Friday, 29 April 2016

ፌደራሊዝም ወዴት እየወሰደን ነው? በመቃብሽ ርግበይ



 የአሃዳዊ ሃገር ግንባታው ሂደትና ውጤቱ 
ክፍል ሁለት

የአፍሪካ ቀንድ የሰው ልጆች የታሪክ ቀጣይነትና ለውጥ ዋናው አካል የሆነው የዛሬዋ ኢትዮጵያ ህዝቦች ታሪክ ስንመለከት እንደግግር በረዶ የረጋ አይደለም፡፡ ከሰሜን ወደ ደቡብ ከደቡብ ወደ ሰሜን ፣ ከሰሜን ወደ ምስራቅ፣ ከምስራቅ ወደ ሰሜን እየደጋገመ ሲናጥ የመጣ ነው፡፡ ለአጭር ጊዜ ቦግ ብሎ የከሰመው የአህመድ ግራኝ መር የምስራቅ ኢትዮጵያ ህዝቦች ሃያልነትና ማስፋፋትን ጨምሮ ‹‹የሰሎሞናዊያን›› ሰሜኖች እና የኦሮሞ ህዝብ የገዥዎችና የህዝብ እንቅስቃሴ ለረጂም መቶ አመታት የነበረ ነው፡፡ የሰሜን ኢትዮጵያ ገዥዎች ወደ ምስራቅ እና ደቡብ ኢትዮጵያ የተስፋፉት ድንገት በሚኒሊክ ጊዜ አይደለም፡፡ የሃድያዋ ንግስት ኢሌኒ፣ የወላይታው የትግሪያን ዳይናስቲ፣ የዛይላ ወደብ ንግድ ወዘተ ሰሜኖች ወደ እነዚህ አካባቢ በተለያየ ወቅት ያደረጓቸው ማስፋፋት ማሳያ ናቸው፡፡ በተመሳሳይ እስከ ራያ የዘለቀው የ16ኛ ክ/ዘመን የኦሮሞ ህዝብ እንቅስቃሴም በአፍሪካ ቀንድ ህዝቦች ትልቅ የሆነ የባህልና የስነልቦና ለውጥና መገለባበጥ የፈጠረ መሆኑን መካድ አይገባም፡፡ እነዚህ የሰው ልጅ እድገት ውጤት የሆኑ ከ ወደ የነበሩ ንቅናቄዎችና ግንኙነቶች ለዘመናዊቷ ኢትዮጵያ መመስረት እርሾዎች ናቸው፡፡ እነዚህ ከተለያየ አቅጠጫ የተደረጉ የመስፋፋት፣ የጦርነት፣ የመዋዋጥ፣የማስገበር ወዘተ መስተጋብሮች ግን ቋሚ የሆነ የጠቅላይነት ውጤት አምጥተው ማእከላዊ መንግስት ለመመስረት ያስቻሉ አልነበሩም፡፡ አንዴ አንዱ ክፍል የበላይት ሲያገኝ፣ ሌላ ጊዜ ሲዳከም ሌላኛው የበላይነት ሲይዝ፣ አንዳንዴም ሃይል መመጣጠን ወይም መዳከም ተፈጥሮ በየራሱ ተራርቆ አካባቢያዊ አገዛዝ መስርቶ በየጎጆው ሲኖር በእንዲህ ያለ ቀጣይነትና ኢቀጣይነት ሲያልፍ የመጣ ነው፡፡
ኢትዮጵያ በአንድ ማእከላዊ መንግስት የምትተዳደር አገር የሆነችው አንዴ ሲጠናከር አንዴ ሲላላም ቢሆን የዘመናት የተሳሰረ ታሪክ የነበራቸው የሰሜን ኢትዮጵያ ህዝቦች እንዲሁም በሰሜናዊው ኢትዮጵያ የተሳሰረ ታሪክ ውስጥ ተሳታፊ ያልነበሩትን የዛሬዋን ኢትዮጵያ ደቡብ፣ ደቡብ ምዕራብና ምስራቅ ህዝቦችን በማካተት ነው፡፡ ማእከላዊ መንግስት ሆና እንደ አገር የቆመችው በአፄ ሚኒሊክ ዘመን ነው፡፡ አፄ ሚኒሊክ ወደ ማእከላዊ መንግስት የሰበሰቧቸው ህዝቦች በቀደምት ታሪካቸው ታሪካዊ፣ ጂኦግራፊያዊ፣ ስነ ልቦናዊ፣ አስተዳደራዊና ኢኮኖሚያዊ ትስስር እንደነበራቸው ከፍ ሲል በሃገራዊ ግንባታ ቀጣይነትና ኢቀጣይነት የነበረውን ሂደት አይተነዋል፡፡
ስለሆነም እስከ አፄ ሚኒሊክ ጊዜ በደቡብም ሆነ በሰሜን ኢትዮጵያ የእድገት ሂደቱን የጨረሰ ማዕከላዊ መንግስት አልነበረም፡፡ ሁለቱንም አካባቢዎች በመቆጣጠር ማዕከላዊ መንግስት መመስረት የቻለ ሚኒሊክ ብቻ ነው፡፡
ከዚህ አንፃር የኢትዮጵያ ማእከላዊ መንግስት አመሰራረት ከጊዜ ልኬታ ከምስራቅ አውሮፓ ሀገራት አመሰራረት የሚመሳሰል ባህሪ ያለው ሆኖ እናገኘዋለን፡፡፡ በዋነኛነት ግን የኢትዮጵያ አፄዎች ማእከላዊ መንግስት የመመስረት መነሳሳት ከአውሮፓ ይለያል፡፡ አፄዎቹ እጅግ ወግ አጥባቂ ፊውዳሎች ሲሆኑ የተጠናከረ ማእከላዊ መንግስት ለመመስረት የገፋፋቸው ኢኮኖሚያዊ እድገቱ ሳይሆን የውጭ ወራሪ ሃይሎች ስጋት ነው፡፡ በዚህም ኢትዮጵያ ገና የባላባታዊ ስርአት ከመደምሰሱ በፊት ማእከላዊ መንግስት ለመመስረት ቻለች”” በመሆኑም የኦሮሞ ህዝብን ጨምሮ ሌሎች የደቡብ፣ የምስረቅና ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች በኢትዮጵያ ማእከላዊ መንግስት ለመመስረት በሚደረግ ሂደት በሚኒሊክ በማእከላዊ መንግስት የገቡ እንጂ ቀደም ሲል የነበረን ማዕከዊ መንግስት በሌላ ማእከላዊ መንግስት የተፈፀመ የቅኝ ግዛት ጠቅላይነት ስላልሆነ ከዛን ጊዜ ጀምሮ በአንድ ማእከላዊ መንግስት ከሌሎች የኢትዮጵያ ህዝቦች ጋር አብሮ የነበረ በመሆኑ የብሄር ጭቆና የደረሰበት እንጂ የቅኝ ግዛት ሊባል አይችልም፡፡
ከዛን ጊዜ ጀምሮ ግን ህዝቦቹ በማእከላዊ መንግስት ማግኘት የሚገባቸውን የእኩልነት ቦታ አላገኙም፡፡ እጅግ አግላይ፣ በዝባዥና አጥፊ የሆነ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ባህላዊና ታሪካዊ ጭቆና ደርሶበታል፡፡ ይህ ደግሞ የአብዮቱ ማቀጣጠያ ዋናው ጥያቄ የብሄር ጥያቄ እንዲሆን አደረገው፡፡
የተማከለ የአንድነት መንግስት ምስረታው ህገመንግስታዊ የሆነው ደግሞ በአፄ ሃይለስላሴ ነው፡፡ በህገመንግስቱ የኢትዮጵያና መንግስቷ/ ንጉሷ/ ህልውና ምድራዊ ሳይሆን ሰማያዊ መሆኑን በሚያትት ፍልስፍና ከግማሽ ምዕተአመት በላይ አዘገመች፡፡ ፍልስፍናው የኢትያጵያ አንድነት ፍፁማዊነትን የንጉሷም ሰማያዊ ቅብነትን ለማስረገጥ ትልቅ ሚና የነበረው ቢሆንም የኤርትራና የኦጋዴን ፖለቲካ ትልቁን ፍልስፍና የሚገዳደሩ ነበር”” በ1950ዎቹ የግሎባል ፖለቲክስ በኢትዮጵያ ወጣት ትውልድ ላይ ጫና ማሳደሩ ሌላው አዲስ ክስተት ነበር፡፡ ንጉሱ ግን ይህን ክስተት በቅጡ ያስተዋሉት አልነበረም፡፡ መጨረሻው መጥፊያቸው የሆነው ግን የወጣቱ ትውልድ ንቅናቄ የወለደው ህዝባዊ ማዕበል ተፈጠረ፡፡ የኢትዮጵያ ተማሪዎችን እንቅስቃሴ የኢትዮጵያ አብዮት ወለደ፡፡
አሃዳዊነት በአዲስ ወታደራዊ ጉልበት
የየካቲት 66 ህዝባዊ አብዮት የአፄዎች ስርወመንግስት እንዲያበቃለት ቢያደርግም ለብሄር ብሄረሰቦች የዘመናት ጥያቄ መልስ መስጠት አልቻለም፡፡ በተጠናከረ ወታደራዊና የከተማና የገጠር ቢሮክራሲ ነባሩን አሃዳዊ ስርአት አጠናክሮ ቀጠለበት፡፡
ቀድም ብሎ እንዳየነው የብሄር ብሄረሰቦችን በራስ እድል በራስ የመወሰን መብት አለመታወቅና አልፎ ተርፎም በሃይል መታፈኑ የንጉሳዊ ስርአት አሀዳዊ መንግስት ዋና መለያ ነበር፡፡ የንጉሱ ስርአት የብሄር ንቃተ ህሊና እንዲደበዝዝና ብሄራዊ ማንነት እንዳያድግ አድርጓል፡፡ ይህ በሁለት መልኩ የተከናወነ ነበር፡፡ ብዙሃኑን የሀገሪቱ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች በመጨቆን ሲሆን ለአማራ ህዝብ ደግሞ የብሄር ንቃተ ህሊናውን እንዳያዳብር የማንሳፈፍ ስትራቴጂ ነበር የተከተለው፡፡ በአንድ በኩል የአማራ ብሄራዊ ማንነት በኢትዮጵያ ማንነት ሲጨፈልቀው በሌላ በኩል ደግሞ በጎጃሜነቱ፣ በጎንደሬነቱ፣ በወሎየነቱና በሽዋነቱ በተበጣጠሰ በጣም በጠባቡ በወንዝና በተራራ በተከለለ ድንበሮች እንዲያስብ አደረጉት፡፡ በዚህ የገዥዎች ፕሮጀክትም አማራ የሚባል የለም የሚለውን መሬት ላይ ያለውን እውነት የሚክድ ቅጥፈትን ብዙዎች እንደእውነት እስከመቁጠር ደረሱ፡፡
ይህ የአማራነትን ህልውና ያለማወቅና የማዳከም ስትራቴጂ በብሄሮች ላይ ከተካሄደው ጭቆና ለየት የሚለው አማራው በቋንቋው እንዳይጠቀም፣ በባህሉ እንዳይደሰት፣ ወይም ታሪኩን እንዳያነሳ ፊት ለፊት በማገድ የተፈፀመ አለመሆኑ ነው፡፡ ስለሆነም የሌሎች ብሄር ብሄረሰቦች የራሳቸውን እድል በራሳቸው እንዳይወስኑ ተደርገው በመቆየታቸው የአማራ ህዝብም ብሄራዊ ማንነቱ ተድበስብሶና ተደፍቆ እንዲቆይ አድርጎታል፡፡ የአማራ ህዝብን ብሄራዊ ማንነቱን በኢትዮጵያ ብሄርተኝነት ሸፍኖ እንዳያድግ አግዶት የቆየ ነው፡፡ በአጠቃላይ የአማራ ዴሞክራሲያዊ ብሄርተኝነት እንዳያብብ የማገድ እርምጃ ነበር በደርግም የቀጠለው፡፡ አልፎ ተርፎም የተከበረ ህዝብ ስም ከተራራ መጠሪያ ያለፈ ትርጉም እንደሌለው ተነገረን፡፡
ስለዚህ በድህረ የካቲት 66 ኢትዮጵያ መሰረታዊ ለውጥ ካልታየባቸው የአገሪቱ መሰረታዊ ፖለቲካዊ ጥያቄዎች መካከል አንዱ የብሄር ጥያቄ ነው፡፡ ለብሄር ብሄረሰቦች የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብታቸው ለማስተናገድ ደርግ ዝግጁ አልነበረም፡፡ ‹‹ኢትዮጵያ ትቅደም›› የሚለውን የሚቃረን ማንኛውም አስተሳሰብ ወንጀል መሆኑ በአደባባይ አወጀ፡፡
የደርግ መንግስት በስልጣን ላይ በቆየባቸው 17 አመታት ውስጥ የህዝቡን ጥቅምና መብት አፍኖ የነበረ መንግስት ነው፡፡ ገና ስልጣን ላይ ሲወጣም ገዥነቱ የፈለቀው ከህዝቦች መልካም ፍቃድ ስላልነበረ ይልቁንም በአመፅ የተነሳሳ ህዝብ ከፊቱ ተደቅኖ ስለነበረ ደርግ የባእድ ሀይል መንግስት ድጋፍን በከፍተኛ ደረጃ የሚሻ መንግስት ነበር፡፡ እናም የውጪ ሃይሎችን በተለይም የሶቭዮት ህብረትን ወታራዊ ድጋፍ በመጠቀም የህዝቦች ትግልን ለመጨፍለቅ ማድረግ የሚችለውን ሁሉ አደረገ፡፡
ይህ ደግሞ የእውነተኛ አብዮቱ መጀመሪያ እንዲሆን አደረገው፡፡ በዩኒቨርስቲ የተማሪዎች እንቅስቃሴ ግንባር ቀደም የነበሩ ወጣቶች የተለያዩ ቡድኖችና ድርጅቶች በመፍጠር ወደ ትጥቅ ትግል ተሸጋገሩ፡፡ የተማሪዎች ንቅናቄ ንድፈ ሃሳባዊ/ምሁራዊ/ ትንታኔ ቢሰጠውም አንግቦት የተነሳው የመሬት ለአራሹና የብሄረሰቦች ጥያቄ ያልተማረው አርሶ አደር አባቶቹ ሲያነሱትና ሲታገሉለት የነበረ አጀንዳ ነው፡፡ ስለሆነም ከተማሪ እንቅስቃሴ የመነጩ የግራ ሃይሎች ዱር ቤቴ ብለው ወደ ገጠር /ወደ አርሶ አደር ቤት/ ሲወጡ ይዘውት የሄዱት የመታገያ አጀንዳ የራሱ የአርሶ አደሩ ነበሩ፡፡ የአርሶ አደሩ ጥያቄ ደግሞ ብሄራዊና መደባዊ ጥያቄዎች ናቸው፡፡ የትጥቅ ትግል ለማካሄድ ወስነው የተደራጁ ቡድኖች ይዘውት የተነሱበት አላማ ወደመጨረሻ ቢያደርሱትም ባያደርሱትም የተለያየ ተቀፅላዎች ቢሰጣቸውም ይዘውት የተነሱት አጀንዳ የአርሶ አደሩ ነበር”” ነገር ግን ፀረ ወታደራዊ መንግስት የተካሄደው ትግል ረዘም ያለ አመታት በመውሰዱና እጅግ ደም አፍሳሽና ‹‹የአፍሪካ ረጂሙ ጦርነት›› የሚል ተቀፅላ ጭምር ያገኘ ስለነበር የጋራ እሴቶቹ በእጅጉ ተደፍቀው ሃገሪቱ ለብተና የተዘጋጀች መሰለች፡፡ በአጠቃላይ ግን ነባሩ የአርሶ አደሩ ጥያቄ ርእዮተአለማዊ ንድፈ ሃሳብ መልክ እንዲይዝ እንዲመራና ለድል እንዲበቃ በማድረግ ረገድ ኢህአዴግ የተጫወተው አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ሚና ከፍተኛ ነው፡፡ ይህም ሃገሪቱ ወደ ፌደራላዊ ስርአተ መንግስት እንድታመራ አደረገ፡፡
ዓለም በኢትዮጵያ ፌደራሊዝም ዋዜማ
ፌደራሊዝም የሚለው ቃል ወደ እንግሊዝኛ የመጣው በፈረንሳይኛ ቋንቋ በኩል ሆኖ ስረመሰረቱ ግን ከላቲን የተገኘ ቃል ነው፡፡ ፎይዴራተስ (Foedaratus) ማለት ‹‹በስምምነት መገዛት›› (bound by treaty) ሲሆን ፎደስ ( Foedus) ማለት ስምምነት ሲሆን ፌደሬ (Fldere) ማለት ደግሞ መተማመን ማለት ነው”” ቃሉ ሲጠቃለል በመተማመን፣ በስምምነትና በመቻቻል አብሮ መኖር ማለት እንደሆነ ከፍቺው መረዳት ይቻላል፡፡
ጆን ማክ ጋሪይ የተባለው ፀሓፊ በአንድ ፅሑፉ በተጠየቅ ይጀምራል፡፡ ፌደራሊዝም የጎሳና የብሄር ልዩነቶችን ለማቻቻል ያስችላል ብለው ያስባሉን? ይልና መልሱ እንደተጠያቄው እንደሚለያይና ወጥ መልስ እንደማይኖረው ይነግረናል፡፡ እውነት ነው ከፌደራሊዝም እሳቤ ቋሚ ፀብ ያላቸው ሰዎች በብዝሃነት የተመሰረተ ፌደራሊዝም አይሰራም ሃገር በታኝ ነው ይላሉ፡፡ በየብሄረሰቡ /እነሱ የሚሉት በየጎሳው/ የራስ አስተዳደር መስጠት ልዩነት ያላቸው ሰዎች ሃገሪቱን እንድትበታተን ያደርጋታል የሚል አቋም ያራምዳሉ፡፡ ባለፈው እትም ላይ እንደተጠቆመው ለቫልካናይዜሽን ይዳርጋል የሚል አቋም አላቸው፡፡
እዚህ ላይ ስለ ቫልካይናይዜሽን አጭር መረጃ ልስጥ መሰለኝ፡፡ የድሮዋ ዩጎዝላቪያ የምትገኝበት ክልል የባልካን ክልል ይባላል፡፡ ባልካን ማለት በቱርክ ቋንቋ የተራራ ሰንሰለት ማለት ሲሆን ክልሉ የጦርነትና የመከፋፈል ታሪክ አለው”” በተለይም በ19ኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ በአውሮፓ የእነ ጣሊያንና ጀርመን አንድ አገር መሆን በታየበት ዘመን በክልሉ ግን በተቃራኒው ቀድመው የነበሩ በተነፃፃሪ ሰፋ ያሉ ግዛቶች ወደ ትናንሽ አገሮች መፈጠር ተከስቶ ስለነበር በአሁኑ ወቅት በጥቅም ላይ የዋለው የፖለቲካ ቃል ማለትም ‹‹ባልካናይዜሽን››/ መከፋፈል፣ መበታተን/ ከዚያ የመጣ ነው”” ከዛ ጊዜ ጀምሮም ቃሉ ለግዛት መፈራረሶች መገለጫ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ ለምሳሌ በሶቭዮት ህብረትና በዩጎዝላቭያ ከ80 አመታት በኋላ የቫልካናይዜሽን ክስተት ተደርጎ ይቆጠራል፡፡
በፌደራሊዝም ላይ የሚወርዱ አዳፍኔ ነቀፌታዎች በአመዛኙ የሚነሱት ከዚሁ በቀዝቃዛ ጦርነት ዋዜማ ‹‹ኮሚኒስት›› ነበር የሆኑ የምስራቅ አውሮፓ ፌደራሊዝም ሀገራት ላይ የታዬ ፈጣን መበታተን ነው፡፡ የታሪክ አጋጣሚ ሆነና በወቅቱ በምስራቅ አውሮፓ ‹‹ኮሚኒስት›› የነበሩ ሲፈረካከሱ፤ አሃዳዊ የመንግስት ስርአት ይከተሉ የነበሩ ሃገሮች በአንፃሩ አንድነታቸውን ጠበቀው ቀጠሉ”” እውነት ነው ሶስቱ የህብረብሄር ፌዴሬሽን የሆኑት ሶቭየት ህብረት፣ ዩጎዝላቭያ እና ቺኮዝላቫክያ ተበታትነዋል”” ጆን ማክ ጋራይ የተባለው ካናዳዊ ተመራማሪ እንዳለውም ከኮሚኒዝም ወደ አዲስ ስርአት ሲሸጋገሩም ይበልጥ ህመሙ የነበረው በፌደራል ሃገራቱ ላይ ነበር፡፡
እንዲያ ብትንትናቸው እንዲወጡ ያደረጋቸው ግን በፌዴሬሽን ስለተዋቀሩ አልነበረም፡፡ ፌደራላዊ አወቃቀሩ ለመፈራረሳቸው ጠንቅም መንስኤም ተደርጎ ሊወሰድ አይገባም፡፡ ነገር ግን ተንታኞቹ ሆን ብለው ወይም ከግንዛቤ ማነስ ለሀገራቱ መፈራረስ ምክኒያት የሆነ ዋና ምስጢር ዘለውታል፡፡ ፌዴሬሽኖቹ እንዲያ የተበታተኑት በኢኮኖሚ ደካማ ስለነበሩ እና ድክመቱም ፌዴሬሽኑ ያመጣው ነው ብለው ይሞግታሉ፡፡ በሀገራቱ ሙስና እና የብሄራዊ ኢኮኖሚ እቅድ እጥረት ስለነበረ ዜጎች ማግኘት የሚገባቸውን የኢኮኖሚ ፀጋ እና የኑሮ ደረጃ ባለማግኘታቸው ነበር የሚልም ይነሳል፡፡ እንዲህ አይነቱ ድምዳሜ ከፊል እውነት ቢሆንም ለፌዴሬሽኖቹ መፈራረስም ሆነ ለኢኮኖሚ ድቀታቸው ዋናው ምክኒያት የመንግስታቱ ፀረ ዴሞክራሲና አምባገነናዊ ተፈጥሮ ነው፡፡
የሶቭዮት ህብረት ፌዴሬሽን መክሸፍ ከታሪካዊው ሐቅ ስንነሳ የሚያስደንቅ አይደለም፡፡ ምክንያቱም በአለማችን እስከወዲያኛው የዘለቀ ኢምፓየር የለም፡፡ የሶቭዮት ህብረት የፌዴሬሽን ገፅታ የኢምፔየር ገፅታ እንጂ አንድ ህብረብሄር አገርን በፌዴሬሽን የማዋቀር መነሻ ያደረገ አይደለም፡፡ የምዕራብ ኢምፐሪያሊዝም ሊበላህ ነው በሚል የተመሰረተ ሌላው የኢምፔሪያሊዝም ገፅታ ነበር፡፡ ኢምፓየር ደግሞ በባህሪው የፍፁማዊ ቁጥጥር ርዕዮት ነው፡፡ እርግጥ ነው ይህ በኮሙኒዝም ካምፕ በሚጠቃለል ርእዮት የተገነባ ኢምፓየር ፌዴሬሽን በአካባቢው የነበሩ ነባር ማንነትን መሰረት ያደረጉ ግጭቶችና ውጥረቶች ለመቆጣጠርና ለማዳከም ጠቅሟል፡፡ በመሆኑም ከዚህ አንፃር እ.ኤ.አ በ1991 የታላቅዋ ሶቭዮት ህብረት መፈራረስ ለረጂም አስርት አመታት እምቅ ብሄራዊና ክልላዊ ግጭትን ለመቆጣጠር አስችሎ የነበረው እድል እንዲመክን አድርጓል፡፡ በሰበቡም በዞኑ በርካታ ሀገራዊ ግንባታ ግጭቶች እንደ ቼቺኒያ ያሉት ደግሞ ለይቶላቸው በፅንፈኝነት እልቂትን ያስተናገዱ ሆኑ፡፡ የመጀመሪያ ነገር የሶቭዮት ኢምፓየር መፈራረስ ከፊተኞቹ /የእንግሊዝ የኦቶማን ወዘተ/ኢምፓየር ከእነ እንግሊዝ ሲነፃፀር እጅግ ፈጣንና ብዙዎቹ ባልጠበቁትና ባልተዘጋጁበት የሆነ መሆኑ ነው፡፡ እውነታው የምስራቅ ዓለሙ ፌዴሬሽን ካበቃለት የቆየ ቢሆንም እንደ ፀጉራም ውሻ ያለ እየመሰለ መሞቱ ነበር፡፡ በመሆኑም ፌዴሬሽኑ እንዳይፈርስ ራሱን ለመከላከል ቀርቶ የተከሰተውን አይነት ዞናዊ ቀውስ ለመቆጣጠርም ለማለዘብም አልተቻለውም፡፡
እናም የቀዝቃዛው ጦርነት ማብቃትን ተከትሎ በፌደራሊዝም ሁለት ተቃራኒ ክስተቶች ተፈጥረዋል፡፡ በአንድ በኩል ቀደም ሲል እንዳየነው የነበሩ ፌደራል ሀገራት ተበታትነዋል፡፡ ዩጎዝላቭያና ሶቭዮት ህብረት እንዳልነበሩ ሆነዋል፡፡ መበታተናቸው ብቻ ሳይሆን ፍችያቸውም ለሽማግሌ ያስቸገረ እጅግ ጭቅጭቅ ንትርክና ቀውስ የበዛበት ነበር፡፡ ይህ ደግሞ አሀዳዊ ስርአትን ቀልብሳ በፌደራሊዝም ራሷን ለማዋቀር ለተዘጋጀች ኢትዮጵያ ፈታኝ ግሎባል ነባራዊ ሁኔታ ነበር፡፡
ለኢትዮጵያ ፌደራሊዝም ግንባታ ግን አሉታዊ ጫና ያሳረፈው የነባር ፌዴሬሽኖች መፈራረስ ብቻ አልነበረም”” በካናዳም የኵዩቤክ (Quebec) የእንገንጠል ጥያቄ ጎላ ብሎ ወጥቶ ለተደጋጋሚ ህዝበ ውሳኔ ቀርቧል፡፡ በ1995 በተካሄደው ሪፈረንደም መገንጠል እንፈልጋለን ያሉ ኩዩቤከውያን ቁጥር 49 ነጥብ 42 ሲሆኑ የካናዳ አካል ሆነን እንቀጥላለን ያሉት ደግሞ 50 ነጥብ 58 በመቶ መሆናቸው ለብዙዎች አስደንጋጭ ነበር”” የካናዳን ያልተሸራረፈ አንድነት ለሚፈልጉ ብቻ ሳይሆን እንደ እንግሊዝ ላሉ አውሮፓ ሃገራትም አስደንጋጭ ሆነ፡፡ ይህ የነባር ፌደራል ሀገራት መበታተን እና የአዲስ እንገነጠላለን የሚሉ ወገኖች በወቅቱ መከሰት በኢትዮጵያ ፌደራሊዝም አቀንቃኞች ላይ ከባድ ጫና ነበረው፡፡ በአንፃሩ የፌደራል አደረጃጀቱን ለሚቃወሙ ጠንካራና ተጨባጭ መከራከሪያ ሆኖ አገልግሏል”” ይህንን የፌደራል አወቃቀር ወይም የህብረብሄር ፌደራሊዝም የሚቃወሙ እንደ መኢሶን፣ ኢህአፓ፣ ኢዲዩ፣ የሃይለስላሴ አልጋወራሾች፣ ኢፒዲኤም ያሉ ስደተኛ ድርጅቶች በመጨረሻ ሰአት ወደ አንድ መሰባሰብና ከደርግ ጋር ግንባር መፍጠር በርካታ የሀገሪቱ ብሄር ብሄረሰቦችና ታጋይ ድርጅቶች ሳይቃጠል በቅጠል እንዲሉ ከማእከላዊ መንግስት ከወዲሁ ለማምለጥ አቆበቆቡ፡፡ እናም የኢትዮጵያ እጣ ፈንታ ከሶማሊያ፣ ከላይበሪያና ዩጎዝላቭያ የተለየ እንደማይሆን በብዙዎች ዘንድ ጨለምተኝነት ነገሰ፡፡ እንግዲህ ይህንን ጨለምተኝነት አልፎ ኢትዮጵያን እንደሃገር የተረጋጋችና አንድነቷን የጠበቀች እንድትሆን ከየትኛውም ፖለቲካ ሃይል በላይ በድርጅታችን ኢህአዴግ ጫንቃ ላይ ያረፈ ነበር፡፡ (በቀጣይ እትም ኢህአዴግ አደጋውን ለማስወገድና ዛሬ እያየናት ያለችውን ፌደራላዊት ዴሞክራሲያዊት ሀገር እውን እንድትሆን የወሰዳቸውን ፖለቲካዊ አቋሞች እንመለከታለን፡፡ በ25ኛ አመት የግንቦት 20 የድል በዓል ዋዜማ ላይ አይደል ያለነው፡፡ ቸር ሰንብቱ፡፡)