የሁለተኛውን የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዘመን ለማሳካት ከተያዙት ቁልፍ ስራዎች መካከል
ብቁ የሰው ሀይል ማፍራት የሚለው ቀዳሚውን ስፍራ ይይዛል፡፡ በእቅድ ትግበራውም 80 በመቶውን የሚሆነው በዝቅተኛና መካከለኛ ደረጃ
ከቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ዘርፍ ለማፍራት አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡ በዚህ አቅጣጫ መሰረትም ሰፊ ህዝባዊ መሰረት ያለው የጥቃቅንና
አነስተኛ ዘርፍ በምርት ጥራትና ምርታማነት በተሰጠው ልዩ ትኩረት ዘርፉን ለሚቀላቀሉ ዜጎች ከፍተኛ ድጋፍ እየተደረገ ይገኛል፡፡
እነዚህ ዜጎች ራሳቸውን ከመቻል አልፎው ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ ለሚደረገው ሽግግር የጀርባ አጥንት እንዲሆኑ ለማስቻልም የቴክኒክና
ሙያ ትምህርት ስልጠና ተቋማት ኢንተርፕራይዞችን በአራት የድጋፍ ማዕቀፎች ማለትም የካይዘን አቅም ግንባታ፣ የስራ ፈጠራ አቅም ግንባታ፣
የቴክኒካል ክህሎት አቅም ግንባታ እና የቴክኖሎጂ አቅም ግንባታ እንዲያገኙ የማድረግ ተግባር ይከናወናል፡፡
በዚህ መሰረትም በአዲስ አበባ በመንግስት፣ በግልና በመያድ የተቋቋሙ 336 የቴክኒክና ሙያ
ትምህርት ስልጠና ኮሌጆችና ተቋማት ከላይ በተጠቀሰው አቅጣጫ የሰው ሃይል እያመረቱ ይገኛሉ፡፡ በተለይም የመንግስት ማሰልጠኛ ተቋማት
በአራቱ የድጋፍ ማዕቀፎች በቀጥታ ከኢንተርፕራይዞች ጋር በመስራታቸው ውጤቶች መመዝገብ ችለዋል፡፡
ለውጤቱ መገኘት ደግሞ የቴክኒክና ሙያ ትምህርት ስልጠና አሰልጣኞች በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳሉ፡፡
በቅርብ እትሞቻችንም የአሰልጣኞች ከሚሰሩበት ተቋም ተልእኮ በመነሳት ኢንተርፕራይዞችን በሚደግፉበት ወቅት ከሚያስተውሉት ችግር በመነሳት
የፈጠራ ግኝቶቻቸውን ለማበርከት መብቃታቸውን አንስተናል፡፡
የዛሬው የፈጠራ አምዳችንም የፈጠራ መነሻ ተመሳሳይ ታሪክ አለው፡፡ አሰፋ ዘለቀ ይባላል፡፡
ትውልዱ በሰሜን ሸዋ ሸኖ አካባቢ ሲሆን የመጀመሪያ እና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱንም እዛው በሸኖ ከተማ ተከታትሏል፡፡ የ12ኛ ክፍል
ትምህርቱን እንዳጠናቀቀ በቀድሞ ቴክኒክና ሙያ አሰልጣኞች ማሰልጠኛ በአሁኑ አዳማ ዩኒቨርስቲ ለአራት አመታት የማኑፋክቸሪንግ ዲፓርትመንት
ስልጠናውን ተከታትሏል፡፡
ስልጠናውን አጠናቆ በ1995 ዓ.ም በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወደሚገኘው ከፍተኛ
20 ቴክኒክና ሙያ ተቋም በአሰልጣኝነት ተቀጠረ፡፡ በ2005 ዓ.ም ወደ ተግባረዕድ እስኪቀየር ድረስ ለአስር አመታት አገልግሏል፡፡
በነበረው ቆይታም 70 በመቶ የተግባር፤ 30 በመቶ የንድፈ ሀሳብ ስልጠናን በመስጠት ግዴታውን በአግባቡ እንደተወጣ ይናገራል፡፡
የፈጠራ ዝንባሌውን አስመልክቶ እንደሚናገረው ቀደም ሲል አንዳንድ ነገሮችን በቤት ውስጥ በመስራት እና የኤሌክትሮኒክስ ቁሳቁሶችን
የመጠገን ሙከራዎች ያደረግ እንደነበረ አጫውቶናል፡፡ ወደ ኮሌጅ ባቀናበት ጊዜም ተሰጦውን መሰረት አድርጎ የማኑፋክቸሪንግ ዘውግ
ቀዳሚው ምርጫው አደረገ፡፡
ቀደም ብሎ እንደጠቀስነውም በሰለጠነበት መስክ ለማስልጠን ተመደበ፡፡ በተራው ወጣቶችን ማሰልጠንም
ተያያዘው፡፡ አሰፋ በሰለጠነበት ዘመን እና ቀደም ብሎ ባሳለፋቸው የስራ ዘመናት አሰልጣኞች በሚገባ እንዳያሰለጥኑ ሰልጣኞችም ክህሎታቸውን
እንዳያዳብሩ የሚያደርግ አንድ ማነቆ እንደነበር ይናገራል፡፡ እሱም ከፍተኛ የሆነ የግብአት ችግር ነው፡፡ አይደለም ለፈጠራ ደረጃ
የሚያደርስ ሀሳብ ማንሳት ቀርቶ በተለያዩ የስልጠና ክፍሎች ለሚቀላቀሉ ሰልጣኞች ማስተማሪያ የሚሆን ግብአት አለመኖር ፈታኝ እንደነበር
ያስታውሳል፡፡ ዛሬ ላይ ችግሩ ከመቀረፉ በዘለለም ጠቃሚ ግኝቶችን ለማበርከት የሚያበቃ አቅርቦት መኖሩ የተሻለ ለመስራት የሚያነሳሳ
መሆኑን ይመሰክራል፡፡ ዘንድሮ ለስድስተኛ ጊዜ በተከናወነው ሀገር አቀፍ የፈጠራ እውቅና አስቀድሞ በ1998 ከፍተኛ 20 ቴክኒክና
ሙያ ማሰልጠኛ እያለ በአነስተኛ ቦታ ላይ ለመጠቀም የሚያስችል ቀላል እና ቀልጣፋ የሽመና መስሪያ ሰርቶ ነበር፡፡ በወቅቱም በስራው
ለተሰማሩ ግለሰቦች ተሰጥቶ ተሞክሮ ጥሩ ውጤት እንደተገኘበትም ከደረሰው ግብረ መልስ መረዳቱንም ያስታውሳል፡፡
ለኣዳዲስ ፈጠራዎች ትኩረትና ጊዜውን የሚሰጠው አሰፋ እንሆ በ2008 ዓ.ም በተከናወነው ሀገር
አቀፍ የፈጠራ እውቅና የወርቅ ሜዳልያ ባለቤት መሆን ችሏል፡፡ መምህሩ ሶስት የፈጠራ ውጤቶች አሉት፡፡ ከነዚህ መሀከል የክብ ቶቦላሬ
ማጠፊያ አንዱ ነው፡፡ መነሻ ሀሳቡ ደግሞ ከማሰልጠን ስራው ጋር ተያይዞ መሆኑ ያስገርማል፡፡ ከጥቂት ወራት በፊት በሚያሰለጥንበት
ተግባረዕድ ተቋም ተማሪዎች ቆይታቸውን አጠናቀው ብቁ ለመሆን የተግባር ፈተና ወይም ሲኦሲ ተፈትነው ማለፉ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ታዲያ
በዚህ መሀል ክብ ብረቶችን ማጠፍ አንዱ የፈተናው አካል ነበርና ይህንን የሚያደርግ መሳሪያ ከተቋምም ከገበያም መጥፋቱ ለፈጠራው
መነሻ አደረገለት፡፡ በመቀጠል ችግሩን ለመፍታት ከባልደረቦቹ ጋር በመነጋገር ሀሳቡን በሚያብላለበት ቅፅበት ድጋፍ ከሚያደርጉላቸው
ጥቃቅንና አነስትኛ ኢንተርፕራይዞች የተገኘ ችግር መሆኑም ፈጠራውን ለመተግበር ሌላው ገፊ ምክንያት ሆነው፡፡ በልደታ እና ቂርቆስ
ክፍለ ከተሞች ከሚደግፏቸው 17 ኢንተርፕራይዞች የአብዛኞቹ ችግር የብረት ማጠፊያ መሳሪያው መሆኑ ይበልጥ እረፍት የነሳው አሰፋም
ከተቋሙ በተገኙ አነስተኛ ቁሳቁሶች ችግሩን የሚፈታ መሳሪያ ሰርቷል፡፡ ራሱም እንደነገረን ለአዲስ ፈጠራው ግብአት የጠየቀው ጠቅላላ
ወጪ 1200 ብር ብቻ ነው፡፡
ቀደም ሲል በችግሩ ውስጥ የነበሩት ኢንተርፕራይዞችንም የመሳሪያውን አሰራር በመውሰድ በሌሎች ተቋማት በማሰራት እና ራሳቸውም
በመስራት ጥቅም ላይ ማዋላቸውን ሲናገር መላ ያበጀለትን ችግር እንደተቃለለ ይናገራል፡፡ ሁለተኛው ፈጠራውም በተመሳሳይ በእንጨት
እና ቅርሳቅርስ የሚሰሩ ኢንተርፕራይዞችን ድጋፍ ሲሰጥ ያስተዋለው ክፍተት የጫረው ነው፡፡ ይህም ኢንተርፕራይዞቹ የቀርከሀ ስራዎቻቸውን
በሚያመርቱበት ወቅት የማለስለስ ስራው እጅግ አድካሚና ረጅም ጊዜ መፍጀቱን በችግር ማንሳታቸው በዲፓርትመንት እንዲነጋገሩበት ምክንያት
ሆነ፡፡
በተቋሙ ከባልደረቦቹ መምህራን ጋር ሀሳቦችን በመለዋወጥ ለቀርከሀም ለእንጨትም ማለስለሻ የሚያገለግል መስሪያ ማበጀት
እንደቻለ አሰፋ ያስረዳል፡፡ በዚህ መሰረትም ቴክኖሎጂውን በቀጥታ መስራት ሳይሆን የአሰራሩን ሀሳብ ዝርዝር በስዕል ለኢንተርፕራይዞች
መስጠቱን እና በቀርከሀ ምርት በስፋት ለሚታወቀው የደቡብ ክልል ቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ እውቀቱን ማሸጋገር መቻሉም አስረድቷል፡፡ ጊዜና
ጉልበትን በመቆጠብ የጥራት ደረጃን በማሻሻል የበኩሉን አስተዋፅኦ የሚያበረክት መሆኑም የታመነበት ሲሆን በሀገር ደረጃም ጥቅሙ የላቀ
እንደሆነ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የተረጋገጠ መሆኑን የፈጠራው ባለቤት ይናገራል፡፡
በሚያስለጥንበት ወቅት በአንድ ስራ ቦታ አብረውት ከሚሰሩት ውስጥ ወጣት በረከት ፀጋዓብ በተመሳሳይም የብዙ ፈጠራዎች
ባለቤት ነው፡፡ በተቋሙ ተጋገዞ የመስራት ባህል የጠነከረ መሆኑን ይናገራል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ሀሳቦችን በመደጋገፍ ለስራዎቻቸው
እሙን መሆን እንደሚጠቀሙበት አስረድቷል፡፡ መስል ፈጠራዎችም ሆኑ አዳዲስ ግኝቶች መንግስት በተሰጣቸው እውቅና ልክ ተግባር ላይ
ውለው የህብረተሰቡን ችግር መቅረፍ የሚቻልበትን አግባብ ማመቻቸት ቢቻል ጥሩ ነው የሚል አስተያየትም ሰጥቷል፡፡
በሶስተኛ ደረጃ የሰራው ደግሞ በቅጂ የተከናወነ ነው፡፡ ይህም ከዘመናዊ መረጃ መረብ ኢንተርኔት በመውሰድ በአንድ መሳሪያ
ሩዝ፣ ጤፍና ስንዴ መዝራት የሚያስችል ነው፡፡ ያሉትን ሶስት ቀዳዳዎች በመቀያየር የተጠቀሱትን ዘሮች በመስመር መዝራት የሚያስችል
ሲሆን ቀድሞ ከተሰራበት ፕላስቲክ በብረት በመተካት እና በቀላሉ መንከባለል እንዲችል የመግፊያ ጎማውን ከፍ በማድረግ እንዳሻሻለው
አሰፋ ያብራራል፡፡
ቴክኖሎጂው መቶ በመቶ ተጠናቆ ወደ ተጠቃሚው ለማስተላለፍ 2500 ሺህ ብር ተተምኖለታል፡፡ ይህ ደግሞ በአሁኑ ሰአት
በስፋት እየተከናወነ ላለው ግብርና እጅግ ጠቃሚ መሆኑን በመረዳት የሳይንስና ቴክሎጂ ሚኒስቴር የወርቅ ሜዳሊያ እና የስድስት ሺህ
ብር ሽልማት አበርክቶለታል፡፡ ለዚህ አመርቂ አፈፃፀሙም የተግባረዕድ ተቋም የወርቅ ሽልማት አበርክቶለታል””
‹‹ሽልማት ለጥረት እውቅናን ከመስጠት አልፎ ለቀጣይም ብርታትን የሚያስታጥቅ የሞራል ግብአት ነው›› ይላል አሰፋ፡፡
በሽልማት ብቻ ሳያበቃ በዘንድሮው አመት በኢትዮ ቻይና ቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ተቋም የማስተርስ ትምህርት እድል አግኝቶ እየተከታተለ
ይገኛል፡፡ ለሰሯቸው ስራዎች ሌላኛ ማበረታቻ ነው የሚለው አሰፋ ሌላም ሃለፊነት እንደተጣለበት ያምናል፡፡ ይህም በቆይታው የሚያገኘውን
እውቀት ለተሻለ ፈጠራ እና የማሰልጠን አደራን ያስረከበው መሆኑን፡፡ ሀገራችን የሚያስፈልጋትን ስንልጡን የሰው ሀይል በመገንባት
በግሉ ጠንክሮ እንደሚሰራ እና ፈጠራዎቹንም በተመሳሳይ ችግር ፈቺ ሆነው እንዲቀጠሉ ትጋቱን እንደሚቀጥል ምኞቱን ገልጿል፡፡
አሰፋም ‹‹ዛሬ ላይ የበርካታ ፈጠራ ባለቤቶች ማህበራዊ ችግሮቻችንን መሰረት አድርገው መፍትሄ እየለገሱ ይገኛሉ፡፡ ከምንም
በላይ ደግሞ በትስስር በመስራት ለሚስተዋሉ ክፍተቶች መላን ማበጀት ለዘላቂ የኢንዱስትሪ ልማት መረጋገጥ ትልቅ ሚና አለው›› ይላል፡፡
እኛም በፈጠራ አምዳችን ያስነበብነው ተሞክሮ የሚያሳየው ይህንኑ ነው፡፡ ፈጠራ ለማህበራዊ ችግሮች ምላሽ መስጠት መቻሉ
መቀጠልም መበረታታትም ይገባዋል፡፡ ነገር ግን የተሰሩ ፈጠራዎች የመብዛታቸውን ያክል ለህብረተሰቡ ጥቅም ላይ የሚውሉበት እድል መክፈት
አለበት መልዕክታችን ነው፡፡
No comments:
Post a Comment