Saturday, 28 March 2015

በኢህአዴግ አመራር የማሽቆልቆል ጉዞዋ ተገትቶ ወደ ቀድሞ ስልጣኔዋ እየተመለሰች ያለች ሀገር!

እኛ ኢትዮጵያውያን በአንድ ወቅት የሚያኮራ ታሪክ ባለቤት የሆነውን ያህልያለ ፉት ስርዓቶች በተከተሉት የተሳሳተ ፖሊሲ ምክንያት በዓለም ላይ አንገታችንን ያስደፋ የኋላቀርነትና የተመፅዋችነት፣ የጦርነትና የብጥብጥ፣ የጭቆናና የፀረ ዴሞክራሲ ምድር ተብለን እስከመታወቅ ደርሰን ነበር። ሀገራችን በርካታ ልዩነቶች ባላቸው ብዙ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች የተዋቀረች ሕብረ ብሔራዊ ሀገር ብትሆንም በየወቅቱ የነበሩት ስርዓቶች ይህንኑ እውነታ በአግባቡ ለማስተዳደር የሚያስችል አቅጣጫ ባለመከተላቸው በዓለም ከምትታወቅበት የስልጣኔና የእድገት  ማማ ወርዳ ወደ ማያቋርጥ የማሽቆልቆል ጉዞ በመግባቷ በዓለም ላይ የረሃብና ኋላቀርነት ምሳሌ ለመሆን መብቃታችን ሲያሳፍረን፣ ሲያስቆጨንና ሲያንገበግበን ቆይቷል።


የተከበራችሁ የሀገራችን ህዝቦች!
ሀገራችን ዓለም ካደነቀው ከፍተኛ የስልጣኔ ማማ ተነስታ የዓለም ህዝቦች ጭራ ያደረገን ታሪክ እንዲቀየር ሰላማዊ የመፍትሄ አማራጭ ያቀረቡ ኢትዮጵያውያን ባለፉት ስርዓቶች በግፍ ተገድለዋል፡፡ እኩልነትና ዴሞክራሲ ይስፈን ብለው የታገሉ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የህይወትና የአካል መስዋዕትነት ከፍለዋል። በየወቅቱ የነበሩ ገዥዎችም በየጊዜው ይነሱባቸው የነበሩ የህዝብ ጥያቄዎች ለማፈን ከፍተኛ ጥረት ቢያደርጉም የትኛው የህዝብ ጥያቄዎችንና ትግሎችን ለአፍታም ቢሆን ማስቆም አልቻሉም ነበር። በአምባገነኖች ይፈፀሙባቸው የነበሩ ግፍና መከራዎችን አሜን ብለው ሳይቀበሉ ለመብታቸው፣ ለእኩልነታቸውና ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸው የተፋለሙ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የአምባገነኖችን ግፍና በደል ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ አሽቀንጥረው ጥለው አዲስ ምዕራፍ እውን አድርገዋል። የዛሬ 23 ዓመት በኢህአዴግ ግንባር ቀደም መሪነት የተጀመረው ስኬታማ ጉዞ የኢትዮጵያ አሳፋሪ የታሪክ ምዕራፍ እንዲቀየር፣ የህዳሴ ጉዞአችንም እንዲጀመር አድርጓል።
የተከበራችሁ የሀገራችን ህዝቦች!
ከውጭ ወራሪ ነፃነቷ ተጠብቆ የኖረችው ሀገር ባለቤት የሆነው የኢትዮጵያ ህዝብ ሀገራዊ ነፃነቱን የማንነቱ አንዱና ዋነኛ መለያው አድርጎ ይመለከታል። የሀገራችን ህዝብ አፍሪካውያን ጥቁር ህዝቦች ከቅኝ ገዥዎች መዳፍ የሚወጡበትን መንገድና ወኔ ያመላከተ የነፃነት ተምሳሌትም ነው። አሁን ያለው ትውልድም ይህን የፅናት ፈለግ በማስቀጠል ዳግም የስልጣኔ ማማ ላይ የደረሰች ሀገር ለመፍጠር ደፋ ቀና ማለት ከጀመረ ውሎ አድሯል። የተጀመረው የህዳሴ ጉዞም እውን መሆን የሚችለው ከዚህ በፊት ለውድቀት የዳረጉንን ችግሮች ምንጭ አውቆ ስህተቱን አርሞ በተገቢው ሁኔታ መጓዝ ሲችል ብቻ እንደሆነ ኢህአዴግ በጥብቅ ያምናል። ይህን እምነቱንም ከሚመራበት ፕሮግራም ጋር አዋህዶ፣ ህዝቡን አሳምኖና አሳትፎ ወደ ተግባር በመቀየሩ ስኬታማ ውጤቶች ማስመዝገብ ችሏል።