1.ችግሮቻችንን ያለምህረት እንገምግም፣ ከችግሮቻችን እንቆራረጥ
2009
በድርጅታችን ኢህአዴግ ሰፊ ዳግም በጥልቀት መታደስ ንቅናቄ የሚካሄድበት መሆኑ ይታወቃል፡፡ በጥልቀት መታደስ ለምን አስፈለጊ ሆኖ
እንደተገኘም በቂ የህዝብ ግንኙነት ስራ ተሰርቷል ማለት ይቻላል፡፡ መዋቅራችን ብቻ ሳይሆን በጥልቀት መታደስ ለምን አስፈለገ በሚለው
ዙሪያ በህዝብ ኮንፈረንስም መግባበት ለመፍጠር ጥረት ተደርጓል፡፡ አሁን በምንገኝበት ድርጅታዊና ሃገራዊ ሁኔታ ጉዟችንን ሊቀለብሱ
የሚችሉ ፖለቲካዊ ብልሽቶች አጋጥመውናል፡፡ ይህንን ሲባል ግን ግምገማው እስካሁን ለመጣነው ጉዞና ለተገኙ ድሎች በዜሮ የሚያጣፋ
መሆን የለበትም፡፡
ነባራዊ
ሁኔታው ስንገመግም መነሻችን እና አተያየታችን የተዛባ መሆን የለበትም፡፡ ያጋጠሙን የውስጥ ድርጅትና ሀገራዊ ተግዳሮቶችና እንቅፋቶች
በስኬቶች ላይ ሆነን ያጋጠሙን ናቸው የሚለውን የድርጅታችን ግምገማ በጥብቅ መጨበጥ ይገባል፡፡ በመሆኑም በጥልቀት መታደስ አለብን
ሲባል ከችግሮቻችን መቆራረጥ አለብን ማለት እንጂ እስካሁን ያሳካናቸው ስራዎቻችንን የሚደፈጥጥና የሚክድ መሆን አለበት ማለት አይደለም፡፡
በጥልቀት መታደስ አስፈላጊ የሆነው እሰካሁን የረባ ስራ ስላልሰራን ይህንን ሀጥያት ለመናዘዝ ሳይሆን በስኬት ላይ ሆነን ያጋጠሙን
ችግሮች ግን አቃልሎ መታየት የሌለባቸው ብቻ ሳይሆኑ በተለየ የተሃድሶ ንቅናቄ መልክ በፍጥነት ካልቀለበስናቸው አጠቃላይ ድሎቻችንም
የሚበሉ የህዳሴ ጉዟችንም የሚያደናቅፉ ከባድ ችግሮች ናቸው፡፡ የመጀመሪያው
ሊሰመርበት የሚገባና መግባበት ሊደረስበት የሚገባ ነጥብ ይህ ነው፡፡