Saturday, 29 August 2015

የኢትዮጵያ ህዳሴና GTP II ከብሩክ ከድር (part 1)




የኢትዮጵያ ሚሊኒየም (2000 ዓ.ም) ዋዜማ አዲሱን ሺህ ዓመት ስንቀበል በሚሊኒየም አደራሽ በተደረገ መርሃ ግብር ላይ ታላቁ መሪያችን መለስ ዜናዊ ‹‹መጪው ዘመን የኢትዮጵያ ህዳሴ ይሆናል!!›› ማለታቸው ይታወሳል፡፡ ያሳለፍነው ሚሊኒየም ሀገራችን በአንድ ወቅት ከዓለም ታላላቅ ስልጣኔዎች መካከል የነበረችበትና በሂደትም ፀጋዋን በአግባቡ መጠቀም ባለመቻሏና ብዝኃነቷን በብቃት መምራት የሚያስችል ሁኔታ ባለመፈጠሩ ቀደሞ የነበራት ዝናና ገናናነት በሂደት በማሽቆልቆል የተተካበት ሁኔታም ተፈጥሯል፡፡ በማያቋርጥ የኋሊዮሽ ጉዞ ያለፈችበት ወቅትም ነበር፡፡
ታላቁ መሪያችን መለስ ዜናዊ በሚሊኒየም አደራሽ ባደረጉት ንግግር ‹‹ላለፍንበት ሁኔታ ተጠያቂዎቹ እኛና እኛው ብቻ ነን፡፡›› በሚል ያስቀመጡት ሀሳብ የሚያመለክተን የተሻለች ሀገርን ለቀጣዩ ትውልድ ማስረከብ እስካልቻልን ድረስ የትውልድ ተጠያቂነትም የማይቀር እውነታ መሆኑን ነው፡፡ ሀገራችን ወደ ቀድሞ ገናናነት ዘመኗ ዳግም የመመለስ ጉዞ የህዳሴ (renaissance) እቅዳችን መነሻም ከዚህ እልህና ቁጭት የሚነሳ ነው፡፡     
የኢትዮጵያ ህዳሴ የሚለው ፅንሰ ሀሳብ በተግባርም ሆነ በንድፈ ሀሳብ ደረጃ በሀገር ውስጥም ይሁን በውጪው ማህበረሰብ ዘንድ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተለመደ የመጣ ጉዳይ ሆኗል፡፡ ይህ ጽንሰ ሀሳብ ለኢትዮጵያዊያን ያለው ትርጉም ላቅ ያለና ነገን በዛሬ የመስራት ያህል ነው፡፡ በአንድ ወቅት በድቅድቅ ጨለማ ውስጥ ለነበረችና ዜጎቿ በድህነትና በከፋ ረሃብ ሲማቅቁ የነበሩባትን ሀገር ወደ ከፍታ ዘመን የሚመልስ ታላቅ ሀገራዊ ፍኖተ ካርታ (roadmap) ነው፡፡ የኢትዮጵያ ህዳሴ ማለት በዓለም አደባባይ ተሰሚነታችን ጎልቶ የሚወጣበትን ታሪክ በጋራ ጥረታችን የምንገነባባት ቁልፍ የርብርብ ማዕከል ነው፡፡ይህም በመሆኑ በዛሬውና በነገው ትውልድ መካከል ለሀገራዊ ቅብብል ድልድይ ሆኖ የሚያገለግል የርብርብ አጀንዳችንም ጭምር ተደርጎ ይወሰዳል፡፡   
የኢትዮጵያ ህዳሴ መሰረት የተጣለው መቼ ነው?
የሀገራችን ህዳሴ መሰረት የተጣለው መቼ ነው ካልን ለሁለት ወቅቶች ከፍተኛ ትርጉም መስጠት ያስፈልጋል፡፡ ቀዳሚው ወቅት አፋኙ የደርግ ስርዓት በህዝባዊ ትግል የተገረሰሰበት ወቅት ነው፡፡ የድህነት ዘበኛ፣ የብዝሃነት ጠላት፣ የትምክህተኝነት ወኪልና የግዛት አንድነት አቀንቃኝ የነበረው ደርግ በከፋና እልህ አስጨራሽ ትግል መወገዱ ለሀገራችን ህዳሴ ቀዳሚው መሰረት ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡ ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ የህዳሴያችን መሰረት ይበልጥ የተጣለውና በአስተማማኝ መልኩ ነጥሮ የወጣው የዛሬ አስራ አራት ዓመት የተሃዳሶው መስመር ጠርቶ በወጣበት ወቅት ነው፡፡ ምንም እንኳ በህዝባዊ የትጥቅ ትግል ደርግ ከተወገደ በኋላ ሀገራችን ፊቷን ወደ ሰላምና መረጋገት፣ ልማትና ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ አዙራ የነበረ ቢሆንም የመድረኩን ባህሪ በትክክል ተረድቶ የጠራ አሰላለፍ ያለው ትግል በማድረግ በኩል ግን የውስጠ ድርጅት አደጋዎች አጋጥመው እንደነበር ይታወሳል፡፡ በወቅቱ ያጋጠመውን ውስጣዊ የመበስበስ አደጋ በከፍተኛ ብስለት ያለምንም ደም መፋሰስ በሀሳብ ትግል አሸናፊነት በመጠናቀቁ በወሳኝ መልኩ የሀገራችን ህዳሴ መሰረት እንዲጣል አድርጓል፡፡  
 የሀገራችን ቁልፍ ጠላት ከድህነት በላይ ሊሆን እንደማይችል፣ ትግላችን በኪራይ ሰብሳቢነትና በልማታዊነት መካከል እንደሆነ፣ ሀገራችንን ከከፋ ድህነትና ኋላ ቀርነት አውጥተን ወደ ብልፅግና ዘመን ለማምራት ብሔራዊ መግባባትን በመፍጠር በተደራጀ የህዝብ ተሳትፎ መንቀሳቀስ እንደሚገባን ያስቀመጥበት ወቅት ነበር፡፡ ባለፉት የተሃዳሶው ዘመናት በወቅቱ የተጠቀመጡት የመታገያ አጀንዳዎች ተለቅመው መተግባር ጀምረዋል፣ ፍሬያቸውም በመታየት ላይ ነው፡፡ ዛሬ ላይ ሆነን ያለፉት የተሃድሶው ዓመታት ስናይ ሀገራችንን ከድህነት አረንቋ ለማውጣት የሞት የሽረት ጉዳይ ማድረግ እስካልቻልን ድረስ ሀገራዊ ህልውናችን ጭምር አደጋ ላይ እንደሚወድቅ የተቀመጠው አቅጣጫ ትክክለኛና ወደፊት የምናደርገውን ግስጋሴ  ያፈጠነ እንደነበር መውሰድ ይቻላል፡፡        

የኢትዮጵያ ህዳሴ ማረጋገጫዎች 
ሀገራችን ህዳሴዋን እያረጋገጠች ስለመሆኑ በርካታ ማሳያዎች ማቅረብ ይቻላል፡፡ ከብዙ ማሳያዎች ውስጥ ግን ከፍተኛ ትርጉም ያላቸውን የተወሰኑ ጉዳዮች በማንሳት የኢትዮጵያ ህዳሴ በየመስኩ እየተረጋገጠ ስለመሆኑ ማሳየት ይቻላል፡፡ ቀዳሚው የህዳሴያችን ማረጋገጫ በወሳኝ ሀገራዊ ጉዳዮች እየተፈጠረ ያለው ብሔራዊ መግባባት ነው፡፡ ከወርቃማው ታሪካችን እንደምንገነዘበው የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በጋራ ጉዳይ ቆመው በአንድነት ጠላትነት ፋሽስት ጣሊያንን የመከቱበት የአድዋ ድልን ያህል አሁንም በድህነት ላይ በጋራ ለመዝመት የተነሳሳንበት ወቅት ተፈጥሯል፡፡ ብሔራዊ መግባባት በጥቃቅን ጉዳዮች ላይ ጭምር በጋራ መቆምን የግድ የሚል ፍልስፍና ሳይሆን በወሳኝ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ባጋራ መቆምን የሚጠይቅ አስተሳሰብ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ከታየ በህገ መንግስታችን፣ በጋራ ጠላቶቻችን ዙሪያ እየፈጠርነው ያለ መግባባት ህዳሴያችንን እውን ከማድረግ አኳያ የራሳቸው ከፍተኛ ፋይዳ አላቸው፡፡
ምንም እንኳ አሁንም በከፋ ድህነት ውስጥ የሚቃቀው ህዝባችን ቁጥር ቀላል የሚባል ባይሆንም ባለፉት ሁለት አስር ተከታታይ ዓመታት ሀገራችን ሚሊዮኖችን ከአስከፊ ድህነት ውስጥ ማውጣት ችላለች፡፡ በምግብ እህል ራሳችንን እስከመቻል ደርሰናል፡፡ ትልልቅ ሀገራዊ ፕሮጀክቶችን በራሳችን ወጪ መገንባት የሚያስችል ሀገራዊ አቅምም ፈጥረናል፡፡ ገፅታችን በውስጥ እየተገነባ ሲመጣ በውጭ ግንኙነት ረገድ ተሰሚነታችን እየጨመረ መጥቷል፡፡ ከምስራቅ ኢስያ ሀገራት ልምድ ተነስተን ስናይ በተለያዩ ምክንያቶች የተሰደደው ዲያስፖራ ወደ ሀገሩ ተመልሶ የለውጥ አካል መሆን መቻሉም አንዱ የህዳሴያችን ምልክት ተደርጎ ይወሳዳል፡፡ 
እነዚህና የመሳሰሉት ማሳያዎችን ስንመለከት የሀገራችን የህዳሴ ጉዞ ተጨባጭ በሆነ መልኩ እየታየ፣ እየጎመራ፣ ወይም በተስፋ ሰጪ ምህዋር ውስጥ የሚገኝ መሆኑን ነው፡፡    

No comments:

Post a Comment