ታላቁ የህዳሴ ግድብ 5ኛ ዓመቱን ሊያከብር በዋዜማ
ላይ ነው። ጥቂት ቀናቶች ብቻ ይቀሩታል። የግድቡ 5ኛ ክብረበዓል “ታላቁ የህዳሴ ግድባችን የማንነታችን አሻራ ያረፈበት የህዳሴያችን
ብርሃን ነው” በሚል መሪ ቃል የሚከበር ይሆናል። ታዲያ ክብረ-በዓሉን አስመልክቶ ከወዲሁ የሚወጡት መረጃዎች “የሚያጠግብ እንጀራ…”
እንዲሉ ፍፃሜውን የሚያመላክቱ ናቸው ማለት ይቻላል።
መረጃዎች እንደሚጠቁሙት የታላቁ ህዳሴ ግድብ
የሃይድሮና ኤሌክትሮ ሜካኒካል ስራዎች በራሳችን አቅምና ብቃት በብረታ ብረት እና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን በመከናወን ላይ ይገኛል።
ግድቡ ከባህር ጠለል በላይ 145 ሜትር ከፍታ ይኖረዋል። እስካሁን ድረስም ከዚህ ውስጥ 75 ሜትር ያህሉ ስራው ተከናውኗል። ከባህር
ጠለል በታች ደግሞ 35 ሜትር ተገንብቷል። ግድቡ ሲጠናቀቅ የሚፈጠረው ሰው ሰራሽ ውሃ የሚተኛበትን ቦታ የመመንጠርና የማመቻቸት
ስራም በፍጥነት እየተከናወነ ነው። አጠቃላዩ ግንባታም ከ50 በመቶ በላይ መጠናቀቁም ተገልጿል።
ከግንባታው ጎን ለጎንም የተለያዩ የመሰረተ ልማት
ስራዎች በመከናወን ላይ ናቸው። የአውሮፕላን ማረፊያ፣ ከአሶሳ ወደ ግድቡ የሚያስኬድ የ108 ኪሎ ሜትር ተለዋጭ መንገድና የሃይል
ማስተላለፊያ መስመር ዝርጋታ በመከናወን ላይ ናቸው። እነዚህ ክንዋኔዎችም ግድቡ ላለፉት አምስት ዓመታት የተጓዘባቸው አቅጣጫዎች
ትክክለኛ መሆናቸውን እንዲሁም የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የራሳቸውን አሻራ በማሳረፍ ህዳሴያቸውን ብርሃንነት አሻግረው
ለማየት የሚያስችለውን ተግባራት መፈፀማቸውን ያመላክታሉ።
እንደሚታወቀው ምንም እንኳን ሀገራችን ለኤሌክትሪክ
ኃይል ማመንጫነት ያሚያገለግሉ በርካታ ቢኖራትም፤ በተፈጥሯዊ የውሃ ሃብቷ የመጠቀም መብቷ ተገድቦ ቆይቷል፡፡ ለዚህ በምክንያትነት
የሚጠቀሱት ሀገሪቱን ጨምድዶ ይዞ የነበረው የከፋ ድህነት እንዲሁም ያለፉት መንግስታት የነበራቸው የአስተሳሰብ ውስንነት እንደነበር
አይታበይም፡፡ ዳሩ ግን ዛሬ ላይ የሀገራችን ህዝቦች እነዚህን ውስንነቶች ቀርፈው በራሳቸው የተፈጥሮ ሃብት ተጠቃሚ ከመሆን ባሻገር፣
ህዳሴያቸውን ብሩህ ለማድረግ ታላቅ ግድብ ለመገንባት የዛሬ አምስት ዓመት ተልመው አሻራቸውን በማኖር ላይ ናቸው፤ ማንነታቸውንም
እያሳዩ ነው። ይህ ታላቅ ኩራታቸውም ነው።
እርግጥ በህዝብ ተሳትፎና በህዝቦች መፈቃቀድ
ላይ የተመሰረተ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትና መልካም አስተዳደር የሰፈነባት፣ ማህበራዊ ፍትህ የነገሰባት፣ ከድህነት ተላቃ መካከለኛ ገቢ
ያላት ኢትዮጵያ እውን የማድረግ ራዕይን የሰነቀው የኢፌዴሪ መንግስት የመሪነት ሚናውን ላላፉት አምስት ዓመታት በብቃት ተወጥቷል።
ኩራታችን የሆነውን በተፈጥራዊ የውኃ ሀብታችን የመጠቀም መብታችንን በበቂ ዲፕሎማሲያዊ ክህሎት ታጅቦ አረጋግጧል፡፡
ላለፉት 12 ዓመታት ሀገራችን ባለ ሁለት አሃዝ
ዕድገት እያስመዘገበች ነው። ይህም ዛሬ ላይ በተፈጥሯዊ የውሃ ሀብቷ በመጠቀም መብቷ በማትደራደርበት ደረጃ ላይ እንድትደርስ ያደረጋት
ይመስለኛል፡፡ በአሁኑ ወቅት እየተጠናከረ የመጣው የህዝቧ የልማት ቁርጠኝነት እንዲሁም መንግስት የሚያከናውናቸው ሁለንተናዊ የልማት
ስራዎች ዘላቂና ከባቢያዊ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጡ መሆን ችለዋል፡፡
የግድቡ ግንባታ ሀገራችን በተፈጥሮ ሀብቷ የመጠቀም
መብትና አቅም ያላት መሆኑን ያረጋገጠ ታሪካዊ ክስተትነቱ እርግጥ መሆኑ ነጋሪ የሚያሻው ጉዳይ አይመስለኝም። ለዚህ አባባሌ አስረጅነት
ቢያንስ ሁለት አብነቶችን መጥቀስ እችላለሁ። የመጀመሪያው በታችኛው የተፋሰሱ ሀገራት
እንደ ግል ሀብት በሚቆጠረው የአባይ ወንዝ መጠቀም የማይታሰብ ጉዳይ ሆኖ ቢቆይም፤ ኢትዮጵያ በወንዙ የመጠቀም መብቷን በተግባር
ያሳየችበት ታሪካዊ ድርጊት መሆኑ ነው። ሁለተኛው ደግሞ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊ አቅም አባይን መገደብ እንደማይቻል እርግጠኞች የነበሩ
በርካቶች ቢሆኑም፣ ሀገሪቷና ህዝቦቿ ላለፉት 12 ዓመታት ባስመዘገቡት ዕድገት እየተመሩ የራሳቸውን ልማት በራሳቸው አቅም የሚገነቡበት
ደረጃ ላይ መድረሳቸውን ያስመሰከሩበት ግድብ ስለሆነ ነው፡፡
በመሆኑም የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ
ዛሬ ላይ ከግማሽ በላይ መድረሱ፤ አንድም በተፈጥሯዊው የውኃ ሀብታችን የመጠቀም መብታችንን ያመላከተ፣ ሁለትም ታላላቅ ፕሮጀክቶችን
የመገንባት ችሎታችንንና አቅማችንን እንዲሁም የሀገራችን በህዝቦች ሁለንተናዊ ትብብራቸው እጥረቶቻቸውን መቅረፍ እንደሚችሉ ለዓለም
ያሳዩበት የማንነታቸው መገለጫ መሆኑ ነው።
መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ህዝቡ ባለፉት ዓመታት
ውስጥ 12 ቢሊዩን ብር ለግድቡ ግንባታ ለግሷል። ከዚህ ውስጥ 8 ነጥብ 1 ቢሊዩን ብሩ ለግንባታ ስራው ውሏል። በዘንድሮው ዓመትም
500 ሚሊዩን ብር ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ለመሰብሰብ ተችሏል። እነዚህ የቁጥር ዕውነታዎች የሚያሳዩት ህዝቡ ለግድቡ ግንበታ
በባለቤትነት መንፈስ ምን ያህል እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ነው። ማንነታዊ አሻራውንም በግድቡ ላይ በማስቀመጥ መጪውን የህዳሴ ዘመን
ከወዲሁ በብርሃን እንዲሞላ እያደረገ መሆኑም እንዲሁ። ከሁሉም በላይ በራስ የተፈጥሮ ሃብት ፍትሐዊ በሆነ መንገድ መልማት የየትኛውም
ህብረተሰብ መብት መሆኑን በተሳትፎው ዕውን እያደረገ መሆኑን የሚያሳይ ይመስለኛል።
ታዲያ እዚህ ላይ የሀገራችን ህዝቦች እንደ ማንኛውም
ሀገር ህዝብ በውሃ ሃብታቸው በመጠቀም ከድህነት የመላቀቅ መብት እንዳላት ማወቅ ተገቢ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ እርግጥም ኢትዮጵያን
ጨምሮ ሁሉም የላይኛው የናይል ተፋሰስ ሀገራት ህዝቦቻቸውን ከድህነት የማውጣት የቤት ስራ ፊታቸው ላይ ተደቅኖ ይገኛል፡፡ ይህን
የቤት ስራቸውን በብቃት ለመወጣት ደግሞ ሁሉንም የተፈጥሮ ሃብታቸውን በተገቢው ሁኔታ አልምተው መጠቀም ይኖርባቸዋል። እናም ከተፈጥሮ
ሃብታቸው አንዱ የሆነው ውሃን ለልማት የማዋል ጉዳይ ጊዜ የሚሰጡት ሊሆን አይችልም።
በመሆኑም ኢትዮጵያና ሌሎች የላይኛው ተፋሰስ
ሀገራት በውሃ ሀብታቸውን ተጠቅመው የምግብ ዋስትናቸውን እንዲሁም የሃይል አቅርቦትን በማሳደግ ለኢንዱስትሪው ኢኮኖሚ ምቹ ሁኔታ
መፍጠርን ዋነኛውና ወሳኙ አማራጭ ካደረጉ ቆይተዋል፡፡ በዚህም በሆደ ሰፊነትና በአርቆ አሳቢነት በውሃው እኩል ተጠቃሚነት ላይ ለሁለት
አስርት ዓመታት ሲደራደሩ ቆይተዋል፡፡ ሂደቱ አንድ ጉልህ ግንዛቤን ያስጨበጠናል፡፡ እርሱም የተፋሰሱ ሀገራት በውሃው የጋራ ተጠቃሚነት
ላይ ብቻ መመስረታቸውን እንዲሁም ይህ ሃሳባቸው ማንንም ለመጉዳት የታሰበ አለመሆኑን ነው፡፡
ሁላችንም እንደምናውቀው አንዱን ተጠቃሚ ሌላውን
ተጎጂ ያደረጉት ሁለቱም የቅኝ ገዥዎች ስምምነቶች ከግብጽና ከሱዳን በስተቀር ሌሎቹን የተፋሰሱ ሀገራት ያገለሉና በሃይል ላይ የተመሰረቱ
ናቸው፡፡ ከዚህ አንጻር የተፋሰሱ ሀገራት በጋራ ተጠቃሚነት መርህ ላይ የተመሰረተው የኢንቴቤው የስምምነት ማዕቀፍ፤ የውሃ ባለሃብቶቹን
የላይኛው ተፋሰስ ሀገራትንም ይሁን ዋነኛ ተጠቃሚ የነበሩትን የታችኛው ተፋሰስ ሀገራት ያጠቃለለ ሰጥቶ መቀበል አካሄድን የተከተለ
ነው፡፡ እኛ ግድቡን እንገነባለን እነርሱ ደግሞ ከደለልና በትነት መልክ ከሚባክን ውሃ ይድናሉ ማለት ነው። አዎ! ሀገራችን የምታካሂደው
የህዳሴ ግድብም ከዚህ ዕውነታ የመነጨ በመሆኑ የትኛውንም ሀገር የማይጎዳ፣ ይልቁንም የታችኛዎቹን የተፋሰሱን ሀገራት የሚጠቅም ነው።
እንደሚታወቀው የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ
ግንባታ እንዲከናወን የተወሰነው ከጎረቤት ሀገር ሱዳን ድንበር እጅግ ተጠግቶ ነው፡፡ ይህም ግድቡ ለመስኖ አገልግሎት ሊውል እንደማይችል
ያሳያል። እናም ውሳኔው የኤሌትሪክ ሃይልን የማመንጨትና የሃይል አቅርቦትን በማሳደግ ሀገራዊ ልማትን ከማፋጠን ውጪ ሌላ አጀንዳ
የለውም፡፡ የኤሌትሪክ ሃይል ማመንጫ ግድቦች ሃይልን ከማመንጨት ባሻገር አንድ ጠብታ ውሃም ቢሆን እንደማያባክኑ ግልፅ ነው፡፡ ከዚህ
ይልቅ ግድቡ በታችኛው የተፋሰሱ ሀገራት ውስጥ በየዓመቱ ሲደርስ የቆየውን ከፍተኛ የውሃ ትነት መጠን የሚያስቀር በመሆኑ ጠቀሜታው
የጎላ ነው። ድንገተኛ የጎርፍ አደጋንም ይታደጋል። ከዓባይ ወንዝ የሚሄደውን ደለል መጠንን የመቀነስ ሚና ይኖረዋል። (ለምሳሌ ያህል
በግብፁ የአስዋን ግድብ ላይ ሊፈጠር የሚችል ደለልን 50 በመቶ ያህል ይቀንሳል) ከዚህ በተጨማሪም የውሃ ቁጠባንና በበቂ ሁኔታ
የማስተዳደር ሁኔታንም ይፈጥራል።
በሌላ ጎኑ ደግሞ ሀገራችን ከግንባታው የምትጠቀመው
ነገር ይኖራል። ይኸውም የህዳሴው ግድብ ግንባታ ሲጠናቀቅ የሚፈጥረው ሰው ሰራሽ ሃይቅ 187 ሺህ 400 ሄክታር ይሸፍናል። ከዚህ
ሃይቅ የአሳ ምርት ማግኘት ይቻላል። በግድቡ ማጠናቀቂያ ላይ በዓመት ከ5ሺህ እስከ 10ሺህ ቶን የአሳ ምርት እንደሚገኝ ይገመታል።
እርግጥ እ.ኤ.አ በ1995 በወጣ አንድ ሪፖርት ላይ እንደተመለከተው፤ ይህ ምርት ግብፅ በየዓመቱ ከናስር ሃይቅ ብቻ ከምታገኘው
ከ12ሺህ እስከ 23 ሺህ ቶን የአሳ ምርት ጋር ሲነፃፀር አነስተኛ ነው— ንፅፅሩ ከእጥፍ በላይ ነውና። ይሁንና የአሳ ሃብቷን በስፋት
ለመጠቀም ላሰበችው ሀገራችን ከምርቱ ጀማሪነት አንፃር ሲታይ ሊያበረታታ የሚችል መሆኑ አይካድም።
ከእነዚህ ተጨባጭ ሃቆች በመነሳትም ሀገራችን
የምታካሂደው ታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ህዝቦቿ የራሳቸውን አሻራ በማሳረፍ የህዳሴያቸውን ብርሃን ፈንጣቂ ፕሮጀክት ለማየት ከማለም
የሚያከናውኑት መሆኑ ዛሬ በ5ኛ ዓመቱ ክብረበዓል ላይ ሊታወቅ ይገባል። የትኛውንም ወገን ለመጉዳት አይደለም። ይህን ሃቅም ሌላው
ቢቀር እስካሁን ድረስ የግድቡን ግንባታ ሂደት ከጎበኙት ከ170 ሺህ በላይ ህዝብና ከ350 በላይ የውጭ መገናኛ ብዙሃን መረዳት
የሚቻል ይመስለኛል። ያም ሆነ ይህ ግን ግድቡ የህዝባችን አሻራ ያረፈበት የህዳሴያችን ብርሃን ብቻ መሆኑን መገንዘብ የሚገባ ይመስለኛል።
No comments:
Post a Comment