Monday, 24 August 2015

የኢትዮጵያ ወጣቶችና የመሰረታዊ ለውጥ ትግላቸው part 1

ቅድመ 1983 ዓ.ም የነበረው የፖለቲካ ኢኮኖሚ ሁኔታ በጥቂቱ

ኢትዮጵያ ጥንታዊ አገር ናት፡፡ የአፅመ ቅሪቶችና የሌሎች ማጣቀሻዎች ሳይጨመሩ እስከ አሁን የተደረጉ ጥናቶችንና ስምምነት የተደረሰባቸውን ታሪካዊ ማጣቀሻዎች ብቻ ብንወስድ አገራችንና ህዝቦቿ ከ3 ሺህ ዓመት በላይ ታሪክ ያላቸው ናቸው፡፡ የአገራችን ህዝቦች ጥንታዊ ብቻ ሳይሆኑ ቀድመው ስልጣኔ ከጀመሩ ጥቂት የዓለም አገራት ህዝቦች ተርታ የምንመደብ እንደሆንንም ብዙ የውጭ አገር ምሁራን ሳይቀሩ ያረጋገጡት ጉዳይ ነው፡፡ በምስራቅ አፍሪካ ከእንጨት ቴክኖሎጂ ቀድሞ ከመጀመሩ ጋር ተያይዞ የእርሻ ቴክኖሎጂ በክልላችንም ሆነ በአገራችን ቀድሞ እንደተጀመረ ምርምሮች ያረጋግጣሉ፡፡ ቢያንስ ቢያንስ ጤፍንና ቡናን ለዓለም ገፀበረከት ማቅረባችን ለማንም የተሰወረ አይደለም፡፡ እንስሳትን በማላመድ ጥቅም ላይ ካዋሉ ህዝቦች ተርታም እንደምንመደብ የተረጋገጠ ነው፡፡ በጥቅሉ በግብርናው መስክ ቀድመው ከጀመሩት እንመደባለን፡፡
በግብርና ቴክኖሎጂ ብቻ ሳይወሰን በኪነ-ህንፃ ጥበብም ከግሪክ፣ ከአረቢያና ከአንዳንድ የህንድ አካባቢዎች የሚመጣጠን የዘመናዊ ህንፃ ጥበብን ቀድመን እንደጀመርን አሁን ድረስ ያሉ አሻራዎች ህያው ምስክሮች ናቸው፡፡ የአክሱም፣ የላሊበላ፣ የጎንደር ፣ የሐረር ጀጎል ግንብ፣ በደቡብ የጥያ ትክል ድንጋይ የመሳሰሉት ለዚህ ዋቢ ማሳያዎች ናቸው፡፡ ክልላችንም ሆነ አገራችን ከላይ በተጠቀሱት ሳይወሰኑ የኃይማኖት ብዝሃነትና የቋንቋ ብዝሃነት በሰፈነበት ነባራዊ ሁኔታም ገዥዎቹ እየቆሰቆሱ ከፈጠሩት ግጭት ባሻገር ህዝቦቿ በመግባባትና በመቻቻል ለፍትሀዊ ጥቅም በአብሮነት መኖር ዋና መገለጫቸው ነው፡፡ የራሳችን ፊደል ያለን ከመሆናችንም በላይ በጥበበ ቃላት ግንባታ መነሻ አቅም ነበረን፤ ይህ ደግሞ ለሳይንስና ቴክኖሎጅ እድገት የራሱ አቅም ሊኖረው የሚችል ነበር፡፡ በራሳችን ታሪክ፣ ቋንቋ፣ ባህል እና እሴት እንዲሁም ሥነ-ልቦና የምንኮራና የውጭ ጠላትን ተደጋጋሚ እና ተከታታይ የጥቃት ሙከራ ተባብሮ በመመከት ነፃነታችንን አስከብረን የመቆየት አኩሪ ታሪክ ያለን ሲሆን የአማራ ክልል ህዝቦችም ለዚሁ አገራዊ ኩራታችን መጠበቅ የበኩላቸውን አኩሪ ተግባር አከናውነዋል፡፡
በዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ረገድም አስፋፍተንና አዳብረን አገልግሎት ላይ አላዋልነውም እንጂ የኦሮሞ አባገዳ ስርዓት በየ8 ዓመቱ የስልጣን ሽግግር የሚያደርጉበት ሁኔታ ነበር፡፡ ይህን በምርጫ የሚገለፅ የዴሞከራሲ ገጽታ ያለው የስልጣን ሽግግር በጥናትና ምርምር በማዳበር ለላቀ ጥቅም አውለነው ቢሆን ኖሮ በዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታም ቀድመው ከጀመሩት ተርታ መመደብ እንችል ነበር፡፡ ሆኖም በአግባቡ ቀምረን ስራ ላይ ሳናውለው ቆይተናል፡፡
እነዚህ የስልጣኔ አሻራዎች ከ15ኛው ክፍለ ዘመን ወዲህ አንስቶ እየተሸረሸሩ በመምጣታቸው ድህነትና ኋላቀርነት፣ግጭትና ደም መፋሰስ፣ አለመግባባትና መናቆር እየተከማመሩ ሂደው የማታ ማታ ከ1950ዎቹ እስከ 1980ዎቹ መጀመሪያ እንደ አገር በጋራ የማንቀጥልበት ሁኔታ አንዣብቦ ነበር፡፡ ትልቅ ከነበርንበት ወደ
2
አልተቋረጠ የቁልቁለት ጉዞ ሲያንሸራትቱን የነበሩት ችግሮች ምንድን ናቸው? ብለን ስንመረምር ፊት ለፊት የሚታዩት የብሔሮችና፣ የብሔረሰቦችና የህዝቦች ብዝሃነትንና እኩልነትን የሚያከብር ሁኔታ አለመኖሩ፤ የሃይማኖት እኩልነት አለመከበር፤ የእድገትና ብልፅግና መሰረት የሆኑት መሬት፣ ጉልበት፣ እውቀት እና የካፒታል አቅም በጥቂቶች እጅ ገብቶ ብዙሃኑ የበይ ተመልካች መሆኑ በንድፈ ሃሳብም ሆነ በተግባር ተረጋግጦ ያደረ እውነት ሆነ፡፡
በእኛም አገር ሆነ በሌሎች አገሮች የተደረጉ ጥናቶችና ተግባራዊ ተሞክሮዎች ቀድመው ያደጉ አገሮች የሚያረጋግጡት የእድገታቸው ሚስጥር በህዝባቸው ዘንድ የተሳካ የህግ የበላይነት መረጋገጡ፣ የዜጎች ሀብት የማፍራትና የሀብትና የንብረት ባለቤትነት በአስተማማኝ ሁኔታ መከበሩ፣ የገዥዎች /በስልጣን ላይ ያሉ ስርዓቶች/ ስልጣን የተገደበ መሆን፣ ምንም እንኳ በየአገሩ የነበሩ ኋላቀርና ፀረ-ዴሞክራሲ አገዛዞች ህዝብን ከመበዝበዝና ከመጫን ወደ ኋላ ያሉበት ጊዜ ባይኖርም ቀድመው መለወጥ የቻሉ አገሮች መነሻ ምክንያቱ ስርዓቱ በህግ በተደነገገ የስልጣን ክፍፍል ውስጥ ህዝብ ላይ የሚያሳድረው ጫና በተወሰነ ደረጃም ቢሆን በህግ የተገደበ መሆኑ፣ ዜጎች አንፃራዊ ነፃነት አግኝተው የግላቸውን፣ የቤተሰቦቻቸውንና የጋራ ልማታቸውን እንዲያፋጥኑና በዚህ ሂደት አማካኝነት የአካባቢና የአገር እድገትም እንዲፋጠን አግዟል፡፡
በእኛ አገር ለዘመናት የቆዩ ስርዓቶች ስልጣናቸው በአግባቡ የተገደበና በታወቀ የህግ አግባብም የሚመሩ አልነበሩም፡፡ እስከ 1970ዎቹ መጨረሻ የነበሩ ስርዓቶች አርሶ አደሮች ያለምንም እገዛ በራሳቸው ጥረት ያመረቱትን ምርት ለገዥዎቹ ይሰፍራሉ፤ የገዛ በሬዎቻቸውንና የእርሻ መሳሪያዎቻቸውን ይዘው ለገዢዎች ያገለግላሉ፤ ደክመውና ጥረው ግረው ያመረቱትን የስርዓቱ ባለስልጣናትን ወታደሮች ይቀሟቸዋል፡፡ በአሰኘው ጊዜ የፈለገውን አይነት መዋጮ ይሰበስባል፡፡
በ1848 ዓ/ም ሰሜን ኢትዮጵያን ለመጎብኘት የመጣና የነበረውን በፍዳና በስቃይ የተሞላውን የአርሶ አደሩን ህይወት በአንክሮ ተመልክቶ የታዘበውን ዋልተር ፕላውደን የተባለ እንግሊዛዊን ጠቅሶ እንደዘገበው «…አርሶ አደሮች ከምርታቸው… ለሹም ይሰፍራሉ፡፡… የገዛ በሬዎቻቸውን ጠምደው የንጉሱንና የአገር ገዥውን መሬት ያርሳሉ። …አባወራው በራሱ ኪሳራ የተወሰኑ ቁጥሮች ያሏቸውን ወታደሮች ይቀልባል። አገር ገዥው በሬ፣ በግ፣ ፍየል፣ ቅቤ፣ ማርና ሌሎች የሚያስፈልጉትን ነገሮች የመውሰድ መብት አለው። ገዥው ከሚገዛቸው አርሶ አደሮች …ባሻው ጊዜ ከእያንዳንዱ አርሶ አደር መዋጮ ይቀበላል።» (የባህልና ቱሪዝም ቢሮ ... ፤17)
በአማራ ክልልም ሆነ በአገራችን የነበሩ ስርዓቶች የህዝብን ሠላምንና ደህንነትን ጠብቀው በተረጋጋ መልኩ ወደ ልማትና እድገት እንዲረማመዱ የሚያግዙ ሳይሆኑ የላቀ ስልጣን ጨብጠው የአብዛኛዎቹን ህዝቦች ሀብትና ንብረት ለመምጠጥ ሲሉ በሚቆሰቁሱት ጦርነት ህዝቦች ለደህንነታቸው ዋስትና ሳይኖራቸው የኖሩ ናቸው፡፡ ከግብርና ተነስተው ወደ ካፒታል እድገት ለማምራት፣ ከዝቅተኛ እስከ ከፍተኛ የንግድ እንቅስቃሴ መስፋፋት ነበረበት፡፡ ህግና ስርዓት በአስተማማኝ ሁኔታ ባልሰፈነበት፣ ለንግድ እንቅስቃሴ የተመቸ የሰውና የሸቀጥ ዝውውር ማድረግ የሚያስችል ሠላማዊ ሁኔታ ባልሰፈነበት ይህን ማከናወን የሚቻል አልነበረም፡፡ በመሆኑም ያደጉ አገሮች ለእድገታቸው ያገዛቸው እነዚህንጉዳዮች ደረጃ በደረጃ እያሻሻሉ መሄዳቸው ነው፡፡ ከላይ የተጠቀሱት ሁኔታዎች የተመቻቹላቸው ሲሆን በእኛ አገር ደግሞ በተቃራኒው የተመቸ የሠላም፣ የፍትህና የልማት ሁኔታ አልነበረም፡፡
የተጠቀሰው ሁኔታ ዝቅተኛ ምርታማነት ፀንቶ እንዲቆይ ያስገደደ ከመሆኑም በላይ በየወቅቱ እየተፈራረቁ የሚከሰቱ የድርቅ አደጋዎች አርሶ አደሩ ከገዥዎች ምዝበራ ያተረፈውን አንጡራ ሀብት እያደቀቁ ህዝቦቿን ለስቃይና ለሞት ሲዳርጉ ኖረዋል፡፡ የሩቁን ትተን እንኳ ከ1880 እስከ 1980 ለመቶ ዓመት የዘለቀውና ወቅት እየጠበቀ የሚከሰተው ተከታታይ ድርቅና እሱን ተከትሎ የሚስተዋለው ረሃብ በሰውና በእንስሳት ላይ እልቂት የፈጠረበት ሁኔታ እንዳለ ከፊሉን በአይናችን ተመልክተነዋል፡፡ ከላይ የተጠቀሱት ችግሮች ተደምረው በህዝባችን ውስጥ አልችልም ባይነት፣ ተስፋ መቁረጥ፣ ተረጅነትና ጠባቂነት ቀላል ባልሆነ ደረጃ ተንሰራፍተው የቆዩበት ሁኔታ ተስተውሎ ቆይቷል፡፡
በአንድ ወቅት ትልቅ የነበርን ቢሆንም ከላይ ዘርዝረን በጠቀስነው ሁኔታ ከትልቅነት ማማ ቁልቁል ተንሸራተን እንደ ህዝብና እንደ አገር በጋራ ያለመኖር አደጋ አናዣቦብን ነበር፡፡ ሆኖም ይህን አስከፊ ሁኔታ ህዝቦች በተናጠልና በጋራ በመሰላቸው አግባብ ታገሉት እንጂ ዝም ብለው አልተመለከቱም፤ አልተቀበሉትም፡፡ በዚሁ ፀረ-ጭቆናና ብዝበዛ ትግል ውስጥ የትላንት ወጣቶች ትግል ግንባር ቀደምና በትውልድ አኩሪ ንቅናቄ ነበር፡፡
1.1.2 የአገራችን ህዝቦች በተለይም የወጣቶች ተጋድሎ
በአገራችን ለዘመናት እየተፈራረቁ የዘለቁ ስርዓቶች ለህዝብ ሠላም፣ ዴሞክራሲ እና በየደረጃው ተጠቃሚ የሚሆንበትን ስርዓት ለመገንባት ተፈጥሯዊ ሁኔታቸው የማይፈቅድና በመጣጭነት ህዝብን ሲያሰቃዩ የኖሩ በመሆናቸው ህዝቦቹ ከመታገል የቦዘኑበት ሁኔታ እንዳልነበረ ታሪክ ያረጋግጥልናል፡፡ የህዝቦቹ ትግል ያልተደራጀና የተበታተነ ስለነበር በወቅቱ የተደራጀው ፀረ-ዴሞክራሲ ኃይል በቀላሉ ተቆጣጥሮት ዘልቋል፡፡ የሩቁን ትተን ከ1930ዎቹ ጀምሮ እስከ 1980ዎቹ መጀመሪያ ድረስ ጉልህ የሆነ የተደራጀና የተናጠል የህዝቦች ተጋድሎ ተካሂዷል፡፡ በዚህ ውስጥ የወጣቶች ሚና ጉልህ ነበር፡፡
የህዝቡ ተጋድሎ በአጠቃላይ በተለይም ደግሞ የወጣቶች ግንባር ቀደም ንቅናቄ የኢትዮጵያን ንጉሳዊ አገዛዝ ስልጣንን ቀይረው የሚፈልጉትን ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ ስርዓት በወቅቱ መገንባት ባይችሉም ከኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ጋር የተቃኘ የአንገዛም ባይነት ትግል አካሂደዋል። በአማራ ክልል ሁኔታም በ1930ቹ የተካሄደው የጎጃም ገበሬዎች አመጽ፣ በተለያዩ አካባቢዎች የተካሄዱ የአርሶ አደሮችና የየአካባቢው ፊውዳሎች ፍጥጫና የ1964/5 የወሎ ረሃብን ተከትሎ የተቀሰቀሰው ህዝባዊ አመጽ ወዘተ… የሚጠቀሱ ናቸው።
የአማራ ክልል ህዝቦችን ጨምሮ የኢትዮጵያ ህዝቦች ፀረ-ብዝበዛና ፀረ-ጭቆና ተጋድሎ ትምህርት ቀመስ በሆነው ኃይል ድጋፍ ማግኘት የጀመረው ከ1950ቹ ወዲህ ነው። በአቤ ጎበኛ እንደተጻፈ ጠቅሶ የባህልና ቱሪዝም ቢሮ ባሳተመው የአማራ የባህልና ኪነ-ጥበብ መጽሐፍ እንደተጠቀሰው፣
«ተረግጦ ተገፍቶ፤
አልቅሶ ተጠቅቶ፣
ተርቦ ተጠምቶ።
በድንቁርናና በህመም በስቃይ በረሀብ በችግር፣
እየተንገላቱ ዘላለም ከመኖር፣
ከእኩልነትና ከነጻነት ጋር ይሻላል መቃብር።
እንኳን ከውርደት ጋር እንኳን ከችግር ጋር ከደዌ፣ ከጥቃት፣
ከክብርም ጋር ቢሆን ከብዙ ጌትነት፣
ኑሮ ጣዕም የለውም ከሌለው ነጻነት።»
(ባህልና ቱሪዝም ቢሮ; 2001፤ 169)
በዚህ መልክ እየተቀነቀኑ የየህብረተሰብ ክፍሉን የሚያነሳሱ ጽሑፎችና አስተያየቶች መውጣት ጀመሩ። በ1960ቹ ህዝባዊ ትግሉን የተማሪዎች ንቅናቄ የበለጠ ወደ ላቀ ደረጃ አሳደገው። ነባራዊው የህዝቦች መደባዊና ብሔራዊ ጭቆና በድፍረት የተገለጠው ከአማራ ህዝቦች አብራክ በወጣውና የተማሪዎች ንቅናቄ አባልና ግንባር ቀደም መሪ በነበረው የያኔው ዘመን ወጣት ዋለልኝ መኮንን ሲሆን በወቅቱ የሚከተለውን ጽፏል።

No comments:

Post a Comment