1.ችግሮቻችንን ያለምህረት እንገምግም፣ ከችግሮቻችን እንቆራረጥ
2009
በድርጅታችን ኢህአዴግ ሰፊ ዳግም በጥልቀት መታደስ ንቅናቄ የሚካሄድበት መሆኑ ይታወቃል፡፡ በጥልቀት መታደስ ለምን አስፈለጊ ሆኖ
እንደተገኘም በቂ የህዝብ ግንኙነት ስራ ተሰርቷል ማለት ይቻላል፡፡ መዋቅራችን ብቻ ሳይሆን በጥልቀት መታደስ ለምን አስፈለገ በሚለው
ዙሪያ በህዝብ ኮንፈረንስም መግባበት ለመፍጠር ጥረት ተደርጓል፡፡ አሁን በምንገኝበት ድርጅታዊና ሃገራዊ ሁኔታ ጉዟችንን ሊቀለብሱ
የሚችሉ ፖለቲካዊ ብልሽቶች አጋጥመውናል፡፡ ይህንን ሲባል ግን ግምገማው እስካሁን ለመጣነው ጉዞና ለተገኙ ድሎች በዜሮ የሚያጣፋ
መሆን የለበትም፡፡
ነባራዊ
ሁኔታው ስንገመግም መነሻችን እና አተያየታችን የተዛባ መሆን የለበትም፡፡ ያጋጠሙን የውስጥ ድርጅትና ሀገራዊ ተግዳሮቶችና እንቅፋቶች
በስኬቶች ላይ ሆነን ያጋጠሙን ናቸው የሚለውን የድርጅታችን ግምገማ በጥብቅ መጨበጥ ይገባል፡፡ በመሆኑም በጥልቀት መታደስ አለብን
ሲባል ከችግሮቻችን መቆራረጥ አለብን ማለት እንጂ እስካሁን ያሳካናቸው ስራዎቻችንን የሚደፈጥጥና የሚክድ መሆን አለበት ማለት አይደለም፡፡
በጥልቀት መታደስ አስፈላጊ የሆነው እሰካሁን የረባ ስራ ስላልሰራን ይህንን ሀጥያት ለመናዘዝ ሳይሆን በስኬት ላይ ሆነን ያጋጠሙን
ችግሮች ግን አቃልሎ መታየት የሌለባቸው ብቻ ሳይሆኑ በተለየ የተሃድሶ ንቅናቄ መልክ በፍጥነት ካልቀለበስናቸው አጠቃላይ ድሎቻችንም
የሚበሉ የህዳሴ ጉዟችንም የሚያደናቅፉ ከባድ ችግሮች ናቸው፡፡ የመጀመሪያው
ሊሰመርበት የሚገባና መግባበት ሊደረስበት የሚገባ ነጥብ ይህ ነው፡፡
2. ለስኬቶቻችችን ተገቢ ሚዛን መስጠት
ነገር
ግን ለድሎቻችን ተገቢ ቦታ መስጠት ይኖርብናል፡፡ ሳይንሳዊ ግምገማ የሚባለው የተሰራውና ያልተሰራውን በሚዛኑ ማስቀመጥ የሚችል ነው፡፡
ድሎቹንና ስኬቶቹን በትክክልና በሚዛኑ ሳይንሳዊ በሆነ መልኩ የማይመዝንና የማይተነትን ሃይል በፍፁም ተራማጅ አስተሳሰብ ሊኖረው
አይችልም፡፡ ስኬቶችን በትክክል ማየት የቻለ ሃይል ጉድለቶቹን በአግባቡ ማየት አይሳነውም፡፡ በትክክል ሲባል ሳያጋንንም ሳያንኳስስም
ማለታችን ነው፡፡ ስኬቶችን ብቻ ከልክ በላይ አጋንኖ ማጉላት ራስህን የማርካት ድንዛዜ በመፈጠር ከእውነታ እንድታፈነግጥም ያደርጋል፡፡
ይህ ደግሞ በአመራሩ ሚዛን እና በህዝቡ ሚዛን ልዩነት ይከሰታል፡፡ ለተንሳፋፊነት ፖለቲካዊ ብልሽት ይዳርጋል፡፡
በሌላ
በኩል ስኬቶችን እያንኳሰሱ ፣ ችግሮች መለጠጥም ትክክልኛ የህዳሴ አመራር ጥበብ አይደለም፡፡ በተለይም ደግሞ እንዲህ አይነቱ ግምገማ
እየተደጋገመ ሲሄድ በልማተ ሃይሎች ውስጥ ሚዛነ የማጣትና ጨለምተኝነት እንዲነግስ ስለሚያደርግ ለልማትና ለውጥ ያለውን መነሳሳትን
ጭምር እንዲሰለብ ያደርጋል ፡፡ ተስፋ መቁረጥም ያስከትላል፡፡ ይህንን እንደ ጥሩ እድል በመጠቀም ስራውንና መስመሩን ለማብጠልጠል
ለሚፈልጉ ተፃራሪ ሃይሎች ጥቃት ይዳርጋል፡፡ በዚህ ፖለቲካዊ ጥቃትም የልማት ሃይሎች/ተጠቃሚ የሆኑትንም ጭምር/ ይሰለባሉ፡፡ ያገኙትን
ጥቅም ከማጣጣም ይልቅ የጎደለውን ከልኩ በላይ ለጥጠው በመመልከት ዘላቂ ጥቅማቸውን የሚፃረር ተግባር እስከመተባበር ይሄዳሉ፡፡ ስለሆነም
ጨለምተኝነቱ ከአስፈፃሚው ተሻገሮ ወደ ህብረተሰቡ ሲሰርግ አጠቃላይ ሀገራዊ እውነታውን የማይመጥን ቀውስ ይፈጠራል፡፡ በመሆኑም ጉድሎቶቻችንን
ቀርፈን በአዲስ ግለት የህዳሴ ጉዟችንን ለማስቀጥል ካለን ድርጅታዊ ቁርጠኝነት ያነሳሳነውን የተሃድሶ ንቅናቄ በህዝቡም በአባላችንም
የተሳሰተ ሰሜት እንዳይፈጥር ሁለተኛው ሊሰመርበት የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡
በእርግጥ በኢህአዴግ የሁኔታ ግምገማ ለጥንካሬዎች ብዙ ጊዜ ሰጥቶ መገምገምና
በተንተን ከጊዜ በጀት አንፃርም ረዘም ያለ ጊዜ መስጠት እምብዛም የተለመደ አይደለም፡፡ ይህ ግን በአንድ በኩል የራሱ የሆነ ችግር
አለው፡፡ ሰዎች ለነገሮች ያላቸው አረዳድ ለየቅል ስለሚሆን እውነታውንንና ነበራዊ ሁኔታውን በትክክልና በሚዛኑ አለማየት ያስከትላል፡፡
ይህ ደግሞ በሰዎች አተያይ ጨለምተኛነት ይፈጥርና ለጉድሎቶችም በትክክለኛ ሚዛን ማስቀመጥ ያስቸግራል፡፡ ድክመቶችን በትክክል አለማስቀመጥና ከልኩ በላይ መለጠጠም አብዮታዊነት አይደለም፡፡ትክክለኛው አብዮታዊና ተራማጅ ግምገማ ለስኬቶችንም በልካቸው ለችግሮችም
በልካቸው የሚያይ አይን ያለው፡፡
ስኬቶች
ከኛ ጋር ያሉ ናቸው ማንም አይወስድብንም የሚለው በመርህ ደረጃ ትክክል ነው፡፡ ድክመቶች ላይ ብቻ ትኩረት እንስጥ የሚለው መነሻው
በችግሮች ላይ ለመረባረበ የሚገፋው አዎንታዊ፣ አብዮታዊና ህዝባዊ መነሻው ያለው ነው፡፡ ነገር ግን ችግሩ ለመፍታት የልማት ሃይሎችን አሟልቶ እና አቀናጅቶ
ለማሰማራትና ለማረባረብ የልማት ሃይሎቹ መጀመሪያ በስኬቱና በጉድለቱ ግልፅ እና ሚዛናዊ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ማድረግ ቀዳሚ ስራ ነው፡፡
የነበርንበት
መነሻ ከዚህ ነው፤ አሁን እዚህ ደርሰናል፤ ይህንንን ይህንን አሳክተናል፤ ነገር ግን ከእቅዳችንና ከህዝባችን ፍላጎት አንፃር እዚህ
ድረስ መድረስ ነበረብን፤ ወደዚህ እንዳንደርስ ያደረጉን ማነቆዎች ደግሞ እነዚህ፣ እነዚህ ናቸው ተብሎ በግልፅ ማቅረብና መግባበት
ላይ መድረስ ያስፈልጋል፡፡ ከዚህ ውጪ በተግባርም እንደሚታየው አንዳንዴ ከላይ እስከታች መርዶ ነጋሪ ጡርምባ ነፊ መሆን፣ አንዳንዴ
ደግሞ ሁሉም መድረክ ጮቤ የሚረገጥባቸው ድሎች ብቻ የሚሰበክባቸው ማድረግ በግምገማ ሂደቶቻችን የሚታዩ ልናርማቸው የሚገቡ ጉድለቶች
ናቸው፡፡
3. መደበኛ
ስራዎቻችን ላይ እንረባረብ
በአሁን
ወቅት ድርጅታችን ኢህአዴግ ዳግም በጥልቀት መታደስ የተሰኘው መሰረታዊ ፖለቲካዊ እቅድ በማቀድ እንቅስቃሴ ላይ የገባንበት ወቅት
ላይ መሆናችን ይታወቃል፡፡ ይህ በጥልቀት የመታደስ ንቅናቄ በመሪ ድርጅቱ ከመሪ ድርጅቱም በአመራሩ የተጀመረ ቢሆንም በወጣለት መርሃ ግብር መሰረት ወደ መላው አባላችን፣
ወደ መንግስት መዋቅርና ወደ ህዝብ እየተቀጣጠለ የሚቀጥል አመቱን በሙሉ የሚዘልቅ ቁልፍ እቅድ ነው፡፡ እስካሁን ከመንግስት መዋቅርና
ከህዝብ ጋር በጥልቀት ለመታደስ መወሰናችን ይህንን የወሰንበት ምክንያት ምን እንደሆነ መግባባት ላይ ደርሰናል፡፡ ይህ በቀጣይ ይበልጥ
እየሰፋና እየጠለቀ ይሄዳል፡፡ በጥልቀት የመታደሱ ጉዳይም የመንግስት መዋቅሩና ህዝቡ ያላቸው ድርሻ በዝርዝር ይገመገማል ሀገራዊ
መግባባትም ይፈጠራል፡፡ ይህንን ታሳቢ ያደረጉ የእቅዶች ማስተካከያ፣ የአደረጃጀቶች ለውጥ፣ የሰው ሃይል ስምሪት ለውጦች ይደረጋሉ
ተብሎ ይጠበቃል ፡፡
በጥልቀት መታደስ ንቅናቄ ገብተናል ማለት መጀመሪያ የመታደሱ ምዕራፍ ጨርሰን ቀጥለን ወደ ልማትና መልካም አስተደደር ተግባራት እንገባለን ማለት
አይደለም፡፡ መታደሰ ከተግባራት ውጪ አይታሰብም፡፡ ማነቆዎቻችን ከመሰረቱ በጣጥሶ መጣል በተጋጋለ የህዝብ ማዕበል ወደ መፈፀም የምነገባው
በተሃድሶው አቅጣጫ ቢሆንም የመታደስ መርሃ ግብሩ እስኪጠናቀቅ ከተግባር
ውጪ ይኮናል ማለት አይደለም፡፡ በመሆኑም አቅጣጫችን መሆን ያለበት እየታደስን እንሰራለን እየሰራን እንታደሳለን የሚል ነው፡፡
ከዚህ
አንፃር በዘንድሮ የከተማችን አመታዊ እቅድ የዝቅተኛ የህብረተሰብ ክፍል የልማት ተጠቃሚነትና የኑሮ ውድነትን ማቃለል የሚያስችሉትን
ስትራተጂካዊ ስልታዊ እቅዶችን አቀናጀቶ መፈፀምና መረባረብ ልዩ ትኩረት የሚሰጠው ይሆናል፡፡ ይህንን እቅድ ለማሳካት ደግሞ ካለ
ልማታዊ ሰራዊት የሚታሰብ አይደለም፡፡ የልማት ሰራዊቱ ዋናው መሪ ደግሞ ድርጅት ነው፡፡ በየሴክተሩና ቀጠናው ያለችው መሰረታዊ ድርጅትና
ህዋስ ናት፡፡
እንደሚታወቀው
በከተማችን ከልማት አንፃር ሁለት ጎልተው የሚሰሙ ጉዳዮች አሉ፡፡ አንደኛ ስራ አጥነት ችግርን የመፍታትና የስራ እድል ፈጠራን የማስፋት
ጉዳይ ነው፡፡ ሁለተኛ ደግሞ የአብዛኛው የከተማችን ነዋሪ እየተፈታተነ የሚገኘው የኑሮ ውድነት ነው፡፡ እነዚህ ሁለት የህዝቡ ጥያቄዎች
ዘንድሮም ለሚቀጥሉት አመታትም ዓበይት ጥያቄዎች ሆነው መቀጠላቸው አይቀርም፡፡ በአንድ አመት የሚወገዱ አይደሉም፡፡ አካቻምናም አምናም
ሰርተናል፡፡ ዘንድሮም ዋናው የርብርብ ማእከል ይህ ይሆናል፡፡ ለከርሞም እንሰራለን፡፡ ስለሆነም ይህ ጥያቄ በአንድ ጊዜ ተሰርቶ
የሚጠናቀቅ የቤት ስራ ሳይሆን ዓመታት የሚፈጅ መሆኑ ግልፅ መሆን ይኖርብናል፡፡ የስራ አጥነት ችግር አለም አቀፍ ችግር በመሆኑ
የብዙ መንግስታት ትልቁ አጀንዳ እንጂ የሀገረችን ብቸኛ ልዩ ገፅታ አይደለም፡፡ በዚህ ዙሪያ እስካሁን ያስመዘገብነው ውጤትን በማደብዘዝ
ችግሩም የኢትዮጵያ ብቻ አድርጎ በማቅረብ በህብተሰቡ የተዛባ ግንዛቤ እንዲያዝ በሌሎች ሃይሎች የሚደረገው ፕሮፓጋንዳ በተደራጀ መልኩ
ማምከን ይገባናል፡፡ አንድ መሰረታዊ መግባባት ሊያዝበት የሚገባ ጉዳይ ይኸው ነው፡፡
ዋናው ትኩረታችን ግን ከየትኛውም አመት በተሻለ ችግሩን ለማቃለል መረባረብ
ላይ መሆን አለበት፡፡ የህዝባችን አበይት ጥያቄዎች እንደመሆናቸው የመንግስት ስልጣን ይዘን ሀገሪቱንና ከተማውን እስከመራን ድረስ
ጊዜ መመለስ የመንግስት ግዴታ ነው፡፡ የመሪ ድርጅታችን ግዴታ ነው፡፡ የእያንዳንዱ አመራራችን፣አባላችንና መዋቅራችን ዋናው ተልእኮ
ነው፡፡ ዋናው ተልእኮ በመሆኑ ደግሞ ሁላችንም የምንለካበት ይሆናል፡፡ ምክንያቱም በተለያዩ ሰነዶቻችን ከዚሀ ቀደም እንደተቀመጠው
የስራ እድል ፈጠራም ሆነ የኑሮ ውድነትን የማቃለል ጉዳይ የአንድ ሴክተር ተግባር አይደለም፡፡ የስራዎቻችን ቁልፍ መመዘኛ እያንዳንዷ
ስራ እና ተግባር ድህነትን በማረድ ምን ፋይዳ አላት የሚል ነው፡፡
ይህ ስራ
ዘንድሮ ገና የምንጀምረው አይደለም፡፡ ለአለፉት የተሃደሶ አመታት ስንዘምትበት የነበረ ውጤትም ያገኘንበት ዋናው ግንባር ነው፡፡ ባለፉት አመታት ስራ አጥነት ለማስወገድ እና ኑሮውድነትን
ለማቃለል የሰራናቸው የምንኮራባቸው ስኬቶች ከህዝባችን አልፎ የውጭ አጋሮቻችን የመሰከሩለትና ያደነቁት ስኬት መጨፍለቅ የለብንም፡፡
በዚህ ዙሪያ የአተያይና አገማገም ህፀፅ እና ብዥታ ሊኖረብን አይገባም፡፡
በየአመቱ
ለመቶ ሺዎች የከተማችን ነዋሪዎች የአጭርና የረጂም ጊዜ የስራ እድል ፈጠረናል፤ይህ ጊዜያዊና ቋሚ የስራ እድል የሚባለው ነው፡፡
በዚህ ዙሪያ የተሰራ ስራ ከስትራቴጂው አንፃር ፣መስራት ከነበረብንና ከህዝባችን/በተለይ ከወጣቱ/ እርካታ አንፃር ሲመዘን ሰፊ ጉድለት
ቢኖርበትም ከነጉድለቱም ቢሆን ብስኬት የተገመገመ ትልቅ ስራ ነው፡፡ ነገር ግን ዛሬም እጅግ ብዙ ወጣት/ሴትም ወንድም/ ስራ አጥ
አለ፡፡ ይህ ስራ አጥ ወጣት የቤተሰቡ ጥገኛ ነው፡፡ የቤተሰቡ ጥገኛ ነው ማለት በቤተሰቧ ገቢ የሚያስገባ አባወራ ወይም እማወራ
ብቻ ገቢዋን የሚሻማት ግን እድሜያቸው ለስራ የደረሰ ስራ ያለያዙ ልጆቹ ጭምር ስለሚሆን ቤተሰቡ የመወዳደር አቅም ያጣል፡፡ ቤተሰቧ
በገበያ የተወሰነ የሸቀጦች ዋጋ በጨመረ ቁጥር የኑሮውድነቱን መሸከም ያቅታታል፡፡ ምክንያቱም በዋጋ ጭማሪው ልክ የቤተሰቧ ገቢ ሳይጨምር
ስለሚቀር ነው፡፡ ይህንን ችግር እንዴት ስትራጂካሊና ታክቲካሊ መፈታት እንዳለበት ግልፅ ፖሊሲና አቅጣጫ አለን፡፡ በርካታ ስልቶችንም
ተነድፈው ስራ ላይ ውለዋል፡፡ በከተማችን የኮንስትራክሽን ዘርፍ፣ ባህልና ቱሪዝም ዘርፍ፣ የማዘጋጀቤታዊ ጉዳዮች ዘርፍ፣ አሁን ደግም
የአከባቢ ጥበቃ ስራዎች የስራ እድልን በሚፈጥር አቅጣጫ እንዲመሩ ተደርጓል፡፡ ለምሳሌ የኮንስትራክሽን ዘርፍ፣ ከዘርፉም የጋራመኖሪያ
ቤቶች ፕሮጀክት ብቻ በየአመቱ እስከ60 ሽህ የሰው ሃይል የስራ እድልን እየፈጠረ ይገኛል፡፡
ቀደም
ሲል እንደተጠቀሰው ከልማት አኳያ የስራ እድል መፍጠርና የኑሮ ውድነት ጉዳዮች የዚህ አመትም የህዝባችን ዋና ጥያቄዎች ናቸው፡፡
በተለያዩ የህዝብ መድረኮች የነዋሪም ሆነ የወጣቶች በተለይ/ የሴትና ወንድ ወጣቶች/ ደጋግሞ ያነሱት የስራ ፍጠሩልን የኑሮ ውድነቱን
አማርሮናል የሚል ነው፡፡ ይህ ማለት እስካሁን በዚህ ዙሪያ በርካታ ሰኬታማ ስራዎች የተሰሩ ቢሆኑም ዛሬም ስራ አጥነትና ኑሮ ውድነት
ዋና ፈተናችን ነው ብለን እንውሰድ፡፡ ዋና ፈተና ነው ማለት ዋናው የርብርብ ማእከል ይሆናል ማለት ነው፡፡ ምክንያቱም ችግሩን ከመፍታት
ውጪ ሌላ አማራጭ የለውም፡፡በመሆኑም የከተማው አስተዳደር ዋናው የልማት እቅድ በዚህ ላይ ያተኩራል፡፡ በሀገር አቀፍ ደረጃ መንግስት
ከፐብሊክ ሰራተኛ እና ሌሎች ደመወዝ ተከፋይ አካላት ኢኮኖሚው አቅም በፈቀደውና ከማክሮ ኢኮኖሚ ባለው አንደምታ እየተመዘነ የደመወዝ
ማስተካከያ ሊደረግ የሚችል፡፡ በዚህ ጉዳይ ለጊዜው በዝርዝር የምንለው አይኖርም፡፡ በከተማ ደረጃ የስራ እድልና የኑሮ ውድነት የመቋቋም ጉዳይ እጅግ የተሳሳሩ በመሆናቸው ይህንን በተቀናጀ እቅድ ለመፍታት ርብርብ
ይደረጋል፡፡ ከዚህ አንፃር በከተማችን አራት እርስ በራሳቸው የሚመጋገቡ እቅዶች ታቅደዋል፡፡ እነዚህ እቅዶችን በብቃት ማሳካት የህዝባችን/አባላችንም
የህዝብ አካል በመሆኑ ተጠቃሚ ይሆናል/ እርካታ ማረጋገጥ ይኖርብናል፡፡
የአዲስ
አበባ ህዝብ ባለፉት ወራት የፀረሰላም ሃይሎች ጥሪና እንቅስቃሴ በማምከን የከተማው ሰላም አስጠብቋል፡፡ ይህ የተመለከተ አመራራችን
ይህን ህዝብ በምን እንካሰው የሚል ጥያቄ ሲያነሳ ነበር፡፡ ህዝቡ ሰላሙን የጠበቀው እስካሁን ያገኘውን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም/ እያንዳንዱ
ወደ ኪሱ ስለገባ ላይሆን ይችላል፡፡ እስካሁን በከተማውና በግሉ ያገኘው ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጥቅም በምንም መልኩ መነካት አይፈልግም፡፡
መነካት አይፈልግም ማለት ግን ረክቷል ማለት አይደለም፡፡ በርካታ የልማትና የመልካም አስተደዳር ጥያቄዎች አሉት፡፡ ጥያቄ ብቻ ሳይሆነ
በጊዜውና በፍትሃዊነተ ስላልሰራን በቅሬታ ጭምር የሚገለፅ የልማት ጥያቄ አለው፡፡ ስለሆነም ይህ ህዝብ በተለይም ወጣቱ የከተማውን
ሰላም በማስጠበቅ ላሳየው የፀና አቋም የሚጠብቀው ሌላ ካሳ የለም፡፡ ህዝቡ ከመንግስት የሚጠብቀው የተጀመረው ልማት በተሻለና ፍትሃዊ
በሆነ ደረጃ ማከናወንና መመለስ ነው፡፡
ከዚህ
አንፃር ቀጥለው የተጠቀሱትን አራት እርስ በራሳቸው የሚመጋገቡ እቅዶችን ለማሳካት አባላችን፣ አመራራችንና መዋቅር መረባረበ አለበት፡፡
አራቱ እቅዶች እርስበራሳቸው የተሳሳሩ የህዝባችን ኢኮኖሚ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ፣ ከኢኮኖሚው ፍትሃዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡና
የኑሮ ውድነትን መቋቋም የሚያስችሉ ናቸው፡፡
1. የስራ እድል ፈጠራ፤
በዘንድሮ
እቅዳችን በአንድ በኩል ነባር ኢንተርፕራይዞች ለማጠናከር የሚሰሩ ስራዎች ይኖራሉ፡፡ በነባር ኢንተርፕራይዞች ያሉን የመልካም አስተደደር
ገፅታ ያላቸው ጥያቄዎችን በመፍታት በዘርፉ አንቀሳቀሾች የሚነሳ ቅሬታ መፍታት እንደተጠበቀ ሆኖ አዳዲስ የስራ እድሎች መፍጠር ይገባል
በሚል በመነሻነት ከ200ሺህ በላይ በጊዚያዊና በቋሚ የስራ እድል ይፈጠራል፡፡ ከዚሁ ከ80 በመቶ በላይ በቃ ዘርፍ የሚፈጠረ የሰራ
እድል ይሆናል፡፡ ከጥቂት አመታት ወዲህ የተደረጉ ጥረቶች ቢኖርም በዚህ ዘርፍ የነበረው አንድ ችግር የሚፈጠረው የስራ እድል/የውሸት
ሪፖርት እንዳለሆኖ/ የሚበዛው ጊዜያዊ መሆኑ ነው፡፡ ጊዚያዊ የስራ እድል የሚባለው ረጂሙ አንድ አመት በመሆኑ ይህ ሰው ሃይል በየአመቱ
ስራ ሊፈጠርለት የሚፈልግ ሃይል በመሆኑ ስራው ውሃ ቅዳ ውሃ መልስ አድርጎት ቆይቷል፡፡ በዘንድሮ የስራ እድል ፈጠራ ግን ሶስት
አራተኛው ቋሚ የስራ እድል መፍጠር የኖርብናል ተብሎ ታቅዷል፡፡ አባሎቻቸን ስራ አጦችን በየመንደሩ በመለየት፣ ወደ ስራ እንዲገቡ
በማሳመን፣ እንዲደራጁ በማድረግ እንዲሀም ወጣቶቹ ከተደራጁ በኋላም በየጉራንጉሩ የሚያጋጥማቸው ቢሮክራሲያዊ ማነቆዎች እንደወገድላቸው
መታገል ይኖርባቸዋል፡፡ የስራ እድል መፍጠር ማለት በግለሰብ ደረጃ ተጠቃሚ ማድረግ ብቻ ሳይሆን የቤተሰቧ ገቢም እንዲጨምር ስለሚያደርግ
ተፈጥራዊ የኑሮ ውድነትን ለመቋቋም ትችላለች ማለት ነው፡፡ ስትራቴጂካሊ የከተማን ነዋሪ የኑሮ ውድነት የሚፈታው የእያንዳንዷ ቤተሰብ
ገቢ እንዲጨምር በማድረግ ነው፡፡
2. ሸማች ማህበራትን ማጠናከርና የተለያዩ ድጋፎች መስጠት፡፡
የህብረት
ስራ ማህበረት እንደ አንድ የኢኮኖሚ ኢንተርፐራይዝ እና ራስ አገዝ ተቋማት የአባሎቻቸውንና የአከባቢ ህብረተሰብ የማህበረ ኢኮኖሚ
ሁኔታ በማሻሻል ወሳኝ ሚና ይጫወታሉ፡፡ ዓላማችን በአጋጠሟት ያልተረጋጋ የፋይናንስ ቀውስ፣የምግብ አቅርቦት እጥረት ፣ አለም አቀፈ ያልተመጣጠጠነ እድገት ፣ ፈጣን የአየር ንብረት ለውጥ እንዲሁም የአከባቢ መራቆት መጨመር ላይ ችግሩን በመቋቋመ የህብረት ስራ ማህበራት
ትልቅ ድርሻ ተጫወተዋል፡፡ በተለይም የሸማቾች የህብረት ስራ ማህበራት ለህብረተሰቡ የተለያዩ ሸቀጦችን በማቅረብ የአቅርቦት እጥረትንና
የዋጋ ንረትን በማረጋጋት ሚኖራቸው ድርሻ እጅግ ከፍተኛ ነው፡፡ በከተማችን የሚገኙ የሸማች ማህበራት መንግስት እንዲቋቋሙ ሲያደርግ
ከህዝብ ውግንናው የመነጨ ነው፡፡ በዋጋ ንረት የሚጎዳው አብዛኛው የአብዮታዊ ዴሞክራሲ መስመራችን ማህበራዊ መሰረት የሆነው ዝቅተኛ
ገቢ ያለውና ድሃ ህዝብ ነው፡፡ ዋናው የኑሮ ውድነትን የሚቋቋምበት ስትራጂያዊ መፍትሄ ገቢው እንዲጨምር መሆኑ እንደተጠበቀ በሸማች
ማህበር ተደራጅቶ ሸቀጦችን በተነፃፃሪ ርካሽ በሆነ መልኩ እንዲያገኝ ማድረግም መንግስት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራበት መጥተል፡፡ እንደሚታወቀው
የሸማች ማህበራቱ ሱቆች እንዲያገኙ ተደርጓል፡፡ ተጨማሪ ሱቆች የሚሰሩባቸው ቦታዎችም ተሰጥታቸዋል፡፡ የህብረት ሱቅና መዝናኛ ይባሉ
የነበሩት ተቋማት ከነሙሉ ሃብታቸው እንዲሰጣቸው ተደርጓል፡፡ በ2009 እቅድም ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶታል፡፡ በመሆኑም አባሎቻችን
እነዚህ ማህበራትን በመምራት የህዝቡን ተጠቃሚነት ይበልጥ እንዲያረጋግጡ እንደ አንድ ትልቅ ተልአኮ ወስደው መስራትና እስካሁነ የነበራቸው
ድርሻ በመገመገም በዚህ ዙሪያ ያለውን ጉድለት ማረም ይጠበቀባቸዋል፡፡
3. ህገወጥ ንግድን መቆጣጠር
በሸማቾች የህብረት ስራ ማህበራት፣ በነጋዴ ፎሮሞች፣ በተለያዩ የህዝብ አደረጃጀቶች የተደራጀው ህዝባችን እዚያው ሳለ
ለልማቱ ጠንቅ የሆኑ የኮንትሮባንድና ህገ-ወጥ ንግድ ተግባሮችን ለማጋለጥ አዘጋጅተን ማረባረብ ይኖርብናል፡፡ የህዝባችን የኑሮ ውድነት የሚያባብሱ ህገወጥ
ንግድ፣ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ እና አላግባብ ጥቅም ለማግኘት
ወይም በፖለቲካዊ ምክንያቶች የሚደረገው ምርቶችን የመደበቅ አሻጥሮችን ለማምከን ትኩረት ሰጥተን ልንሰራበት ይገባል፡፡
ጥቂቶቹ ተጠቅመው ሲንደላቀቁ አብዛኛው ህዝብ ለድህነት የሚዳርገውን ህገ-ወጥ ንግድ ለማጋለጥና የህዝቡን አቅም በአጀንዳው ዙሪያ አሳምነንና ተልዕኮ ሰጥተን በግንባር
ቀደምነት ልንመራው ይገባል፡፡
4. የሴፍት ኔት ፕሮግራም መተግበር
የከተሞች የልማታዊ ሴፍት ኔት ፕሮግራም ዘንድሮ ተግባራዊ
ይሆናል፡፡ የተለያዩ ቅድመ ስራዎች ሲከናወኑ ቆይተው አሁን ወደ ተግባር የሚሸጋገርበት ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ የከተሞች ምግብ ዋስትና ፕሮግራም በኢትዮጵያ ባሉ ከተሞች /አዲስ አበባን ጨምሮ/ በየምዕራፉ ተግባራዊ የሚደረግ ሲሆን በፕሮግራሙ ተጠቃሚ የሚሆኑት የድሃ ድሃ የሆኑ ግለሰቦችና ቤተሰቦች ናቸው፡፡ ይህ
ፕሮግራም የከተማችን ነዋሪዎች የኑሮውድነትን ለማቃለል የሚያገለግል፣ ሰዎች ተጨማሪ ገቢ እንዲያገኙ የሚያደርግ በመሆኑ በዚህ
ፕሮግራም ተጠቃሚ መሆን ያለባቸው በፍትሃዊነት እንዲለዩ መደረግ ይኖርባቸዋል፡፡ በዘንድሮ በከተማችን በተወሰኑ ወረዳዎች ተግባራዊ
የሚደረገው ይህ ፕሮግራም ከ130 ሽህ በላይ ተጠቃሚ ይሆናሉ፡፡ በሌላ አነጋገር ለ130 ሺህ ገቢ ይፈጠራል ማለት ነው፡፡ ይህ በጥቃቅንና
አነስተኛ ዘርፍ 215 ሺህ የስራ እድል ለመፈጠር ከተያዘው እቅድ ውጪ ነው፡፡ በመሆኑም በፕሮግራሙ ተጠቃሚ መሆን ያለባቸወ የድሃ
ድሃ በመሆናቸው ልየታው ከየትኛው አቀጣጫ ከሚመጣ አድልዎና ከኪራይ ሰብሳቢነት በነፃ መልኩ እንዲከናወን የድርጅታችን አባላት ድርሻቸው
የሚጫወቱበት አንድ ተልእኮ ነው፡፡
ማጠቃለያ፤
በአጠቃላይ
ከላይ የተዘረዘሩትን የከተማችን ነዋሪዎች ገቢ የሚጨምሩና የኑሮውድነትን ለመቅቋምና የዋጋ ንረትን ለመቆጣጠር የሚያስችሉ ስትራቴጂያዊና
ስልታዊ እቅዶችን በሚፈለገው አቅጣጫ እንዲሳኩ የድርጅታችን አባላት የአደረጃጀታቸውና የግል እቅዳቸው አካል አድረገው መውሰድ ይኖርባቸዋል፡፡
በተሃድሶ መንፈስና በሰራዊት አቅም ለሰኬታማበታቸውም መረባረብ ይጠበቅባቸዋል፡፡ እየታደስን እንሰራለን እየሰራን እንታደሳለን በሚል
መሪ ቃል ሁለቱም ተግባራት አጎራርሰን ማሳካት ይኖርብናል፡፡
No comments:
Post a Comment