Monday, 24 August 2015

የኢትዮጵያ ወጣቶችና የመሰረታዊ ለውጥ ትግላቸው part 2

በማስከተልም ዋለልኝ ህዝባዊ መንግስት ይመስረት ብሎ ሞገተ። ምን ዓይነት ህዝባዊ መንግስት? በሚለውም ላይ «እውነተኛ ህዝባዊ መንግስት፤ ሁሉም ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች እኩል የሚሳተፉበትና ህዝቦቹ የየራሳቸውን ቋንቋ፣ ባህል፣ ታሪክ የሚጠብቁበትና የሚያሳድጉበት መንግስት ይመስረት» (ዋለልኝ; 1961፤3፡) በማለት ታግሎ መስዋዕት ሆኗል።ዋለልኝን እንደ አብነት ጠቀስን እንጂ በሺዎች የሚቆጠሩ ፊደል ቀመስ የለውጥ ንቅናቄው ግንባር ቀደም ወጣቶች በርካታ ነበሩ፡፡
በ1960ዎቹ የነበረው የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ንቅናቄና በየአካባቢው አርሶ አደሩ ያቀጣጠለው ፀረ-ፊውዳል ንቅናቄ በ1966 የንጉሱን ስልጣን ገረሰሰ፡፡ የህዝቡ ንቅናቄ የፊውዳሉን ስርዓት ቢያስወግድም የአቢዮቱ አንቀሳቃሾች በአግባቡ የተደራጁ ስላልነበሩ በወቅቱ የተደራጀ አቅም የነበረው ወታደራዊ ስርዓት ተቆጣጥሮ የህዝቡን ንቅናቄ ለመጨፍለቅ ሲል ያለምንም ደም ኢትዮጵያ ትቅደም!! ከሚለው አንስቶ ተከታታይ አፋኝ መፈክሮችን ቀርፆ በአስርሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን በቀይ ሽብር ዘመቻ ጨፈጨፈ፡፡ ሠላማዊ ትግል ለውጥ እንደማያመጣ የተገነዘቡት የለውጥ ኃይሎች በብሄራዊም ሆነ በህብረ-ብሔራዊ መልክ ትግላቸውን አቀጣጠሉ፡፡በትግል መስመር ጥራትና በአፈፃፀም ቁርጠኝነት ስርዓቱን ተቃውመው የተንቀሳቀሱ ሁሉ ለፀረ-ደርግ ትግሉ እኩል አስተዋጽኦ ነበራቸው ለማለት ያስቸግራል፡፡ ሆኖም ከተቃውሞ ጀምሮ እስከ ለየለየት የጦር ሜዳ ውጊያ በማምራት 17 ዓመትን በወሰደ ከባድ መስዋዕትነት ለዘመናት በህዝቦች ጫንቃ ላይ ተንጠላጥሎ የኖረው የፊውዳልና ቅሪት ፊውዳል እንዲሁም አምባገነኑ የደርግ ስርዓት እስከ አፈና መዋቅሩ ፈራረሰ፡፡ በዚህም የኢትዮጵያ ህዝቦች መሰረታዊ የልማት፣ የዴሞክራሲና ዘላቂነት ያለው ሠላምን ለማረጋገጥ የተደረገው ስር ነቀል አብዮታዊ ፍልሚያ የመጀመሪያው ምዕራፍ በህዝቦች ንቁ ተሳትፎ በድል ተጠናቀቀ፡፡ የዚህ የጦር ሜዳ ፍልሚያና ክቡር መስዋዕትነት እንዲሁም ድል ግንባር ቀደም ተዋናኝ የያኔ ዘመን ወጣቶች የዛሬ አንጋፋዎች ድርሻ ከፍተኛ ነበር፡፡
ግንቦት 20/ 1983 ዓ.ም የተገኘው ህዝባዊ ድል የዘመናት የህዝቦች ተጋድሎ ድል የተቀናጀበት የአብዮቱ የመጀመሪያ ምዕራፍ እንጂ የመጨረሻ አልነበረም፡፡ የህዝቦች ትግል ወደ ኋላ ሳይል አስተማማኝ መሰረት የሚይዘው ህዝቦች አንግበዋቸው ለተነሷቸው የሠላም፣ የዴሞክራሲና የልማት ጥያቄዎች ህጋዊ ዋስትና የሚሰጥ ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ ህገ-መንግስት በህዝቦች ተሳትፎ መረቀቅና መጽደቅ ነበረበት፡፡ ይህ የመሰረታዊ ለውጥ ንቅናቄው ሁለተኛው ቁልፍ ምዕራፍ ነበር፡፡ ህዝባዊና ቀጣይነት ያለው ህገ-መንግስት አርቅቆና በህዝብ የነቃ ተሳትፎ በማጽደቅ ወደ ዘላቂ ሠላም፣ ልማትና ዴሞክራሲ ጉዞ ለማምራት ሁሉም ያገባናል ባዮች በሂደቱ፣ ከመነሻ እስከ መዳረሻው ሊሳተፉ ይገባ ነበር፡፡ በመሆኑም በኢህአዴግ የሚመራው ጊዜያዊ መንግስት የነበረውን ስርዓት “አስወግጃለሁ፤ ስልጣን ይገባኛል” ሳይል አንድ ወር ባልሞላ ጊዜ አሉ የሚባሉ ተቃዋሚ ፓርቲዎች እና ተሰሚነት ያላቸው ግለሰቦች ጭምር የተሳተፉበት የሽግግር መንግስት ተመሰረተ:: በዚህ ጊዜ ውስጥ ለዘመናት ተንሰራፍቶ የቆየውን ህገ-ወጥነት በማጽዳት፣ ለሠላምና መረጋጋት እንዲሁም ለህዝብ ነፃና የተመቸ እንቅስቃሴ እንቅፋት የነበሩ ህገ ወጦችና ሽፍቶች ህዝቡን ባሳተፈ መልኩ በህግ ስር እንዲውሉ ህዝቡ በሠላማዊ መልኩ በነፃነት እንዲንቀሳቀስ ሰፊ ስራ ተከናወነ፡፡ በሽግግር መንግስቱ አማካኝነት የህገ-መንግስት አርቃቂ ኮሚሽን ተዋቀረ፡፡ ኮሚሽኑ ባዘጋጀው መነሻ ሃሳብ ላይ ከ16 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ህዝቦች በረቂቅ ሰነዱ ተወያይተው ማስተካከያና ማሻሻያ ሃሳብ ካቀረቡ በኋላ ወኪሎቹ የበለጠ ተወያይተው እንዲያፀድቁለት፣ በዴሞክራሲያዊ ምርጫ ወኪሎችን መርጦ በተወካዮች አማካኝነት ቀናትን በወሰደ ውይይት ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ ህገ-መንግስት ህዳር 1987 ፀደቀ፡፡ ከላይ የተጠቀሱት ስኬታማ ተግባራት የተከናወኑ በዛን ዘመን የነበሩ ወጣቶችና የአሁን ዘመን ጎልማሶች ግንባር ቀደም ተዋናኝነት ነበር፡፡
ህገ-መንግስቱ ከሠላም አኳያ በአገራችን አስተማማኝና ዘላቂ ሠላም የሚረጋገጥባቸው አንቀፆች አስቀምጧል፡፡ የህዝቦች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብት እንዲከበር፣ የዘመናት የግጭት አንድ ምክንያት ሆኖ የቆየው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች የራስን እድል በራስ የመወሰን መብት እስከመገንጠል እውቅና ሰጠ፡፡ በመሆኑም ከብዙዎቹ የዴሞክራሲ ስርዓትን ከሚያራምዱ አገሮች በተለየና በአደገ መልኩ የግለሰብና የቡድን መብቶቻችንን አጣምሮ የሚያከብር የዴሞክራሲ አይነትን የሚፈቅድ ህገ-መንግስት ባለቤት ሆንን፡፡ በብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የሚገለፀው የቡድን መብት ብቻ ሳይሆን የሃይማኖትና የፆታ እኩልነቶችም ሕገ-መንግስታዊ ዋስትና አግተዋቷል፡፡ ከኢኮኖሚ ልማት አኳያ የዜጎች አንጡራ ሀብት ጉልበት ማንም ሌላ ኃይል በማያዝበት ሁኔታ የዜጎች አንጡራ ሀብት ማለትም ሆነ፡፡ መሬት የጋራ የተፈጥሮ ፀጋ በመሆኑ በመንግስትና በህዝብ እጅ ሆኖ ዜጎች አልምተው ሊጠቀሙበት
6
ተደነገገ፡፡ ይህም የኢኮኖሚና የፖለቲካ ፍትሃዊነትን ያሰፈነ ውሳኔ ነው፡፡ በነዚህ ስኬታማ ተግባራት የያኔ ዘመን ታጋይ ወጣቶች ህዝባቸውን በማንቃትና በማደራጀት የመሪነት ድርሻቸውን ተወጥተዋል፡፡
በማህበራዊ ለልማት መስክ የፆታና የአካባቢ እንዲሁም የብሔር ልዩነቶች ሌሎች አድሎ የሚፈጥሩ ቅድመ ሁኔታዎች ሳይኖሩ ሁሉም እድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ ዜጎችን የመማር መብት የሚያስከብር ሆነ፡፡ የትምህርት ፍትሃዊነት በቦታ (በከተማና በገጠር) ተደራሽ መሆን ብቻ ሳይሆን በፆታ፣ በብሔርና ብሔረሰብ ፍትሃዊነቱ መረጋገጥ ያለበት መሆኑ በህገ-መንግስቱ በግልጽ ተመላክቷል፡፡ ከዴሞክራሲ ስርዓት አኳያ ስልጣን በህዝብ ይሁንታ እንጅ ከህዝብ ይሁንታ ውጭ ፈጽሞ የማይፈይድ መሆኑ በግልጽ ተመላከተ፡፡ ወጣቶች ሂደቱን በመምራትና ህዝቡን በማደራጀት ታሪካዊ ተልዕኳቸውን በብቃት ተወጥተዋል፡፡
በጥቅሉ መሰረታዊ የህዝብ መብቶችንና ጥቅሞችን በልማታዊና ዴሞክራሲያዊ አግባብ ለሚያረጋግጡ የህዝብ ጥያቄዎች በተሟላና ዘላቂነት ባለው መልኩ መልስ ሰጥቷል፡፡ የፌዴራሉን ህገ-መንግስት ተከትሎ የአማራ ክልልም የራሱን ህገ-መንግስት በምክር ቤቱ አፀደቀ፤ በክልሉ የሚገኙ ብሔረሰቦችም በሚኖሩበት መልክዓ ምድር የራሳቸውን ምክር ቤት አደራጅተው ራስን በራስ የማስተዳደር መብታቸውን ተጎናፀፉ፡፡ ለዘላቂ ሠላማችንና ለአብሮነታችን ዋስትናና ወሳኝ ቅድመ ሁኔታ የሆነው ህገ-መንግስት ፀድቆ ተግባራዊ መሆኑ፣ የኢትዮጵያን ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ አብዮት ሁለተኛ ምዕራፍ ያበሰረ ትልቅ ድል ነው፡፡ በዚህ ረገድ የአማራ ክልል ወጣቶች ከአገራችን ወጣቶች ጋር ጣምራ ትግልና ድል ተጎናፅፈዋል፡፡
የአገራችን አብዮት ሦስተኛው ምዕራፍ በልማታዊ ዴሞክራሲያዊ ጎዳና፣ በህዝብ ይሁንታ ላይ የተመሰረተን ህዝባዊ መንግስት መስርቶና ዘላቂ ሠላምን አረጋግጦ፣ በመሰረተ ሰፊና በአደገ ገጽታ ስራ ላይ የዋለ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ፤ ፈጣን፣ ፍትሃዊ እንዲሁም ህዝቡ በየደረጃው ተጠቃሚ የሚሆንበትን የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማትን በቀጣይነት ማረጋገጥ ይጠይቃል፡፡
1.1.3 የህዝባዊ መንግስት ምስረታና የሠላም፣ ልማትና የዴሞክራሲ ንቅናቄ ውጤቶች
የኢትዮጵያ የመሰረታዊ ለውጥ ንቅናቄ ሦስተኛውና ረጅሙ ምዕራፍ ከ1988 ዓ.ም አንስቶ ቀጠለ፡፡ በዚህ ምዕራፍም የወጣቶች ግንባር ቀደም ንቅናቄ ሌላ መተኪያ አልነበረውም፡፡
ሀ/ አስተማማኝና ዘላቂ ሠላምን የማረጋገጥ ትግልና ውጤቶቹ
ድርጅታችን ብአዴን-ኢህአዴግና በሱ የሚመራው ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መንግስታችን ከሽግግር መንግስት ወቅት አንስቶ በትኩረት የያዘውን የሠላምና የመረጋጋት ተግባራት ቀጣይነት ለማስጠበቅ በትጋት ተንቀሳቅሷል፡፡ ለዘመናት ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ ህገ-ወጦችና፣ ጉልበተኞች የአቅመ ደካሞችን ሀብትና ንብረት እንዲሁም ህይወት እንደፈለጉ አደጋ ላይ እየጣሉ ያሻቸውን እያደረጉ የማይጠየቁበት፣ አልፎ አልፎም የሽፍትነትን ስራ በተከታታይ በማከናወናቸው በደጋፊዎቻቸው የሚሞካሹበት ነባራዊ ሁኔታ ነበር፡፡
ብአዴን-ኢህአዴግ ህዝቡን በማንቃት እና በማደራጀት ህገ-ወጥነትን ጉልበተኛነትን፣ በሌላው ላብና ጉልበት ተንጠልጥሎ የመኖርን መጥፎ አባዜ ለመግታት ከፍተኛ ጥረት አድርጓል፡፡ በአንድ በኩል ከደርግ ድምሰሳ ጋር ተያይዞ ተበትኖ የነበረውን በመቶ ሺዎች የሚቆጠር ወታደርና የጦር መሳሪያ በአግባቡ በመሰብሰብ ወታደሩን የሠላምና የተሃድሶ ትምህርት በመስጠትና በማስተማር ወደ ምርት ስራ እንዲገባ አቅም የፈቀደውን በማመቻቸት፣ የተበተነውን የጦር መሳሪያ በመልቀም ህዝባዊ ሚሊሻንና ፖሊስን አሰልጥኖ በማስታጠቁ ሠላማዊነትና ህጋዊነት እንዲረጋገጥ ከፍተኛ ጥረት አድርጓል፡፡ በዚህ ረገድ ወጣቶች ለህይወታቸው ሳይሰስቱ የህዝባቸውን አስተማማኝ ሰላምና ፀጥታ ለማስከበር ተንቀሳቅሰው በከፈሉት አኩሪ መስዋዕትነት የህዝባቸውን ሰላም አስተማማኝና ዘላቂ ማድረግ ችለዋል፡፡
ከመደበኛ የማምረት ተግባሩ ሳይነጠል የአካባቢውን ሠላም የሚጠበቅ ህዝባዊ ሚሊሻን በህዝብ ተሳትፎ በመመልመል እና በማሰልጠን እንዲሁም ቀጣይነት ያለው የአቅም ግንባታ በማድረግ ከህዝቡ የተደተራጀ እንቅስቃሴ ጋር በመሆን የሠላሙ ጉዞ በአስተማማኝ ሁኔታ እንዲዘልቅ ገንቢ ሚና ተጫውቷል፡፡ በፀረ-ዴሞክራሲ አምሳያ የተቀረፀውን የቀድሞ ፖሊስ የተሀድሶ ትምህርት ከመስጠት በተጨማሪ አዳዲስ የፖሊስ አባላት በህዝብ ተሳትፎ ተመልምለው፣ ህዝባዊ ሥነ-ምግባር የተላበሱ ሆነው ህዝብን እንዲያገለግሉ፣ የፖሊስ ኃይሉ ማዕከላዊ ስራ ወንጀል ከመፈፀሙ በፊት መከላከል እንዲሆን፣ ለዘላቂ ወንጀል መከላከል ሰፊ መሰረት ያለው ደግሞ ማህበረሰባዊ የፖሊስ እንቅስቃሴ (Community Pollicing) በዝርዝር የአፈፃጸም ስርዓት ተደራጅቶ ከከተማ እስከ ገጠር ህብረተሰቡ ከፖሊስ ጋር ተደራጅቶ ሰላምን አስተማማኝ የማድረግ ብቻ ሳይሆን ለዘላቂ ሠላም ቁልፍ ተፈላጊነት ያለው የአካባቢ ልማት እንዲረጋገጥ የበኩሉን አወንታዊ አስተዋጽኦ በማበርከት ላይ ይገኛል፡፡ በዚህ ተግባር የወጣቶች ተሳትፎ ቀጥተኛና ተኪ ያልነበረው ነበር፡፡
ህዝባዊ ፖሊስና ሚሊሻ ከዋናው ባለቤት ከህዝቡ ጋር በመሆን በየደረጃው ከሚገኘው የአስተዳደር መዋቅር ቀጥተኛ አመራር እያገኘ ሠላም በራሱ ምርት እንዲሆን ዜጎች በነፃነት በፈለጉት ጊዜ፣ ከቦታ ቦታ ተዘዋውረው ኑሯቸውን ለማሻሻል እንዲተጉ፣ የሀብትና ንብረታቸው ከለላና ጠበቃ እንዲኖረው መሰረተ ሰፊና ቀጣይነት ያለው ስራ ተሰርቷል፡፡ ከወንጀል መከላከል አልፈው የሚፈፀሙ ወንጀሎችን አጣርቶ ለህግ በማቅረብ እና በማስቀጣት እንደ ሁሉም ተግባራቶቻችን ሁሉ የአፈፃጸም ድክመት ያለበት ቢሆንም ወሳኝ ገጽታው ወንጀለኞች ወንጀል ፈፅመው ከተጠያቂነት እንደማያመልጡ የሚያረጋግጡ ተግባራት ተከናውነዋል፡፡ በአጠቃላይ ባለፉት 24 ዓመታት ሠላም በራሱና ከሌሎች የዴሞክራሲና የልማት ተግባራት ጋር በድምር ተመጋግበው እንዲያድጉ በዚሁ ሂደትም ህዝባችን የሠላም አየር እንዲተነፍስ፣ ሠላማዊና የሰከነ ሁኔታም እንዲረጋገጥ ብአዴንና ህዝቡ አኩሪ ተግባራትን ፈፅመዋል፡፡

No comments:

Post a Comment