Wednesday, 24 May 2017

የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሕገ-መንግስት መሰረታዊ ዓላማዎች

የኢ... ሕገ-መንግስት የኢትዮጵያ ህዝቦች በሃገራቸው መፃኢ ዕድል ላይ ብሩህ ተስፋ ሰንቀው እንደ አንድ ማህበረሰብ እንዲነሳሱ የሚያደርጋቸውን ዓላማ ያስቀመጠ ነው፡፡ ዓላማዎቹ በህገ-መንግስቱ መግቢያ ላይ የሰፈሩ ናቸው፡ ይህም አጠር ባለ መንገድ ሲገለፅ ያለፈውን የተዛባ ግንኙነት በማስተካከል እና ባለፈው ያፈሩትን የጋራ ሃብት፣ ትስስርና እሴት ስላላቸው በፍላጎታቸውና በራሳቸው ፈቃድ ዘላቂ ሰላም፣ ዋስትና ያለው ዴሞክራሲ እንዲሰፍን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እድገታቸው እንዲፋጠን የሚያስችል የጋራ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ማህበረሰብ ለመገንባት ቃል የገቡ መሆናቸውን፣ ይህን ለማሳካት የግለሰብም ሆነ የብሄሮች ብሄረሰቦች ህዝቦች መብቶችና የፆታ እኩልነት ማረጋገጥ፣ ባህሎችና ሃይማኖቶች ያለ አድሎና ልዩነት እንዲራመዱ ማድረግ ፅኑ እምነታቸው እንደሆነ መወሰናቸውን …. የሚል ነው፡፡ የሕገ-መንግስታችን መግቢያ ዘላቂ ሰላም፣ ዋስትና ያለው ዴሞክራሲ፣ ፈጣን ኢኮኖሚያዊ ልማት፣ አንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማህበረሰብ ግንባታ የሚሉ ዓላማዎችና ራዕዮች በግልፅ አስቀምጧል፡፡ እነዚህ የህገ-መንግስታችን ዓላማዎች የማይነጣጠሉና እርስ በርሳቸው የተሳሰሩ ናቸው፡፡




ዘላቂ ሰላምን ማረጋገጥ

የሰላም ዘላቂና አስተማማኝ መሆን በራሱ እንደ ግብ ሊቆጠር የሚችልና የሚገባ ቢሆንም ሰላም በሌለበት ልማትና የሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች መከበር ፍፁም የሚታሰብ አይሆንም፡፡ የኢትዮጵያ ህዝቦች የፖለቲካ መብቶች በመረገጣቸውና ኢኮኖሚያዊ ጥቅሞችን ተነፍገው በአገራቸው ባይተዋርና ባዕድ በመሆናቸው ምክንያት ባካሄዱት ትግል ከፍተኛ የሆነ ሰብአዊና ቁሳዊ ኪሳራ ማስከፈሉ የሚታወቅ ነው፡፡ እልህ አስጨራሽ ትግሉ መላ የአገራችንን ህዝቦች በአሰቃቂ ድህነትና ኋላ ቀርነት አዙሪት ውስጥ አስገብቶ ቆይቷል፡፡ በመላ ሃገሪቱ የተቀሰቀሰው ዓመፅና ጦርነት የልማት አጀንዳ ከመዝጋቱም ባሻገር የነበረውንም ጥቂት ሃብት እንዲወድምና ለጦርነት እንዲውል በማድረግ፣ አምራቹን ዜጋ እየቀጠፈ ሃገራችንን ወደ ብተና፣ ህዝቦቻችንም ወደ እልቂት የመራ አደጋ ነበር፡፡ ስለሆነም ሕገ-መንግስታችን ይህንን ነባራዊ ሁኔታ ከመሰረቱ የመቀየርና ዘላቂ ሰላም የማረጋገጥ ዓላማ ማስቀመጡ ተገቢ ይሆናል፡፡ በሕገ-መንግስቱ ማንኛውም ዓይነት አለመግባባት በሰላማዊ፣ በዴሞክራሲያዊና በሕጋዊ መንገድ የሚፈታበት ሕጋዊ ማዕቀፍ መቀመጡ ለዘላቂ ሰላም ዋስትና ይሆናል፡፡

ዋስትና ያለው ዴሞክራሲ ማስፈን

ሕገ-መንግስታችን ዋስትና ያለው ዴሞክራሲ የማስፈን ዓላማ በማስቀመጡ የኢትዮጵያ ህዝቦች በሃገራቸው የላቀ እምነት በማሳደር ለዓላማው ስኬት እንዲነሳሱ የሚያደርጋቸው ይሆናል፡፡ በሃገራችን ሁሉም ሰብአዊና ዴሞከራሲያዊ መብቶችና የማንነቶች የእኩልነት ጥያቄዎች የታፈኑበት ታሪክ አልፏል፡፡ ዋስትና ያለው ዴሞክራሲ ማስፈን የሚፈለገው አንዱ ምክንያት ሰብአዊና ዴሞከራሲያዊ መብቶችና የማንነቶች የእኩልነት ጥያቄዎችን ለመመለስና የአፈና ስርዓቶች እንዳይመለሱ ዋስትና ለመስጠት ነው፡፡ ዴሞክራሲ በሌለበት የመልካም አስተዳደር ጉዳይም የሚታሰብ አይደለም፡፡ በሃገራችን ሁኔታ የዴሞክራሲ አፈና የተፈፀመው ከኢኮኖሚ ጭቆና ጋር ተሳስሮ ነው፡፡ በአብዛኛዎቹ የአገራችን አካባቢዎች ብሄራዊ ጭቆና የደረሰባቸው የኢትዮጵያ ህዝቦች የሃብት ምንጭ የሆነውን መሬታቸውን በመንጠቅ የተፈፀመ እንደነበረ የሚታወቅ ነው፡፡ አፋኝ ስርዓቶች ተወግደው የመልማት መብት ቢረጋገጥም ዘላቂነት ሊኖረው የሚችለው ዋስትና ያለው ዴሞክራሲ ሲኖር ነው፡፡

ፈጣን ኢኮኖሚያዊና ማሕበራዊ ዕድገት ማረጋገጥ   

የኢትዮጵያ ብሄሮች ብሄረሰቦች ህዝቦች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድገታቸውን ለማፋጠን ቃል ገብተዋል፡፡ ይህም የህገ-መንግስታችን አንዱ ዓላማ ነው፡፡ በሃገራችን ፈጣንና ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ ልማት የማምጣት ጉዳይ ከህልውና ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ስርዓታችን ቀጣይነት የሚኖረው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ሲፋጠንና የኢትዮጵያ ህዝቦች በአኗኗራቸው ላይ ተጨባጭና የማያቋርጥ ለውጥ ሲመዘገብ ነው፡፡ ይህ አጀንዳ ያለፉት ስርዓቶች ያልመለሱት እና የኢትዮጵያ ህዝቦች ከአዲሱ ሕገ-መንግስታዊ ዴሞክራሲዊ ስርዓት የሚጠብቁት በመሆኑ የህገ-መንግስቱ ዓላማ ሆኖ ተቀምጧል፡፡ በሌላ በኩል ዘላቂ ሰላምና ዋስትና ያለው ዴሞክራሲ ከፈጣን የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ውጭ ቀጣይነት ሊኖራቸው አይችልም፡፡

አንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማሕበረሰብ መገንባት

በሕገ-መንግስታችን መግቢያ የተቀመጠው ሌላው ዓላማ አንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማሕበረሰብ መገንባትን የሚመለከት ነው፡፡ ይህ ዓላማ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ገፅታዎች ያሉት በመሆኑ ከእነዚህ ገፅታዎች አኳያ ምን ማለት እንደሆነ በግልፅ መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡
()   የአንድፖለቲካ ማሕበረሰብ ምንነት
አንድ የፖለቲካ ማሕበረሰብ የመገንባት ጉዳይ በውስጡ በርካታ የስርዓት ግንባታ አጀንዳዎች የያዘ ቢሆንም ጥቂቶችን ወስደን ስንመለከት አንዱ በሕገ-መንግስትና በሕገ-መንግስታዊ ስርዓት ግንባታ ላይ የጋራ ሀገራዊ መግባባትን መፍጠር ማለት ነው፡፡ ዜጎችና ማህበረሰቦች ለሕገ-መንግስት ተገዢ በመሆን ህገ-መንግስቱን የማክበርና የማስከበር ሃላፊነትን የተሸከሙበትና የሕግ የበላይነት የሰፈነበት ሕገ-መንግስታዊ ስርዓትን መገንባት ማለት ነው፡፡ በሕገ-መንግስታዊ ዓላማዎች ላይ የጋራ አቋምና ተመሳሳይ አመለካከትን መያዝ ማለት ነው፡፡ ሁለተኛ አንድ የፖለቲካ ማህበረሰብ ግንባታ ሲባል የጋራ ሃገራዊ ራዕይ በመላበስና ተመሳሳይ አመለካከት በመያዝ ሀገራወዊ ራዕዩን ማሳካት ማለት ነው፡፡ ሃገራችን በቀረፀችው ራዕይ ላይ የጋራ አቋም በመያዝ ራዕዩን እውን ለማድረግ ዜጎችና ማህበረሰቦች አንድ ሆነው የሚረባረቡበት ሁኔታ መፍጠር፣ በሌላ በኩል ይህ ራዕይ እንዳይሳካ ዕንቅፋት የሚሆኑና የሚቀለብሱ አፍራሽ እንቅስቃሴዎችና ድርጊቶችን ያለማስተናገድ፣ መታገልና ማስወገድ ማለት ነው፡፡ ሶስተኛው ጉዳይ በሃገራዊ እሴቶች፣ በመሰረታዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነትና በወሳኝ ሃገራዊ ፖሊሲዎች ላይ ተመሳሳይ አመለካከትና የጋራ አቋም መያዝም ያጠቃልላል፡፡ ብዝሃነትን መቀበል፣ እኩልነትን ማክበርና በአብሮነት ላይ የተመሰረተ ሕበረ-ብሄራዊነትን ማጎልበት ላይ የጋራ አቋም መያዝ ያስፈልጋል፡፡ ለሃገራችን ፀጥታና ደህንነት ዋስትና በሚሰጡ ሃገራዊ ፖሊሲዎች ላይ የማይዛነፍ አቋም መያዝ ይገባል፡፡
()   አንድ የኢኮኖሚ ማህበረሰብ ምንነት
አንድ የኢኮኖሚ ማሕበረሰብ ግንባታ ዓላማ ከኢኮኖሚያዊ ትስስርና ተጠቃሚነት ጋር የተያዘ ነው፡፡ ልማታዊ አስተሳሰብን የበላይነት የሰፈነበትና ድህነትን ለማጥፋት በሚካሄዱ ሃገራዊ የልማት አጀንዳዎች ላይ የጋራ አመለካከት በመያዘ ለልማታዊነት የሚረባረብ ማህበረሰብን መፍጠር ማለት ነው፡፡ ሁለተኛው ገፅታ ለፈጣን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት ወሳኝ የሆኑ መሰረታዊ የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲዎች የተከበሩበትና በእነዚህ የፖሊሲ ማዕቀፎች ላይ የሚመራ ማህበረሰብን መገንባትና ፈጣን ልማትን ማረጋገጥ ማለት ነው፡፡ ይህም በአንድ ሃገራዊ የመገበያያ ገንዘብ የመጠቀም፣ ከገንዘብ፣ ከወለድና ከብድር ጋር የተያያዙ ሃገራዊ ፖሊሲዎችን የማክበርና የመፈፀም ጉዳይን ያጠቃልላል፡፡ ሶስተኛው የነፃ ገበያ ማዕቀፍን መሰረት ያደረገ የካፒታል፣ የዕቃዎችና ምርቶች የሰውና ጉልበት ዝውውር ፖሊሲን መከተል ማለት ነው፡፡ አራተኛው ጉዳይ የመሰረተ ልማት አቅርቦትና ትስስርን ይይዛል፡፡ ኢንቨስትመንትና ካፒታል፣ ሰራተኛና ምርቶች ከአንድ አከባቢ ወደ ሌላው አከባቢ በቀላሉ እንዲደርሱ የሚያስችል የአየርና የየብስ መሰረተ ልማትን መዘርጋት፣ የፈጣን መረጃ ልውውጥ ቴክኖሎጂን ማስፋፋት፣ በሁሉም የሃገሪቱ ክፍሎች አስፈላጊ የሃይል አቅርቦትን ማሟላትና ህዝቦቻችንና ክልሎቻችንን በጠንካራ ገመድ ማስተሳሰር የዚህ አካል ነው፡፡ አምስተኛው ገፅታ ከሚመዘገበው ዕድገት ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ ላይ ያተኮረ ሲሆን የዕድገት ዕድሉ ለሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎችና የኢትዮጵያ አካባቢዎች ተደራሽ የማድረግ፣ ይህንን ዕድል መጠቀም ለማይችሉትም በተለየ ሁኔታ በመደገፍ የዕድገቱና የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ለውጡ ተጠቃሚ ማድረግን ያስፈልጋል፡፡


No comments:

Post a Comment