Wednesday, 15 April 2015

ሰፊውን የከተማ ህዝብ ያሳተፈና ተጠቃሚ ያደረገ የጥቃቅንና አነስተኛ ልማታችን ( አብይ ርዕስ ህዳሴ ጋዜጣ )


በከተማ ልማትና ኢንዱስትሪ ፖሊሲያችን በግልፅ እንዳስቀመጥነው የከተማ ልማታችን ቁልፍ ማጠንጠኛው ሰፊውን የከተማ ህዝብ ሊያሳትፍና ሊያነቃንቅ የሚችለውን የጥቃቅንና አነስተኛ ልማት ዘርፍ መሆኑ ይታወቃል፡፡ የጥቃቅንና አነስተኛ ልማት ሰፊ የስራ ዕድልን በመፍጠር፣ የከተሞቻችንን ዕድገት በማፋጠን፣ ለግብርናና ገጠር ልማት ቀጣይ ዕድገት የቅርብ ድጋፍ በመስጠት እንዲሁም የአዳዲስ ባለሃብቶችንና ኢንዱስትሪያሊስቶችን መፍጠሪያ መድረክ ሆኖ በማገልገል ወደ ኢንዱስትሪ መር ልማት ለምናደርገው ሽግግር የማይተካ ሚና እየተጫወተ ይገኛል፡፡
ከግብርና ክፍለ ኢኮኖሚ ቀጥሎ ሰፊ የስራ እድል በመፍጠር ዜጎች በኢኮኖሚ ተዋናይ እንዲሆኑ ከማስቻል አንፃር የጥቃቅንና አነስተኛ ዘርፍን የሚተካ ዘርፍ በአለም የለም። በሃገራችን ከተሞችም የአርሶ አደሩን ያህል የኢኮኖሚ መሰረት ሊሆን የሚችለው በብዙ መልኩ ከአርሶ አደሩ ጋር የሚመሳሰል ባህሪ ያለው ጉልበቱንና ንብረቱንም አጣምሮ የሚረባረበው የአነስተኛና ጥቃቅን ተቋም ተዋናይ ነው፡፡ በዚህ ዘርፍ የሚሰማራው የከተማ ህዝብ ዋነኛ ክፍል የሚሸፍን በመሆኑ የልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መስመራችን አስተማማኝ መሰረት ነው ብለን እናምናለን፡፡
ይህንን የፀና አቋምና እምነት በመያዝም የዘርፉ ስትራቴጂ ፀድቆ ተግባራዊ መሆን ከጀመረ ከ2003 ዓም ወዲህ ብቻ ባለፉት አምስት ዓመታት በሃገር ደረጃ በዘርፉ ከ8 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ወደ መስኩ ተቀላቅለዋል ወይም የስራ ዕድል ተፈጥሮላቸዋል፡፡
ዜጎች በቤቶችና መንገድ ኮንስትራክሽን፣ ታላቁ የህዳሴ ግድብን ጨምሮ በሃገሪቱ እየተገነቡ ባሉት ትላልቅ ፕሮጀክቶች እንዲሁም በሌሎች አነስተኛና መለስተኛ ፕሮጀክቶቻችን፣ በከተማ የኮብልስቶንና ሁለንተናዊ የገጠርና የከተማ መንገዶች በመሰማራት የስራ ዕድል ብቻ ሳይሆን የኢንተርፕራይዝ ባለቤትነት አስፋፍተናል፡፡
በኢንዱስትሪው ዘርፍ በርካታ መለስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትራሊስቶች፣ በኮንስትራክሽን ዘርፉ፣ በርካታ የስራ ተቋራጮች  እና አገልግሎት ሰጪዎች አፍርተናል””  እስከአሁን በተገኘው ስኬት ብቻ በመመዘን ኢህአዴግ የተከተለው የልማት አማራጭ ትክክለኛነት በብዙሃን ዘንድ ጠንካራ እምነትና መነቃቀትን ፈጥሯል፡፡ 
በሀገራችን በተዘረጉ የልማትና የመልካም አስተዳደር መርሃ ግብሮች በመታገዝና  በዜጎችዋ ጥረትና ትጋት ሀገራችን ብሎም መዲናችን አዲስ አበባ ፈጣንና ተከታታይነት ያለው እድገት እያስመዘገበች ስለመሆኑ እንኳን የጥረቱና የስኬቱ ባለቤቶች የሆኑ የከተማችን ነዋሪዎች የዓለም ማህበረሰብም የሚመሰክረውና የሚገነዘበው ሃቅ ነው፡፡
የከተማችንን ውስብስብ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች የመለወጥ ሂደት ሰፊ ጥረትና ጊዜ የሚጠይቅ መሆኑን የሚገነዘበው ድርጅታችን ኢህአዴግ ዋናው መፍትሄውም ሁሉም የከተማችን ነዋሪ የሚሳተፍበት ልማት ማቀጣጠል ነው የሚል የፀና አቋም በመያዝ የህዝቡን የልማት ጥያቄ ለመመለስ እየተጋ ያለ ድርጅት ነው፡፡
ድርጅታችን ኢህአዴግ አዲሱን ሚሊኒየም በከፍተኛ የህዳሴ መነሳሳት በተቀበልንበት ወቅት የአዲስ አበባ ትንሳኤ እውን ይሆናል ብሎ ቃል በገባው መሰረት እንሆ በሁሉም መስክ በለውጥ ሃዲድ የምትምዘገዘግ ከተማ ማየት ችለናል፡፡ የከተማችን የስራ አጥነትንና ኑሮ ውድነትን ችግር የምንፈታበት ቁልፍ ከጥቃቅንና አነስተኛ ልማት ስትራቴጂያችንና ፓኬጅ የመነጨ ከተማ አቀፍ የስራ እድል እቅድ መሆኑን በማስመር ሰፊ እቅድና የድጋፍ ማዕቀፍ ነድፈን ስንረባረብ ቆይተናል፡፡ ይህ ዘርፍ ትክክለኛ አማራጭ ስለመሆኑም ዛሬ ከንድፍ ሃሳብ ትንታኔ ወጥቶ በተግባር ማረጋገጥ ተችሏል”” በሂደቱም ተስፋ ሰጪ ውጤቶች እየተመዘገቡ ይገኛሉ፡፡

የስራ እድል ፈጠራ ከማስፋት አንፃር በዘርፉ የተገኙ ስኬቶች፤
በተከሰተው የኢኮኖሚ ቀውስ ምክንያት ኑሮ ውድነት በተለይም ያለፉት አስር ዓመታት የአለማችን መንግስታት ራስ ምታት ሆኗል፡፡ ይህ በተለይም እንደኛ ባሉ በድህነት ላይ ላሉ ህዝቦች በእንቅርት ላይ ጀሮ ደግፍ ነው፡፡ የኑሮ ውድነትን ለመቋቋም አንዱና ዋናው መንገድ የሕብረተሰቡን ገቢ ማሣደግ መሆኑን የሚያምነው ድርጅታችን ኢህአዴግ በስትራቴጂክ ዘመኑ የሥራ ዕድል በስፋት የመፍጠር ጉዳይ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት ከብዙ ሃገራት በተቃራኒ በርካታ አዳዲስ የስራ እድሎች እንዲፈጠሩ አድርጓል፡፡
አለም አቀፍና ሃገራዊ ባህሪ ያለውን የኑሮ ውድነት የማቃለል ጉዳይ እንደሀገር በቀጣይም ከፍተኛ ርብርብ የሚጠይቀን መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ በአሳለፍነው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን የኑሮ ውድነቱን መቋቋም የቻሉ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች መፍጠር ችለናል፡፡
ባለፉት አራት አመት ተኩል ጊዜ ብቻ በከተማችን በማኑፋክቸሪንግ፣ በኮንስትራክሽን፣ በአገልግሎት፣ በከተማ ግብርና ዘርፍ እና በንግድ ዘርፍ በድምሩ ለ730 ሺህ በላይ ዜጎች የስራ እድል ለመፍጠር ተችሏል፡፡ ድርጅታችን ኢህአዴግ ለዘርፉ በሰጠው ቁልፍ የልማት ትኩረት መሰረት ይህንን የሚመራና የሚያስተባብር የመንግስት መዋቅሩ ላይ ሰፊ የማስፈፀም አቅም ግንባታ በማካሄድ ዜጎቹ ከእለት ጉርስ አልፈው በዘላቂነት በዘርፉ በመቆየት ወደ ተሻለ እድገት የሚሸጋገሩበት ሁኔታ ለመፍጠር ሰፊ ስራ ተሰርቷል፡፡
በዚህ ጥረትም ከጊዜ ወደ ጊዜ ቋሚ የስራ ዕድል የሚያገኙ ዜጎች ቁጥር ጨምሯል”” ከዚህ አንፃር በእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዘመኑ አመታት የተፈጠሩት የስራ እድሎች በቋሚና በጊዜያዊ ሲታይ 555 ሺህ 369 በቋሚ እና 175 ሺህ 533 በጊዜያዊ የተፈጠሩ የስራ እድሎች ሲሆኑ  በቋሚነት  የሚፈጠሩ የስራ እድሎች እየጨመሩ መምጣታቸውን እንገነዘባለን፡፡ ይህ ደግሞ የከተማችን ነዋሪዎች የስራ አጥነት ችግር በቋሚነት እየተቀረፈ እንዲመጣ ከማስቻሉም በተጨማሪ  የእነዚህ ዜጎች በከተማችን ህዳሴ የሚያኖሯቸው ሚናም ከፍ እንዲል አስችሎታል፡፡
የከተማ ልማት ስትራቴጂያችን በቅድሚያ በጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት ልማት ላይ እንዲያተኩር የተደረገው ግን የኑሮ ውድነትን ለመቋቋም ብቻ በማለም በአጭር ጊዜ እይታ ታጥረን አይደለም”” ይልቁንስ መካከለኛ ገቢ ያለው ህብረተሰብ የመፍጠር ሃገራዊ ራዕያችንን  የማሳካት ፋይዳ ያለው መሆኑ እስከአሁን በዘርፉ በመሰማራት ወደ ሃብት ጉዞ የጀመሩ የከተማችን ወጣቶች፣ ሴቶችንና ሌሎች ነዋሪዎች ምስክሮች ናቸው””
የጥቃቅንና አነስተኛ ልማት ሰፊ የስራ ዕድልን በመፍጠርና ገቢ በማስገኘት ጊዜያዊ ችግራቸውን ከመፍታት ባለፈ ከተሞችን በመገንባት ረገድም ወሳኝ ሚና እየተጫወቱ ይገኛሉ፡፡
ዛሬ በከተማችን እየተገነቡ ያሉ በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ የጋራ መኖሪያ ቤቶች፣ የመንገድ ፕሮጀክቶችና ሌሎች ግንባታዎች የእነዚህ  አዲስ ትውልድ ኮንትራክተሮችንና ባለሙያዎች አሻራ እያረፈባቸው ያሉ ናቸው፡፡ በከተማ ፅዳትና ውበት በመደራጀት ከተማችንን አዲስ አበባን ፅዱና ውብ እንድትሆን ወሳኝ ሚና እየተጫወቱ ያሉትም በዚህ ዘርፍ ተደራጅተው እየተጉ ያሉ ዜጎች መሆናቸውን ስንመለከት የተከተልነው የልማት አማራጭ በአንድ ድንጋይ ሁለትም ሶስትም ወፍ መምታት እንደሚያስችለን አረጋግጦልናል፡፡

የኢንዱስትሪ ኤክስቴንሽን ድጋፍ
ድርጅታችን ኢህአዴግ የሀገራችንና የከተማችን ልማት ዘላቂ ዋስትና የሚኖረው ቀጣይነቱን በማረጋገጥ ብቻ ሳይወሰን የሃብት ክፍፍል ፍትሃዊነት በማረጋገጥ ብቻ ነው የሚል የፀና አቋም አለው”” ፍትሃዊን የሃብት ክፍፍሉ ተግባራዊ መሆን የሚችለው ደግሞ በኒዮሊበራል መንገድ ጥቂቶች ባለፀጎች በሚቆጣጠሩት ኢኮኖሚ ወይም በሶሻል ዴሞክራሲ መንገድ በዳረጎት አይደለም”” ህዝባችን እድሉ ከተሰጠው ራሱን በጥረቱ መለወጥ የሚችልና የድርጎኛ አስተሳሰብን የሚፀየፍ በላቡና ጥረቱ መኖርን የሚመርጥ ህዝብ መሆኑ ይታወቃል፡፡ በአለፉ አመታትም ይህንን አረጋግጧል፡፡
የህዝባችንን ከድህነት ለመውጣትና በጥረቱ ለመለወጥ ያለውን ዝግጁነት በሚገባ የሚገነዘበው ድርጅታችን ኢህአዴግም በከተማ ልማት ማእቀፍ ውስጥ በቀረፀው የጥቃቅንና አነስተኛ ልማት ስትራቴጂ የድሃውን የከተማችን ነዋሪ ጥረት የሚደግፉ የቴክኒክና ስራ አመራር ስልጠና፣ የመስሪያ ቦታ፣ የፋይናንስ፣ የገበያ ትስስርና ቀጣይነት ያለው የኢንዱስትሪ ኤክስቴንሽን ድጋፍ በመቅረፅ ተግባራዊም አድርጓል፡፡
 በጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርኘራይዞች ዘርፍ ተደራጅተው አብዛኛዎቹ ወደ መስኩ ለመግባት ፍላጎቱ ያላቸው ዜጎች የሚያጋጥማቸው ፈተና የዘመናዊ የቴክኒክና የሥራ አመራር ክህሎት ትጥቅ መሆኑ ግልፅ ነው፡፡ ከዚህ አኳያ በአንቀሳቃሾች ላይ የሚታዩ የክህሎት ችግሮችን ለመቅረፍ በቴክኒክና ሙያ ተቋማት የተለያዩ ስልጠና  መስጠት አስፈላጊ መሆኑ ስለታመነበት በከተማችን  የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆችና የማሰልጠኛ ተቋማት እንዲቋቋሙና ገበያ ተኮር ስልጠና እንዲሰጡ ጥረት ተደርጓል፡፡ በዚህ መሰረትም ባለፉት አመታት ለ159 ሺህ ወጣቶችና ሴቶች የቴክኒክ ስልጠና ሙያ ክህሎት  መስጠት ተችሏል፡፡ ይህም ከስራቸዉ ጋር ተያይዞ የሚያጋጥሟቸውን ችግሮችን በተለይም የስራ አመራር ክህሎት እጥረትን እና የኢንተርፕራይዞችን  የውስጥ ችግሮችን በራሳቸዉ የሚፈቱበትን አቅም ፈጥሮላቸዋል””
የኮብልስቶን ፕሮጀክት ስልጠናን በተመለከተ በ7 ሺህ 599 ኢንተርፕራይዞች ለታቀፉ 134 ሺህ 895 አንቀሳቃሾች ስልጠና መስጠት የተቻለ ሲሆን ምንም የቴክኒክ እዉቀት ለሌላቸው እና ምንም የመነሻ ገንዘብ የሌላቸዉ የመነሻ ካፒታል የሚያገኙበት እድል በመፍጠር  በቀጣይ ወደ ሌሎች እድገት ተኮር ዘርፎች እንዲሸጋገሩ የማድረግ ስራም ተሰርቷል፡፡


ዘርፉ በፋይናንስ እጦት እንዳይታነቅ የተቀረፀ ስልት
የጥቃቅንና አነስተኛ አንቀሣቃሾች ክህሎትና ጉልበታቸዉን ተጠቅመዉ ሀብት መፍጠር እንዲችሉና ስራቸውን እንዲያሰፉ የሚያጋጥማቸው ሌላ ማነቆ ፋይናንስ ነው፡፡ በመሆኑም ድርጅታችን ኢህአዴግ በዘርፉ ስትራቴጂ ባስቀመጠው መሰረት የፋይናንስ አቅም ችግራቸዉን ከመቅረፍ አኳያ የፋይናንስ አቅርቦት ማመቻቸት ተቀዳሚ ተግባር ተደርጎ ተወስዷል”” በመሆኑም በዘርፉ ስትራቴጂ መሠረት ኢንተርፕራይዞቹ የካፒታላቸውን 20% እንዲቆጥቡ ምክርና ድጋፍ በመስጠት 2 ቢሊዮን 740 ሚሊዮን በላይ በመቆጠብ የተሻለ የኢንቨስትመንት አቅም  እንዲኖራቸው ተደርጓል፡፡
በመስኩ የተሰማሩ ወገኖቻችን የካፒታል እጥረት ለመፍታት ሌላ የተከተልነው የመፍትሄ አቅጣጫ በቂ የብድር አገልግሎት የሚያገኙበትን መንገድ ማመቻቸት ነበር፡፡ በዚህም በከተማችን 166 ሺህ 968 አንቀሳቃሾች ከ3 ቢሊዮን 800 ሚሊዮን ብር በላይ የብድር አገልግሎት በማግኘት ስራቸውን ለማስፋፋት ችለዋል፡፡
እንዲህ ዓይነት የፋይናንስ ስርዓትና ድጋፍ በመዘርጋቱም  በስትራቴጂክ ዘመኑ በመጀመሪያ ዓመት ዝቅተኛ የነበረዉ የአንቀሳቃሾች ምርታማነትና ተወዳዳሪነት በእቅድ ዘመኑ መጨረሻ ጥሩ ደረጃ እንዲደርስ ያደረገ ሲሆን ይህም ከአነስተኛ ወደ መካከለኛ ኢንዱስትሪ የሚደረገዉን ሽግግር እንዲፋጠን አድርጓል፡፡ ኢንተርፕራይዞቹ  ከአገር ዉስጥ ገበያ ባሻገር የዉጪ ገበያዎችን ጭምር  እንዲጠቀሙም አስችሏቸዋል፡፡

የማምረቻና መሸጫ ማእከላት አቅርቦት፤
በከተማችን በእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዘመኑ በጥቃቅንና አነስተኛ ልማት ዘርፍ ለተሰማሩ ዜጎች የተደረገው ድጋፍ የመስሪያና መሸጫ ቦታ ማመቻቸት ነበር፡፡ በተያዘው እቅድ መሰረትም በቢሊዮን የሚቆጠር በጀት በመመደብ የማምረቻ፣ የማሳያና የመሸጫ ህንጻዎችና ሼዶችን በመገንባት በተለያየ ሙያ ዘርፍ ለተደራጁ ስራ አጥ ዜጎች በማስተላለፍ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ተደርገዋል፡፡ በዚህም አማካኝነት በከተማችን የሚታየዉን ስራአጥነት ከመቀነስና የህዝብ ሀብትን ለተጠቃሚዎች ፍትሀዊ በሆነ መልኩ ከማዳረስ አኳያ ዛሬ  በርካታ የከተማችን ወጣትና ሴቶች  ህይወት እንዲለወጥ ተደርጓል፡፡
መሬት የህዝብና የመንግስት በመሆኑ ምክንያት መንግስት ለእነዚህ የሚሆን መሬት ያለብዙ ውጣ ወረድ ማዘጋጀት በመቻላችን ለማምረቻና መሸጫ ማእከላት ግንባታ የሚውል 1 ሚሊዮን 106 ሺህ 894 ካ.ሜ መሬት ለእነዚህ ወገኖቻችን እንዲውል ተደርጓል፡፡ በተዘጋጀው መሬትም  87 የማምረቻና መሸጫ ሕንፃዎች እና ከአንድ ሺህ በላይ ሼዶች በመገንባት በ16 ሺህ 142 ኢንተርፕራይዞች ለታቀፉ ከ72 ሺህ በላይ ለሚሆኑ አንቀሳቃሾች ማስተላለፍ ተችሏል፡፡

የገበያ ትስስር፤
የከተማው አስተዳድር በኢህአዴግ መሪነት በዘርፉ የተሰማሩትን ከድህነት ለመውጣት ለሚያደርጉት ጥረት የሰጠው ሌላው ድጋፍ የገበያ ትስስር ነው፡፡
ከዚህም አኳያ ባሳለፍነው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዘመን በከተማችን ለሚገኙ ኢንተርፕራይዞች በመንግስት ልማት ፕሮጀክቶች፣ በተቀናጀ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ ከግብአትና አገልግሎት አቅራቢነት እስከ ስራ ተቋራጭነት፣ እንዲሁም ከመካከለኛና ከፍተኛ ኢንዱስትሪዎች ጋር በማስተሳሰር እና ከፌደራል እስከ ወረዳ በሚዘጋጁ የተለያዩ ባዛሮች እንዲሳተፉ በማመቻቸት በአጠቃላይ ከ10 ቢሊየን ብር በላይ የገበያ ትስስር እንዲፈጠርላቸው ተደርጓል፡፡
በመጀመሪያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዘመን የኢንዱስትሪ ኤክስቴንሽን አገልግሎት አሰጣጥን አስመልክቶ በዘርፉ ልማት ስትራቴጂ መሰረት በቅድሚያ የኢንተርፕራይዞችን ችግሮች በጥናት በመለየት፣ ችግር ፈቺና በፍላጎት ላይ የተመሠረተ የኢንዱስትሪ ኤክስቴንሽን አገልግሎት መስጠት አስፈላጊ በመሆኑ ለአንቀሳቃሾች የክህሎትና የስራ አመራር ስልጠና በመስጠት፤ በማጠናቀቂያ የብቃት ምዘና በማረጋገጥ፣ ቀጣይነት ያለው የካይዘን ሥርዓት እንዲከተሉ ማድረግ የተቻለ ሲሆን ኢንተርፕራይዞቹ  በዋጋ፤ በምርት ጥራት እና በአቅርቦት ተወዳዳሪ እንዲሆኑ የማስቻል ስራ  ተከናውኗል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ ለ581 ኢንተርፕራይዞች የቴክኖሎጂ ሽግግር የተደረገላቸዉ ሲሆን እስካሁን 470 ቴክኖሎጂዎችን ማሸጋገር ተችሏል፡፡
የኢንዱስትሪ ኤክስቴንሽ አገልግሎት በማመቻቸት ለ12 ሺህ 750 አንቀሳቃሾች የንግድ ስራ አመራር ክህሎት አገልግሎት በመስጠት በኢንተርፕራይዞች የሚታየዉን የሂሳብ መዝገብ አያያዝን ክፍተት፣ የምርት ጥራት መጓደልን እና የመሳሰሉትን ችግሮች ከመፍታት አኳያ ከፍተኛ ሚና ተጫዉቷል፡፡ በቀጣይም የስራ አመራር ክህሎትና የኢንተርፕረነርሽፕ ስልጠና ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡

የአማራጭ አልባዎቹ የቁራ ጩኸት
ከቅዠት መዝሙር ባለፈ የሚጨበጥ አማራጭ የማያቀርቡ ሊበራሊዝምና ሶሻል ዴሞክራሲ ኢኮኖሚ አማራጫችን ነው የሚሉ ተቃዋሚዎች ድርጅታችን ኢህአዴግ ከድሆች በመወገኑና ለእነዚህ ለዘመናት እድል ተነፍጓቸው የነበሩ ሴቶችንና ወጣቶችን በመወገን ላሳየው ወገንተኝነት አምርረው ሲያወግዙና በኋላ ቀርነት ሲያብጠለጥሉት ቆይቷል፡፡ ከዚህም አልፈው የመስመራችንን ልማታዊነት በመገንዘብ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ የከተማችን ሴቶችና ወጣቶች በመስኩ መሰማራታቸው አንዴ የኢህአዴግ አባላት ናቸው አንዴ ድንጋይ ቀጥቃጭ ባለ ድግሪ የሚሉ ቅፅሎችን በመለጠፍ ለማሸማቀቅና እንደ ትናንቱ ስራን እየተጠየፈ በድህነት መንገድ  እንዲቀጥል አደናቃፊ ተግባራት ፈፅመዋል፡፡ ዛሬም ከዚህ ተግባራቸው አልተቆጠቡም፡፡
የራሳቸውን አማራጭ ማቅረብ የማይችሉና በደፈናው የኢህአዴግን አማራጭ መተቸት እንደአማራጭ የሚመለከቱ ተቃዋሚዎቻችን የአለም ኢኮኖሚ እውነታን በመካድ ጭምር የጥቃቅንና አነስተኛ ልማት የአማራጭ ማጣት ፖሊሲ አድርገው ሲያቀርቡት እንሰማለን፡፡ ይሁን እንጂ ጥቃቅንና አነስተኛ ልማት እንደነ አሜሪካ፣ ጃፓንና ህንድን ጀርመንና ቻይና የመሳሰሉ የበለፀጉና በማደግ ላይ ባሉት ሃገራት ከድህነት አንስቶ በእድገት ጐዳና እንዲራመዱ ያስቻለ ባለውለታ ነው፡፡ በኢንዱስትሪና ማኑፋክቸሪንግ ልማት የላቀ ደረጃ ላይ የደረሰችውና እንደነ ቶዮታና ሶኒ ያሉ አለም አቀፍ ግዙፍ ኩባንያዎችን ያፈለቀችው ጃፓን ከ50% በላይ የሚሆነው የማኑፋክቸሪንግ ምርቷ የሚገኘው ከጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት ነው፡፡ በዚችው ሃገር ይኸው ዘርፍ ከ4ዐ ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ ዕድል ፈጥሯል፡፡  ጃፓን እንዴት ሰለጠነች ቢባልም ሚስጥሩ በጥቃቅንና አነስተኛ ልማት መሆኑ ግልፅ ነው፡፡
የከተማችን ልማት ሞተር በጥቃቅንና አነስተኛ ዘርፍ የሚሰማሩ በብዙ መቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ የከተማችን ነዋሪዎች መሆናቸውን ከልብ የሚያምነው ድርጅታችን ግን በተከተለው ትክክለኛ የልማት አማራጭ፤ ዜጎቻችን እያሳዩት ባለው ስኬት ለድህነት ጥብቅና የቆሙ ሃይሎች በዘንድሮም ምርጫ መራጩ ህዝብ በካርዱ የማይገረሰስ መልእክቱን ደግሞ እንደሚያስተላልፍላቸው እንተማመናለን፡፡

የስኬት መንገዳችንን አጠናክረን እንቀጥላለን
ድርጅታችን ኢህአዴግ ነገን ቀና ብለን ለመሄድ ዛሬ ወገብ በሚያጎብጡ ተግባራት እንረባረብ ባለው መሰረት በዘርፉ የተሰማሩና በቀጣይም ለሚሰማሩ ወገኖቻችን ይበልጥ ውጤታማ እንዲሆኑ ለማስቻል አዳዲስ ስልቶችንና ፓኬጆችን በመቀመር በበቀጣይ አምስት ዓመታት ስራ ላይ እንዲውሉ ያደርጋል፡፡ በዚህ መሰረት በቅርብ አመታት የተቋቋመው አዲስ ካፒታል እቃ ፋይናንስ ንግድ ስራ አክስዮን ማህበር የተባለ የማሽነሪ ሊዝ ኩባንያ እንዲጠናከር ይደረጋል፡፡     
በዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅዳችን ላስቀመጥነዉ መዋቅራዊ ሽግግር እውን መሆን ጉልህ ፋይዳ ባለው የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ የተሰማሩና ወደፊትም በዚህ ዘርፍ የሚሰማሩ የጥቃቅንና አነስተኛ አንቀሳቃሾችን ማነቆዎች በመፍታት ለኢንዱስትሪው ሰፊ መሰረት እንዲሆኑ ለማስቻል የማምረቻ ማዕከላት የእሴት ሰንሰለትን መሰረት ባደረገ አኳሃን በክላስተር እንዲደራጁ በማድረግ የክላስተር ማዕከላቱ ያሉባቸውን ችግሮች በመፍታት ለማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ ለተለዩ ክላስተሮች የእሴት ሰንሰለት ጥናት በማካሄድ የቴክኖሎጂና የማሽነሪ ፍላጎት የማሟላቱ ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡
ዘርፉ የስራ እድል በመፍጠር፣ ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል የሚያሰፍንና መልካም አስተዳደርን የሚያረጋግጥ እንዲሁም የልማታዊ ባለሃብቶች መፈልፈያና ለኢንዱስትሪ ልማት መሰረት የሚጣልበት እንደመሆኑ መጠን በማምረቻ ኢንዱስትሪ በተለይም በውጭ ምርት ማምረትና ገቢ ምርትን በመተካት ላይ ለተሰማሩና ለሚሰማሩ ኢንተርፕራይዞች የተመረጠ የተቀናጀና ሁሉን አቀፍ ድጋፍ በልዩ ትኩረት በመስጠት ተወዳዳሪነታቸውን ማረጋገጥ ልዩ ትኩረት የሚሰጠው ይሆናል፡፡
በቅድሚያ የዳሰሳ ጥናት በማድረግ የኢንተርፕራይዞችን ፍላጎትና ችግሮች በመለየት ችግር ፈቺና በፍላጎት ላይ የተመሠረተ የኢንዱስትሪ ኤክስቴንሽን /የቴክኒካል ክህሎትና የስራ አመራር ስልጠና፤ የቴክኖሎጂ ሽግግር፣ ቀጣይነት ያለው የካይዘን ሥርዓት/ ተግባራዊ በማድረግ ኢንተርፕራይዞች በምርትና አገልግሎት ጥራት፣ በዋጋና አቅርቦት ተወዳዳሪ በመሆን በቀጣይነት እያደጉ  ለኢንዱስትሪዉ መሰረት እንዲሆኑ ይደረጋል፡፡
ልዩ ትኩረት የሚሹ የህብረተሰብ ክፍሎችን በተለይም ሴቶች፣ ወጣቶች፣ አካል ጉዳተኞችና HIV/AIDS በደማቸዉ የሚገኝ ዜጎቻችንን በዘርፉ ልማት በልዩ ሁኔታ በማሳተፍ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቀሚነታቸውን ማሳደግና የልማቱ አቅም እንዲሆኑ ማድረግ ትኩረት የሚሰጠው ይሆናል፡፡



ኢህአዴግን መምረጥ የተጀመሩ የልማት ስራዎችን ማስቀጠል ነው!