ህዳር 16 ረፋድ ላይ ነበር የአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ወደ ዝግጅት ክፍላችን የላከው የሚዲያ ሽፋን
ደብዳቤ በእጄ የገባውና መመደቤን ያወኩት፡፡ አላማውም ወደ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ መሆኑ ደግሞ አስፈነደቀኝ፡፡ በደብዳቤው
እንዲህ የሚል ጎልቶ ይነበባል፡፡ “2ኛው ዙር የኪነ ጥበብ ለህዳሴ ጉዞ” እነሆ በእለቱ የመሄድ አጋጣሚውን ማግኘቴ አስደስቶኝ ከቢሮ
የሚያስፈልጉኝን ግብአቶች በመያዝ ወደ ቤት አቅንቼ ለጉዞዬ ስሰናዳ በእለቱ ይተላለፍ የነበረ የምሽት ዜና ትኩረቴን ሳበው፡፡
ዜናው የሻሸመኔ ከተማ ነዋሪ ወ/ሮ አሰለፈች ፀጋዬ የ33 ሺህ ብር ቦንድ መግዛታቸውን ያትት ነበር፡፡ ወይዘሮዋ
የግድቡ ስራ ከጀመረ ከ2003 ጀምሮ በ1 ሺህ ብር ቦንድ ግዥ የጀመሩት ድጋፍ ዛሬ ላይ በችርቻሮ ንግድ ተሰማርተው በሚያገኙት ገቢ
የ33 ሺህ ብር ቦንድ ለመግዛት መብቃታቸውን ለኢብኮ ጋዜጠኛ ያስረዳሉ፡፡