Thursday, 2 April 2015

ኢትዮጵያ ወይ አበዳሪ ወይ ተበዳሪ ይሞታል ብላ የምታምን ሃገር አይደለችም ከማህደር ብርሃነ




የዛሬ ብዕሬን ላነሳ የገፋፋኝ ከሃገሬው ባለድግሪ በታች እውቀት ‹‹የሰጣቸው›› ባለድግሪ የሃገሬ ተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች የሰሞኑ ንግግር ነው፡፡ በዚህ ለከት በሌላቸው አንደበታቸው ተናድጄ በበኩሌ እንዲህ ከሆነ ትምህርት በአፍንጫዬ ይውጣ አልልም”” ትምህርትማ የዕድገት መሰለል ነው፡፡ በእውነተኞቹ የሃገሬ ልጆችም ህዳሴ ግድብ ሲገነባ፣ ባቡር ሲገነባ፣ የአርሶ አደሩ ምርት ሲያሳድግ፣ በዲፕሎማሲ መድረክ የአህጉራችን ወኪሎች ስንሆን … ወዘተ አሳይቶኛልና፡፡
የተቃዋሚ ፓርቲዎች ትልቁ መገለጫ ማንነት ‹‹ትምክህት›› ነው፡፡ በድንቁርና የተገነባ ‹‹ትምክህት›› የስነልቦና ጠቢባን ምን ብለው እንደሚገልፁት ባላውቅም የተቃዋሚ ፓርቲዎች ትምክህት የሚመነጨው ግን እየኖርንባት ያለችው ሃገርና ህዝብን በትክክል ካለማወቅ ይመነጫል፡፡ በእነሱ ቤት ስለሃገር የሚያውቁ እነሱ ናቸው፡፡ ህዝቡ ዓይንም ጆሮም የለውም፡፡ ስለሆነም በኢትዮጵያ የመድብለ ፓርቲ ስርዓት የለም ካሉት ይቀበላቸዋል፡፡ በኢትዮጵያ ሰላም የለም ሃገሪቷ ከጫፍ ጫፍ ታምሳለች ፍርክስክሷ እየወጣች ነው ካሉትም ዓይኑን ሳያሻሽ ያምናቸዋል፡፡ በሃገሪቱ ልማት የለም፣ መሰረተ ልማት አልተሰራም፣ በአባይ ግድብ አንዲት ጠጠርም አልተቀመጠም በቴሌቪዥን የሚታየው ሃሰት የቴሌቪዥን ቅንብር ነው ካሉትም ‹‹ትክክል ናችሁ›› ብሎ ያምናል፡፡ በዓለም የሚበደር ብቸኛ መንግስት የኢትዮጵየያ መንግስት ነው ብለው ቢነግሩትም ሳያንገራግር ይቀበላቸዋል፡፡ . . . ተቃዋሚዎቻችን እንዲህ ብለው ስለሚያምኑ ዓይናቸውን በጨው በማጠብ በቴሌቪዠን መስኮት ብቅ ብለው ህዝቡን ዓይንህን ሳይሆን እኛን እመን ሲሉ እያስተዋልን ነው፡፡ ይህ ድንቁርና የፈጠረው ትምክህት ካልሆነ ምን ሊባል ይችላል፡፡
በእነሱ ቤት እነሱ እንጂ የኢትዮጵያ ህዝብ በሃገሩ እየተካሄደ ስላለው ሁሉ የመመዘን መዝኖም የመረዳት እውቀት የለውም፡፡ ስለ ዓለም እውነታም ምንም የሚያውቀው ነገር የሌለ መሃይም ነው፡፡ እንዲህ ያለ የነተበ የህዝብ ንቀት ጫንቃቸው የተሸከሙት ነባሮችና አፍለኞች የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች በዘንድሮ የምርጫ ቅስቀሳ እነሱ ብቻ የሚያቁት ህዝብ የማያውቀው ሚስጢርና እውነት ይዘው ብቅ ብለዋል፡፡ ህዝብን መናቅ ጫፍ ሲረግጥ እንዲህ ነው፡፡ ‹‹ልማት የለም›› ብለው መናገር በአደባባይ መሳለቂያ ያደርጋችኋል ብለው መካሪዎቻቸው ስለመከርዋቸው በእነሱ ቤት የመራጩ ህዝብ ጀሮ እናገኝበታለን ያሉት ዓለማዊ እውነት  በኢትዮጵያ መንግስት ብቻ የታየ ክስተት አድርገው ያቀርባሉ”” ይኸውም የአትዮጵያ መንግስት በሃገሪቱ እያካሄደው ያለው ልማት ከመንግስታትም ከዓለም አቀፍ ገንዘብ ቋማት ተበድሮ ነው የሚል ውሃ የማይቋጥር ንግግር ነው፡፡ አንድ ጥያቄ ማንሳት ግን ይቻላል ‹‹እስቲ የአለማችን የኢኮኖሚ ቁንጮ ከሆነችው ታላቋ አሜሪካ እስከ ሩቅ ምስራቅ ለልማት የማይበደር መንግስት ካለ ጥቀሱልን ?›› ሌላ ቢቀር በ2010 በተከሰተው የኢኮኖሚ ቀውስ ወቅት የአሜሪካ ተቋማት ከቻይናም ከአረብ ሃገራትም እስከ ትሪሊዮን መበደራቸውን በተመለከተ የተለቀቀውን ዜና አልሰማንም አይሉም፡፡
ስለሆነም መበደር በራሱ የሚወገዝ ነው የሚባል መግባባት የለም፡፡ በዓለምም የማይበደር ሃገር የለም፡፡ ሊያነጋግር የሚችለው ለምን እና እንዴት ይበደራል የሚለው ነው፡፡ ኢትዮጵያ በደርግ ዘመንም ትበደር ነበር፡፡ በኢህአዴግ ዘመን ትበደር ነበር ስለዚህ ልዩነት የለውም የሚል ውሃ የማይቋጥር መከራከሪያ ማቅረብ ከድንቁርና የመነጨ ‹‹ትምክህት›› ካልሆነ ምን ሊባል ይችላል”” ምክንያቱም አያውቅም ብለው የሚንቁት የኢትዮጵያ  ህዝብ ሃገሪቷ በደርግ ጊዜ ለምን ትበደር እንደነበረች በአሁን ዘመን ለምን እንደምትበደር ምክንያቱና እውነቱን በደንብ ለይቶ ያውቃልና፡፡
ሌላው ብድሩ በምን ሁኔታ ነው የሚገኘው ብሎ ማየት ያስፈልጋል፡፡ ሃገራት ብድርን የሚያገኙበት መንገድ በልማታዊም ኢልማታዊ በሆነ መንገድ ሊሆን ይችላል፡፡ ብዙ ጊዜ እንደሚባለው ፖሊሲያቸውን በመሸጥ ብድር የሚያገኙ መንግስታት አሉ፡፡ ይህም ብድሩን የሚያገኙት አበዳሪዎች የሚያቀርቡት የኢኮኖሚ ፖሊሲ በመቀበል ይሆናል፡፡ ይህ ምን ማለት ነው ከተባለ ለምሳሌ ባንክን ለውጭ ባለሃብቶች ክፍት አድርጉት ይህንን ያህል ብድርና እርዳታ እንሰጣችኋላን በሚል የሚቀርበውን ድርድር ተቀብሎ ብድሩን ማግኘት ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ አካሄድ የኪራይ ሰብሳቢዎችና ሌተቀን የምናወግዘው የኒዮሊበራሊዝም መንገድ በመሆኑ በመጨረሻ የሀገር ውድቀትን ያስከትላል፡፡የኢትዮጵያ መንግስት የብድር መንገድ ከዚህ ውጪና ፍፁም የፀዳ ስለመሆኑ ማንም የሚያውቀው ሐቅ ነው፡፡ ተቃዋሚዎች ይህንን የኢህአዴግ መንግስት ለምዕራባውያን ፖሊሲ አልገዛም ባይነቱን ‹‹ድርቅና›› እንደሃጥያት በመቁጠር ሲያወግዙት በዚህ አቋሙም ከምዕራባውያን የመሞዳሞጃ መንገድ ቆጥረው በደጃፋቸው ሽር ብትን ይላሉ፡፡
ስለሆነም የኢትዮጵያ መንግስት የብድር አቅጣጫም ከአጠቃላይ ልማታዊ ባህሪው የሚመነጭ የሃገሪቱን ሉዓላዊነትና የኢኮኖሚ ነፃነት የሚያስጠብቅ ነው፡፡ ይቺ ሃገር እኮ ከሁለት ዓስርት ዓመታት በፊት በየዓመቱ እስከ 14 ሚሊዮን ዜጎቿ ከለጋሾች ስንዴ የሚሰፈርባት እያለችም ጭምር ከበጀቷ እስከ 50  የሚሸፈነው ከውጭ ብር ነበር፡፡ ይህ ብድር ደግሞ ይውል የነበረው ለጦርነት ነበር፡፡ ዛሬም ከአበዳሪ ሃገራትና ተቋማት ትበደራለች፡፡ ይህንን እየተበደረች ያለች ሃገራችን ብድሩ ሙሉ በሙሉ ለታወቀ ፕሮጀክት ነው የምትበደረው፡፡ ይህ የብድሯ መጠንም ከዓመት ዓመት እየቀነሰ መጥቶ ዛሬ ከአጠቃላይ በጀቷ ከ20 በመቶ በታች ሆኗል፡፡ ከ80 በመቶ በላይ በጀቷን ከሃገር ውስጥ ሀብቷ መመደብ ችላለች፡፡ ይህ ደግሞ ነፃ ኢኮኖሚ መገንባት አለብን የሚለውን የኢህአዴግ ከትጥቅ ትግል ጀምሮ የነበረ የቆየ አቋም የሚያሳይ ነው፡፡
ሌላው ማንም ሰው በግለሰብ ደረጃም ቢሆን ብድር ስለጠየቀ አያገኝም፡፡ ለመበደርም መታመን ያስፈልጋል፡፡ መታመን ሁለት ዓይነት ነው፡፡ አንድም የአበዳሪዎችን የማትጠረጠር ተላላኪና ጉዳይ አስፈፃሚ መሆን ነው፡፡ አድርግ የተባለውን ሁሉ የሚያደርግ ሆኖ መገኘት፡፡ ሌላው መታመን አበዳሪዎች ቢወዱህም ቢጠልሁም የተበደረውን በልቶና ጠጥቶ አያባክነውም ሰርቶ ይመልሰዋል የሚል ነው፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት ከታላላቅ የፋይናነስ ተቋማት እጅግ መሰረታዊ በሆኑ የኢኮኖሚ ፖለሲ ጉዳዮች ልዩነት አለው፡፡ በዚህ ልዩነቱ ምክንያትም ብዙ የብድር ፕሮፖዛሎቹ ውድቅ ተደርጎበታል፡፡ ነገርግን ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የእነዚህ አበዳሪዎችና የኢትዮጵያ መንግስት የሻከረ ግንኙነት በእጅጉ ተለውጧል፡፡ እንደ ህዳሴ ግድብ ያሉትን ታላላቅ ፕሮጀክቶች መስራት መጀመራችን ለልማት ያለን ቁርጠኝነት ማንም እንደማያግደን አሳይቷል፡፡ የህዳሴ ግድብ ትልቅ የዲፕሎማሲ ድልም ጭምር ያመጣ ፕሮጀክት ሆኗል”” ስለሆነም በኢትዮጵያና በፋይናንስ ተቋማትና አበዳሪዎች የነበረው ግንኙነት ተሻሽሏል ስንል በኢትዮጵያ መንግስት የመጣ መሰረታዊ የፖሊሲ አቅጣጫ ለውጥ ስለመጣ አይደለም፡፡ በፋይናንስ ተቋማቱና በአበዳሪ ተቋማት ዘንድ ግን ግልፅ ለውጥ ይታያል፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት ታማኝ ተበዳሪ፣ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚም ታማኝ አዳጊ ኢኮኖሚ መሆኑን ተረድቷል፡፡ ስለሆነም ለኢትዮጵያ የሚሰጥ ብድር አደጋ የሌለው /zero risk/ ይሉታል፡፡ እንዲያ ካልሆነ እነዚህ ፋይናንሰ ተቋማት ከአኛ በቀር ስለአለም አያውቅም ብለው የኢትዮጵያ ህዝብን ለማደናገር እንደሚጣጣሩት ተቃዋሚዎች ሳይሆን በራቸውን ላንኳኳ ሁሉ ብራቸውን በጆንያ እየሸከፉ የሚያሸክሙ አይደሉም፡፡
የኢትዮጵያ መንግስትም እንዲሁ በንዝህላልነት ወይም እሴት ለማይጨምሩ ጉዳዮች የሚበደር አይደለም፡፡ ለመከላከያና ለፅጥታ ሃይሏ ከአጠቃላይ በጀቷ 2 በመቶ ብቻ በመመደብ በዓለም ዝቅተኛ በጀት የመደበች ሃገር እንዴት ሰላሟን ጠብቃ በዓለም ሰላም ማስከበርም ከፍተኛ ሚና ማስመዝገብ ቻለች ዓለም ከኢትየጵያ ብዙ ለመማር መጣር አለባት እያሉ እየፃፉባት ያለች ሃገር እያንዳንዷ ሳንቲም ለልማት እየዋለች ለመሆኗ እድገቷ ማረጋገጫ ነው፡፡
ስለሆነም የኢትዮጵያ መንግስት ገንዘብ ሰጪ ስለተገኘ ብቻ የሚያግበሰብስ አይደለም፡፡ አበዳሪዎቹም እንዲሁ ገንዘባቸውን እያፈሱ ለጠየቃቸው ሁሉ የሚበትኑ አይደሉም፡፡ የኢትዮጵያ መንግስትም አበዳሪ ይሞታል ብሎ የሚበደር አይደለም፡፡ አበዳሪዎችም እንደዛው፡፡ ስለሆነም ኢትዮጵያ ወይ አበዳሪ ወይ ተበዳሪ ይሞታል ብላ የምትበደር ሃገር አይደለች