Sunday, 10 April 2016

አመራሩና ፈፃሚው ለጋራ ዓላማ የተነሱበት መድረክ



ጋቢት 10 በአዲስ አበባ ቲያትርና ባህል አዳራሽ የከተማው የመንግስት ሰራተኛው ለታላቅ ጉዳይ ተሰባስቧል፡፡ አዳራሹ ካፍ እስከ ገደፍ ጢም ብሎ በሰው ተሞልቷል”” ወጣቶች፣ ጉልማሶች፣ መምህራን፣ የጤና ባለሙያዎች፣ የፋይናንስ ባለሙያዎች … የማይታይ የሙያተኛ አይነት የለም፡፡ መቼ ይህ ብቻ የከተማው ከፍተኛ አመራሮችና የቢሮ ሃላፊዎች፣ ክቡር ከንቲባው ጭምር በአዳራሹ ተገኝተዋል፡፡ ምናልባት ይህ አዳራሽ በቅርብ አመታት ውስጥ ይሀን ያህል ብዛት ያለው ሰው አስተናግዶ የሚያውቅ አይመስለኝም፡፡
መቀመጫ ወንበር ያጣው በየደረጃው ላይ ተደራድሯል፡፡ በየግድግዳው ጥግ የቆመውንም ቤቱ ይቁጠረው፡፡ የአዳራሹ ሙቀት ገና ከማለዳው ከፍ ብሏል፡፡ ሙቀቱ ከባህር ጠለል በላይ 2400 ሜትር ከፍታ ላይ የምትገኘው አዲስ አበባ ነው ብሎ መውሰድ እጅጉን ይከብዳል፡፡ ሀቁ ግን ይሄ ነው፡፡ ሙቀቱ ጨምሯል፡፡ ገሚሱ ሙቀቱን ለመከላከል ኮትና ሹራቡን ያወልቃል፡፡ ገሚሱ ማስታወሻ ደብተሩን ያገላብጣል፡፡
በእለቱ የመንግስት ሰራተኛውና አስተዳደሩ ለአንድ አለማ ነበር የተገናኙት፡፡ ይህም ህዝብ ተጠቃሚ የሚሆንበትን ልማትና እድገት ይበልጥ በማረጋገጥና የተጀመረውን የመልካም አስተዳደር ችግር ከስሩ መንግሎ የመጣል ስራ በጋራ እንነሳ የሚልና በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች እየተመዘገበ ያለውን ሁሉን አቀፍ እድገትና የታዩ ክፍተቶችን በተመለከተ በከተማው ውስጥ ካሉ የአስተዳደሩ ሰራተኞች ጋር ለመምከር ነው፡፡ ውይይቱን ያዘጋጀው የፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ ነው፡፡ ለሁለት ተከታታይ ቀናት የቆየው ይህ ውይይት ከ1200 በላይ ሰራተኞች በ8 የተለያዩ ቡድኖች በመከፋፈል ተሳትፈውበታል፡፡ በቡድን ውይይቶቹ የሞቀ ውይይትና ክርክር ተካሂዷል፡፡
በአብዛኛውም የጋራ መግባባት ላይ በመድረስ ነበር ወደሀይል መድረኩ የቀረቡት፡፡ በሀይል መድረኩ የየቡድኑ ተወካዮች ቡድናቸውን በመወከል አጠቃላይ የቡድን ውይይታቸውን ይዘት አቅርበዋል፡፡ የመኖሪያ ቤት ችግር፤ የኑሮ ውድነት፤ የሰራተኛውና የመምህራን ጥቅማ ጥቅም፤ የትምህርት ጥራት በተመለከተና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ ጥያቄዎችም ቀርበዋል፡፡ በተጨማሪም በከተማው የሚታዩ ችግሮች መነሻቸው የመልካም አስተዳደር ችግር ነው፤ አንዳንዶቹም በግልፅ ካለመወያየት የመነጩ ናቸው፤ በመንግስት ሰራተኛው የስራ ዝውውርና የቅጥር ሁኔታ ላይ በፖለቲካ አመለካከትና በብሄረ የሚሰሩ ስራዎች አሉ፤ የመልካም አስተዳደር ችግር ሲፈጥሩ የነበሩ ሰዎች ወደ ካቢኔነት መጥተዋል፤ ከአንድ ቦታ በግምገማ ያነሳችሁትን አመራር ወደ ሌላ የተሻለ ቦታ ትመድባላችሁ የሚሉ ሀሳቦችም ተንፀባርቀዋል፡፡
ከመንግስት ሰራተኛው ለተነሱ የተለያዩ ጥያቄዎች ከመድረክ ምላሻቸውን የሰጡት የፐብሊክ ሰርቪሰና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ ሃላፊው አቶ ይስሀቅ ግርማይ ናቸው፡፡ በዘንድሮው አመት ከምን ጊዜውም በተለየ ሁኔታ የከተማችንን የለውጥ ጉዞ ወደ ህብረተሰባዊ የእድገትና ስርነቀል ለውጥ እንቅስቃሴ በማሳደግ ዘላቂ ልማታዊ አስተሳሰብና ተግባር የመገንባት ስራ ከፍተኛ ትኩረት የተሰጠው ጉዳይ ነው ይላሉ ሃላፊው፤፤፤ዐዐ፡አስተዳደሩ ባለፉት አመታት የመንግስት ሰራተኛውን የትምህርት ደረጃ ለማሻሻል በራሱ ወጪ ከሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርስቲ ጋር በመተባበር ከመጀመሪያ ዲግሪ እስከ ሁለተኛ ዲግሪ ድረስ ለ658 የመንግስት ሰራተኞች ሙሉ ደሞዝ እየከፈለ ማስተማሩን ለማሳያነት አንስተዋል፡፡

ይህ ተግባር በዘንድሮው አመትም ተጠናክሮ ይቀጥላል የሚሉት ሃላፊው በዘንድሮውም አመት እንዲሁ ከኮተቤ ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ 153 ያህል ሰልጣኞች በመጀመሪያ ዲግሪ፣ እንዲሁም 46 የማስተርስ ዲግሪና 2 የዶክትሬት ዲግሪ እጩ ተማሪዎችን በሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ በማስተማር ላይ መሆናቸውን ነው የገለፁት፡፡ ይህ አሀዝ መምሀራን አይጨምርም ያሉት ሃላፊው በክረምት ወደ ትምህርት ገበታ የሚገቡትን መምህራን ቁጥር ሲጨምር በብዙ እጥፍ ከፍ እንደሚል ነው የተናገሩት፡፡
መንግስት የሰራተኛውን የትምህርት ደረጃ ለማሻሻል እያወጣ ያለው ወጪ ከፍተኛ ሀብት ነው ይህንን የመንግስት ሰራተኛው ከግንዛቤ ሊያስገባው ይገባል በማለት ምላሻቸውን ሰጥተዋል፡፡ መልካም አስተዳደርን ማስፈን ለአመራሩ ብቻ የሚተው ጉዳይ አይደለም፤ ሰራተኛውም የድርሻውን ሊወጣ ይገባል ሲሉ ተጨማሪ ሀሳብ ሰጥተዋል፡፡
በብሄር የስራ ቅጥር ይፈፀማል የሚለው አዲስ አበባን በፍፁም የሚመለከት አይደለም፤ ቢሮው የለየው ዋናው ችግር ዝውውር፣ እድገትና ቅጥር በሚፈፀምበት ጊዜ መመሪያና ደንብን ሳይጠብቁ የሚፈፀሙ ቅጥሮች መኖራቸውን ነው ይላሉ፡፡ በተግባር የተገኙ ችግሮች አሉ ብለዋል፡፡ ለአብነት ባለፉት 10 ወራት ውስጥ ከተፈፀመው 10 ሺህ 97 ያህል ቅጥር ውስጥ ስንፈትሽ 499 የሚሆኑ ከህግና ስርአት ውጪ የተፈፀሙ ቅጥሮችን አግኝተናል፡፡ ቅጥሩ በቀጥታ ውድቅ እንዲሆን ነው ያደረግነው፡፡ ውድቅ ብቻ ማድረግ ሳይሆን ይህን ቅጥር የፈፀመው አካል በህግ ተጠያቂ እንዲሆን ተደርጓል፡፡ ስለዚህ ሲቪል ሰርቪሱ ከአድሎ ነፃ ነው፡፡
የፖለቲካ አመለካከትን መሰረት ያደረገ የቅጥር የዝውውር፤ የደረጃ እድገት ስራ አይሰራም፡፡ መመዘኛችን አጠቃላይ የትምህርት ደረጃና ዝግጁነቱን የአገሪቱን ፖሊሲና እስትራቴጂ የማስፈፀም አቅምን መሰረት ያደረገ አሰራር ነው የምንከተለው፡፡ በመንግስት ሰራተኛችን ውስጥ አባል የሆነ፤ አባል ያልሆነ፤ ገለልተኛ የሆነ ሊኖር ይችላል፡፡ ይህን ሁሉ ያቀፈ ነው የመንግስት ሰራተኛው፡፡ የእኛ የምዘና አሰራር ውጤት ተኮር ነው፡፡ የተሻለ የሰራ የሚሸለምበት፤ ወደኋላ የቀረ የሚደገፍበት ነው፡፡ የፈለገውየፖለቲካ አመለካከት ሊኖረው ይችላል፡፡ ሆኖም ግን አሁንም በተጨባጭ የሚታዩ ችግሮች ካሉ አጣርተን እርምጃ የማንወስድበት ምንም ምክንያት የለም ነው ያሉት፡፡ በምላሻቸው አመራሩም ሆነ ሰራተኛው የህዝብ አገልጋይ ነው ያሉት አቶ ይስሀቅ በመልካም አስተዳደር ጉዳይ ለተፈጠረው ችግር ሁለቱም የድርሻቸውን ይወስዳሉ ብለዋል፡፡
የማጥራት ስራውን በሰፊው ጀምረናል፤ ቁጥራቸው ጥቂት ቢሆንም አሁንም ህዝቡን የሚያንገላቱ ተገቢ አገልግሎት የማይሰጡ እንዳሉ ከህዝቡ ጋር በነበረን መድረክ ለይተናል፡፡ እነዚህም ላይ የማጥራት ስራው ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡ በመሬትና በደንብ ላይ የጀመርነውን ስራ በንግድ፤ በትራንስፖርት በቤቶች ላይም እንዲሁ በንድፈ ሀሳብ ብቻ ሳይሆን በተግባር የማጥራት ስራውን ከዳር እናደርሳለን፡፡ እስከ አሁን የሰራነው ስራ ከህብረተሰቡ ጥያቄ አንፃር በቂ ባይሆንም በጅምር ደረጃ ግን ጥሩ የሚባል ነው፡፡ የህብረተሰቡም አስተያየት በርቱ ከጎናችሁ ነን የሚል ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡ አያይዘውም በድለላ በኪራይ ሰብሳቢነት ችግር ውስጥ ያለ አመራር በካቢኔነት ተሹሟል ለሚለው አስተያየት ይህ የማይሆን ነው ሲሉ ምላሻቸውን ሰጥተዋል፡፡
ምክንያቱም ድለላ ባለቤቱ ሌላ ነው፡፡ አመራር ባለቤት አለው፡፡ አሁንም በተቻለ መጠን አጥርተን በደረስንበት ልክ እርምጃ ወስደናል፡፡ ይህ ሲባል በአመራር፤ በሰራተኛ ላይ ሊሆን ይችላል በተጨባጭ የድለላ ስራ ውስጥ የገባ ካለ በየጊዜው እያጠራን እንሄዳለን፡፡ ስርአታችን እራሱን በራሱ ማጥራት ባህል ስላለው የማናስተካክልበት ምንም ምክንያት የለም”” አስተዳደሩ በምንም ምክንያት ደላላ የሆነ አመራር ካቢኔ የሚያደርግበት ምንም አይነት ፖለቲካዊ ምክንያት የለም፡፡ ሊኖርም አይችልም ነው ያሉት፡፡ በኪራይ ሰብሳቢነት የተገመገመ፤ የስነ ምግባር ችግር ያለበትን ወደኋላፊነት ያመጣንበት ሁኔታ የለም፡፡
በተመሳሳይ ከመኖሪያ ቤት ችግር ጋር ተያይዞ ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሻቸውን የሰጡት አቶ ይድነቃቸው ዋለልኝ የአዲስ አበባ ቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ ሃላፊ ናቸው፡፡ ባለፉት 10 አመታት ከ140 ሺህ በላይ በላይ ቤቶች ተገንብተው ለነዋሪዎች ማስተላለፍ መቻሉ ለከተማው አስተዳደር ትልቅ ድል ነው ብለዋል፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥ የመንግስት ሰራተኛውን የቤት ችግር ለማቃለል ለመንግስት ሰራተኛው ብቻ የ20 በመቶ የልዩ እጣ ተሳታፊ እንዲሆን ወስኖ እየሰራነው ብለዋል፡፡ በዚህ መሰረትም በ2007 ዓ.ም በመጋቢት ወር በወጣው 10ኛው ዙር የቤት ማስተላለፊያ እጣ ብቻ ከተመዘገቡ 18 ሺህ የመንግስት ሰራተኞች ውስጥ ከ10 ሺህ 200 በላይ ሰራተኞች የቤት ባለቤት እንዲሆኑ መደረጉን ተናግረዋል፡፡
በቤት ፈላጊ ምዝገባ ወቅት የተመዘገበው አጠቃላይ ቤት ፈላጊ ከ900 ሺህ በላይ ነው ያሉ ሲሆን ቤቱን ገንብቶ ለማሰረከብ ከ300 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ ይጠይቃል ነው ያሉት፡፡ ይህ ወጪ ለህዳሴ ግድብ ከሚያስፈልገው አጠቃላይ ወጪ 3 እጥፍ ማለት ነው ሲሉ የፕሮጀክቱን ግዝፈት ያሳያሉ፡፡ ይህን ለማድረግ ደግሞ ረጅም ጊዜ፤ ግዙፍ የፋይናንስ አቅም ይጠይቃል ብለዋል፡፡ ሆኖም የከተማው አስተዳደር የቤት ችግሩን ለመቅረፍ ሌት ተቀን እየሰራ ነው ያሉ ሲሆን በአሁኑ ሰአት እንኳ 40 በ60ን ጨምሮ 172 ሺህ ቤቶች በግንባታ ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ እስከ አሁንም የከተማ አስተዳደሩ ከ35 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ አድርጎ ግንባታቸውን በማገባደድ ላይ ይገኛል ነው ያሉት፡፡
ከትምህርት ጥራትና ተደራሽነት ጋር ተያይዞ ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሻቸውን የሰጡት የትምህርት ቢሮው ምክትል ሃላፊ አቶ ሀ/ስላሴ ፍሠሀ ናቸው፡፡ የትምህርት ጥራትን በተመለከተ የሚፈለገውን ውጤት ለማምጣትም የትምህርት ጥራት ፓኬጅን ነድፈን እየሰራ ነው ብለዋል፡፡ የትምህርት ፖሊሲው የሀገሪቷን ቀጣይ የኢንዱስትሪ ሽግግርና የአለምን ነባራዊ ሁኔታ ከግምት ያስገባነው ያሉት ሃላፊው ለትምህርት ጥራትና የወተመህና የመምህራን ሀላፊነትም ጉልህ ድርሻ እንዳለው ገልፀዋል””
ለዚህም የተሻለና ጠንካራ የወተመህ አደረጃጀት ያላቸው ትምህርት ቤቶች የተሻለ ውጤት እያስመዘገቡ ነው ያሉ ሲሆን ወደኋላ የቀሩትም ይህን ተሞክሮ ሊወስዱ ይገባል ነው ያሉት፡፡ የክፍል ጥምርታውን ለማሻሻል ችግሩ በሚታይባቸው የማስፋፊያ አካባቢዎች የትምህርት ቤቶች የማስፋፊያ ህንፃ ግንባታ እየተከናወነ ሲሆን በተሻለ ፍጥነት ላይም ይገኛል ነው ያሉት፡፡
የመምህራንን የእድገት ደረጃ ለማሻሻል በሀገር አቀፍ ደረጃ ምላሽ ለመስጠትም ከሲቪል ሰርቪስና የሰው ሀብት ቢሮ ጋር በቅንጅት እየሰራን ነው፡፡ በቅርቡም ይፋ እናደርጋለን ነው ያሉት፡፡
አገራችን እያስመዘገበችው ባለው ሁሉን አቀፍ እድገት በከተማችን የነበረው የድህነት ምጣኔ ከነበረበት 29 ነጥብ 6 በመቶ ወደ 18 ነጥብ 9 በመቶ ዝቅ ብሏል ያሉት ደግሞ አቶ ፈይኖ ፎላ የፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ሃላፊ ናቸው፡፡
እንደአለም ባንክ መረጃ መሰረት የሀገራችን እድገት 11 በመቶ ሆኖ ለረጅም ጊዜያት በዘለቀበትና አለምን ባስደመመበት ወቅት በከተማችን የ14 በመቶ በላይ እድገት መመዝገቡን ነው ያነሱት”” ሆኖም አሁንም አዳጊ የሆነውን የህዝቡን የልማት ጥያቄ በሚገባ ለመመለስ የከተማው አስተዳደር አሁንም የመካከለኛና የረጅም ጊዜ እቅድ አውጥቶ እየሰራ ነው ብለዋል፡፡
የኑሮ ወድነቱ ከንግድ ስርአቱ መዛባት የመነጨ ነው ለሚለው ጥያቄ ምላሻቸውን የሰጡት የንግድ ቢሮ ሃላፊው አቶ ትዕግስቱ ይርዳውናቸው፡፡ ፍትሃዊ አገልግሎት በመስጠት ዘላቂ ደንበኝነት ያለው አሰራር እንዲኖር ለማድረግ የንግድ ሪፎርም ተዘጋጅቶ ተግባራዊ እየተደረገ ነው ብለዋል”” ምርቶች ላይ ለጤና ጠንቅ የሆኑ ባዕድ ነገሮችን የመቀላቀልና ሆን ብሎ ሰው ሰራሽ የምርት እጥረት የመፍጠር ዝንባሌዎችን ከህብረተሰቡ በሚቀርቡ ጥቆማዎች መሰረት የማስተካከያ እርምጃ እየወሰድን ነው ብለዋል፡፡
ችግሩን በዘላቂነቱ ለመፍታት የንግዱ ማህበረሰብ ከሸማቾች ማህበረሰብ ጋር ጤናማ ግንኙነት እንዲኖረው ለማስቻል ሰፊ ስራ ይሰራል ነው ያሉት፡፡ ባለፉት 4 አመታት በሸማች ማህበራት አማካኝነት ከአምራች ገበሬዎችና ኢንዱስትሪዎች ጋር በመስራት ሸማቹ ማህበረሰብ የተሻለ ምርት በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያገኝ እያደረግን ነው፤ ሆኖም አሁንም አልፎ አልፎ የሚስተዋሉ እጥረቶችን በተጠና መልኩ ለመቅረፍ በተጠናከረ መልኩ መስራት ይጠበቃል ነው ያሉት፡፡
በውይይቱ ማጠቃለያ ላይ ክቡር ከንቲባ አቶ ድሪባ ኩማ በተነሱ ጉዳዮች ላይ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡ የደሞዝ ጭማሬን በተመለከተ ለተነሳው ሀሳብ የደሞዝ ጭማሪ እንዲሁ በዘፈቀደ የሚደረግ ሳይሆን ኢኮኖሚያችን ባደገ ቁጥር ጥናት ላይ በተመረኮዘ ሁኔታ የሚተገበርነው ብለዋል፡፡ የትራንስፖርት ችግሩን በተመለከተም ለረጅም አመታት የመንግስት ሰራተኛው ችግር ሆኖ የቆየውን የትራንስፖርት ችግር ለመቅረፍ የተወሰደው እርምጃ አስተዳደሩ የመንግስት ሰራተኛውን ችግር ለመቅረፍ ከሰራቸው በርካታ ስራዎች መካከል አንዱ ነው ብለዋል፡፡ ለዚህም የከተማ አስተዳደሩ ከ60 ሺህ በላይ የመንግስት ሰራተኞችን ተጠቃሚ እያደረገ ላለው የፐብሊክ የትራንስፖርት አገልግሎት ከ125 ሚሊዮን ብር በላይ ክፍያ እንደፈፀመ ነው የገለፁት፡፡ በቀጣይም የመምህራንን የስራ መውጫ ሰአት ከግምት ያስገባና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎችንም ያማከለ የትራንስፖርት አገልግሎት በከተማው ለመጀመር ቅድመ ሁኔታዎች በመጠናቀቅ ላይ መሆናቸውን ነው የገለፁት፡፡ በዚህም የመንግስት ሰራተኛውን የትራንስፖርት ወጪ ዜሮ ለማድረግ እየሰራን ነው ያሉት፡፡
በተጨማሪም በጋራ መኖሪያ ቤቶች ማሰተላለፍ ላይ ያለው መጓተት ለቤቶቹ የሚያስፈልገውን የመንገድ፤ የውሃና የመብራት የመሰረተ ልማቶችን ሙሉ በሙሉ አሟልቶ ለማስተላለፍ በሚሰራው ስራ አማካይነት ነው የሚፈጠር ነው ብለዋል፡፡ በቀጣይም ይህንን ችግር ለመቅረፍ በተሻለ ፍጥነት በመስራት እልባት ማምጣት እንደሚገባ አስቀምጠዋል፡፡ አያይዘውም በከተማው ካለው የሊዝ ዋጋ አንፃር የቤቶቹ ማስተላለፊያ ዋጋ ከፍተኛ አይደለም ያሉ ሲሆን የከተማ አስተዳደሩ ለቤቶች ግንባታ መሬት በነፃ እያቀረበ ነው ያለው ይህ ደግሞ የነዋሪውን የኑሮ ደረጃና የገቢ መጠን በማገናዘብ የተደረገ ነው ብለዋል፡፡
የከተማ አስተዳደሩ እስከ አሁን በከተማው ይስተዋሉ የነበሩ በርካታ ችግሮችን እየቀረፈ መጥቷል ያሉ ሲሆን ችግሩን መቅረፍ ብቻ መፍትሄ አይሆንም ብለዋል፡፡
ለዚህም ችግር ፈጣሪውን አኳል የማጥራት ስራም የመልካም አስተዳደር ማስፈንና የፀረ ኪራይ ሰብሳቢነት ትግሉ ዋና አቅጣጫ ተደርጎ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡ በምላሻቸው መጨረሻ በየትኛውም የመንግስት መስሪያ ቤት የሚገኝ አመራርም ሆነ ፈፃሚ መልካም አገልግሎት የመስጠት ግዴታ አለበት፡፡ ይህንን በአግባቡ ሊወጣ ይገባል ሲሉም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
በውይይቱ ላይ የተሳተፈው የመንግስት ሰራተኛው መንግስት በከተማው ከጀመረው ሁሉን አቀፍ የልማትና የመልካም አስተዳደር እንቅስቃሴ ጎን በፅናት እንደሚሰለፍ ድጋፉን አሳይቷል፡፡ በውይይቱ ከተሳተፉ የመንግስት ሰራተኞች መካከል አንዷ የሆኑት ወ/ሮ ሉሊት መኮንን ከአዲስ አበባ ቤቶች ግንባታ ፕሮጀክት ቢሮ የግንባታ ግብአት ቁጥጥር ኬዝ ቲምነው የተገኙት፡፡
የተጀመረውን የመልካም አስተዳደር ስራ ዳር ለማድረስ ይህን የመሰሉ ውይይቶች ጠቀሜታቸው የጎላ ነው ይላሉ፡፡ በውይይቶቹ ላይ በተነሱ ሀሳቦችና ጥያቄዎች ላይ ከመድረኩ የተሰጠው ምላሽ አጥጋቢ ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡ የመልካም አስተዳደር እጦት ቀጥተኛ ተጎጂ የሚሆኑት ሴቶች ናቸው ያሉት አስተያየት ሰጪዋ በፀረ ኪራይ ሰብሳቢነትና መልካም አስተዳደርን የማስፈን ስራ ውስጥም የሚኖራቸው ሚና ጉልህ ሊሆን ይገባል ብለዋል፡፡
ከቂርቆስ ክፍለ ከተማ ዑራኤል 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የመጣው መምህር ስዕሉ ተክሌ በበኩሉ የመምህራንን የትምህርት ደረጃ ለማሻሻል እየተሰሩ ያሉ በጎ ስራዎች ጥሩ ናቸው ያለ ሲሆን ሀገር ሲለማ ሁሉም በየደረጃው ተጠቃሚ ይሆናል፤ መምህራንም የሚጠበቅብንን ሙያዊ ሃላፊነት በመወጣት የተጀመረውን የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎች ልንደግፍ ይገባል ብሏል፡፡
በተጨማሪም የትምህርት ጥራትን ማስፈን ለመንግስት ብቻ የሚተው አይደለም ያለ ሲሆን መምህራን በዚህ ረገድ ያለባቸውን ጉልህ ሙያዊ ሃላፊነት በአግባቡ በመወጣት ሊሰሩ ይገባል ነው ያለው፡፡
ከተቀናጀ የመሬት መረጃ ማዕጀከል የተገኙት ወ/ሮ አለምፀሐይ ለማ በበኩላቸው መንግስት አሁን የጀመረውን የፀረ ኪራይ ሰብሳቢነት ትግል በሌሎች ተቋማትም አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባዋል ነው ያሉት፡፡
መልካም አስተዳደርን ማስፈን የህልውና ጉዳይ ነው የሚሉት ወይዘሮዋ ለዚህም የእያንዳንዱ የመንግስት ሰራተኛ ሀላፊነት ከፍተኛ ነው ይላሉ”” በቀጣይ የህዝብ አገልጋይነትን በተግባር በማስመስከር የምንፈልገውን ውጤት ለማስመዝገብ የሞት ሽረት ትግል ልናደርግ ይገባል ብለዋል፡፡
ሌላኛዋ አስተያየት ሰጪ መምህር ሜሮን ጋሹ በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ 15 ትምህርት ጽህፈት ቤት የኢኒስፔክሽን ባለሙያ ናት”” የሁለቱ ቀን ውይይት ጥሩ ነበር ትላለች””
በተለይም ለመወያያ የተዘጋጁት ሁለቱም ሰነዶች አጠቃላይ የከተማውን ነባራዊ ሁኔታ የዳሰሱና አሉ የሚባሉ የመልካም አስተዳደር ማነቆዎችን የለየ መሆኑ ይበልጥ አሳታፊ እንዲሆን አድርጎታል ብላለች”” በአጠቃላይ በቡድን ውይይት ወቅት ለተነሱ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ከአቅም ግንባታ ቢሮ ሃላፊውና ከክቡር ከንቲባው የተሰጡ ምላሾችም አመርቂና ይበል የሚያሰኙ ናቸው ብላለች””
ለመወያአሁን ላይ የመልካም አስተዳደር ጉዳይ የህዝብ አጀንዳ ሆኗል”” በተጨባጭ በውይይቱ የታየውም እውነት ይህ ነው፡፡ ለተከታታይ ሁለት ቀናት የተካሄደው ውይይት በአጠቃላይ የህዳሴ ጉዞአችን ዋነኛ ተግዳሮት የሆነውን የመልካም አስተዳደር ችግርና የኪራይ ሰብሳቢነት ፖለቲካል ኢኮኖሚን በማዳከም ልማታዊ ፖለቲካል ኢኮኖሚ የበላይነት እንዲይዝ ጉልህ አስተዋፅኦ ይኖረዋል፡፡
ይህን መሰል መድረኮች በየጊዜው ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል”” የተሰሩ ስራዎች፤ የተወሰዱ የማጥራት እርምጃዎችን በየጊዜው ለህብረተሰቡ በማሳወቅ የትግል አድማሱን ከዳር ማድረስና የህዳሴያችንን ባቡር በፍጥነት መሳፈር ይጠበቅብናል”” እንላለን”” ሰላም፡፡

No comments:

Post a Comment