Friday, 8 April 2016

ሁሉም ለወጣቶች ተጠቃሚነት!



 “ማንን ይዞ ጉዞ” እንዲሉ የከተማችንም ሆነ የሀገራችን ልማትና ሰላም ያለ ወጣቶች የነቃ ተሳትፎ ይረጋገጣል ብሎ ማሰብ ዘበት ነው፡፡ ይሄ ደግሞ ወጣቶች ካላቸው እምቅ አቅም ጋር የተያያዘ ብቻ ሳይሆን ከተማችንም ይሁን ሀገራችን እንደ አብዛኛው ታዳጊ ሀገራት የወጣቶች ሀገር በመሆናቸው ነው፡፡ ይህ ፀጋ ነው፡፡ ይህ ፀጋ ግን በሀገር ግንባታ ሃላፊነቱን በብቃት የሚወጣው በትምህርት ሲገነባ፣ ጤናው ሲጠበቅ፣ በስነ ምግባር ሲታነፅና ተጠቃሚነቱም የሀገሪቱ ኢኮኖሚ በሚፈቅደው አቅም እያደገ ከመጣ ብቻ ነው፡፡ ወጣቱን አግላይ የሆኑ አስተሳሰቦችና ሀገራዊ ፖሊሲዎች በአሳታፊ አስተሳሰቦችና ፖሊሲዎች ሲተኩ ብቻ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ የህግ ማዕቀፎች ወሳኝ ድርሻ አላቸው፡፡ በሀገራችን ወጣቶች እንደማንኛውም የህብረተሰብ ክፍል መብቶቻቸው ህገ መንግስታዊ ዋስትና አግኝተዋል፡፡ ወጣቶችን በተለየ ሁኔታ የሚያስተናግዱ ፖሊሲዎችና ፓኬጆችም ተቀርፀዋል፡፡
የወጣቶችን ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ተሳትፎ ለማሳደግና ተጠቃሚነታቸውንም ለማረጋገጥ በሀገራችን ታሪክ የመጀመሪያ የሆነው ሀገር አቀፉ የወጣቶች ፖሊሲ በ1996 ዓ.ም ተቀርፆ ስራ ላይ ውሏል፡፡ የፖሊሲ አቀራረፁ በራሱ በሚሊዮን በሚቆጠሩ ወጣቶችና የሚመለከታቸው አካላት በስፋት እንዲሳተፋበት ነበር የተደረገው”” ወጣቶች በዴሞከራሲያዊ አመለካከት ብዝሀነትን በመቀበልና በማክበር ለሀገር ግንባታ ድርሻቸውን እንዲወጡ እየተደረገ ነው”” በተደራጀ መንገድ ተጠቃሚነታቸውን እንዲያረጋግጡ በርካታ የገጠርና የከተማ ወጣቶችን ማዕከል ያደረጉ እቅዶች ስራ ላይ ውለዋል፡፡ በተፈጠረላቸው ምቹ ሁኔታም “የበይ ተመልካች” ከመሆን ወጥተው በየደረጃው ከልማቱ እየተቋደሱ ይገኛሉ፡፡
የወጣቶችን ፖሊሲ ባገናዘበ መልኩም በመጀመሪያው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዘርፈ ብዙ የሆኑ የወጣቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት የሚያሳድጉ ስራዎች ተሰርተዋል፡፡ በከተማችንም በተመሳሳይ የአዲስ አበባ የወጣቶች የእድገት ፓኬጅ ተቀርፆ ተግባራዊ ሲደረግ ቆይቷል፡፡
በመጀመሪያው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ትግበራ ወቅትም ከወጣቶች ተጠቃሚነት አንፃር ብርሃን ፈንጣቂ ተግባር ተከናውኗል፡፡ በዚህም በጥቃቅንና አነስተኛ ዘርፍ ብቻ ለ735 ሺህ 722 የህብረተሰብ ክፍሎች የስራ እድል የተፈጠረ ሲሆን በዚህም 70 በመቶ ተጠቃሚ የሆኑት ወጣቶች ናቸው፡፡ በአምስት አመት ውስጥ ብቻ ወጣት አንቀሳቃሾች የ3 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር የብድር አገልግሎት ተጠቃሚ መሆን ችለዋል፡፡ ከ1 ሺህ በላይ ሼዶች ተገንብተው በርካታ ወጣቶች ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡ በተመሳሳይም በትምህርትና በጤናውም ዘርፍ ከተደራሽነትና ከአገልግሎት አሰጣጥ ጥራት አኳያም ወጣት ተኮር እንዲሆኑ ማድረግ ላይ አበረታች ስራዎች ተከናውነዋል፡፡
በአሁኑ ሰአት በከተማችን ለወጣቶች የቤተ መፅሀፍት፣ የስነ ተዋልዶ፣ የኮምፒውተር ስልጠና፣ የኢንተርኔት፣ የሻወር፣ የካፍቴሪያ፣ የዲኤስቲቪ፣ የቤት ውስጥ ጨዋታዎችና ሌሎችንም አገልግሎቶች የሚሰጡ 102 ወጣት ማዕከላት ተገንብተው አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ፡፡ ከዛሬ 24 አመት በፊት አምስት ብቻ የነበሩት ቤተመፅሀፍት አሁን ላይ 80 ደርሰዋል፡፡ 61 የስፖርት ሜዳዎችና አንድ ጂምናዚየምም ተገንብቷል፡፡ በፖለቲካ ተሳትፏቸውም አሁን ላይ በክፍለ ከተማና በወረዳ ደረጃ አብዛኛው የአመራር ቦታ በወጣቶች የተሸፈነ ሲሆን በየደረጃው በሚገኙ ምክር ቤቶች 30 በመቶ የሚሆነውን መቀመጫ ይዘዋል፡፡
ውጤቱ ወጣቶችና መንግስት ተቀራርበው በጋራ የመስራታቸው ስኬት ነው፡፡ በየጊዜው በሚካሄዱ ውይይቶች ከተጠቃሚነታቸው አኳያ ጎደለ የሚሉትን በግልፅ በማቅረብና ለተግባራዊነቱም በጋራ በመንቀሳቀሳቸው የተገኘ አንፀባራቂ ድል ነው፡፡ የከተማ አስተዳደሩ በየወቅቱ በየደረጃው ከሚገኙ ወጣቶች ጋር ውይይት በማድረግና የሚነሱ ሀሳቦችን ከወጣቶች ጋር በመሆን ወደ ተግባር በመቀየር ከተማዋን በፈጣን የእድገት ግስጋሴ ላይ አስገብተዋል፡፡
ነገር ግን ወጣቶችን በከተማውና ሀገራቸው ጉዳይ ተሳታፊና ተጠቃሚ ከማድረግ አንፃር የተሰራው ስራ የተለያዩ ጉድለቶች የሚታዩበት ነው፡፡ ወጣቱ በሀገር ግንባታ ያለው ሚና ከተሳታፊነት ወደ ባለቤትነት ማሳደግ ግድ ይላል፡፡ የወጣቱን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ተብለው የሚቀረፁ እቅዶችም ሆነ የሚገነቡ ተቋማት በርካታ ጉድለቶች ያሉባቸው ናቸው፡፡ በአጠቃላይ የተሳታፊነትና የተጠቃሚነት ጉዳይ ከራሱ ከወጣቱም እንዲሁም ከመንግስት በኩል የሚታዩ በፍጥነት መታረም ያለባቸው ጉድለቶች አሉት፡፡ እነዚህ ጉድለቶች ፈጥኖ ለመፍታት ደግሞ ቀርቦ መነጋገር ያስፈልጋል፡፡
የዚህ አካል የሆነውና ከአንድ ሺህ በላይ የከተማችን ወጣቶች የተሳተፉበት የወጣቶች የተሳትፎና የንቅናቄ ኮንፈረንስ በቅርቡ በኮኮብ አዳራሽ ተደርጓል፡፡ ለሁለት ቀን ያክል በተደረገው የውይይትና የምክክር መድረክ ወጣቶች እንደ አካባቢያቸው ተጨባጭ ሁኔታ በርካታ ጥያቄዎችን አቅርበዋል፡፡ ከተጠቃሚነታቸው አኳያ እየተሰሩ ያሉ በርካታ ተግባራትንም አንዳንድ አካላት እንደሚሉት “አይኔን ግንባር ያድርገው ምንም ለውጥ አይታየኝም” አላሉም፡፡ ይልቁንም እየተከናወኑ ያሉ ዘርፈ ብዙ ተግባራትን በአይናችን እያየን ስለሆነ ሌላ ምስክር አንሻም አሁንም ግን እየጨመረ የመጣውን የወጣቱን ፍላጎት ለማርካት ከዚህ በላይ መስራት ይጠበቃል የሚል ይዘት ያለው ሚዛናዊ ሀሳቦች ተንሸራሽረዋል፡፡
በመጀመሪያው ቀን በየክፍለ ከተማቸው የሞቀ ውይይት በማድረግ ሀሳቦቻቸውን ተጋርተዋል”” የተነሱ ጥያቄዎች በቡድን አወያዮች ምላሽ ተሰጥቶባቸው በተሻለ መግባባት የተጠናቀቀ ሲሆን የከተማ አመራሩን የሚመለከቱ ነጥቦች ደግሞ በየቡድኑ ተለይተው በሀይል መደረኩ ቀርበው ተገቢውን ማብራሪያ ከማግኘታቸውም በላይ ለቀጣይ ስራዎች በግብአትነት ተይዘዋል፡፡
በሀይል መድረኩ የቀረቡ ጥያቄዎች ጠቅለል ብሎ ሲታዩ ወጣቶች በጥቃቅንና አነስተኛ ከምንም ተነስተው ተጠቃሚ መሆን ቢችሉም ከተደራጁ በኋላ ክትትልና ድጋፍ ያንሳል፣ የስራ እድል ተጠቃሚው ቁጥርስ ምን ያህል ትክክል ነው፣ በርካታ ወጣት ማዕከላት ቢገነቡም የተሟላ አገልግሎት መስጠት ላይ የሚሰተዋለው ክፍተትና የመዝናኛና ማዘውተሪያ ቦታዎች ከወጣቱ ፍላጎት አንፃር ተመጣጣኝ አለመሆናቸው፣ የትምህርት ጥራት አለመረጋገጡና በትምህርት ቤት አካባቢ ሺሻና ሌሎች አዋኪ ነገሮች መኖራቸው፣ የብድር አቅርቦት ማስያዣ በዝቷል፣ 20 በመቶ እንዲቆጥቡ መደረጉ አቅም የሌላቸውን አያበረታታም፣ ልማታዊው መንግስት በርካታ ለውጦችን እያመጣ ቢሆንም ለዚህ እንቅፋት የሚሆኑትን የመልካም አስተዳደር ችግሮችና ኪራይ ሰብሳቢነት በከተማችንም በሀገራችንም አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሰዋል፡፡ በዚህ ላይ የከተማ አስተዳደሩ ምን አስቧል? ከተለያዩ ክልሎች እየፈለሱ የሚመጡ ወጣቶች ለወንጀል ድርጊት ተጋላጭ እየሆኑ ነው ከዚህ ላይስ ምን ታስቧል? የሚሉና ሌሎችም ተያያዥነት ያላቸው ጥያቄዎች ቀርበው በሚመለከተው አካል ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል፡፡
የአዲስ አበባ ኢህአዴግ ኮሚቴ ጽሕፈት ቤት ሃላፊ አቶ ተወልደ ገብረፃድቃን ለተነሱ ሀሳቦች ማጠቃለያ ሰጥተዋል፡፡
የስራ አጥ ቁጥሩን በሚፈለገው ደረጃ መቀነስ ያልተቻለው በመንግስት ይህንን ተግባር እንዲመሩት ሀላፊነት የተሰጣቸው ተቋማት በስራ አጥልየታ፣ የስራ አማራጭ መለየት ላይና የአመለካከት ለውጥ ማምጣት ላይ በተቀናጀ መንገድ ባለመንቀሳቀሳቸው መሆኑን ይገልፃሉ፡፡ ነገር ግን በወጣቱ ላይ ያለው የአመለካከት ችግርም መዘንጋት የለበትም ይላሉ””
እንደሚወራው የስራ እድል ተፈጥሯል ወይ ለተባለው ጥያቄ የተደራጀ መረጃ አለመኖሩ እንጂ የስራ እድል ፈጠራው ከሚባለውም በላይ መሆኑንና ይህ ባይሆን ኖሮ በከተማችን አሁን ላይ ያለው ልማት፣ ሰላምና መረጋጋት የማይታሰብ እንደነበር አቶ ተወልደ አስምረውበታል፡፡
በከተማችን ከክልሎችም በተለየ መልኩ በዚህ አመት ብቻ 1 ሺህ 300 የመሰናዶ መምህራንን ከሶስት ዩኒቨርስቲዎች ጋር በመተሳሰር የሁለተኛ ዲግሪያቸውን እንዲማሩ መደረጉ በአንድ በኩል የመምህራንን አቅም በማሳደግ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ በሌላ በኩል ደግሞ በዚያውም ደሞዛቸው ስለሚጨምር የመምህራንን ጥቅም ከማረጋገጥ አኳያ ከሚሰሩ በርካታ ስራዎች መካከል ማሳያ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡
ከተለያዩ ክልሎች እየፈለሱ ለተሻለ ህይወት ወደ ከተማችን የሚመጡ ወጣቶች በከተማችን ወጣቶች የስራ እድል ተጠቃሚነት ላይም ተፅዕኖ መፍጠራቸው እርግጥ ነው ያሉት አቶ ተወልደ ዋናው መፍትሄው ግን ክልሎች ሰፊ የስራ እድል እንዲፈጥሩ ማድረግ መሆኑን አስገንዝበዋል”” ቅድሚያ ለከተማችን ወጣቶች ቢሰጥም ከሌሎች አካባቢዎች የሚመጡ ወጣቶችም መዲናቸው ስለሆነችና ለከፋ ስደት ከሚዳረጉትም ይሄ የተሻለ በመሆኑ ጉልበታቸውንና እውቀታቸውን ተጠቅመው ተጠቃሚ የሚሆኑበት ሁኔታ ግን መኖሩንና በቀጣይም በዚሁ መንገድ እንደሚቀጥል ሃላፊው አብራርተዋል፡፡
በመጨረሻም ከመልካም አስተዳደር ችግሮችና ፀረ ኪራይ ሰብሳቢነት ትግሉ ላይ ወጣቶች በስፋት መሳተፉ እንዳለባቸውና በተለይም ሰላም ከሌለ ለውጥም ልማትም ስለማይታሰብ በንቃት ሊጠብቁት እንደሚገባ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
20 በመቶ እንዲቆጥቡ ቅድመ ሁኔታ መቀመጡ ለደንበኛው ዋስትና በመስጠት ተጨማሪ የሚፈልገውን ብድር እንዲያገኝ ያስችላል ተብሏል”” ከአቅም ጋር የተያያዘውን ችግር ለማቃለልም በአንድ ላይ የሚደራጁ ወጣቶች አንዳቸው ለአንዳቸው ዋስ የሚሆኑበት ማለትም የጠለፋ ዋስትና እና ሌሎች አማራጮችም መኖራቸውን ለወጣቶች ግልፅነት ተፈጥሯል፡፡ ኮንፈረንሱ ከመጀመሪያው እስከ መጨረሻው በሞቀ ተሳትፎና ተነሳሽነት ነው የተካሄደው፡፡
ከምንም ተነስተው ውጤታማ የሆኑ ሶስት ወጣቶች ተሞክሯቸውን ሲያቀርቡ ከተሳታፊዎች ከፍተኛ ሙገሳ ተችሯቸዋል፡፡ ከነዚህ ውስጥ ቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 7 ጥረት የመኪና እጥበትን ወክሎ የመጣው ወጣት ብሩክ ማርቆስ ይገኝበታል፡፡ በ1997 ዓ.ም አራት ሆነው በጠለፋ ዋስትና 8 ሺህ ብር ተበድረው ስራ መጀመራቸውንና 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በማስመዝገብ በሁለተኛ ዙር ወደ መካከለኛ ኢንተርፕራይዝነት መሸጋገራቸውን ተናግሯል፡፡ ከዚህ ስኬት ለመድረስ በርካታ ችግሮችን እንደተጋፈጡና በተለይም ከማንኛውም ሱስ ነፃ መሆናቸው በትዕግስት ለማለፍ እንዳስቻላቸው ሲናገርም በአፀፋው ከፍተኛ ጭብጨባ ለግሰውታል፡፡ በስራ ምክንያት ዱባይ፣ ጀርመን፣ ጣሊያን፣ ግሪክ፣ ፈረንሳይ፣ ስፔን፣ ቻይና የመሄድ እድልም እንዳገኘ ሲናገር ለተሳታፊዎች ግርምትን ፈጥሯል፡፡
እኛም የስኬታችሁ ምስጢር ምን ይሆን ስንል ጥያቄ አቅርበንለት ነበር፡፡ ቁርጠኝነትና የአላማ ፅናት በመያዝ ከተደራጁበት የመኪና እጥበት በተጨማሪ ሌሎችን ስራዎችንም እንደሚያከናውኑና በሂደትም የመኪና አስመጭነት ፈቃድ በመውሰድ ባለፈው አመት ብቻ ከ40 የማያንሱ መኪናዎችን በዚህ አመትም እስከምንገኝበት ወር 30 የሚሆኑ መኪኖችን በማስገባት እየሸጡ እንደሚገኙ ነገረን፡፡
በቀጣይም 52 ሰራተኞችን በመቅጠር የስሚንቶ ውጤቶችን ለማምረት ባቀረቡት ጥያቄ መሰረት አንድ ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ እንደተፈቀደላቸውና በቅርቡም በዚሁ ዘርፍ ለመሰማራት መዘጋጀታቸውን ይናገራል፡፡
ወጣት ቆንጅት ታገሰ ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ከወረዳ አራት ነው የመጣችው፡፡ ኮንፈረንሱ የተለያዩ ሀሳቦች በግልፅ ተነስተው በቂ ማብራሪያ የተሰጠበት በመሆኑ የተሻለ ግንዛቤና ተነሳሽነት እንደፈጠረላት ትናገራለች፡፡ በመድረክ ምላሽ የተሰጠባቸውን ጥያቄዎች ክፍለ ከተሞችና ወረዳዎች ታች ላይ ወርደው በተግባርም ሊመልሷቸው እንደሚገባ አሳስባለች፡፡
መድረኩ በቀጣይ አምስት አመት ተግባራዊ ለሚደረገው የወጣቶች የእድገት ፓኬጅ በግብአትነት የሚጠቅሙ በርካታ ልማታዊ ሀሳቦች የቀረቡበት ነው ያሉን ደግሞ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ ዮናስ አረጋይ ናቸው፡፡
ከወጣት ማዕከላት አገልግሎት አሰጣጥ ጋር ተያይዞ የሚታየውን ክፍተት ለማረም ቢሮው የተለያዩ እርምጃዎችን መውሰድ መጀመሩን ይናገራሉ፡፡ ለአብነትም ጃንሜዳ የሚገኘውን ወጣት ማዕከል የአዲስ አበባ ወጣቶች ፌዴሬሽን እንዲያስተዳድረው እንቅስቃሴ መጀመሩንና በሌሎችም ክፍለ ከተሞች ተመሳሳይ አሰራርን በማስፋት ወጣቶች በቅርበት እንዲከታተሉት የማድረጉን ስራ እንደሚያስፋፋ አመላክተዋል””
ከስፖርት ማዘውተሪያ ቦታዎች ጋር ተያይዞ የሚነሳውን የተደራሽነት ችግር ለመፍታትም ወጣት ማዕከላት በአጠገባቸው 3 በ1 ሜዳ እንዲኖራቸው ለማድረግ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ነግረውናል፡፡
መጋቢት 19 እና 20 በወረዳ ደረጃ አጠቃላይ ከ60 ሺህ በላይ ወጣቶች ከአካባቢያቸው ተጨባጭ ሁኔታ አንፃር ጥያቄዎቻቸውን በስፋት እንዲያቀርቡ ውይይት ይደረጋል፡፡ በዚህም ወረዳው በምን በምን ዘርፎች ለወጣቶች የስራ እድል ለመፍጠር ማቀዱን ያስረዳል፡፡ በስራ ላይ የሚታዩ የመልካም አስተዳደርና የኪራይ ሰብሳቢነት ችግሮችንም ትግል በማድረግ በከተማ ደረጃ እንደተካሄደው ሁሉ ስኬታማ ውይይት በማድረግ ወጣቶች የተሻለ የስራ ተነሳሽነት ይዘው እንደሚወጡ ይጠበቃል፡፡

No comments:

Post a Comment