የፅሁፉ ሰበብ
ከጥቂት ወራት በኋላ አምባገነኑ የደርግ ስርአት የተገረሰሰበትን 25ኛ አመት የግንቦት 20 በዓል እናከብራለን፡፡
ኢህአዴግ እንደ ድርጅት መንግስትም እንደመንግስት እስከአሁን በዓሉን እንዴት ለማክበር ማሰባቸውን ባላውቅም ዝምታው ግን አልገባኝምም
አልጣመኝምም፡፡ 25ኛ አመት ነው፡፡ ሩብ ክፍለ ዘመን፡፡ የብር ኢዮቤልዩ፡፡ በዜጎች ደም የተመሰረተች የአንዲት ዴሞክራሲያዊት ሃገር
በዓል ቀርቶ ግለ ሰቦችም ልደታቸውን በተለየ ፕሮግራም ያከብሩታል”” ምክንያቱም 25 አመት ማለት የሰው ልጅ የአፍለኛ እድሜውን አጠናቆ ራሱን ወደ በርካታ ሃላፊነቶች የሚያዘጋጅበት
ነው፡፡ ወደ ላቀ የህይወት ምእራፍ የሚንደረደርበት ነው፡፡
ለአንድ ድርጅት፣ ለአንድ መንግስት፣ ለአንድ ሃገር ሲሆን ደግሞ ከዚህ የላቀ ትርጉም አለው”” እናም 25ኛ የግንቦት በአል ሲከበር ኢትዮጵያ
በአዲስ አስተሳሰብ የተጓዘችባቸው አመታት ስኬትና ጉድለቶችን መገምገም፣ ከግምገማ በመነሳትም ለወርቅ ኢዮቤልዩ ለሚደረገው ጉዞ አቅጣጫዎች
የሚቀየሱበት ይሆናል ብዬ አስባለሁኝ፡፡ ይህ የሃሳብ ብልጫ ሰበብ ሆነብኝና ብእሬን አነሳሁ፡፡ ሃሳብ ለመጫር ያህል ማለት የምችለውን
እንሆ አልኩ፡፡
መነሻችን ምን ነበር?
መንደርደሪያችን በግርድፉ የ1960ዎቹ ትውልድ የሚባለው ነው፡፡ ያ ትውልድ፣ትውልድን ያናወጠ ትውልድ ነው ይሉታል፡፡
ተራሮችን ያንቀጠቀጠ ብለው የሰየሙትም አሉ፡፡ የሚባለውን ልድገመውና አብዮት የመደቦች መሸጋሸግና መገለባበጥ ነው የሚለው የወቅቱ
ፖለቲካ ሃይሎችና ሰዎች የወል እምነትም፣ ፍልስፍናም፣ ርዕዮትም ነበር፡፡ ሃገሪቷም በሚሳይል ፍጥነት ከስዩመ እግዚአብሄር ወደ ስዩመ
ማርክስሌኒንዝም ተስፈነጠረች፡፡
በምድረ ኢትዮጵያ የሶስቱ ስላሴዎች ልዕልና በሶስቱ ኮሚኒስቶች /ማርክስ ኤንግሊስ እና ሌኒን/ የተነጠቀች ትመስላለች፡፡
ሁሉም ሶሻሊስት ነኝ አለ፡፡ ማለትና መሆን ግን ለየቅል ነበር፡፡ አለም አቀፋዊነትን /ኢንተርናሲዮናል/ መመሪያችን ያለው ሃይል
ሁላ ገና ከመንደሩ ሳይወጣ በኢትዮጵያ ትርጓሜና ግብ ላይ ተለያይቶ ተቧቀሰ፡፡ አድዮስ አለምአቀፋዊነት!
በተምታታ እሳቤና ተግባር የኢትዮጵያ አብዮት እጅግ ቅራኔዎች የተካረሩበት ሆኖ ተመርቷል፣ ተራምዷል፣ ተተራምሷል፣
አብዮቱ ልጆቹን በልቷል፡፡ መጨረሻም የፖለቲካ ትግል የመጨረሻ ጫፍ በሆነው አፈሙዝ ትግል ተጠናቋል፡፡ ተጠናቋል ማለትም የሚቻል
ቢሆንም ቅሪላዎች ግን አልተንጠፈጠፉም፡፡ አሉ፡፡
በዚህ ምንም አይነት ለመቻቻል እድል የማይሰጥ ምህረት የለሽ የአብዮት ሂደት (እንደሚባለውም) ላይመለሱ የተደመሰሱ
ሃይሎች የነበሩትን ያህል ነገርግን ህመም የበዛበት በርካታ የቀጠሉ መቆሳሰሎችና ጠባሳዎች ትቶም አልፏል፡፡ ቀጥሏልም፡፡
እርግጥ ነው በተለይ ከገዥመደቦች ተቋማዊ ስርአት አንፃር በኢትዮጵያ ሽግሽጉ ሙሉ በሙሉ ተጠናቅቋል ሊባል ይቻላል፡፡
በ1967 ወታደራዊ ጊዚያዊ መንግስት የመንግስት ስልጣኑ በመቆጣጠሩ አብዮቱ ሽንፈት የተበየነበት አብዮት ገፅታ ቢይዝም እስከወዲያኛው
አልከሸፈም፡፡
በሌላ ገፅታው በወቅቱ ከነበረው እሳቤ አንፃር ከተመለከትነው አሮጌ ስርአትን በመደምሰስ አዲስ ስርአትን ይገነባል
በሚለው መፈክር በአሮጌው ስርአት መቃብር የላባደራዊ/ወዛደራዊ/ አምባገነንነት የተረጋጋጠበት ስርአት የመተካት እቅድ ግን በትልቁ
የአለም ፖለቲካ ለውጥ ምክንያት ከሽፏል፡፡ በዚህ የሚቆጩ ያሉትን ያህል እንኳንም የአለም ሁኔታ ተለወጠ እንኳንም አልሆነ የሚሉም
አሉ፡፡
ኢህአዴግን ጨምሮ ሁሉም በወቅቱ መመሪያችን
ማርክሲዝም ሌኒኒዝም ነው ይሉ የነበሩ ድርጅቶች ከስም በስተቀር የሶቭዮት መር የምስራቁ ዓለም ተወዳዳሪነት መፈረካከስን ተከትሎ
በሀገር ውስጥም ርእዮተአለማዊ ሽግሽግ አድርገዋል፡፡
ያደረጉት ሽግሽግ ስትራቴጂካዊ ነው ታክቲካዊም
ነው ብሎ መደምደም አይቻልም፡፡ ለጊዜው የሰው ሆዱ የወፍ ወንዱ አይታወቅም ብለን ከማለፍ በቀር መልስ መስጠት የሚቻል አይደለም፡፡
በውዴታ ብቻ ሳይሆን በግዴታም አዲሱን የአለም የፖለቲካ ሽግሽግ የተቀበሉ መኖራቸው ግን አንድ ሁለት የለውም፡፡
ከዚሁ የኢትዮጵያ አብዮትን የአለምአቀፍ
አብዮት አካል ለማደረግ ከነበረው የተለያዩ ሃይሎች መወጣጠር ባሻገር ግን በየትኛውም የትግል አግባብና ርእዮተአለማዊ አስተሳሰብም
ቢሆን መልስ ማግኘት የነበረባቸው ሃገራዊ ቁልፍና በርካታ አበይት አጀንዳዎች ነበሩ፡፡ በመሆኑም መታወቅ ያለበት እነዚህ ከርእዮተአለም
በላይ የሆኑ ሀገር በቀል አጀንዳዎች ናቸው አብዮቱን ያቀጣጠሉት እንጂ አብዮት የፈጠራቸው አይደሉም፡፡
የኢትዮጵያ አብዮት ቁልፍ አጀንዳዎች የእኩል
ተጠቃሚትና ተሳታፊነት ጥያቄዎች ሲሆኑ በመደባዊ ጭቆናና በብሄራዊ ጭቆና መልክ የሚገለፁ ነበሩ፡፡ እነዚህን ቁልፍ የህዝቦች የዘመናት
ጥያቄዎች ለመመለስ በግድ ደም ካልፈሰሰ ስርየት የለም እንደሚባለው ደም አፍሳሽ በሆነ ትግል መመለስ የነበረባቸው ባይሆኑም የሆነው
ግን ይኸው ነው”” በኢትዮጵያ ሁኔታ እነዚህን ቁልፍ ጥያቄዎች ለመመለስ ደም አፍሳሽ የሆነ የፖለቲካ ትግል ማካሄድ ግድ ያለበት
ሁኔታ የተፈጠረው ‹‹በመሬት አንድነት›› እና ‹‹በህዝቦች አንድነት›› አስተሳሰብ አራማጆች መካከል የማይታረቅ ቅራኔ ውስጥ በመግባታቸው
ነው፡፡
ሁለቱም ሃይሎች አንዱ ሌላውን ከመደምሰስ
ውጪ የያዘው አቋም ማሳካት የማይቻል ሆኖ ቅራኔው በትጥቅ ትግል ብቻ መፈታት የሚችልበት ብቸኛ እድል በመያዙም የባላባታዊ ስርአት
የሆነው የአፄዎች ስርአትን ለማስወገድ ከተከፈለው መስዋእት በላይ ያስከፈለ ትግል ማካሄድን ጠየቀ፡፡ በአብዮቱ ዘመን ትልቅ ሚና
የነበራቸው ሃይሎች በስማቸው አልያም በፕሮግራማቸው ‹‹አብዮት›› ወይም ‹‹ሶሻሊዝም›› የሚል ቃል ተቀጽላ የሚጠቀሙ አልያም የአብዮት
መገለጫ ተደርጎ የሚወሰደው የላባደር/ ወዛደር ስም ስለሚጠሩ የየራሳቸው ተከታይ ማፍራት ችለዋል”” በዚህ ሂደት በአብዮቱ አፍላ ወቅት ወታደራዊ
ደርግ የመንግስት ወንበር በመያዙ፣ ኢህአፓ ራሱን የተማሪና የወጣቱ ወካይ ሆኖ በመምጣቱ ሁለቱም የያዙት ተከታይ ከየትኛውም ቡድንም
ሆነ ድርጅት እጅግ የላቀ ነበር፡፡
ሁለቱንም ቡድኖች የሚመራው አመራር በመሰረቱ
የመሬት አንድነት አድናቂና የፍፁማዊ አንድነት አምላኪ በመሆኑ በዚህ ዙሪያ ተቃርኖ ባይኖረውም፤በኢትዮጵያ አብዮት ቁልፍ ጥያቄዎች
የነበራቸው የአተያይ ልዩነት ያንያህል የሰፋ ባልሆነበት ሁኔታ ተሸናናፊነታቸው ከተሞችን በደም ባጥለቀለቀ ትግል እንዲደመደም ሆኗል፡፡
በዚህ ወቅት ድንኳን ሰባሪው መኢሶን በመሃል በመግባት የነበረው የአጫዋችነት ሚና በፍፁም መዘንጋት የሌለበት ሆኖ እናገኘዋለን፡፡
ከላይ ለመጠቆም እንደተሞከረው የኢትዮጵያ
ህዝቦች ቁልፍ ጥያቄ የብሄር ብሄረሰቦች እኩልነት ጥያቄ ሲሆን በሀገሪቱ የነበረው የመደቦች ተቃርኖው አንድና ዋነኛ መልክም ብሄራዊ
ጭቆና ሆኖ እያለ የአብዮቱን የትግል መድረክ የተቆጣጠሩት በአንዳንዶቹ አገላለፅ ‹‹የታላቋ ኢትዮጵያ›› ተከታዮች ‹‹የፍፁማዊ አንድነት››
አምላኪዎች በመሆናቸው በብሄር ዘውግ የተደራጁ ድርጅቶች በጥቅል ‹‹ፀረ አንድነት›› የሚል ቅጥያ ተለጥፎላቸዋል፡፡
ስልጣኑን በተቆጠረው ወታደራዊ ቡድንም
ሆነ ባልተቆጣጠረው ተስፈኛው ሃይል እኩል የተገፉ ነበሩ፡፡ እነዚህ ገፍያን ቡድኖች በሶስቱም ሃይሎች የሚሳደዱ ነበሩ፡፡ በተሸነፈው
ነባር ስርአት አስመላሽ/ ኢዲዩና መሰሎቹ/፣ አዲስ ገዢ መደብ ሆኖ በአፈሙዝ ቤተመንግስቱን በተቆጣጠረው ደርግ እንዲሁም ስልጣኑ
የሚገባኝ ለኔ ነው በሚለው ኢህአፓ በሶስት አቅጣጫ የሚመቱ ቡድኖች ሆኑ፡፡
የማታማታ ግን ገፊዎች እየተፈረካከሱ ግፍዓኑ
እየተጠናከሩ መጥተው የብሄር ጥያቄ የማይሸራረፍ የህዝቦች ጥያቄ ነው ብለው በተነሱ ሃይሎች አሸናፊነት የአብዮቱ የመጀመሪያ ምዕራፍ
የሆነው የትጥቅ ትግል ከተደመደመ አንድ አራተኛ ምዕተ አመት አስቆጥሯል፡፡
የማይሸራረፍ የመሬት አንድነት ጥያቄ ወይስ
የማይሸራረፍ የህዝቦች መብት ጥያቄ መመለስ የሚችል አንድነት የሚለው አተካራ ግን ዛሬም ቢሆን ሞቶ የተቀበረ አጀንዳ አልሆነም፡፡
ዛሬም ‹‹የፍፁማዊ አንድነት ተከታዮች ዘመን›› ተመልሶ ይመጣል የሚለው ሃይል የተስፈኝነት ትግሉ አላቋረጠም፡፡ በሌላው ፅንፍ
‹‹የፍፁማዊ ነፃነት›› አቀንቃኝም ጥያቄውን አላነሳም፡፡ የፌደራል ስርአቱ በሌላ ብልሃት የመጣ የአቢሲያኒስት ተንኮል ነው የሚለውም
አልጠፋም፡፡ ‹‹የህዝቦች አንድነት›› ተከታይ አስተሳሰብ ወካይ ሃይል ደግሞ መንግስታዊ ስልጣን ይዞ የሩብ ምዕተአመት እድሜ አስቆጥሯል፡፡
በዚህ በኩል ያለው ተቋማዊ አቅምን ወደ
ጎን ትተን የአስተሳሰብ አቅም ሚዛን መገምገም ይገባል”” የህዝቦች አንድነት አስተሳሰብ ፍፁማዊ ልዕልና አረጋግጧል ወይ፤ ይህንን አስተሳሰብ ፍፁማዊ ልዕልና እንዲያረጋገጥ
ሩብ ክፍለዘመን በቂ ነው አይደለም፣ መልሱ አሉታዊ ቢሆንም አዎንታዊ ብቁና ሳይንሳዊ ምላሽ እንዲያገኝ ማድረጊያ ጊዜው አሁን ነው፡፡
በመሆኑም ከዚህ አንፃር የብሄር ተኮር ፌደራላዊ ስርአት ግንባታ ተስፋ፣ ስጋትና እውነታን የግምገማውና ምዘናው ማጠንጠኛ ማድረግ
ይገባል ብዬ አምናለሁኝ፡፡
ፌደራሊዝም ወዴት እየወሰደን ነው?
ኢትዮጵያ የብዝሃነት አገር ነች፡፡ በውስጧ
ራሳቸውን ያለምንም መምታታት ማንነታቸውን የሚገልፁ ብሄርና ብሄረሰቦች አሏት፡፡ ይህ ብዝሃነት በፍፁም በማንም ሊካድ የማይችል ቢሆንም
አሰያየሙ ላይ ግን ልዩነቶች አሉ፡፡ ብሄር፣ ዘር፣ ነገድ፣ ጎሳ የመሳሰሉ ስያሜዎች ስራ ላይ ይገኛሉ፡፡ ከእነዚህ አሰያየም በስተጀርባ
ደግሞ አመለካከት አለ፡፡ ይህ ምልከታ በራሱ ኢትዮጵያ እንዴት መዋቀር አለባት ለሚለው ትርክትም የተለያየ አማራጭ እንዲቀርብ ያደርጋል፡፡
ኢትዮጵያ የረጂም ክፍለዘመን ህልውና ያላት
ሃገር ናት የሚል የታሪክ ትርክት የምንቀበል ከሆነ ከዚሁ መሳ ለመሳ ትልቁን ድርሻ የሚወስደው አወቃቀሯ የተማከለ አስተዳደር ሳይሆን
ያልተማከለ አስተዳደር /ፌደራላዊ ይዘት ያለው/ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በተማከለ አስተዳደር እሳቤ የተዳደረችው በንጉስ ቴድሮስ /በተግባር
ባይሳካለትም/፣ ንጉስ ሚኒሊክ፣ ንጉስ ሃይለሰላሴና የደርግ መንግስት ዘመን ብቻ ነው””
ይህ ደግሞ መሃል ላይ የተሰነቀረ ከመቼውም
ዘመን ጎላ ብሎ ከታየው የንጉስ ዮሃንስ ፌደራላዊ አወቃቀር /de facto federal system/ ሁለት አስርት አመታት በስተቀር
ለአንድ ክፍለ ዘመን ተኩል የታየ ስርአተ መንግስት ነው ይላሉ ዶክተር አሰፋ ፍስሃ፡፡
በየዘመኑ የትግራይ፣ የበጌምድር፣ የጎጃም፣
የወሎ፣ የሀውሳ፣ የሸዋ ባላባቶች የአከባቢያቸው ገዥዎች እንደነበሩ የታወቀ ነው፡፡ በተመሳሳይ እንዲህ ያለ የላላ አንድነት በደቡብንና
ደቡብ ምዕራብ አከባቢም የነበረ ነው፡፡ የግቤ አምስት ነገስታት ተብለው የሚተወቁት ሊሙ ኢናሪያ፣ ጎማ፣ ጉማ፣ ጌራ እና ጅማ ተብለው
የሚታወቁትም ሙሉ በሙሉ የተለያዩ ባይባሉም ትስስራቸው ግን ፌደራላዊ መልክ ነበረው፡፡
የእነዚህ ነፃ አስተዳደር ያበቃው ሚኒሊክ
ሰኔ 14/ 1890 በእምባቦ ጦርነት የጎጃሙን ንጉስ ተክለሃይማኖትን ካሸነፉ በኋላ ነበር፡፡ በእርግጥ የግቤ ሞናርኪ ብቻ ሳይሆን
የወለጋና ኢሉባቦር ነፃ መንግስታትም ጭምር ነው ህልውናቸው ያከተመው”” የኦሞ ስልጣኔ የሆኑ እና በ14ኛና በ15ኛ ክ/ዘመን ጀምሮ የራሳቸው ህልውና እንደነበራቸው የሚገልፁ የከፋ፣
የወላይታ /ንጉሰ ጦና/፣ ሲዳማ፣ ከምባታ እና የም /ጃንጃሮ/ ነፃ ግዛቶች መኖራቸውንም መርሳት አይገባም፡፡ ነባሩ የእስልምና ሱልጣኔት
ታሪክ ያለው የምስራቁ ክፍል የአፋር፣ የሶማሊያና የሀረሪ
ኤምሬቶች ነፃ ግዛቶችም፡፡ የሀውሳ ሱልጣኔት
ስርወ መንግስት ማእከል የሆነው የአፋር ነፃ ግዛት ያከተመው በ1930 እኤ አ ሃይለስላሴ ሙሉ በሙሉ ስልጣኑን እንደተቆጣጠሩ ነበር፡፡
በተለይም ከ8ኛው ክ/ዘመን ጀምሮ የእስላም መንግስት ማእከል ብቻ ሳይሆን የምስራቅ ኢትዮጵያ የፖለቲካና ባህል ማእከል ሆና እስከ
ዘመናችን የዘለቀችውን ሀረር የመሰለ ለረጂም ክፍለ ዘመናት የቀጠለ ከተማ መንግስት /City state/ በደጋማው ኢትዮጵያም ማግኘት
አይቻልም፡፡
በዚህ ረገድ ሀረር ወደር የላትም፡፡በድምር
የታሪክና የፖለቲካ ሳይንስና ማህበራዊ ሳይንስ ተመራማሪዎች እንደሚያስረግጡት እነዛ አካባቢያዊ ግዛቶች ከማእከላዊ መንግስት ጋር
የነበራቸው ግንኙነት ሙሉ በሙሉ የተበጠሰ ነው ባይባልም ከማእከላዊ መንግስት ጋር የነበራቸው ትስስር ቀጥታዊ ያልሆነ በዋነኝነት
ግብርን በመክፈል ነበር፡፡ ዶክተር ፍስሃም በመፅሀፋቸው እንዲህ ይሉናል፤
‹‹In short, the majority
of the Kingdoms of the South, South West and Eastern sides existed as
autonomous units only indirectly associated with the center usually marked by
the payment of tributes.”
ከውጫዊ ገፅታ አንፃር ኢትዮጵያ ከሞላ
ጎደል አሁን ያለችበት ቅርፅ የያዘችው በአፄ ሚኒሊክ ዘመን ነበር፡፡ ስርአተ መንግስቷም ለአንድ ክፍለ ዘመን ተኩል አሃዳዊ ሆኖ
ቆይቷል፡፡ ከደርግ መደምሰስ ማግስት ግን ኢትዮጵያን በአንድ አሃዳዊ ስርአት ማስቀጠል እንደማይቻል ግልፅ ነበር፡፡ በፌደራላዊ ስርአት
መተዳደር ነበረባት፡፡ ይህ አንዳንድ ወገኖች እንደሚሉት የፖለቲካ ሃይሎች ጠባብ ፍላጎት የፈጠረው አይደለም”” የፌደራላዊ ስርአተ መንግስት አወቃቀር
የኢትዮጵያ ህዝብ ነባራዊና ህሊናዊ ዝግጅት ያልፈጠረው አድርጎ መመልከት የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረ ሰቦች ለዘመናት /በሰላ መልኩ ደግሞ
ለ17 አመታት/ ያካሄዱትን ትግልና መስዋእትነት ላይ የሚፈፀም ክህደት ነው፡፡
ከመንግስት ቅርፅ አንፃር በአለማችን ከሁለት
ደርዘን የማያንሱ በፌደራል ስርአት የሚተዳደሩ ሃገራት የአለም ህዝብን 40 በመቶ የሚይዙ መሆናቸውን ስንመለከት የፌደራል አወቃቀር
በአመዛኙ የትላልቅ ሃገሮች አደረጃጀት መሆኑን ልብ እንላለን፡፡ በእርግጥ በቆዳ ስፋታቸው ጠበብ ያሉ ሃገራትም የፌደራሊዝም አደረጃጀትን
ይሆነኝ ብለው የተቀበሉ አሉ፡፡
ምክንያቱም ይህንን እንዲሆን የሚገፉ ሌሎች
ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ታሪካዊና ባህላዊ የየሃገራቱ ተጨባጭ እውነታዎችም ስላሉ”” ስለሆነም በየትኛው መመዘኛም ቢሆን ኢትዮጵያ
የፌደራል ስርአተ መንግስትን መምረጧ ቅቡል ያደርገዋል፡፡ ሩዋል ብሊንደንባቸር እና ሮናልድ ዋትስ የተባሉ ፀሃፍት ፌደራሊዝምን ተመራጭ
የሚያደርገው መሰረታዊ ምክንያት ለሰላምና መቻቻል በእጅጉ ተመራጭ መሆኑ በሚከተለው መልኩ ይነግሩናል፡፡
‹In the contemporary
world, federalism as a political idea has become increasingly important as a
way of peacefully reconciling unity and diversity within a political system.›
እርግጥ ነው እንዲህ ያለ አስተሳሰብ ዘግይቶ
የመጣ እንጂ ያኔ ኢትዮeያ ወደ ፌደራላዊ ካምፕ በተቀላቀለችበት ወቅት አልነበረም፡፡ ይልቁንስ በወቅቱ የዩጎዝላቪያ ፌደሬሽን መፈረካከስ
በፌደራሊዝም ላይ መጥፎ ጥላው በጣለበት አለማዊ ሁኔታ ነበር ፌደራላዊት ኢትዮጵያ የተጠነሰሰችው፡፡ አሁን አሁን ግን የፖለቲካ መሪዎች፣
ልሂቃን እና ጋዜጠኞች ፌደራሊዝም ጤናማ፣ ዋስትና ያለውና አዎንታዊ ፖለቲካዊ ተቋም መሆኑን እየተናገሩለት ይገኛሉ፡፡ ይሉናል ከላይ
የተጠቀስናቸው ሁለቱ ምሁራን ‹‹Federalism in a Changing World›› በሚለው ስራቸው፡፡
የሆነው ሆኖ በኢትዮጵያ በፌደራላዊ አወቃቀሩ
መሰረት የውስጥ አደረጃጀቷን ማስተካከል ግድ የሚል ነበር፡፡ የፌደራሊዝም ስርአተመንግስት በአንዳንድ ሀገሮች መንግስትን የማዋቀር
አንድ መንገድ ወይም ስልት ሲሆን ብሊንደንባቸር እና ዋትስ እንዳሉት በኢትዮጵያ ግን ከዚህም በላይ የጠለቀ ትርጉም ወይም አንደምታ
አለው፡፡
እርግጥ ነው ትላልቅ ሀገሮች የፌደራሊዝምን
መንገድ የሚመርጡት በአንድ የማዕከላዊ አስተዳዳር በተዋቀረ መንግስት ማስተዳደር ከባድ ስለሚሆንባቸው ነው፡፡ በኢትዮጵያ ግን በመሰረቱ
ከዚህ መነሻ በእጅጉ የተለየ ፖለቲካዊ መነሻ ነበረው፡፡ ኢትዮጵያ በፌደራሊዝም እንድትዋቀር የተደረገችው ከፊቷ የተደቀነው በአንድነት
የመቆየትና ያለመቆየት አደጋ ስለነበረ ነው፡፡ ብቸኛው ፍቱን መድሃኒትም ያ ስለነበረ ነው፡፡ ሌላ የተሻለ አማራጭ አልነበረም፡፡
ስለሆነም የፌደራል ስርአቱ ዋና ምሰሶ
የአንድነት በልዩነት ማወቀር ነው፡፡ ይህ ግን በተለይ ‹‹በፍፁማዊ አንድነት›› አቀንቃኞች ብቻ ሳይሆን በሌሎች ዜጎችም አዲሱ አወቃቀር
ሃገሪቷን ይበታትናታል ባልካናይዜሽን በኢትዮጵያ ይታያል የሚል ጭንቀት ነበራቸው፡፡ ሟርትም ጭምር”” የፌደራሊዝም ስርአቱ ሻምፒዮን ኢህአዴግ
ግን ይልቁንስ በኢትዮጵያ ቫልካናይዜሽን የሚፈጠረው በፌደራል የማዋቀሩ ድፍረት አጥተን ካፈገፈግን ብቻ ነው የሚል እምነት ያዘ፡፡
የግንባሩ ሊቀመንበር ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ይህንን እውነት በተለያያ ሚዲያ ሲገልፁት
ተደምጧል፡፡ በአንድ ወቅት ታላቁ መሪ መለስ ዜናዊ /ጥር 2011 እ ኤ አ/ ለሮይተርስ በሰጡት ማብራሪያ የምንፈራውን ቫልካናይዜሽን
መቀልበስ የምንችለው ለብሄር ብሄረሰቦች እውቅና የሰጠ ፌደራላዊ ስርአት ስንገነባ ብቻ ነው ነበር ያሉት፡፡ እኔም በዚህ ሃሳብ መቶ
በመቶ እስማማለሁ፡፡ ለዛሬ የፅሁፌ መቋጫም ይኸው ነው፡፡
No comments:
Post a Comment