GTP I የተፈፀመበት
አግባብና ውጤቱ ከህዳሴያችን አንፃር የነበረው ፋይዳ
የመጀመሪያው
ዙር ዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ፈጣን፣ ተከታታይና ፍትሃዊነት ያለው የኢኮኖሚ ዕድገት ማስመዝገብና መዋቅራዊ ለውጥ ማምጣት
ላይ ትኩረት አድርጎ ሲፈፀም የቆየ ሲሆን በርካታ አንፀባራቂ ውጤቶችም የተመዘገቡበትና ለሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሸን ዘመን
እቅድ ጠቃሚ ልምዶች የተገኙበት ነበር፡፡ የሀገራችንን ህዳሴ ማረጋገጥ የምንችለው የተለጠጡና ወገብ የሚያጎብጡ እቅዶችን አቅደን
በመተግበር ብቻ መሆኑን ታምኖበት ተግባራዊ በመደረጉ የጀመርነውን የዕድገት ግስጋሴ ከፍ ወዳለ ደረጃ ለማድረስ አስችሏል፡፡ በየደረጃው
ከአመራር እስከ ህዝብ ድረስ በተደረጉ ጥልቀት ያላቸው ግምገማዎች እቅዱ በአግባቡ ተገምግሞ አቅጣጫዎች ተቀምጠዋል፡፡ የአፈፃፀም
ግምገማው እንደሚያመለክተው ከተቀመጡ ግቦች ውስጥ ቀድመው የተሳኩ፣ በእቅዱ መሰረት የተሳኩ ግቦችና በተለያዩ ምክንያቶች በግባችን
መሰረት ያልተሳኩ ግቦች መኖራቸውን መገምገም ተችሏል፡፡ በመላ ህዝባችን ከፍተኛ ንቅናቄ ታጅበን የፈፀምነው የመጀመሪያው 5 ዓመት
እቅድ በብዙ መልኩ ስኬታማና ጠቃሚ ሀገራዊ ልምዶችም የተወሰዱበት እንደነበር መውሰድ ይቻላል፡፡
የኢኮኖሚ
ዕድገትና የህዝብ ተጠቃሚነትን ከማረጋገጥ አንፃር በአማካይ 10.1
በመቶ ዕድገት ማስመዝገብ የተቻለ ሲሆን በከተማችን በአማካይ በ15 በመቶ በላይ ፈጣን እድገት ተመዝግቧል፡፡ የኢኮኖሚ ዕድገቱ ከፍተኛ የስራ ዕድል የፈጠረ ሲሆን ዓመታዊ አማካይ የነፍስ
ወከፍ ገቢያችን በሀገር አቀፍ ደረጃ 700 ዶላር ደርሷል፡፡ በከተማችን የድህነት ምጣኔው በ1997 ከነበረበት 38.7 በመቶ በ2007 ወደ 22 በመቶ ዝቅ እንደሚል ተገምቷል፡፡ የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ለውጥን ስንመለከት ከ2003-2006 ባሉት አራት ዓመታት
የአገልግሎት ዘርፍ በ2003 64.18 % የነበረው በ2006 ወደ 62.6% ዝቅ ያለ ሲሆን የኢንዱስትሪ ዘርፍ ደግሞ ከ34.79
% ወደ 34.46% ከፍ ብሏል፡፡ ከዚህ በመነሳት መረዳት የሚቻለው የከተማው አብዛኛው ኢኮኖሚ የሚመነጨው ከአገልግሎት ዘርፍ መሆኑን
ነው፡፡ የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ለውጥ ማረጋገጥ ለእድገታችን ዘላቂነትና ወደ መካከለኛ ገቢ ኢኮኖሚ ለምናደርገው ጉዞ ወሳኝ በመሆኑ በመጀመሪያው
ዙር የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ከተጠበቀው ይልቅ የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግር በከተማችን ወደ አገልግሎት ዘርፍ ያዘነበለ ነበር፡፡
የአገልግሎት ዘርፍ ማደግ በከተማችን ኢኮኖሚ ውስጥ ያለው ፋይዳ እንደተጠበቀ ሆኖ የኢኮኖሚውን ምርታማነት፣ የስራ ዕድልና የገበያ
አቅም ለመፍጠር በማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ልማት ላይ እመርታ ማምጣት የሞት የሽረት ጉዳይ ተደርጎ ሊወሰድ የሚገባው ነው፡፡
የመሰረተ
ልማት ፕሮግራሞችን በማሳካት ረገድ በኤሌክትሪክ ሀይል አቅርቦት፣ የመንገድ መሰረተ ልማት ዝርጋታ፣ የባቡር መንገድ ዝርጋታ፣ የቴሌኮሚኒኬሽን
አገልግሎት በማዳራስ፣ ንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦትን በማሳደግ ረገድ አመርቂ ውጤቶች ተመዝግበዋል፡፡ በማህበራዊ ልማት ረገድ የትምህርት
ስርጭትና ሽፋን በማሳደግ እንዲሁም የጤና አገልግሎትን በማዳረስ ረገድ አንፀባራቂ ውጤቶች ተመዝገበዋል፡፡ የማስፈጸም አቅም ግንባታና
ልማታዊ መልካም አስተዳደርን በማረጋገጥም ረገድ እንዲሁ ያለው የእቅድ ምዕራፍ ትርጉም ያለው ርቀት መሄድ ተችሏል፡፡ በአጠቃላይ
አፈፃፀማችን የሚያመለክተው መካከለኛ ገቢ ያለው ዜጋና ከተማ ለመፍጠር የያዝነው ራዕይ ከተቀመጠው ጊዜ አስቀድመን ማሳካት እንደሚቻል
ሲሆን አሁንም ትርጉም ባለው ደረጃ በከተማዋ ውስጥ የሚታየውን ድህነት ለመቅረፍ ቀን ከሌት መስራት የሚጠበቅብን መሆኑንንም መገንዘብ
ያስፈልጋል፡፡
እነዚህንና
ሌሎች ሀገራዊና ከተማ አቀፍ ስኬቶች እንደተጠበቁ ሆነው በሁሉም መስክ ያስመዘገብናቸው ለውጦች በመጠን ረገድ ጎልተው የወጡ ቢሆንም
በሚፈለገው መጠን ጥራትን በማረጋገጥ ረገድ ክፍተቶች አሉ፡፡ ብቁ፣ ጥራት ያለውና ተወዳዳሪ ሆኖ ለመገኘት በየመስኩ ርብርብ ማድረግ
ይጠይቀናል፡፡ የህዝብ ፍላጎት አዳጊ መሆንና ሞጋች ህብረተሰብ እየተፈጠረ ከመሄዱ አኳያ ይህንን ሁኔታ በተጨባጭ የተረዳ እንቅስቃሴ
ሊኖረን ይገባል፡፡
የመጀመሪያው
ዙር እቅድ ስኬታማ ሊሆን የቻለው የእቅዱ ፈፃሚ ሀይሎች በተደራጀ ንቅናቄ በመንቀሳቀሳቸው በተለይም ህዝቡ በእቅዶቹ ዙሪያ እየመከረ፣
አፈፃፀማቸውን እየገመገመ፣ ሲፈጸሙ በባለቤትነት የእቅዱ ፈፃሚ ሆኖ መረባረብ በመቻሉ ነው፡፡ ይህም በሁለተኛው ምዕራፍ እቅድ ይበልጥ
እየተረጋጋጠ ሊሄድ የሚገባው ነው፡፡ የእቅዱ ዋነኛ ባህሪ መሰረታዊ የአመለካከት ለውጥና ሽግግርን (transformation) ማምጣት
ላይ ትኩረት ያደረገ ከመሆኑ አኳያ የልማት ሀይሎች የነቃ ተሳትፎ ተኪ የሌለው ሚና ይጫወታል፡፡ ሁለተኛው ዕቅድ ረቂቅ ለህዝብ ውይይት
በቀረበበት ወቅት በከተማችን በተከፈቱ የህዝብ መድረኮች መረዳት እንደተተቻለው ለቀጣዩ እቅድ ስኬታማነት ህዝቡ ከምንጊዜውም በላቀ
ሁኔታ ድጋፉን የሰጠ መሆኑን ነው፡፡ በ10ኛው የድርጅታችን ኢህአዴግ ድርጅታዊ ጉባዔ ላይም ረቂቅ እቅድ ፀድቆ ከቀጣዩ በጀት ዓመት
ጀምሮ ተግባራዊ መደረግ የሚጀምር ሲሆን ለዚህ እቅድ ተፈፃሚነት በየደረጃው ያለ አመራራችንና መዋቅራችን በከፍተኛ ወኔና እልህ መንቀሳቀስ
ይጠበቅባቸዋል፡፡
GTP II ከህዳሴያችን
አንፃር ምን ትርጉም ይኖረዋል?
የልማታዊ ዴሞክራሲያዊ መስመራችን በተሞክሮነት
የሚወስዳቸው የምስራቅ ኢስያ ፈጣን ኢኮኖሚ ያስመዘገቡ ሀገራት (Asian Tigers) ወይም The
Four Asian Dragons የምንላቸው ታይዋን፣ ደቡን ኮሪያ፣ ሆንግ ኮንግና ሲንጋፖር ከ1960ዎቹ እስከ
1990ዎቹ መጨረሻ ድረስ ፈጣንና ተከታታይነት ያለው አስደናቂ እድገት በልማታዊ መንገድ ማስመዘገብ ችለዋል፡፡ ህዝባቸውን ከድህነት
በማውጣት ዛሬ ሀገራቱ በዓለም ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ መፍጠር የሚችሉ ሀገራት ሆነዋል፡፡ ደቡብ ኮሪያና ታይዋን በአይቲ ማኑፋክቸሪንግ
ዘርፍ በዓለም ቀዳሚ ሀገራት ናቸው፡፡ ሆንግ ኮንግና ሲንጋፖር ደግሞ በዓለም በመሪነት የሚቀመጡ የፋይናንስ ማዕከላት መሆን ችለዋል፡፡
እነዚህ ሀገራት እዚህ ደረጃ ላይ መድረስ የቻሉት በተከታታይ ሊያሰሩ የሚችሉ እቅዶችን አቅደው፣ ወገባቸውን ጠበቅ አድርገው መፈጸም
በመቻላቸውና ልማታዊ አመራር ጥበብን በመከተላቸው ነው፡፡
ከዓለም ፈጣን ኢኮኖሚዎች ውስጥ አንዱ የቻይና
ኢኮኖሚ ነው፡፡ በዓመታዊ ጠቅላላ ምርት ሁለተኛው የዓለም ትልቁ ኢኮኖምም ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ ባለፉት 30 ዓመታት ኢኮኖሚያቸው
በአማካይ በ10 መቶ ሲያድግ ቆይቷል፡፡ ይህም ሆኖ ግን እንደ ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (IMF) ሪፖርት መሰረት ከድህነት ወለል
በታች 6.1 በመቶ ህዝብ ይኖርባታል፡፡ ቻይና ከ1953 ጀምሮ እስከ 2015 ድረስ 12 ጊዜ ያህል ተከታታይ የ5 ዓመታት እቅድ
ስትተገብር ቆይታለች፡፡ በዚህ ውስጥ ከ1958-1962 ድረስ የነበረው ሁለተኛው ዙር እቅድ ታላቁ እመርታዊ ለውጥ የሚል ስያሜ ነበረው፡፡
ሌሎች በመሃል ያሉ የስትራቴጂክ እቅድ ዓመታት የየራሳቸው ስያሜና ልዩ የትኩረት ማዕከላት ነበሯቸው፡፡ በእነዚህ ዓመታት ውስጥ በተከታታይ
ሲተገበር በነበረው እቅድ ውስጥ ከጊዜ ወደ ጊዜ ሀገሪቱን ወደ ኢንዱስትሪ ማዕከልነት በመቀየር፣ በድህነት ውስጥ ያለን ህዝብ የማውጣትና
ሀገሪቱን የማዘመን ስራዎች ትኩረት ተሰጥቷቸው ስለተመሩ ዛሬ ቻይናን ባለ ግዙፍ ኢኮኖሚ ባለቤትነት አምጥተዋል፡፡
እኛ የመጀመሪያውን ዙር የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን
እቅድ በስኬት አጠናቀን ወደ ሁለተኛው ስንሄድ የወጣነው ደገት ቢኖርም አሁንም አሁንም እጅግ ብዙ ያልወጣነው ደገት መኖሩን መገንዘብ
ያስፈልጋል፡፡ ህዳሴያችን የተከታታይ ትውልዶች ትግልን የሚጠይቅና ጉዞው ያለምንም መሰነካከል ፍጥነቱን ጠብቆ እንዲቀጥል ማድረግ
ይገባል፡፡ ከድቅድቅ ጨለማ ወጥተን የብርሃን ዘመንን ለማምጣት የምስራቅ ኢሲያ ሀገራት ያለፉበትን ውጣ ውረድ፣ የረገጡት ድንጋይ
መርገጥና የከፈሉትን መሰዋዕትነት ይበልጥ መክፈል ይጠይቃል፡፡ ዛሬ የጀመርነው የህዳሴ ጉዞ የነገዋን ኢትዮጵያ በማበጀት ሂደት ውስጥ
ያለውን ከፍተኛ ትርጉም በመረዳት በላቀ እልህና ወኔ ለቀጣዩ ተልዕኮ በየመስኩ ራስን ማዘጋጀት ያስፈልጋል፡፡