያዊ ምርጫ በካርዳቸው የልማታዊ ዴሞክራሲያዊ የተሃድሶ መስመራችንን ቀጣይነት አረጋግጠዋል፡፡ ይህ ለድርጅታችን ኢህአዴግ ትልቅ ስኬትና ከባድ ኃላፊነትም ነው፡፡ በመሆኑምለ2008 እቅድ ዓመት ብቻም ሳይሆን ለሁለተኛው የእድገትና ትራንሰፎርመሽን እቅድ ዘመን ጥንካሬዎቻችንን እና ድክመቶቻችንን ገምግመን ጥንካሬዎቹን ይበልጥ ለማጎልበት ድክመቶቻችንን ለማረም የሚያስችል ትምህርት መውሰድና ዝግጅት ማድረግ ይጠበቅብናል፡፡
 
1/ የኢህአዴግ የተሃድሶ መስመር ምሰሶዎች ፣ የከተማ አስተዳደሩ
  ራዕይ ተልእኮና የህዝባችን ፍላጎት
 
የተሃድሶ መስመራችን ምሰሶዎች ልማት፣ ዴሞክራሲና መልካም አስተዳደርን ማረጋገጥ ነው”” እነዚህ ዓላማዎች እየተሳኩ ሲሄዱ አስተማማኝ ሰላም እየተረጋገጠ ይሄዳል ተብሎ ይታመናል፣ ሰላም የልማትና የመልካም አስተዳደር መነሻም ውጤትም ሊሆን ይችላል፡፡ ለማልማት አስተማማኝ ሰላም ያስፈልጋል ልማትና የህዝብ ተጠቃሚነት ካለ ደግሞ አስተማማኝ ሰላም ይኖራል፡፡ ስለዚህ አንዱ የሌላኛው መነሻ ወይም ውጤት በመሆን በተመጋጋቢነት እየተጠናከረ ስለሚሄድ ሰላም የልማት፣ የዴሞክራሲና የመልካም አስተዳደር አካል ተደርጎ ይወሰዳል፡፡
 ልማት ስንል በተሃድሶ መስመራችን አቅጣጫ መሰረት ፈጣን፣ ቀጣይነት ያለው ህዝቡ በየደረጃው ተጠቃሚ የሚሆንበት ልማትና እድገት እንደሆነ በግልጽ ተቀምጧል፡፡ ይህ ማለት ልማትና እድገት ሊኖር ይችላል፡፡ ነገር ግን ፈጣን ካልሆነና ቀጣይነት ከሌለው ለመገመት የሚያስቸግር አደጋ ሊገጥመን ይችላል ማለት ነው፡፡ እድገት ኖሮ ህዝቡ በየደረጃው ተጠቃሚ የሚሆንበት ካልሆነ ሰላም አይኖርም፣ ጤናማ እድገት አይሆንም ማለት ነው፡፡ ይህን መነሻ በማድረግ ድርጅታችን ኢህአዴግ ፈጣን፣ ቀጣይነት ያለው፣ ህዝቡ በየደረጃው ተጠቃሚ የሚሆንበት ልማትና እድገት የማረጋገጥ ግልጽ የልማት አቅጣጫ በተሃድሶ መስመራችን አንጥሮ በማስቀመጥ ተግባራዊ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡
ከተማችን አዲስ አበባ በ2017 መካከለኛ ገቢ ካላቸው ከተሞች ጋር ተወዳዳሪ የሆነች፣ ለኑሮና ለስራ ምቹና የመልካም አስተዳደር ተምሳሌት እንድትሆን የማድረግ ራዕይ አንግቦ ሰላም የማረጋገጥ ፈጣን፣ ቀጣይነት ያለውና የከተማችን ህዝብ በየደረጃው ተጠቃሚ የሚሆንበት ልማት የማረጋገጥ ዴሞክራሲና መልካም አስተዳደር የማስፈን ተልእኮ ለማሳካት እየተረባረበ ይገኛል፡፡ በዚህ መሠረት በተሃድሶ መስመራችን ከተቀመጠው አቅጣጫና በመጀመሪያው ዙር የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ከተቀመጡት ግቦች አንፃር ያለንበት ደረጃ ምን ይመስላል? ሊጠናከሩ የሚገባቸው ስኬቶችና በፍጥነት ሊታረሙ የሚገባቸው ክፍተቶችን ጠቅለል ባለ መልኩ እንደሚከተለው ለማንሳት ተሞክሯል””
 
2/ ባለፉት አምስት አመታት የተገኙ ድሎች
 
ከተሃድሶ በኋላ  በአገር ደረጃ ልማት፣ መልካም አስተዳደር፣ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ድሎች እንደተጠበቁ ሆነው በመዲናችን አዲስ አበባም በተለይም ባለፉት አምስትና ስድስት ዓመታት ፈጣን የልማትና እድገት ግስጋሴ እየታየ መሆኑ ዓለም የመሰከረለት ሃቅ ሆኗል፡፡ በቤቶች ልማት ረገድ የከተማ አስተዳደራችን ከ136,000 በላይ ቤቶች ለተጠቃሚ በማስተላለፍ ከ 675,000 ህዝብ በላይ ተጠቃሚ ያደረገ ስኬታማ የቤት ልማት ኘሮግራም እየተካሄደ ይገኛል፡፡ የቤት ልማት ኘሮግራማችን የመጠለያ ችግርን ከመፍታት ባሻገር የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪውን በማሳደግና የስራ እድል በመፍጠር እንዲሁም ፍትሃዊ የሀብት ክፍፍል በማረጋገጥ ረገድ ጉልህ ሚና እየተጫወተ ይገኛል፡፡
በከተማችን ባለፉት አምስት ዓመታት ሲካሄድ በቆየው መጠነ ሰፊ የስራ እድል ፈጠራና የኢንተርኘራይዞች ልማት ኘሮግራም በዕቅድ ዘመኑ ለ735,772 ዜጎች የስራ እድል በመፍጠር የኑሮ ውድነትን ከመቋቋም አኳያ ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል፡፡ ከኢንተርኘራይዞች ልማት አንፃር የማደራጀት፣ የማሰልጠን፣ የብድር አቅርቦት፣ የገበያ ትስስር፣ በቴክኒክና ሙያ የኢንዱስትሪ ኤክስቴንሽን ድጋፍ በመስጠት፣ ባለፉት ሁለት ዓመታት ደግሞ የድጋፍ አሰጣጡን ለማጠናከር በ 114 ወረዳዎች የአንድ ማእከል አገልግሎት ማደራጀት ተችሏል፡፡ በዚህም በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ የከተማችን ወጣቶችና ሴቶች ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡ በዚህ ዘርፍ ያለው ችግር የድጋፍና ክትትል አሰጣጥ ስርዓቱ ደካማ ስለሆነ መስተካከል አለበት፡፡
በከተማችን ከተመዘገቡት አመርቂ ውጤቶች አንዱ በመሰረተ - ልማት የመጣው አስደናቂ ለውጥ ነው፡፡ የመንገድ ልማት ሽፋኑን ባለፉት አምስት ዓመታት ብቻ ከ 9.2 በመቶ ወደ 20.1 በመቶ በማሳደግ ከፍተኛ ውጤት ተመዝግቧል፡፡ የከተማችንን የውሃ አቅርቦት ችግር ለመፍታት በተደረገው ርብርብ በቀን የሚመረተውን የውሃ መጠን ከ 265 ሺህ ሜትር ኪዩብ በእቅድ ዘመኑ መጨረሻ ወደ 599 ሺህ ሜትር ኪዩብ በማሳደግ ሽፋኑን ከ 64 በመቶ ወደ 90 በመቶ ማድረስ ተችሏል፡፡ በዚህም ተቋም ያለው ዋናው ችግር የአገልግሎት አሰጣጥ ስርዓቱ ደካማ በመሆኑ መስተካከል አለበት”” በመንገድ ግንባታ ሂደት የነበሩ መጓተቶችን፣ የጥራትና የቅንጅት ችግሮችንም በተመሰሳይ በቀጣይ መፍታት አለብን””
በማህበራዊ ልማት ዘርፍ፣ የትምህርት ተደራሽነትና ጥራትን ለማሳደግ የተደረገ ጥረትና የተገኘው ውጤት፣ ሞዴል ትምህርት ቤቶች የመፍጠር እንቅስቃሴና አበረታች ውጤን ማሳየቱ፣ ቀጣይነት ያለው ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት መረጋገጡ በስኬት የሚገለፅ ነው፡፡ በጤና ልማት በኩልም በአብዛኛው ወረዳዎች ጤና ጣቢያዎች በመገንባትና ነባር ሆስፒታሎችንም በማስፋፋት የጤና ሽፋን አገልግሎቱ መቶ በመቶ መድረሱ፣ የእናቶችና ህፃናት ሞት በከፍተኛ ደረጀ መቀነሱ፣ ሴቶች በልማት ቡድን ተደራጅተው የጤና ልማት ባለቤት መሆን መጀመራቸውን እንመለከታለን”” ከዚህም በተጨማሪ የወጣት ማእከላት መስፋፋታቸው፣ የጎዳና ተዳዳሪን ወጣቶችን ስራ ማስያዝ፣ ወላጅ አልባ ህፃናትን መንከባከብ፣ አረጋውያንን መንከባከብ፣ አካል ጉዳተኞችን መንከባከብ መጀመራችን በማህበራዊ ልማት ከተገኙ ስኬቶቻችን መካከል ሊጠቀሱ ይችላሉ፡፡ በዚህ ዘርፍ ያሉ የስራ ጥራትና የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮች እንደየተቋሙ መገለጫና ባህሪ ተገምግመው አንድ በአንድ መስተካከል ይገባቸዋል፡፡
ባለፉት ዓመታት የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከቶችና ተግባራትን እየታገልን ገቢያችን ከዓመት ዓመት እያደገ እንዲመጣ በማድረጋችን፣ ከበጀታችን የካፒታል ወጪ በአማካይ 66 በመቶ እንዲይዝ በማድረግ የከተማችን ልማት በፍጥነት እያደገ እንዲመጣ አድርጓል፡፡
ከፍ ሲል በተገለፁና በሌሎች ተጨማሪ ምክንያቶች የከተማችን አማካይ የእድገት ምጣኔ ከአጠቃላይ አገራዊ አማካይ የእድገት ምጣኔ በላይ ሆኖ ተገኝቷል፡፡ የድህነት ደረጃው በመጀመሪያው የእቅድ ዘመን ከነበረበት 28.1 በመቶ ወደ 26 በመቶ ወርዷል”” በ2007 መጨረሻ የድህነቱ ደረጃ ወደ 22 በመቶ እንደሚወርድ ተገምቷል፡፡ የስራ አጥነት ምጣኔው ከነበረበት 27.9 በመቶ ወደ 23 በመቶ ወርዷል፡፡ (ይህ ስሌት የ2007ትን ተጨማሪ መረጃ አይጨምርም)፡፡ ይህ እውነታ የሚያሳየው ነገር ቢኖር የተሃድሶ መስመራችን፣ ፖሊሲያችንና ስትራቴጂያችን የህዳሴ ጉዟችንን በአስተማማኝ ሁኔታ እየመራና እያፋጠነ መሆኑን፣ የከተማችን አስተዳደርም ተልእኮውን ከመወጣት አንፃር አበረታች ውጤቶች እያስመዘገበ መሆኑን ያመለክታል፡፡
 
3/ የ2007 ሃገራዊ ምርጫ ምን ይነግረናል?
 
የዘንድሮው ሃገራዊ ምርጫ በባህሪው ለየት ያለ ነበር፡፡ በአንድ በኩል የኒዮ-ሊበራል አሽከሮች የተሃድሶ ጉዟችንን በመቀልበስ ከተቻለ ለማሸነፍ ካልተቻለ ለመበጥበጥ ከቅድመ ምርጫ ጀምረው ሰፊ ርብርብ ያካሄዱበት፤ በሌላ በኩል አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ድርጅታችን የልማታዊ ዴሞክራሲያዊ መስመራችንን ቀጣይነት ለማረጋገጥ የተፋለመበት ምርጫ ነበር፡፡ ከዚህ አንፃር ምርጫው የተመራበት አግባብ ለቀጣይ ስራዎቻችን ምን ትርጉም ይኖረዋል? ምን ትምህርት እንወስዳለን? ምን አይነት ድምዳሜዎች ማስቀመጥ እንችላለን? የሚሉ ነጥቦችን በሚመልስ መንገድ አጠር አድርጎ ማየቱ ጠቃሚ በመሆኑ እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡
 
 - በጠራ ስትራቴጂ፣ እቅድና ጥብቅ የአመራር  
  ዲሲኘሊን ግቦቹን ያሳካ ደማቅ ፍፃሜ
 
ምርጫው በጠራ ስትራቴጂና እቅድ የተመራ ነበር፡፡ ስትራቴጂው የ2002 ምርጫን መነሻ ያደረገ ሆኖ ግልፅ ህሊናዊና ነባራዊ የሁኔታ ግምገማ፣ የሃይሎች አሰላለፍ፣ ስትራቴጂካዊ ግቦች፣ መሠረታዊ የማስፈፀሚያ አቅጣጫዎችን የመለሰ ነበር፡፡ ስትራቴጂውን ተግባራዊ ማድረግ የሚያስችል በየደረጃው ጥራት ያለው እቅድ እንዲዘጋጅ ተደርጓል፡፡
አመራሩና መዋቅራችን ከጅማሬው የስራ ክፍፍል በማድረግ የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራን የሚመራና የምርጫ ስራን የሚመራ ብሎ በማደራጀት እርስ በርሱ እየተመጋገበ በጋራ ኮሚቴዎችና ራሱን ችሎ በምርጫ ኮሚቴ የከተማና ክ/ከተማ የጋራ መድረክ በየሳምንቱ እየገመገመ፣ ልምድ እየተለዋወጠ፣ ችግሮችን እየለየና መፍትሄዎችን እያስቀመጠ በጥብቅ ዲሲኘሊን የተመራበት አግባብ ለቀጣይ ስራዎቻችን ምሳሌ የሚሆነን ነው፡፡
አባሉም ምርጫው በስኬት እንዲጠናቀቅ በእቅድ ከመመራት ጀምሮ፣ ራሱን፣ ቤተሰቡንና የቅርብ ጎረቤቱን በፍጥነት የምርጫ ካርድ እንዲወስድ በማድረግ፣ በኔትወርክ አማካይነት የድርጅታችንን የምርጫ መልዕክቶች በአፋጣኝ እንዲተላለፉ በማድረግ፣ አፍራሽ የቅስቀሳ ጽሁፎችንም ሆነ መልዕክቶችን ሲያይ ለሚመለከተው አካል በፍጥነት የማስተላለፍና በአመለካከት የመታገል፣ በድምፅ መስጫው ዕለትም በስሩ የያዛቸውን መራጮች በነቂስ በማውጣት ምርጫው ቀድመን በያዝናቸው ግቦች መሰረት እንዲጠናቀቅ የተጫወተው ሚና ከፍተኛ እንደነበር መውሰድ ይቻላል፡፡
በውጤቱም ምርጫው ከጅማሬው እስከ ፍፃሜው ሰላማዊ፣ ነፃና ፍትሃዊ፣ ዴሞክራሲያዊ፣ በህዝብ ዘንድ ተአማኒነት ያተረፈና በሚያስገርም ሁኔታ በሁሉም ምርጫ ጣቢያዎች ኢህአዴግ በአሸናፊነት በማጠናቀቅ የምርጫ ግቦቻችን ሙሉ በሙሉ የተሳኩበት ደማቅ ፍፃሜ ሆኖ ተጠናቋል፡፡
ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ በምርጫው ሂደት የታዩ የተለያዩ ክፍተቶችም ነበሩ፡፡ በእቅድ ዝግጅት እስከ ወረዳ በተሻለ ደረጃ የተዘጋጀ ሲሆን የታችኛው መዋቅር ላይ የግል እቅድ ግን መጓተትና መንጠባጠብ እንዲሁም የጥራት ችግር ነበረበት፡፡ በመራጮች ምዝገባ ሂደትም ከተሰጠ አቅጣጫ ውጪ የመስራትና ለማስመዝገብ የመፈለግ አልፎ አልፎ የታየ ጉድለት ነበረ፡፡ ይህ ለቀጣይም ትምህርት ሊወሰድበት ይገባል፡፡
 
 -የተሃድሶ መስመራችን ቀጣይነት በምልአተ  
  ህዝቡ ይሁንታ ያገኘበት ምርጫ
 
ህዝባችን የተጀመረው ፈጣን የለውጥ ጉዞ እንዲቀጥል ካለው ፅኑ ፍላጎት በመነሳት 2007 ምርጫ ከምርጫ 2002  በበለጠ ይሁንታውን የሰጠበት ስኬታማ ምርጫ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ነገርግን ያስመዘገብናቸው ድሎች እንደተጠበቁ ሆነው የልማት ፍሬዎችን ማጣጣም የጀመረና በከፍተኛ ደረጃ ለውጥ ፈላጊ ህብረተሰብ በመፍጠራችን እንዲሁም ያልተፈቱ የመሰረተ-ልማት ችግሮች ማለትም እንደ ውሃ፣ መብራት፣ ትራንስፖርት ያሉ በኛ የአፈፃፀም ጉድለት ምክንያት የሚፈጠሩ የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችም እያሉ ኢህአዴግ የራሱን ችግሮች በራሱ የማረም ባህል አለው በሚል እምነት ከነጉድለታችን ይሁንታውን እንደሰጠን መገንዘብ ይገባል፡፡
ከምርጫ 2007 የምንወስደው መመረጣችንን ብቻ ሳይሆን ህዝባችን ምን ያህል ከባድ ኃላፊነት እንዳሸከመንና ኃላፊነታችንን ለመወጣት ከፍተኛ ዝግጅት ማድረግ እንዳለብን ጭምር ነው”” ለዚህም ነው ድርጅታችን ኢህአዴግ ከምርጫ 2007 ማግስት ጀምሮ ሁለተኛ ዙር የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ አዘጋጅቶ ህዝቡን ወደ ማወያየት የገባው፡፡ በቀጣይ የህዝቡ ግብአት ታክሎበት ዳብሮ ከፀደቀ በኋላ በቀጥታ ወደ ስልጠናና ትግበራ የሚገባ ይሆናል፡፡ ስለዚህ አመራራችንና አባላችን ህዝቡ የሰጠንን ኃላፊነት በብቃት ለመወጣት የተሟላ ህዝባዊ ተነሳሽነት፣ ስነ-ምግባርና ሁለገብ ዝግጁነት ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡
 
 - የዜሮ ድምር የነውጥ ፖለቲከኞችን  
  በዴሞክራሲያዊ መንገድ ያሰናበተ ምርጫ
 
2002 ዓ.ም በተካሄደው 4ኛ ዙር አገር አቀፍ ምርጫ ኢህአዴግ ተቃዋሚዎችን በዝረራ ማሸነፉ የአውራ ፓርቲ እውን መሆንና ከፍ ወዳለ አዲስ ምዕራፍ መሸጋገራችንን የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትራችን መለስ ዜናዊ በምርጫው ማግስት በሐምሌና ነሃሴ 2002 በታተመው አዲስ ራዕይ መጽሔት ባወጣው ፅሁፍ ገልፆ ነበር። ይህ እውነታ የተፃፈው ኢህአዴግ ለቀጣይ ተከታታይ ምርጫዎች በከፍተኛ ድምፅ በማሸነፍ በአውራ ፓርቲነት ሊቀጥል እንደሚቻል ታሳቢ በማድረግ ነበር።
በ2007 አገር አቀፍ ምርጫም ኢህአዴግ ከ2002 አገራዊ ምርጫ በተሻለ ደረጃ ሙሉ በሙሉ በማሸነፍ የአውራ ፓርቲነት ቦታውን አጠናክሮ ቀጥሎበታል፡፡ የዜሮ ድምር የነውጥ ፖለቲከኞችን ህዝቡ በዴሞክራሲያዊ መንገድ ጥግ አስይዞ ሸኝቷቸዋል። ይህ የሚያሳየው ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ የተሃድሶ መስመራችን ምን ያህል ስር እየሰደደ እንደሆነና ህዝቡን በየደረጃው ተጠቃሚ እያደረገ እንዳለና ስለሆነም ህዝቡ የተጀመረውን ልማት፣ ዴሞክራሲና ሰላም እንዲቀጥል ያለው ፍላጎት ከፍተኛ መሆኑ፣ ያሉትን የመልካም አስተዳደር ችግሮችንም ቢሆን ሊፈታው የሚችለው ራሱ ኢህአዴግ መሆኑን በመተማመን እንደሆነ በግልፅ ነግሮናል።
አንዳንድ ወገኖች ኢህአዴግና አጋሮቹ ሙሉ በሙሉ በማሸነፍ ሁሉንም ወንበሮች ጠራርገው መያዛቸው ለዴሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታውና የመድብለ ፓርቲ ስርአቱን አደጋ ላይ የሚጥል ነው የሚል ስጋት ሲሰነዝሩ ይደመጣሉ። ይህ አባባል አንድም የተቃዋሚዎቹን ማንነት በትክክል አለማወቅ አልያም የመድረኩን ባህሪ በትክክል አለመገንዘብ ሊሆን ይችላል፡፡ ዋናውና መሰረታዊው ጉዳይ ተቃዋሚዎች ጥጋቸውን የያዙት በዴሞክራሲያዊ ምርጫ እስከሆነ ድረስ በአውራ ፓርቲ የሚመራ የተረጋጋ የመድብለ ፓርቲ ስርዓት መዳከም ምክንያት ሊሆን እንደማይችል መደምደም እንችላለን፡፡
የከተማችን የ2007 ምርጫ ውጤት ከ2002 የምርጫ ውጤት የተሻለ እንደሆነ ግልፅ ነው። የምርጫ ሂደቱም ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ ፍፁም ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊ በህዝብ ዘንድ ተአማኒነት ያተረፈ፣ ተቃዋሚዎች ሳይቀር የአዲስ አበባን የምርጫ ሂደትና ውጤት መሰረት አድርገው ለመተቸት የተቸገሩበት ሲሆን በሂደቱም በውጤቱም ካለፉት ምርጫዎች የተሻለና አንዳንድ ከራሳችን የምንወስዳቸው ትምህርቶች እንደተጠበቀ ሆኖ በዋና ዋና መመዘኛዎች ሲታይ እንከን የለሽ ምርጫ ነበር ማለት ይቻላል።
 
 - ክፍተቶቻችንን በግልፅ እንድንለይ ያስቻለ 
   ምርጫ
 
አብዛኛው መራጭ ምርጫው ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እና የህግ ልዕልና ተጠብቆ እንዲጠናቀቅ ተደራጅቶ ተንቀሳቅሷል”” በሌላ በኩል ግን አብዛኛው ህዝብና የመንግስት መዋቅር ትኩረታቸውን በምርጫ ላይ ባደረጉበት ሂደት አንዳንድ ግለሰቦች አጋጣሚውን ተጠቅመው ህገ ወጥ ፍላጎታቸውን ለማሟላት ሲሞክሩ ታይተዋል”” ለምሳሌ የመንግስትና የህዝብን መሬት አላግባብ መውረር፣ ህገ ወጥ ግንባታን ህጋዊ ለማድረግ  ጫና ማድረግና የመሳሰሉት ምልክቶች ታይተዋል። እነዚህን ምልክቶች ግን በተነፃፃሪ የጥቂት ሰዎች ዝንባሌና ተግባር ስለሆኑ ለጊዜው አቆይተን በአብዛኛው ህዝብ ለተሰሩ ጥሩ ነገሮች አውቅና ሰጥቶ መስተካከል አለባቸው ብሎ የሰነዘራቸው ክፍተቶች የነበሩ ቢሆንም ይህ መራጭ ግን ድምፁ ለኢህአዴግ የሰጠ ነው፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ ለተቃዋሚዎች ድምፁን የሰጠ አለ”” ተቃዋሚዎች ድምፅ ለምን አገኙ ምክንያቱ ምንድን ነው? በቀጣይ ምን ትምህርት እንወስዳለን? ብለን ማየት ይገባናል፡፡ አንደኛው ምክንያት የመልካም አስተዳደርና አገልግሎት አሰጣጥ ችግሮች ጎላ ብሎ የታየባቸውና በሚፈለገው ደረጃ ባለመቅረፋችን ቅር የተሰኙ ዜጎች፣ ከልማቱ ተጠቃሚ ያልሆኑ ወገኖች  መኖራቸውና የልማቱ ባለቤት አድርገን ማንቀሳቀስ ባለመቻላችን ቅር የተሰኘ መራጭ ቁጥሩ ቀላል አለመሆኑ፣ የአካባቢ ልማት ጥያቄዎች ማለትም ኮብልስቶንና የውስጥ ለውስጥ መንገድ ያልተዳረሰባቸው አካባቢዎች፣ የጎረፍ ማስወገጃ መሸጋገሪያ ድልድዮችና መከላከያ ግንቦች ጥያቄ አለመመለሳችን፣ የወጣት ማዕከላት ጥያቄና የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች ጥያቄ ያልተመለሰላቸው አካባቢዎች፣ በውሃ እጥረት፣ መብራት፣ ትራንስፖርት ችግሮች ቅሬታ ያላቸው ዜጎች የተቃውሞ ድምፃቸውን (Protest vote) የሰጡበት ሁኔታ እንዳለ ማየት ይቻላል።
ሁለተኛ አንዳንድ ወገኖች ደግሞ ኢህአዴግ እንደሚያሸንፍ ገምተው ነገር ግን የተወሰነ ተቃዋሚ ‹‹ለፓርላማ ድምቀት›› መቀላቀል አለበት በሚል አስተሳሰብ በተለይም የተማረ ከሚባለው የህብረተሰብ ክፍል በግልፅ በግል ሚዲያዎችም ጭምር ሲራመድ የነበረና እኛም እንደ አንድ አደገኛና አሳሳች ዝንባሌን ለይተን ዝንባሌውን ለማስተካከል የተንቀሳቀሰንበት ሁኔታ ስለነበር ተቃዋሚዎች ድምፅ ያገኙበት አንድ ምክንያት ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል።
ሶስተኛው እና ትልቁ ምክንያት ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ ስርአታችንን ከመሰረቱ የማይቀበሉና የሚቃወሙ የኪራይ ሰብሳቢ ሃይል መሰረት የሆኑ ያለፈው ስርአት ናፋቂዎችና ተስፈኞች የትምክህት፣ የጠባብነትና የአክራሪነት አስተሳሰብ አቀንቃኞች በድምር የሚወክላቸው ኪራይ ሰብሳቢ ሃይል ወደ ስልጣን እንዲመጣ የሚፈልጉ፣ በህገ ወጥ መንገድ ፍላጎታቸውን ለማሟላት የተንቀሳቀሱ ጥቅማቸው የተነካባቸው፣ ለስርአታችን በተለያየ ምክንያት ከባድ ጥላቻ ያላቸው  ቁጥራቸው ምን ያህል ነው የሚለውን ትተን አነሰም በዛም ለተቃዋሚ ድምፃቸውን መስጠታቸው ሌላ እውነታ ነው፡፡ በድምር ተቃዋሚዎች አሁን ላገኙት ድምፅ የነበረው ተፅእኖ ብቻ ሳይሆን በቀጣይም ጊዜ የሚጠብቅ አደገኛ ሃይል መሆኑን ተገንዝበን ፋታ ሳንሰጥ ጠንክረን መስራት ይኖርብናል።

No comments:

Post a Comment