Sunday, 20 March 2016

የሚመጥን የትግል ቁርጠኝነት እናቀጣጥል




ዴሞክራሲያዊ ስርአት በሁለት ሃይሎች ማለትም በልማታዊና ኪራይ ሰብሳቢ ሃይሎች የሚታየውን ቅራኔ በምንም ተአምር ማስቀረት አይቻልም፡፡ እንዲህ አድርጎ ማሰብም ስህተት ነው፡፡ የሚንደው የልማታዊ ዴሞክራሲ አማራጭና የሚናደው የኪራይሰብሳቢነት አማራጭ የምንገኝበት መድረክ ተፎካካሪ አስተሳሰቦች ናቸው፡፡ድርጅታችን ኢህአዴግ የዛሬ 15 አመት የተሃድሶ መስመር ትግል ሲያቀጣጥል የስርአቱን አደጋ በግልፅ ፈርጆ ማስቀመጡ ይታወቃል፡፡ በወቅቱ ግልፅ እንደተደረገውና በኋላም በስትራቴጂና ፖሊሲ ሰነዶች በየዘርፉና መስኩ የተተነተነው ኪራይ ሰብሳቢነት/የጥገኝነት ዝቅጠት/ ከስርአታችን የሞት ሽረት ትንቅንቅ የሚያደርግ አደጋ መሆኑ ተሰምሮበት ያደረ ጉዳይ ነው፡፡
ይህ ከሆነ ዘንዳ የሽግግር ጉዟችን እስኪጠናቀቅ ኪራይ ሰብሳቢነት በተግባርም በአስተሳሰብም እየተፈታተነን መቀጠሉ አይቀርም፡፡ አንድ ልብ ሊባል የሚገባው እውነታ በልማታዊ ዴሞክራሲያዊ መስመራችን ድል አድራጊነት የሚፈጠረው ሃገራዊ ኢኮኖሚያዊ እድገት ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍልና ተጠቃሚነትን በጥብቅ ዲስፕሊን እያረጋገጠ ካልሄደ በአንፃሩ የኪራይ ሰብሳቢ ሃይል ከሚመዘገበው እድገት ከሚገባው በላይ ድርሻ በመውሰድ የገንዘብ አቅሙን በማሳደግ ተመልሶ የልማታዊ ዴሞክራሲ ስርአቱን የሚገዳደርበት ጡንቻው የሚፈረጥምበት ሁኔታ የመፍጠር አደጋ እንዳለው በምንገኝበት መድረክ ከበቂ በላይ ምልክቶችና ማሰያዎች አሉ፡፡የምንገነባው ስርአት በካፒታሊዝም አጥር ውስጥ የሚታይ ኢኮኖሚያዊ ስርአት በመሆኑ እንደ ድርጅት የሌት ተቀን ጥረታችን ጠንካራ ሃገራዊ ባለሃብት የመፍጠር ቢሆንም ይህንን ባለሃብት ከመንግስት መዋቅሩ የሚያገኘው ድጋፍና አገልግሎት ከመስመራችን ያላፈነገጠና ከአድልዎ የፀዳ የመሆኑ ጉዳይ እጅግ መሰረታዊ ነው፡፡ አሁን የሚታው አገልግሎት አሰጣጣችን ግን ሁሉንም በጅምላ የሚያስተናግድ ብቻ ሳይሆን ልማታዊ ባለሃብትም ጭምር ወደ ህገወጥ ጥግ የሚገፋ ገፋፊ ዝንባሌና ተግባር ነው፡፡ በበርካታ መድረኮች ህዝቡ /ባለሃብቱም ጭምር/ በግልፅ እንደሚያነሳቸው አንዳንድ ተቋሞቻችን ባለ ጉዳይ በእግሩ ብቻ ሄዶ ጉዳዩን ማስፈፀም የማይችልበት ሁኔታ እየተፈጠረ ነው፡፡ በዚህ ምክንያት ደግሞ ፈጣን አገልግሎት ማግኘት የሚገባው የህብረተሰብ ክፍል/ባለሃበትም ጭምር/ አገልግሎት አለማግኘቱ ብቻ ሳይሆን አገልግሎቱን ማግኘት የማይገባው ጥገኛ ሃይል አገልግሎቱን እያገኘ በልማታዊ ሃይሉ ተደራራቢ ጫና እንዲያሳርፍ ያደርጋል፡፡ ይህ ደግሞ ኪራይሰብሳቢው እንዲፈረጥም በአንፃሩ ልማታዊ ሃይሉ እንዲኮሰምን ያደርጋል:: ፈጣን እድገቱ ቢቀጥልም ከእድገቱ ተገቢውን ድርሻ የማያገኝ ሃይል እየሰፋ ሲሄድ ደግሞ የቅሬታው ጥልቀት እየጨመረ ይሄዳል፡፡ ይህ አይነት ቅሬታ ሲደማመርና ጊዜ ሲወስድ ደግሞ ሁሉንም ጠራርጎ ሊወስድ የሚችል የህዝብ ማዕበል ሊያስነሳ እንደሚችል ማንም ሊጠራጠር አይገባውም፡፡ በመሆኑም የመጀመሪያው ጉዳይ መድረኩ ሁለት የማይታረቁ ሃይሎች ትንቅንቅ የሚደረጉበት መሆኑን ማስተዋል ይገባል:: በልማታዊነትና በኪራይሰብሳቢነት መካከል የሚካሄደው የሞት ሽረት ትግል በልማታዊ ዴሞክራሲያዊ መስመራችን ድል አድራጊ በሚሆንበት አቅጣጫ ሊጓዝ የሚችለው የተፋላሚ ሃይሎች ማንነትና አሰላለፍ ጥርት ብሎ ሲቀመጥና በእነዚህ ሃይሎች መካከል የሚካሄደው ትግል በአብዮታዊ ሃይሉ የበላይነት የሚጠናቀቅበት ሁኔታ ሲፈጠር ነው፡፡ በእነዚህ ሁለት ሃይሎች  የሚካሄደው ትግል በአንዱ አሸናፊነት የሚደመደም የሞት ሽረት ትግል እንጂ በዘላቂነት በአንድ ቤት የሚያኖራቸው በድርድር የሚያቀራርቡት የጋራ አጀንዳና ተጠቃሚነት የለም፡፡ በተለይም የልማታዊ ሃይሎች ጥቅም በምንም ምክንያት ከኪራይ ሰብሳቢ ሃይል በመደራደር የሚያገኘው ቅንጣት ታህል ጥቅም የለም አይኖርም፡፡ በመሆኑም የመጀመሪያው ጉዳይ በሁለቱም ሃይሎች መካከል ከሚደረገው የማህበራዊ ሃይሎች አሰላለፍ የመነጨ ትግል በልማታዊ ሃይሎች አሸናፈነት እንዲደመደም ከሆነ የልማታዊ ሃይሎች አታጋይ ድርጅት ራሱ ከጎራ መደበላለቅ የፀዳ አሰላለፍና ውስጣዊ ሁኔታ ሊኖር ይገባል፡፡ የምንገኝበትን ሁኔታ ከዚህ አንፃር መፈተሽና ትክክለኛ ድምዳሜዎችን መያዝ ይገባል፡፡

ውስጣችን ማየትና የውስጠ ድርጅት ትግል መለኮስ

የድርጅታችን መለያ ባህሪ ተደርገው ከሚወሰዱ እሴቶች አንዱ ችግሮችን ወደ ውስጥ በማየትና በመገምገም ድክመቶችን በአብዮታዊ ዴሞክራሲ ትግል ማረም ነው፡፡ ድርጅታችን በየትኛውም ወቅት የሚያጋጥሙ ችግሮችንና ፈተናዎች፣ ጨለምተኛ አስተሳሰቦችም ሆኑ ተግባራት፣ የአስተሳሰብ መዋዥቅም ሆነ የአሰላለፍ መደበላለቅ፣ የመስመር ጥራትም ሆነ ከአፈፃፀም የሚከሰት ችግር ሲያጋጥመው ሁሌ የሚገመግመው ከውስጥ ድርጅት ሁኔታ ጋር በማጣበቅ ነው፡፡አሁን ያለንበት ሁኔታና እያጋጠሙን ያሉ ችግሮች በመሰረቱ 10 ድርጅታዊ ጉባኤ የተገመገሙና በትግል ልንፈታቸው የሚገቡ ችግሮችና ድክመቶች ተብለው አቅጣጫ የተቀመጠባቸው ናቸው፡፡ በጉባኤው በመልካም አስተዳደር፣ በልማት ተደራሽነትና ተጠቃሚነት፣ በውስጠ ድርጅት ዴሞክራሲና በሌሎች ጉዳዮች የህዳሴ ጉዟችንን ሊያደናቅፉ የሚችሉ ችግሮች እንዳሉብን ተገምግሟል፡፡ ይህንን መነሻ በማድረግም በሃገር ደረጃ፣ በየክልሎችና በከተማችን አዲስ አበባ የመልካም አስተዳደርና የልማት ተጠቃሚነትና ተደራሽነት የንቅናቄ እቅድ ወጥቶ በርካታ ስራዎች ሲሰሩ ቆይተዋል፡፡ የመልካም አስተዳደርና የኪራይሰብሳቢነት ችግር መከሰቻ ማእከል ናቸው በተባሉት ሴክተሮችና የድርጅትና የመንግስት መዋቅር ትኩረት በማድረግም ሰፋ ያለ ጊዜ የወሰደ ግምገማ፣ ሂስና ግለሂስ ተደርጓል፡፡ ይህንን ተከትሎም ችግሮችን በመለየት ችግሮች የሚፈቱበት እቅድ ተዘጋጅቶና ሰፊ የአመራር ሽግሽግ ጭምር በማድረግ ሰፋፊ ስራዎች ተከናውነዋል፡፡ እየተከናወኑም ይገኛሉ፡፡ ነገር ግን እየመጣ ያለው ለውጥ በተገመገመው ልክ መቆራረጥ የሚታይበት አይደለም፡፡በከተማችን በተለኮሰው የከተማውን ህዝብ ጭምር ያካተተ ንቅናቄ ችግሮች እንዲለዩና እንዴትና መቼ መፈታት እንዳለባቸውም መግባባት መፍጠር መቻሉ በከተማዋ ቀጣይነት ያለው ልማትና ሰላም ተጨባጭ አወንታዊ ሚና እየተጫወተ መሆኑ ግልፅ ነው፡፡ ባለፉት ወራት የጥፋት ሃይሎች በከተማችን አዲስ አበባ የሁከትና ብጥብጥ ቀውስ ለመፍጠር ያልቆፈሩት ጉድጓድ ባይኖርም እንዳይሳካላቸው ያደረገው በዋነኝነት ህዝቡ ለደቂቃዎችም ቢሆን ልማቱና ሰላሙን እንዲደናቀፍ ለመፍቀድ ዝግጁ ስላልሆነ ነው፡፡ ይህ ማለት ግን የአዲስ አበበ ከተማ ህዝብም እንደሌሎች የሃራችን ህዝቦች በፍጥነት ሊፈቱለት የሚገባቸው የመልካም አስተደደር ችግሮችና የኪራይ ሰብሳቢዎች በደሎች እንዲሁም የልማት ጥያቄ ስለሌለው አይደለም፡፡ እነዚህ አንገብጋቢ ጥያቄዎች በፍጥነት እና ህዝቡን በሚያረካ መልኩ ካልተፈቱ ህዝቡ ወደ ከፍተኛ የተቃውሞ ደረጃ አይገባም ብሎ መውሰድ አይቻልም፡፡ስለሆነም ከመልካም አስተዳደርና ከኪራይ ሰብሳቢነት አንፃር ያሉ ህዝቡን ያማረሩና የድርጅታችን ማህበራዊ መሰረት ጥቅሞችና መብቶች የሚጋፉ ድክመቶች በጠንካራ የውስጠ ድርጅት ትግል በመፍታት መሰረታዊ ለውጥ ማምጣት ካልቻልን አደጋ ውስጥ እንደምንወድቅ ሁላችንም መግባባት ይኖርብናል፡፡ የሚታዩብን ድክመቶችና ችግሮች በትግል የማረም ጉዳይ ለምንታገልለት አላማ ስንል የምናካሂደውና ለጀመርነው የህዳሴ ጉዞ ቀጣይነት ብቸኛ አማራጭ መሆኑም እንደዚሁ የጋራ መግባባት ላይ ልንደርስበት የሚገባንና በቁርጠኝነት ልንተገብረው የሚያስፈልግ ጉዳይ ነው፡፡

ብረቱን ሳይቀዘቅዝ መቀጥቀጥ

በዘንድሮ የዝግጅት ምዕራፍ ተደራራቢ መድረኮች አካሂደናል፡፡ባደረገ ቅኝት መዋቅራችን ለማጥራት፣ መልሶ ለማደራጀትና ለማሸጋሸግ በዚህም መነሳሳት ለመፍጠር ጥረት ተደርጓል፡፡ በእነዚህ መድረኮችም በየአካባቢው ያሉትን የመልካም አስተዳደር ችግሮችና የኪራይ ሰብሳቢነት ተግባራትና አመለካከቶችን በአመራር፣ በፈፃሚና በአባላት መድረኮች በዝርዝር ወጥተው የመታገያ አጀንዳ ሆነዋል፡፡ ከዚህ በመነሳትም የችግሮቹ ምንጭና የመፍትሄ አቅጣጫ በማስቀመጥ ለመግባባት ተሞክሯል፡፡ እነዚህ ችግሮች በተለይም በመልካም አስተዳደርና አገልግሎት አሰጣጥ ያሉ ችግሮች፣ መንስዔዎች፣ የመፍትሄ ሃሳቦች፣ እንዴት እንደሚፈቱ፣ በማን እንደሚፈቱና መቼ እንደሚፈቱ አንጥሮ በማውጣት በመልካም አስተዳደር ሰራዊት በተሟላ መንገድ ተግባራዊ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ይህንንም የሚመራበት ራሱን የቻለ የንቅናቄ ማቀጣጠያ ሰነድም ተዘጋጅቷል፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ የህዝብ ቅሬታ ከሚቀርብባቸው ሴክተሮች ውስጥ በቀዳሚነት ከሚታዩት አንዱ መሬት ልማትና ማኔጅመንት ዘርፍ ነው፡፡ በዚህ ዘርፍ ቀደም ባሉት አመታት ይታይ የነበረው በጠራራ ፀሃይ የሚፈፀም የመሬት ወረራን ማክሰም ቢቻልም አሁንም መሬትን በአግባቡ ለታለመለት ልማታዊ ተግባር የማዋልና ህዝቡም ተገቢ አገልግሎት በፍጥነት፣ ከእንግልትና ሙስና በፀዳ ሁናቴ የማስተናገዱ ጉዳይ እጅግ አሳሳቢ ሆኖ ይታያል፡፡ በመሬት ፕላን መስተንግዶ፣ በመልሶ ማልማት ግምት አወሳሰንና ምትክ ቦታ አሰጣጥ፣ በግንባታ ፍቃድና ቁጥጥር፣ በህገወጥ ግንባታ ያለው እርምጃ አወሳሰድ ፍትሃዊነት መጓደል፣ የባለጉዳዮች የይዞታ ሰነድ በሰበብ አስባቡ ማነቅና ማጥፋት፣ ወዘተ በፍጥነት መፈታት ያለባቸው ችግሮች በመሆናቸው በዝግጅት ምዕራፉ ችግሮችን ለመለየት በተደረገው ግለት ልክ ችግሮችን የመፍታት ንቅናቄው መቀጣጠል አለበት:: ቀደም ሲል ለማብራራት እንደተሞከረው በዚህ ዙሪያ ያለውን ማነቆ አለመፍታት ማህበራዊ መሰረታችን የሆነው የከተማው ህብረተሰብና ልማታዊ ባለሃብቱን ተጠቃሚነት መጉዳት ብቻ ሳይሆን በአንፃሩ ኪራይ ሰብሳቢ ሃይሉ አላግባብ ተጠቃሚ የሚሆንበት እድል እንዲሰፋ በማድረግ በስርአቱ ላይ ተደማሪ አደጋ የሚፈጥር ሃይልን የሚመግብ ይሆናል፡፡በንግድ ዘርፉም በነጋዴው ላይ የሚታየው የግምት አወሳሰን፣ በንግድ ቤቶች የሚወሰደው እርምጃ አድሎ፣ በሙስና እና ሌሎች ኢፍትሃዊ ትስስር አላግባብ ንግድ ፍቃድ ማደስ፣ አንዳንድ መመሪያዎችና አዋጆችን ለኪራይሰብሰሳቢነት ተግባርና
አመለካከት ዋሻ አድርጎ መጠቀም፣ ወዘተ ይታያል፡፡ በቀጥታ በከተማው ነዋሪ ቤት ለቤት በሚሰጥ አገልግሎትም ተመሳሳይ የሆኑ ጉድሎቶች እንዳሉብን በተለያዩ መንገዶች ማረጋገጥ ተችሏል፡፡ ለምሳሌ በውሃና ፍሳሽ ዘርፍ ከጥገና፣ ከአዲስ መስመር ቅጥያ፣ ከቆጣሪ ንባብ የአገልግሎት ክፍያ፣ የሽንት ቤት ፍሳሽን በአግባቡ ከመምጠጥ ጋር ተያይዞ በነዋሪውም በባለሃብቱም የሚሰሙ ምሬቶች ተቃልለው የሚታዩ አይደሉም፡፡ እነዚህን ለአብነት ብናነሳም በፅዳት አስተደደር፣ በትምህርት ዘርፍ፣ በጤና ዘርፍ፣ በጥቃቅንና አነስተኛ፣ በኢንዱስትሪ ዘርፍና በሌሎች ዘርፎች በርካታ የመልካም አስተዳደርና የኪራይ ሰብሳቢነት ችግሮች አሉብን፡፡ አሁን መመዘን ያለበት የተለዩ ችግሮች በምን ያህል ፍጥነትና ጥራት እየተፈቱ ናቸው የሚል ነው፡፡ ይህ ደግሞ የእያንዳንዱ መዋቅር፣ አመራርና አባል ሃላፊነት ነው፡፡ ነገር ግን አፈፃፀማችን ሲታይ የድርጅታችን ጉባኤ አቅጣጫ የሚመጥን ፍጥነትና ግለት አለው ሊባል የሚቻል አይደለም፡፡ በድርጅታችን ጉባኤም ሆነ በከተማችን የአመቱ እቅድና የየእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዝግጅት እንደተሰመረበት ሁሉም የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በአጭር ጊዜ መፍታት እንደማይቻል በግልፅ ተቀምጧል፡፡ ይህንንም እቅድ መነሻ በማድረግም በከተማችን ከቀጠና እስከ ከተማ በተደረጉ የህዝብ መድረኮች ለመግባባት ጥረት ተደርጓል:: ነገር ግን በጊዜ የለንም መንፈስ መፈታት እንዳለባቸው የተለዩ ከባቢያዊና ከተማ አቀፍ ችግሮችን ለመፍታት የሚደረገው መነሳሳትና ርብርብ እንደሚጠበቀውና ሁሉን አቀፍ ነው የሚባል አይደለም፡፡በመሆኑም በእያንዳንዷ ሌሊት ሳትፈታ የምታድረው ችግር በማህበራዊ መሰረታችን ከፍተኛ ጉዳት የምታስከትል በአንፃሩ የኪራይሰብሳቢ ሃይሉን ይበልጥ ተጠቃሚ የምታደርግ መሆኗን በመገንዘብ እዚህም እዛም የፈታናቸውን ጉዳዮች ከመቁጠር ወጥተን ሊያስከትል የሚችለውን አደጋ የተገነዘበ ለውጥ ማምጣት ይጠበቅብናል፡፡ ብረትን በፈለጉት ቅርፅ መስራት የሚቻለው እንደጋለ ነው እንደሚባለው የራሱ ውስንነት ቢኖረውም በዝግጅት ምዕራፍ በሁሉም ሴክተሮች የተለዩ የመልካም አሰተዳደርና ኪራይሰብሳቢነት ችግሮችን የልማት ሃይሎችን መነሳሳት የሚጨምር አመራር መስጠት ይኖርብናል፡፡



No comments:

Post a Comment