Friday, 27 May 2016

“ልማትን መደበኛ ተግባሩ ያደረገ የከተማ ህብረተሰብ ተፈጥሯል” አቶ ተወልደ ገ/ፃድቃን



የግንቦት 20 25ኛ ዓመት የድል በዓልን ምክንያት በማድረግ ባዘጋጀነው ልዩ ዕትም ጋዜጣ የግንቦት 20 እንግዳ አድርገን ያነጋገርናቸው የአዲስ አበባ ኢህአዴግ ኮሚቴ ጽ/ቤት ሃላፊ
አቶ ተወልደ ገ/ ፃድቃን ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተውናል፡፡ መልካም ንባብ፡፡ 


ህዳሴ፡- አስከፊውን የደርግ ስርዓት ለማስወገድ የተከፈለው መራራ መስዋዕትነት እንዴት ይገልፁታል?
አቶ ተወልደ፡- ሁሉም እንደሚያውቀው ቀደም ብሎ መላው የሀገራችን ህዝቦች በአስከፊ የጭቆና ስርዓት ሲማቅቁ እንደነበር ይታወቃል፡፡ እንደ አንድ ሀገር ከተመሰረተች በኋላ የተለያዩ የፊውዳል ስርዓቶች እየተፈራረቁ በህዝቡ ላይ ብሄራዊና መደባዊ ጭቆና ሲያደርሱበት ኖረዋል፡፡ ይህንን ጭቆና ለመቅረፍ በተለያዩ አካባቢዎች የተለያዩ ትግሎችን ሲያካሄዱ የቆዩ ሲሆን በርካታ የአርሶ አደሮች የአመፅ እንቅስቃሴዎች ነበሩ፡፡ ቀጥሎም በ1960ዎቹ አካባቢ የሀይለ ስላሴን ስርዓት ለመገርሰስ ወይም ለመውደቅ ምክንያት የሆነው የከተማው ተማሪ፣ ላብ አደር ባጠቃላይ አርሶ አደሩ በሙሉ ፀረ ብሄራዊና መደባዊ ጭቆና ላይ ሰፊ ትግል አካሄደዋል፡፡
ለፆታ እኩልነት፣ ለፍትህ፣ ለብሄር ብሄረሰቦች እኩልነት በተለይ የተማሪዎች ንቅናቄ ሰፊ ትግል ሲያደርጉ ቆይተዋል”” በተለያየ መንገድ ማለት ነው፡፡ ነገር ግን ትግሉ የተደራጀ ስላልነበር በህዝብ እንቅስቃሴና ንቅናቄ የሀይለ ስላሴ ስርዓት ሲወድቅ በወቅቱ የተደራጀ የደርግ ሀይል ስለነበር ህዝቡን ነጥቆ ስልጣን ላይ ወጣ፡፡ ህዝቡን የደርግ ወታደር ሀይሉን ከቀማው በኋላ ከትጥቅ ትግል ውጭ ስልጣኑን በሰላማዊ መንገድ ሊያስረክብ እንደማይችል ታመነበት፡፡ በወቅቱ የነበሩ የተማሪዎች ንቅናቄ አመራሮች ይህንን ሲያውቁ የተለያዩ አደረጃጀቶችን መፍጠር ጀመሩ፡፡ ስልጣን የሰፊው ህዝብ መሆን እንደማይችል ካረጋገጡ በኋላ ወደ ትጥቅ ትግል ገቡ፡፡
ከዛ በኋላ ግን በ1967 ዓ.ም የአሁኑ ኢህአዴግ በህወሓት አማካኝነት ወደ በረሀ ወጥቶ የትጥቅ ትግሉ ጀመረ፡፡ ቀጥሎም በቅደም ተከተል የቀድሞው ኢህዴን/ብአዴን፣ ኦህዴድ፣ ደኢህዴን እያለ ለ17 ዓመታት ያህል ብሄር ብሄረሰቦች መብታቸው እንዲከበር፣ ዴሞክራሲ በሀገሪቷ እንዲረጋገጥ፣ ፍትህ እንዲሰፍን፣ ለሰላም ለልማት ለእኩልነት ብለው መራራ ትግል አካሄደዋል፡፡
የትጥቅ ትግሉ ታሪክ በአጭር ጊዜ ተወርቶ የሚያልቅ አይደለም፡፡ በርካታ መራራ የትግል አመታት የታለፈበት ስለሆነ የዚህን ያህል ጊዜ ያስፈልጋል ታሪኩን በደንብ ለመተንተንና ግንዛቤ ለማስጨበጥ፡፡ በጥቅሉ ግን ከጫፍ እስከ ጫፍ ምንም እንኳ የትጥቅ ትግሉ በአንድ አቅጣጫ ቢጀመርም ህዝቡ በአራቱም አቅጣጫ ታግሏል፡፡ ለምሳሌ በወቅቱ ህወሓት ወደ ትጥቅ ትግሉ ገብቶ ሲታገል የተለያዩ ብሄር ብሄረሰብ ተወላጆች ከአራቱም አቅጣጫ ተቀላቅለው አብረውት ሲዋጉ ነበር፡፡ ቀጥሎም ኢህዴን ማለትም የኢትዮeያ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ የአሁኑ ብአዴን ሲመጣ የተለያዩ ብሄር ብሄረሰቦችን አካቶ ሲታገል ቆይቷል፡፡ ኦህዴድ ሲፈጠርም ህዝባዊ አድማሱ ሰፋ፡፡ የደቡብ ኢትዮeያ ተወላጆችም አንድ አደረጃጀት ፈጥረው በትጥቅ ትግሉ መጨረሻ ዓመታት ታግለዋል፡፡
ስለዚህ የትጥቅ ትግሉ በጣም መራራ የነበረ ሲሆን መስዋዕትነትን የሚጠይቅ፣ የታጠቀን ታጋይ ብቻም ሳይሆን አርሶ አደሩ የከተማው ነዋሪ ለአላማው ከፍተኛ መስዋዕትነት የከፈለበት ሁኔታ ነው የነበረው፡፡ ይህንን መራራ ትግልና ከፍተኛ መስዋዕትነትን ለመክፈል የብሄር ብሄረሰቦች እኩልነት ዴሞክራሲ፣ ሰላም፣ ልማት እንዳይረጋገጥ ዘግቶ የበነረውን ሀይል ለማስወገድ አስቻለ ማለት ነው፡፡
ህዳሴ፡- ግንቦት 20 የህዳሴአችን መሰረት ነው ስንል ምን ማለታችን ነው? ይህንንስ በተጨባጭ ተሞክሮ እንዴት ይገልፃል?
አቶ ተወልደ፡- ግንቦት 20 የህዳሴአችን መሰረት ነው ስንል የትጥቅ ትግሉ የተካሄደበት ዋነኛው ምክንያት ደርግን ለማስወገድ የመጨረሻ አላማ ተደርጎ የተወሰደ አይደለም፡፡ ልማት ለማምጣት፣ ዴሞክራሲያዊት ሀገር ለመመስረት፣ የብሄር ብሄረሰቦች፣ የሴቶች፣ የሀይማኖቶች እኩልነት ለማረጋገጥ ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን ለማስከበር፣ እድገት፣ ብልፅግና የህዝቦች ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ መጀመሪያ ይህንን ለማድረግ የሚያስችል ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር ስለነበር ነው፡፡ ይህን እንዳይደረግ ዘግቶ የያዘን ሀይል መወገድ ስለሚያስፈልግ ብሄር ብሄረሰቦች በአንድነት ተነሱ፡፡
እነዚህን መብቶችና ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ካልተቻለ ሰላምን ማረጋገጥ አይቻልም፣ ዴሞክራሲያዊ መብት ማስከበር አይቻልም፣ ልማት ለማምጣት መላውን ህዝብ ማስተባበር አይቻልም በዚህም ምክንያት ከላይ የጠቀስኳቸውን ለማረጋገጥና ህዝቡን በየደረጃው ተጠቃሚ ለማድረግ ዘግቶ ይዞ የነበረን የደርግ ስርዓት በትጥቅ ትግል ገርስሶ መጣል ያስፈልጋል፡፡ ይህንንም በመፈፀም የትግሉ የመጀመሪያ ምዕራፍ ተጠናቀቀ፣ ሁለተኛው የትግል ምዕራፍ ተበሰረ ማለት ነው፡፡ የህዳሴ ጉዞ መነሻ ማለት ይህ ነው፡፡
በዚህም ምክንያት ሁለተኛው የትግል ምዕራፍ የተሀድሶ ጉዟችን መነሻ ነው ብለን እንወስዳለን፡፡ የደርግ የታጠቀን ሀይል ካስወገድን ኢህአዴግ ታግየ ድሉን ያመጣሁ እኔ ነኝና ስልጣኑን መያዝ ያለብኝእኔ ነኝ አላለም፡፡ በወቅቱ የተለያዩ ፖለቲካ ፓርቲዎች ወደ አንድ ጠረጴዛ መጥተው በአንድ አዳራሽ ውስጥ እንዲመክሩ አንዲዘክሩ እንዲከራከሩ የሚያስችል ምቹ ሁኔታ ተፈጠረ፡፡ ይሄም አንዱ የዴሞክራሲያዊ ስርዓት መነሻ ሆኖ ተወሰደ፡፡ የሽግግር መንግስት ምስረታ ጉባኤ ተካሄደ፣ ከዛ ቀጥሎም ህገ መንግስት ተረቀቀ፣ በህዝብም የነቃ ዴሞክራሲያዊ ተሳትፎ የህገ መንግስቱ ረቂቅ በተወካዮቹ እንዲፀድቅ ተደረገ፡፡
ይህ ሁሉ ተግባር ለህዳሴ ጉዟችን የመሰረት ድንጋይ
4 HÄs¤ ግንቦት 20 qN 2008
ነው፡፡ በአሁኑ ሰዓት እየተገበርነው ያለው ስራ በሙሉ በህገ መንግስታችን ማዕቀፍ ስር ሆነን ነው፡፡ ስለዚህ ይህንን ለማድረግ እንዳንችል በሩን ዘግቶና ቆልፎ የነበረን ሀይል በሩን በርግደን ከፍተን ባናስወግደው ኖሮ ላለፉት 25 አመታት የተሰሩ ስራዎችና ስናስመዘግባቸው የመጣናቸው ድሎች ሊኖሩ አይችሉም ነበር፡፡ የዚህ ሁሉ ውጤትና የህዳሴ ጉዟችን መነሻ የግንቦት 20 ድል ነው ስንል ለዚህ ነው፡፡
ከዚህ ጋር አያይዘን ነው ግንቦት 20 የብሄሮች የትግል ውጤት ነው የምንለውም፡፡ ምናልባት የብሄር ብሄረሰቦች የትግል ውጤት ነው ስንል መጀመሪያ ላይ ለማንሳት እንደሞከርኩት አንደኛ በተበታተነና ባልተደራጀ መንገድ ሁሉም የኢትዮeያ ብሄር ብሄረቦች ሲታገሉ ቆይተዋል፡፡ ሁለተኛ ይህ ትግል እንዲጠነሰስ ምክንያት የሆነ በ60ዎቹ መጀመሪያ የሀይለስላሴን ስርዓት ለማስወገድ መላው የኢትዮeያ ብሄር ብሄረሰቦች በጋራ በገጠርም በከተማም ስርዓቱን አንቀጥቅጠው እንዲገረሰስ ያደረጉት ትግል መነሻውም ይሄው ነው፡፡ ትግላቸውንም አካሄደው መስፍናዊውን አፋኝ ስርዓት ሲገረስሱ ሌላ ወታደራዊ ሀይል ተተካ፡፡ ይህንንም ስርዓትም ሁሉም ብሄር ብሄረሰቦች በከፈሉት መስዋዕት ተወገደ፡፡
ትግሉ የሁሉም ብሄር ብሄረሰብ ውጤት ነው ሲባል መራራውን የትጥቅ ትግል ከሰሜን ኢትዮeያ ተነስቶ ወደ መሀል ሀገር ሲገሰግስ መላው አርሶ አደር ታጋዩን በደስታ በመቀበል የሰው ሀይል መልምሎ፣ ስንቅን በማቀበልም ትልቅ አስተዋፅኦ በማበርከት የራሱን ድርሻ ተወጥቷል፡፡ ባጠቃላይ ህዝቡ ትግሉን ሲመራ የነበረውን ድርጅት ተንከባክቦ ነው እዚህ ደረጃ ላይ በሙሉ ልብ ተቀብሎ ያደረሰው፡፡ ከዚህ ህዝብ አብራክ የፈለቁ የሁሉም ብሄር ብሄረሰብ ታጋዮች ደግሞ በዚህ ድርጅት ጥላ ስር ሆነው ታግለዋል አላማው ከዳር እንዲደርስም እስከመጨረሻ መስዋዕትነትም ከፍለዋል፡፡
ገና ከመነሻው ጥያቄው የህዝብ ነው ትግሉም የህዝብ ነበር ድሉም የመላው ህዝብ ነው የምንልበት ምክንያትም ጥያቄው የመላው ኢትዮeያ ህዝብ ስለነበር ነው፡፡ ጥያቄውም እንዲመለስለት ሁሉም ህዝብ በእኩል ስለታገለ ነው፡፡ በየአካባቢው መስዋዕትነትም ስለከፈለ ነው፡፡
ህዳሴ፡- አዲስ አበባችን ከግንቦት 1983 ዓ.ም በፊት ምን ነበር ያጣችው? ምንስ ትመስል ነበር?
አቶ ተወልደ፡- ሁሉም የሀገራችን ከተሞችና ገጠሩ ክፍል በዴሞክራሲ እጦት ሲማቅቁ ነው የኖሩት፡፡ ከተሞች ሲመሰረቱ ለልማት፣ ለህዝቦች ተጠቃሚነት፣ የእድገት ማዕከል እንዲሆኑ ታስቦ ሳይሆን ለአስተዳደራዊ ስራዎች ቢሮክራሲውን ለማገልገል ተብለው የሚፈጠሩ ከተሞች ነበሩ፡፡ የአዲስ አበባ አመሰራረትም ከዚህ የተለየ አይደለም፡፡
በተለይ ከተማችን አዲስ አበባ የሀገሪቷ ማዕከል እንደመሆኗ መጠን በሁሉም መስክ የመጠቀ እድገት ሊኖራት ይገባ ነበር፡፡ በአደረጃጀቷ፣ ለህዝቡ በምታረጋገጠው ዙሪያ መለስ መብቶች፣ በመልካም አስተዳደርና ከሁሉም በላይ ልማትና እድገት ለማረጋገጥ የህዝቦቿን ተጠቃሚነትና የኑሮ ሁኔታን ለማሻሻል በሚያስችል መንገድ ሲሰራ አልቆየም፡፡
ይልቁንም ከተማዋ የቢሮክራሲ መገልገያ ሆና ወጣቱ እየታነቀ ወደ ማያምንበት ጦርነት የሚማገድባት መማር እንደ ጥፋት የሚወሰድበት፣ ተስፋ የቆረጠ ህዝብ የበዛበት ሁኔታ ነው የነበረው፡፡
ኢህአዴግ በ1983 አዲስ አበባ ሲገባ አዲስ አበባ ምን ትመስል ነበር ለተባለው ከተማዋ በጣም የተጎሳቆሉ መኖሪያ ቤቶችና ድሀ ህዝብ የሚኖረባት የድህነት መገለጫ ከተማ ነው የነበረችው፡፡ ለስሙ ግን ዋና ከተማ ተብላ የምትጠራ እንጂ በየመንደሩ ያረጀ ያፈጀና የተጎሳቆለ መኖሪያ ቤቶች ነው የነበሯት፡፡ አብዛኛውም የከተማዋ ህዝብ በከፍተኛ የድህነት አዝቀት ውስጥ ይማቅቅ የነበረ ሁኔታ ነው የነበረ፡፡ ይህንንም ችግር ለመፍታት ምንም አይነት ጥረት የማይደረግበት ሁኔታ ነው የነበረው፡፡
ህዳሴ፡- ባለፉት 25 ዓመታት የመጡ ለውጦችስ እንዴት ይገለፃሉ?
አቶ ተወልደ፡- መንግስት በመሰረተ ልማት፣ በኢኮኖሚ ልማት፣ በዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ የተረጋጋ የኑሮ ሁኔታ በከተማዋ እንዲፈጠረ የቻለውን ሁሉ በማድረግ በአጭር ጊዜ በርካታ ስራዎችን ሰርቶ ውጤት ማስመዝገብ ችሏል፡፡ ለምሳሌ ከዴሞክራሲ አንፃር ስናይ የከተማዋ ህዝብ በተለያየ መንገድ ዝንባሌና ፍላጎቱን ይገልፅልኛል በሚለው መንገድ ተደራጅቶ እንዲንቀሳቀስ፣ በፆታ፣ በማህበር፣ በንግድና በተለያዩ ማህበራትና አደረጃጀቶች እንዲደራጅና ፍላጎታቸውን በተደራጀ መንገድ እንዲገልፁ እንዲሁም ለዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታም የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እንዲወጡ ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል”” ህዝቡም በቀጥታ በየደረጃው በሚገኙ ምክር ቤቶች ተወካዮቹን እንዲመርጥና በስፋት እንዲሳተፍ ተደርጓል፡፡
በዚህም በከተማችን ብቻ 38 ሺህ ያህል የምክር ቤት አባላት የሚገኙ ሲሆን እነዚህ ዜጎች በቀጥታ በየምክር ቤቶቻቸው እንዲወስኑ የሚያስችል ስርዓት ተዘርግቷል፡፡ ከወረዳ እስከ ከተማ ምክር ቤቶች ማለት ነው፡፡ በአገር ደረጃም ከታየ ከአምስት ሚሊየን ህዝብ በላይ በየደረጃው በሚገኙ ምክር ቤቶች በቀጥታ እንዲወስን አስችሎታል፡፡ ሌላው ህዝብም በየጊዜው እየተገኘ ስለ ኑሮው፣ ስለመልካም አስተዳደሩ፣ ስለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታውና ስለሰላሙ እንዲመክር ችግሮችን እንዲያነሳና እንዲከራከር፣ መፍትሄ እንዲያስቀምጥ የሚያደርግበት ምቹ የፌዴራሊዝም ስርዓት አለው፡፡ ይህ በሀገራችን ያልነበረ ሲሆን በአሁኑ ሰዓት ትልቅ ለውጥ አምጥቷል፡፡
ከልማት አኳያም የከተማችን የመሰረተ ልማት ስራን ስንመለከት በከተማችን ከ83 በፊት የመንገድ ሽፋናችን ከሶስት በመቶ በላይ የማይበልጥ ሲሆን በመጀመሪያ የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ስንጀምርም ከዘጠኝ በመቶ በላይ አላለፈም ነበር፡፡ አሁን ላይ ግን እስከ 21 በመቶ የደረሰበትና የመንገድም ጥራት ደረጃውን የጠበቀ ዘመናዊ መንገድ መስራትና መገልገል ችለናል፡፡
ከተማችን በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ከ83 ዓ.ም በፊት በጣም የተጎሳቆለች ከተማ የነበረች ስትሆን በአሁኑ ሰዓት ግን በሁለት መንገድ ዘመናዊ ከተማ እየሆነች ትገኛለች፡፡ በሁለት መንገድ ስንል በመንግስት ቤቶች ልማት ፕሮግራም ደሀና መካከለኛ ገቢ ያለውን ነዋሪ ተጠቃሚ የሚያደርግ የቤት ልማት እየተከናወነ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ ባለሀብቱ የተለያዩ ሪልስቴቶች የራሱን መኖሪያ ጭምርና የተለያዩ የመገልገያ ህንፃዎችን በመገንባት ከተማዋ ከተጎሳቆለና ለማየት ከሚያስጠላ መንደርነት ወጥታ በዘመናዊ ህንፃዎችና መንደሮች እየተለወጠች ትገኛለች፡፡
በቤት ልማት ኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ በአሁኑ ሰዓት የቤት ችግርን ከመቅረፍ ባሻገር ለበርካታ ዜጎች የስራ እድል መፍጠሪያና በኢንዱስትሪው መስክ በርካታ ኢንዱስትሪያሊስቶች እየፈሩበት ነው፡፡ ወጣቱ በጥቃቅንና አነስተኛ ተደራጅቶ በመስራት ተጠቃሚነቱን እያረጋገጠ ጥሪት በመቋጠርና ወደ ባለሀብትነት እየተሸጋገረ ነው፡፡ ሌላው የተቀናጀ የመኖሪያ አካባቢም ከመፍጠር አንፃር ዘመናዊ መንገድ፣ ፍሳሽ ማስወገጃ፣ ትምህርት ቤቶች፣ የህክምና ተቋማት፣ አረንጓዴ ልማትና በርካታ የአገልግሎት መስጫ ተቋማት ከአፈፃፀም አንፃር ክፍተት ቢኖርባቸውም በተሳካ ሁኔታ የተቀናጀ የመኖሪያ ሁኔታ መፍጠር ተችላል፡፡
 19 HÄs¤ የካቲግንቦት 20 qN 2008
በሌላ በኩል ይህ የቤት ግንባታ የመኖሪያ ቤት እጦት ችግር ከመቅረፍ በዘለለም ፍትሃዊ የሀብት ክፍፍልን ያረጋገጠ ሆኗል”” በዚህም በቤቶች ልማት ፕሮግራማችን ከ600 ሺህ ህዝብ በላይ ተጠቃሚ የሆነበትን ስርዓት ፈጥረናል፡፡ አሁንም በስፋት እየተገነባ ነው፡፡ በአሁኑ ሰዓት እየተሰሩ ያሉ መሰረት ልማቶች እየተለመዱ በመምጣታቸውና ልማቱም እንድሚቀጥል ህዝቡ በመተማመኑ ከዚህ ቀደም ስንሰራና ስንጨርስ ብርቅ ይሆኑብን የነበሩ ልማቶች አሁን ላይ ትላልቅ ሜጋ ፕሮጀክትም ስንሰራ ምንም የማይመስለው ትውልድ እየበዛ መጥቷል፡፡ ይህ ማለት እየለመደው ስለመጣ ማለት ነው፡፡ ሆስፒታሎቻችንን ብናይ ከዚህ በፊት አንድ ህንፃ ገንብተን ካጠናቀቅን በጣም ብዙ ይወራለት የነበረ ሲሆን አሁን ላይ በአምስቱም ሆስፒታሎቻችን አምስት ዘመናዊ ትላልቅ ህንፃዎችን እንደ አዲስ ሆስፒታል ገንብተን አጠናቀን ወደ ስራ አስገብተናል ነገር ግን እንደ አዲስ የማይታይበት ሁኔታ ነው ያለው ለምን ሲባል ልማት በህዝቡ ዘንድ መደበኛ ስራ መሆኑን አረጋግጧልናል፡፡
በትምህርት መስክ ከመጀመሪያ ደረጃ እስከ ሁለተኛና ከፍተኛ ተቋም ድረስ ህንፃ ገንብቶ ወደ ስራ ማስገባት እንደ መደበኛ ስራ ነው እየታየ የመጣው፡፡ በባቡር ትራንስፖርትም ብዙ ሰው በእድሜአችን እናየዋለን ብሎ የማይገምተው ነገር በተግባር በአጭር ጊዜ ተጠቃሚ የሆነበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ የከተማዋን የትራንስፖርት ችግርም ለመቅረፍ በጣም በርካታ የማሻሻያ እርምጃዎች እየተወሰዱ ነው፡፡

ከመልካም አስተዳደርና ከአገልግሎት አሰጣጥ አንፃር በርካታ ችግሮች አሉ፡፡ ነገር ግን ለማሻሻል ሪፎርም ተዘጋጀቶ ተግባራዊ ለማድረግ ጥረት እየተደረገ ነው፡፡ ባጠቃላይ ሲታይ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታችንን ለማሻሻል ህዝቡንም የልማቱ ተሳታፊና ተጠቃሚ ለማድረግ እየተደረገ ያለ ጥረትና ውጤቱ በሁሉም መስክ የሚጨበጥና የሚታይ ለውጥ እየመጣ ነው፡፡ በዚህም የከተማችን ህዝብ የተረጋጋ ህይወት እንዲመራ የሚያስችል ውጤት ነው እየተመዘገበ ያለው፡፡ ይሄ ደግሞ የግንቦት 20 ፍሬና ቱሩፋት ነው፡፡
ህዳሴ፡- የአዲስ አበባ እድገት በሀገራችን የከተሜነት አስተሳሰብና እድገት እንዲመጣ ምን አስተዋፅኦ እያደረገ ነው?
አቶ ተወልደ፡- ከተማችን አዲስ አበባ ዋና የሀገሪቷ ማዕከል አንደመሆኗ መጠን ለሌሎች ከተሞች ምሳሌ መሆን አለባት፡፡ ይጠበቅባታልም፡፡ እስካሁንም ለሌሎች ሞዴል የሆኑ ስራዎችን እየሰራች ነው፡፡ ልምድ የሚፈልግ አካል እንደ አወሳሰዱ ነው”” በእኛ ከተማ እየተሰራ ያለው ሁሉም ስራ ግን ለልምድ ተብሎ ሳይሆን ለከተማው እድገትና ለህዝቡ ተጠቃሚነት በማሰብ ነው”” እግረ መንገዱን ግን የሚሰራው ስራ ለሌሎች ከተሞች ብቻም ሳይሆን ለሌሎች ሀገሮችም ልምድ የሚወስዱበት ቢሆን ችግር የለውም፡፡ እስካሁንም የሀገራችንን የክልል ከተሞች እንተውና በአፍሪካ ደረጃ እንደኛ በቤቶች ልማት እየተሰራ ያለውን ግዙፍ የቤቶች ፕሮግራም መስራት አልቻሉም፡፡ ብዙ የአፍሪካ ሀገሮች አሁን ላይ ከቤቶች ልማት ፕሮግራማችን ልምድ እየወሰዱ ነው፡፡ ከመንገድም ልማት ፕሮግራማችንም እንዲሁ፡፡ በአጭር ጊዜ ይህን ያህል መጠነ ሰፊ የመንገድ ልማት የሚያካሂድ ሀገር ከሰሃራ በታች የለም፡፡
ስለዚህ ለሀገራችን ከተሞች ብቻም ሳይሆን ለአፍሪካ ሀገራት ልምድ ሊሆን የሚችል ውጤት ነው እየተመዘገበ ያለው፡፡ በተለይ ህዝብን በማሳተፍ የአካባቢ ልማትን የማረጋገጥ ጉዳይም በምሳሌነት ሊወሰዱ የሚችሉ በርካታ ነገሮች ከተማችን ላይ እየተሰሩ ነው፡፡ ዋናው ነገር እኛም ከሌሎች እንማራለን ሌሎችም ከኛ ከተማ ስራዎችና ልማቶች ይማራሉ፡፡
ህዳሴ፡- ይህ ሁሉ ውጤታማ ስራ ከተሰራ እንደ ተግዳሮት የሚነሱ ነገሮች ምን ምን ናቸው?
አቶ ተወልደ፡- የህዳሴአችን ጉዞ የሚያጓትትና የሚያደናቅፍ ምናልባትም በከፍተኛ ቁርጠኝነትና ትግል ካልተቀረፈ ወይም ካልተፈታ ሊያደናቅፉን የሚችሉ ማነቆዎች አሉ፡፡ አንዱ ፖለቲካው ኢኮኖሚው ነው፡፡ ፖለቲካ ኢኮኖሚው ለኪራይ ሰብሳቢነት የሚያመች ስለሆነ ነው፡፡ አጠቃላይ ስርዓቱ በእድገትና ታዳጊ ስለሆነ ብዙ አሰራሮቻችን ኋላ ቀር ናቸው፡፡ አመለካከታችን ኋላ ቀር ነው፡፡ ነገር ግን በየጊዜው እድገት ቢኖርም አሁንም ከኋላ ቀርነት አመለካከትና ተግባር የተላቀቅን አይደለንም፡፡ ስለዚህ ኪራይ ሰብሳቢነት ስንል መገለጫው ብዙ ነው፡፡ በአንድ በኩል ባልሰራህበት ለስራህ ለድካምህ የማይመጥን የስራህ የድካምህ ዋጋ ያልሆነ በአቋራጭ የመክበርና የመለወጥ ተግባር ዘረፋ ስርቆት ይሄ አንዱ መገለጫ ነው፡፡ ከመነሻችንም ነበረ አሁንም አለ፡፡ ትልቁ ማነቋችንም ይሄ ነው፡፡ ይህ ደግሞ በመንግስትና በህብረተሰቡ ውስጥ ያሉ ኪራይ ሰብሳቢዎች ተሳስረው የሚፈፅሙት ስለሚሆን ችግሩ በሁሉም ዘንድ ነው ያለው፡፡ እንደ ግለሰብ ሳይሆን እንደ ህብረተሰብ ነው ልንታገለው የሚገባው፡፡ ስለዚህ ከስርአቱ ትልቁ ማነቆ አንዱና ዋነኛው ኪራይ ሰብሳቢነት በመሆኑ በትጋት ልንታገለውና ከምንጩ ልናደርቀው ይገባል፡፡
ሁለተኛው ማነቆ ኋላ ቀር አመለካከቶች የትምክህት፣ የጥበት፣ የአክራሪነት አመለካከቶች አሉ፡፡ ሙሰኛው ሌላ በነዚህ ውስጥ ነው የሚደበቀው፡፡ እነዚህን በመጠቀም ነው የራሱን ትርፍ የሚያግበሰብሰው፡፡ ትምክህት፣ ጥበት፣ አክራሪነት ሲባል ተራ ቃላት ሊመስሉ ይችላሉ ነገር ግን ሀገር የሚያጠፉ ናቸው፡፡
በትምክህትና በጥበት የሚገለፁ በተለያዩ አካባቢዎችም የሚታዩ ምልክቶች አሉ፡፡ በአክራሪነትም በተመሳሳይ መንገድ”” በሀይማኖት ሽፋን ፍላጎትን በሌላው እምነት ላይ ለመጫን የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች በሙሉ ሀገር የሚያጠፉ ናቸው፡፡ በነዚህ ጥላስር ደግሞ ሌላ ሊሸጉጥ ስለሚችል እንደተራ ጥበት፣ ትምክህት፣ አክራሪነት ተብሎ ሊወሰድ አይገባም፡፡ በጣም ትልቅ የስርዓታችን ጋሬጣና እንቅፋቶች ናቸው፡፡ ስለዚህ ዋናው የህዳሴ ጉዟችን ዋነኛ ማነቆ ኪራይ ሰብሳቢነት ነው፡፡ ስለዚህ ህዳሴአችንን በተጠናከረ መንገደ እንዲቀጥል ከሆነ በላቡና በጥረቱ ውጤት ለመጠቀም የሚያስብ ዜጋ መፍጠር አለብን፡፡
ይህንን ዜጋ ከፈጠርን አመራራችን የዜጋው ተምሳሌት ነው ይሆናል እንደ ህብረተሰብ እንደዚህ አይነት አስተሳሰብ ካልተፈጠረ ግን አመራሩም ከህብረተሰቡ ነው የሚፈጠር፡፡ ስለዚህ አመራሩ ይህን ኋላ ቀር አመለካከትና ተግባር ሰብረህ ውጣ ነው እንጂ እየተባለ ያለው እርሱ አይደለም የፈጠረው፡፡ ችግሩን የፈጠረው አጠቃላይ ፖለቲካል ኢኮኖሚው ነው፡፡ ነገር ግን ፖለቲካል ኢኮኖሚውን የመቀየር ሀላፊነት ተሰጥቶታል ለአመራሩ፡፡ የተሰጠውን ሀላፊነት ግን በአግባቡ እየተወጣ አይደለም፡፡ ይጎትተዋል፡፡ ፖለቲካል ኢኮኖሚው እየጎተተ ወደ ጭቃው ያዘቅጠዋል ማለት ነው፡፡ ስለዚህ አሁን ዋናው ችግራችንን ማነቋችን ከኪራይ ሰብሳቢነት ፖለቲካል ኢኮኖሚ የሚነሳ የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከትና ተግባር ነው፡፡ ይሄም በመኖሩ ለልማታችን፣ ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታችን እንቅፋት እየሆነ ነው፡፡ ይህን መፍታት አለብን፡፡
ልማታዊው ሀይል እንዲጎለብት ኪራይ ሰብሳቢነትም እንዲቀጭጭ ማድረግ አለብን በአሰራር በአደረጃጀት በአመለካከት ግንባታ በሁሉም መጠነ ሰፊ እንቅስቃሴ ካልተደረገ የኪራይ ሰብሳቢነት አደጋ ትልቅ ፈተና ነው፡፡ የስርዓታችንና የህዳሴ ጉዟችንም ትልቅ ፈተናና አደጋ ነው ተብሎ ሊወስድ ይችላል”” መፍትሄውም ህብረተሰባዊ ለውጥ ማምጣት ነው፡፡ የኪራይ ሰብሳቢነት ፖለቲካል ኢኮኖሚውን ለመቀየር አንደኛና ዋነኛው መፈትሄ እድገቱን ማፋጠን ነው፡፡
ህዳሴ፡- እናም እድገቱ ራሱ ፖለቲካል ኢኮኖሚውን እየቀየረ ይሄዳል እያልን ነው?
አቶ ተወልደ፡- አዎ! እድገቱ ራሱ ፖለቲካል ኢኮኖሚውን እየቀየረው ይሄዳል፡፡ ስለዚህ እድገቱን በትክክል አቅጣጫ ማስኬድ ይጠይቃል፡፡ ህዝቡንና ዜጋውን ተጠቃሚ እያደረገ ከሄደ፣ እድገቱ ደግሞ መዋቅራዊ ሽግግር ካረጋገጠ ከአገልግሎት ወደ ማኒፋክቸሪንግ ቋሚ ወደሆኑ መዋቅሮች እየተሻገገረ የሚሄድ ልማት ከሆነ ልማታዊው ፖለቲካል ኢኮኖሚው ኪራይ ሰብሳቢ ፖለቲካል ኢኮኖሚውን አሽመድምዶ ይጥለዋል፡፡ መዋቅራዊ ሽግግር ስንል በሁለት መንገድ ነው፡፡ አንደኛ በኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግር መምጣት አለበት፡፡ ወደ አምራችነት በተለይ የኢንዱስትሪ አምራችነት የሚያሸጋግር ሁለተኛ የአመለካከት ለውጥ ማምጣት አለብን፡፡ ይህንን የሚያፋጥን የውስጠ ድርጅት ጥራትና ጥንካሬ ትግል ማጠናከር አለብን፡፡ በህብረተሰቡ ውስጥ ደግሞ ትግል የመለኮስ ስራ መስራት ድርጅቱንና መንግስትን መልሶ እንዲያጠናክር ሰፊ የህብረተሰብ ተሳትፎ እንዲኖር ማድረግ ይኖረብናል፡፡ ልማታዊ ሰራዊት ብለን እንዳስቀመጥነው የድርጅት የመንግስትና የህዝብ የተቀናጀ እንቅስቃሴ ነው የአመለካከት ለውጥ የሚያመጣው፡፡ ተግባራዊ ማድረግ ነው ያለብን፡፡
ህዳሴ፡- ለመላው የከተማችን ህዝብ ግንቦት 20ን አስመልክተው የሚያስተላልፉት መልዕክት ካለ?
አቶ ተወልደ፡- በመጀመሪያ እንኳን ለ25ኛው አመት የግንቦት 20 የድል በዓል በድጋሚ በሰላም አደረሳችሁ እላለሁ፡፡ በመቀጠልም አሁን ላይ ሆነን የግንቦት 20 የድል በዓል ስናከብር የምናያቸውና በውል ልናስተውላቸው የሚገቡ ነገሮች አሉ፡፡ አንደኛው በጣም ተስፋ የሚሰጡ ለውጦችን ያስመዘገብንበት በፈጣን የእድገት ጎደና የምንራመድበት እድገት ማምጣትና ልንለወጥ የምንችል ህዝቦች መሆናችንን ያረጋገጥንበት ጉዞ ነው የተጓዝነው፡፡
በተለይ ከተሃድሶ በኋላ ለ14 ዓመታት ያሀል ባለመቋረጥ በአማካይ ባለድርብ አሀዝ እድገት በተከታታይ አስመዝግበናል፡፡ ይሄ ደግሞ በብዙ ሀገሮች ያልታየና እኛ ግን ተግባራዊ ያደረግነው የእድገት ጉዞ ነው፡፡ ይሄ የሚያሳየን ነገር ምን ያህል የተሀድሶ መስመርና የተሀድሶ ፖሊሲና ስትራቴጂዎቻችን የለውጥ ፖሊሲና ስትራቴጂ መሆኑን ያሳያል፡፡ ያስመዘገብነው ለውጥ መሰረተ ሰፊ ሁሉም ብሄር ብሄረሰቦች እኩል የተጎናፀፉት ነው፡፡ ይሄ ደግሞ የግንቦት 20 ቱሩፋትና ፍሬ ነው፡፡ ይህ በያዝነው መንገድ ከቀጠለ ለውጡ በጣም አስተማማኝና በአጭር ጊዜም መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገራት ተርታ እንድንሰለፍ የሚያስችል ሁኔታን የሚያረጋግጥ ነው፡፡
የሩብ ክፍለ ዘመን ሂደታችንን ስንገመግም፡፡ በአንድ በኩል አሁን እየተፈጠረ ያለና ሂደቱ የሚፈጥራቸው በሌላ በኩል ሂደቱ የሚፈጥራቸውና እየታዩ ያሉ ዝንባሌዎች ይህንን ፈጣን የህዳሴ ጉዟችንን አዳጋ ላይ ሊጥሉ የሚችሉ ነገሮች ግን አሉ፡፡ ጠያቂ ህብረተሰብ ተፈጥራል፡፡ ይህ ጠያቂ ህብረተሰብ የተፈጠረው ደግሞ በተሀድሶ መስመራችን ነው፡፡ ጠያቂ ህብረተሰብ ከሌለ ደግሞ ለውጥ የለም ለውጥ የሚፈልግ ህብረተሰብ መፍጠር ነው ያለበን ብለን ነው የፈጠርነው፡፡ ድርጅታችንና መስመሩ የፈጠረው ነው፡፡ ነገር ግን ራሱ ህብረተሰቡን ለማሳተፍ ከፖሊሲያችን ስትራቴጂዎቿችን የመነጩ አሰራሮችና መርሆዎችን መሰረት አድርገን በፍጥነት ካልመለስን ግን አደጋ ላይ እንወድቃለን ማለት ነው፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ ይህንን እንዳናደርግ የሚያደርገን የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከትና ተግባርን በቁርጠኝነት ለመታገል አመራሩና አባሉ ህዝቡ በተደራጀ መንገድ ለመብቱ ሲታገል ነው”” ህዝቡ መብቱን በገንዘብ መሸጥ የለበትም፡፡ መብቱን በገንዘብም መግዛት የለበትም፡፡ አመራሩ መንግስትና ህዝብ የሰጠውን ተልዕኮ በአግበቡ መወጣት አለበት፡፡ ህዝቡ መብቱን በትግል ማስተካከል ሲችል ደግሞ የኪራይ ሰብሳቢነት አመላከከትና ተግባር እየተናደ ልማታዊ አስተሳሰብና ተግባር እየጎለበት ይሄዳል፡፡ በዛውም ልክ የህዝቡ ተጠቃሚነት እየተረጋገጠ ይመጣል፡፡
ለውጡም የማያቋርጥና መጠነ ሰፊ ሆኖ ይቀጥላል ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ይህንን ለማድረግ መላው አመራራችን፣ አባላችን ምልዓተ ህዝቡ መንግስትና ድርጅታችን የመልካም አስትዳደርን ችግር ለመፍታት፣ ኪራይ ሰብሳቢነትን ከስር መሰረቱ ለመናድ እና ልማታዊ አስተሳሰብንና ልማትን ለማፋጠን ቆርጦ እንደተነሳ ሁሉ ከድርጅታችንና ከመንግስታችን ጎን ተሰልፎ ባለፉት አመታት ያስመዘገባቸውን ድሎች ወደፊትም በማስቀጠል የህዳሴ ጉዟችንን ለማፋጠን በሩብ ክፍለ ዘመኑ የድል በዓል ቃል ኪዳን ገብተን አብረን ልንታገል ይገባል የሚል መልዕክት አስተላልፋለሁ፡፡

የ25ኛ ዓመት የግንቦት 20 የብር ኢዮቤልዩ በዓልን አስመልክቶ ከኢህአዴግ ም/ቤት ፅ/ቤት የተሰጠ መግለጫ




ህዝባዊነታችንን ጠብቀን የአገራችንን የህዳሴ ጉዞ እናፋጥን!

የተከበራችሁ መላ የአገራችን ህዝቦች

ሃያ አምስተኛው የግንቦት 20 የብር ኢዮቤልዩ በዓል ባለፉት የትግልና የድል አመታት ባካሄዳችሁት እልህ አስጨራሽ ትግልና በከፈላችሁት መስዋዕትነት አምባገነናዊ የደርግ ስርአት ተወግዶ፤ አገራችንን ከጥፋት አፋፍ ላይ አድርሷት የነበረው የዘመናት የማሽቆልቆል ጉዞ ተቀልብሶ በምትኩ የህዳሴና የከፍታ ጉዞ እንድትጀምር ያስቻላት በመሆኑ ታላቅና ታሪካዊ ብሄራዊ በዓላችን ነው፡፡ በዓሉን ስናከብር በሩብ ምእተ አመት ጉዟችን ያገኘናቸውን ድሎች አጠናክረን ለማስቀጠልና የሚያጋጥሙ ችግሮችንና ፈተናዎችን በተለመደው ህዝባዊ ጽናት እየታገልን በማለፍ የህዳሴ ግስጋሴያችንን ለማስቀጠል በመዘጋጀት ነው፡፡

ያለፉት ሃያ አምስት ዓመታት የአገራችን ህዝቦች በድርጅታችን ኢህአዴግ መሪነት በየወቅቱ የሚያጋጥሙ ፈተናዎችን በፅናት በመታገል፣ በተሳካ ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ አቅጣጫ እያለፉ በርካታ አኩሪ ድሎችን ያስመዘገቡበት ዓመታት ነበሩ፡፡ በሩብ አመቱ ጉዟችን ሊጠናከሩና ሊሰፉ የሚገባቸው በርካታ ድሎችን የተጎናጸፍንበት ከመሆኑ ባሻገር  ለቀጣዩ የአገራችን የህዳሴ ጉዞ ጠቃሚ ልምዶችና ትምህርቶች ያገኘንበት በመሆኑ የበዓሉን ፋይዳ ከፍተኛ ያደርገዋል፡፡

አገራችን ኢትዮጵያ የተጓዘችበት የሩብ ምዕተ ዓመት ጉዞ ለዘመናት ያለፍንበት የማሽቆልቆል ሂደት ተገትቶ በሁሉም መስኮች ወደፊት የተራመድንበት ነበር፡፡ አገራችን የአዲሱን ሥርዓት ግንባታ የጀመረችው ከምንም ነገር በፊት የዴሞክራሲ መብቶች ያለገደብ የሚከበሩበት ሁኔታ በመፍጠር ነበር፡፡ ለዘመናት በማሽቆልቆል ጉዞ ውስጥ የኖረችው አገራችን ከማንኛውም ዓይነት ውድቀት ነፃ ልትወጣ የምትችለው የዜጎቿና የህዝቦቿ ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ሲከበሩ ብቻ መሆኑ ታምኖበት መሠረተ ሰፊ የዴሞክራሲ ስርአት መገንባት የተጀመረው የደርግ ሥርዓት ከወደቀባት ከመጀመሪያዋ ዕለት ጀምሮ እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡ ላለፉት ሃያ አምስት ዓመታት መጀመሪያ በሽግግሩ ቻርተር፣ ቀጥሎም በኢፌዴሪ ህገ-መንግስት በመመራት የተካሄደው የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ፣ የግለሰብና የቡድን መብቶች ተደጋግፈው እንዲከበሩ አስችሏል፡፡

በኢትዮጵያ የሚገነባው ዴሞክራሲያዊ ስርአት መሠረተ ሰፊ ብቻ ሳይሆን፣ ህጋዊ ዋስትና የተረጋገጠበት ይሆን ዘንድ፣ ህዝቡ ቀጥተኛና ወሳኝ ሚና በተጫወተበት አኳኋን ህገ-መንግስታችን ጥልቅ ዴሞክራሲያዊ ባህርይ ተላብሶ እንዲቀረፅ ተደርጓል፡፡ አገራችን በምትመራበት ዴሞክራሲያዊ ህገ-መንግስት ዓለም አቀፍ መስፈርቶችን የሚያሟሉ የዴሞክራሲ መርሆዎች የህገ-መንግስታችን የማዕዘን ድንጋይ ሊሆኑ ችለዋል፡፡ የሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ህገመንግስታዊ እውቅናና ጥበቃ ተደርጎላቸዋል፡፡ የብሔርና ብሔረሰብ፣ የሃይማኖትና የፆታ እኩልነት መብቶች ተከብረዋል፡፡ በአገራችን ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ህዝቦች የሉዓላዊ ስልጣን ባለቤቶች ለመሆን በቅተዋል፡፡ ላለፉት ሁለት አሰርት ዓመታት ዴሞክራሲያዊ ህገ-መንግስታችንን በመከተል በተካሄደው ጥረት አገራችን ኢትዮጵያ ለዘመናት ከኖረችበት ፀረ-ዴሞክራሲያዊ አገዛዝ በመላቀቅ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታን ልትያያዝ በቅታለች፡፡

የዴሞክራሲያዊ ስርአታችን አሁንም በለጋ እድሜ ላይ የሚገኝና ተጠናክሮ መቀጠል የሚገባው መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ በአገራችን ለዘመናት ስር ሰደው ከቆዩት የጸረ ዴሞክራሲያዊ አገዛዞች ታሪካዊ ሁኔታ እንዲሁም የዴሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታ ከፍተኛ ደረጃ ከደረሰባቸው አገሮች ልምድ አኳያ ሲታይ በሩብ ምእተ አመት ጉዟችን የተመዘገቡ ስኬቶች ስርአቱ የደረሰበትን የጥንካሬ ደረጃ የሚያሳዩ ናቸው፡፡ በዴሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታችን የተመዘገቡ ስኬቶች ከስርአቱ ተፃራሪ የነበሩ አስተሳሰቦችን ለማሸነፍ ዴሞክራሲያዊና ህዝባዊ ትግል በማድረግ የተገኙ የአገራችን ህዝቦች የትግል ውጤቶች ናቸው፡፡ የመንግሥት ሥልጣን በህዝብ ነፃ ምርጫ ብቻ የሚያዝ እንዲሆን በየምርጫው የተደቀኑ ፈተናዎችን በፅናት ታግሎ በማለፍ በየአምስት አመቱ ነጻ፣ ፍትሃዊና ዴሞክራሲያዊ ምርጫዎች ተካሂደዋል፡፡ የብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች መብቶችን ተግባራዊ ለማድረግ በብዝሃነት ላይ የተመሰረተውን ፌዴራላዊ ሥርዓት ተግባራዊ ለማድረግ ከፍተኛ ህዝባዊ ትግል ተካሂዷል፡፡

የተከበራችሁ የአገራችን ህዝቦች

ያሳለፍነው የሩብ ምዕተ አመት ጉዞ በኢኮኖሚያዊና በማህበራዊ መስኮችም ስር-ነቀልና መሰረታዊ ለውጦች የመጡበት ነበር፡፡ በሃያ አምስት ዓመታት ጉዟችን ኢኮኖሚያችን ለዘመናት ከኖረበት የማሽቆልቆል ጉዞ ወጥቶ ፈጣንና ህዝቡ በየደረጃው ተጠቃሚ በማድረግ ላይ የሚገኝ ዕድገት የተመዘገበበት ነው፡፡ ላለፉት ሃያ አምስት ዓመታት በአማካይ በየዓመቱ ከ8 በመቶ በላይ አገራዊ ዕድገት ተመዝግቧል፡፡ በተለይ ከተሃድሶ መጀመር በኋላ ባሉት 14 ዓመታት ደግሞ በአማካይ ከ10 በመቶ በላይ ዓመታዊ ዕድገት የተመዘገበ መሆኑ በእርግጥም አገራችን ኢትዮጵያ ለዘመናት የዘለቀውን የማሽቆልቆል ጉዞ ምእራፍ በአስተማማኝ ደረጃ ተዘግቶ ቀጣይነት ያለው የዕድገት ጎዳና የተያያዘች መሆኑን ያሳያል፡፡ የተከተልነው ትክክለኛ የፖሊሲ አቅጣጫ ኢትዮጵያ የፈጣን ብቻ ሳይሆን ህዝቡን በየደረጃው ተጠቃሚ ማድረግ የሚችል ፍትሃዊነት ያለው እድገት ማስመዝገብ የቻለች አገር መሆኗ የተረጋገጠበት ነው፡፡ በአገራችን የተመዘገበው እድገት በሁሉም የኢኮኖሚና ማህበራዊ መስኮች የተመዘገበ ከመሆኑ ባሻገር ከገጠር እስከ ከተማ ሁሉንም አካባቢዎችንና የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ያደረገና በማድረግ ላይ የሚገኝ ሁሉን አቀፍና መሰረተ ሰፊ ነው፡፡ 

በገጠር አርሶ አደሩ ከመሬት ሳይነቀል ምርታማነቱን እንዲያሳድግና እንዲጠቀም በተከፈተው ዕድልና በተሰራው ዘርፈ ብዙ ስራ ለዘመናት በድህነት የኖሩት የአገራችን አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች ምርታማነታቸውና ገቢያቸው እንዲሻሻል ተድርጓል፡፡ በከተሞችም የአነስተኛና ጥቃቅን፣ የማኑፋክቸሪንግና የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው እንዲስፋፋ መደረጉና በዚህም ሰፊ የህዝብ ተጠቃሚነት መረጋገጥ መጀመሩ በእርግጥም አገራችን ፈጣን ብቻ ሣይሆን ፍትሃዊ ዕድገት እያመጣች መጓዟን የሚያረጋግጥ ነው፡፡ በድርጅታችን የሚመራው ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መንግስታችን ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መሠረት ልማት መስፋፋት በሰጠው ትኩረት በሁሉም የአገራችን አካባቢዎች ለዕድገት ቁልፍ የሆነ የመሠረታዊ ልማት አገልግሎቶች እንዲስፋፉ አስችሏል፡፡ ከአነስተኛ ግድቦች ግንባታ አስከ ታላቁ የህዳሴ ግድብ የዘለቀው የኢነርጂ ልማት፣ ቀበሌን ከቀበሌ ከሚያገናኙ የገጠር መንገዶች እስከ ረዣዥም የባቡር መንገዶችና ደረጃቸውን የጠበቁ  የአውሮፕላን ማረፊያዎች ግንባታ ፣ ከትንሿ ምንጭ ማጎልበት እስከ ትላልቅ የመጠጥና የመስኖ ግንባታ የተስፋፋው የውሃ ልማት፣ ከአናሎግ ወደ ዲጂታልና ፋይበር ኬብሎች የተሸጋገረው የቴሌኮም አውታር ዝርጋታና የመሳሰሉት አገራችን ተወዳዳሪ ኢኮኖሚ ለመገንባት ለምታደርገው ጥረት ሁነኛ አቅሞች በመሆን ላይ ይገኛሉ፡፡
     
በማህበራዊ ልማት መስክ ትምህርትን ለማስፋፋት በተደረገው ጥረት ከአገሪቱ ህዝብ መካከል 30 በመቶ ያህሉ ከአጸደ ህጻናት እስከ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ባሉት ደረጃዎች በመደበኛ ትምህርት ላይ ይገኛሉ፡፡ በአሁኑ ጊዜ ከ27 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች በትምህርት ገበታ ላይ የሚገኙባት  አገራችን አነስተኛ ቁጥር ያለው ህዝብ ያላቸውን ሃያ አምስት የአፍሪካ አገሮች ድምር የህዝብ ብዛት ያህል የሰው ኃይል በማስተማር ላይ ትገኛለች፡፡ ይህ ትልቅ ውጤት አገራችን ትምህርት የልማት ውጤትና የልማት መሳሪያ ብቻ ሳይሆን፣ የህዝብ ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጫ እንዲሆን በማመን ያደረገችው አኩሪ እንቅስቃሴ ውጤት ነው፡፡ በጤና መስክ በተለይ ደግሞ መከላከልን ማዕከል ያደረገ የጤና አገልግሎት በማስፋፋት የተካሄደው እንቅስቃሴ በአገራችን ጤናው የተጠበቀ ህብረተሰብ ለመገንባት አስችሎናል፡፡ የጤና ተቋማትንና የጤና ባለሙያዎችን ለህብረተሰቡ ተደራሽ እንዲሆኑ በማድረግ ከፍተኛ ስኬት ተመዝግቧል፡፡ ባለፉት አመታት ህዝቡን በማሳተፍ በተካሄዱ ዘርፈ ብዙ ተግባራት ቀደም ሲል የዜጎቻችንን ህይወት እንደ ቅጠል ሲያረግፉ የነበሩ እንደ ወባ ያሉ ተላላፊ በሽታዎችን በመከላከል የበርካታ ዜጎቻችንን ህይወት መታደግ ተችሏል፡፡ የእናቶችንና የህጻናትን ሞት በመቀነስ የተገኘው ውጤትም አበረታችና ተጠናክሮ መቀጠል የሚገባው ነው፡፡

ምንም እንኳ በማህበራዊና አኮኖሚያዊ ልማት መስክ  የህዝባችን ችግሮች ሙሉ በሙሉ ያልተቀረፉና ጥረቱን አጠናክረን መቀጠል የሚገባን መሆኑ ባያጠያይቅም፣ አገራችን በፈጣን የዕድገት ጎዳና መረማመዷ በተጨባጭ የማሽቆልቆል ምዕራፍ የተዘጋበትና ትክክለኛ የህዳሴ አቅጣጫ እንደተከተለች የሚያሳይና የተከተልናቸውን ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ትክክለኛነት የሚያረጋግጥ ነው፡፡ ቀደም ባሉት ጊዜያት በአገራችን በየወቅቱ በተከሰቱ የድርቅ አደጋዎች ምክንያት በርካታ ዜጎቻችንን ህይወታቸው ሲቀጠፍ እንደነበር  የሚታወስ ነው፡፡ ካለፈው አመት ጀምሮ እስከ ያዝነው አመት የዘለቀው ከአለም የአየር ንብረት መዛባት ጋር ተያይዞ የተከሰተው ድርቅ አገራችን በታሪኳ ካጋጠሟት የድርቅ አደጋዎች ከፍተኛው የሆነና የ10ነጥብ2 ሚሊዮን ዜጎቻችን የእለት እርዳታ ፈላጊዎች እንዲሆኑ የዳረጋቸው ቢሆንም በዋነኛነት  ባለፉት 25 አመታት የድል ጉዟችን በፈጠርነው አገራዊ የልማት አቅም ድርቁ ወደ ረሃብነት ሳይቀየር የዜጎቻችን ህይወት መታደግ መቻሉ የወርቃማ ድሎቻችን አንዱ ማሳያ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ በአጠቃላይ አሁንም ድህነት፣ ስራ አጥነት፣ ድርቅ፣ የመኖሪያ ቤት እና የመሳሰሉትን ችግሮችን የመፍታት ስራ ደርጅታችን አጽንኦት ሰጥቶ በመንቀሳቀስ ላይ የሚገኝ ሲሆን በቀጣይም አጠናክሮ የሚቀጥልበት የትኩረት ማእከሉ ይሆናል፡፡  

የተከበራችሁ የአገራችን ህዝቦች

ባለፉት ሃያ አምስት ዓመታት አገራችን ከተጎናፀፈቻቸው ከፍተኛ የትግል ትሩፋቶች መካከል ሌላው ዘላቂና አስተማማኝ ሠላም የሰፈነባት አገር መሆኗ ነው፡፡ ከዘመነ መሳፍንት ጀምሮ በማያባሩ የእርስ በእርስ ግጭቶች ብዙ ዋጋ የከፈለችው አገራችን፣ ባለፉት ሃያ አምስት ዓመታት የአስተማማኝ ሠላም ባለቤት ልትሆን ችላለች፡፡ ውስጣዊ ችግሮቿን በዴሞክራሲ መሳሪያነት ለመፍታት የተንቀሳቀሰችው አገራችን የዜጎችንና የህዝቧን መብት አክብራ ለመጓዝ በመቻሏ የአስተማማኝ ሠላም ባለቤት ለመሆን ችላለች፡፡ ከ20ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ጀምሮ ለሰላሳ ዓመታት ያህል ባልተቋረጠ ጦርነት የተጠበሰችውና “ሁሉም ነገር ወደ ጦር ግንባር” በሚል መፈክር ትታወቅ የነበረችው አገራችን፣ እነሆ ባለፉት ዓመታት መላ ትኩረቷን በዴሞክራሲ፣ ሠላምና ልማት ላይ አድርጋ ወደፊት እየተራመደች ትገኛለች፡፡ “ከድህነትና ኋለቀርነት በላይ ጠላት የለንም” በማለት መላ የአገራችን ህዝቦች የሚያካሄዱት አኩሪ ትግል ውስጣዊ ሰላማችንን ዘላቂና በፅኑ መሠረት ላይ የተገነባ እንዲሆን አድርጓታል፡፡ አገራችን ኢትዮጵያ የራሷን ውስጣዊ ሠላም ለማረጋገጥ የቻለችባቸው እነዚህ ዓመታት ለአፍሪካ ሠላም መጠናከር ልዩ አስተዋፅኦ ያደረገችባቸው ዓመታትም ነበሩ፡፡ ከቡሩንዲ እስከ ሩዋንዳ፣ ከላይቤሪያ እስከ ሶማሊያ፣ ከዳርፉር እስከ ደቡብ ሱዳን በዘለቀ ውጤታማ የሠላም ማስከበር ተሳትፎ ከራሷ አልፋ የአፍሪካውያንን ሠላም ያስከበረች አገር መሆኗን አስመስክራለች፡፡ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ቀንድ ጎረቤቶቿ ሁሉ የሚተማመኑባት የሠላምና የመልካም ጉርብትና ምንጭም ሆናለች፡፡
       
መላ የአገራችን ህዝቦች ባካሄዱት አኩሪ ትግል ኢትዮጵያ በገጠርና በከተማ የለውጥና የዕድገት አገር መሆን ጀምራለች፡፡ ይህን ተከትሎም በዓለም አቀፍ ደረጃ የነበረው የጦርነትና ረሃብተኛነት ምስሏ በፍጥነት መቀየር ጀምሯል፡፡ በጦርነትና በረሃብ ተምሳሌነት ትገለፅ የነበረችው ኢትዮጵያ አሁን ደግሞ የፈጣን ዕድገት አብነት ሆናለች፡፡ በፈጣን የዕድገት ታሪካቸው በእስያ ነብርነት እንደተሰየሙት የምስራቅ እስያ አገሮች ሁሉ ፈጣን ዕድገታችንን ተከትሎ ኢትዮጵያም በአፍሪካ አንበሳነት መታወቅ ጀምራለች፡፡ በኢትዮጵያ የመጣውን ለውጥ በቅርብ የሚከታተሉ አፍሪካውያን ወንድምና እህቶች ብቻ ሳይሆኑ፣ የኢትዮጵያን ዕድገት በጥርጣሬ ይመለከቱ የነበሩ የገበያ አክራሪ ኃይሎች ጭምር የሚቀበሉበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡

የተከበራችሁ የአገራችን ህዝቦች

ባለፉት ሃያ አምስት ዓመታት በአገራችን እውን የሆነው መልካም ነገር ሁሉ በአንድ በኩል ድርጅታችን በህዝብ አጋልጋይነት መንፈስ እየተመራ አገራችንን በፍጥነት ለመለወጥ በቀየሳችው ትክክለኛ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ለመመራት በመቻላችን፣ በሌላ በኩል ደግሞ መላ የአገራችን ህዝቦች ከዳር እስከዳር ለለውጥ ተነሳስተው በቁርጠኝነትና በተደራጀ ንቅናቄ በመንቀሳቀሳቸው የተገኘ ውጤት ነው፡፡ ከድርጅታችን ትክክለኛ አቅጣጫና ከህዝባችን አኩሪ ትግል ውጭ በአገራችን የማሽቆልቆል ምዕራፍ ተዘግቶ አስተማማኝ የዕድገት ምዕራፍ ሊከፈት እንደማይችል ግልጽ ነው፡፡ በየምዕራፉ ያጋጠመንን ፈተናዎችና እንቅፋቶች ሁሉ በህዝባዊ ፅናትና በብስለት እየመከትን ለአኩሪ ውጤት ልንበቃ የቻልነው በእርግጥም ህዝባችንን ይዘን አገራችንን በመልካም ጎዳና ለመምራት ባካሄድነው የተሳካ ትግል ነው፡፡

ባለፉት ሃያ አምስት ዓመታት በሁሉም  መስኮች ለውጥ እያመጣን በተጓዝንበት ሂደት የተጎናፀፍናቸው ድሎች ለጀመርነው ረጅሙ የአገራችን የህዳሴ ጉዞ መሰረት የሚሆን ጅምር ለውጥ እንደሆነ ድርጅታችን በጥብቅ ይገነዘባል፡፡ በተጨማሪም ይህን የለውጥ ሂደት ሊያደናቅፉ የሚችሉ ፈተናዎች ያልተለዩበት የለውጥ ሂደት እንደነበረም ይቀበላል፡፡ ትላንት ከትላንት ወዲያ የነበሩት የሥርዓቱ ፈተናዎች በትግል ከተፈቱ በኋላ በመንገዳችን ላይ አዳዲስ ፈተናዎች እየተጋረጡ እንደሆነና እነዚህንም በተለመደው ፅናትና ህዝባዊ ወገንተኝነት መፈታት እንዳለባቸው ይገነዘባል፡፡ የግንቦት 20 የብር ኢዩቤልዩ በዓልን በምናከብርበት በዚህ ታሪካዊ ወቅት እያጋጠሙን የሚገኙ ችግሮችንና ፈተናዎችን በመፍታት ለቀጣይ ድል ለመዘጋጀት ቃል ኪዳናችን የምናድስበት መሆኑን ድርጅታችን በጽኑ ያምናል፡፡

የተከበራችሁ የአገራችን ህዝቦች

ድርጅታችን ኢህአዴግ  የትግል መስመሩን ባጠራበት የተሃድሶ እንቅስቃሴው በአገራችን ለዘመናት ስር ሰዶ የቆየው የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከትና ተግባር የልማታዊ ዴሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታችን ዋነኛ ፈተና መሆኑን አንጥሮ በማስቀመጥ፣ ባለፉት አመታት በአንድ በኩል የልማታዊ አስተሳሰብና ተግባርን በማጎልበት በሌላ በኩል የኪራይ ሰብሳቢነትን ፖለቲካ ኢኮኖሚ ለማዳከም የሚያስችሉ ትግሎች የተካሄዱ ቢሆንም አሁንም ኪራይ ሰብሳቢነት የስርአታችን ዋነኛ ፈተና እንደሆነ ይገኛል፡፡ ኪራይ ሰብሳቢነት በሚል ስያሜ የሚታወቀው በመንግስትና በህዝብ ሃብትና ፀጋ ህጋዊ አስተዋፅኦ ከሚፈቅደው በላይ ካለአግባብ የመጠቀም አመለካከትና ተግባር አሁንም የልማታዊ ዴሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታችንን እየተፈታተነው ይገኛል፡፡ ይህ ችግር በኢኮኖሚ መስክ ካለአግባብ በመጠቀም ብቻ ሳይወሰን ለመልካም አስተዳደር እጦትና በዴሞክራሲያዊ ሂደቱ ላይ ችግር እያስከተለ እንደሚገኝ በመገንዘብ በ10ኛው ድርጀታዊ ጉባኤያችን ምልአተ ህዝቡን ያሳተፈ ትግል ማካሄድ እንደሚገባን አቅጣጫ መቀመጡ የሚታወስ ነው፡፡ በጉባኤያችን አቅጣጫ መሰረት የተለያዩ ተግባራት በመከናወን ላይ የሚገኙ ቢሆንም አሁንም መሰረታዊ ለውጥ ለማምጣት የቀጣይ ትግል የሚጠይቅ ሆኖ ይገኛል፡፡

ድርጅታችን ኢህአዴግ የኪራይ ሰብሳቢነትን አመለካከትና ተግባር በቁርጠኝነት የመታገል ጉዳይ የተጀመረውን ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ የለውጥ ሂደት ከሚያጋጥመው አደጋ የመጠበቅ የህልውና ጉዳይ መሆኑን ያምናል፡፡ ከኢትዮጵያ ህዝቦች መብት፣ ተጠቃሚነትና ዴሞክራሲያዊ አንድነት በላይ ምንም ፍላጎት ለሌለው ድርጅታችን፣ ህዝብን ያስመረሩ ድክመቶች ይታረሙ ዘንድ ራሱን የማጥራትና የማብቃት ስራ አጠናክሮ የሚቀጥልበት መሆኑን ሊያረጋግጥላችሁ ይወዳል፡፡ ይህ ኢህአዴግና ሥርዓቱን ከማንኛውም ጉድፍ የማፅዳት ጉዳይ ደግሞ ከህዝቡ ተሳትፎና ትግል ውጭ ሊሳካ እንደማይችልም ድርጅታችን  በፅኑ ያምናል፡፡ በመሆኑም የግንቦት ሃያን የብር ኢዩቤልዩ በአል በምናከብርበት በዚህ ታሪካዊ አጋጣሚ ምልአተ ህዝቡ በአገራችን በመካሄድ ላይ ያለውን ፀረ-ኪራይ ሰብሳቢነት ትግል ወደ አንድ ደረጃ ከፍ ለማድረግና ለችግሮቻችን ዘላቂና አስተማማኝ መፍትሄ ለማስገኘት የጀመረውን ተሳትፎና ትግል አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪውን ያቀርባል፡፡

የተከበራችሁ የአገራችን ህዝቦች

አገራችን የማሽቆልቆል ጉዟዋ ተገቶ የከፍታ ጉዞ ላስጀመራት ታላቅ ድል ለመብቃት የቻለችው በርካታ ልጆቿ በከፈሉት ክብር መስዋእትነት በመሆኑ ድሉን አጠናክሮ የማስቀጠል ጉዳይ ከሁሉም ዜጎቿ የሚጠበቅ አደራ ነው፡፡ ዛሬም እንደትላንቱ ሁሉ አገራችንን ወደ ላቀ የዕድገት ደረጃ ላይ የማድረስ ጉዳይም ከፈተናዎች የፀዳ ሆኖ ሊካሄድ የማይችል መሆኑን ድርጅታችን ይገነዘባል፡፡ ህዝባዊ ድሎቻችን የሚጎለብቱትና የሚጠናከሩት በየመድረኩ የሚያጋጥሙንን ፈተናዎች በፅናትና በብስለት በማለፍና ለውጤት በማብቃት መሆኑ ካለፈው የትግልና የድል ጉዟችን በትምህርትነት የሚወሰድ ዋነኛ ቁም ነገር መሆኑ ግንዛቤ ሊወሰድበት ይገባል፡፡

የግንቦት ሃያን የብር ኢዩቤልዩ በአል በምናከብርበት በዚህ ታሪካዊ አጋጣሚ በሥርዓታችን ፊት የተደቀኑ ፈተናዎችን ከህዝባችን ጋር እጅ ለእጅ ተያይዘን እንደምንፈታቸውና አገራችን የ50ኛውን አመት የወርቅ ኢዩቤልዩ የድል በዓሏን ስታከብር ወደ ከፍተኛ ገቢና የበለጸገ ህብረተሰብ ለመሸጋገር አስተማማኝ ደረጃ ላይ እንደምትደርስ በመተማመን ነው፡፡

ይህ የአገራችን ሩቅ አላሚ ራእይ ሊሳካ የሚችለው ሁሉም የአገራችን የህብረተሰብ ክፍሎች እጅ ለእጅ ተያይዘው የድርሻቸውን መወጣት ሲችሉ መሆኑ ካለፈው የትግልና የድል ጉዟችን  የምንገነዘበው መሰረታዊ ጉዳይ ነው፡፡ በመሆኑ የገጠሩም ሆነ የከተማው የአገራችን ምልአተ ህዝብ በተደራጀ ንቅናቄ በልማትና በዴሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታው ሚናውን አጠናክሮ እንዲቀጥል ድርጅታችን በዚህ ታሪካዊ የድል በአል  ጥሪውን ያቀርባል፡፡ ሁሉም የአገራችን ዜጎች በተሰማራችሁበት መስክ ሁሉ በትጋት በመስራትና የሚያጋጥሙ ፈተናዎችን በጽናት በማለፍ አኩሪ ድል ለማስመዝገብ ርብርብ በማድረግ በድህነት ላይ የጀመርነውን ዘመቻ በድል ለማጠናቀቅ የሚጠበቅባችሁን አገራዊ ተልእኮ እንድትወጡ ደርጅታችን ጥሪ ያቀርብላችኋል፡፡ የአገራችን ሴቶችና ወጣቶች አደረጃጀቶቻችሁን በማጠናከር ተሳትፏችሁንና ተጠቃሚነታችሁን በማስፋት የአገራችን የህዳሴ ጉዞ በማፋጠን ተልእኳችሁን አጠናክራችሁ እንድትወጡ ድርጅታችን ጥሪውን ያቀርባል፡፡

ድርጅታችን አንግቦ የተነሳውን ህዝባዊ አላማ ከዳር ለማድረስ መላ የድርጅታችን አባላት ህዝባዊ ወገንተኛነታችሁንና የአላማ ጽናታችሁን በመጠበቅ በሁሉም መስኮች የግንባር ቀደም ሚናችሁን በተለይ ደግሞ እራስን ከኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከትና ተግባር በማጽዳት ሌሎችን በመታገል የግንባር ቀደም ሚናችሁን ከምንጊዜውም በላይ አጠናክራችሁ እንድትቀጥሉ ድርጅታችሁ ጥሪውን ያቀርብላችኋል፡፡

የህዳሴ ጉዟችን በስኬታማነት ይቀጥል ዘንድ የልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መንግስታችን የማስፈጸም አቅም መጠናከር እንደሚገባው ድርጅታችን ይገነዘባል፡፡ ባለፉት 25 አመታት ሲቪል ሰርቪሱ ቀድሞ ከነበረበት የገዥዎች አገልጋይነት ወደ ህዝባዊ አገልግሎት ሰጭነት ለማሸጋገር በርካታ ስራዎች የተሰሩ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ አሁንም ከሚፈለገው ደረጃ ላይ ያልደረሰና በተለይ ህዝባችንን ለቅሬታ የዳረጉ የመልካም አስተዳደር ችግሮች በስፋት የሚታዩበት ነው፡፡ ይህንን ሁኔታ ለመቀየር የመንግስት ተቋማት አመራሮችና ሰራተኞች የተጀመረውን የሪፎርምና የለውጥ ስራ አጠናክሮ በማስቀጠል፣ የህዝብ አገልጋይነት አመለካከትና ብቃት በማጎልበት የሚጠበቅባችሁን ተልእኮ በብቃት እንድትወጡ ድርጅታችን ጥሪውን ያቀርባል፡፡

በአገራችን በተፈጠረው ከፍተኛ የትምህርት እድል በሁሉም ደረጃዎች በርካታ ቁጥር ያላቸው ዜጎቻችን የትምህርት እድል ተጠቃሚ መሆናቸውንና በዚህ ረገድ መምህራን እያበረከቱት ያለውን አስተዋጽኦ ድርጅታችን ይገነዘባል፡፡ መምህራን የህዳሴ ጉዟችንን ከግብ ማድረስ የሚችል ሁለንተናዊ ብቃት ያለው የሰው ኃይል በማፍራት ትውልድን በአግባቡ የመቅረጽ ከባድ ተልእኳችሁን አጠናክራችሁ እንድትወጡ ድርጅታችን ጥሪውን ያቀርባል፡፡

ዴሞክራሲያዊ ህገ መንግስታዊ ስርአታችን ለዜጎቻችን ካጎናጸፈው መሰረታዊ መብቶች ውስጥ ፍትህ የማግኘት መብትና ለዚሁ መብት ተግባራዊነት የዳኝነት ነጻነት የተረጋገጠ መሆኑ ነው፡፡ በዚህ ረገድ ከ25 አመት በፊት ለአብዛኛው የአገራችን ህዝብ እንደ ሰማይ ርቆ ይታይ የነበረው ፍትህ የማግኘት መብትን በማረጋገጥ ዘርፈ ብዙ ስኬቶች የተመዘገቡ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ አሁንም በፍትህ አገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚታዩ የመልካም አስተዳደር ችግሮች ህዝባችን በህገ መንግስቱ የተጎናጸፈውን መብት በተሟላ ሁኔታ እንዳያገኝ እንቅፋት እየፈጠረበት እንደሚገኝ ድርጅታችን ይገነዘባል፡፡ ስለሆነም የፍትህ ተቋማት የተጀመረውን ሪፎርም በማጠናከር የዜጎችን ህጋዊ መብቶች በማስከበር በህገ መንግስቱ የተሰጣችሁን ከባድ ኃላፊነት በብቃት እንድትወጡ ድርጅታችን ጥሪውን ያቀርባል፡፡

ባለፉት የትግልና የድል አመታት የአገራችን የጸጥታ ኃይሎች የውጭ ወረራን በመመከት፣ የሽብር ድርጊቶችን ጨምሮ የጸረ ሰላም ኃይሎች እንቅስቃሴዎችን በማክሸፍና በመከላከል እንዲሁም በሌሎች አገሮች የሰላም ማስከበር ተግባር በመሳተፍ አንጸባራቂ ስኬቶችንና ድሎችን በማስመዝገብ የአገራችን ህዝብ የተረጋጋና ሰላማዊ ህይወት እንዲኖር  ህዝባዊ ተልኳችሁን በብቃት እየተወጣችሁ መሆኑን ድርጅታችን ይገነዘባል፡፡ አሁንም “በጥባጭ ካለ ማን ጥሩ ይጠጣል” እንዲሉ የአገራችን እድገትና ለውጥ በበጎ የማይመለከቱ የውጭና የአገር ውስጥ የጸረ ሰላም ሃይሎች ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ሰላማችን ለማደፍረስ ለመሞከር ወደኋላ እንደማይሉ በመገንዘብ ህዝባዊ ተልእኳችሁን አጠናክራችሁ እንድትወጡ ድርጅታችን ጥሪውን ያቀርባል፡፡

በምንከተለው በነጻ ገበያ መርህ የሚመራ ልማታዊና ዴሞክራሲያው ስርአት ግንባታ የግል ባለሃብቶች ሚና ከፍተኛ ሆኖ ይገኛል፡፡ ከዛሬ 25 አመታት በፊት በአገራችን ከ500ሺ ብር በላይ ኃብት ማፍራት ከማይፈቀድበት የእዝ ኢኮኖሚ በመላቀቅ በአገራችን የተፈጠረውን ምቹ ሁኔታ ተጠቅመው ከፍተኛ ኃብት ያፈሩ በርካታ ባለሃብቶች ተፈጥረዋል፡፡ በአገራችን እየተመዘገበ ላለው እድገትም የበኩላቸውን ድርሻ እየተወጡ ይገኛሉ፡፡ የአገራችን ባለሃብቶች ለዚህ ስኬት የበቁት ግንቦት 20 ባጎናጸፋቸው ድልና እየተገነባ በሚገኘው የልማታዊና ዴሞክራሲያዊ ስርአት አማካኝነት መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ስለሆነም የአገራችን ባለሃብቶች የስርአቱ አደጋ ከሆነው የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከትና ተግባር እራሳችሁን በማጽዳት ባላችሁ ብቃት አማካኝነት በጤናማ የገበያ ውድድር መርህ በመመራትና በመወዳዳር በልማታዊ አቅጣጫ እራሳችሁን እና አገራችሁን በመጥቀም በአገራችን የህዳሴ ጉዞ ተልእኳችሁን አጠናክራችሁ እንድትወጡ ድርጅታችን ጥሪውን ያቀርብላችኋል፡፡

በውጭ አገር የምትኖሩ ኢትዮጵያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊን በአገራችን በሚካሄደው ሁለንተናዊ ለውጥ ተሳትፏችሁን በማጠናከር እራሳችሁን፣ ቤተሰቦቻችሁንና አገራችሁን በመጥቀም የድርሻችሁን እንድትወጡ ድርጅታችን ጥሪውን ያቀርባል፡፡

ባለፉት ሁለት አስርት አመታት ህገ መንግስቱ ያጎናጸፋቸውን መብት ተጠቅመው በርካታ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተደራጅተው  በነጻነት  በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛሉ፡፡ የፖለቲካ አቋም ልዩነቶች እንደተጠበቁ ሆኖ ድርጅታችን ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር በሚያግባቡ መሰረታዊ አገራዊ ጉዳዮች ላይ በትብብር ለመስራት የወሰደውን ግልጽ አቋም አጠናክሮ የሚቀጥልበት ይሆናል፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ም/ቤቶች በማጠናከር ድርጅታችን የበኩሉን ድርሻ አጠናክሮ ለመወጣት የተዘጋጀ መሆኑን በድጋሜ እያረጋገጠ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ህግንና ሰለማዊ የትግል አቅጣጫን በመከተል በአገራችን የህዳሴ ጉዞ የድርሻቸውን እንዲወጡ ጥሪውን ያቀርባል፡፡

በመጨረሻም ባለፉት 25 አመታት የተጎናጸፍናቸውን ወርቃማ ድሎቻችንን ጠብቀን የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከትና ተግባር በመድፈቅ የአጋራችንን ህዳሴ ለማረጋገጥ በድርጅት፣ በመንግስትና በህዝብ አቅሞች የተደራጀ የልማት ሰራዊት ግንባታ ድህነትን ታሪክ ለማድረግ እጅ ለእጅ ተያይዘን የህዳሴ ጉዟችን እናፋጥን፡፡

 “በብዝሃነት ላይ የተመሰረተ ዴሞክራሲያዊ አንድነት ለህዳሴያችን”

ዘላለማዊ ክብር ለትግሉ ሰማዕታት”